አዲስ አበባ/ኢዜአ/፣ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ የሆነው የባህል ስፖርት ተገቢውን ትኩረት እንዳላገኘ የስፖርት ባለሙያዎች ገለጹ።
የባህል ስፖርት ከክርስቶስ ልደት በፊት በስድስተኛውና ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ይዘወተር እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ።
በኢትዮጵያ ገበጣ፣ የገና ጨዋታን፣ ፈረስ ጉግስንና የቀስት ኢላማን ጨምሮ 294 የባህል የስፖርት አይነቶች እንዳሉ ተፈራ መኮንን የተባሉ የባህል ስፖርት ተመራማሪ ያካሄዱት ጥናት ያሳያል።
ከእነዚህ የባህል ስፖርቶች መካከል 13ቱ ህግና ደንብ ወጥቶላቸው በአገር አቀፍና በክልሎች ደረጃ ውድድር እየተካሄደባቸው የሚገኙ ናቸው።
ገበጣ፣ ገና፣ ፈረስ ጉግስ፣ የቀስት ውድድር፣ ኩርቦ፣ ቡብና ሻህ ህግና ደንብ ወጥቶላቸው ከሚካሄዱ ስፖርቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
እንዲያም ሆኖ ግን ስፖርቱ ከህብረተሰቡ ጀምሮ በሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እየተሰጠው እንዳልሆነ ነው የአዲስ አበባ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንትና የባህል ስፖርት ኢንስትራክተር አቶ መስፍን ከበደ የሚናገሩት።
ከባህል ስፖርቶች ይልቅ ለዘመናዊ ስፖርቶች ይበልጥ ትኩረት እየተሰጠ መምጣቱ የኢትዮጵያ ማንነት የሆነው የባህል ስፖርትን ያዳክመዋል የሚል ስጋት እንዳላቸውም ጠቅሰዋል።
የባህል ስፖርቶች ዳኛና ኢንስትራክተር የሆኑት አቶ ሹመቴ ታረቀ ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የባህል ስፖርቷን ያስተዋወቀችበትና የተሳተፈችበት መድረክ እንደነበር አስታውሰው አሁን ግን ወደኋላ እየቀረ መሆኑን ይገልፃሉ።
ተተኪ ስፖርተኞችንና ባለሙያዎች በማፍራት ዘርፉን ማሳደግ ከተፈለገ የባህል ስፖርቱን እስከ ክልል በማውረድ ህዝባዊ መሰረት ማስያዝ ይገባል የሚል ሀሳብ አቅርበዋል። ለዚህም የክልሎችና የባለሙያዎች ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነም ገልጸዋል።
ስፖርቱ ከውድድሩ ባለፈ የአገሪቷን ባህል የሚያስተዋውቅና ለቱሪዝም እድገቱ አስተዋጽኦ የሚያበርክት በመሆኑ ትኩረት እንደሚያሻው አመልክተዋል።
የባህል ስፖርቶች አሰልጣኝ አቶ ጌታቸው ዱጉማ የዘመናዊ ስፖርት መሰረት የሆነው ባህላዊ ስፖርት በቂ ትኩረት ባለማግኘቱ በሚፈለገው ደረጃ እንዳላደገና የህብረተሰቡ እንቅስቃሴ እየተዳከመ መምጣቱን ገልጸዋል።
መንግሥት የባህል ስፖርት በኢትዮጵያ እንዲያድግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በስፋት ማከናወን አለበት ይላሉ።
የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ስፖርቱን ለማስፋፋት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን የፌዴሬሽኑ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በላይነህ ኃይሌ ይገልጻሉ።
እስከ 1997 ዓ.ም ህግና ደንብ ወጥቶላቸው ይካሄዱ የነበሩ ስፖርቶች ሰባት እንደነበሩና ከተጠቀሰው ጊዜ በኋላ ስድስት ስፖርቶች ህግና ደንብ ወጥቶላቸው እንዲካሄዱ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተለያዩ ክልሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች፣ የአሠልጣኝነትና የዳኝነት ሥልጠናዎችና የስፖርት ውድድሮች በማካሄድ ስፖርቱ ይበልጥ እንዲዘወተር ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ እነዚህን ተግባራት እያከናወነ ቢገኝም ለስፖርቱ እድገት የመንግሥት ድጋፍና ትብብር ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል።
በ1990 ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ ስፖርት ፖሊሲ ዜጎች በባህላዊ ስፖርት መሳተፍ እንዳለባቸው የተቀመጠ ቢሆንም ዘርፉ ከመንግስት እየተደረገለት ያለው ድጋፍ ግን በቂ እንዳልሆነም ገልጸዋል።
ፌዴሬሽኑ ከስፖርት ኮሚሽን በዓመት የሚያገኘው በጀት 410 ሺህ ብር ነው ሲሉም ተናግረዋል፤
በዚህ በጀት ስፖርቱን መምራት እንደማይቻል የሚናገሩት ኃላፊው ስፖንሰር የማፈላለግ ስራዎች በፌዴሬሽኑ በኩል ቢሰሩም በሚፈለገው መጠን ሊሳካ እንዳልቻለ ጠቅሰዋል።
የስፖርት ኮሚሽን የስፖርት ተሳትፎና ውድድር ዳይሬክቶሬት የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫልና ኩነቶች ባለሙያ አቶ ሃይለማርያም ታረቀኝ መንግስት ለባህል ስፖርት ባለው አቅም ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ይናገራሉ።
በአገር አቀፍ ደረጃ ስፖርቱን ለባህል ስፖርት ፌዴሬሽኑ ለውድድርና ስልጠና አስፈላጊውን የፋይናንስና የቁሳቁስ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ስፖርቱን የማስፋፋትና የማሳደግ ሃላፊነት ያለበት በመሆኑ ሀብት በማሰባሰብና ገቢ በማመንጨት ስፖርቱን ማሳደግ ይጠበቅበታል ይላሉ።
የባህል ስፖርቶችን ለማስተዋወቅ በስፋት መስራት እንደሚገባ፤ ይህም ለስፖርቱ ገቢ ለማግኘት እንደሚረዳ ነው አቶ ሃይለማርያም ያስረዱት።
በየዓመቱ የሚካሄዱ ውድድሮች እያደጉ በመምጣታቸው በተወሰነ መልኩም ቢሆን የባህል ስፖርት መነቃቃት እያሳየ መምጣቱንና ስፖርቱ የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ የጋራ ርብርብ እንደሚጠይቅም አንስተዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 2011