መቼም እንግዲህ ይሄ ታክሲ አያሳየኝ የለው! ለነገሩ ይሄኛውን እንኳን ያስተዋልኩት እዚያ ትልቁ ሰማያዊ ተሽከርካሪ ላይ ነው፡፡ ያ ማነው ስሙ ‹‹ፐብሊክ ሰርቪስ›› ማለቴ የመንግሥት ሠራተኞችን ከቤት ወደ መሥሪያ ቤት እና ከመሥሪያ ቤት ወደ ቤት የሚወስደው ሰማያዊው ተሸከርካሪ ማለት ነው(አሁን ተግባብተናል)፡፡ በነገራችን ላይ ወደ ዋናው ጉዳይ ከመግባቴ በፊት እዚህ ተሸከርካሪ ላይ አንድ ያስተዋልኩትን ሌላ ነገር ላስቀድም፡፡ ጠዋት ጠዋት እንኳን መቀመጫ መቆሚያ አይገኝም፤ ማታ ማታ ግን በባዶ ወንበር ነው የሚሄደው፡፡ ለምን ይሆን? እዚሁ ተሽከርካሪ ውስጥ ስጓዝ አንድ ቀልደኛ ሲያወራ የሰማሁት ነገር እውነት ሳይሆን አይቀርም ። እንግዲህ እሱ ሲል እንደሰማሁት ማታ ማታ ባዶ የሚሆነው ብዙ ሰዎች ‹‹ክላስ›› ስላላቸው ነው። ስለሚማሩ ማለት ነው፡፡
ነገሩን ሲያጣምመው ደግሞ ‹‹ማታ ማታ ወደ ሌላ ክላስ የሚሄዱም አሉ›› ብሎ ፈገግ አሰኝቶን ነበር፡፡ ብቻ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ግን ማታ ማታ የጠዋቱን ያህል የሰው ብዛት የለውም፡፡ ኧረ ጉድ! ይሄ አሁን የነገርኳችሁ አስተውሎት ቀጥሎ ከምናገረው ዋናው ጉዳይ ጋር ለካ ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ ቆይ ግድለም እንደምንም አገናኘዋለሁ! ምንም እንኳን ብዙ ቀን የማስተውለው ቢሆንም የአንድ ቀኑ ግን የተለየ ሆኖብኝ ነው ዳግመኛ እንዳስብበት ያደረገኝ፡፡ አንድ በዕድሜ አንጋፋ የሚባሉ ሰውዬ ናቸው ይህንን ትውስታዬን የመለሱት። የክፍል ውስጥ ‹‹ሀንድ አውት›› ይዘዋል፡፡ እንግዲህ ሰውዬው እየተማሩ ነው ማለት ነው፤ ሰሞኑን ፈተና ያለባቸው ይመስላል ።የሚያነቡትን የትምህርት አይነትና የትምህርት ደረጃ አላየሁትም(ምናልባት ለዶክትሬትም ሊሆን ይችላል)፡፡ እኔን የገረመኝ በዚህ ዕድሜያቸው እንዴት እስከዶክትሬት ዲግሪ ድረስ አልጨረሱም ብዬ አይደለም(ገና ለመጀመሪያ ዲግሪም ሊሆን ይችላል)፣ ባይጨርሱስ ለምን በዚህ ዕድሜያቸው ይማራሉ ብዬም አይደለም። ግን በዕድሜ ገፋ ያሉ ስለሆነ ብዙም ስላልተለመደ ነገሩን ትኩረት እንዲሰጠውና የሌሎችን ሁሉ እንዳስታውስ ስላደረገኝ ነው ያስገረመኝ።
በዚያ ላይ እኝህ ሰውዬ የታሪክ መጽሐፍ፣ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ወይም ጋዜጦችንና መጽሔቶችን ሲያነቡ ማየት ነበር የሚያመሳስላቸው። አሁንም ልድገመውና ለምን ተማሩ ማለቴ ሳይሆን ኑሮን ለማሻሻል ስለመሰለኝ ነው፡፡ የሰውዬው መነሻ ሆነኝ እንጂ ይሄ ነገር በተደጋጋሚ ያስተዋልኩት ነው፡፡ በትራንስፖርት ጋዜጣና መጽሔት ከሚነበበው ይልቅ ‹‹ሀንድ አውት›› የሚያነብ ነው የሚበዛው፡፡ ጥሩ ነው መነበቡ፤ ዳሩ ግን እውቀት ፍለጋ አይደለም፡፡ ኑሮን ለማሻሻል የሚደረግ ሩጫ ነው፡፡ ካሉበት የሥራ መደብ የተሻለ የሥራ መደብ ለመቀጠር ሲባል ነው፡፡ ይሄን ነገር የሚያጠናክርልኝ አንድ ጓደኛዬ የነገረኝን ገጠመኝ ላጫውታችሁ፡፡ ይህ ገጠመኙን ሲያወራ የሰማሁት ጓደኛዬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪውን እየተማረ ሳለ ነው፡፡ እናም ክፍል ውስጥ አንድ ቀን መምህሩ እንዲህ አላቸው፡፡ ‹‹እስኪ ሳትዋሹ እውቀት ለመጨመር ብላችሁ የምትማሩ እጅ አውጡ›› አለ መምህሩ። ሁሉም ተማሪ እየተያየ ዝም አለ ። መምህሩም ቀጥሎ ይህን ያለበትን ምክንያት አብራራ። ተማሪዎች በተለይም ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን የሚማሩት እውቀት ለመጨመር ሳይሆን ኑሮን ለማሻሻል ብለው ነው፤ የተሻለ ቅጥር ለማግኘትም ነው። መምህሩ ያንን ያለበት ምክንያት ደግሞ ትምህርት ላይ ደካማ ሆነውበት ተናዶ ነው። እውቀት ፍለጋ ስላልሆነ የሚማሩት የሚፈልገውን ያህል አልሆኑለትም፤ አይገባቸውም ማለት ነው። እንደምንም ብለው ወረቀቱን መያዝ ብቻ ነው ፍላጎታቸው።
የመምህሩን ነገር እውነት መሆኑን የምናረጋግጠው ደግሞ ይሄው በየመንገዱ በምናየው ነገር ነው፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ በሚወራው ወሬ ነው፡፡ እስኪ በየመሥሪያ ቤቱ ልብ በሉ! ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ የሚማሩት የተሻለ ሥራ ለመቀጠር እንጂ የማህበረሰብ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር ለመሥራት አይደለም ። ይሄ እንግዲህ የአገሪቱ የኑሮ ሁኔታ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ቢሆንም ግን እውቀት አለመፈለግን በአገሪቱ የኑሮ ሁኔታ ብቻ የሚወሰን አይደለም፤ ስንፍናውም አለ፡፡ ያንኑም ‹‹ሀውንድ አውቱን›› የማያነብም እኮ አለ፡፡ ይሄን ነገር የሚያጠናክርልኝ አንድ የሰማሁትን ገጠመኝ ልንገራችሁ፡፡ ደራሲ ዓለማየሁ ገላጋዬ በሸገር ኤም ኤም እንግዳ ሆኖ ሲያወራ የሰማሁት ነው፡፡ አንድ አባት አንድን ወጣት ‹‹ለምን አታነብም፣ ለምን አትማርም?›› ብለው ይጠይቁታል፡፡ ‹‹ወጣቱም ምን እየበላሁ ነው የምማረው? ይላቸዋል፡፡ ቃሉ ቢከብድም እንደሰማሁት ልጠቀመውና ‹‹ምን እየበላህ ነው የደደብክ?›› አሉት ይባላል፡፡ እዚህ ላይ ግን ልብ መባል ያለበት ነገር የኑሮ ሁኔታም ቀላል ችግር አይደለም፡፡
ሰው ስለኑሮ እያሰበ አዕምሮው ነፃ ሊሆን አይችልም ። የሚያስበው ስለነገው ነው፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ መጽሐፍ፣ ጋዜጦችና መጽሔቶች የቅንጦት ይመስሉታል፡፡ ትርፍ ጊዜና ገንዘብ ያለው ሰው የሚያነባቸውና የሚገዛቸው ይመስለዋል፡፡ ለዚህም ነው በአገራችን ጋዜጣና መጽሔት ብዙም አይነበብም የሚባለው፡፡ ድህነት ብቻ ነው ምክንያቱ እንዳንል ደግሞ አሁንም ሌላ አፍራሽ ምክንያት እናገኛለን፡፡ ለዚህ እንደምሳሌ ትምህርት ቤቶች አካባቢ እንሂድ! ብዙ ጊዜ በትምህርት ውጤታማ የሚሆኑት በኑሮ የሚጎሳቆሉ ተማሪዎች ናቸው፡፡ ብዙ ነገር የማይቸግራቸው ተማሪዎች ትምህርት ላይ ትኩረት አያደርጉም፡፡ ምናልባት ይሄም የኑሮ ሁኔታ ይሆን? የድሃ ልጅ ስለሆንኩ ከዚህ ውጭ አማራጭ የለኝም በሚል ትኩረት ስለሚሰጡት ይሆን? ዞሮ ዞሮ ግን ስንፍናም በትልቁ አለ ።
ትምህርትን ለኑሮ ማሻሻያነት መጠቀም ምናልባት የኑሮ ሁኔታ ሊሆን ይችላል፡፡ መጽሐፍ፣ ጋዜጣና መጽሔት አለማንበብ ግን ስንፍና ነው፡ ፡ እንዲያውም ከዚህ የባሰ እኮ ስለውጭ አገር ኳስ፣ ስለፊልም፣ ስለመንደር አሉቧልታ ይወራል አይደል? ትምህርት እንዲህ ለተሻለ ሥራ መፈለጊያ ሲሆን፤ ስኬታም አይሆንም፡፡ ተማሪነታችንን እናስታውስ፡፡ ለፈተና ብለን ቀኑ ሲደርስ ስናነብ ሽምደዳ እንጂ ጽንሰ ሀሳቡ አይገባንም፡፡ ፈተና በሌለበት ሰሞን ስናነብ ግን በጥልቀት ነበር የሚገባን፡፡ ያ ማለት የምናነበው ለእውቀት ነበር እንደማለት ነው፡፡ ሌላም ማሳያ እንጥቀስ፡፡ በአንድ ኮሌጅ በር ላይ ሄዳችሁ ከውስጥ ሲወጡ አሥር ተማሪ አስቁማችሁ ብትጠይቁ ቢያንስ ስምንቱ ‹‹አካውንቲንግ›› ሊሉ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ተማሪዎች የአካውንቲንግ ሳይንስ ፍቅር ይዟቸው አይደለም፤ ወይም የአገሪቱ የምጣኔ ሀብት ላይ እንመራመራለን ብለው አይደለም፤ የተሻለ ቅጥር ያለው እዚያ ላይ ነው ሲባል ስለሚሰሙ ነው ። ይሄ እኮ ግልጽ ነው፡፡ ተማሪዎች 12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ጨርሰው የዩኒቨርሲቲ ቅጽ ሲሞሉ ችሎታቸውንና ምኞታቸውን ሳይሆን ‹‹የቱ ነው ቶሎ የሚቀጠርበት?›› ብለው ነው የሚጠይቁ፡፡ ለዚህም ነው ያለፍላጎታቸውና ያለችሎታቸው ገብተው ሲማረሩ የሚሰማው ።
ከዚያ በኋላ እንግዲህ ሲመረው በውሃ ቀጠነ ምክንያት ሁሉ ድንጋይ ውርወራ ይጀምራል! ኧረ ጎበዝ ትምህርትን ለኑሮ ብቻ አናድርገው! ለማወቅም እናንብብ! በቃ እውቀት ከሀብት ይበልጣል የሚለው አባባል ውሃ በላው ማለት ነው? አስታውሳለሁ ትምህርት ቤት እያለን ‹‹ከእውቀትና ከሀብት›› እየተባለ እንከራከር ነበር ። ታዲያ ሀብት ይበልጣል ያለ ተማሪ እንደሰነፍ ስለሚታይ አብዛኞቻችን ‹‹እውቀት›› ነበር የምንል፡፡ አሁን ግን ሀብት መባሉ ነው መሰለኝ ። እውቀት ካለ ሀብት ይኖራል የሚለው ግን አስታራቂ ሀሳብ ነው፡፡ ችግሩ ሀብትም ያለእውቀት መሆኑ ነው! ስለዚህ ማወቅ ለሁሉም ይሆናልና ለማወቅም እናንብብ!
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2011
ዋለልኝ አየለ