በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይከናወኑ የቀሩ ተስተካካይ ጨዋታዎች በወጣላቸው መርሀ ግብር መሰረት ዛሬና ነገ ይከናወናሉ። በአዲስ አበባ ስታዲየም 10 ሰዓት መከላከያ ድሬዳዋ ከተማን ይገጥማል። በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው መከላከያ በዛሬው ጨዋታው ባለ ድል ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በ15ኛው ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን 1 ለ0 የረታው መከላከያ ከድሉ ማግስት የሚያደርገው ጨዋታ መሆኑን ተከትሎ የአሸናፊነት ግምትን ለመውሰድ ችሏል። ድሬዳዋ በአንፃሩ 13 ጨዋታዎችን አድርጎ 14 ነጥብ በመሰብስብ 12ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን ተከትሎ ከዛሬው ጨዋታ ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዞ ለመውጣት በቀላሉ ለጦሩ እጅ እንደማይሰጥ ይጠበቃል። የሁለቱም ክለቦች የነጥብ መቀራረብን ተከትሎ አሸናፊው ቡድን በወራጅ ቀጣና ከሚገኙ ክለቦች በነጥብ እንዲርቅና
የሚፈጠር መሆኑን ተከትሎ ጠንካራ የሆነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴና ፉክክር ይኖራል የሚል ግምትን አሳድሯል። በዛሬው እለት በተመሳሳይ የአምናው ቻምፒዮን ጅማ አባጅፋር በደቡብ ፖሊስ ከደረሰበት አስደንጋጭ የስድስት ለአንድ ሽንፈት ማግስት በሜዳው የደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌ የሚገኘውን ደደቢትን መግጠሙ ለማንሰራራት ይረዳዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ይሁን እንጂ ጅማ አባጅፋር በዛሬው ጨዋታ ድል ካልቀናው ቡድኑ ወደ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ስጋት አሳድሯል። የ2010 ዓ.ም ቻምፒዮናዎቹ አባ ጅፋሮቹ የዘንድሮው የውድድር ዓመት ብዙም ጠንካራ የሚባል እንቅስቃሴ አላሳዩም የሚል ትችት ለማስተናገድ ተገደዋል። አባጅፋር ዘንድሮ በአፍሪካ መድረክ ተሳትፎ ምክንያት ከድካምና ከጉዳት ጋር እየታገሉ እንደ መጀመሪያው ዓመት የፕሪሚየር ሊግ ተሳትፏቸው ወጥ የሆነ አቋም ማሳየት ተስኗቸዋል። በተጨማሪም ቡድኑ በፋይናንስ ችግር ምክንያት ላለፉት ሦስት ወራት የተጫዋቾቹን ደመወዝ ባለመከፈሉ በተጫዋቾች ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታን አስከትሏል። በ4ኛ ሳምንት ቀሪ ጨዋታ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ካደረጉት ጨዋታ ቀደም ብለው ልምምድ ለመሥራት ፈቃደኝነት አለማሳደራቸው ሲነገር በአዲስ አዳጊው ደቡብ ፖሊስ ከባድ ሽንፈት ማስተናገዳቸውን ተከትሎ ከደደቢት ጋር የሚያደርጉት የዛሬው ፍልሚያ ለአባ ጅፋር ህልውናው መሆኑ ተነግሯል።
ተጋጣሚው ደደቢትም የውጤት ሆነ የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ የሚገኝ እንደመሆኑ የዛሬው ጨዋታ ለመውጣትና ለመውረድ የሚያደርገው ትልቅ ትግል ነው። ደደቢት 14 ጨዋታዎችን አድርጎ 4 ነጥብ ብቻ በመሰብሰብ የመጨረሻውን 16ኛ ደረጃ ይዟል። በመሆኑም የዛሬው ጨዋታ የሞት ሽረት የሆነ ጨዋታ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ባለ ሜዳዎቹ ጅማ አባ ጅፋር እስካሁን በሊጉ ባደረጋቸው 11 ጨዋታዎች 14 ነጥብ ሰብስቦ 13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ የዛሬው ጨዋታውን ጨምሮ አራት ተስተካካይ ጨዋታ ያለው ሲሆን፣ ደደቢት የነገውን ጨምሮ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታ ይኖራቸዋል ።
እሁድ የካቲት 10 ቀን 2011 ዓ.ም የፕሪሚየር ሊጉ መሪ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ከባህርዳር ከተማ ጋር ይገጥማል። መቐለ ሰብዓ እንደርታ ባህርዳርን ካሸነፈ ከተከታዩ ሲዳማ ቡና ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት ከፍ በማድረግ የሊጉን መሪነት ማጠናከር የሚችል ሲሆን፣ በአንጻሩ ባህርዳር ከተማ ካሸነፈ አሁን ካለበት ስድስተኛ ደረጃ ወደ አራተኛ ከፍ ማለት ይችላል።
በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ከሚካሄዱት ሦስት ተስተካካይ ጨዋታዎች ውጪ ቀሪ አምስት ተስተካካይ ጨዋታዎች እስከ የካቲት 21 ቀን 2011 ዓ.ም የሚካሄዱ ይሆናል። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ29 ነጥብ ሲመራ ሲዳማ ቡና በ27 ነጥብ ሁለተኛ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ26 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል።ደቡብ ፖሊስ፣ ስሑል ሽረና ደደቢት ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጣና ውስጥ ይገኛሉ።
ዳንኤል ዘነበ