ሰው ሰራሽ አስተውሎት ( አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ) ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የሰው ልጆች የዕለተ ዕለት ኑሮ ለማቃለል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል። በተለያዩ ዘርፎች ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው ። ከፍተኛ ጠቀሜታ እያበረከተ ከሚገኝባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ በጤና ዙሪያ ችግር ፈቺ ፣ ፈጣንና በቀላሉ ለመገልገል የሚያስችል ነው። በጤናው ዘርፍ የሚገኙ ልህቃን የተለያዩ ውሳኔዎችን እንዲያስተላልፉ ሰው ሰራሽ አስተውሎት የላቀ ሚና እየተጫወተ ነው።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት ከመቼውም ጊዜ በላይ ሀኪሞች ውሳኔ የሚያስተላልፉበትን መንገድ እየቀየረ መጥቷል ። ለምርመራ፣ ለህክምና እቅድ እና ለህዝብ ጤና አያያዝ ፤ ለህሙማነ ክትትል መረጃዎችን በማስተላለፍ በሀኪሞች ውሳኔዎች ላይ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። በቅርቡ ጎግል ሄልዝ ያወጣው ዘገባ እንዳመላከተው ሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ) ሀኪሞች ታካሚዎችን እንዲንከባከቡ እና በሽታን እንዲያድኑ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ይገኛል።
አደገኛውን የጡት ካንሰርን ከማጣራት አንስቶ የሳንባ ነቀርሳ በሽታን በብቃት ለይቶ ለማወቅ የላቀ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ እየተስታዋለ ያለውን መሻሻሎች ከሌሎች ቴክኖሎጂዎች በተለይም የስማርት ስልክ ካሜራዎች እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች ጋር በማገናኘት ሰዎችም ስለ ጤናቸው የበለጠ መረጃ እንዲኖራቸው አዳዲስ መንገዶችን እየከፈተ ይገኛል።
በቅርቡ ጎግል ሄልዝ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም አዲስ መተግበሪያ ይፋ አድርጓል። መተግበሪያው የስማርት ስልክ ካሜራን በመጠቀም ሰዎች የገጠማቸውን የቆዳ በሽታ ምንነት መለየት የሚያስችል መጠቀሚያ ይፋ አድርጓል። መተግበሪያው በዘርፉ የሚስታዋለውን ውስብስብ ችግር ለመቅረፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።
የሰውነት ውጫዊ ሽፋን የሆነው እና በሰውነት ውስጥ ትልቁ አካል የሆነው ቆዳ የተለያዩ ተግባራትን የሚያከናውን ወሳኝ የሰውነት ክፍል ነው። ከከባቢ ጋር በቀጥታ ስለሚገናኝ ሰውነትን ከበሽታ አምጪ ተህዋሲያን ለመከላከል፣ የሰውነት ሙቀትን ለማመጣጠን፣ ኦክሲጅን ወደ ውስጥ ለማስገባት እና ሌሎች ተያያዥ ተግባራትን በማከናወን ለሰው ልጆች ጤና ከፍተኛ ሚና ያበረክታል። በአጠቃላይ መሰረታዊ የሆኑትን ጡንቻዎች ፣ አጥንቶች ፣ ጅማቶች እና የውስጥ አካላት ይጠብቃል ።
የቆዳ በሽታዎች፣ በሰው ቆዳ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ማናቸውም በሽታዎች ወይም ችግሮች የሚያጠቃልል ሲሆን የቆዳ በሽታዎች ሰፋ ያሉ ምክንያቶችም አሏቸው። በቆዳ ላይ ከሚከሰቱ ሽፍታዎች አንስቶ ሌሎች በሰው ልጅ ቆዳ ላይ የሚስታዋሉ በሽታዎች የቆዳ በሽታዎች ምልክት ከመሆን ባሻገር ሌሎች ከባድ በሽታዎችንም ሊያመለክቱ እንደሚችሉ የዘርፉ ልህቃን ያስረዳሉ።
የቆዳ በሽታ የተለመደ ህመም ሲሆን ከልጅ እስከ አረጋውያን ድረስ ያሉትን በሁሉም የዕድሜ ክልሎች የሚገኙ ሰዎችን የሚያጠቃ እና የተለያዩ ጉዳቶችን ከሚያስከትሉ የሰው ልጆች ችግሮች አንዱ ነው። መረጃዎች እደሚያመላክቱት የሰዎችን ቆዳ ሊጎዱ የሚችሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ የቆዳ በሽታዎች ሲኖሩ፤ ነገር ግን አብዛኛዎቹ የቆዳ በሽታዎች ወደ ዘጠኝ የተለመዱ ዓይነቶች ሊመደቡ ይችላሉ። ከነዚህ መካከል በባክቴሪያ የሚመጡ ኢንፌክሽኖች፣ በፈንገስ የሚመጡ ኢንፌክሽኖች እንዲሁም በጥገኛ ተህዋሲያን የሚመጡ ኢንፌክሽኖች ተጠቃሽ ናቸው።
የሰው ልጆች የእጹዋትን የተለያዩ ክፍሎችን የቆዳ በሽታዎች ለማከም መጠቀም ከጀመረበት ከጥንት ጀምሮ የቆዳ በሽታዎችን ለመለየት እና ለማከም የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ ውከለዋል። በአሁኑ ዘመን ቅባቶች፣ አንቲ ባዮቲክስ፣ ቫይታሚን ወይም ስቴሮይድ መርፌዎች፣ የጨረር ሕክምና እና ሌሎች መፍትሄዎችን ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ።
በቅርቡ ጎግል ይፋ ያደረገው መተግበሪያ ግን ከሁሉም ቀለል ያለ እና በዘርፉ እውቀት የሌላቸው ሰዎች ጭምር የቆዳ በሽታቸውን ለመረዳት እና የመፍትሄ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችል መሆኑ ለየት ያደርገዋል። መተግበሪያው የቆዳ ህክምና ቀጣይ ብሩህ አቅጣጫ አመላካች ተደርጎ ተወስዷል።
መተግበሪያውን ጎግል ባስተዋወቀበት ዘገባ እንዳመላከተው፤ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሁለት ቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የተለያየ አይነት የቆዳ በሽታ ችግር እንደሚስተዋልባቸው ገልጿል። ሆኖም በዓለም ዙሪያ ይህን ችግር ለማከም የሚረዱ የዘርፉ ሃኪሞች እጥረት ከፍተኛ በመሆኑ አብዛኛው ሰው ከባድ ችግር ውስጥ ለማሳለፍ ይገደዳል። ለችግሩ መፍትሔ ለማግኘት ወደ ጉግል የፍለጋ አውታረ መረብ ፊቱን ያዞራል። በየጊዜው በርካቶች ለችግራቸው መፍትሄ ለማግኘት የጎግል አውታረ መረብን ያስሳሉ።
መተግበሪያው በስልክ ካሜራ አማካኝነት ችግሩ የተስተዋለበትን የሰውነት ክፍል ሶስት ምስሎች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ያነሳል። በመቀጠል የቆዳውን አይነት፣ችግሩ ምን ያህል ጊዜ እንደቆየ እና ሌሎች የችግሩን ምንነት ለመረዳት የሚያስችሉ ምልክቶችን ይጠይቃል። በመጨረሻም የተሰጡትን መረጃዎች የሰው ሰራሽ አስተውሎቱ ካጣራ እና ከተነተነ በኋላ በመረጃ ቋቱ ከገቡለት 288 አይነት የቆዳ፣ የጸጉር እና የጥፍር ችግሮች መካከል የተጠቃሚው ችግር ምን እንደሆነ ያሳውቃል።
መተግበሪያው የቆዳ በሽታዎችን ብቻ ሳይሆን ሌሎች በሽታዎችንም ለመለየት ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል ጎግል ጠቁሟል። በቆዳ ባሻገር ከጻጉር እና ከጥፍር ጋር በሚዛመዱ ጉዳዮች ላይ ምን እየተከናወነ እንዳለ ለመረዳት እና መፍትሄዎችን ለማመላከት እገዛ እንደሚያደርግ በዘገባው ላይ ተመላክቷል።
መተግበሪያው ከሶስት ዓመት በላይ የምርምር እና የምርት ልማት ጥረት በኋላ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ እስከ አሁን ድረስ የመተግበሪያውን ትክክለኛነት የሚያረጋግጡ የተለያዩ ጥናቶች በተለያዩ አካላት ተጠናቀው የታተሙ ሲሆን በመተግበሪያው ዙሪያ ሌሎች በርካታ የምርምር ውጤቶች በቀጣይ ጊዜያት ይጠናቀቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጎግል አስነብቧል።
ኔቸር ሜዲስን በተሰኘው መጽሄት በጎግል ስለ ተካሄደው ቆዳ በሽታዎች የምርምር እና መተግበሪያው የቀረበው ጽሁፍ እንዳስነበበው መተግበሪያውን ለማበልጸግ የተሄደበት እና የቆዳ በሽታን ለመለየት የተካሄደው ጥናት ጥልቀት ያለው መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን መተግበሪያው ከአሜሪካ የቆዳ በሽታዎች ተመራማሪዎች ስለ ትክክለኛነቱ ምስክርነት ተሰጥቶታል።
ሌሎች በርካታ ድረገጾች እና መጽሄቶችም ስለመተግበሪያው የተለያዩ ዘገባዎችን ይዘው ወጥተዋል።
በቅርቡ ጎግል ጃማ ኔትዎርክ በተሰኘው ድረ ገጽ ያወጠው ዘገባ እንዳመላከተው፤ መተግበሪያው በቆዳ በሽታ ዘርፍ ከሰለጠኑ ባለሙያዎች ባሻገር በዘርፉ ምንም አይነት እውቀት የሌላቸው የህክምና ባለሙያዎች ጭምር የቆዳ በሽታዎችን ለመለየት እና ሁኔታዎችን ለመተንተን የሚያስችላቸው መሆኑ መተግበሪያውን ልዩ ያደርገዋል።
የበለጠ እርግጠኛ ለመሆን መተግበሪያውን የተለያዩ ሰዎች ላይ በመሞከር የማረጋገጥ ስራ የተሰራ ሲሆን፤ በተለያዩ የእድሜ ደረጃዎች፣ በተለያዩ ጾታዎች፣ በተለያዩ ዘሮች እና ለሁሉም ሰው እየገነባን መሆናችንን ለማረጋገጥ ሞዴላችን እንደ ዕድሜ ፣ ጾታ ፣ ዘር እና የቆዳ አይነቶች ያላቸው ሰዎች ላይ ተሞክሯል። ለዚህም የ65 ሺህ ምስሎችን እና በምርመራ የተያዙ የቆዳ ሁኔታዎችን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የቆዳ ህክምናን የሚያሳዩ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ጤናማ ቆዳዎች ናሙናዎች ተወስደዋል።
በቅርቡ መተግበሪያው በአውሮፓ ህብረት ምርጥ የህክምና መሳሪያ በሚል የህክምና ማረጋገጫ አግኝቷል። በቀጣይ ወራት በህክምናው ዙሪያ የተለያዩ ተግባራትን ለማከናወን ታቅዷል። በርካቶችም በቆዳቸው ላይ የሚከሰቱ ችግሮቻቸውን መፍትሄ የሚያስገኝ እና ጥያቄዎችን ምላሽ የሚሰጥ ይሆናል።
መተግበሪያውን የመጠቀም ፍላጎት ያላቸው አካላትም በኢሜይል አድራሻቸው ከአሁኑ መመዝገብ እንደሚችሉ ጎግል ያስታወቀ ሲሆን ተመዝጋቢዎቹ የመተግበሪያው ቀዳሚ ተደራሽ እንደሚሆኑ አብራርቷል። ለወደፊቱ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የጎለበተ የቆዳ ህክምና መሣሪያ ለምርምር እና ቀዳሚ ተጠቃሚ የመሆን ፍላጎት ያላቸው ሰዎች የተቀመጠውን ቅጽ መሙላት አለባቸው።
ቅጹ የወደፊት ተጠቃሚውን ሙሉ መረጃዎችን ማለትም አካባቢን ፣ ቋንቋ እና የመሣሪያ ዓይነት ላይ ፍላጎት እንዲሁም ሌሎች መረጃዎችን አካቶ የሚይዝ ነው። ቅጹ ከተሞላ በኋላ በሚመለከታቸው ህጎች እና መመሪያዎች መሠረት የሚከናወኑ ለፕሮግራሙ የብቁነት መስፈርቶችን እና ሌሎች ሁኔታዎችን ለሚያሟሉ ግለሰቦችና ድርጅቶች መተግበሪያውን እንደሚያቀርብ ጠቁሟል።
መተግበሪያው ወደ ስራ ሲገባ ቅጹን ከሞሉት መካከል ለመጠቀም ብቁ የሆኑ መጀመሪያ ተጠቃሚ ይሆናሉ ያለው ጎግል፤የመጀመሪያ ብቁነትን ለመወሰን ስለ አካባቢዎ ፣ ስለ ቋንቋ እና ስለ መሣሪያ ዓይነቶች በቅጹ ላይ የተቀመጡ መረጃዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ። ሌሎች የስነሕዝብ መረጃዎች እንደአማራጭ እና የቆዳ ዓይነቶችን ተወካይ ናሙና ለማረጋገጥ ጥቅም ላይ ይውላሉ። በቅጹ ላይ የሚቀመጡ መረጃዎች ለቆዳ ህክምና ምርምር እና መተግበሪያውን ለባለቤቱ ለማድረስ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን መረጃው በቅጹ ላይ የሚሞሉ መረጃዎች ለ180 ቀናት ብቻ የሚቆይ ይሆናል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2013