በተለምዶ ስስታምነት በማህበረሰባችን ዘንድ የተነቀፈ ባህርይ ቢሆንም አንዳንድ ሰዎች አስተውለውትም ይሁን ሳያስተውሉት በእለት ከእለት እንቅስቃሴያቸው ሲተገብሩት ይስተዋላል። የስስት ባህሪያችን እያደገና እየተጠናከረ ሲመጣ ደግሞ ወደ ስግብግብነት ከፍ ይልና ከሰዎች ጋር የሚኖረንን መልካም ግንኙነት ያሻክርብናል፤ አለፍ ሲልም ከማህበረሠቡ እስከመገለል ያደርሰናል። ለመሆኑ ስስት በሰው ልጅ አእምሮ ውስጥ እንዴት ሊከሰት ይችላል? ምንስ ጉዳት ያስከትላል? እንዴትስ ማስወገድ ይቻላል? ስንል የማህበራዊ ሳይንስና አመራር ባለሙያ የሆኑትን አቶ ዘላለም ይትባረክን አነጋግረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል።
ባለሙያው እንደሚያብራሩት ስስት የሚፈጠረውና እንደ ጸባይ በሰው ልጅ ውስጥ ሊደጋገም የሚችለው በሁለት እሳቤዎች አማካኝነት ነው። “የመጀመሪያው ያለኝ ነገር አይበቃኝም” ወይም “ሊያልቅብኝ ይችላል” ወይም “ደግሜ አላገኘውም” ከሚል ፍርሃት አዘል መረዳት የሚመነጭ ነው። ሁለተኛው ደግም “ለእኔ” የሚል ስር የሰደደ የራስ ወዳድነት አስተሳሰብ ነው። ሁለቱም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ሲሆኑ ያለንን እንዳንሰጥ ስንካፈል ደግሞ አይን የሌለን የሚያደርግ የአስተሳሰብ ድክመት መገለጫ ሲሆኑ ሁለቱም ባህሪዎች ፍርሃት ወለድ በሽታዎች ናቸው። ይህም ደግሞ ህይወትን እንዳናጣጥም፣ ባለን እንዳንረካና እንዳንደሰት በማድረግ ሁሌ ሌላ በመፈለግ የሚያዋትት እና ያለን ያከማቸነውንም የሚያበላሽ ይሆናል።
ስስት የሚጀምረውም በህጻንነት ሲሆን ለህጻን ልጅ እድሜያዊ ጸባይ በመሆን ሰው ሁሉ ከተወለደበት አንስቶ እስከሚያድግበት ድረስ የሚታይበት ይሆናል። ይህም ስሜታዊና በአስተሳሰብ ጨቅላ ከመሆን ጋር በተያያዘ የሚከሰት ተፈጥሮአዊ ባህሪ በመሆኑ ህጻን ልጅ ያዬ፣ የሰማ፣ የቀመሰውን አልያም የያዘና የጨበጠውን ሁሉ የእኔ እና ለእኔ ብቻ ሲል ይስተዋላል። ሆኖም ከህጻንነት ወደ አዋቂነት ወይም ልጅ ከመሆን ወደ ትልቅነት ሲያድግ ግን ከስሜታዊነት ይልቅ ወደ አስተሳሰባዊነት ስለሚሸጋገር ምክንያታዊነቱ፣ ማገናዘብ፣ ማመዛዘን፣ መምረጥ፣ መለየት ወዘተ ክህሎቱ ፈርጥመው ሲወጡ እነዚህ ጸባዮች እየጠፉ ይመጣሉ። ይህም ጤነኛ በሆነ መልኩ በአካልም ሆነ በአስተሳሰብ የሚያድግ ሰው የእድሜ መገለጫዎች ናቸው። በተቃራኒው ሰው አካሉ ብቻ በማደግ አስተሳሰቡ ሲቀነጭር ግን ስሜታዊነቱ ስለሚበረታ እድሜው የትልቅ ቢሆንም አስተሳሰብና ማንነቱ ግን የህጻን ወይም እንጭጭ (ያልበሰለ) ስለሚሆን ለማካፈል ስስታም እና ለመካፈል ደግሞ ስግብግብ ይሆናል። በመሆኑም ስስት ጤነኛ ያልሆነ እድገት መገለጫም ጭምር ተደርጎ ይወሰዳል።
በስነልቦናው ዘርፍ የምሁራንን ጥናትና ምርምር ስራዎችን ለንባብ የሚያበቃው ‹‹ሳይንስ ሳይኮሎጂ ቱደይ›› መጽሄት ላይ የወጣ ጥናት እንደሚያመለክተው የሚስገበገቡና የሚሳሱ ሰዎች አስተሳሰብ ናርሲዝም (ጤናማ ያልሆነ ራስን የማምለክ በሽታ፣ ድባቴ፣ የወንጀለኝነት ስሜት፣ ጭንቀት ወዘተ) የሚያጠቃቸው ሲሆን በተጨማሪም ስስት ልክ እንደ አደገኛ እጽ ሱስ የማስያዝ አቅምም እንዳለው ያመለክታል። በእርግጥም ለድህነት፣ ሙሰኝነት፣ ወንጀለኝነት፣ ጥቅመኝነት፣ የሌሎችን መሻትና አልጠግብ ባይነት ሁሉ መነሻው ስግብግብነትና ስስት ናቸው።
* መርካት አለመቻል ወይም በቃኝን አለማወቅ፡ ጠገብኩ፣ ይሄ ደግሞ ለሌላ አለማለት
* የበዛ፣ የጠና ራስ ወዳድነት
* አቋራጭ መንገድን መፈለግ፤ በተለይ ሙስናና ወንጀል
* ቅናት፣ መቅናት
* ርህራሄን (አዘኔታን) ማጣት እና ሸዋጅ/አታላይ/ደላይ መሆን የስግብግብነትና ስስት መገለጫዎች ናቸው። እነዚህ ሁኔታዎች ደግሞ በቀጥታ ከማህበረሰቡ እንድንገለል ያደርጉናል። በመሆኑም የራሳችንን ጸባይ በመገምገም ከስስታምነት ወደ ለጋስነት መሸጋገር ይገባናል። እዚህ ላይ ለጋስነት ከስስታምነት ለመውጣት ብቻ ሳይሆን የራሱም ጠቀሜታዎች አሉት። በቅርቡ ዶክተር ሶፊያ በሚባሉ የዘርፉ ባለሙያ የተካሄደ “ጌሪንግ አፕ” ጥናት እንደሚያመለክተው ለረጅም ጊዜ ሳያቋርጡ የሚሰጡና የሚለግሱ ሰዎች የሰውነት ቆዳቸው አያረጅም፤ አካላዊ ምስላቸው ጠንካራ ይሆናል፤ ፀጉራቸው አይነቃቀልም። ባጠቃላይ ለጋስ በመሆናቸው በርካታ አካላዊና ስነልቦናዊ ጠቀሜታዎችን ያገኛሉ። በሌሎች ምሁራኖችም የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የሚለግሱ ሰዎች እረጅም እድሜ ይኖራቸዋል፣ በቀላሉ ከታመሙበት ያገግማሉ እና በጣም ጤነኛና ደስተኛ ናቸው።
ከስስታምነት ለመላቀቅ የሚከተሉትን መንገዶች መጠቀም ይጠቅማል፤
1. በመጠን መኖር መቻል። ያለኝ ይበቃኛል ይህን ፈጣሪዬ ይባርክልኝ አይነት የህይወት መረዳትን በመጀመር ማግበስበስ፣ መንሰፍሰፍ ወይም መንቆጥቆጥን ማቆም።
2. መስጠትና መለገስ መልመድ። ስንሰጥ ሃብታችን እየጨመረ ይሄዳል፤ ደስተኛና በራስ የሚተማመን ኩሩ ሠው ያደርጋል፣ መስጠት ዘርፈ ብዙ ሲሆን ይህም ጊዜ፣ ገንዘብ፣ እውቀት፣ ጥበብና ጉልበት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ከተሰጠን ወይም ካለን እኛም የምንችለውን ያህል ለሌሎች እንሰጣለን እንደማለት ነው። በሀይማኖታዊ እይታም ለሌሎች ስንሰጥ የምንሰጠው ለፈጠረን አምላክም ጭምር እንደሆነ ማስታወስ ይገባል (ለድሃ የሚሰጥ ለአምላኩ ያበድራል እንደሚባለው። ስንሞት የምንስገበገብለት የምንሳሳለት ሃብታችንን ሁሉ ይዘነው እንደማንሄድ ማስታወስ ይገባል። ስለዚህ ስግብግብነትንም ሆነ መሳሳትን ከህይወታችን ለማስወገድ፤ ለሌሎችም መኖር መቻልን መልመድ፣ ከገንዘብ ውጭ የሆኑ ሰብአዊ ተግባራት ላይ ትኩረት ማድረግ፣ ሌሎችን እንደራሳችን መውደድ እንዳለብን መረዳት ከስስታምነት ወደ ለጋስነት ለመሸጋገር ይረዱናል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2013