ኑሮን መኖር ከጀመርን ሁላችንም አሳዛኝ ክስተት እንደሚገጥመን ሁሉ አዝናኝና አስደሳች ሁኔታዎችንም ማስተናገድ አንዱ የህይወት ገፅታ ነው፡፡ ለዛሬው አሳዛኙን የህይወት ገጠመኞቻችንን ልተውና ስለሚያዝናኑንና ሁሌም እያስታወስን ስለምንስቅባቸው የህይወት ገጠመኞቻችን እናውጋ፡፡ ሁላችንም እንዳደግንበትና እንደየአካ ባቢያችን ሁኔታ ባህሪያችንም ይለያያል፡፡ ይህንንም የሚያረጋግጥልን አመለካከታችን፣ ተመሳሳይ ለሆነ ነገር ያለን የየግል አስተያየት፣ በጥቅሉ በሁሉም ሊያስብል በሚያስችል ሁኔታ የሰው ልጅ የሚገነባው ተወልዶ ባደገበት አካባቢና ማህበረሰብ ነው፡፡ ለምሳሌ ገጠር ተወልዶ ያደገ ልጅ ድንች፣ ወተትና የባቄላ እሸት ወዘተ ስጡኝ እያለ ያለቅሳል እንጅ መቼም እንደ አዲስ አበባ ልጅ ኬክ፣ ክሬም፣ ፒዛና በርገር ካልተገዛልኝ ብሎ አያለቅስም፡፡
በከተማውና በገጠር መካከል ያለው ልዩነት የተለመደና ፀሐይ የሞቀው አገር ያወቀው ጉዳይ ነው፡፡ የሚገርመው ነገር ግን ከገጠርም መካከል ቆለኛው ደገኛውን፣ ደገኛው ደግሞ ቆለኛውን ሲተርበው መስማታችን ነው፡፡ በአጠቃላይ አንዳችን ለአንዳችን ጉድለቶቻችንን ነቅሰን በማውጣት ገነው እንዲወጡ ለማድረግ እንጥራለን፡፡
አንድ ከተማ የሚኖር ሰው ወደ ገጠር የአገራችን ክፍል ቢወጣ በሚያያቸው ነገሮች ሁሉ መደነቁ አይቀርም በተለይ ደግሞ ጫማ ሳይጫሙ ጅራፍ እያጮሁ ከብቶችን የሚያግዱ ህፃናትን ሲያይ በጣም መደነቁ አይቀርም፡፡ እንደዚሁም ከገጠር ዱላውን እንደያዘ አዲስ አበባ ሲገባ የሚያያቸው ነገሮች በሙሉ አስቧቸውና ገምቷቸው የማያውቃቸው ይሆኑና
መስሎ አይታየውም፡፡ ወደ ተነሳሁበት አብይ ጉዳይ ልመልሳቹህና የገጠር ባህሪዎቼን ከከተማ ኑሮ ጋር ለማስማማትና ለማስተዋወቅ ስዋትር የገጠሙኝንና አጀብ ያሰኙኝን ጉዳዮች ልንገራቹህ፡፡
በጊዜው ይገጥሙኝ የነበሩት ጉዳዮች እኔን ከማስገረም አልፈው ብዙዎችን በእኔ ላይ ፈገግ እንዲሉ ምክንያት ሁነው አልፈዋል፡፡ ታዲያ ይህ ጉዳይ ማንኛውንም ሰው ከገጠር እንደመጣ አዲስ አበባ ውስጥ ሊገጥሙት የሚችሉ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ገጠር እያለሁ መኪና የማየው ከወር አንድ ጊዜ አልያም እንደነገሮች ክስተት ነበር፡፡ ወፍጮ ቤት ወይም ገበያ በምላክበት ጊዜ ከተማዋን መሃል ለመሃል ሰንጥቋት በሚያልፈው መንገድ ዳር ለረጅም ደቂቃዎች በመቆም አነስ ያለች የኤንጅኦ ወይም አምቡላስ መኪና አይቼ እመለሳለሁ፡፡ታዲያ የዛን ቀን መንፈሴ በደስታ ይፍነከነካል፡፡ በተለይ ደግሞ ማታ ከከተማ ስመለስ ከሰፈር ልጆች ጋር በመሆን ስላየሁት የመኪና መልክ፣ ስለፍጥነቷ፣ ስለጎማው ጥንካሬና ስለሹፌሩ ጀግንነት አወራላቸዋለሁ፡፡ ከተማ መሄዴንና መኪና ማየቴን ያልሰሙና እንድነግራቸው ላልጠየቁኝ የሰፈሬ ልጆች ምክንያት በመፈለግ ስለጉዳዩ እነግራቸዋለው፡፡
የዩኒቨርሲቲ ውጤት መቶልኝ አዲስ አበባ ተመድቤ እስክመጣ ድረስ አዲስ አበባ በምናብ እየሳልኩ ከመመኘትና ከመናፈቅ ውጪ አላቃትም ነበር፡፡ ቀኑ ደረሰና ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን መጥራት ጀመሩ የኔ ዩኒቨርሲቲም ስለጠራ በተባልኩበት ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አዲስ አበበ አመራሁ፡፡ ልክ መጨረሻ ላይ መድረሳችን ተነገረንና ወረድን፡፡ እኔም ወዲያውኑ ከሚቀበለኝ ሰው ጋር ተገናኝቼ ከመናኽሪያው በመውጣት ታከሲ መጠባበቅ ጀመርን፡፡ እኔ ግን የመኪናዎች ሁኔታ በጣም ስላስገረመኝ እነሱን መከታተል ጀመርኩ፡፡ ወዲያው ደግሞ ያልጠበኩትና ግራ የሚያጋባ ትይንት ተመለከትኩ፡፡ አትኩሬ ከምል አገላብጬ አየሁት ብል ይቀለኛል፡፡
ወገቡ ላይ ሳነብ አንበሳ ባስ ይላል፡፡ የእርዝመቱንና በውስጡ የያዛቸውን ሰዎች ብዛት ስመለከት መኪና ነው ብዬ ለማመን ተግደረደርኩ፡፡ አስቡት እኔ እማያቸው የነበሩት መኪናዎች ከአንበሳ ባስ አንፃር እንደ ቆሎ የሚቃሙ መስለው ታዩኝ፡ ፡ ሌላው ነገር ደግሞ ወገቡ ላይ ሸብ ያደረገው ነገር ነበር፡፡ ልክ እሱን እንዳየሁ ገጠር ያሉ እናትና እህቶቼ ትዝ አሉኝ ወገባቸውን በመቀነት ሸብ ካደረጉ በኋላ ቢሰሩ አይደክሙ በወገባቸው ላይ የሚያስቀምጡት ነገር በቀላሉ አይወድቅም፡፡ ለነገሩ ወገቡን ሸብ ባያደርግ ኑሮማ መች ይህን ሁሉ ሰው ይይዝ ነበር ስል አሰብኩ፡፡ይህን ሁሉ ሰው እየጫነ የማይደክመው ወገቡን በመቀነት አደግድጎ ለሥራ መነሳቱ መሆኑን ተገነዘብኩኝ፡፡ አንበሳ ባስ በሚለው ስሙም ለመስማማት ጊዜ አልወሰደብኝም፡፡
አንበሳ ባስን ልክ እንዳየሁት እንደማልሳፈርበት ለራሴ ቃል ገብቼ ነበር፤ ነገር ግን አንድ ቀን ከጓደኛዬ ጋር ሁነን ታከሲ ስንጠብቅ ታከሲ ጠፋቶ ለብዙ ደቂቃ ቁጭ ካልን በኋላ ሁሉም ወደ ሆነ አቅጣጫ እየተመለከተ መጣች መጣች ማለት ጀመሩ። እኔም መጣች ወደ አሉበት አቅጣጭ መመልከት ስጀምር ልክ ውሃ ውስጥ እንዳለ ጉማሬ ጎንበስ ቀና ጎንበስ ቀና የሚል ምልክት አየሁ ወዲያውኑ እኛ ጋር ደረሰችና ሳያት ከገጠር ስመጣ አውቶቡስ ተራ ያየሁት አንበሳ ባስ ነበር፡፡ ቀለል አድርገው መጣች ሲሉ እንዴ ከዚህም በላይ ትልቅ መኪና አለ ማለት ነው ስል ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ልቤ በፍርሃት መራድ ጀመረ ነገር ግን ምንም ምርጫ አልነበረኝም ከመሳፈር ውጭ፡፡ በማመንታት ላይ እያለሁ ጓደኛዬ ቀድሞ ገብቶ ና ሲለኝ እምቢይ እንዳልል ውርደት መስሎ ስለታየኝ ሳመነታ ሁለት እጄን በሁለት ኪሴ ከትቼ ገባሁ፡፡ አገባቤን ላየ ልክ አንበሳ ባስ አዲስ አበባ ከገባ ጀምሮ ስሳፈር የኖርኩ ነበር የሚመስለው፡፡ ነገር ግን ዘንጬ ገባሁ እንጅ ዘንጬ አልወጣሁም፡፡ የሆነ ፌርማታ ላይ ለመቆም ሲሞክር ሁለቱም እጆቼን በኪሶቼ ስለነበሩ ባሱ ለመቆም በሚሞክርበት ወቅት ሚዛኔን መጠበቅ አቅቶኝ በኃይል አፈናጥሮ ከሰው ጋር አጋጨኝ፡፡ በዚህ ሰዓት ለመቆም ሳይሆን ላለመገልበጥ እየሞከረ ስለመሰለኝ ጮኩኝ ሁሉም ወደ እኔ አፈጠጠ፡፡ ግማሹ ሲስቅ ገሚሱ ግራ ተጋብቶ ምን ማለት እንዳለበት ግራ በመጋባት ሁኔታውን ይከታተላሉ፡፡ ብቻ ምን ልበላቹህ የዛን ቀን ብቻ አንበሳ ባስ ላይ እንደተሳፈርኩ አሳውቄ ወረድኩ፡፡ ከወረድኩ በኋላ ግን በሁኔታው በጣም ስለተበሳጨሁ እንዴት ቆይ በዚህ ዘመን ለባስ አጠቃቀም አዲስ እሆናለው ስል እራሴን ጠየቅኩ፡ ፡ አዲስ አበባ ካልመጣን ዘመናዊነትን መላመድ አለመቻሉ ገረመኝ፡፡
አዲስ አበባ ከገባሁ ወራቶች ተፈራርቀዋል፡፡ እኔም እየዞርኩ የአዲስ አበባን መውጫ መግቢያዋን ለማወቅ በቅቻለው፡፡ ብዙ ሰዎችንም ለመተዋወቅ ችያለሁ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ከተወለድኩበት አካባቢ የመጡ የሰፈሬ ልጆችንም ተዋውቄያለሁ፡፡ ከዚህም አልፎ አብሬ መዋል ማደር የዘወትር ሥራዬ ሁኗል፡፡ አንድ ቀን ከአንድ አብሮ አደግ ጓደኛዬ ጋር ስንጨዋወት ከወሬ ወሬ የተነሳ ባስ ውስጥ ስለሆንኩት ሁሉ ነገርኩት፡፡ እንደነገሩ ከሳቀ በኋላ ብዙም ሳይደነቅ የኔን ጉድ ብትሰማ ምን ልትል ነው አለኝ፡፡ መቼም ከእኔ አይበልጥም ካልኩት በኋላ ለመስማት እየጓጓሁ
ስለጉዳዩ እንዲነግረኝ ምልክት አሳየሁት፡፡ምን መሰለህ የሆንኩት አለና ቀጠለ፡፡ ገና ከተወለድኩበት ቀየ እንደመጣሁ ባንድ ካፌ ውስጥ አስተናጋጅ ሁኜ ተቀጠርኩና ሥራ ጀመርኩ በሁለተኛው ቀን አንድ የካፌው ደንበኛ የሆነ ሰው ለመገልገል መቶ ታዘዝኩት፡፡እሱም የሚፈልገውን ያህል ጊዜ ከቆየ በኋላ ካፌውን ለቅቆ ወጣ እኔም የተጠቀመበትን ወንበር ለማጸዳዳት ስሄድ 5ብር አገኘሁ ታዲያ ይህን ጊዜ ነው ጉድ የሆንኩት አለኝ፡፡ ከዛማ ይህን ብር ይዥ ለመስጠት ስሮጥ መኪናውን አስነስቶ ከካፌው አካባቢ ተፈተለከ፡፡ እኔ የእግረኛ መንገዴን ይዤ ስሮጥ እሱም በቪቲዝ መኪናው ሲከንፍ መጨረሻ ላይ የትራፊክ መብራት አስቆመውና ደረስኩበት፡፡ ወዲያውኑ እያለከለኩ ብሩን ስሰጠው ግራ ስለገባው ስለጉዳዩ ነግሬው ብሩን እንዲቀበለኝ ለማድረግ ስሞክር ሳቁ አመለጠውና በጣም ከሳቀ በኋላ 5ብር ጨምሮልኝ ስለ ጉርሻ/ ቲፕ በደንብ አስረድቶ ላከኝ ብሎ ሲነግረኝ እውነትም የኔ ቀላል መሆኑን በመረዳት ለመፅናናት ሞከርኩ፡፡
ከዛም ቀጠለና እንደሱው አስተናጋጅ ስለሆነው ጓደኛው ስለገጠመው ገጠመኝ አጫወተኝ፡፡ጓደኛው አዲስ ከመሆኑ የተነሳ ወገብ ላይ የሚታሰረውን የብር ማስቀመጫ ቦርሳ ልክ እንደ ሱፍ ሸሚዝ አንገቱ ላይ ግጥም አድርጎ በማሰሩ የተነሳ በካፌው ውስጥ ይስተናገዱ የነበሩ ደንበኞች በሙሉ በአንድ ጊዜ ቤቱን በሳቅ ሞቅ አደረጉት ብሎ ሲነግረኝ እኔም ብኖር እንዴት ልስቅ እንደምችል እያሰብኩ በጣም ሳኩኝ፡፡
ማንም ሰው አዲስ የትምህርት ቦታ፣ የመኖሪያ ቦታና የስራ ቦታ ሲተዋወቅ የሚገጥሙትና ሊገጥሙት የሚችሉ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ብዙ ሰው ከክፍለ ሀገር ሲመጣ የእኔ እጣ ፈንታ እንደሚገጥማቸው ካወኩ በኋላ ብዙዎችም እንደገጠማቸው ስሰማ ጉዳዩ ቀላል እንዳልሆነ ተገነዘብኩኝ፡፡ አዲስ አበባ ካልተመጣ ትልቅ ህንፃ፣ ባቡርና ዘመናዊ መኪናዎችን ማየት አይቻልም፡፡ አይተነው ስለማናውቅ አዲስ አበባ ስንመጣ ማያደናግረው ሁሉ ያደናግራል፡፡ ቀደምት የሥልጣኔ ባለቤት መሆናችንን ባሰብኩት ጊዜ ደግሞ ህመሜ እየባሰ መጣ የባቡር ሐዲድ በ1917 ዓ.ም የዘረጋን ህዝቦች ግን አሁንም ብዙዎቻችን አዲስ አበባ ካልመጣን ባቡር ማየት አንችልም፡፡ መንግሥት ከዘመኑ እኩል መራመድ አለበት ህዝብን የሚመራው አካል ካልዘመነ ህዝብ ሊዘምን አይችልም፡፡ በመዲናችን ብቻ ተጠራቅመው ለብዙዎቻችን ብርቅ የሚሆኑ ነገሮችንም መንግሥት ብዙው ህዝብ ወደአለበት ወደ ክልል ከተሞችና አነስተኛ ወደ ሆኑ ከተሞች እንዲስፋፉ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ዘመኑ በሚፈልገን ልክ እንዘምን መልዕክቴ ነው፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 2011
ሞገስ ፀጋዬ