ደብረ ብርሃን ከተማ አሁን አሁን የኢንዱስትሪዎች መፍለቂያ እየሆነች ነው። በኢንቨስትመንቱ የውጭና የሀገር ውስጥ ባለ ሀብቶችን በከፍተኛ ሁኔታ ቀልብ እየሳበችም ትገኛለች። ለዚህ አብነት ካስፈለገ ዳሽንና ሐበሻ ቢራን ጨምሮ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎችን መጥቀስ ይቻላል። በውጭ ባለ ሀብቶች የሚንቀሳቀሱ ትልልቅ ካፒታል ያላቸው ፋብሪካዎች በዚህችው ከተማ ውስጥ መገኘታቸው የተፈላጊነቷን መጠን ማሳያ ነው። በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፉም ወተት ማቀነባበርያ ፋብሪካዎቿን ብቻ ማንሳት በቂ ነው።
ደብረ ብርሃን‹‹ የፀሐይ›› ከተማ እየተባለች ትጠራለች። በ1446 ዓ.ም በአፄ ዘርያቆብ የተቆረቆረች ዕድሜ ጠገብ ከተማ በመሆኗ የከተሞች አያት እየተባለች እስከ መጠራት ደርሳለች። ከተማዋ 9 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ 41 ሰሜን ኬክሮስ እንዲሁም 39 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ 32 ምሥራቅ ኬንትሮስ ላይ ትገኛለች። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ቀድሞ 120 ሺህ የነበረው ነዋሪዋ ዘንድሮ 400 ሺህ ደርሷል። የአየር ንብረቷ ለጤና ተስማሚና ረጅም ዕድሜ መኖር የሚያስችል ደጋማ መሆኑ ይነገርለታል ።
የሰሜኑ የሀገራችን ክፍል መውጫ የሆነችው ደብረ ብርሃን ለአዲስ አበባና ለአማራ ክልል እህት ከተሞቿ ካላት ቅርበት አንፃርም ከአዳማ ውጭ ካሉ ከሌሎች የሀገራችን ከተሞች በተሻለ ቅርበት ላይ ነው ያለችው። ከሀገራችን ዋና መዲና አዲስ አበባ 130 ኪሎ ሜትር ላይ ትገኛለች። ማህደሯ ሲገለጥ ታሪኳም ሆነ ባህሏና ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር በእጅጉ የተያያዘ ነው። የቀደምት ታሪክ፣ ባህሎች እና ስልጣኔ መሰረት መሆኗ ይነገራል ። ለ300 ዓመት የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ጭምር ሆና በማገልገል ትታወቃለች። በሀገር መሪነቱም፣ በዕምነቱም ፣ በኪነ ጥበቡም ትላልቅ ሰዎች መፍለቂያም ናት።
ከሀገሪቱ የተለያዩ አቅጣጫ የመጣውን እንግዳ ተቀብላ የምታስተናግ ልዩና ውብ ከተማ ናት። በተለይም ከአጎራባችዋ ኦሮሚያና አዲስ አበባ ቅርበቷን መርጠው የሚጎበኟት ብዙ ናቸው ። ከዚህም በመነሳት ይመስላል አዲስ አቤዎች ‹‹ የንጹህ አየር ማስተንፈሻችን ናት›› ይሏታል።
የከተማዋ ነዋሪና በልብስ ስፌት ሥራ የተሰማራው ወጣት ጌራ ደምለው በተለይ ከሰው ብዛት የተነሳ የሥራ ተደራሽ ሆነው ኑሯቸውን ማሸነፍ ያልቻሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ‹እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል› እያሉ በመምጣት ያለ ምንም ችግር የሚሰሩባት፣ የሚኖሩባትና ሕይወታቸውን የሚለወጡባት ከተማ መሆኗንም አጫውቶናል።
‹‹ባለፉት ዓመታት በብዙ የሀገራችን ከተሞች ግጭት ሲከሰት፣ ንብረት ሲወድምና ብዙ ጥፋቶች ሲከሰቱ ደብረ ብርሃን ላይ ሰላም ነበር›› ያሉን ደግሞ ሌላዋ ነዋሪ ወይዘሮ ሺማጫሽ ጣሌ ናቸው። እንደ ወይዘሮዋ የብዙ የውጭና የሀገር ውስጥ ታላላቅ አልሚዎችን ቀልብ የመሳቧ ምስጢርም ከዚሁ የመነጨ ነው። ገቢዋም ቀላል የማይባል ዳጎስ ያለ ነው። ይሄ ሁሌ ጥሪቷ በዚህ ወር የክልሉን ዋና ከተማ ባህር ዳርን ጨምሮ ሰልፏን ከነጎንደርና ደሴ ከተሞች ጋር ለማስተካከል አብቅቷታል። ወደ ትልቅ ከተማ ‹‹ሪጅኦ ፓሊታን›› ከተማነት አሸጋግሯታል። ይሄ ሁኔታ ለነዋሪ የሚሰጠው ዕድል ብዙ ነው። በተለይ ለረጅም ጊዜ የነበረውን የነዋሪዎቿን ጥያቄ ለመመለስ ያስችላል። የአገልግሎት ተደራሽነት ያሉ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በመፍታት ዓይነተኛ መፍትሄ ያመጣል ተብሎ ይገምታል። መንገድን ጨምሮ ሌሎች የመሰረተ ልማት ችግሮችን በመፍታት ትልቅ አቅም ይፈጥራል የሚል ዕምነት አለ።
የአማራ ክልል ከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የአቶ በሰላም ይመኑ ሀሳብም ይሄን የነዋሪዎቹን አስተያየት የሚያጠናክር ነው። እንደ አቶ በሰላም ከተሞች ከአንድ ወደ ሌላ ደረጃ ሽግግር በሚያደርጉበት ጊዜ ለነዋሪዎቻቸው የሚሰጧቸው ብዙ ጥቅሞች አሉ። ከባለ ሁለት እርከን አስተዳደር ወደ ሶስት እርከን አስተዳደር የሚያድጉበት ሁኔታ አለ። በመሆኑም ሽግግሩ በሚያስተዳድሩት ከተማ ውስጥ ያልተማከለ አስተዳደር ስርዓት ተዘርግቶ እንዲተገበር ይረዳል። ለምሳሌ የትልቅነት ‹‹ሪጅኦ ፓሊታን›› ደረጃ ያገኘ ከተማ አስተዳደር ከዚህ ቀደም ይሰጠው የነበረውን የአንድ ማዕከል አገልግሎት ወደ ተለያዩ ዘርፎችና አስተዳደር እርከኖች የሚያፈስበት ሁኔታ አለ። ለአብነትም አንድ ሪጅኦ ፓሊታን ከተማ አስተዳደር ክፍለ ከተማ ይኖረዋል። በክፍለ ከተማው ውስጥም ቀበሌ አስተዳደር አለ። ከዚህ ቀደም አንድ ከተማ አስተዳደር የነበረው ወደ ትልቅ ከተማነት በሚያድግበት ጊዜ ጽሕፈት ቤት የነበሩት ወደ መምሪያ ደረጃ ይሸጋገራሉ። በከተማ አስተዳደር ደረጃ አዳዲስ ጽሕፈት ቤቶች ይከፈታሉ። ክፍለ ከተማ የሚባል አዲስ መዋቅር ይፈጠራል። በዚህ መዋቅር ስርም የተለያዩ ተቋሞች ይኖራሉ።
ክፍለ ከተማ ከራሱ ስልጣን ቆርሶ ለቀበሌ አስተዳደር ይሰጣል። ቀበሌ አስተደደር በተሰጠው ስልጣን መሰረት የሚያከናውናቸውን ተግባሮች ያወርዳል። በዚህ ጊዜ የመንግስት አስተዳደር ለሕዝብ ተደራሽ የሚሆንበት ስርዓት ይፈጠራል። ያልተማከለ አስተዳደርን ተግባራዊ በማድረግ ከተማ አስተዳደሮች የሚያስተዳድሩትን ሕዝብ አገልግሎት ፍትሃዊና ግልጽ በሆነ መንገድ ይሰጣሉ። ይሄኔም በከተማው ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ይቀረፋሉ።
የደብር ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ደስታ አራጌ ሀሳብም የአቶ በሰላምን ሀሳብ ያጠናክረሉ። ከንቲባው ሽግግሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት አስተዋፆ ማድረጉን በማሳያ አስደግፈው ይጠቅሳሉ። እንደ ከንቲባ ደስታው ከተማዋ ቀደም ብሎ በነበረችበት አግባብ ሁሉንም የማስተናገድ አቅም ነበራት። ፋብሪካዎች እየጨመሩ የቆዳ ስፋቷ እየበዛና የሕዝቧ ቁጥር ከፍ እያለ ሲመጣ ግን መዋቅሯ አረጀ። ለ10 ዓመት የታቀደው በሦስት ዓመት፣ ለሁለት ዓመት የታቀደው በአንድ ዓመት ቢጠናቀቅም ለመዋቅሯ አቅም ሊፈጥር አልቻለም። ሁሉም ነዋሪዎች ለጥያቂያቸው ምላሽ ለማግኘት የግድ ከንቲባውንና የከተማ አስተዳደሩን ማግኘት ነበረባቸው። እነዚህ አመራሮች ደግሞ ለሁሉም ጥያቄ በአንድ ጊዜ ምላሽ ለመስጠትና ለመወሰን ጊዜ እያነሳቸው ጉዳዮች እያደሩ መጡ። ልማቱንም ሆነ ነዋሪዋን የማስተናገድ አቅሟ ተዳከመ። የሕዝብ አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ ተሳናት። የልማት ፋላጎቶቿንም መመለስ አልቻለችም። የመልካም አስተዳደር ችግሮቿ ተበራከቱ። በዚህ የተነሳ ነዋሪው በተደጋጋሚ ይሄን ችግር የሚፈታ መዋቅር እንዲኖራት ጥያቄውን ሲያሰማ የቆየበት አግባብ ነበር።
ይህንን የህዝብ ጥያቄና አቤቱታ መነሻ በማድረግም አመራሩ ለረጅም ጊዜ ለክልሉ ጥያቄ ሲያቀርብ መቆየቱን ያስታውሳሉ። በዚሁ ጉዳይ ላይ ነዋሪውን ማወያየቱን ይጠቁማሉ። ከተማዋ ወደ ሪጅኦ ፓሊታን ያደገችው ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው ነው የሚሉት ከንቲባ ደስታ የከተማው ነዋሪ በዚህ እጅግ ተደስቷል። በቅርቡ ደስታውን የሚገልፅበት የድጋፍ ሰልፍም አንደሚያደርገ ይናገራሉ።
ከንቲባው እንደሚሉት አሁን ላይ ከተማዋ በአምስት ክፍለ ከተማ የተደራጀች ነች። 29 የከተማ ቀበሌ አላት። የገጠር ማዕከል የሆኑ 13 ንዑስ ቀበሌዎች ባለቤትነቷንም አረጋግጣለች። በአዲሱ አደረጃጀት የገጠር ቀበሌዎች ወደ ከተማው የሚገቡበት ሁኔታ ይኖራል። ይሄም ገቢዋን የበለጠ ያሳድጋል፤ የሥራ ዕድልም ይከፈታል። ደብረ ብርሃንን ወደ ሪጅኦ ፓሊታን ለማደግ ያስቻላትም ይሄው አቅሟ ነው።
ለምሳሌ ያህል አንድ ፋብሪካ ብቻ በጥቂት ጊዚያት ውስጥ ለ42 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረበት ሁኔታ አለ። እንደ ወተት ፋብሪካን መሰረት ያደረገው የአግሮ ኢንዱስትሪም ሆነ የሌሎቹ ገበያና ግብዓት አቅርቦት ከዞኑ አርሶ አደሮች ተጠቃሚነት ጋር እንዲተሳሰር ተደርጓል። ቆላ ውስጥ አምራቾችም ወደ ከተማ መጥተው ተጠቃሚነትን በተመጋገበ ሁኔታ የሚጋሩበት ዕድል ተፈጥሯል። ከከተማው አልፎ ከክልሉና ለኦሮሚያ ክልል እየተጠቀሙ ይገኛሉ። ዳሽንና ሐበሻ ቢራ ብቻ ለመንግስት ከፍተኛ ግብር ይገብራሉ። ከተማ አስተዳደሩ በራሱ የሚያስገባው ገቢ ቀላል አይደለም። ወደ እዚህ ደረጃ ካደረሳት አንዱ መስፈርትም ይሄው ወጪን የመሸፈን አቅሟ የጎለበተ መሆኑ እንደሆነ ይናገራሉ።
በበጀት ዓመቱ ማዘጋጃ ቤቱ ለመሰብሰብ አቅዶ ከነበረው 120 ሚሊዮን ብር በዘጠኝ ወሩ ብቻ 145 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ለአብነት ይጠቅሳሉ። በቀሪው ጊዜ እስከ 200 ሚሊዮን ብር እንደሚሰበሰብም በእርግጠኝነት ይናገራሉ። ከዚህ ውጭ ባለው 507 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ አቅም መኖሩንም ገልፀውልናል። ገቢ የመሰብሰብ አቅማቸውን አሟጠው የመሰብሰብ ዕቅድ አላቸው። በዚህ በኩል ትኩረት ሰጥተው ይሰራሉ። ደብረ ብርሃን እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ ብዙ ለከተማነት ያስመረጣት ምቹ ሁኔታና መልካም አጋጣሚዎች እንዳሉም አብራርተዋል። ሆኖም ባለፈው ስርዓት እድገቷ ወደ ኋላ የተጎተተበትና በልማት ወደ ኋላ የቀረችበት ሁኔታ ነበር። የኢኮኖሚ አቅሟም የተዳከመበት ሁኔታ ተፈጥሮ ቆይቷል። በመልካም አስተዳደር ችግሮች የተተበተበች በመሆኗ ነዋሪዋም ምቾት አልነበረውም። አመራሩ ይሄን ሁሉ ችግር መፍታት ይጠበቅበታል። በዚህ ላይ መዋቅሩ አዲስ እንደመሆኑ ከተማዋ አዲስ አደረጃጀትም ያስፈልጋታል። የክፍለ ከተማ ፣የወረዳና ቀበሌ መምሪያ፣ ጽሕፈት ቤት ሊኖራት ግድ ይላል። ይሄ አደረጃጀት በመንግስት አቅም ብቻ የሚፈፀም አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ከተማዋን ባለሀብቶች ጨምሮ አንዳንዱ በዚህ ላይ የራሱን አስተዋፆ ማድረግም ይኖርበታል። ከተማ አስተዳደሩ የቤት ሥራው ብዙ መሆኑን ሳይጠቅሱ አላለፉም።
ከኮቪድ ጋር ተያይዞ ነዋሪውን የክትባት አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ይሰራል። ሳኒታይዘርና ሌሎች መከላከያዎች ሳይዘነጉ ጥንቃቄ ማድረግ የሚያስችል ግንዛቤ መፍጠርም ዕቅዱ ነው። አሁን ላይ ነዋሪውን 98 በመቶ የአፍና አፍንጫ ጭንብል ተጠቃሚ መሆን ችሏል።
ከንቲባው እንዳሉት ሁሉም ከንቲባዎች የየራሳቸውን አሻራ ጥለው ያለፉባትንና በእሳቸው ጊዜ ይሄን ዕድል ያገኘችውን ደብረ ብርሃንን የበለጠ ለማሳደግ ይሰራሉ። ደብረ ብርሃኑ ሰላም የሰፈነባት ከተማ ነች። በሁሉ ነገር ኢትዮጵያዊት የሆነች ከተማ ነች። ሁሉም ብሔር ብሔረሰብ፣ የተለያየ እምነት ተከታይ በፍቅር የሚኖርባት ከተማ ናት። ሕዝቧም ሆነ አመራሩ ከተማዋ ስታድግና ስትለወጥ ማየት ነው ፍላጎቱ። ለእሳቸው ከዚህ በላይ ደስታ የሚሰጣቸው ምንም ነገር የለም። እኛም ደስታቸው የከተማዋ ነዋሪዎች በሙሉ የሚጋሩት ሆኖ እንዲዘልቅ በመመኘት ጽሑፋችንን ቋጨን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2013