ነገር የት መቼ እንደሚከሰት አይታወቅም፤ አለመግባባት፣ ጠብ ማለቴ ነው። እኔን በቅርቡ ታክሲ ላይ አጋጥሞኛል። የበሳውን ላንሳ ብየየ ነው። ጧት ነው፤ ከሰፈር ታክሲ ይዤ ወደ ሜክሲኮ እየሄድኩ እያለ፤ በአምስት ብር መንገድ ላይ። ኪሴ ውስጥ ዝርዝር የሚባል አልነበረም። መቶ ብር ነው የያዝኩት፤ ለዚያውም የዘንድሮ መቶ ብር፤ የአስር ብር ግምት።
ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ስለነበር ጉዞው የእንፉቅቅ ነው። መሀል መንገድ ስንደርስ መሰለኝ ረዳቱ ሂሳብ ጠየቀ። ላስቸግርህ ነው፤ ዝርዝር አልያዝኩም ብዬ መቶ ብር ልሰጠው እጄን ዘረጋሁ። ኧረ… ፤ገና መውጣችን እኮ ነው ተባልኩ። አሁንም እንዲቀበለኝ ጠይቅሁ፤ ያልሰማኝ መስሎ ዝም አለ። ጉዳዩ ወደ አሽከርካሪው ደረሰ። እኛ ገና መውጣችን ነው፤ እንዴት በዚህ ሰአት መቶ ብር ይወጣል ሲል አሽከርካሪው ጉዳዩን አጋጋለው። ምን እዚህ… ተባልኩ።
ሁኔታው መቶ ብር ያወጣሁ ሳይሆን ጎራዴ የመዘዝኩ ነው ያስመሰለብኝ። በነጻ አሳፍሩኝ አላልኩ፤ ይቅርታ ገንዘብ አልያዝኩም ብል ምን ልባል ነበር ስል ለራሴው አሰላሰልኩ። የ‹‹ታክሲ ተራ ስድብ›› ይሰነዘረብኝ ጀመር፤ እንዳውም በቃ ውረድ ተባልኩና መኪናው ቆመ። ይኼኔ እኔም ስሜት ውስጥ ገባሁ። በሩ እንደ ተከፈተ ረዳቱን ይዤው ወረድኩ። ማን ያላቀን። የሆኑ ሰዎች ባይገላግሉን ብዙ ቦታ እንዳረስ ነበር።
አንድ ሰው ግን ሁላችንንም ሊያረጋጋን ሞከረ፤ አረጋጋን እንጂ። ግዴሌም ነገር አብርዱ አለን። ይህ ሰው ነገር ማብረድ ጥሩ ነው፤ ጋሼ ግዴለም እኔን ስሙኝ ሂሳቡ ተከፍሏል፤ ሁሉንም ነገር ይተውት አለኝ።
አሸከርካሪና ረዳቱንም አንዳንዴ እንደህ ያለ ነገር ሲያጋጥም ማለፍ ነው እንዳለባቸው ነገራቸው። መኪና ሲቆም ጊዜ ይባክናል፤ ደርሶ በመመለሱ ላይ ተጽእኖ ያሳድራል፤ በንዴት ማሽከርከር ሌላ ችግር ሊያስከትል ይችላል፤ በዚህ ላይ አለመግባባቱ ከቀጠለ ሌላም ችግር ይከተላል ሲል አስገነዘበ። ችግሩ ታክሲ ላይ እንደሚያጋጥምም ገልጾ፣ ብዙዎች ሂሳቡን ትተው ጉዟቸውን እንደሚቀጥሉም ነገራቸው። ሜክሲኮ ደርሰን፤ አብረን ወረድን።
እኔ ግን ገጠመኙን በህሊናዬ ማመላለስ ውስጥ ገባሁ። የውዝግቡ ምንጭ ዝርዝር አለመያዝ ነው። ዝርዝር እከሌ ይያዝ የሚል ህግ የለም። ሁሉም ቢይዙ ነገር ይቀላል። አንዱን ባለእዳ ማድረግ ግን ትክክል አይደለም። ይህ ሲሆን ውዝግብ ይነሳል። መብትና ግዴታን አለመረዳት ስለሚኖር።
ውዝግብ ሲነሳ በህግ የሚፈታበት አግባብ እንዳለ ሆኖ እዚያም ሳይደርስ ነገር አብርዱ በሚል መፍታት የሚቻልበት መንገድም አለ። ለደግ ሲባል መደራደር ውስጥ መግባት ያስፈልጋል። በአንድና በሁለት ብር የተነሳ አጥንት የሚሰብር ስድብም መሰንዘር የለበትም፤ ሲሰነዘር መስማት ግን ተለምዷል፤ ድብድብ ተከስቶ ጉዳት ደርሶ ያውቃል። ይምቱበት አይምቱበት አላውቅም እንጂ ሌባ ጎማ የሚመዙ አሽከርካሪዎችና ረዳቶችም ያጋጥማሉ። የአንድ ሺህ ወይም የመቶ ብሮች ኪሳራም መድረስ የለበትም፤ ግን ሲደርስ ይታያል። በር በሀይል በሚዘጉ ተሳፋሪዎች የተነሳ የበር መስታወት ተሰብሮ ያውቃል፤ በሩም የተሰበረበት ሁኔታ ያጋጥማል።
የመብትና የግዴታ ጉዳይ ለድርድር አይቀርቡም ብያለሁ። ይህን በሚገባ የማያውቁ ግን ሲያጋጥሙስ ፤ ይህን መተግበር የማይቻልበት ሁኔታ ሲፈጠርስ፤ አውቀው የሚጥሱ ቢኖሩስ። ያኔ ነገር አብርድ የሚባለውን መተግበር ብልህነት ነው። ይህ ሲተገበር በሁለት ብር የተነሳ የሺህ ብር ጉዳት አይደርስም፤ አንዱ ወገን ነገር ለማብረድ ሲል ከመብቱ ወይም ከግዴታው ያጎላል። ለዚያ ወቅት ማለት ነው። በቃ፤ ያ ቅጽበት ያልፋል። በሁለት ብር የተነሳ ደም አይፈስም፤ አካልም አይጎልም። ጨጓራም አይበግንም። ውድ ጊዜም አይባክንም፣ ሰብእናም አይጎዳም። በስሜት ላይም ጉዳት አይደርስም።
ሌባ ተያዘ ሲባል የሚፈጠረውን ትእይንት መቼም የማያውቅ አይኖርም። ሌባ ከተያዘ መደብደብ አለበት የሚሉ በርካቶች ናቸው። ሌባ ተይዞ ዱላ አይጠየቅም የሚለውን ይዘው ይሆን? ለሌባ ካለን ጥላቻ የተነሳ አንድ ሰው ሌባ ስለተባለ ብቻ ሌባ የተባለውን እንሰድባለን፤ እንማታለን። በዚህ አይነት ሁኔታ የሚቀጠቀጡ ሌቦች በርካታ ናቸው።
የሚገርመው ደግሞ ሌባ የተባለው ሰው እጅ ከፍንጅ ሲያዝ ያልተመለከትን፣ ማን እንደ ተሰረቀ፣ ምን እንደ ተሰረቀ የማናውቅ ድንገት አካባቢው ላይ የደረሰን ጭምር ሌባውን የማርያም ጠላት ብለን እንሰድባለን፤ እንመታለን። በሌለን በቂ መረጃ ላይ ተመሥርተንም ስለሌባው ለመጣው ሁሉ ማብራሪያ እንሰጣለን።
የእኛ ድርሻ ሌባውን ይዘን ለፓሊስ መስጠት መሆኑን እንዘነጋለን ወይም አናውቅም። ሌባ የተባለው ሌባ መሆን አለመሆኑን አጣርተው የሚደርሱት ፓሊስ እና አቃቢ ህግ ናቸው። ቅጣት የሚወስነውም ፍርድ ቤት ነው። እኛ መክሰስ፣ መረጃ መስጠት፣ መመስከር ነው ድርሻችን፤ ግን ይህን አናደርግም።
ሌቦች የሰረቁትን ሰው ሌባ ብለው በሚቀጠቅጡበት በዚህ ዘመን እኛም ሌባ አገኘን ብለን የምንማታ የምንሳደብ ከሆነ ሊደርስ የሚችለውን ችግር አስቡት። ሰው መጉዳት አለ፤ ነገር ወደራስ ዞሮም መጎዳት ሊኖር ይችላል። በቦታው ፓሊስ ደርሶ አፋፍሶ ሊወስደንና መጠየቅም ሊኖር ይችላል። በተገኘው ግርግር ውስጥ ዘሎ መግባት ሰውንም ራስንም ለጉዳት መዳረግ ነው።
እንዲህ አይነት ችግሮች ሲያጋጥሙ ሁሌም የሚሻለው ነገር አብርድ ብሎ ገላግሎ ችግር ሰምቶ፣ አስማምቶ ማለያየት ነው፤ አልያም ጉዳዩን ለፓሊስ ማሳወቅ ወይም እንዲያሳውቁ መርዳት።
በሀገራችን እዚህም እዚያም ለሚፈጠሩ ግጭቶች ምክንያቶቹ የህዝቡንና የሀገሪቱን ሰላም መሆን የማይፈልጉ ሀይሎች ቢሆኑም፣ ግርግር ውስጥ ዘሎ የመግባት መጥፎ ልማድም አለ። ልክ ሰውዬው ሌባ ስለተባለ ብቻ መደብደብ ውስጥ እንደተገባው ማለት ነው።
እነዚህ ሐይሎች ሰላም በመኖሩ ሳቢያ ጥቅማቸውን ያጡ በመሆናቸው በተቻለ መጠን ግርግርና ግጭት እንዲፈጠር ይፈልጋሉ። በሀገራችን ትንሽ ግርግር ሲፈጠር ዘለው የሚገቡ ብዙ መሆናቸውን የሚያውቁት ጠላቶቻችን ይህን ደካማ ጎናችንን እንደ መሳሪያ ሲጠቀሙበት ቆይተዋል።
እነዚህ ሀይሎች ግርግርና ግጭት እንዲነሳ እሳት ብቻ ነው የሚጭሩት። እኩይ አላማቸውን ያልተረዱ ወገኖች ንፋስም፣ ተቀጣጣይም በመሆን ያገለግላሉ። ከዚያ በኋላ ሁሉም እንደየፍላጎቱ ግጭት ውስጥ ይዋኛል። ፓለቲከኞቹ የራሳቸው አላማ አላቸው፤ አለመረጋጋት መፍጠርና መንግስትን ማሳጣት፤ ወደ ስልጣን ያመጣናል ብለው ያሰቡትን ለማሳካት አንድ መንገድ ይሆናቸዋል።
ለእዚህ የሚጠቀሙባቸው ያኮረፉ የፖለቲካ ሀይሎች አሉ። ሌሎች የግጭትን ወቅት ለዘረፋ ምቹ አድርገው የሚመለከቱም አሉ። የት ሆነው ሊበሉት እንደሆነ ባይታወቅም ይዘርፋሉ። ቂም የቋጠረም ካለ ይበቀልበታል።
በሀገራችን ከተቀሰቀሱ ግጭቶች የምንረዳውም ይህንን ነው። በተቆፈረልን ቦይ ሁሉ የመፍሰስ በሽታ አለብን። ቆም ብለን አናስብም። የጸረ ሰላሞች መሣሪያ እንሆናለን። ድንጋይ ሲወረወር አጎንብሰን ማሳለፍ ሲገባን ደረታችንን ነፍተን እንወጣለን። ነገር ማብረድን ትተን እናቀጣጥላለን።
በዚህ ምክንያት ሀገር እና ህዝብ ይደማሉ። ህግ ማስከበር ሲመጣ የሚሆነውን አስቡት። የግርግሩን አላማ ሳይገነዘቡ ዘሎ መግባት ዋጋ ያስከፍላል።
ነገር አብርዱ የሚል ያስፈልገናል። በዚያ ክፉ ቀንና አጋጣሚ ነገር አብርዱ የሚል ብናገኝ ነገሮችን ቆም ብለን ማየት እንችላለን። ነገር አብርድ የሚለውን እሴታችንን በሚገባ መጠቀም ይኖርብናል። አባቶቻችን እኮ ነገር አብርዱ እያሉ እየሸመገሉ፤ ነገሮችን ወደ ቀድሞ ይዞታው እየመለሱ ነው እዚህ ያደረሱን። ነገር እብርድ!!
ዘካርያስ ዶቢ
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2013