‹‹ኧረ እንደው እገሊት በሠላም ተገላገለች?›› ከሚለው ጥያቄ ጎን ለጎን “ለመሆኑ ምን ወለደች?” መባሉ የተለመደ ነው፡፡ የጥያቄው ምላሽ “ወንድ” የሚል ከሆነ ታዲያ ‹‹ጎሽ ጎሽ…›› የሚል የፈገግታ ምላሽ ለእናት እንደ ማበረታቻነት ይበረከታል፡፡ በተቃራኒው ሴት እንደሆነች ከታወቀ የእናትን በሠላም መገላገል ፈጣሪን ለማመስገን ታክል ብቻ ‹‹ትሁን›› ይባላል፡፡ ይህ የማህበራዊ ፆታ መነሻ የሆነው ድርጊት ታዲያ በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ ይልቁንም ከቦታ ቦታ ይለያይ እንጂ ለወንድና ለሴት የሚደረገው እልልታ እንኳ ልዩነት እንዳለው ይነገራል፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች ወንድ ሲወለድ ጥይት እስከ መተኮስም ይደርሳል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያሉ የሴቶችን የበታችነት መስበክ የሚጀምሩት እያንዳንዱ ትንንሽ የሚመስሉ ነገር ግን በነገ የልጆች ሕይወት ላይ ትልቅ አሻራን የሚጥሉ በተግባር የተደገፉ አመለካከቶች እኩልነትን በሚዘምሩ ግለሰቦች ሳይቀር በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሲተገበሩ ይስተዋላል፡፡ በእልልታ የተጀመረው ይህን መሰል ድርጊት ልጆች አደግ ሲሉ በሚገዛላቸው መጫወቻ ቁሳቁስም ይንፀባረቃል፡፡ ለወንዱ ሽጉጥና አውሮፕላን በመግዛት መግደልም ሆነ ያሻውን ማድረግ እንደሚችል እንዲሁም ደግሞ መኪናም ሆነ አውሮፕላን ማሽከርከር ትችላለህ በሚል በቁስ ተደግፎ ያድጋል፡፡ ዕድሜው ሲጨምርም በየመንገዱ ሴቷን ካልገደልኩሽ እንደሚያሰኘው በየዕለት ተዕለት ኑሯችን የምናስተውለው መሪር ሀቅ ነው፡፡ በሌላ በኩል ለሴቷ አሻንጉሊት በመስጠት የቅጠል ወጥ እየሰራች እንድትጫወት ይደረጋል፡፡ በዚህም ሴት ልጅ የአባወራውን ሆድ ከመሙላትና ልጅ ከማሳደግ የእናትነት ሚና የዘለለ አስተዋፅዖ እንደሌላት እየተነገራት ታድጋለች፡፡
የሴቶችን የበታችነት የሚያጎሉ አባባሎችም እንዲሁ በሰፊው ይነገራሉ፡፡ አንዳንዴማ የሴቷን ጉብዝና ለመግለጽ ‹‹ወንድ ነሽ›› ይሏታል፡፡ ይህም ሴት በመሆንሽ ምንም ማድረግ አትችይም፡፡ ነገር ግን አቅምሽ ሲጐለብት ወንድ የሚለውን መጠሪያ ማግኘት ትችያለሽ እንደማለት ነው፡፡ በማሕበረሰቡ ውስጥ የተገነባውን ይህን መሰል ከባድ አመለካከት ሰብረው በመውጣት ድልን መቀዳጀት ታዲያ ፈታኝ እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡ ነገር ግን አገሪቱ አሉኝ ብላ የምትኮራባቸው ውጤታማ እንስቶች እንዳሉም አይካድም፡፡
የበርካታ ሙያ ባለቤት ሴቶች፣ አልሞ ተኳሽ ሴት ወታደሮች፣ ብቁ ሴት ጀነራል መኮንኖች፣ ተራራና ሸንተረሩን ዱርና በረሃው ሁሉ አቋርጠው ተፈጥሮ ሳያግዳቸው አሸናፊ መሆን የቻሉ ሁሉ ሲጠሩ ታዲያ የሥነልቦናቸው ጥንካሬ ማሳያም ይሆናል፡፡ በዚህ መልኩ በዓለም አቀፍ የሠላም ማስከበር ታሪክ ሁለተኛዋ አፍሪካዊት ምክትል ኮማንደር ሴት ጀነራል መኮንንና በመከላከያ ሚኒስቴር የበጀትና ፕሮግራም ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀነራል ዘውዴ ኪሮስ ከአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት የተገኙ ዕንቁ መሆናቸው አመለካከቱ ሚዛናዊነት የጎደለው እንደሆነም ያመላክታል፡፡ እኛም ለዛሬ ከእኚህ ታላቅ ጀነራልና ከሌሎች በሠራዊት ውስጥ ጉልህ ሚና ካላቸው ሴት ወታደሮች ጋር ያደረግነውን ቆይታ ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡
ተሳትፎና ግዳጅ አፈፃፀም ብርጋዴር ጀነራል ዘውዴ፤ በውትድርና ውስጥ ከ30 ዓመታት በላይ እንዳሳለፉ ያስታውሳሉ፡፡ በሠራዊቱ ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ እንደ ማንኛውም የሠራዊት አባል እንደሆነ በማንሳት፤ ሴት በመሆናቸው ብዙ ፈተና ሊያጋጥም እንደሚችልም አልሸሸጉም፡፡ ዋናው ግን ዓላማ ነው ባይ ናቸው፡፡ ውትድርና ለሴቶች ይከብዳቸዋል የሚለው አስተሳሰብም ተጨባጭነት የሌለው በሥራ ውጤት የሚለካ ነው ሲሉ አመለካከቱን ይነቅፉታል፡፡
ቀድሞ የወንድና የሴት በሚል በተለዩ ሥራዎች ሴቶች የቤት ሥራ በዋናነት ይሰጣቸዋል፡፡ በአደባባይ ተወጥቶ የሚሰሩ በተለይም ውትድርና የወንድ በሚል ከተፈረጁት መስኮች ውስጥ ነው። ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ዘርፉ ከባድና ብዙ ውጣ ውረዶች ይበዙበታል ከሚል ዕሳቤ የተነሳ ነው፡፡ በዚህም ሴት ልጅ አትችለውም ሲባል ይደመጣል። ዳሩ ግን ሴቶች የማይሰሩትም ሆነ ውጤታማ መሆን የማይችሉበት መስክ አለመኖሩን ደግሞ ይህን አመለካከት ሰብረው በመውጣት ከስኬት ማማ የደረሱ እንስቶች ሕያው ምስክር ይሆናሉ፡፡ በሠራዊቱ ውስጥም ሴቶች በመሆናቸው የተለየ የሚሰጣቸው ግዳጅ የለም። በተግባርም በጦርነቱም ሆነ በሠላማዊ ሂደቱ ለሠራዊት የሚሰጠው ግዳጅ በሙሉ ተሳታፊ እንዲሆኑ ይደረጋል። የሚሰጠውን ግዳጅም በአግባቡ እየፈፀሙ ይገኛሉ፡፡
ውትድርና የቡድን ሥራ ነው የሚሉት ጀነራሏ፤ በእያንዳንዱ ቡድን የሴቶች ተሳትፎ መኖሩን ያረጋግጣሉ፡፡ በተልዕኮ አፈፃፀምም ከወንዶች እኩል አንዳንዴም ከዛ አለፍ ብለው ይታያሉ፡፡ ይህም የሚሳየው ‹‹ሴቶች አይችሉም›› ከሚባል ይልቅ ዕድሉ ከተሰጣቸው በሁሉም የሥራ መስክ ገብተው ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ነው፡፡ ውትድርናም ሴቶች ሊሳተፉበት የሚችሉበት እንደሆነም በሕብረተሰቡ ዘንድ ዕምነት ሊኖር ይገባል፡፡ የአስተሳሰብ ድህነትና ኋላቀርነት ካልሆነ በቀርም ሴቶች ይችላሉ፡፡
የሴቶች በሠራዊት ውስጥ ከወንዶች እኩል ተሳትፎ ያደርጋሉ፡፡ በአገር ውስጥ በሚጋጠሙም ሆነ ከአገር ውጪ በሚመደቡባቸው ግዳጆችም እኩል በመሳተፍ እንደሚታዩ ከሎጅስቲክስ ህብረት ዋና መምርያ የሰው ሀብት ዕቅድና ሪፖርት ባለሙያ ሻምበል አሰገደች አየለ ትገልፃለች፡፡ ከዚህ ባለፈም ጥሩ አስተዋፅዖ አበርክተው ስኬትንም ሲቀዳጁ ይስተዋላል፡፡ ሴቶች ለግዳጅ ሲጠሩም ከወንዶች በተለየ ሳይሆን ከወንዶች እኩል ተሰልፈው በተላኩበት ሁሉ ግዳጃቸውን በአግባቡ ይወጣሉ፡፡ ውትድርና ከውጪ በሩቅ ሆኖ ለሚመለከተው ለሴቶች ከባድ እንደሆነ እንዲስብ ቢያደርገውም ቀላል እንደሆነ የምትናገረው ደግሞ በአገር መከላከያ ሚኒስቴር የመከላከያ ኮሙዩኒኬሽን ኤሌክትሮኒክስ ሳይበር ዋና መምሪያ ኢንስፔክሽን ባለሙያ ሻምበል ጌጤነሸ ፍቃዱ ናት፡፡
ሴቶች ቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆናቸው በውትድርናው መስክ ሲገቡም በተሻለ አፈፃፀም ተልዕኳቸውን ሲወጡ ይስተዋላል፡፡ የተለያዩ ግዳጆች ላይ ሲሰማሩም አዛኝና ሩህሩህነታቸው ጎልቶ ይታያል። ሥራው ከትምህርት ዓለም እስከ ተለያዩ ግዳጆችና ተልዕኮዎች መወጣት ድረስ ዕርስ በዕርስ መረዳዳት የተሞላበት ነው፡፡ ከሠራዊቱ ጋር ያላቸው ማህበራዊ ግንኑነትም በጣሙን ጥሩ በመሆኑ ሥራዎችን በጥሩ መግባባትና አገራዊ ስሜት እንዲከናወን ጉልህ ድርሻ ያበረክታል፡፡ ለሠላምና አንድነቱ ሴቶች ከቤት ውስጥ ጀምሮ ትልቅ ሚና የሚጫወቱ በመሆናቸው በአሁኑ ወቅት የሚስተዋሉ አለመረጋጋትና ግጭቶች እንዲሁም አንድነትን የሚሸራርፉ ተግባራት በቀላሉ የማረም አቅም እንዳላቸው ነው ሻምበል ጌጤነሽ ዕምነቷን የምትናገረው፡፡ በመሆኑም በቤት ውስጥ ካለችው እያንዳንዷ ሴት ጀምሮ በሠራዊቱ ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ እስካላቸው ሰቶች ሁሉም ለሰላም መረጋገጥና የሕዝቦች እንድነት መጎልበት የበኩላቸውን ሚና መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሻምበል አሰገደች በበኩሏ፤ ሠላም ይበልጥ ትርጉም ያለው ለሴቶች እንደሆነ ማሳያዎችን በማንሳት ትዘረዝራለች፡፡ ሴቶች፣ እናት፣ እህት፣ ሚስትና ሁሉ ነገር በመሆናቸው ለሠላም ትልቅ ቦታና ዋጋ ይሰጣሉ፡፡
በዚህም አገሪቱ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ አለመረጋጋቶችንም ለማስቀረት ሴቶች በሁሉም ስፍራ በመገኘት የአገሪቱን ዳር ድነበር ከማስከበር ባሻገር ሠላምንም ያስከብራሉ፡፡ በሠራዊቱ ውስጥ ተሳታፊ ከሆኑ ሴቶች ውጪም እንዳንዷ በቤት ውስጥ ትልቅ የቤተሰብ ኃላፊነት የተሸከሙና የነገ አገር ተረካቢ ትውልድ የሚቀርጹ እናቶችም ልጆቻቸውን በአንድነት መንፈስ ውስጥ እየቀረጹና የሠላምን ዋጋ እንዲረዱ በማድረግ ሊያሳድጉ እንደሚገባ ታሳስባለች፡፡ በቀጣይስ ምን ይደረግ? በመከላከያ ውስጥ በዛ ያለ የሴቶች ቁጥር ጎልቶ እንደማይታይ ትዝብቷን የምትናገረው ሻምበል ጌጤነሽ፤ ይህም አመለካከቱ ገና እንደሆነ ማሳያ ይሆናል ትላለች፡፡ የሚታጠቋቸው ትጥቆች፣ እግረኛ፣ አየር ኃይልና ልዩ ኃይል እነዚህ ሁሉ ለሴቶች ከባድ ተደርጎ ይታያል፡፡ ሆኖም ግን ውስጥ ተዘልቆ ሲታይ በቤተሰብና በማህበራዊ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ኃላፊነትን መሸከም ለሚችሉ ሴቶች ውትድርና ከባድ አለመሆኑን ታስረዳለች፡፡
አክብዶ የሚያሳየውም ለዘመናት የሚስተዋለው ኋላቀር አመለካከት ነው፡፡ ሻምበል ጌጤነሽ፤ ከራሷ በመነሳት እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረሷ በጀግንነቱ የሚታወቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስላፈራት እንደሆነም ትገልፃለች፡፡ በመሆኑም ሴቶች አላስፈላጊና ወደኋላ የሚያስቀሩ አመለካከቶችን ወደጎን በማለት ሠራዊቱ በሚጓዝበት ሁሉ ጠንክሮ መስራትና ማገልገል ይገባቸዋል፡፡ በዚህም ሴቶች ከእናትነት የዘለለ በአገራቸው ላይ ትልቅ ድርሻ መወጣት እንደሚችሉ ማስመስከር ይኖርባቸዋል፡፡ ከቤት እመቤትነት በዘለለ በተለያዩ ግዳጆች ውስጥ በመሰማራት አገራዊ ኃላፊነት መወጣት እነደሚችሉ አመኔታ ለማሳደር በተሰማሩበት መስክ ‹‹እኩል ነን›› ከሚለው ንግግር ባለፈ ውጤታማ መሆንና የሴቶች ተሰሚነት እንዲጎላም በመሥራት ማስመስከር እንደሚገባ ሻምበል ጌጤነሽ ትገልፃለች፡፡ ለወደፊቱ ውትድርና ቀድሞ በነበረውና በአሁኑ ወቅት እንደሚታየው እንደማይሆን ጀነራሏ ይጠቁማሉ፡፡ ቴክኖሎጂ እያደግ በመምጣቱ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም የሚደረግ ውጊያም ነው የሚኖረው፡፡ ይህም ሳይንሱን ያወቀና የተማረ ሰው በሙሉ መሥራት ያስችለዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ሴቶች ወደፊት በውትድርና ሥራ ቢሰማሩ የቴክኖሎጂ ውጤቱን ተጠቅመው ተምረው ለተሻለ ውጤት እንዲደርሱ የሚያስችል ነው፡፡ ውትድርና የጉልበት ሥራ ሳይሆን በዕውቀትና በሳይንስ የሚመራ ጥበብ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ለሴት ለወንድ በሚል የሥራ ክፍፍል ማድረግ የድሮና ኋላቀር ጎታች አመለካከት ነው፡፡ በመሆኑም ዋናው ሴቶች ሊያተኩሩበት የሚገባው በትምህርትም በሳይንሱም ብቁ ሆኖ መገኘትን ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ በተሰማሩበት ዘርፍ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ እልህና ወኔ ብቻ እንደሚያስፈልግ ነው ጀነራል ዘውዴ የሚነገሩት፡፡ ለወጣት ሴቶችም ትምህርት የብዙ ችግሮች መፍቻ ቁልፍ ነውና መማር እንዳለባቸው ይመክራሉ።
በሁሉም የሥራ ዘርፍ መሳተፍ እንዳለባቸውና ‹‹የእንችላለን›› መንፈስን ሊያዳብሩ ይገባል፡፡ እንደሚችል የተቀበለ ይችላልና ሴቶች አይችሉትም የሚለውን አስተሳሰብ ባለመቻል ማጠናከር ከችግሩ የመውጣቱን መንገድ አጥብቦ አዳጋች ያደርገዋል፡፡ በመሆኑም ለሁሉ ነገር ወሳኟ ሴቷ በመሆኑ መቻሏን በተግባር ማሳየት ይጠበቅባታል፡፡
በተለይም በአሁኑ ወቅት ያለው ትውልድ እኩል የመሥራት ሁኔታው የተሻለ በመሆኑ ይህን ምቹ ሁኔታ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም መደጋገፍ ይገባል ሲሉ ጀነራሏ ይመክራሉ፡፡ የቤት ሥራ ብቻ በጫንቃ ከመሸከም በመውጣትም የጋራ እንደሆነ ማመንና ማሳየት ይኖርባታል፡፡ በተለያዩ የትምህርት እርከኖች ላይም ሴቶች ከፍተኛ አፈፃፀም በማስመዝገብ አሸናፊ ሆነው ይታያሉ፡፡ ይህ ውጤትም በሥራ መተርጎም ይኖርበታል፡፡
የቀለም ትምህርት ብቻ ሳይሆን በሥራ ዓለምም በተመሳሳይ የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ሊያሳዩ ይገባቸዋል፡፡ ይህ የሴት አይደለም በሚል የሚገፉት ዘርፍ መኖር የለበትም፡፡ ‹‹እችላለሁን!›› የዘወትር ትጥቃቸው በማድረግ በትምህርት የተሻለ ዕውቀት የያዘ አሸናፊ መሆኑ አይቀሬ ነውና በውትድርናውም ሊሳተፉ እንደሚገባ በመግለጽ፤ በተለይም በአሁኑ ወቅት ተቋሙ ምሁራን ዕጩ መኮንኖች እንዲገቡ ማሻሻያዎች እያደረገ በመሆኑ በዚህ ዕድልም ተሳታፊ ሆነው አገሪቱ ካሰበችው እንድትደርስ የበኩላቸውን መወጣት እንደሚገባቸው መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 9/2011
ፍዮሪ ተወልደ
I’ve learned so much from this blog and have implemented many of the tips and advice into my daily routine Thank you for sharing your knowledge!