በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ካላቸው አገራት መካከል የምትመደበው ኢትዮጵያ፤ የቴሌኮም ዘርፍ በአንድ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ በብቸኝነት ተይዞ በመቆየቱ ተጠቃሚዎች በዋጋም ሆነ በአገልግሎት ጥራት አማራጭ ሳይኖራቸው ቆይቷል።
በአሁኑ ጊዜ የቴሌኮም አገልግሎትን በብቸኝነት እየሰጠ የሚገኘው ኢትዮ ቴሌኮም ከአንድ መቶ ሃያ ስድስት ዓመታት በላይ በመንግሥት ሥር ሲተዳደር ቆይቷል፡፡ከአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር የሞባይል ስልክ አገልግሎት ተጠቃሚ ካላቸው ተቋማት መካከል አንዱ እንደመሆኑ የገበያ ድርሻው ለውጭ ኩባንያዎች አጓጊ ሆኖ መቆየቱም ይነገራል፡፡
ባለፉት ሶስት ዓመታት መንግሥት የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም በመቅረጽ ሲተገብራቸው ከነበሩ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጉዳዮች መካከል በመንግሥት ብቻ ተይዘው የነበሩ የኢኮኖሚ ሴክተሮችን ለግሉ ዘርፍ ክፍት የማድረግ ሥራዎች ይገኙበታል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ወደ ግል የማዘዋወሩን ሂደት ለዚህ ዋነኛ ማሳያ ሆኖ የሚቀርብ ሲሆን መንግሥትም በቴሌኮም አገልግሎት ልምድና አቅም ያላቸው የውጭ ኩባንያዎች እንዲሳተፉ ለማስቻል ረዘም ያለ ጊዜ በመውሰድ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
ሂደቱን ለማስፈጸም ነጻና ገለልተኛ የኮሙኒኬሽን ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን እንዲቋቋም የሚፈቅድ አዋጅ አውጥቷል ፡፡ ባለስልጣኑ ሁለት ተጨማሪ የቴሌኮሙኒኬሽን ድርጅቶችን ገበያ እንዲገቡ በሩ መክፈቱን በማሳወቅ፣ በዘርፍ ውስጥ ለመሰማራት ፍላጎቱ ላላቸው ኩባንያዎች ይፋዊ ዓለም አቀፍ የጨረታ ጥሪ አቅርቧል፡፡ይሕን ተከትሎም ከተለያዩ አገራት ከ12 በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ ከረጅም ጊዜ የግምገማ ስራ በኋላም ሁለቱ ድርጅቶች ተለይተዋል፡፡
የቴሌኮም ዘርፉን ለውጪ ተቋማት ለመጀመሪያ ጊዜ ክፍት ያደረገችው ኢትዮጵያ፣ከቀናት በፊት ታሪካዊ የተባለለት ውሳኔን አስተላልፋለች፡፡የሚኒስትሮች ምክር ቤት ቅዳሜ ግንቦት 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ባካሔደው ስብሰባ ዓለም አቀፍ ጥምረት ለኢትዮጵያ የተባለው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቅንጅት ያቀረበውን የጨረታ ሰነድ ተመልክቶ ፈቃድ እንዲሰጠው ወስኗል፡፡
በኢትዮ ቴሌኮም ከ120 ዓመታት በላይ በብቸኝነት ተይዞ ወደነበረው ዘርፍ ለመግባት ፈቃድ ያገኘውና በኢትዮጵያ የቴሌኮም ታሪክ ቀዳሚው የውጭ አገልግሎት ሰጪ ለመሆን የተመረጠው ጥምረትም ከፍተኛ የፈቃድ ክፍያ ዋጋ እና አስተማማኝ የመዋዕለ ነዋይ ፍሰት ዕቅድ ማቅረቡ ተመራጭ እንዳደረገው ታውቋል፡፡ፈቃድ ለማግኘት 850 ሚሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያ መንግስት እንደሚከፍል ታውቋል፡፡
በዘርፉ የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸው የተለያዩ ታዋቂ የቴሌኮም ኩባንያዎች ስብስብ የሆነው ግሎባል ፓርትነርሽፕ ፎር ኢትዮጵያ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ውስጥ ከ750 በላይ ተጠቃሚዎች እንዳሉት ይነገራል። ሳፋሪኮም፣ ቮዳኮም፣ ቮዳፎን፣ ሱሚቱሞ ኮርፖሬሽን እንዲሁም ሲዲሲ ግሩፕ የተባሉ ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኩባንያዎች በጥምረት ያቋቋሙት ኩባንያዎች ናቸው ፡፡
ሳፋሪኮም የኬንያ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢና ድርጅት ነው ፡፡ እኤአ በ1997 የተቋቋመው ሲሆን በምሥራቅ እና በመካከለኛው አፍሪካ ትርፋማ ከሆኑ ድርጅቶች አንዱ ነው ። በሞባይል ገንዘብ ማስተላለፍ፣ በኢ ኮሜርስ ግብይት እና ሌሎችም አገልግሎቶችን ይሰጣል።
ዋና መስሪያ ቤቱን ናይሮቢ ላይ ያደረገው ድርጅት በተለይም ኤምፔሳ በተባለው የሞባይል ገንዘብ ማስተላለፊያ አገልግሎቱ ይበልጥ ይታወቃል፡፡እኤአ በ2020 ከኬንያ የቴሌኮም ገበያ 64 ነጥብ 5 በመቶ ድርሻን መውሰዱና 35 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሚሆኑ 4ሺ500 ቋሚ እና 1900 ጊዜያዊ ሰራተኞች እንዳሉትም ተመላክቷል፡፡
ቮዳኮም ሌላኛው ድርጅት ነው፡፡ድርጅቱም የኢንተርኔት፣የተንቀሳቃሽ ስልክ ጥሪ እንዲሁም ከገንዘብ ዝውውር ጋር የተያያዙ በአፍሪካ ሰፊ የቴሌኮም አገልግሎት ከሚሰጡት መካከል ይጠቀሳል ። መነሻውን ደቡብ አፍሪካ ያደረገው ቮዳኮም፤ በታንዛንያ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሞዛምቢክ፣ ሌሶቶ እና ኬንያ ውስጥ አገልግሎት ይሰጣል።የሞባይል ኔትወርክ ዝርጋታው ከ295 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ እያደረገ ይኛል፡፡ቮዳኮም ቢዝነስ አፍሪካ በሚል Vodacom Business Africa (VBA) በ48 አገራት ንግድ ነክ አገልግሎቶች ይሰጣል። ከቮዳኮም 60ነጥብ5 በመቶ የሚሆነው የባለቤትነት ድርሻ የብሪታኒያው ቮዳፎን ነው።
የጥምረቱ አካል የሆነው ሌላኛው ድርጅት የብሪታኒያው ቮዳፎን ነው፡፡ በእስያ፣ አፍሪካ፣ አውሮፓ የተንቀሳቃሽ ስልክ ጥሪ፣ ኢንተርኔትና ሌሎችም ተያያዥ አገልግሎቶች ይሰጣል፡፡ በ21 አገራት ውስጥ ኔትወርክ ዘርግቷል። በኢንተርኔት አማካይነት የተለያዩ ኤሌክትሮኒክስ ነክ መገልገያዎችን በማስተሳሰር የሚታወቀውና ‘ኢንተርኔት ኦፍ ቲንግስ’ የሚባለውን አገልግሎት በተለይም ለንግድ ተቋማት ያቀርባል።
አውሮፓ ውስጥ በኔትወርክ ዝርጋታ የአንበሳውን ድርሻ እንደያዘ የሚነገርለት ቮዳፎን፤አፍሪካ ውስጥ ከ42 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሞባይል ገንዘብ መለዋወጫ አገልግሎትን እንዲጠቀሙ ማስቻሉንም መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
እንደ አውሮፓውያኑ ከ1980ዎቹ ወዲህ የተስፋፋው ቮዳፎን የስልክ ጥሪ፣ የጽሑፍ መልዕክትና ኢንተርኔት የሚያቀርብ ሲሆን፤ አውሮፓ ውስጥ የ5ጂ ዝርጋታ ላይ በስፋት ይሠራል።በአፍሪካ በጋና፣ በሊቢያና በካሜሩን፤ በመካከለኛው ምሥራቅ ደግሞ በኳታር፣ በባህሬንና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፤ በእስያ ደግሞ በጃፓን እና በሕንድ አገልግሎት ይሰጣል።
ሱሙቲሞ ኮርፖሬሽን የጃፓን ተቋም ሲሆን ቴሌኮምን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማራ ነው።እኤአ በ1919 ጃፓን ውስጥ የተመሰረተ ሲሆን በመላ ዓለም 66 አገራት እና ቀጠናዎች ላይ ይንቀሳቀሳል።74 ሺ 920 ሰራተኞችም አሉት፡፡
የብሪታንያው ሲዲሲ ግሩፕ እንደ አውሮፓውያኑ በ1948 ከተመሰረተ ወዲህ ላለፉት 70 ዓመታት በተለይ ደሃ አገራት ለመደገፍ በፋይናንስ ዘርፍ ሲሠራ ቆይቷል ። በአፍሪካ እና እስያ አገሮች ውስጥ ይበልጥ ይሰራል ፡፡ በ1998 ላይ ሴልቴል በተባለ የአፍሪካ የሞባይል ስልክ ድርጅት ኢንቨስት ማድረጉ ከቴሌኮም ዘርፍ እንቅስቃሴው አንዱ ነው። ጠቅላላ ሃብቱም 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ፓውንድ ስለመሆኑ እና ባለፉት ዓመታትም ከ1200 ቢዝነሶችን ድጋፍ ማድረጉ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
እነዚህን የመሳሰሉ ግዙፍ ተቋማትን በጥምረት ያቀፈው አዲሱ የቴሌኮም ተቋምም ከ110 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ባላት አገር ውስጥ ሰፊ የገበያ ዕድል ያለው ሲሆን ዘመኑ ያፈራቸውን የቴሌኮም ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የተለያዩ አገልግሎቶችን እንደሚያቀርብም ይጠበቃል።
የኩባንያዎቹ ዘርፈ ብዙ ልምድ በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ ውስጥ ጉልህ ለውጥ እንደሚያመጣም በበርካቶች እምነት ተጥሎበታል ፡፡ ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ሲገቡ፤ የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ከመሳብ ባሻገር፣የአገልግሎት ክፍያ እንደሚቀንስ እንዲሁም የአገልግሎት ጥራትና ፍጥነት እንደሚጨምርም ተጠቁማል ፡፡ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችም የቴሌኮም ዘርፉ ለውድድር ክፍት መሆኑ ጥራት ያለው አገልግሎት በርካሽ ዋጋን ከማስገኘቱ ባሻገር ለሥራ ፈጠራና ለውድድር በር ይከፍታል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ውሳኔውን ታሪካዊ ስለመሆኑ አፅዕኖት የሠጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣ኢትዮጵያን ሙሉ ለሙሉ ወደ ዲጂታል አገልግሎት የማስገባት ዕቅዳችን ፈር ይዟል›› ብለዋል፡፡ በአጠቃላይ ከ8 ቢሊዮን ዶላር በሚበልጥ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት፣ እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ ከተደረጉት የውጪ ቀጥተኛ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰቶች ብልጫ እንዲኖረው እንደሚያደርግም አስገንዝበዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ፣ውሳኔው ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ተገምግሞ መተላለፉን ጠቁመው፣ ውጤቱም አገሪቱ በምታካሂደው የምጣኔ ሀብታዊ ለውጥ ሂደት ውስጥ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን አፅዕኖት ሰጥተውታል፡፡ ከአገር ኢኮኖሚ አስተዋፅዖ ባሻገር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ጥራት ያለው አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ያስችላል ›› ብለዋል።
የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባም፣‹‹የተሰጠው ፈቃድ ሚሊዮኖች ጥራት ያለው አስተማማኝ አገልግሎትን እንዲያገኙ በማስቻል በአገሪቱ የቴሌኮም ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል›› ነው ያሉት፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር አማካሪ ዶክተር ብሩክ ታዬ፣በጨረታው የተመረጠው ተቋም በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ እስከ 1 ነጥብ5 ሚሊዮን የሚደርሱ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን እንደሚፈጥርና 8 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ መዋዕለ ንዋይን ወደ አገሪቱ እንደሚያስገባም አስገንዝበዋል፡፡
የ4ጂ እና የ5ጂ የኢንተርኔት አገልግሎቶችን በማቅረብ ረገድም፣ በተለይ ሳተላይት በመጠቀም ከሁለት ዓመት በኋላ መላው አገሪቱ የ4ጂ የኢንተርኔት ሽፋን እንዲያገኝ ያደርጋል ብለዋል።ይህም እንደ አገር ከተቀመጡ የ2025 የዲጂታል ስትራቴጂ፣ የ10 ዓመቱ መሪ ዕቅድ፣ የአገር አቀፍ ሪፎርም ግቦች ጋር የተጣጣመ ስለመሆኑ ነው ያመላከቱት፡፡
በተለይ በስልክና በኢንተርኔት የአገልግሎት ጥራት ላይ የሚያስከትለው ለውጥና የዋጋ ቅናሽ በተለያዩ ዘርፎች ላይ አወንታዊ እድገትን ያመጣል የሚሉም አልታጡም፡፡‹‹መሰል ኩባንያን ወደ ገበያው መምጣት ምጣኔ ሀብቱ ላይ አወንታዊ ሚና በማሳደር የፋይናንስ ተቋማት፣ አምራቾችና በሌሎችም ዘርፎች ያሉ ተቋማት በተሻለ ቴክኖሎጂ ታግዘው አገልግሎት እንዲሰጡ ከፍተኛ አቅም ይፈጥራልም››ተብሏል፡፡
የመንግስትን የዕዳ ጫና ከመቀነስ ባሻገር የኩባንያውን አሰራር ማቀላጠፍ፣ የቴሌኮም ተደራሽነትና የአገልግሎት ክፍያ ለማመጣጠን ተጠቃሚዎች በተሻለ ዋጋ ጥሩ አገልግሎት የሚያገኙበት ዕድል እንደሚያመቻች እንዲሁም ውድድርን ለማበረታታት ከፍተኛ አቅም የሚፈጥር መሆኑንም ተገልጿል፡፡
የዓለም ባንክ ከፍተኛ አመራርም ይሕን እሳቤ ይጋሩታል፡፡በኤርትራ፣በኢትዮጵያ፣ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን የአለም ባንክ ዳይሬክተር፣ ኡስማኔ ዲዋን‹‹Why Ethiopia needs to open its telecom market››በሚል ባሰፈሩት ሀተታ፣ ኢትዮጵያ የቴሌኮም ገበያን ክፍት በማድረግ ዘርፈ ብዙ ትርፎችን እንደምትቋደስ ጠቅሰዋል፡፡ ዝቅተኛ ክፍያ፣ ከፍተኛ ጥራት እንዲሁም ለደንበኞች ተጨማሪ አማራጮችን የሚያስተዋውቅ አቅሙ ግዙፍ ስለመሆኑ አስገንዝበዋል፡፡
ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ ቀጣይ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሁለንተናዊ ተሳትፎ መሰረት የሚጥል ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚያስችል አስረድተዋል፡፡ የውጭ ኩባንያዎች ወደ ዘርፉ መቀላቀል ለኢትዮ ቴሌኮም ስጋት ሳይሆን የውድድር መንፈስ በመፍጠር አቅምን ለማጎልበት እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ይሑንና መንግሥት የተለያዩ የፖሊሲ ማእቀፎችን በማዘጋጀት ኢትዮ ቴሌኮምን ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲቀጥል በሚያስችሉ አሰራሮች መደገፉን መዘንጋት የለበትም ።
የአሁኑን ውሳኔ አገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ችግር አንጻር የተመለከቱ የምጣኔ ሃብት ምሁራኑ አልጠፉም፡፡ ኢትዮጵያ ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመውጣት፣ በብድር ተጀምረው ያላለቁ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለመጨረስ፣ ብሎም በዓለም የንግድ መድረክ የምትወቀስባቸው የኢኮኖሚ አቋሞች ላይ ለውጥ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ማሳያ እርምጃ እንደሆነም ነው ያስረዱት፡፡
የጥምረቱ አጋር ድርጅቶችን ከኢትዮጵያ ጋር በቴሌኮም ዘርፉ በጋራ ለመስራት እድል በማግኘታቸው መደሰታቸውን በመጠቆም ስለ ቀጣይ ተግባራቸውም ማብራሪያን ሰጥተዋል፡፡ የሳፋሪ ኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፒተር ዴግዋ ፣ቀደም ባሉት ዓመታት የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ኃይል በደንበኞቻችን ላይ ያሳደረውን ተፅእኖ በተጨባጭ አይተናል፣ በኢትዮጵያም ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብረን በመስራት ተመሳሳይ ለውጥ ለማምጣት እንፈልጋለን ብለዋል ፡፡ ድርጅቱም በመጪው ጥር አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አሳውቀዋል፡፡
የቮዳኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ሻሜል ጆሱፐ፣ጥምረቱ ጥራት ያለው የቴሌኮም መሰረተ ልማት በመገንባት የቴክኖሎጂ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ ሂደት ከፍተኛ ልምድ ባላቸው የተዋቀረ ነው፣ በኢትዮጵያ ዜጎች ህይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
የቮዳቮን ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኒክ ሪድ፣ውሳኔው‹‹ለኢትዮጵያ ትልቅ እመርታ ነው፣እኛም በዲጂታል አገልግሎት ተዋናይ በመሆን የኢትዮጵያን ግዙፍ ኢኮኖሚና የልማት አቅም ለማሸጋገር እንፈልጋለን፣ አካታች እና አስተማማኝ የዲጂታል ማህበረሰብ እውን እናደርጋለን›› ብለዋል ፡፡
ሱሚቶሙ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ፕሬዚዳንት፣ኮርፖሬሽኑ በአለም አቀፍ ደረጃ በተለይም በእስያ እና በጃፓን ያለውን ልምድ በመጠቀም በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ለማድረግ ሕዝቦቻችን የተሻለ ህይወት እንዲመሩ ለማገዝ እንደሚተጋ ማረጋገጫን ሰጥተዋል፡፡
በአፍሪካ የሲዲሲ ኃላፊ ትንቢት ኤርሚያስ በበኩላቸው፤ በዲጂታል መሰረተ ልማት ዘመናዊ አስተማማኝ እና ዘላቂ ኢኮኖሚን እውን ማድረግ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ገበያውን መቀላቀል እንደሚያስቻል ጠቁመው፣ድርጅታቸውን በዚህ ረገድ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና ሕዝቦችን የኢኮኖሚ እድሎችን ለመፍጠር እድገትን እውን ለማድረግ ዝግጁ ስለመሆኑ አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ወደ ግል የማዘዋወሩን ሂደት እንደ አገር ሆነ ተጠቃሚ የሚሰጠው ሁለንተናዊ ጥቅም እንደተጠበቀ ሆኖ ጉዳትም ሊያስከትል እንደሚችል ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባ የሚያስገነዝቡ የምጣኔ ሃብት ምሁራን ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡
ድህነትን በዋናነት የሚያነሱት ባለሙያዎቹ በግል ድርጅቶች እንደመመራቱ የአገልግሎቱ ዋጋ ሊያሻቅብ ይችላል የሚል ስጋት ያነሳሉ፡፡ለዚህ ስጋት ምላሽ የሚያቀርቡት በአንፃሩ፣መንግሥት የተቆጣጣሪነት ሚናውን በበቂ ሁኔታ ቢወጣ ስጋቶቹን መመከት እንደሚቻሉ አፅዕኖት ሰጥተውታል፡፡
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2013