ስድስተኛው አገራዊ ምርጫን ተከትሎ ከአንድ መቶ በላይ ፓርቲዎች ተመዝግበው ነበር። ይሁንና በተለያዩ ምክንያቶች ወደ 47 ወርደዋል። ከነዚህም ውስጥ አንዳንዶቹ ፓርቲዎች መስፈርትን ባለማሟላታቸው ከውድድሩ የወጡ ሲሆን ከፊሎቹ ደግሞ በራሳቸው ምክንያት ራሳቸውን ከምርጫው ያገለሉ ናቸው። በዚህም በኦሮሚያ ክልል ከገዢው ፓርቲ ውጪ አሁንም በተፎካካሪነት የቆየው የኦሮሞ ነጻነት ንቅናቄ /ኦነን/ ፓርቲ ይገኛል። ለመሆኑ ይህ ፓርቲ በተለይ ለክልሉ ህዝብ ምን አማራጭ ይዞ ቀረበ፤ ከሌሎቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎችስ ምን የተለየ ፖሊሲ ይዞ ቀረበ፤ እና ሌሎች መሰል ጥያቄዎችን በማንሳት ከፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ደረጀ በቀለ ጋር አጠር ያለ ቆይታን አድርገን የሰጡንን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ሊከናወን ጥቂት ጊዜ ቀርቶታል። ለዚህ ምርጫ የእናንተ ዝግጁነት ምን ይመስላል?
አቶ ደረጀ ፡- እንደጀመርነው አካባቢ ጥሩ እንቅስቃሴ ነበረን። ብዙ ተስፋዎችም ያሉበት እንደሆነ ተመልክተናል። ምክንያቱም ሁሉ ነገር በነጻነት የሚከወንበት ነበር። ከቀደሙት ምርጫዎችም የተሻሉ እድሎችን እንደሚያመጣ አሳምኖን ስንሰራበት ቆይተናል። አሁን ግን በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ጥቂት ቦታዎች ላይ ብቻ ተመራጮችን እንድናቀርብ ተገደናል። በተለይም በነበረው የጸጥታ ሁኔታና አንዳንድ የብልጽግና አመራሮች በሚያደርጉት ያልተገባ ተግባር አባሎችን ለማስመዝገብ እጅግ ከባድ ሆኗል። በስድስት ወረዳዎች ላይ ያቀረብናቸው እጩዎች እስከዛሬ ድረስ መመዝገብ አልቻሉም። ይህንንም ለምርጫ ቦርድ አሳውቀናል። ውሳኔውንም በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን።
ውድድራችን ኦሮሚያና አዲስ አበባን ይይዛል። በዚህም ነጻ የመወዳደር ሜዳ ያለው አዲስ አበባ ላይ ነው። ኦሮሚያ ላይ ከብልጽግና ውጪ ለመሳተፍ አስቸጋሪ ነው። ብዙ አፈና እየተከናወነ ይገኛል። ስለዚህም ያለነጻነት ምርጫውን ማከናወን አዳጋች ነው። ሆኖም ብልጽግና በምርጫ ቦርድ ውሳኔ ነገሮችን የሚያስተካክል ከሆነ የእኛ ዝግጁነት ጠንከር ያለ ነው። በኦሮሚያ ጠቅላላ አካባቢ ለፓርላማ 46 መቀመጫዎችን ለውድድሩ አመቻችተናል። በኛ በኩል 860 ሺህ አባላትም አሉን።
አዲስ ዘመን፡- የእናንተ ፓርቲ ከሌሎቹ ፓርቲዎች የሚለየው በምንድነው?
አቶ ደረጀ፡- በዋናነት የሚለየው ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ቦታ መስጠቱ ነው። ለዚህም ማሳያው ምንም እንኳን ተወዳዳሪነቱ በኦሮሚያና አዲስ አበባ ላይ ቢሆንም ከአባላቱ ጭምር ብሔር ብሔረሰቡን ያቀፈ ነው። አማራው፣ ጉራጌው ሌሎችንም ያቀፈና እየሰራ ያለም ነው። የኦሮሞ ነጻነት ቢልም የሁሉንም ዜጋ ነጻነት ለማስከበር የሚሰራ መሆኑ ለየት ያደርጋዋል። ሁሉን አቀፍ ፓርቲ እንጂ አግላይ አይደለም።
እኛ በምንሰራበት አገራዊ ቋንቋዎች ውስጥ እያንዳንዱ ብሔር እንዲካተትና እንዲሰራ የምንፈቅድ ነን። ስለዚህም ለኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ አገራዊ ጥቅም የሚቆም ማንኛውም ሰው ከመጣ ተቀብለን የምናስተናግድና በፕሮግራማችን የአንዱን ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ብሔር ብሔረሰብ አገራዊ ጥቅም ለማስከበር የምንለፋ ሆነን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡- የእናንተ ፓርቲ ምን የተለየ ነገር ይዞ ይመጣል?
አቶ ደረጀ፡– ከስሙ አንጻር ብቻ የታየ ከሆነ ለኦሮሞ ብቻ ነው። ሆኖም ፓርቲያችን ለሁሉም፣ በሁሉም የሚንቀሳቀስ አገራዊ እንደሆነ ነው የምናምነው። ስለዚህም ሥራውም ለሁሉም ነው። ሥራችን አንድነት ነው። ለዚህ ደግሞ ህብረት እንጂ አንድ ብሔርን ነጥሎ መያዙ ውጤታማ አያደርግም። በመሆኑም በጥምረት አገርን ለማሻገር እንሰራለን። ለዚህም በአብነት የማነሳው እኔ ፓርቲዬን ወክዬ ቅማንትንና ጎንደሬውን ለማስታረቅ ሄጃለሁ። እየሰራሁም ነው። እናም በፓርቲያችን አይመለከተንም የምንለው አገራዊ ጉዳይ የለም።
በአገራዊ አንድነት ጉዳይም እንዲሁ በጥልቀት በመሰባሰብ መስራት ግዴታችን እንደሆነ የምናምን ነው። እናም ፓርቲያችን አዲስ ተስፋ፤ በአንድነት ለአንዲት አገራችን ይዞ ይመጣል እንጂ ለኦሮሞ ብቻ አይሆንም። ስለዚህም የለውጡና ይዘን የምንመጣው ነገር መለኪያው ስም ሳይሆን ተግባራችን ይሆናል። አንድነት ሊፈጠርም ሊቆምም የሚችለው በግለሰብ ማንነት ውስጥ ነው። ግለሰቡ ማንነቱን አክብሮ ሌሎችን ለማክበር የሚሞክር ከሆነ ራሱንም ሌሎችንም ያቆማል። የአገሩን አንድነትም ያስከብራል። ብሔሩን ጭምር ሊያጎላና አርአያ ሊያደርገው ይችላል። እናም የእኛም ፓርቲ ይህንን አስቦ የሚሰራ ነው።
ማህበር የምንመሰርተው በሰውነት ስንለካካ ብቻ ነው። አንድነትም መምጣት የሚጀምረው የበላይና የበታች የሚለውን አስተሳሰብ ስንተው ይሆናል። አለዚያ ማንም እኩል ስለማይሆን ልዩነት ይሰፋል። ሰውነትም ዋጋ ያጣል። እናም ማህበራችን ጠንካራና ለአገር የሚበጅ ለማድረግ ሰውነት ልኬት አንድነት ብርታት መሆን አለበት። እያንዳንዱ ፓርቲ ቆሞ እንዲሄድ ከፈለገም ይህ ነገሩ ጎልቶ ሊወጣ ያስፈልጋል። እኛም ለኦሮሞም ሆነ ከዚያ ውጪ ላለው ብሔር ይዘን የምንመጣው ነገር የሰውን ዋጋ ማሳየት ይሆናል። እኔ ሰው ነኝ፤ ከዚያ ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ ከዚያ የተወለድኩበት አካባቢና ብሔሬ ኦሮሞ የሚለውን ልኬት አመጣለሁ። ይህ አስተሳሰብም በሁሉም ላይ ሆኖ እንዲቀጥል እንፈልጋለን ፤ እንሰራለንም። ሂደቱ እንዳይዛባና ልኬቱ ውጤት እንዲያገኝም እናደርጋለን።
አዲስ ዘመን፡- ኦነን ምን አይነት ፖሊሲን ይከተላል ?
አቶ ደረጀ፡- ነጻ ገበያ በአገሪቱ ውስጥ እንዲፈጠር ማድረግ የመጀመሪያው ፖሊሲያችን ነው። ይህ ሁኔታ አገርን የተሻሉ አማራጮችን እንድታገኝ ያደርጋታል። በተለይም ከብዙ አገራት እቃዎች መጥተው አገር ውስጥ በተሻለ ጥራትና ዋጋ እንዲቀርቡ ማድረግን ይህ አማራጭ ጥሩ እንደሆነ ፓርቲው ያምናል። ሻጭም ሆነ ሸማቹ ማህበረሰብ በደንብ የሚግባባበት እንደሚሆን ስለሚያስብም ይህንን ስርዓት መከተል የመጀመሪያው ሥራው ይሆናል።
ሌላው የመሬት አስተዳደሩን መቀየር ነው። መሬት የህዝብ ሲሆን፤ ይሸጥ ይለወጥ የሚለውን አሰራር ፖሊሲያችን አይቀበለውም። የሚሰራውም ይህንን ማስቀረት ላይ ነው። ምክንያቱም ገበሬው በራሱ ይዞ የተሻለውን ሁሉ እንዲያደርግበት እድል ይሰጠዋል። ሰፊ የእርሻ ቦታ ለእርሻ እንጂ ለሌላ መዋል እንደሌለበት ያምናል። ይህ ደግሞ ጉልበት ላለበት አገር የተሻለ የእድገት ሁኔታን እንደሚፈጥር ያምናል። ምክንያቱም ብዙው የኢትዮጵያ ህዝብ ኑሮው በግብርናው ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ዘመናዊውን ግብርና ተጠቅመው እድገታቸውን እንዲጨምሩ ማድረግ ነው ዋነኛ አላማው።
ገበሬው ምን ይፈልጋልም ዋና ፖሊሲያችን ነው። ለወንጪ፣ ለጎንደርና ወይም ለሌሎች ገበሬዎች አንድ አይነት ማዳበሪያ መላክ ሥራችን አይሆንም። ምክንያቱም ምን ይፈልጋሉ የሚለው በጥናት ይመለሳል። ማዳበሪያው ተፈጥሮአዊ ማድረግ የፈለገውን ማስገደድም አንፈልግም። ከዚያ ይልቅ የእርሱን የፈጠራ ውጤት ይዘን በዘመናዊ መንገድ የሚሰራበትን ሁኔታ በቅርበት እናመቻችለታለን እንጂ። እናም የአካባቢው ጥናት በዋናነት በፖሊሲው የሚመለስ ይሆናል። ይህንን እፈልጋለሁ እንጂ ይህ ያስፈልግሀል በፖሊሲያችን ተቀባይነት የለውም። ባህላዊው አሰራር ቅድሚያ አግኝቶ በዘመናዊው የሚዘወርበትን መንገድም የማመቻቸት ተግባር ነው የሚከወነው።
ከዚህ በተጨማሪ የትምህርት ሥርዓቱን ከላይ ወደታች ሳይሆን ከታች ወደላይ ጥሩ በሆነ አመራር ጥራት ያለው ትምህርት እንዲሰጥ ማድረግም ፖሊሲያችን ነው። ያልተማረ ሀይል መመራመርም፣ መስራትም አይችልም። አገርም መምራት እንዲሁ አይሆንለትም። እናም በዚህ ላይ ብዙ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ ፖሊሲም ቀርጸናል። በተለይም በአፍ መፍቻ እስከምን ድረስ በኢንተርናሽናሉ እስከምን ድረስ ይማሩ የሚለው ላይ ጥልቅ ሥራ የሚሰራይሆናል። አገራዊ ማንነቶችን ባካተተ መልኩም ነው ይህ ነገር እንዲተገበር ነው በፖሊሲው የተካተተው።
በጤና ፖሊሲያችንም ቢሆን ለውጥ በሚያመጣ መልኩ የተቀረጸ ነው። ባለሙያን ማምረትና ህዝብን መለማመጃ ማድረግ ሳይሆን በጥራት ተመርቆ ለህዝቡ እንዴት ተደራሽ ይሆናል፤ ትክክለኛ ህክምናስ እንዴት መስጠት አለበትና መሰል ጉዳዮችን በተጠና መልኩ ለማከናወን የሚሰራ ነው። ከአካባቢው የበሽታና ከህዝቡ አኗኗር አኳያ የተለየና ህክምናው ትኩረት እንዲሰጠውም የሚያደርግ ነው። የእስከዛሬው አሰራር ከላይ ወደ ታች ነው። የእኛ ግን ከጤና ኬላ ጀምረን የምንሰራበት ይሆናል። ህዝብን በቅርበት እያገኙ የሚሰራበትን አሰራር ነው በፖሊሲያችን ልንሰራ ያሰብነው። ጤና ኬላዎች በጠራ ባለሙያና ህክምና መሳሪያ ተሟልተው አገልግሎት መስጠት የፖሊሲያችን አንዱ አቅጣጫ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በኦሮሚያ ውስጥ ጠንከር ያሉ ፓርቲዎች ለውድድር አልቀረቡም የሚል ትችት ይሰነዘራል። ለመሆኑ የእናንተ ፓርቲ ጠንካራ ተፎካካሪ ነው ብላችሁ ታምናላችሁ? ምንስ ያህል ዝግጅት አድርጋችኋል?
አቶ ደረጀ፡- አዎ። ምክንያቱም እኛ በህዝብ ውስጥ ገብተናል። እስከዛሬ ከነበሩት ውስጥም ብቸኛ ሆነን ለመቆየታችን አደረጃጀታችን በራሱ የፈጠረው ስልት ነው። የእኛ ፓርቲ እኔ የዚህ ፓርቲ አባል ነኝ ብሎ በደረቱ ላይ የለጠፈው መታወቂያ የለም። ከዚያ ይልቅ በአንድ ለአምስት የተቀናጀና አሰራሩን የሚያስረዳ ዲስፕሊን ነው ሲከተል የቆየው። ሁሉም በተቀናጀበት ልክ ስራዎችን ይሰራል። ማንነታችንን ለሚፈለገው ህዝብ ያሳውቃል። ቤተሰብ ጭምር እየፈጠረ የሚሄድና የህዝብ መሆኑን ያሳየ ፓርቲም ነው።
ፓርቲያችን አመራርን በመተቸት አያምንም፤ በማስረዳት እንጂ። አሰራሩ ትክክል አለመሆኑን፣ በምን መንገድ መራመድ እንደሚገባ በሚገባ መጀመሪያ ካሳየ በኋላ ነው በሀሳብ መሞገትን የሚቀጥለው። ይህ ደግሞ የበለጠ ጠንካራነታችንን ለማሳየት የሚያግዝ ነው። በሀሳብ መብለጥ ከተግባርም በላይ ነው። ሀሳብ ሲያሸንፍ ብዙ ነገሮች መፍትሄ ያገኛሉ። እናም እንደተባለው ጠንካራ ፓርቲ ያለመኖሩ ምስጢር እኔ ብቻ ነኝ ተሰሚነት ሊኖረኝ የሚገባው ባዩ በመበራከቱ የተፈጠረ ነው። መተማመን እስካልሰፈነ ድረስ ደግሞ ይህ ሊመጣ አይችልም።
ሰዎችም ሆኑ ፓርቲዎች ፍላጎታቸው ሊከበርላቸው ይገባል። የእኛን ሀሳብ ብቻ መጫን ቅቡልነታችንን መቼም አያመጣውም። አሁን ያለው አሰራር ደግሞ ይህንን የሚያሳይ ነው። ተቀበል፤ ካልተቀበልክ ቦታህ ይወሰዳል፣ እዚህ አትኖርምና መሰል ማስፈራሪያዎች ይገጥሙታል። ለዚህ ሲልም ሳይወድ በግድ ይቀበላል። ይህ ደግሞ መቼም ታማኝ አያደርገንም። ጥንካሬያችንም የሚመጣው በስራ እንጂ በሀሳብ ብልጠት አይሆንም።
ምርጫም ሲታሰብ በዚህ መልኩ መሆን አለበት። ሰው የሚወደውን እንዳያደርግ ብዙ ገደቦች ተጥለዋል። የሰዎቹ ማንነት ሲታይ ከእንትና ፓርቲ ወገን ነው በማለት ሰበብ እየሰጡ የምርጫ ካርድ እንዳያወጡ ጭምር የተከለከሉም አሉ። ይህ ደግሞ ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዳይፈጠሩና እንዳይቀጥሉ እንቅፋት ይሆናል። በተመሳሳይ የሌላ ፓርቲ አባል ሆኖ ጥንካሬው ፓርቲውን እንዲሸነፍ የሚያደርገው ከሆነ በተለያዩ ነገሮች ተደልሎ ወደእነርሱ እንዲመጣም ያደርጋሉ። ይህም ቢሆን በፓርቲዎች መካከል መተማመን እንዳይኖርና ጠንካራ ፓርቲዎች እስከመጨረሻው ተፎካካሪ ሆነው እንዳይቀጥሉ ያደርጋል። ስለዚህም በኦሮሚያ ደረጃ ይህና መሰል ነገሮች የሚታዩ በመሆኑ ጥንካሬያችን ሊፈተን ይችል ይሆናል። ነገር ግን ጠንካራ ነን አይደለንም የሚለውን የሚወስነው ህዝብ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ቀደም የእናንተ ፓርቲ ፌደራሊስት ሀይሎች በሚል ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በመሆን ሲንቀሳቀስ እንደነበር ይታወቃል። አሁን ይህ እንቅስቃሴ ምን ላይ ደርሷል?
አቶ ደረጀ፡– ፌደራሊስት ሀይሎች ሲቋቋም ሰብሳቢ ነበርኩ። በዚህም ብዙ ሥራዎች ሲሰሩበት ቆይተዋል። ሆኖም ምርጫ ቦርድ በርከት ያሉ ፓርቲዎችን በመሰረዙ ምክንያት ሥራዎች ተስተጓጎሉ። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ መንግስት ጦርነት ከትግራይ ጋር ከማድረጉ በፊት እኛ የሰላም መንገድ እንመርጣለን ብለን በግልጽ ተነጋግረን እነርሱም ተነጥለው ለብቻቸው ወጥተዋል። እኛም በሰላም መንገድ ለብቻችን እንታገላለን ብለን ተስማምተን ነበር። ይሁን እንጂ ምርጫ ቦርድ ከዚያም ውስጥ አጣርቶ መስፈርቱን ያሟሉ ጥቂት ፓርቲዎችን ብቻ መርጦ እንዲቀጥሉ አደረገ። በዚህም ያለነው በጣም አናሳ ሆንን። በተወሰኑት እያስኬድን ቆይተን በፍርድ ቤት ያሸነፉትንንና ሀሳባቸው ቅቡልነት ያገኙትን የፌደራሊስት የፓርቲ መሪዎችን በማሰባሰብ እየሰራን እንገኛለን። በኦሮሚያ ብቻ ያሉ ውሳኔ ያገኙ ስድስት ፓርቲዎች ወደ ስብስቡ መጥተዋል።
አዲስ ዘመን፡- በመንግስት አወቃቀር የኦነን ሥርዓት ምን ይመስላል?
አቶ ደረጀ ፡- ፕሬዚዳንታዊ ነው። የአገር ሰላምንና አንድነትን ለማምጣት ከዚህ ስርዓት ውጪ ይሆናል የሚል እምነት የለንም። ምክንያቱም ይህ ሥርዓት የሥልጣን ክፍፍልን ያደርጋል። ፕሬዚዳንቱና አስፈጻሚው አካል የሚገናኙበትን እድል ይሰጣል። ፓርላማው ደግሞ ህግ ያወጣል። የሥራዎችን ውጤታማነት ለማየት ደግሞ ብዙ እድል ያለው ይህ መሆኑን ፓርቲው ያምናል። በዚያ ላይ ደካማ መንግስት እንዳይኖር በፕሬዚዳንቱ የሚመራው የአስፈጻሚው አካል ኢትዮጵያ ጠንካራ መንግስት እንዲኖራት ያደርጋልና አለመስማማቶች ቢኖሩ እንኳን ፈተና ውስጥ አይገባም።
ህዝቡን የረሳ ፓርላማ እንዳይኖርም ያደርጋል። በተለይ በቅርበት ፍትህ የማግኘት ሁኔታን በአጭር ጊዜ የሚያመቻች ነው። ተወካዮች ላሉበት ህዝብም የማገልገልና የማየት እድል የሚሰጥም ነው። ምክንያቱም መቀመጫቸውን ጭምር በህዝብ ውስጥ የሚያደርግ ነው። ከህዝቡ የራቀ ስልጣን ሳይሆን ወደ ህዝቡ የቀረበ ስልጣንም ይሰጣል። ስለሆነም አሁን አገሪቱ ካለችበት ችግር የሚያወጣው የትኛው ነው ቢባል ከዚህ ውጪ አማራጭ እንደሌለ ፓርቲያችን ያምናልና የሚከተለውም ይህንን ነው። በእርግጥ የትኛውም ሥርዓት ቢሆን ደካማ ጎኖች ይኖሩታል። ይህም ስርዓት የተወሰኑ ችግሮች አሉበት። ሆኖም ግን ካለው አሰራርና ሁኔታ አንጻር ለአገር የሚበጀው ፕሬዚዳንታዊ እንደሆነ አምነንበት እንከተለዋለን።
አዲስ ዘመን፡- በምርጫ ህግ ሁሉን አሳታፊ መሆን ግድ ነው። ከዚህ አኳያ ፓርቲያችሁ ሴቶችንና የአካል ጉዳተኞችን ምን ያህል አሳትፏል፤ ተሳትፏቸውስ በምን መልኩ ነው። ለይስሙላ የሆነባቸውም እንዳሉ ይታያልና ?
አቶ ደረጀ፡– ይህ ሁኔታ ከእኛ አንጻር ሲታይ ከ8መቶ 60 ሺህ አባሎቻችን 60 በመቶ የሚሆኑት ሴት ወጣቶች ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ በአመራርነት የተቀመጡት ከዋና ጸሐፊ ጀምሮ ቦታ ያገኙ ናቸው። ለውድድር ከቀረቡት ውስጥ ማለትም ከ46ቱ ውስጥ 18ቱን የያዙትም ሴቶች ናቸው። ስለዚህም ፓርቲያችን የተማረውንና ሴቶችን በማሳተፍ መልኩ የተሸለ አማራጭ የሰጠና የሚሰራ ነው። እንደውም ከሌሎቹ አባላት መስራት የሚችሉና ሀሳቡን ሙሉ ለሙሉ የተቀበሉትም እነርሱ መሆናቸውን ያየንበት ፓርቲ ሆነናል።
የአካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ግን እስከ አሁን ፓርቲያችንን ለመቀላቀል የመጣ የለም። እንዲሳተፉልን ብዙ ጥረናል። ሆኖም አልተሳካልንም።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት የኑሮ ውድነቱ ንሯል። ከዚህ አንጻር የእናንተ ፓርቲ ምን አስቧል? ምንስ አይነት ስትራቴጂ ይከተላል?
አቶ ደረጀ፡- በአገሪቱ ላይ ኑሮውና የህዝብ ብዛቱ አልተጣጣመም። ለዚህ ደግሞ መሰረቱ ሥራአጥነት መስፋፋቱ ነው። የሥራ እድል መፍጠር ማለት መንገድ ላይ ሻይ እንዲሸጡ ማድረግ ብቻ አይደለም። በአንድ ብርጭቆ ሻይ ትርፍ ምሳ መብላት ይቻላል ወይ የሚለው መጠናትና መመለስ አለበት። ያ ካልሆነ ግን ሥራው ወዲህ ምግቡ ወዲያ ይሆንና የኑሮ ውድነቱ እየገዘፈ የማይበላው ይበዛል። ስለሆነም ለተመጣጣኝ ሥራ ተመጣጣኝ ክፍያ የሚኖርበትን ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ግብርናው ላይ የሚሳተፈውን ሰው ማብዛት፤ በራሱ ሰርቶ ትርፋማ የሚሆንበትን መንገድ መቀየስና ኢንዱስትሪዎችን በአገር ውስጥ ማስፋፋትና ተጠቃሚነትን ማገልበት ይገባል።
በኢትዮጵያ ደረጃ አንድ ሰራተኛ የሚባል ሰው በትንሹ በአማካኝ አራት ሰውን ይመግባል። ስለዚህም የማይሰራ ሦስት ሰው አለ ማለት ነው። ያንን ለመመገብ ደግሞ የተሻለ የሥራ አማራጭ ግድ ነው። በዚህም በአገራችን አቅም ደረጃ ለመስራትና ይህንን ክፍተት ሊሞላ በሚችል መልኩ ለመንቀሳቀስ ስትራቴጂ ነድፈናል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ግብርናው ላይ፣ የኢንዱስትሪ ዘርፉ፣ በኮንስትራክሽኑና ሌሎች ተያያዥ የሥራ እድል ማስገኛ መንገዶች ላይ መስራት በዋናነት ትኩረታችን ነው። የቦታ የለኝም ጥያቄን መመለስም ለሥራ አማራጩ ትልቅ መፍትሄ የሚሰጥ ስለሆነ ከተማን ሳይሆን ገጠሩንም ጭምር መጠቀም ላይ መስራት ስትራቴጂአችን ነው። የተማረውንና ሥራውን ማመጣጠንም ሌላው ስትራቴጂአችን ነው። ለዚህ ደግሞ የተማረውን የሚሸከም ኢኮኖሚ መገንባት የግድ ይላል። ስለዚህም ይህ ዋነኛ ትኩረታችን ይሆናል።
አዲስ ዘመን።- አገራዊ ምርጫውን ተከትሎ እያጋጠማችሁ ያለ ችግር ካለ ቢያነሱልን?
አቶ ደረጄ፡– ብዙ ችግሮች አሉ። ይሁንና እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ተወዳዳሪነታቸውን የሚደርስብን እንግልት ግን በጣም ይበዛል። ብዙ አባሎቻችን እንዳይመዘገቡ ከማድረግ በተጨማሪ ሀብት ንብረታቸው ጭምር ተወስዶባቸው ለህይወታቸው ፈርተው አዲስ አበባ ይገኛሉ። ለውድድር የሚሆኑ ምቹ ሁኔታዎችም እያገኙ ነው ለማለት ያስቸግራል። በአዲስ አበባ የሚወዳደሩት ብቻ ናቸው በአሁኑ ሰዓት ነጻ እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉት። ስለዚህም ገዢው ፓርቲና ምርጫ ቦርድ ይህንን ማመቻቸት ካልቻሉ አሁንም ችግሮቹ እንደሚቀጥሉ ይሰማኛል። ነገር ግን ገዢው ፓርቲ እንደሚናገረው ከሆነ ይህንን የሚያደርጉ አካላትን ተጠያቂ በማድረግ ወደነበርንበት ከመለሰ ጥሩ ሁኔታ ይኖረናል። ምርጫ ቦርድም እንዲሁ እንዲፈታልን ያቀረብናቸው አቤቱታዎች አሉና ምላሹን በአፋጣኝ ከሰጠን ብቸኝነታችንን በጠንካራ ሥራና ተወዳዳሪነት የምናስቀጥል ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የውጪ ሀይሎች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ሲገቡ ይታያል። ለመሆኑ ይህንን ጉዳይ እንዴት ያዩታል?
አቶ ደረጄ፡– እኔ ይህንን አገላለጽ በተለየ መልኩ አየዋለሁ። ምክንያቱም ጣልቃ ገቡ ሳይሆን መባል ያለበት የአንተን ቡኮ እኔ ጓዳህ ገብቼ ላቡካልህ እንደማለት ነው። ካለበለዚያ አንተ ማቡካት አትችልም ነው። በርህ የሚከፈተው በእኔ ብቻ ነው የሚል ነው ዋና አላማቸው ። ይህ ደግሞ ለእኛ ኢትዮጵያውያን መቼም የሚዋጥ አይደለም። ባያውቁን ነው እንጂ እንደእነርሱ አይነቶችን ተጋፊዎች መግበንም አሳፍረንም እናውቃለን። መቼም ለማንም ሀሳብ ስንገዛ ታይቶ አይታወቅም። ሀሳቡም ሀይሉም ያለን ህዝቦች ነን። ምንም እንኳን በሀሳብ ልዩነት እየተጋጨን ቢሆንም በአገር ለመጣ ግን እጅ እንደማንሰጥ የጣሊያኑን የሁለት ጊዜ ጦርነት ማንሳት ብቻ በቂ ነው።
አገር ለማንም በምንም አትሸጥም። ስልጣንና ጥቅምም የሚለውጣት አይደለችም። ይህ ደግሞ ከደማችን የተቀመጠና ዛሬም ድረስ የሚዘዋወር ነው። ስለዚህ ለእነርሱ ያደሩ ሆዳሞችም ቢሆኑ መቼም አገራችንን ለመንካት ባይሞክሩ ነው የሚሻላቸው። ይህንን አልፈው ከመጡ ግን የቀረው ይቀራል እንጂ እንደ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን እንደግለሰብም የሚምራቸው ይኖራል ብዬ አላስብም። ማንም በእኛ ላይ የበላይ የመሆን መብት የለውም። ማንም ሊደነፋብንም አይችልም። ማንም የሌላ አገር ተገዢ መሆንን አይመኝም። ስለሆነም ለአገር የሚከፈለው መስዋዕትነት ቀላል አይሆንምና ይህንን የሚያደርጉ አካላትን ልብ በሉ ማለት እፈልጋለሁ።
አሁን ያለው ጫና ለምን ትለማላችሁ ባይነት ያመጣው ነው። መልማት ደግሞ ራሳቸው በአወጡት ህግ ጭምር መብት ነው። እናም መብት እየጣሱ ህግ አላከበራችሁም የሚለው የሚያስቅና ያልታየ ጉዳይ ነው። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ገዢውን ፓርቲ ተቃውሜ የቆምኩት አገሬን ሰላም ለማድረግ እንጂ አገሬን ለሌላ አሳልፌ ለመስጠት አይደለም። ገዚው ፓርቲም ከተፎካካሪዎች ጋር የሚፋለመው የተሻለ አማራጭ ለአገሬ ይዤ መጥቻለሁ ሲል ነው። በዚህ መካከል ደግሞ የርዕዮት አለም ልዩነት እንጂ የአገር ጥቅም ድርድር ውስጥ አይገባም። ሁሉም ፓርቲ ለአገር መቆም ግዴታው ነው። አለዚያ አገር በሌለበት ማንን ሊያስተዳድር ስልጣን ይይዛል። ራሱም ላይኖር ይችላል። ስለሆነም የአገር ጉዳይ እንደ ፓርቲም ሆነ እንደግለሰብ መተኪያ የሌለው ነው። ጦርነት ካስፈለገም ራስን መስዋዕት የማድረግ ጉዳይ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያየ አካሄድ ህዝቡን እንዳይተማመንና የውጪ ሀይሎች ጣልቃ ገብነት እንዲንሰራፋ አድርጓል ይባላል፤ እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ ደረጄ፡- አንዳንድ ክስተቶች ሲታዩ እውነትነት እንዳለው ያሳያል። ለአብነት የፖለቲካ ፓርቲዎች አገር አቀፍ እንዳይሆኑ የተዘራው መጥፎ ዘር አላስቻለም። ስለዚህም በአካባቢያቸው ብቻ እንዲወሰኑ አድርጓቸዋል። ከዚያ ባሻገር ሊካፈልህ ነው። ግደለው የሚለውም ስብከት የፓርቲዎች አባላት በዚያ ሄደው ለአገራቸው እንዳይሰሩም ገድቧቸዋል። ህዝብም የሚማገደው በዚህ የተነሳ ነው። ይህ ግን የትክክለኛው ፖለቲካ አስተሳሰብ አይደለም። ስልጣን ህዝብን በመማገድ ሳይሆን በፍላጎት የሚሰጥ መሆን አለበት። ህዝብ ፈልጎ ያስቀመጠው ካልፈለገው የሚያወርደውም ይሆናል። ነገር ግን በጉልበትና እርሱን በመማገድ የገባ ከሆነ መቼም አይለቅም።
ለአገሩ መልካም ፍሬ ለማስገኘትም ይቸገራል። ምክንያቱም ሀይሉ ህዝቡ ሳይሆን ጉልበቱና ስልጣኑ ነው። ስለዚህም አሁን ለአገር የሚያስፈልገው ጉልበት ሳይሆን በሀሳብና በፖሊሲ ህዝብን ማሸነፍ ነው። ህግ እንጂ ጦርነት ወይም ግጭት ማንንም አይረታም። ህግና ህግን መሰረት አድርጎ መስራት ከምንም በላይ ያስፈልጋል። ህወሓት ከእኛ ሌላ አገሪቱን የሚገዛ ሀይል መኖር የለበትም። ይህ ከሆነ ግን አገሪቱ ለምን አትበታተንም ብለው የሚሰሩ ናቸው። ይህ አስተሳሰብ ግን አልበጃቸውም ራሳቸውን በታተናቸው እንጂ። ስለሆነም አሁንም አገር ስትኖር ፤ ህዝብ ሲወደን ነውና ሁሉ ነገራችን ሰላም የሚሆነው እያንዳንዳችን ይህንን ማድረግ ላይ መስራት ይገባናል።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለዎት ?
አቶ ደረጄ፡- አገርን የሚመሩ ወጣት አመራሮች ዛሬ ያስፈልጉናል። እናም በእያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ያሉ ነባር አካላት በአዲሱ ሊተኩ ይገባል። አገር አሰራርን የሚያሻሽል ትውልድ ያስፈልጋታል። ቢያንስ የቆዩት መልቀቅ እንኳን ባይችሉ አስተሳሰባቸውን በአዲሱ መቀየር አለባቸው። እይታቸውም ከዘመኑ ጋር የተዋሀደ መሆን አለበት። አዲስ ዓይንና እውቀት ማምጣት ላይ እንጂ በነበርኩበት ልጓዝ መቼም አያራምድም። ስለዚህም ዘመኑን የዋጀ ተግባር ስንቃቸው መሆን ያስፈልገዋል።
ነባርና በጥላቻ የተሞሉ ካድሬዎችም ለአገራቸው ህልውና ሲሉ ቆም ብለው በማሰብ ሁኔታዎችን ማሻሻል ይገባቸዋል። ህዝብን ማረጋጋት የሚችሉ ካድሬዎች እንዲፈጠሩም እድል ይስጡ። በውጪ ጣልቃ ገብነት ዙሪያ ህዝቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም መንግስት በአንድነት መሰለፍ አለበት። በተለይ መንግስት አንድ እርምጃ ወደ ህዝቡ መጠጋትና ምን እናድርግ ማለት መጀመር ይኖርበታል። ከህዝብ ዘንድ የሚመጣ ሀይል መፍትሄ ሰጪ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም። ህዝብም ቢሆን የተዘራበትን ጥላቻ አቁሞ ለአገሩ መረባረብና አገሩን ማቆም ይኖርበታል። ከዚያ በኋላ ብዙ ነገሮችን መለወጥ እንደሚችል ከእርሱ የተለየ የሚያውቅ የለም።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን።
አቲ ደረጄ ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2013