በምዕራቡ የሀገራችን አካባቢ በመገንባት ላይ የሚገኘው የአርጆ ዴዴሳ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ሀገሪቱ አለኝ ከምትላቸው የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች አንዱ ነው። ፕሮጀክቱ በዓመት ሁለት ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ በማጠራቀም እስከ 80 ሺህ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም አለው።
በ2003 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞለት የነበረው የአርጆ ዴዴሳ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት 50 ሜትር ከፍታ እና 502 ሜትር ርዝመት ያለው ነው። ለግድቡ ግንባታ የሚውል ሁለት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ከመንግሥት ተመድቦለት ነው ግንባታው የተጀመረው።
ሆኖም የግድቡ ግንባታ በእቅዱ መሰረት ሊሄድ አልቻለም። በሀገሪቱ ውስጥ እጅግ ከተጓተቱ ሜጋ ፕሮጀክቶች አንዱ ሊሆን ችሏል። ከመስኖ ልማት ኮሚሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው እስከ መጋቢት 30/2013 ዓ.ም የዋናው ግድብ ግንባታ የተጠናቀቀ ሲሆን የትርፍ ውሃ ማስወጫና ኮርቻ ግድብ ግንባታ ገና በጅምር ሥራ ላይ ሲሆን በአማካይ 82 በመቶ ላይ ይገኛል።
የመስኖ ልማት ኮሚሽን የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ እንደሚሉት፤ ፕሮጀክቱን በሶስት ዓመታት ለማጠናቀቅ ነው እቅድ ተይዞ የነበረው። በሶስት ዓመት ማጠናቀቅ እጅግ ከባድ እንደሆነ ቢታወቅም በኮንትራክተሮች ጫና በማሳደር በአፋጣኝ እንዲያጠናቀቁ ለማድረግ አጭር ጊዜ መቀመጡን አብራርተዋል። ሆኖም ጫና ለማሳደር የታሰበው አልተሳካም።
ከሀገራዊ ሪፎርም በፊት በነበረው ጊዜ ፕሮጀክቱን በተያዘለት በሶስት ዓመት ውስጥ ማጠናቀቅ ባይቻል እንኳ ጥቂት ዓመታትን ዘግይቶ ለማጠናቀቅ ጥረት የተደረገ ቢሆንም ሳይሳካ ቆይቷል። ከለውጡ በኋላም ጥረት ሲደረግ ነበር፡ ከለውጡ በኋላ ባለው ጊዜ የአርጆ ዴዴሳን ጨምሮ የሌሎች የተጓተቱ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜ እንዳይጠናቀቅ ምክንያት የሆኑ ችግሮችን የመለየት ሥራ ተሠርቷል።
የአርጆ ዴዴሳ ፕሮጀክትን ካጋጠሙት እና አሁንም ችግር ሆኖ ከቀጠሉ ተግዳሮቶች መካከል የወሰን ማስከበር ከባዱ እና ዋነኛው ችግር መሆኑን ያብራሩት አቶ ብዙነህ፤
በክልል ደረጃ ካሉ ከፍተኛ አመራሮችና ከዞን አመራሮች ጋር ውይይት በማካሄድ በክልል ደረጃ መሰራት ያለበትን ሥራ ክልሎች መሥራት እንዳለባቸው፣ በፌዴራል ደረጃ መሰራት ያለበትን የፌዴራል መንግሥት እንዲሰራ በመገባደድ ላይ በጀት ዓመት የተለያዩ ውይይቶች ተደርገዋል። ማን ምን ማከናወን አለበት በሚለው ላይ መግባባት ተደርሷል።
እንደ አቶ ብዙነህ ማብራሪያ፤ ችግሩ መፈታት እንዳለበት መግባባት ላይ ከተደረሰ በኋላ ጥሩ እንቅስቃሴዎች ቢኖሩም አሁንም ችግሩ ሙሉ በሙሉ ሊቀረፍ አልተቻለም። ግድቡ ውሃ በሚይዝበት ቦታ ላይ የሚኖሩ ነዋሪዎች አሁንም አልተነሱም። ነዋሪዎቹ እያሉ የትርፍ ውሃ ማስወጫ እና የኮርቻ ግድብ መገንባት ከባድ ሆኗል። የኮርቻ ግድብ ለመስራት ውሃው የሚተኛበት 12 ሺህ ሄክታር ማለትም ከ3500 እስከ 4000 የሚደርሱ አባዎራዎች ናቸው በቦታው የሚገኙት።
እነዚህ አባዎራዎች የሚሰፍሩበት ቦታ በሀሳብ ደረጃ ስምምነት የተደረሰበት ቦታ መዘጋጀቱን ያብራሩት አቶ ብዙነህ፤ ያንን ቦታ በህጋዊ መንገድ የመስኖ ልማት ኮሚሽን ተረክቦ፤ በአካባቢው መሰራት ያለባቸውን ማህበራዊ ተቋማት የመስራት ሃላፊነት እንዳለበት አብራርተዋል። ኮሚሽኑ ሃላፊነቱን ለመወጣት ማህበራዊ ተቋማትን የመገንባት ተግባሩን በማከናወን ላይ ነው። የማህበራዊ ተቋማት ግንባታው እንደተጠናቀቀ ነዋሪዎቹ ቦታውን እንደሚለቁ አብራርተዋል። በ2014 በጀት ዓመት ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም አቶ ብዙነህ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ከትርፍ ውሃ ማስወጫ ጋር ተያይዞ የዲዛይን ችግር ስለነበረበት ችግሩን ለመቅረፍ የዲዛይን ለውጥ ማድረግ የግድ እንደነበር ያብራሩት አቶ ብዙነህ፤ የዲዛይን ለውጥ የማድረግ ሥራ ደግሞ ጊዜ የሚፈልግ በመሆኑ ፕሮጀክቱ እንዲጓተት የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል ሲሉ ያብራራሉ ።
የግንባታውን ዘርፍ እየተፈታተነ ያለው የሲሚንቶ እጥረት የአርጆ ዴዴሳ ፕሮጀክትን ለማጠናቀቅ እየተደረገ ባለው ጥረት ላይ ጥላ አጥልቷል የሚሉት አቶ ብዙነህ፤ ችግሩን ለመቅረፍ የፋብሪካውን ግንባታ የሚያካሂዱ አካላት በቀጥታ ከሲሚንቶ ፋብሪካዎች እንዲገዙ በማድረግ ችግሩን በመጠኑ ማቃለል ቢቻልም፤ ሙሉ በሙሉ አልተፈታም።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2013