የመወዳደሪያ እድሜው ገና በወጣቶች ጎራ እያለ ከእድሜ ታላላቆቹ ጋር በታላላቅ የውድድር መድረኮች ጠንካራ ተፎካካሪ መሆን የቻለው አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ ከዚህ ቀደም በርካታ ጊዜ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የነገው ተስፋ እንደሚሆን ተነግሯል። ዮሚፍ ይህንን በተግባር ማሳየት የቻለውም ከሁለት ዓመት በፊት የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ፖርትላንድ ዩጂን ላይ ሦስት ሺ ሜትሩን 7፡57፡21 በሆነ ሰዓት አሸንፎ ወርቅ ሲያጠልቅ ነበር።
ዮሚፍ ይህን ድሉን በበርሚንግሃም የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ላይ8:14.41 በሆነ ሰዓት ማስጠበቅ ችሏል። በውድድሩ ላይ ያሳየው ድንቅ ብቃትና በተፎካካሪዎቹ ላይ የወሰደው የበላይነት ከእድሜው አኳያ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ውጤት በጠፋበት አምስትና አስር ሺ ሜትር ቀነኒሳን የሚተካበት ወቅት እንደተቃረበ ማሳያ ነው። በዚህ ውድድር ብቻም ሳይሆን በዋናው የዓለም ቻምፒዮናም ይህን ማሳየት የቻለ አትሌት በመሆኑ ብዙዎች ተስፋ አድርገውበታል።
ቁመተ ለግላጋው ባለተሰጥኦ አትሌት በወጣቶች ቻምፒዮና ከአፍሪካ እስከ ዓለም ቻምፒዮና እንዲሁም በዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳየ የሚገኘው ድንቅ ብቃት የነገ የኦሊምፒክ ተስፋነቱን ያረጋግጡለታል። ዮሚፍ ሪዮ ኦሊምፒክ ላይ ሜዳሊያ ማጥለቅ ባይችልም በመድረኩ ያለውን ልምድ አንድ ደረጃ ከፍ ማድረግ ችሏል። የብቃቱ ጥግ ላይ ለመድረስ እየተንደረደረ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ከእድሜው አኳያ ብዙ ርቀት ተጉዟል ማለት ይቻላል።
ይህ ወጣት አትሌት ካለፈው ወር አንስቶ በተለያዩ የዓለማችን ከተሞች እየተካሄዱ በሚገኙ የዓለም የቤት ውስጥ የዙር ውድድሮችም አስደናቂ ብቃት በማሳየት ትግሉን ከሰዓት ጋር አድርጓል። ከሳምንት በፊትም በዚሁ በቤት ውስጥ የዙር ውድድር በአሜሪካ ሚልሮስ ጨዋታዎች የአንድ ማይል የቤት ውስጥ የዓለም ክብረወሰን ለመስበር ተቃርቦ በሽርፍራፊ ሰከንዶች ሳይሳካለት ቀርቷል። የዚህ ርቀት የዓለም ክብረወሰን ዮሚፍ ከመወለዱ ከስድስት ወራት በፊት እኤአ 1997 በሞሮኳዊው ድንቅ አትሌት ሂቻም ኤልግሩዥ የተያዘ ሲሆን፣ ዮሚፍ ክብረወሰኑን ለመስበር ያደረገው ትልቅ ጥረት 3:48.46 በሆነ ሰዓት ውድድሩን እንዲያጠናቅቅ አስችሎታል። ይህ ሰዓት ግን የቀድሞውን ክብረወሰን ለመስበር በዜሮ ነጥብ ዜሮ አንድ ማይክሮ ሰከንድ የዘገየ በመሆኑ እድለኛ ሳይሆን ቀርቷል።
ዮሚፍ ለጥቂት ባለመለጠው ክብረወሰን ቁጭት ውስጥ ሆኖ በሌላኛው የቤት ውስጥ የዙር ውድድር ዛሬ በበርሚንግሃም ላይ በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር የሚያደርገው ፉክክር በጉጉት ይጠበቃል። ዮሚፍ ከሳምንት በፊት ሞክሮ ያልተሳካለት የኤልግሩዥ የማይል ክብረወሰን ቢሆንም በሳምንት ልዩነት የኤልግሩዥን ሌላ ክብረወሰን የማሻሻል እድል ገጥሞታል። የአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር የቤት ውስጥ ክብረወሰን በኤልግሩዥ 3:31.18 በሆነ ሰዓት የተያዘ ሲሆን፣ ይህን ክብረወሰን ያስመዘገበው የማይል ክብረወሰኑን ካስመዘገበ ከአስር ቀናት በኋላ ነበር። ዮሚፍ የማይል ክብረወሰኑን ባያሳካም ከኤልግሩዥ ጋር ሊጋራው የሚችል ተመሳሳይ ታሪክ ገጥሞታል።
በዛሬው ውድድር ዮሚፍ ክብረወሰን ለማሻሻል የተሻለ እድል እንዳለው ከተፎካካሪዎቹ ጥንካሬ አኳያ ከወዲሁ ቅድመ ግምቶች እየወጡ ይገኛሉ። በዚህ ውድድር በዘንድሮው ዓመት የቤት ውስጥ የዙር ውድድሮች በተለያዩ ሦስት ከተሞች ማሸነፍ የቻሉ ሦስት አትሌቶች ተካተዋል። የመጀመሪያው ጠንካራ ተፎካካሪ የአስራ ዘጠኝ ዓመቱ ኢትዮጵያዊ አትሌት ሳሙዔል ተፈራ ሲሆን፣ ከሳምንት በፊት ርቀቱን ፈጣን በተባለለት 3:35.57 ሰዓት ቶረን ላይ ማሸነፉ ይታወሳል። ማድሪድ ላይ አሸናፊ የነበረው ቢትዌል ቢርገን እንዲሁም ካርልሹር ላይ ማሸነፍ የቻለው ቪንሰንት ኪቤት በዛሬው ውድድር ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁ ኬንያውያን አትሌቶች ናቸው።
በተለይም በተመሳሳይ መድረክ ባለፈው ዓመት በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና በርሚንግሃም ላይ በወንዶች አንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቅ ክስተት የነበረው ወጣቱ አትሌት ሳሙዔል ተፈራ ከዮሚፍ ጋር የሚያደርገው ፉክክር ትልቅ ትኩረት አግኝቷል። በርቀቱ ብልጭ ድርግም የሚለውን የኢትዮጵያ ተስፋ ዳግም እንዲያንሰራራ ያደረገው ሳሙዔል ከመሆኑ አኳያ የተሰጠው ግምት ቀላል የሚባል አይደለም። በታላላቅ የውድድር መድረኮች የማናውቀው ሳሙዔል ተፈራ ድንገት ባለፈው ዓመት በቤት ውስጥ የዓለም ቻምፒዮና ልምድ ያላቸውን አትሌቶች ያሸነፈበት መንገድም ኢትዮጵያ ጠንክራ
ከሠራች ስኬታማ እንደምትሆን ያሳየ ነበር።
ይህ አትሌት በርቀቱ እኤአ ከ2012 ቱርክ ኢስታንቡል ደረሰ መኮንን ካስመዘገበው ውጤት ወዲህ የመጀመሪያው ሲሆን፣ በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ወርቅ ሲያስመዘግብ ከኃይሌ ገብረስላሴና ደረሰ መኮንን ቀጥሎ ሦስተኛው አትሌት ነው። አገር አቀፍ ውድድር አሸንፎ በለንደን ቻምፒዮና ኢትዮጵያን መወከል የቻለው ሳሙዔል በወጣቶች የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና በእድሜም በልምድም ከሚበልጡት የዓለማችን ጠንካራ አትሌቶች ጋር ተፎካክሮ ማሸነፍ ብቻም ሳይሆን ከሃያ ዓመት በታች የዓለም ክብረወሰንን 3፡ 36፡05 በሆነ ሰዓት የግሉ ማድረግ የቻለ ጠንካራ አትሌት ነው። ሳሙዔል ከመነሻው አንስቶ ብቃቱን እያሳደገ በትልቅ ደረጃ ቻምፒዮን እስከመሆን የደረሰ አትሌት መሆኑ ወደ ፊትም በትልቁ የዓለም ቻምፒዮናና ኦሊምፒክ መድረኮች ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት አትሌት መሆን ችሏል።
አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 2011
ቦጋለ አበበ