ኢትዮጵያ ሰማንያ በላይ ብሄረሰቦች የሳሏት የጋራ ምስላቸው ናት።ብዙ ሃሳቦች፣ ብዙ ታሪኮች የተዋሀዱባት የተዋጡባትም ድብልቅ እውነት ናት።ብዙ ዓይነት ባህሎች፣ ብዙ ዓይነት ስርዐቶች በአንድነት ያቆሟት የሰውነት ስጋና ደም እንዲህም ናት።በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ አለች።የእውነት ጥጋችንም ናት።
ኢትዮጵያ ሲባል አቤት የምንለው ሁላችንም ነን።በደስታዋ የምንደሰተው በኀዘኗ የምናዝነው በጋራ ነው ምክንያቱም የጋራ ስዕላችን ናትና።በኢትዮጵያዊነት ውስጥ እኔነት የለም።እኛ ብለን በጋራ እንድንጠራ የሚያደርግ የጋራ ታሪክ ያለን ህዝቦች ነን።በትልቅ ዓለም ላይ የደመቅን ገናና ህዝቦች ነን።አሁን ላይ አንዳንዶች ይሄን ረጅም ዘመን ያስቆጠረ አንድነት ለማላላት የተንኮል ሴራ ሲሸርቡ ይታያል።ውብ መልካችን እንዳይጠይም ለዘመናት የገነባንው ታሪካችን እንዳይበላሽ ለጠላት ጆሮ መስጠት የለብንም።
በትላንትናዋም ሆነ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ የእያንዳንዳችን አሻራ ጎልቶ ይታያል።ከትላት እስከዛሬ የሌለንበት ጊዜ የለም።የእኔና የእናተ በጋራ መቆም ከኃይልና ከሞገስ ባለፈ ኢትዮጵያ ሙሉ ሆና እንድትታይ የሚያደርጋት ደማቅ ውበቷ ነው።ከመካከላችን አንዳችን ከጎደልን ኢትዮጵያ ጎዶሎ ናት ማለት ነው።ኢትዮጵያ እንዳትጎድል እኛ መጉደል የለብንም።ስለዚህም ሙሉ ሆነን እንድንታይ አንዳችን ለአንዳችን እናስፈልጋለን ማለት ነው።
ኢትዮጵያን ከባህላችን፣ ከወግና ስርዐታችን ውስጥ ያበቀልናት የወርቅ ሙዳያችን ናት።ከመልካችን፣ ከታሪካችን ውስጥ የመዘዝናት የአብሮነታችን ውጤት ናት።በተናጠል እንገነባታለን ብለን የምናስብ ከሆነ ተሳስተናል።በህብረት እንጂ በተናጠል የምትገነባ ኢትዮጵያ የለችም።በውይይትና በመነጋገር እንጂ በቅራኔ የምትበለጽግ ሀገር የለችንም።በሥራና በሃሳብ የበላይነት እንጂ በኔነትና በአጉል ራስ ወዳድነት የምትቆም ሉዐላዊ ሀገር የለችም።
ቀለማችን እንዳይደበዝዝ..የአባቶቻችን የአደራ ቃል እንዳይታጠፍ ለጋራ ጥቅም በጋራ መቆም አለብን።እኛ የኢትዮጵያ መልኮች ነን።እኛ የሀገራችን ውበትና ደም ግባት ነን።ኢትዮጵያ እያንዳንዱ ዜጋ ከደሙ እያጠቀሰ የቀለማት ውብ ስዕሉ..ውብ ፊደሉ ናት።በውብ ስዕላችን ውስጥ ነው ያለንው።በውብ ፊደላችን ውስጥ ነው የተጠለልነው።
እንደ ዜጋ በእውቀታችንም ሆነ በምንችለው በማንኛውም ነገር ለሀገራችን ምርጡን ልናደርግ ይገባል።የምንፈልጋት ሀገራችን በሃሳባችን ውስጥ ናት።አሁን ላይ ከዚም ከዚያም የተለያዩ አፍራሽና ገንቢ ሃሳቦች የሚሰሙበት ጊዜ ላይ ነን።የበግ ለምድ ለብሰው ጥሩ መስለው በመታየት ሀገር ለማፍረስ ከላይ ታች የሚሉ በርካታ ግለሰቦች የመኖራቸውን ያክል በመልካምነት ለሀገራቸው የቻሉትን በጎ ነገር ለመሥራት ደፋ ቀና የሚሉም አይጠፉም።እናንተ ከየትኛው ወገን ናችሁ?
በጊዜያዊ ጥቅም ተታላችሁ ሀገራችሁ ላይ ክፉ የምታደርጉ ከሆነ እመኑኝ የእጃችሁን የምታገኙበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።ክፉዎች ሁሌጊዜም እንደተቀጡ ነው።መታሰቢያቸውን ከምድር ያጠፋ ዘንድ የአምላክ ዓይኖች ክፉን በሚያደርጉ ላይ እንደሆኑ ልታውቁ ይገባል።የአባቶቻችን አደራ ይፋረደናል።የድሀ ህዝብ ዕንባ ይቀጣናል።እውነቱ ይሄ ነው።ያሉብንን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግሮች በንግግር እየፈታን ነገ ላይ ለምትፈጠረው ለአዲሲቷ ሀገራችን የበኩላችንን ማዋጣት ነው የሚበጀን።
በሀገራችን ጉዳይ ላይ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ከሀገር ፍቅር መገለጫዎች ውስጥ አንዱ ነው።ከስሜታዊነት ወጥተን በሰከነና በተረጋጋ መንፈስ ለሀገራችንም ሆነ ለህዝባችን ምርጡን የምናደርግበት ጊዜ እንዲመጣ ሁላችንም መትጋት ይኖርብናል።ስሜት አደገኛ ነው..መጥፎ ነገሮች ሁሉ ካለምክንያትና ካለማሰብ የተፈጠሩ ናቸው።የእስከአሁኑ የሀገራችንም ችግር ከዚህ የዘለለ አይደለም።
በስሜት ታሪክ የምናበላሽ፣ በስሜት በወንድማማቾች መካከል ጠብን የምንዘራ፣ በስሜት ሀገር የምናፈርስ፤ ንብረት የምናወድምና የሰው ህይወት የምናጠፋ ብዙዎች ነን። ስሜት ውስጥ እውቀት የለም..ስሜት ውስጥ ማሰላሰል የለም።ስሜት የድቁርና ወንድም ነው።ምንም ነገር ለማድረግ ከመወሰናችን በፊት በትክክለኛ ሁኔታ ላይ መሆናችንን ማጤን ያስፈልገናል።ሀገር በምክንያት እንጂ በስሜት አትመራም።በየትኛውም የህይወት ጉዟችን ውስጥ ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች ጠቃሚ ሆነን እንድንቆም ምክንያታዊ መሆን ይጠበቅብናል።
ከሃሳባችን መካከል ምርጡን እያዋጣን ባለንበት በቆምንበት ቦታ ሁሉ ለአንድነታችን የምንተጋ ከሆነ ክብራችንን ማንም አይወስድብንም።በአብሮነት የምትደነቀው የጥንቷ ኢትዮጵያ አልናፈቀቻችሁም? እኔ ግን ናፍቃኛለች።የአባቶቻችን የኩራት ጥግ የሆነችው፣ እውነት ባወቁ..ፍቅር በሰነቁ ነፍሶች የቆመችው ያቺኛዋ ኢትዮጵያ ናፍቃኛለች።አንድ ሀገር አንድ ህዝብ ናፍቆኛል፡፡
ሳባዊቷን..ምኒሊካዊቷን ጥቁር ወይዘሮ..ያቺን አክሱማዊቷን..ቴዎድሮሳዊቷን..አብዲሳ አጋይቷን እመቤት ልቤ እሷን ይለኛል።ያቺ የአፍሪካ ኩራት፣ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ሰንደቅ የነበረችው እንቆጳ ጊዮን ምድር ነፍሴ እሷን ትሻለች።ድሮነትን በዛሬአችሁ ውስጥ ፍጠሩ።የአባቶቻችን ፍቅር የአያት ቅድመ አያቶቻችን መዋደድ ዛሬ በእኔና በእናተ ነፍስ ላይ ያቆንጉል።
ዓለም ያከበራትን፣ የግሪክ ጸሐፍት፣ የአቴንስ ልዑላን በድርሰቶቻቸው ያወደሷትን ከነአናዊት ኢትዮጵያ በሁላችን ነፍስ ውስጥ እንድትበቅል እፈልጋለሁ።ቀለማችን እሷ ናት።እውነተኛ መልካችን፣ እውነተኛ ማንነታችን እሷ ናት።ዛሬ ላይ ሌላ ነን..የአባቶቻችን ጸዐዳ መልክ መልካችን ላይ የለም።የአያት ቅድመ አያቶቻችን መልካም ነፍስ ነፍሳችን ላይ የለም..በፍቅር ያጌጡ የፊተኞቻችን ቅን ልቦች በልቦቻችን ላይ የሉም።
ዛሬ ሌላ ነን።በወንድሞቻን ሞትና መፈናቀል የምንደሰት፣ በሀጢያት የምንስቅ፣ ፈጣሪን በመርሳት የምንኖር እንደዚህ ነን።ብዙ ነገራችን አባቶቻችንን አይመስልም።እነሱ የሌሎች መደነቂያ ነበሩ ዛሬ እኛ በሌሎች መደነቅ ግብራችን ሆኗል።በሌሎች ሀገራት ባህልና ወግ እምነትና ስርዐት ኖረን የእኛ የሆነውን አጥተናል።እኛነታችንን ተነጥቀናል።የአባቶቻችንን የአደራ መልክ አጠይመናል።
የሌሎችን ለብሰን፣ በሌሎች አጊጠን የእኛ የሆነውን ድንቅ ባህል፣ ውብ ተፈጥሮ በርዘናል።የውጭውን የባዕድ አስተሳሰብ አንድ ሳይቀር ወስደን ብዙዎች የሚፈልጉትን ምርጡን ሀበሻነት ከሌላ መጤ ባህል ጋር ቀይጠንዋል።አሁን እኛ የቱን እንደሆንን አናውቅም።ብዙ ነገራችን ድብልቅ ነው።የራሳችን መልክ ጠፍቶብና።መሀል ላይ ነን..ገና ራሳችንን ፈልገን አላገኘንውም።
የእውቀት ማነስ በፈጠረብን አደገኛ ተጽዕኖ ከሁሉም ትልቁን ራሳችንን አጥተን የሰዎች ሆነናል።አባቶቻችን እንዲህ አልነበሩም።ሌሎች እየፈለጓቸው፣ ሌሎች እየናፈቋቸው በብዙ መፈለግ ውስጥ ኖረው ያለፉ ነበር።እኛ የነሱ ልጅ ዛሬ ላይ ስልጣኔ መስሎን ሀገር ሸጠን ባህል በርዘን በሀበሻና በፈረንጅኛ መካከል ላይ ቆመናል።አውሮፓና ኢሲያ ለአንድ ወር ሄደን አማርኛ የሚጠፋብን።ተወልደን ያደግንበትን ኢትዮጵያዊነት የምንረሳ እንዲህ ነን።ራሳችንንም ሆነን ታሪካችንን ለመታደግ ጊዜው አሁን ነው፡፡
የእኛ የሆነውን ወግና ባህላችንን፣ እምነትና ስርዐታችንን፣ ቋንቋና ልማዳችንን ትሩፋታችንንም በሚገባ በመጠቀም አንቆ ከያዘን ፈረንጅኛ አስተሳሰብ እንወጣለን ብዬ አስባለው።ለአዲሷ ኢትዮጵያ አዲስ ሆነን መብቀል አለብን።የእኛ የሆነውን የአባቶቻችንን እውነት በመኖር ቀጣይ ዕድላችንን እንወስን እላለሁ።ያኔ ምናልባት ካሰብንው የስልጣኔ ጥግ እንደርስ ይሆናል።ዓለምም ራሳችንን ሆነን ሲያየን በባህላችንና በስርዐታችን ተደንቆ እኛ እነሱን ለመምሰላችን ቀርቶ እነሱ እኛን የሚመስሉበት ጊዜ ይፈጠራል።
ስልጣኔ ያለው ራስን በመሆንና የራስ የሆነን ነገር በማድነቅ ውስጥ ነው።ወደ ኋላ ሄደን የተውንውን፣ የረሳንውን ማንነታችንን ማየትና መረዳት ይኖርብናል።ከስማችን ጀምሮ ሁሉ ነገራችን የሌሎች በሆነበት ሁኔታ ላይ ከዚህ የተሻለ አማራጭ የሚኖረን አይመስለንም።ወዛችሁን መልሱት።የመጣንበት፣ የበቀልንበት የአባቶቻችን ማሕጸን ድንቅ ነው።
ሀገራችሁን በሃሳባችሁ አኑሯት እንጂ አትግደሏት።ኢትዮጵያን እንደፈለጋችሁ አድርጋችሁ ልትስሏት ብሩሹም ሸራውም እጃችሁ ላይ ነው።ልብ ልትሉት የሚገባ አንድ ነገር ቢኖር ባበላሻችኋት ሀገራችሁ ላይ የምትኖሩት እናተና ልጆቻችሁ ናችሁና የዛሬ ድርጊታችሁ ነገም ይከተላችኋልና ምርጧን ሀገር ለመሳል ምርጥ ሰአሊ መሆን ይጠበቅባችኋል።በአባቶቻችን ስም እንጠራ።መልካም አባት፣ መልካም ትውልድ አናጺና መሀንዲስም በመሆን ይቺን ሀገር ላቆዩልን ጥበበኛ እጆች፣ ቅን ልቦች፣ አዛኝ ነፍሶች ራሳችንን እናስገዛ፡፡
ዛሬም ኢትዮጵያ በተለያዩ ዓለም አገራት በእውቀታቸው ጥግ የደረሱ በርካታ የተማሩ ልጆች አሏት።አገር ውስጥም ኢትዮጵያ ዕድገት፣ልማትና አንድነት ለማስጠበቅ ሌት ተቀን በቅንነትና በትጋት የሚሠሩ ልጆች አሏት።በተለይ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የዕድገት ግስጋሴ በተለይ ኢትዮጵያ የታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ አፋጥና ወደ መጨረሻው ምዕራፍ መድረሷ ያስደነገጣቸውና ያስደነበራቸው አገራት የተለያዩ ሴራዎችና ጫናዎችን እየፈጠሩባት ናቸው።ለእነዚህ ሴራዎችና ጫናዎች አንዱ ተጨባጭ ማሳያ የሚሆነን በቅርቡ አሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ የመንግሥት ባለስልጣናት ላይ የጣለው የጉዞ ክልከላ ነው፡፡
ስለዚህ ኢትዮጵያዊያን የውጭ ጣልቃ ገብነትን በአንድነት የምንመክትበት ጊዜ ላይ ነን።በውጭ የሚገኙ ዲያስፖራዎችም ለሚወዷት አገራቸው ድምፃቸውን የሚሰሙበት ጊዜ ነው።ከውጭ ተጸእኖ የምንላቀቀው ብቸኛው መንገዳችን አካባቢያችን ብሎም አገራችንን በትጋት ማልማት ስንችል ነው።ድህነትን የምንቀንሰውና ጣልቃ ገብነትን ድል የምናደርገው በህብረትና በአንድነት አገራችንን ስናለማ ነው።ኢንዱስትሪን ስናስፋፋ፣ እርሻን ስናዘመንና የተፈጥሮ ሀብትን ስንጠብቅ ነው፡፡
ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ጫና የሚፈጥሩ አገራትን አሻፈረኝ የምንለው ጥበብ የታከለበት ዲፖሊማሲያዊ መንገድም ስንከተል ነው።ለዚህም ሁላችንም ኢትዮጵያዊያን በተሰማራንበት ሙያ አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት ማድረግ አለብን።ሰሞኑን የውጭ አገራትን ጣልቃ ገብነት በመቃወም በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የታቀውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል። ዘመቻው እኛ ኢትዮጵያዊያን ሉዓለዊነታችን ለውጭ ጣልቃ ገቦች አሳላፈን እንደማንሰጥ በተጨባጭ ያሳየ ነው።
ኢትዮጵያዊን በውስጣችን የሚስተዋሉ ጥቃቅን ልዩነቶች ወደ ጎን በመተው በሀገር ሉአላዊነትና አንድነት ላይ ለሚያዣንብብ ማንኛውም ጥቃት የማይበገር መንፈሰ ጠንካራና ኩሩ ህዝቦች መሆናችንን በእውነተኛ መረጃ በማስደገፍ ልናሳያቸው ይገባል። ምክንያቱም የተባበረ ክንድ፣ በጸኑ መዳፎች ህያው አድርገን ያቆምናት ኢትዮጵያችን ዛሬም ጸንታ እንድትቆም የጥንቱ አብሮነታችን ዋጋ አለው።
ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2013