የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ልጆች የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ወዳጆች ክቡራትና ክቡራን፤ አገራችን ኢትዮጵያ የምትገኝበት ጂኦ ፖለቲካዊ ከባቢ ዛሬም እንደትናንቱ የዓለም ዓይን ማረፊያ ሆኖ ይገኛል። ከሜዲትራኒያን ባህር ቀጥሎ በዓለም ታሪክ ላይ የሚደረጉ የንግድና ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች የሚጠቀሰው ቀይ ባህር ነው።
በዚህ ቀጠና ላይ የበላይነት መያዝ በዓለም አቀፍ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ይታመናል። እናም ብዙ አገራት ከሌላ የዓለም ዳርቻ መጥተው በቀይ ባህር ዙሪያ የጦር መንደሮችን ከመመስረት፣ ወደቦችን ከማልማት የንግድ መስመሮችን ከመዘርጋት ባለፈ በቀጠናው ፖለቲካ ላይ እጃቸውን ከማስገባት ተቆጥበው አያውቁም። ኢትዮጵያ ደግሞ ከቀይ ባህር ጋር አብራ የተፈጠረችና የኖረች አገር ናት።
ከጥንት ጀምሮ በቀይ ባህር ሲደረግ በነበረው ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊና የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ጉልህ ሚና ነበራት። የእኛን ተሳትፎ ከሌሎቹ አገራት ለየት የሚያደርገው የፍላጎታችን ምንጩ ከቀይ ባህር ጋር ካለን ቅርበት ጋር የተያያዘ መሆኑ ነው። ብንፈልግ እንኳን ከቀይ ባህር ፖለቲካ ልናመልጥ አንችልም። እንደ መጥፎ ዕድል ሆኖ አንዳንድ አካላት ቀይ ባህር ላይ ያላቸው ፍላጎት የሚሳካ የሚመስላቸው አገራችን ስትዳከም ነው። ይሄ ደግሞ እንደ ሉዓላዊ አገር በፍጹም ተቀባይነት የለውም።
የአገራችንን ጥቅም በኃይል ወይም በዲፕሎማሲ ተጽእኖ የማጣት ምንም ዓይነት ፍላጎት እንደሌለን መታወቅ አለበት። እኛ እንደ አገር ከቀይ ባህር ጥቅም ለማግኘት ስናቅድ ከሁሉም ጎረቤቶቻችን ጋር በሰጥቶ መቀበል መርህ ተስማምተን እንጂ ከማናቸውም ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ በመግባት አይደለም። የጋራ ፍላጎቶቻችንን በጋራ ለማሳካት ተግባብተን በሰላማዊ መንገድ እንደምንሰራ የዲፕሎማሲ ታሪካችን ምሳሌ መሆን ይችላል።
ኢትዮጵያ በቀይ ባህር አካባቢ ባላት የጂኦ ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ባለፈ የአባይ ውሃ ምንጭ በመሆኗ የአፍሪካን ቀንድና የሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ ሁኔታን የመወሰን አቅም አላት። ከግሪክ ሥልጣኔ ዘመን ጀምሮ አውሮፓውያንና እስያውያን ኢትዮጵያን ለማግኘት ከተጉበት ምክንያቶች አንዱ የአባይን ምንጭ ለማወቅና ለመቆጣጠር እንደሆነ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።
በእነዚህ በሁለት ጂኦ ፖለቲካዊ ምክንያቶች የተነሳ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ብሎም በአፍሪካ አህጉር ደረጃ ጠንካራ እየሆነች ከመጣች ጥቅማቸው የሚነካ የሚመስላቸው አካላት ስጋት ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ ግልጽ ነው። ነገር ግን አንድ መታወቅ ያለበት ሀቅ ድሮም ሆነ ዛሬ ኢትዮጵያ የሌሎች ጥቅም ላይ ምንም ዓይነት ስጋት የመፍጠር ዓላማ የላትም።
በተመሳሳይ የአገራችን ጥቅም ላይ ሌሎች ተጽእኖ እንዲፈጥሩብንም አንሻም። ለውጡን ተከትሎ በቀጠናው የተረጋጋ ሁኔታ እንዲፈጠርና በቀጠናው ያለን ግንኙነት እንዲጠናከር የሰራናቸው ሥራዎች አሉ። ከኤርትራ ጋር ያለን ግንኙነት መታደሱና በአጠቃላይ በቀጠናው ላይ የፈጠርነው መልካም ግንኙነትና ትስስር ቀጠናውን ለሚታዘቡ ኃይሎች ደስ የሚያሰኛቸው ጉዳይ እንዳልሆነ እሙን ነው።
አገራችን ኢትዮጵያ በቅርቡ ከሱዳን ጋር የገባችበት ሁኔታ ከነበረን መልካም የሆነ የረጅም ዘመናት ግንኙነት አኳያ ሲፈተሽም ፈጽሞ መፈጠር የሚገባው እንዳልሆነ ግልጽ ነው። አሁንም ቢሆን ለዘመናት የቆየ በጎ ግንኙነት ታሳቢ በማድረግ በድንበር አካባቢ የተፈጠረውን ችግር በሠላማዊ ሁኔታ ለመፍታት እንሰራለን።
ሱዳኖችም ከመስፋፋትና ከጠብ አጫሪነት ወጥተው ለሠላማዊ መፍትሄ እንደሚቆሙ ተስፋችን ነው። የኢትዮጵያን ሥልጣኔ ማየት የማይሹ አካላት ዋና አላማቸው ደካማ ኢትዮጵያን መፍጠር ነው። ለዚህ ደግሞ ሦስት መንገዶችን ይጠቀማሉ። ኢትዮጵያን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከጎረቤቶቿ ጋር በጦርነት መማገድ፤ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ማዳከምና ኢትዮጵያውያንን በአካባቢና በእምነት ማጋጨት ናቸው። ከጥንት ዘመናት ጀምሮ ኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ ጦርነቶችን ከባዕድ ወራሪዎች ጋር አድርጋለች።
የእነዚህ ጦርነቶች ዋና ዓላማ አገሪቱ ፋታ አግኝታ የሥልጣኔ መንገዶቿን እንዳትከተል ማድረግ ነው። በእርግጥም ጦርነቶቹ በተወሰነ አድክመውን አልፈዋል። ከጦርነቱ ባሻገር የኢትዮጵያን የንግድ መስመሮች በመያዝ ከባህር በር ውጪ ማድረግና ዓለም አቀፍ ብድርና እርዳታ እንዳታገኝ እንዲሁም ታላላቅ ፕሮጀክቶችን እንዳታካሂድ እንቅፋት በመፍጠር የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማሰናከል ጥረት ተደርጓል። የአባይ ግድብምን ሆነ ሌሎች ግድቦችንም ለመገንባት ኢትዮጵያ በታሪኳ ያደረገቻቸው ጥረቶች ያልተሳኩበት አንዱ ምክንያት ይኸው ነበር።
ከአባይ ወንዝ ተገቢውን ጥቅም ማግኘት እንዳንችል ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚውል ገንዘብ እጥረት፣ የእርስ በእርስ ጦርነትና የዓለም ፖለቲካ ተለዋዋጭ አሰላለፍ የሚጠቀሱ ናቸው። አንዳንድ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ በጎረቤት አገራት የሚቃጡ ጦርነቶችን በመቆስቆስና በመደገፍ በአገር ውስጥ የፖለቲካ አማጽያንን በመደገፍና የእርስ በእርስ ጦርነትን በማቀጣጠል ለጋሽ አገራት የገንዘብ ድጋፍ እንዳያደርጉ በመጎትጎት አባይን እንዳንጠቀም የሚቻላቸውን ሁሉ ሲያደርጉ እንደነበር ይታወቃል።
በኢትዮጵያ ላይ ሁለንተናዊ ጫና ለመፍጠር በሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽነት ስም እንዲሁም በሠላምና በሰብአዊ መብት ስም ተጽእኖ ሲደረግ ይታያል። ለውጡን ተከትሎ የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ስናደርግና የፖሊሲ ነፃነታችንን ለማስጠበቅ ስንንቀሳቀስም እግራችንን ከሚጎትቱ አንዱ በዲፕሎማሲ መልኩ የሚመጣ ጫና ነው። እኛ በአሸባሪነት ለመፈረጅ የተገደድንበት የጁንታ የጥፋት እንቅስቃሴ የዲፕሎማሲ አጋሮቻችን በቀላሉ ተመልክተው ጫና ሲያደርጉብን ይታያል።
የመጨረሻው ምጥ ልጁ የሚወለድበት ነው። አባይን በራሳችን ገንዘብ ገንብተን ወደ ፍጻሜ ማድረሳችን በቀይ ባህር የነበረንን ተጽእኖ ፈጣሪነት ለመመለስ ተግተን መሥራታችን፤ ከኤርትራ ጋር የነበረን የተበላሸ ግንኙነት አድሰን ቤተሰባዊነት መመስረታችን፤ የጁንታውን ጦርነት እነርሱ ባልጠበቁት መንገድ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአሸናፊነት መወጣታችን፤ የራሳችንን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የአሥር ዓመት አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መንደፋችን፤ የሕዝቦችን አንድነትና ትብብር በማነቃነቅ ወደ ጠንካራ አገርነት መጓዛችን ያላስደሰታቸው ኃይሎች እንዳሉ ግልጽ ሆኗል።
ይህ ወቅት ኢትዮጵያውያን ሁለት ነገሮችን ለይተው በጽናት የሚቆሙበት ጊዜ ነው። የውስጥ ጉዳያችንና የውጪ ጉዳያችንን። የውስጥ ጉዳያችንን በክርክር በልሂቃን ድርድርና በውይይት የምንፈታቸው ናቸው። የተፈጠሩት በአንድ ሌሊት አይደለም። የሚፈቱትም በአንድ ሌሊት አይደለም። እኛ የዘመናት ችግር ወራሾች ነን። ዕዳ ያለበት ሰው ሁለት ነገር እንዲሰራ ይገደዳል።
በአንድ በኩል ያልነበረበትን ዘመን ዕዳ ይከፍላል፤ በሌላ በኩል ደግሞ አሁን በዘመኑ የገጠሙትን ችግሮች ይፈታል። እኛም የገጠመን ይኸው ነው። የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር የውስጥ ችግሮችን መፍታታችን አጠራጣሪ አይደለም። የውጭው ፈተና ግን ጊዜ የሚሰጠን አይደለም።
የመርከቧ ተሳፋሪዎች መከራከርና መፎካከር የሚችሉት መጀመሪያ መርከቧ ካለች ብቻ ነው። የሰጠሙ ጊዜ ውይይትም ክርክርም ድርድርም ትብብርም ፉክክርም የለም። የአገርም ጉዳይ እንዲሁ ነው። አባቶቻችን የአገራችንን ነፃነትና ሉዓላዊነት አስከብረው የኖሩት የአገራቸው የውስጥ ችግሮች ሳይፈትኗቸው ቀርቶ አይደለም።
በአሁን ወቅት በአገራችን ውስጥ የገጠሙን ግጭቶች የዜጎች ሞትና መፈናቀል እንዲፈጠር እያደረጉ ያሉ ኃይሎች ለአገራችን ሰላምም ሆነ ለዜጎቻችን ህልውና ስጋት በማይሆንበት ደረጃ በቁጥጥር ሥር የማዋልና የሕግ የበላይነትን የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል። ዛሬም ከግራና ከቀኝ የተቃጣብንን አደጋ ለመቀልበስ ቀልብሰንም ወደ ጀመርነው የሥልጣኔ ጉዞ ለመገስገስ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መካሪ ሆነን የምንቆምበት ወቅት ነው።
በተለይም ከፊት ለፊታችን ያሉበን ሁለት አገራዊ ተልዕኮዎች በሚገባ በመወጣት ኢትዮጵያ ልጆቿ እንዳሏት ማረጋገጥ አለብን። ሁለቱ አገራዊ ተልዕኮዎች የህዳሴውን ግድብ ሁለተኛውን ሙሌት ማከናወንና አገራዊውን ምርጫ በስኬት ማጠናቀቅ ናቸው። ሁለቱም የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያንን የነገ ዕጣ ፈንታ ይወስናሉ።
ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሠላማዊ ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ለመጠናቀቅ የመጨረሻዋ ምዕራፍ ላይ ደርሰናል። የተወዳዳሪዎችና የመራጮች ምዝገባ ተከናውኖ ምርጫ ቅስቀሳና ሌሎች ለምርጫው የሚያስፈልጉ ተግባራት ተከናውነዋል። ከሞላ ጎደል አሁን የቀረው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ነው። ይሄንን በስኬት ማጠናቀቅ ለአገራችን ትልቅ ድል ይዞ ይመጣል።
ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የምታደርገውን ሽግግር አንድ ደረጃ እንደሚያሳድገው ምንም ጥርጥር የለውም። በዚህ አጋጣሚ ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒነቱን ጠብቆ እንዲፈጸም ሁሉም አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ያላሰለሰ ጥሪያችንን እናቀርባለን። በመንግሥት በኩል የተጀመሩ የሕግ የበላይትን የማስጠበቅና ሠላም የማስከበር ሥራዎችን አጠናክሮ ይቀጥላል። በተለያዩ አጋጣሚዎች የተፈናቀሉ ዜጎቻችንም በፍጥነት ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ የተለያዩ አካላትንና ሕዝባችንን በማስተባበር ይሰራል።
መንግሥት በትግራይ ክልል የጀመረውን የመልሶ ግንባታ ሥራና የሰብዓዊ ድጋፍ ከአጋሮቹ ጋር አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። የእምነትና የብሔር ልዩነቶቻችንን እንደ ጸጋ ብቻ በመቁጠር አንድ ሆነን እንደ ብዙ፣ ብዙ ሆነን እንደ አንድ በመንቀሳቀስ የጀመርናቸውን ፕሮጀክቶች ሁሉ በተገቢው ደረጃና ፍጥነት በማጠናቀቅ ከቃል ይልቅ ለተግባር ቅድሚያ በመስጠት የመከላከያ ኃይላችንን በሙሉ አቅሙ በመደገፍ የፖለቲካ አመራሮቻችንን በአገራዊ ተልዕኮ ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ፤ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ዲፕሎማቶቻችንን አገራችንን በዓለም መድረክ በብቃት መወከላቸውን በማስከበር፤ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ኢትዮጵያን መውደዳቸውን በአመቺ መንገድ ሁሉ እየገለጹ ከኢትዮጵያና ሕዝብ ጎን መሆናቸውን በማሳየት በኢትዮጵያዊነት ስሜት አንድ ሆነው እንዲቆሙ ጥሪ እናደርጋለን።
በዚህ አጋጣሚ ከህዳሴ ግድባችን ጋር በተገናኘ ኢትዮጵያ ማግኘት ያለባት ጥቅም እንዲጠበቅ አንደበት ሆናችሁ የአገራችን ድምጽ እንዲሰማ ለሀቋ ስትሉ በዓለም አቀፍ መድረኮችና በመካከለኛው ምሥራቅ ሚዲያዎች ላይ እየሞገታችሁ ያላችሁ ብርቅዬዎች ኢትዮጵያ ለእናንተ ትልቅ ክብር አላት። የአገር ልጅነታችሁን ከሥም ባለፈ በተግባር አስመስክራችኋል። ከአገር ሉዓላዊነት ጋር በተገናኘም የሚገጥሙንን ተጽእኖዎች በሙያችሁና በድምጻችሁ እየመከታችሁ ያላችሁ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች እናት አገራችን በጦር ሜዳ ላይ ጀብዱ ከፈጸሙላት ጀግኖቿ ለይታ አታያችሁም። ታሪክም ሲዘክራችሁ እንደሚኖር ጥጥር የለውም።
የብልጽግና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ግንቦት 20 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2013