መሳሪያዎች ናቸው። ሁለቱም መግባቢያ ናቸው። ሁለቱም መረጃ ወይም መልዕክት ማቀበያ/ማስተላለፊያ ናቸው። ሁለቱም ሰብአዊ መሰረት ያላቸው፤ የሰው “ብቻ” ናቸው። ሁለቱም (ተቀባይ ሳይሆኑ) አቀባይ ናቸው። ሁለቱም የቋንቋ ክሂል ሲሆኑ ሁለቱም እውቀትን (በእውቀት ላይ የተመሰረተ አጠቃቀም ይኖር ዘንድ) አጥብቀው ይፈልጋሉ። ሁለቱ ታላቅና ታናሽ ናቸው፤ ፊትና ኋላ። ሁለቱም የመሰነጃ መሳሪያዎች፤ የታሪክ አካልና አምሳል፤ ታሪክም ናቸው። ቃላት መሳሪያዎቻቸው፤ እነሱም የቋንቋ መሳሪያዎች ናቸው። ይሁኑ እንጂ እንደ “… ናና ጻፍ በለው” ጽሑፍ ፋይዳው ብዙ ነው። በመሆኑም መቸም ቢሆን ያነጋግራሉ፤ ያወያያሉ፤ ያመራምራሉ። ርዕሰ ጉዳይ ሆነውም ያጽፋሉ።
ስለዚህ “ከየትኛው ነን፤ ካ’ፋዊ ወይስ ጡፋዊ?” ብለን ስንነሳ የጉዳዩን ስፋትና ጥልቀት፣ ወርድና ስፋት ከዚህ አኳያ ተገንዝበን ነው ማለት ነው። “ይህን ያልተገነዘበ አለ?” የሚል ካለ “አዎ አለ!!!” ካልን በኋላ ከላይ ከጠቀስናቸው አንዱ ላይ አተኩረን እንመለከተዋለን። በተለይም ለህዝብ ጥቅም ሲባል…
“ከየትኛው ነን፤ ካ’ፋዊ ወይስ ጡፋዊ?” ብለን ስንነሳ አዲስ ነገር ይዘን መጥተናል ብለን በማሰብ አይደለም። ጉዳዩ ተበልቷል፤ ተደልዟል፤ ተሰልቋል፤ እስኪበቃውም ተዘልዝሏል። “ከአድር ባይ ብዕር ባዶ ወረቀት …” ብቻ ሳይሆን አፋዊውን “… ናና ጻፍ በለው” ብሎ እስከ መጎነጥ ሁሉ ተደርሶ የጥቅሶች ሀውልት ተተክሏል። በተለይ በኪነ-ጥበቡ ዘርፍ እየተገላበጠ ተበራይቷል። ፀጋዬ ገብረመድህን በ”ግስ ግሳንግስ” ጉዳዩን ልቡ እስኪጠፋ ደቁሶታል፤ አንኳኩቶም “ኳኳታ …” መሆኑን አመልክቷል። ፕሮፌሰር መስፍን በድፍረት የመጀመሪያው እንጂ ሁለተኛውን አለመሆናችንን ተናግረዋል፤ አብራርተውም ጽፈውታል። ጉዳዩን ከ”ወሬ”ና “ወሬኛ”ነት አኳያ ከነካካነው ደግሞ መውጫ የለንምና እንዝለለው። ስንዘለው ግን የጥላሁን ገሠሠን “አንዳንድ ነገሮች …” አንድ ብለን ነው።
ሰው መልዕክቱን ለማስተላለፍ በርካታ አማራጮች አሉት፤ ከፈጣሪም፣ ከብጤዎቹም፣ ካካባቢውም፣ ከባህልና ወጉም አኳያም መንገዶቹ ብዙ ናቸው። በመሆኑም “በየትኛው …?” ለሚለው መልሱም ሆነ ምርጫው የራሱ ነው። ይህን ስንል ግን ከግልና ግለሰብ ህይወት አኳያ እንጂ ሁሉን በአንድ ከረጢት ከተን አይደለም። ቡድኖች፣ ተቋማት ወዘተ ከራሳቸው ምርጫ በዘለለ በሌሎች (በህግ፣ ባህል፣ ደንብና መመሪያ፣ ማንነታቸው በሰጣቸው ዕድል ወዘተ) (ቅድመ) ሁኔታዎች ምርጫቸው ይገደብና ለእነዛ ህጎች … ይገዙ ዘንድ ይገደዳሉ። “ምንው?” ቢሉ ምላሹ “ለህዝብ ጥቅም ሲባል …” ነው የሚሆነው። ይህን ካላደረጉ ለህዝብ ጥቅም ሲባል በተጎናፀፉት ልዩ መብት እያላገጡ ነው ማለት ነውና አሁንም እንላለን – ያስወቅሳል።
በአገራችንም እኮ ያለው የስነ-ቃል እሴታችን ለሁለቱም ዋጋ የሚሰጥ ቢሆንም ቅሉ ከንግግር የበለጠ ለጽሑፍ ትልቅ ቦታ እንዳለው የሚያሳዩ በርካታ ገለፃዎች፣ ተረትና ምሳሌዎች ወዘተ ያሉ ሲሆን፤ አንዱም “በቃል ያለ ይረሳል፤ በጽሑፍ ያለ ይወረሳል።” የሚለው ነው።
እርግጥ ነው በአሉ ግርማ “ከአድር ባይ ጽሑፍ ባዶ ወረቀት ይሻላል” ብሏል። ትልቅና ዘመን አይሽሬ አባባል ነው። ለህዝብ ምንም የማይጠቅም ሃሳብ ወይም ፖለቲካዊ ርእዮት ለህዝብ ጥቅም ሲባል በተሰጠ መብትና በተፈቀደ የመናገር፣ መፃፍ … መብት የተወደደ የጋዜጣ ገጽ አድር ባይ አስተሳሰብ፣ አውዳሚ ርእዮትና ዴሞክራሲን የሚያጨነግፍ አፍራሽ መመሪያ ሊሰፍርበት አይገባም። ምናልባት ይህን አስበው ከሆነ ተወዳዳሪዎቹ ገፁን ነፃ ያወጡትና ስለ እነሱ በሚገባና ለማወቅ ለማንበብ የሚጓጓን አንባቢ ወሽመጥ የበጠሱት ከዚህ አኳያ ከሆነ እንታገሳቸዋለን። ካልሆነ ግን ጡፋዊ ሳይሆኑ አፋዊ ናቸውና ትዝብታችን ዳር ድንበር፤ ወሰን ዲካ የለውም።
እርግጥ ነው፣ ከሌሎቹ የቋንቋ ክሂሎች አኳያ ሲታይ የጽሑፍ ክሂል ከበድ፣ ጠጠር፣ ቸገርም ይላል። (ጓሽ ስብሀት ገብረእግስዚአብሄር “ጽሑፍህን ተቹብህ እኮ …” ተብሎ ሲነገረው “ወሬ አያስፈልግም፤ ናና ፃፍ በለው” ብሎ መመለሱን እናውቃለን።) ይህ ግን እንደ ግለሰብ ሲያስቡት እንጂ እንደተቋም ወይም ቡድን ሲመለከቱት አይሠራም። ለዚያውም አገርን የሚያክል ነገር ወደ ፊት ይዞ ለመሄድ የሚሽቀዳደም አካል ጽሑፍን ተጠይፎ፣ ከጽሑፍ ርቆ እንዴት ሊሆን ይችላል? ነገሩ “ከአይን የራቀ ከልብ ይርቃል” እንደሚባለው ከጽሑፍ የራቀም ከንባብ ስለመራቁ መካካድ አይቻልምና ነገሩ ነገር ነው።
በበርካታ አገራት (ያደጉቱን ሳይጨምር) እንደሚስተዋለው፤ እዚህም ከምርጫ ‘97 ጋር በተያያዘ በተፈጠረው መነቃቃት ታይቶ እንደነበረው ከተሰጣቸው ገጽም ይሁን የአየር ሰዓት ባለፈ የየራሳቸውን (በህቡእ ጭምር) የህትመት ሚዲያዎችን አቋቁመው ተግባርና ፍላጎታቸውን ለባለ ድርሻ አካላት ሲያስተላልፉ፤ “ከወዳጅ ዘመዶቻቸው” ጋር ሲገናኙ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ከማለትም በታች የቅርብ ቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። “ያ ቀርቶ ሌላ ዘፈን መጥቶ” እንዲሉ ያ ሁሉ ቀረና ዛሬ እንደ በሬ ሽንት ወደ ኋላ …፤ ወደ ባዶ፣ ነጭ ወረቀት . . .
በየትኛውም መስፈርትና መመዘኛ ለህዝብ ጥቅም ሲባል በተጎናፀፉት መብት ማላገጥ ያስወቅሳል፤ እጅግም ያበሳጫል ብቻ ሳይሆን በህዝብና ለህዝብ ጥቅም ሲባል ልዩ መብትን በተጎናፀፈው አካል መካከል ግምብን ይገነባል፤ ገደሉን ይፈጥራል – የአገልጋይና ተገልጋይ አለመግባባት ክፍተትን ይፈጥራል፤ ኮንትራትም ይቋረጥና ከጨዋታው መገፍተር ሁሉ ይመጣል። ከዚያ በፊት ግን ስብሀት “… ናና ጻፍ በለው” እንዳለው እኛም እንላለን ጋዜጣው አፍ ቢኖረው ኖሮ ናና ጻፍብኝ … (በነገራችን ላይ ፕሬስ ድርጅት እነዚህን የቀለጡ ገፆች በተመለከተ “ማስታወቂያ ቢወጣባቸው ኖሮ”፣ “ሌሎች መረጃ ሰጪ ጽሑፎች ቢወጡባቸው ኖሮ” … ኖሮ … ኖሮ … በማለት ለሚቀጥለው ምርጫ ትምህርት ሰጪ በሚሆን መልኩ አስጠንቶ እንደሚያቀርብልን ተስፋ እናደርጋለን።)
እውነት እውነት እኛ ከየትኛው ነን፤ ካ’ፋዊ ወይስ ጡፋዊ? ከላይ እነፀጋዬ ያሉትን ትተን እንኳን የሰሞኑን ተጨባጭ መረጃዎች ብንመለከት ያለምንም ጥርጥር ሁለተኛው ሳንሆን የመጀመሪያው ነን። “ለህዝብ ጥቅም ሲባል …” የሚለውን ይዘን የመጀመሪያው መሆን አለመሆናችንን በማስረጃ እናጠይቅ (ጀስቲፋይ እናድርገው)።
የፖለቲካ አፃፃፍ (Political writing) ሰፊ የጥናትና የተግባር መስክ ሲሆን ከፕሮፓጋንዳ ጽሑፍ (propagandic writing) ዝምድና ያለው ነው። ዓላማውም ፖለቲካን የተመለከተ ሲሆን፤ እሱም የሚያገለግለውን የፖለቲካ አካል ተከታዮቹም ሆኑ ሌላው (በአጠቃላይ ባለድርሻዎቹ) እንዲያውቁለት ማድረግና ዓላማን ለህዝብ በተለይም ለድምፅ ሰጪው ወገን በማሳወቅ ድጋፍ ማሰባሰብ፣ ተጨማሪ ተከታይን ማፍራትና ወደ መንግሥትነት የሚያሸጋግረውን ሙሉ ተቀባይነት ማግኘት ነው። ለዚህ ደግሞ ጋሽ ስብሀት “… ናና ፃፍ በለው” እንዳለው መፍትሔው መፃፍ ነው።
በፖለቲካ እንቅስቃሴ ሂደት ማንኛውም ወገን በልቡ መወደድን፣ ከሌሎች መሰሎቹ ይልቅ እሱ ከፍ ብሎ መታየትን፣ ለስልጣን (መንግሥትነት) መታጨትን … ይፈልጋል፤ ሲጀመርም ዓላማው ይሄው ነው። በመሆኑም በእያንዳንዷ እንቅስቃሴና ተግባር ውስጥ ከፖለቲካዊ ንግግርና አካላዊ ቅስቀሳ ባለፈ ፖለቲካዊ ጽሑፍ (እንዲሁም የእሱ ቤተሰብ የሆነው የፕሮፓጋንዳ ጽሑፍ) በሠፊው ይከናወናል። እስከ ዛሬ እንደታየውም በህትመት ሚዲያ አማካኝነት የተደረገ ቅስቀሳም ሆነ ሌላ ከሌሎቹ የተሻለ ደረጃ ተደራሽና ውጤታማ ሆኖ ነው የተገኘው። ይህንን እጅግ እንኳን ባይባል በተወሰነ ደረጃ ወደ ኋላ ብንወስደውና የሩሲያን (የጥቅምት) አብዮት አንስተን ግንባር ቀደሙን ሌኒን ወስደን ብናየው ይህ አዋጭነቱ የትናየት ሆኖ ነው የምናገኘው።
ከላይ ያልነውን በሌላና የዚህ ፅሑፍ አጋዥ በሆነ ቋንቋ ስንገልፀው የትም አገር ብዕር አልባ ፖለቲካም ሆነ ብዕር ጠል የፕሮፓጋንዳ ቅስቀሳ የለም፤ ያለው (መልካሙ ተበጀ “ብዕር ብዕር ብዕር …” እንዳለው) በዕርን መሰረት ያደረገ፣ ብዕርን ምርኩዝ ያደረገ፣ ብዕርን መሳሪያው ያደረገ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነው በመጨረሻው ሰዓት ዳር ደራሽ የሚሆነው። ለዚህ ምስክሮቹ በርካቶች ሲሆኑ ራቅ ካለው ቭላድሚር ኤሊች ሌኒንን፤ ቀረብ ካሉት ባራክ ኦባማን መጥቀስና “… ናና ጻፍ በለው”ን በተግባር ማየት ይቻላል።
ወጣቶችን በተመለከተ የመጀመሪያውንም የመጨረሻውንም ንግግር ማድረጉና ከእሱ በኋላ የተደረጉት (እስከአሁንም ድረስ) የእሱ ቅጂ ናቸው ተብሎ የሚነገርለት ሌኒን በ”ሦስተኛ ሁሉም-ሩሲያዊ ኮንግረስ” (ኦክቶበር 2 /1922) ላይ ያደረገው ታሪካዊ ንግግር በሚያስገርም ፍጥነት ዓለም አቀፍ ተሰሚነት፣ ተቀባይነትና ተወዳጅነትን በማግኘት መላው አድናቂውን፣ አብዮተኛውንና ዓለም አቀፍ ወዛደሮችን ከጎኑ በማሰለፍ በተቃዋሚዎቹ ላይ ዘገር ይነቀንቁ ዘንድ ያስቻለው በኮንግረሱ ላይ የተናገረው “The Tasks of the Youth Leagues.” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ንግግሩን የያዘ ፓምፍሌት ኖቬምበር 1920 በጋዜጣ ላይ ታትሞ ባልተጠበቀ ፍጥነት 200 ሺህ ኮፒ በመላው ዓለም በመሰራጨቱና አድናቂዎቹ፣ ደጋፊዎቹና አጋሮቹ ዘንድ በመድረሱና ሃሳብ ተቀባይነት በማግኘቱ ሌኒን ውጤታማ ይሆን ዘንድ አስችለውታል። (ይህ ፓምፍሌት በመላው ዓለም ባሉ ቋንቋዎች ከ150 በላይ ጊዜ በላይ ታትሞ ለመሰራጨት የቻለና በወቅቱ ዓለምን ያስደነቀ ሥራ እንደነበር ተዘግቧል።)
ወደ ኦባማም ስንመጣ፣ የመንገዱ (ሚዲየም) ልዩነት ካልሆነ በስተቀር፣ በታየው ደረጃ ውጤታማ የሆኑትና ለዩኤስኤ አሜሪካ ፕሬዚዳንትነት የበቁት ባደረጓቸው አስደናቂና አጓጊ ንግግሮቻቸው ብቻ አይደለም፤ ይበልጥ የጠቀማቸው ወደ ምርጫ ከመምጣታቸው አስቀድመው አቋማቸውን፣ ፍላጎታቸውን፤ ቢመረጡ አሜሪካንን የትና የት እንደሚያደርሷት የገለፁባቸው ሁለት መጻሕፍትን ወደ ሕዝቡ በመልቀቃቸውና የዜጎችን ቀልብ መግዛት በመቻላቸው ነው። የ”ናና ፃፍ በለው …” ፋይዳ እዚህ ድረስ ነው ማለት ነው። (ወደ አገራችን ስንመጣም ተመሳሳይ ሁኔታን የምናገኝ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት በብዕር ስም “እርካብና መንበር”ን መልቀቃቸው፤ ስልጣን ከያዙ በኋላ መጽሐፉ የሳቸው መሆኑ መገለጹ በህዝብ ዘንድ የፈጠረላቸው ተጨማሪ ውዳሴና ሙገሳ የምናስታውሰው ነው።)
በዚህ በሁሉም የግንኙነት መስመሮች (መገናኛ አውታሮ) ቅስቀሳው ይጧጧፋል ተብሎ በሚታሰብበት፤ ሰላምና መረጋጋት እጅጉን በሚያስፈልግበትና ለዚህ የሚሆን ሃሳብ ባጠጠበት፤ አማራጭ የፖሊሲ ሃሳቦች የውሀ ሽታ በሆኑበት የመንደር ጎረምሳ ሁሉ ካልነገስኩ እያለ አገርን ያህል ነገር ቁና ካላደረኩ በሚልበት፤ ዴሞክራሲ፣ ምርጫ፣ መብት ወዘተ ዓይነት ፅንሰ ሃሳቦችን ሁሉም በየፊናው እየተረጎመ ከእኔ ወዲያ … እያለ ምድር የሚለቀው በበዛበት በዚህ ቀውጢ ሰዓት ለህዝብ ጥቅም ሲባል በተሰጠ የተጠቃሚነት ዕድል ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚገልጹት ሃሳብ፤ ወይም የሚፅፉበት እውቀት አጥተው ይሁን ባይታወቅም ባዶ የጋዜጣ ገፆችን እያስኮመኮሙን ነው። (ምናልባት “ከአድርባይ ብዕር ባዶ ወረቀት ይሻላል” ከሆነ ልንስማማ እንችላለን፤ ያ እንዳይሆን ግን እሱም ቢሆን አልተነገረንምና ከ”… ናና ፃፍ በለው …” በቀላሉ መላቀቅ አይቻልም። “… ናና ፃፍ በለው …”
ነገሩ “ካፈርኩ አይመልሰኝ” ሳይሆን አይቀርም ለህዝብ ጥቅም ሲባል የእነሱን ባዶ ገጽ ይዞ በሚዞረው ጋዜጣ አዟሪ የሚዞርበትን ጎዳና አደባባይ እነሱም ማይክራፎን ይዘው በዘፈን እየደነሱ ማጣበባቸው ነው። ነገሩ ከጡፍ አፍ ይቀላልና ትክክል ነው ብንልም ባንልም፤ ጋሽ ስብሀት “… ናና ፃፍ በለው” ያለውን ስናስብ የጽሑፍ ሥራ እንደ አፍ፤ በተዋበ መኪና እየተንሸራሸሩ በትልቅ ሞባይል ቃለ-መጠይቅ እንደማድረግ የቀለለ አለመሆኑን አስቀድሞ መረዳቱን በአድናቆት እንገልፅለት ዘንድ እንገደዳለን።
የህትመት ሚዲያን ለጥናትና ምርምር የተጋለጠ መሆኑ፣ በየግለሰቦች ቤት ሳይቀር በቀላሉ ተሰንዶ በመያዝ በቀላል ማመሳከሪያነት ማገልገሉ፣ ለተለያዩ የንባብ ዓይነቶች የተመቻቸ (እስከ ጥልቅ/ምሁራዊ፣ ሃሳዊ … ንባብ ድረስ) መሆኑ እና ለሌሎች በርካታ ሁኔታዎች የተጋለጠ መሆኑ የተለየ ያደርገዋል። ከዚህ አንፃር የዛሬ ባዶ ገፆችም ወደ ፊት ሲጠኑና ሲመረመሩ የሚሉት ይኖራልና የአሁኑ ዘመን የፖለቲካ ፓርቲዎች የወደፊት ታሪካቸውን ከወዲሁ እየፃፉ ነው ማለት ነውና በእውነት ያሳዝናል። (ስብሃትስ “… ናና ፃፍ በለው” ብሎ ተገላገለ። እነሱ ቢጠየቁስ ምን ይሉ ይሆን? “… ናና አውራ …?”)
መቸም ይህንን ፀሐፊ “… ናና አውራ በለው” የሚል እንዳይነሳ እንጂ ባዶ ገፆችን ለ”አይዞህ ምረጠኝ፣ ጠቅላላ ችግሮችህን ከነሰንኮፋቸው ነቃቅዬ እጥልልሀሉ …” የሚል(ሉ) ፖለቲካ ፓርቲ(ዎች) ከጽሑፍ ሊርቁ እንደማይገባ ሊነገራቸውና ሊማሩበት ይገባል። የጋዜጣው ገጽ ለህዝብ ጥቅም ሲባል ለተፎካካሪዎች ተሸነሸነ እንጂ እንደ ወትሮው ሁሉ ይዟቸው የሚወጣቸው በርካታ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ሌሎች ጉዳዮች አሉት። ተፎካካሪዎችም ይህንን በውል ሊገነዘቡት በተገባ ነበር። ለህዝብ ጥቅም ሲባል የተሰጣቸውንም መብትና ልዩ ጥቅም ሊጠቀሙበት ይገባል እንጂ አሁን እንደሚታየው ሊቀልዱበት አልተፈቀደላቸውም።
አሁንም “ናና አውራ በለው …” እንዳንባል እንጂ በእውነቱ በጋዜጣ ገፆች ላይ እየተዋለ ያለውን ግፍ እነሌኒን ቢሰሙ፤ ኦባማና መሰሎቹ ቢያዩ ምን እንደሚሉ ለማመን ያስቸግራልና ጉዳዩ ስር እንዳይሰድ፤ ባህልም ሆኖ የንባብ ባህልን (የተፃፈ ከሌለ የሚነበብ ሊኖር ስለማይችል) እስከመግደል እንዳይዘልቅ ከወዲሁ አንድ ሊባል ይገባል፤ “… ናና ፃፍ በለው …” ብንልም ባንልም ይህን ህዝባዊ ኃላፊነት እንደ አልባሌ ከንቱ ማድረግ አይገባም እንላለን።
ለሦስተኛ ጊዜ “ናና አውራ በለው …” እንዳንባል ፈርተን ነው እንጂ እኮ ለካ ከዚህ በፊት “ሚዲያውን መንግሥት ተቆጣጥሮታል፤ ተቃዋሚዎችን አፍኗል …” ሲባሉና እኛን አድማጮቹን በኀዘኔታ ከንፈራችንን እንድንመጥ ሲያደርጉን የነበሩት ምሬትና ክሶች “ቧልታይ ትያትር ነበሩ እንዴ?” ብለን እንድንጠይቅ ሁሉ እያሳሰቡን መሆኑን በትህትና ብንገልጽ የጋዜጦች ባዶ ገፆች አምላክ ይፈቅድልናል ብለን እናምናለን። የ”…ናና ፃፍ በለው . . .”ም እንደዚያው።
ምንም እንኳን “ናና ፃፍ” ብንልም ባእድ አስተሳሰብ፣ አውዳሚ ርእዮት፣ አጫራሽ ፍልስፍና … ሊጫንብን፤ እንቶ ፈንቶው ሁሉ ሊረጭብን ይገባል እያልን አይደለም። መስዋእቱ ብዕረኛ በዓሉ ግርማ “ካ’ድር ባይ ብዕር …” እንዳለው ቢቀርብንና ባዶውን ወረቀት ብንሸምት ይሻለናልና የካርዱ ለት እንገናኝ።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2013