ሰሞኑን ታዋቂ የሆነው አንድ ዘፈን ያስተላለፈው መልዕክት የብዙዎችን ቀልብ ስቧል። ምክንያቱም ጉዳዩ መላው ኢትዮጵያውያንን የሚነካ ነው። ዘፈኑ ሲጀምር ‹‹ዲሽታጊና›› ይላል። ትርጉሙን ብዙ ሰው ባያውቀውም በዘፈኑ ስንኞች መሃል የሚደመጡ የአማርኛ ቃላት እና አስደሳች ዜማው ብዙዎች ለዘፈኑ ትኩረት እንዲሰጡ አስገድዷቸዋል። በዘፈኑ መሃል ከሚደመጡ ቃላት መካከል አንድ ጥያቄ አዘል ሐረግ በድምፃዊው አንደበት በሚደንቅ ዜማ ተላልፏል። ‹‹ማን ነው ያለው ምርጥ ዘር?›› ሲል ይጠይቃል። ሁሉም ወደ ምድር የመጣው ተወልዶ ነው። የሚሄደውም ብቻውን ባዶውን የሚለየን በሞት ነው በማለት ሁሉም ሰው እኩል መሆኑን ያወሳል።
ነገር ግን ብዙዎች ራሳቸውን ለይተው፤ ‹‹ጥርት ያልኩኝ ምርጥ ዘር ነኝ፤ የተፈጠርኩት ከወርቅ ብሔር ነው›› ሲሉ ይደመጣል። ምናልባት ሰዎች የዚህ ብሔር ነኝ ብለው ቢያምኑም እውነታው ሌላ ነው። የትኛውም ኢትዮጵያዊ ሦስት አራት ትውልድ ወደ ኋላ ቢቆጠር የሌላ ብሔር ውስጥ ደሙ መቀላቀሉ አያጠራጥርም። ብዙ ኢትዮጵያውያን ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በትዳር ይዛመዳሉ። ምክንያቱም የሚያገናኛቸው ሰው መሆናቸውና በሀሳብ መግባባታቸው እንጂ የሆነ ብሔር ተወላጅነታቸው አይደለም። መርጦ የተወለደ እንደሌለ ሁሉ። ለትዳር የምፈልገው የዚህን ብሔር ተወላጅ ነው ብሎ አስቦ ያገባ የተሳካለት ብዙ አለ ለማለት ያዳግታል። ስለዚህ የአንድ ብሔር ብቻ ተወላጅነት አለ ብሎ መከራከር ይከብዳል።
ዘፋኙ እንደገለፀው፤ ምርጥ ተብሎ የተለየ ቆሻሻ ተብሎ የሚገለል ብሔር መኖር የለበትም። ምክንያቱም ሁሉም ሰው እኩል ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ሰርገኛ ጤፍ ላንለያይ የተደባለቅን ነን። ‹‹ጥርት ያልኩኝ ነኝ›› ማለት አያምርብንም፤ አይሆንም፤ ደግሞም አይደለንም። እሩቅ ሳንሄድ የራሴን ብሔር ላንሳ፤ ዘመዶቼ ብዬ ሳጣራ ኢትዮጵያውያን ምን ያህል የተደባለቅን እንደሆንን ማረጋገጥ ችያለሁ። ጉራጌ፣ አማራ፣ ኦሮሞ እያለ ዝምድናው በራቀ ቁጥር ወደ ኋላ ሲኬድ ትግሬ እና ሌላም ብሔር በእኔ ደም ውስጥ መኖሩን አረጋግጫለሁ።
ብሔር ብቻ አይደለም፤ የተለያየ ሃይማኖት ያላቸው ሰዎችንም በትዳር ተዛምጃለሁ። ታዲያ የቱ ላይ ሆኜ ጥርት ያልኩ ነኝ ከሌላው ዘር የተለየሁ ነኝ በማለት ሌላውን ላንቋሽሽ? የቱ ላይስ ተቀምጬ ይህ የተሻለ ዘር ነው እንዴት ማለት እችላለሁ? እኔ ኢትዮጵያዊ ስለሆንኩ ይህንን ማለት አልችልም።
ዓለም አንድ መንደር እየሆነች ጥቁርና ነጭ እኩል ናቸው እየተባለ በሚዘመርበት ጊዜ፤ እኛ የጥቁር ፈርጥ ምርጥ አፍሪካዊ ነን ከማለት ወርደን ብሔር ሥር ስንወተፍ እጅግ ያሳዝናል። በእርግጥ አካባቢውን የሚጠላ አለ ብዬ አላስብም። አገር ደግሞ ከእኛ ሰፈር ትተልቃለች። የአካባቢዬን ስም መጥራት ክፋት የለውም፤ ከዓለም አንፃር ሲታይ ደግሞ ኢትዮጵያም ታንሳለች፤ ለዓለም ‹‹አፍሪካዊ ነን።›› እንላለን። ስለዚህ ከፍ ብሎ ማየት ያስፈልጋል። የእኔ ብሔር ምርጥ ነው እያለ በብሔሩ ለመነገድ የሚፈልግ በሰፈሩ ጠባብ ምልከታ ጥላቻን የሚዘራ ያላዋቂነት መገለጫ ነው። ይህ ሰው ሰፈሩንና አገሩን ብቻ ሳይሆን እራሱንም ይወዳል የሚል እምነት የለኝም። ምክንያቱም እርሱ የሚፈልገው ዛሬን እንጂ ነገን አይደለም። ስለማንም አይጨነቅም።
አገራችን ባትኖር አካባቢያችን አይኖርም። በእርግጥ ቀድመን ስለአገር ማሰብ አለብን። ለአገር ለወገን የሚጠቅም ሃሳብ እና ፕሮጀክትን አምጥቶ ለብሔር ሳይሆን ለዓለም አስቦ መተግበርን በውጤቱ መደሰት ለጥቂት ሳይሆን ለብዙ መሆን ብዙ ደስታን ይሰጣል። ነገር ግን የአንዳንድ ተማርን ባይዮች ሀሳብ ከዚህ የተለየ መልክ ይዟል። ከሰፈር ሳይወጡ ብዙዎችን ሰፈርተኛ ያደርጋሉ። የእነርሱ ሊበቃ ሲገባ ሌሎችን አጥብበው ለአገር ሌላ ዕዳ ያስቀምጣሉ።
በተለይም በማኅበዊ ትስስር ገጽ ላይ የአዋቂነት ልኬት የሚያውርዱ ጽሑፎች እና ንግግሮቻቸው ላይ የሚዘሩት የማይጠቅም ሀሳብ አንዳንዴ ‹‹ምነው ኢትዮጵያዬ የወላድ መካን ሆነች›› ያስብላል። የእነርሱ ተከታዮች የአላዋቂ ሳሚ እንዲሉ ከእነርሱ ብሰው ቁጭ ይላሉ። በእርግጥ ብሔርን እና አገርን መውደድ መልካም ነው። ነገር ግን በማሰብ ስለትብብር ስለአብሮነትና ስለመደጋገፍ ሲነሳ ኢትዮጵያም የምትጠበን ናት። ምክንያቱም ብዙዎች ለአገር ብቻ ሳይሆን ለዓለም ተርፈው ታይተዋል።
ሰው ማለት አገርን ብቻ ሳይሆን ዓለም ላይ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል አዕምሮ ያለው ትልቅ ባለፀጋ ነው። ታዲያ ይህንን አዕምሮ በብሔር ውስጥ ወሽቆ አገር ማፍረሻ ማውጠንጠኛ መሣሪያ ለምን ያደርገዋል? አገርን እንደመጠበቅ አገር ለማፍረስ ተደጋጋሚ ስህተት ውስጥ መግባት በእርግጥ ዕውቀት ሳይሆን መሃይምነት፣ ታላቅነት ሳይሆን ትንሽነት ነው። ከመነጋገር ይልቅ ተጠላልፎ መጣጣል፤ ከመከባበር ይልቅ መናናቅን መርህ ማድረግ ለማንም አይጠቅምም።
ሃሳብን በሃሳብ ከመሞገት ይልቅ፤ ጠርዙን ይዞ መሃሉን ዘሎ መዘላለፍ በብሔርና በሃይማኖት እየወረዱ መዘላለፍ የልቦናን እግር ከስሌት ይልቅ በስሜት እየነዱ መራመድ የአገርና የትውልድ ዕዳ እንደመሆን ነውና መጠንቀቅ ያሻል።
ልጆቻችን የነገ የዓለም ተስፋዎች ናቸው። እየሄድንበት ያለው መንገድ ካልተስተካከለ ራሳችንን ከብሔር ጥቅም አንፃር ሳይሆን ከዓለም፤ አለፍ ሲል ከአገር አንፃር የምናስብ መሆናችንን ካላስገነዘብናቸው የእኛ ብቻ ሳይሆን የአገራችን መጨረሻም ያሰጋል። ከሕዝብ ብዛታችን አንፃር ሰፋ አድርገን ካየነው የዓለም ስጋት እንዳንሆን፤ እራሳችንን ከዕልቂት እንጠብቅ። ለትውልድ የሚተርፍ ነቀርሳ ተክለን አንለፍ። ራሳችንን አሳንሰን አዕምሯችንን ለጥፋት ከመጠቀም ይልቅ ለአገርና ለዓለም በሚተርፍ ሥራ ላይ እናውለው። ትልቅ ነንና ትንሽ አንሁን። ሰላም!
ናኮር ከአዲስ አበባ
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2013