ሕፃን ልጇን ለመመገብ የኩላሊት ህመሟን ቻል አድርጋ ጎንበስ ቀና እያለች በእግረኛ መንገድ ላይ ዝንጅብል እና ነጭ ሽንኩርት የምትቸረችር አንዲት እናት፤ ከምርጫው በኋላ ማየት እና ማግኘት የምትፈልገውን ስትጠየቅ መልሷ የተወሳሰበ አልነበረም። በእርግጥ የእርሷ መሻት ለአንዳንዶች ተራ ጉዳይ ሊመስል ቢችልም ትልቁ ፍላጎቷ ‹‹ልጆቼ እና እኔ የምንመገበውን በቂ ምግብ ማግኘት፤ ለከባድም ሆነ ለቀላል ሕክምና ያለ እንግልት መታከም መቻል ነው›› የሚል ምላሽ ነው የሰጠችው።
እርግጥ ታማሚዋ እናት ከእርሷ አንፃር ፍላጎቷ ትክክል ነው። የምትፈልገው የቸገራትን ብቻ ነው። ነገር ግን በምርጫው ቅስቀሳ ይህን አደርጋለሁ ብሎ ቃል የገባው ፓርቲ የትኛው ነው? የሚል ጥያቄ ሲቀርብላት፤ ‹‹እኔ የፓርቲዎች ቅስቀሳ የሚባል ነገር ብዙ አይገባኝም፤ በቅርብ አግኝቻቸውም አላውቅም። ነገር ግን የእኔ ፍላጎት የትኛውም ፓርቲ መንግሥት ቢሆን የምፈልገው የሚያሳስበኝ የምበላውና የበሽታዬ ፈውስ ጉዳይ ብቻ ነው›› ብላለች። እርሷ የተመለከተችው ጊዜያዊ ችግሯን ነው። ይሄ ደግሞ ጥፋት አይደለም።
እርግጥ ነው፤ ይህች እናት ለዓመት ለምግብ የምታወጣውን ገንዘብ በአንድ ቀን በማጥፋት ለሚዝናና ሀብታም ዘርፎ ብቻ ሳይሆን ሰርቶ ሀብታም ለሆነው መልሷ ፈገግ ሊያደርገው ይችላል። ምክንያቱም ሁሉም የሚያስበው እንደአኗኗሩ እና እንደየደረጃው ነው። በእርግጥ ሰርቶ ሀብታም የሆነ የተንደላቀቀ ኑሮን የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ስንት ይሆን?… ያው መቼም ይሄ ጉዳይ እጅግ አጠያያቂ መሆኑ አይካድም። አንድ አጥኚ አካል ኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ ሀብታም ከሆኑ ሰዎች መካከል የትኞቹ ትክክለኛውን መንገድ የተከተሉና የሚከተሉ ናቸው ብሎ ቢያስጠና መልካም ነበር።
የኑሮ ደረጃ ጉዳይ ከተነሳ ደግሞ የኢትዮጵያ የገጠር አርሶም ሆነ አርብቶ አደሩ ኑሮው ከከተሜው ጋር የሚነፃፀር አይደለም። የተሻለ አቅም ያለው የገጠር ነዋሪ የሚፈረጥጠው ወደ ከተማ ነው። ይህን ከግንዛቤ በማስገባት በከተማ ያለው የኑሮ ደረጃ ከገጠር ካለው ጋር ልዩነቱን ላስተዋለው አስደንጋጭ ነው። አንዳንዶች እጅግ የተቀናጣ ዘጠኝ ቪላ ቤት ወይም ዘጠኝ ፎቅ ሲኖራቸው አንዳንዱ አንድ ሜትር አልጋ የምታዘረጋ ማደሪያ ቤት አጥቶ ይሰቃያል። ይህ ልዩነት የመጣው በሀብታሙ ጉብዝና በድሃው ስንፍና ነው ለማለት የሚዳፈር ካለ ዕዳውን ራሱ ይወጣው። ግብር ሳይከፍሉ እያጭበረበሩ እየነገዱና የመንግሥት ሠራተኞች ሆነው በሙስና ባጠራቀሙት ገንዘብ ሀብት የሚያካብቱ በበዙበት አገር አብዛኛዎቹ ሀብታሞቹ ለፍተውና እና ሰርተው በብቃታቸው በልጠው ዲታ ሆነዋል ለማለት ያዳግታል። እና የእነዚህ ሰዎች ፍላጎትስ ምን ይሆን? ከምርጫ በኋላ ብቃት ያለው ብቻ ለፍቶ ሀብት የሚገኝበት ሁኔታ መኖር እንዳለበት የሚገልፁትን ፓርቲዎች እና የፓርቲ ዕጩዎች በድምፃቸው ሳይቀጧቸው አይቀርም። ደግነቱ የእነርሱ ቁጥር ከድሃው ስለማይበልጥ፤ ድሃው የሚመርጠው ፓርቲ መንግሥት መሆኑ አይቀርም።
ድሃው ደግሞ የለፋ ብቻ ሀብታም የሚሆንበት አሠራር የሚዘረጋውን ይመርጣል ተብሎ ይገመታል። ያው መቼም እርግጠኛ መሆን ስለማይቻል ማለት የሚቻለው ይገመታል ነው። እርግጥ ነው ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› በሚል ማህበረሰብ ውስጥ ያደገ ባለሥልጣን ገና እንደተሾመ ተስፋው አጭበርብሮ ሀብት ማፍራት መሆኑ የእርሱ ብቻ ጥፋት አይደለም። የቤተሰቡና ያሳደገው ማህበረሰብ እርሱን የቀረፁበት የተንሻፈፈ መንገድ ያመጣው ተፅዕኖ ነው።
ስለዚህ ፓርቲዎች ይህንን ተፅዕኖ ተቋቁሞ ሊሰሩና ሊያሰሩ የሚችሉ ዕጩዎችን ከማዘጋጀት በተጨማሪ፤ በምረጡኝ ቅስቀሳቸው ላይ ፍትሃዊ የሀብት ተደራሽነትና እኩልነት ላይ እንደሚሰሩ ደጋግመው መግለፅ አለባቸው። ይሄንን በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ እያሉ እንኳን ጎዳና ላይ ላለችው ሽንኩርት ቸርቻሪ ቀርቶ ትምህርት ዘልቋታል ተብሎ በመንግሥት ተቋም ለተቀጠረውም የማይገባና ግራ የሚያጋባ የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን ማካሄዳቸው የሚያስተዛዝብ ነው። ቢመረጡ የሚሰሩትን በተጨባጭ በጥናት ላይ የተመሠረተ መረጃ ይዘው የሚያስቀምጡትን አቅጣጫ ለማብራራት ኅብረተሰቡ ድረስ ወርደው መቀስቀስ አለባቸው። ጆሮ ያሰለቸውን ያለፈውን የመውቀስ አንዳንዴም የማይገቡና የማይገቡ ጉዳዮችን መዘብዘብ ማቆም አለባቸው። ያለበለዚያ ‹‹የበላችው ያስተፋታል፤ በላይ በላይ ያጎርሳታል›› እንደሚባለው፤ አንዱ ፓርቲ ሃሳቡን ያስተላለፈበት መንገድ አሰልቺ እና ግራ የሚያጋባ ሆኖ፤ ሌላኛውም በዚያው መንገድ ከቀጠለ የትኛውም ሰው ለመምረጥ መቸገሩ አይቀርም። አነቃቂ፣ ተስፋ ሰጪ፣ ሞቅ ያለ ስሜት የሚነካ ቅስቀሳ ማካሄድ ነው የሕዝብን ልብ የሚገዛው።
አንዳንዶች ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን ግልፅ በሆነ መንገድ አያቀርቡም ሲባል፤ ብዙኃኑ ሕዝብ የማያውቃቸውን የአማርኛ ቃላትን ከመጠቀም አልፈው እንግሊዝኛ ቃላትን በመጠቀም ሕዝቡን ግራ ያጋባሉ። ፓርቲዎች ሕዝቡ የሚፈልገውን ተረድተው ምን ይህል ተዘጋጅተው ቀርበው እያስረዱ ነው? ከተባለ መልሱ ያጠያይቃል። ለምሳሌ የኑሮ ውድነትን እና የዋጋ ግሽበትን ጉዳይ ሲያነሱ ለአርሶ አደሩ እና ለብዙኃኑ የከተማ ነዋሪ ሙያዊ ቃላትን ይጠቀማሉ። ‹‹inflation እናስቆማለን›› ይላሉ። የዋጋ ግሽበት መኖሩን እና ምን ያህል እንደሆነ እንዲሁም በምን መንገድ የኑሮ ውድነት ዕድገትን ለመግታት ወይም ለመቀነስ ምን እንደሚሰሩ በትክክል አያብራሩም። የዋጋ ግሽበቱን በምን ያህል ጊዜ? በምን መልኩ? እንደሚቆጣጠሩ በግልፅ ለሁሉም በሚገባው በቀላል ቃላት በጥናት ላይ ተመስርተው ማስረዳት ሲገባቸው ብዙዎቹ ያም ታታሉ።
በእርግጥ አንዳንዶቹ ፓርቲዎች የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ ምርት በብዛት እንዲኖር እናስችላለን ይላሉ። ነገር ግን ምርት የሚጨምረው በምን መልኩ ነው? ለሚለው ጥያቄ ተጨባጭ መልስ በዝርዝር ሲሰጡ አይስተዋልም። በፊት የተሰራው ለምን አልተሳካም? ኢንቨስተርን በማሰማራት ከሆነ በምን መልኩ ይካሄዳል? እንደተለመደው በተበጣጠሰ የአርሶ አደር መሬት በምርጥ ዘር ለመጠቀም ከሆነ በምን መልኩ ይተገበራል? በማዳበሪያ ምርት ለማሳደግ ታስቦ ከሆነ እንዴት የምርት መጠን እንደሚያድግ በተለይ አርሶ አደሩ በሚገባው መልኩ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። ይህ ሲባል ‹‹አርሶ አደሩን በበሬ ከማረስ እናላቅቃለን›› ሲሉ ይህንን ጉዳይ ተግባር ላይ የሚያውሉት እንዴት ነው? ያው ለማለት ወይም ለመመረጥ ብቻ ማለት አያዋጣም። ሊሆን የሚችለውን እና በትክክል ለመተግበር የታሰበውን በማለት አማራጮችን ማብራራት ሲገባ፤ ድፍን አረፍተ ነገሮችን እየተናገሩ ሕዝብን ማዳፈን የብዙ ኢትዮጵያውያንን ጥያቄ መረዳትም አይደለም።
ምርጫን እያሰቡ የአገሪቱን ከ85 በመቶ ያላነሰ ወደ 90 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብን ማዕከል አለማድረግ እብደት ነው። አዎ! ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በተጨባጭ በቀጣይ 5 ዓመታት የአርሶ አደሩን ጥቅም ለማስጠበቅ ምን ያደርጋሉ? ለአርሶ አደሩ ሊገልፁለት ይገባል። ምርቱ እንዲጨምር ብቻ ሳይሆን፤ መሬቱን እንደማያጣ ማስተማመኛ መስጠት ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት ሕይወቱ የሚቀየርበትን መንገድ አስመልክቶ በምን መልክ እንደሚሰሩ ማሳወቅ አለባቸው። አርሶ አደር ብቻ አይደለም አርብቶ አደሩም ሕይወቱ የሚቀየርበትን ሁኔታ በሚመለከት በግልጽ ቋንቋ ለሁሉም በሚገባ መልኩ አቅጣጫቸውን መግለፅ ከፓርቲዎቹ ይጠበቃል። የሕዝብ ተጠቃሚነትን አስመልክቶ ሲቀሰቅሱና ቃል ሲገቡ በመገናኛ ብዙኃን ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የስብሰባ መድረኮችን በማዘጋጀት ታች ያለው ሕዝብ ድረስ ወርደው ማሳወቅ ካልቻሉ አርሶ አደሩም ሆነ አርብቶ አደሩ ለመምረጥ መቸገራቸው አይቀርም ።
ሌላው የአገሪቱን 22 በመቶ የሚሆነውን አካል ጉዳተኛ ፓርቲዎቹ ቢመረጡ ምን ያደርጉለታል? የሚሰሩለት በምን መንገድ ነው? ለአካል ጉዳተኞች ምን ዓይነት ሕግ ይወጣላቸዋል? አራት ፎቅ ያለው ሕንፃ ቀርቶ ስድስትና ስምንት ፎቅ ያለው ሕንፃ ሊፍት ሳይገጠምለት የንግድ ቦታ፤ የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ወይም የመኖሪያ ቤት በመሆን ላይ ይገኛል። የአካል ጉዳተኛው እንዳይዘነጋ ምን ዓይነት ሕግ ያወጣሉ? ሕጉን ተግባራዊ ለማስደረግ ምን ያህል ይተጋሉ? ይህንን አስመልክቶም ብዙ እንዲሉ ቢጠበቅም አካል ጉዳተኛውን የዘነጉት ይመስላል። የፓርቲ መሪ እና አባል የሆነው የዛሬ ጤነኛ ግለሰብ ነገ አካል ጉዳተኛ የሚሆንበት አጋጣሚ ሊፈጠር እንደሚችል መገመት ቢቻልም፤ አንድ ተወዳዳሪ ፓርቲ ስለአካል ጉዳተኞች ስለ 21 ሚሊዮን ዜጎች መዘንጋቱ ያስተዛዝባል። ብዙዎቹ በምረጡኝ ቅስቀሳቸው ይህን ሲሉ አልተደመጡም።
በሌላ በኩል የአገሪቱን ከ51 በመቶ በላይ ቁጥር የያዙትን ሴቶች ፓርቲዎች እያስታወሷቸው አይመስልም። እርግጥ ነው በዘንድሮ ምርጫ የማይናቅ ቁጥር ያላቸው ሴት ዕጩዎች ለውድድር እንደሚቀርቡ ፓርቲዎቹ በየአደባባዩ ከለጠፏቸው ፖስተሮች አይተናል። ነገር ግን ሴቶች የሚከበሩበትን ሕግ ከማውጣት ባሻገር በትክክል ከልጅነታቸው ጀምሮ ሴቶች በቤት ውስጥ ከወንዶች እኩል የሚታዩበትን ሁኔታ እንዴት እና በምን መልኩ እንደሚያመቻቹ ሲናገሩ አልታየም። ተወዳዳሪ ፓርቲዎቻችን ሰው ሰው የሚሸት ለሰው የቀረበ ቅስቀሳ በማድረግ በትክክል እየተወዳደሩ መሆኑን እያሳዩ አይደለም የሚባለው ለዚህ ነው።
ስለዚህ ፓርቲዎቻችን ወደ ሰው ሕይወት ቅረቡ። ስለነጋዴው ስለ መንግሥት ሠራተኛው ስለሥራአጥ ወጣቶች፣ ስለተማሪዎች እና ስለሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች የምሰሩትን ግለፁ። ስለነጋዴዎች ሲገለፅ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ግብር የሚከፍልበትን፤ የነፃ ገበያ ሥርዓት ሲተገበር በአግባቡ የሚሆንበትን ፓርቲው ለሸማችም ሆነ ለነጋዴው ሁሉንም እንደዜጋ በአግባቡ የሚያይበት ሁኔታ እንደሚኖር ይህንንም አስመልክቶ እንደሚሰሩ መግለፅ ይጠበቅባቸዋል። በንግዱ አካባቢ ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለማቃለል የሚሰሩ ሥራዎችን በሚመለከትና ሌሎችም ከንግድ ዘርፉ ጋር ተያይዞ ያለውን የሙስና ችግር ለመቀነስ የሚሰራበትን ሁኔታ በሚመለከት በዝርዝር መናገር አለባቸው።
በአገልግሎት መስጫ ተቋማት ያሉ የመንግሥት ሠራተኞች በተለያየ መልኩ የኑሮ ደረጃቸው የሚሻሻልበትን እና እነርሱም አገልግሎት ሲሰጡ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ የሚሰሩበትን አሠራር እንደሚዘረጉ በዝርዝር ማሳወቅ ይገባቸዋል። ለሥራ አጥ ወጣቶች ዘላቂ የሥራ ዕድል የሚፈጠርበትን ሁኔታ በዝርዝር እንዲናገሩ ቢፈለግም እየተናገሩ ያለው ቁንፅል መሆኑ የውድድሩ ግለት ቀዝቅዞ እንዲቀጥል እያደረገ በመሆኑ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ውድድሩን የሕዝብ ቀልብ የሚስብ አጀንዳ ይዛችሁ በመምጣት ሞቅ አድርጉልን እንላለን።
ከተሜው ከተቸገረባቸው ጉዳዮች መካከል ቤት ዋነኛው ሲሆን፤ ከቤት በተጨማሪ የትራንስፖርት አቅርቦት ጉዳይንም በዘላቂነት መፍትሔ የሚያበጁለት እንዴት እንደሆነ ተወዳዳሪዎቹ ፓርቲዎች እንዲገልፁልን እንፈልጋለን። መገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ ሌሎችም የዴሞክራሲ ተቋማት የተሻለ ነፃነት እንዲኖራቸው እንደሚሰሩ ማሳወቅን ጨምሮ ሌሎችም የመራጩን ሕዝብ ፍላጎት በትክክል በመረዳት ለሁሉም እንደየድርሻው በምን መልኩ እንደሚሰሩ በግልፅ ማስቀመጥ ካልቻሉ መራጩ ሕዝብ ምን ተረድቶ ማንን ይመርጣል የሚለው ጥያቄ አደናጋሪ ይሆናል።
ብሔርና ሃይማኖት እየመረጡ መደገፍና መምረጥ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። ፓርቲዎች የሚመረጡት በሃሳብ የበላይነት እንጂ በብሔር መሆን የለበትም። ፓርቲዎች ሕዝቡ የጠራ አቋም ይዞ እንዲመርጣቸው ከምርጫ በኋላ የሚያመጡትንና የሚሰሩትን በግልፅ ማስቀመጥ አለባቸው፤ በትክክል ምን እንደምታደርጉ ግለፁ እኛም በሰላም ከቆየን ቃል የገባችሁትን ማድረጋችሁን መርምረን በዚህ ምርጫ ብቻ ሳይሆን በቀጣይም ምርጫ እንመርጣችኋለን። ቃል የገባችሁትን ካላደረጋችሁ ደግሞ ዘንድሮ ብንመርጣችሁም በቀጣይ ሌላውን መርጠን የጀመራችሁትን ሳትጨርሱ ከምትቀሩ ከወዲሁ የሚሰጣችሁን ዕድል ተጠቀሙበት እንላለን።
ዋናው ጉዳይ ተወዳዳሪዎች ሁሉ መርሳት የሌለባችሁ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚፈልገው ዋነኛው ሰላም ነው። አሁን ላይ የሰላም ጉዳይ መላው ኢትዮጵያውያንን እያስጨነቀ ይገኛል። በእርግጥ ፓርቲዎች በምረጡኝ ቅስቀሳቸው ስለሰላም መግለፃቸው የሚካድ አይደለም። ነገር ግን ፓርቲዎች አሁን ሰላም የለም ከማለት በዘለለ፤ ቢመረጡ ሰላምን የሚያመጡት እና የሚያረጋግጡት እንዴትና በምን መንገድ ነው? እነርሱ የሚያመጡት ሰላምስ የሚቀጥለው እንዴት ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች በደንብ እያብራሩ ማሳመን ላይ ክፍተት እየታየ ነው።
ሰላም ለማስፈን እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ነገር ግን ሰላም አሰፍናለሁ ከማለት ያለፈ ዝርዝር ጉዳይ ያስፈልጋል። ሰላም የሚሰፍነው በንግግር፣ በጦርነት ወይስ በምን መልኩ ነው? ሂደቱ እንዴት ይሆናል? በእርግጥ የችግሩ ምንጭ ምን እንደሆነ ፓርቲው አጥንቷል? ካጠና ያገኘው ግኝት እና ችግሩን ለመፍታት በጥናት ላይ የተመሠረተ ምን ዓይነት ሥራ ይሰራል? ወይስ ‹‹ዶሮ ብታለም ጥሬዋን›› እንደሚባለው ሁሉ ሃሳብና ህልማቸው ሥልጣን ብቻ በመሆኑ የሚናገሩት እንዲሁ ሰላም እናሰፍናለን ማለት ብቻ ነው? ዜጎች ተንቀሳቅሶ የመስራት መብታቸው ተገፏል ከማለት በዘለለ፤ ተመራጭ ሆነው ሲቀርቡ ከተመረጡ በትክክል ዜጎች የመንቀሳቀስ መብታቸው ተጠብቆ በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ ተንቀሳቅሰው ሀብት የሚያፈሩበትን ሁኔታ ማመቻቻት ላይ የሚሰሩት እንዴት ነው? ይህን የሚያደርጉት የትኛውን መንገድ ተከትለው ነው? የሚለውን ማብራራት ላይ ክፍተት ይታያል። ስለዚህ ይህንን ክፍተት አሻሽሉልን እንላለን።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2013