ሥዕል ከፍ ያለ ክህሎት ከነጠረና ጥልቅ ሀሳብ ጋር ተዋህዶ በአንድ ገጽ የሚታይበት ጥበብ ነው፡ ፡በብዙ የዘርፉ አጥኚዎች ቀዳሚ የኪነ ጥበብ ዘርፍ መሆኑም ይነገርለታል። ሥዕል የታሪክ አሻራን በጉልህ አድምቆ የማሳየትና ዘመናትን ተሻግሮ የመታየት አቅሙ ከፍተኛ ነው፡፡ የሰው ልጅ ለዘመናት ሥዕልን ለሥልጣኔው፣ ለባህልና ለአኗኗር ዘይቤው ማመላከቻ ሲጠቀምበት ቆይቷል፡፡ በሀገራችን የሥዕል ጥበብ እድገት ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እያሳየ ቢሆንም እድገቱ አዝጋሚ መሆኑ ይነገራል፡፡ ለዚህ ደግሞ በዘርፉ የሚስተዋለው ችግር ማነቆ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በዛሬ የኪነ ጥበብ አምዳችን አንድ የሥዕል ማህበርን እንደማሳያነት እናንሳ።
ማህበሩ በአገራችን የሥዕል ጥበብ ያለበት አጠቃላይ ሁኔታ፣ የሥዕል ጥበብ እድገት ዋንኛ ማነቆዎች፣ ወደፊት ዘርፉ ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ እንዲሆን መከናወን ያለበትን ተግባር እንመለከታለን። በሥነ ጥበብ ዘርፍ ውስጥ የሚካተተው ሥዕል ካሉበት ውስብስብ ችግሮች አንጻር ባለሙያው በተናጠል እንቅፋቶቹን ከመጋፈጥ በጋራ በማህበር ተደራጅቶ መሥራት መፍትሄ ነው በማለት በአንድ ጥላ ስር ተሰባስቧል፡፡ ማህበሩ በሠዓሊና መምህር እመቤት አወቀ ሀሳብ አመንጪነት ነው የተቋቋመው፤ የሴት ሠዓሊያን ማህበር፡፡ እናም ይህ ማህበር የሥዕል ባለሙያዎችን በጋራ በማደራጀት በዘርፉ ተወዳዳሪና በጎ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን እንዲችሉ የማድረግ ዓላማ ሰንቋል፡፡
ማህበሩ ዛሬ ላይ ከሥዕል ትምህርት ቤት ወጥተው ወደ ሥዕል ሙያ መቀላቀል ለሚፈልጉ ሴቶች መንገድ አመላካች፣ ልምድና ተሞክሮን አጋሪ፣ የጀመሩትን አዲስ ሥራ ወደ ህዝብ ማቅረቢያ ምቹ ሁኔታ ፈጣሪ ሆኗል፡፡ አንጋፋና ወጣት የሥዕል ባለሙያዎችን በስሩ አስጠልሏልም። በሀገሪቱ የሥዕል ጥበብ ላይ የራሱን አሻራ በማሳረፍ ላይም ይገኛል፡፡ ሴት ሠዓሊያኑ ‹‹ማህበር›› መስርተው በጋራ መሥራታቸው ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያስገኘላቸው ቢሆንም ያለሙትን ለማሳካት በሥዕል ሙያ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮች ፈተና ሆኖባቸዋል፡፡ ከጅምሩ የሥዕል ጥበብን ለማሳደግ በጋራ መሥራት መፍትሄ አድርጎ የተቋቋመውና ትልቅ ዓላማን ለማሳካት ነበር፡፡ ሆኖም እየተውተረተሩ ቢሆንም በዘርፉ ነጥሮ ለመውጣትና የማህበርተኞችን አቅም ማሳደግ እንዳልቻሉበት ወይዘሮ እመቤት አወቀ የሴት ሠዓሊያን ማህበር መስራች ይናገራሉ።
እየገጠሟቸው ያሉት መሰናክሎች እልፍ መሆናቸውን የሚያነሱት ወይዘሮ እመቤት፤ የማህበሩ ሥራዎች ማስተባበሪያ ቢሮ ችግር፣ ሠዓሊው ሥራዎቹን የሚሠራበት ቦታ አለመሟላት፣ በግል ጥረትና ምቹ ባልሆነ ሁኔታ የተሠራው ሥዕል ማሳያ ቦታ ማጣትና የስንግ ይዘው አላፈናፍን ያሏቸው ችግሮች እንደሆኑ ይገልጻሉ፡፡ ወይዘሮ እመቤት፤ በዓመት ሁለት ወይም ሦስት ጊዜ በሥዕል አውደ ርዕዮች፣ መደበኛ የሥዕል ማሳያና መሸጫ ጋለሪዎች እንዲሁም መሰል መርሀ ግብሮች ላይ የማህበሩ አባላት ሥዕልና የእደ ጥበብ ውጤቶችን ለህዝብ ያቀርባሉ፡፡
እጅግ ውስን በሆነ ቦታና ጊዜ መቅረቡ ደግሞ ተደራሽነቱን ይቀንሰዋል፡፡ ሠዓሊው በአዳዲስ ፈጠራ ሀሳቦች መሪነት የሚያዘጋጀው ሥዕል ቋሚ የሆነ ማሳያና መሸጫ ቦታ ሊገኝለት አልቻለም፡፡ ይህ ችግር የማህበሩ አባላት የተሻሻሉ አዳዲስ ሥራዎችን ሠርተው ወደ ህዝቡ ማቅረብ እንዳይችሉ እንዳደረጋቸው ያስረዳሉ:: ወይዘሮ ሩት አድማሱ የሴት ሠዓልያን ማህበር ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ሠዓሊ፣ የሥዕልና ግራፊክስ ዲዛይን መምህርም ናቸው፡፡ ‹‹ሥዕል የሰዎችን ውስጣዊ ጥልቅ ሀሳብ ማሳያ ልዩ ጥበብ ነው፡፡ በአንጻሩ ግን ጥበበኛው በሚፈለገው መልክ ተጠቃሚ መሆን አልቻለበትም›› በማለት አሁን ላይ የሚገጥማቸውን ፈተናዎች ይዘረዝራሉ፡፡
ኢትዮጵያውያን ጥበበኞች ናቸው። ለዚህ ማሳያው ደግሞ የቀደሙ አባቶቻችን የጥበብ አሻራቸው ያሳረፉባቸው እነ አክሱም፣ ላሊበላ፣ ፋሲል ግምብ፣ በእምነት ተቋማትና ታሪካዊ ቦታዎች ላይ በልዩ ልዩ ቀለማት ተስለውና ተቀርጸው ዛሬ ድረስ የሚያስደምሙ ሥራዎቻቸው መመልከት ከበቂ በላይ ነው፡፡ ሥዕል አንዱ የጥበብ መስክ ነው፡፡ ነገር ግን በአገራችን እድገቱ የዘገየና ያልዘመነ ነው፡፡ የዚህ ምክንያት ምን ይሆን? ስንል ከፈረሱ አፍ እንደሚባለው ባለሙያዎቹን ጠይቀናል፡፡ ወይዘሮ ሩት በሀገር ደረጃ ለስዕል ጥበብ ትኩረት ተሰጥቶ አለመሠራቱ፣ ለሥዕል ሥራ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች ላይ የበዛ ቀረጥ መጣሉ፣ በቂ የሥዕል ትምህርት ቤቶች አለመኖር፣ የሥዕል ማሳያ ቦታዎች በቂ አለመሆንና ለሙያተኛው ምቹ ሁኔታ አለመፈጠሩ ዋነኛ ምክንያት ነው ይላሉ።
እንደ ፕሬዚዳንቷ አመለካከት፤ ማህበረሰቡ ለሙያው ያለው አተያይ ወይም እሳቤ ቀጥተኛ ያለመሆን፤ ሰዓሊ እራሱን የጣለ፣ ፀጉሩን ያንጨባረረ ተደርጎ መሳሉ፤ ተራ ህይወትን የሚመራ ተደርጎ መወሰዱ በውስብስብ ችግር ፈጣሪነት ከሚነሱት መካከል ናቸው፡፡ በተለይ ይህን መሰል አመለካከት በሚዲያ ተፅዕኖ የመጣ መሆኑን ያስረዳሉ። በሙያው ውስጥ የሚገኙት ደግሞ እውነታው ሌላ መሆኑን ለመከራከሪያነት ያነሱታል፡፡
በምናያቸው ድራማዎች፣ ፊልሞችና የስነ ጽሁፍ ውጤቶች ሠዓሊያን የሚሳሉበት ገጸ ባህሪ ህብረተሰቡ ሙያውን በተሳሳተ መንገድ እንዲረዳው አድርጎታል ይላሉ፡፡ ይህ ፈር የለቀቀ እሳቤ ሊስተካከል ይገባል የሚል ምክረ ሃሳብም ይሰነዝራሉ፡፡ የሥዕል መምህርና የሴት ሠዓሊያን ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አይናለም ገብረማርያም በበኩላቸው፤ ‹‹ሠዓሊነት ጥበበኛ እጆች የታደሉ ባለሙያዎች የሚገኙበት ዓለም ነው›› ይላሉ፡፡ አስረጂ ምክንያቶችን ሲያነሱም በአገራችን ብሎም በዓለም ታዋቂ የሆኑትን የጥበብ ሰው እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜተር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌን በቀዳሚነት በመጥቀስ ነው፡፡ በዚህ መነሾ ሠዓሊነት ማለት ከሙያው ውጪ ያሉ ሰዎች በተንጨባረረ ፀጉር እና በተለያዩ ሱሶች በተያዘ ሰው ብቻ የሚመሰል አለመሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ዘመን ተሻጋሪና ታሪክ አስረጂ የሆነውን የስዕል ጥበብ ለማሳደግ፤ ማህበረሰቡ ለሥዕል ጥበብ የሚሰጠው ክብርና ፍቅር ከፍ እንዲል፤ ከትምህርት ቤት ጀምሮ ህጻናት የሥዕል ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ምክትል ፕሬዚዳንቷ ይገልፃሉ፡፡ በሥዕል ጥበብ ትልቅ ቦታ የደረሱ ኢትዮጵያዊያንን በበቂ ሁኔታ ማስተዋወቅ ተገቢ መሆኑንም ያነሳሉ፡፡ ይህን ማድረግ ከተቻለ አሁን ያለውን የተዛነፈ እሳቤ ማስተካከል እና በልኩ እና በወርዱ ተገቢውን ክብር እንዲያገኝ ማድረግ ይቻላል ባይ ናቸው። «የሥዕል ሙያ ለዳቦ አይሆንም» የሚሉት ሠዓሊና መምህር አይናለም፤ ለሀገርና ለህዝብ ጠቃሚ የሆነውን ጥበብ ለሚያፈልቀው ሠዓሊ የሚገባውን መስጠት ይገባዋል የሚል የጸና እምነት አላቸው፡፡
ጥበብ ለሽያጭ ተብሎ የሚከወን ወይም የሚሰናዳ ባይሆንም የጥበበኛው ህያውነት የሚያረጋግጡ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸው ግድ እንደሆነ ይገልጻሉ። ‹‹አንድ ሠዓሊ ሥዕል መተዳደሪያና የገቢ ምንጩ ነውና ሕይወቱን ለመምራትና የተሻሉ ሥራዎችን ሠርቶ ለህዝብ ማቅረብ እንዲችል ቀድሞ ያቀረባቸው ሥራዎቹ ሊሸጡለትና የድካሙን ያህል ሊያገኝበት ይገባል›› የሚሉት ምክትል ፕሬዚዳንቷ፤ ሠዓሊው አንድ የተዋጣለት ሥራ ሠርቶ ለማጠናቀቅ ስት ወርና ከዚያ በላይ እንደሚወስድበት ያነሳሉ፡፡ ስዕሉን ለመስራት የወሰደበትን ጊዜ፣ ለስዕል ስራው ያወጣውን ወጪና ሥዕሉን ለመሥራት የተጠቀመበት እውቀት፣ ሀሳብና ክህሎቱን ተጠቅሞ ለህዝብ ያቀረበውን ሥራ ጥረቱን በሚመጥን መልኩ ገዢ ካላገኘ ሌላ ፈጠራ የታከለበት የነጠረ ሥራ ለመሥራት አቅምና ሞራል እንደማይኖረው ነው የሚያስረዱት፡፡
ማህበረሰቡ በሚዘጋጁ የሥዕል አውደ ርዕዮች ላይ ተሳትፎ የማድረግ ልምዱ ቢዳብር፣ ለሠዓሊው የሥዕል ማሳያ ቦታዎች ቢመቻችለት፣ ሠዓሊው ለሥዕል ሥራው የሚጠቀምባቸው መሳሪያዎች ቀረጥ ቢቀንስና ለዘርፉ መነቃቃት አሉታዊ ሚና ይጫወታል የሚለው ፍሬ ነገር በሙያው ውስጥ ያሉ ሠዓሊያን ሃሳብ ነው፡፡ በባለሙያዎቹ ለሥዕል ጥበብ ማበብ እንደ መፍትሄ ከተቀመጡት ውስጥ አንዱ ዘርፉን ከቱሪዝም ጋር ማገናኘትን ሲሆን፤ ቱሪዝም ከስነ ጥበብ ጋር የጠበቀ ቁርኝት አለው፡፡ ሥዕል ደግሞ የቱሪስት መስህቦችን በማስተዋወቅ ረገድ የላቀ ድርሻ አለው፡፡ ሀገራችን በቱሪዝም ሀብት የታደለች መሆኗ ደግሞ ለዚህ ምቹ ያደርገዋል፡፡ እናም የቱሪስት መዳራሻ ስፍራዎች ላይ የተለያዩ ደረጃቸው የጠበቁ የስዕል ጋለሪዎች ቢመቻቹና ሠዓሊው ሥራዎቹን ቢያቀርብ ለሀገር የውጭ ምንዛሪ ምንጭም መሆን ይችላል፡፡ ሠዓሊ፣ የሥዕልና የግራፊክስ ዲዛይን መምህር የሆኑት ወይዘሮ ሩት አድማሱ የሌሎች ሀገሮችተሞክሮ ልምድ ቢወሰድ መፍትሄ ያመጣል ይላሉ።
ለዚህም የጀርመንዋ ከተማ በርሊን እና የቻይናዋ ቤጂንግ ማሳያ አድርገው ያነሳሉ፡፡ ከተሞቹ የጥንት መንደሮቻቸውን ለይተው ለኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በመስጠት ባለሙያዎች ቅርሶችን እየጠበቁና እየተንከባከቡ ይገለገሉባቸዋል፡፡ አገራቱ የጥንት መንደሮችና ታሪካዊ ቦታዎች የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን በማልማት ለቱሪዝም ዘርፍ እድገትና ለገቢ ምንጭነት ማዋል እንደቻሉ ይጠቁማሉ፡፡ ይህንን ተሞክሮ ወደ ሀገር ቤት በመመለስ ዘርፉንና ቱሪዝሙን በማጠናከር የሠዓሊያንና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ህልም ማሳካት እንደሚያስችልም ያስረዳሉ፡፡ የሥዕል ጥበብ አገራዊ ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ ይህን ትልቅ አቅም በተገቢው ለመጠቀም ደግሞ በዘርፉ የተነሱ ዋና ዋና ችግሮችን በመለየት መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል፡፡ አገርና ህዝብን የመቀየር፤ ታሪክና ማንነትን የማሳየት ትልቅ አቅም ላለው የሥዕል ጥበብ እድገት ሊሠራ ይገባል የሠዓሊያኑ መልዕክት ነው። ሰላም!
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2011
ተገኝ ብሩ