ወይዘሮ ትዕግስት ጥላሁን ይባላሉ፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ስሙ ቡልቡላ አካባቢ ተወልደው ያደጉ የአርሶ አደር ልጅ ናቸው ፡፡ እኝህ ባለጉዳይ በ2012 ዓ.ም ከአርሶ አደር ኮሚቴ እስከ ክፍለ ከተማ ድረስ በዝምድና ጥቅም በመተሳሰር በስማቸው ሌላ ግለሰብ ካርታ አውጥቶ ያገኛሉ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ መንግሥት ለልማት በሚል በወሰደው መሬታቸው እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ምትክ ቦታ ባለማግኘታቸው አስተዳደራዊ በደል ተፈፅሞብኛል ይላሉ ፡፡ይህንን አይቶ ሕዝብ ይፍረደኝ ሲሉ ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል አቤት ብለዋል፡፡
እንደ ወይዘሮ ትዕግስት ገለጻ ፤ በሀገሪቱ ከመጣው ለውጥ ጋር ተያይዞ ለልማት ተነሺ ለሆኑ አርሶ አደሮች እና ልጆች የቤት መስሪያ የሚሆን የቦታ ካርታ እንዲሰጥ መመሪያ ከመንግሥት ወርዷል ፡፡ መመሪያውም ለአባወራዎች ወይም እማወራዎች 500 ካሬ ሜትር ፤ ለአርሶ አደር ልጆች ደግሞ 150 ካሬ ሜትር መሬት እንዲሰጣቸው ይደነግጋል፡፡
ይህን ተከትሎ አርሶ አደር እና የአርሶ አደር ልጅ የሆኑት እማወራዋ ወይዘሮ ትግስት ጥላሁን ለማንኛውም አርሶ አደር እንደሚሰጠው ለእርሳቸውም የመኖሪያ ቤት መስሪያ እንዲሰጣቸው ለቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ማመልከታቸውን ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን የወረዳ 12 የመሬት አስተዳደር በስማቸው 500 ካሬ ሜትር እንደወሰዱ እና ካርታ እና ፕላን እንዳሰሩበት ይነገራቸዋል፡፡ስለዚህ ለሁለተኛ ጊዜ መሬት ለመስጠት መመሪያ እንደሚከለክል የወረዳው የመሬት ማኔጅመንት ያስረዳቸዋል፡፡ በስማቸው በማጭበርበር 500 ካሬ ሜትር የሚለካ ቦታ ካርታ እንደወጣለት የተረዱት ወይዘሮ ትዕግስት ስለጉዳዩ እንደሰሙ ማመን እንደተቸገሩ ይገልጻሉ፡፡
እንደወይዘሮ ትዕግስት ገለፃ፤ ያለእርሳቸው እውቅና እና ፈቃድ በእርሳቸው ስም በሌላ አርሶ አደር ይዞታ ላይ ካርታ ወጥቷል ፡፡ ይህንንም ያደረገው ሰው አቶ አሸናፊ ጌታቸው እንደሚባል ማረጋገጥ ችለዋል፡፡ አቶ አሸናፊ ከወረዳ አስተዳደሮች እና ከክፍለ ከተማ መሬት ባለሙያዎች ጋር እንደሚግባባ ሁሉም የቡልቡላ ነዋሪ ያውቃል ፡፡ ነገር ግን እንዴት አድርጎ በእርሳቸው ስም ካርታ እንዳወጣ ሊረዱ አልቻሉም ፡፡
በስማቸው በተሰራው ካርታ ያለውን ቦታ ሄደው ማየታቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ ትዕግስት፤በቦታው የዕቃ ማስቀመጫ ቤትም ተገንብቶ ማየታቸውንም ገልጸዋል፡፡ ይህን ሲመለከቱ በጣም ማዘናቸውን የገለጹት ወይዘሮ ትዕግስት ፤ የእርሳቸው የይዞታ መሬታ ወስዶ ምንም ምትክ ሊሰጥ ያልቻለ አመራር እንዴት ለአቶ አሸናፊ በእርሳቸው ስም ካርታ ሊያገኝ ቻለ በሚል ክፉኛ ማዘናቸውን ይናገራሉ፡፡
እንደ ወይዘሮ ትዕግስት ገለጻ ፤ በእርሳቸው ስም የታጠረውን ቦታ ካዩ በኋላ ወደ ቀበሌ በመሄድ ካዩት ቦታ ጋር በማጣቀስ ሰነድ እንደጠፋባቸው እና ቀሪ ሰነድ በወረዳው ስለሚገኝ ኮፒ እንዲሰጣቸው በወረዳው የሚገኝ አንድ መሃንዲስ ይጠይቃሉ፡፡ ታጥሮ እና የእቃ ማጠራቀሚያ ተሰርቶበት ያዩት ቦታ ካርታ ኮፒም መሃንዲሱ ሲሰጣቸው ካርታው በስማቸው መሆኑን ያረጋግጣሉ ፡፡ በስማቸው ካርታ እንደወጣ እና ካርታ የወጣበትም ቦታ ከእርሳቸው ይዞታ ውጭ በሌላ ሰው ይዞታ መሆኑን ይረዳሉ፡፡
ወይዘሮ ትዕግስት ስለጉዳዩ ማብራሪያ ለመጠየቅ ወደ ቦሌ ክፍለ ከተማ የሰነድ አልባ ይዞታዎች መስተንግዶ ፕሮጀክት ኃላፊ አቶ ህርከሳ ተመስገን መሄዳቸውን እና ስለጉዳዩ አቶ ህርከሳ ተመስገን ያናግሯቸዋል ፡፡ አቶ ህርከሳ ተመስገንም ስለጉዳዩ ካዳመጡ በኋላ ከጉዳዩ ጋር የተያያዘው ሰነድ ይደብቃሉ፡፡
የተጭበረበረው ካርታው በስማቸው እንዴት ሊሰራ ቻለ?
ሰነዶች እንደሚጠቁሙት ፤ ወይዘሮ ትዕግስት ጥላሁን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 በይዞታ የሚያስተዳድሩትን የገጠር እና የእርሻ መሬት እንደሆነ እና ከይዞታቸውም እንዳልተፈናቀሉ እና ካሳም እንዳልወሰዱ እንዲረጋገጥላቸው በቀን 27 ህዳር 2011 ዓ.ም ለአዲስ አበባ ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ያመለክታሉ፡፡ የወረዳው ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣንም ከይዞታቸው በምንም ምክንያት እንዳልተፈናቀሉ እና ምንም አይነት ካሳም እንዳልወሰዱ ያረጋግጥላቸዋል ፡፡
ይህን ተከትሎ ወይዘሮ ትግስት ጥላሁን ምንም የካሳ ክፍያ ያልወሰዱ እና በልማትም ያልተነሱ መሆናቸውን የተመለከተው ግለሰብ ወይም በወይዘሮ ትዕግስት ገለጻ “የመሬት ደላላ” የሆኑት አቶ አሸናፊ ጌታቸው በወይዘሮ ትዕግስት ስም ካርታ ማሰራት ይፈልጋሉ፡፡ የፈለጉትንም ለማሳካት ወይዘሮ ትዕግስት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 የሚገኙ አርሶ አደር መሆናቸውን የሚያረጋግጡ የአርሶ አደር ተወካዮች እና የወረዳ አመራሮችን በጥቅም በመመሳጠር ያሳምናሉ፡፡ በዚህም ወይዘሮ ትዕግስት አርሶ አደር ስለመሆናቸው አቶ ሰቦቃ ለታ እና አቶ አምዴ ተሰማ በተባሉ የአርሶ አደር ኮሚቴ እና አቶ አብራር መንገሻ እና አቶ ካሰሁን ገብረስላሴ በተባሉ የወረዳ 12 አመራሮችን ማረጋገጫ በጥቅምና በዝምድና በመተሳሰር ያስፈርማሉ፡፡
ማረጋገጫውንም ካገኙ በኋላ ካርታ እንዲሰራላቸው በ1/08/2011 ዓ.ም ለቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ይጠይቃሉ፡፡ በዚህ መሰረት ማመልከቻ በሰጡበት በዚያው ቀን የቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የሰነድ አልባ መስተንግዶ ዴስክ የቴክኒክ ጉዳዮች ማጣሪያ እና መወሰኛ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ወይዘሮ እመቤት ንጉሴ 500 ካሬ ሜትር የመኖሪያ ቤት በትዕግስት ጥላሁን ስም ለአቶ አሸናፊ ካርታ አዘጋጅተው ይሰጣሉ፡፡
በቀን 2/8/2011ዓ.ም ለቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የሰነድ አልባ መስተንግዶ ዴስክ የቤዝ ማፕ አውራሽ ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ መሰረት አወቀ የ”x-y” ኮኦርድኔት 477380,9742, 989428,0177 ፣ የቤዝ ማፕ ቁጥር ደግሞ ቦሌ 12 በማድረግ ለአቶ አሸናፊ ጌታቸው በወይዘሮ ትዕግስት ስም ካርታ ይሰሩላቸዋል፡፡
በቀን 3/8/2011 ዓ.ም ለቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት ማኔጅመንት እና አስተዳደር ገንዘብ ቤት የደረሰኝ ቁጥሩ ባልተገለፀ የደረሰኝ ቅፅ ለምህንድስና አገልግሎት 400 ብር፣ ለካርታ አገልግሎት ሦስት ብር እና የማህደር ማጣሪያ 100 ብር መከፈሉን ሰነዶች ይጠቁማሉ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አቶ አሸናፊ የተባሉት ግለሰብ ከቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የሰነድ አልባ መስተንግዶ ዴስክ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ጋር በወይዘሮ ትዕግስት ስም የግዴታ ውል ይዋዋላሉ፡፡ ውሉም ወይዘሮ ትዕግስት ጥላሁን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ነዋሪ እና የአርሶ አደር ልጅ መሆናቸውን በወረዳ 12 አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በኩል በአርሶ አደር ኮሚቴ፣ በቀጠና አመራሮች እና በወረዳው አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ተረጋግጦ ለክፍለ ከተማው የሰነድ አልባ ፕሮጀክት ዴስክ የተላከው ማስረጃ ያልተጭበረበረ እና እውነተኛ ስለመሆኑ እንዲሁም በቦታው ወይዘሮ ትዕግስትም ሆኑ የትዳር አጋራቸው ከዚህ በፊት ምንም አይነት ካሳ እንዳልወሰዱ በፊርማቸው እንደሚያረጋግጡ እና ከዚህ በፊት ካሳ ወስደው ቢገኙ በሃገሪቱ የፍታብሄር እና የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መሰረት ተጠያቂ ለመሆን ተስማምተው መፈረማቸውን ሰነዱ ይጠቁማል፡፡ ለዚህም ውል ሰጭ አቶ ህርከሳ ተመስገን (የቦሌ ክፍለ ከተማ የሰነድ አልባ ይዞታዎች መስተንግዶ ፕሮጀክት ኃላፊ) ፤ ውል ተቀባይ ደግሞ ወይዘሮ ትዕግስት ጥላሁን ስለመሆናቸው ፤ በውል ሰጭ በኩል ታዛቢዎች አቶ ግደይ ነጋሽ (የቦሌ ክፍለ ከተማ የህግ ጉዳዮች አጣሪ ወሳኝ ባለሙያ ) ፣እመቤት ንጉሴ (የቦሌ ክፍለ ከተማ የቴክኒክ ጉዳዮች አጣሪና ወሳኝ ባለሙያ ) እና አቶ ልዑል ሰገድ ታደሰ ሲሆኑ በውል ተቀባይ በኩል ደግሞ እማኞች አቶ አሸናፊ ጌታቸው ፣ብርሃኑ ሽፈራን እና አቶ እሸቱ ጌታቸው ናቸው የሚል ነው ፡፡ በዚህ መሰረት ሁሉ ነገር ተጠናቆ በቀን 07/8/2011ዓ.ም በወይዘሮ ትዕግስት ስም ካርታ መሰራቱን ሰነዶች ያሳያሉ ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ወይዘሮ ትዕግስት ጥላሁን ለማንኛውም አርሶ አደር ከይዞታው ለቤት መኖሪያ 500 ካሬ ሜትር ይሰጠው የሚለውን መመሪያ ጠቅሰው ካርታ እንዲሰራላቸው ለማድረግ ከወረዳ 12 ወደ ቦሌ ክፍለ ከተማ የሚጻፉ ማስረጃዎች ለመጠየቅ የወረዳ 12 የመሬት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ሲጠይቁ ያልጠበቁት አስደንጋጭ ነገር መስማታቸውን ይገልጻሉ ፡፡
ይህን ተከትሎ ጥር 19 ቀን 2012ዓ.ም በተጻፈ የክስ አቤቱታ አንደኛ አቶ አሸናፊ ጌታሁን ፣ ሁለተኛ አቶ ህርከሳ ተመስገን (የቦሌ ክፍለ ከተማ የሰነድ አልባ ይዞታዎች መስተንግዶ ፕሮጀክት ዴስክ ኃላፊ) ፣ ሶስተኛ አቶ ግደይ ነጋሽ (የቦሌ ክፍለ ከተማ የህግ ጉዳዮች አጣሪ እና ወሳኝ ባለሙያ) እና አራተኛ ወይዘሮ እመቤት ንጉሴ (የቦሌ በክፍለ ከተማ የቴክኒክ ጉዳዮች አጣሪ እና ወሳኝ ባለሙያ) የሆኑትን መክሰሳቸውን ወይዘሮ ትዕግስት ጥላሁን አመልክተዋል፡፡ ከወረቀት ሰነዶች የተገኘው ማስረጃ እንደሚጠቁመው ተከሳሾች የወይዘሮ ትዕግስት ባልሆነው የሌላ ሰው ይዞታ ላይ በመለወጥ እና የወይዘሮ ትዕግስትን ፎቶ ግራፍ ያለወይዘሮ ትዕግስት
እውቅና ለጥፈው በስማቸው በሕገ ወጥ መንገድ የወጣው ካርታ በማሰራታቸው ጉዳዩ ተጣርቶ ለሕግ እንዲያቀርቡ ይጠይቃል፡፡
ጥር 19 ቀን 2012 ዓ.ም በተጻፈው የክስ ሰነድ እንደሚገልጸው ተበዳይዋ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 በስሜ ሕጋዊ ግብር እንደሚከፍሉ እና በእጃቸው የሚገኝ በምስራቅ ወይዘሮ ሙሉ መልካ ፣ በምዕራብ አቶ ግዛው ወልደ ስርዓት በሰሜን ወይዘሮ አበበች ዳቢ፣ በደቡብ አቶ ወርቁ ኃይለማሪያም የሚያዋስኑት በግምት ሁለት ቀርጥ ያህል የእርሻ መሬት ይዞታ
አላቸው፡፡ ይሁን እንጂ 1ኛ ተከሳሽ በምን አይነት ሁኔታ በእጁ እንደገባ በማይታወቅ ፎቶግራፋቸውን ለቦሌ ክፍለ ከተማ የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት በማቅረብ የአቶ አባይ መልካ ህጋዊ ይዞታ በሆነው 500 ካሬ ሜትር ካርታ ቁጥር ቦሌ 12/65/5/4/44876/00 በቀን 07/08/11 ዓ.ም የተሰጠ ካርታ ከ2ኛ እስከ 3ኛ በአቤቱታው ላይ ከተጠቀሱት የቦሌ ክፍለ ከተማ ባለሙያዎች ጋር በጥቅም በመመሳጠር ካርታ አሰርተው በእጃቸው ይገኛል ፡፡
ስለዚህ ተከሳሾች አባሪ ተባባሪ በመሆን 1ኛ ተከሳሽ የአመልካችን ስምና ፎቶ ግራፍ በማስለጠፍ እና በሕገወጥ መንገድ በሌላ ሰው ይዞታ ላይ በስማቸው ካርታ በማሰራት ከ2ኛ እስከ 3ኛ የተጠቀሱት ባለሙያዎች ካርታ የተዘጋጀበት ይዞታ አቶ አባይ መልካ ይዞታ መሆኑን እያወቁ ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር ተመሳጥረው የሌላ ሰው ይዞታ በመለወጥ ፎቶግራፋቸውን ለጥፈው በስማቸው ካርታ በማዘጋጀታቸው የፈጸሙት ወንጀል ተጣርቶ ለፍርድ ቤት እንዲቀርብላቸው
ያመለክታሉ ፡፡ ፍርድ ቤትም አቶ አሸናፊ ጌታቸውን እና ተባባሪ የሆኑትን የክፍለ ከተማ አመራሮችን ከሰሩት የተጭበረበረ ሰነድ ጋር እንዲቀርቡ ይጠይቃሉ፡፡ ነገር ግን ሰነዱን ሊያቀርቡ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በፖሊስ ሰነዱ እንዲቀርብ ይደረጋል ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ፍርድ ቤት ምክንያቱ በውል ባልታወቀ ነገር መዝገቡ መዘጋቱን ለከሳሽ ይነግራቸዋል፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ በመከሰቱ እና ልጅ በመውለዳቸው ምክንያት ከሳሽ ጉዳዩን በእንጥልጥል መተዋቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ ትዕግስት ፤ ከዚህ በኋላ ወዴት መሄድ እንዳለባቸው መጨነቃቸው ወይዘሮ ትዕግስት ይገልጻሉ፡፡ በዚህ መካከል የአዲስ ዘመን ዝግጅት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ስሙ ቡልቡላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከመሬት ጋር ተያይዞ በርከት ያሉ የምርመራ ዘገባዎች መሰራታቸውን ይሰማሉ፡ ፡ ይህን ተከትሎ ወይዘሮ ትዕግስት ስለሁኔታው በስልክ ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል አቤት አሉ ፡፡ ዝግጅት ክፍሉም “ስለጉዳዩ ማስረጃ ሰነድ ይኖራቸው ”እንደሆነ ወይዘሮ ትዕግስትን ጠየቀን ፡፡ ይሁን እንጂ “ስለጉዳዩ ምንም ማስረጃ ሰነድ በእጃቸው እንደሌላቸው እና ሁሉን ማስረጃዎች በክፍለ ከተማ ይገኛል” ሲሉ
ጠቆሙን፡፡ ዝግጅት ክፍሉም ወደ ቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ማኔጅመንት በመሄድ የመሬት ማኔጅመንት ኃላፊ የሆኑትን አቶ ኡመር ደሴ ስለጉዳዩ የሚገልጸውን ማስረጃ እንዲሰጡን ጠየቀን ፡፡ ኃላፊውም ከሁለት ቀን መመላለስ በኋላ ማስረጃውን እንድናገኝ ወደ መዝገብ ቤት በመምራት ተባበሩን፡፡ ይሁን እንጂ መዝገብ ቤት ስለተፈጠረው ችግር የሚያስረዳ ምንም አይነት ሰነድ ሳይገኝ ቀረ፡፡
የአዲስ ዘመን ዘግጅት ክፍልም ስለሰነዱ የክፍለ ከተማውን የሰነድ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት
ጠየቀ፡፡ ጽሕፈት ቤቱም “ ዋና ሰነዱ (ኦርጅናል ዶክመንቱ) ለምርመራ በፖሊስ ስለተፈለገ 21/5/2012ዓ.ም በወንጀል ትራፊክ የምርመራ ምክትል ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት ለሙስና ወንጀሎች ምርመራ ምክትል ዳይሬክቶሬት ተሰጥቷል ”የሚል ምላሽ ተሰጠን ፡፡ ይህን ምላሽ ተከትሎ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ሰነዱ ይገኝበታል ወደተባለው አራዳ ጊዮርጊስ አካባቢ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት በማቅናት ሰነዱን እንዲሰጡን ጠየቅን ፡፡
ይሁን እንጂ በወንጀል ትራፊክ የምርመራ ምክትል ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት ለሙስና ወንጀሎች ምርመራ ምክትል ዳይሬክቶሬት ተወካይ የሆኑት ፖሊስ ሰነዱን ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል እንደማይሰጡ ነገር ግን ወደ ክፍለ ከተማው እንደሚመልሱት ነገሩን ፡፡ ይህን ተከትሎ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ከቀናት በኋላ ወደ ቦሌ ክፍለ ከተማ በማምራት ስለሰነዱ ጠየቅን ፡፡ ሰነዱንም አገኘን ፡፡ አርባ ሰባት ገፅ የያዘ ሰነድ ነው፡፡
“በፖሊስ ከተወሰደ ከዓመት በላይ የሆነው ሰነድ ኦርጅናል ስለመሆኑ ምን ያህል እርግጠኛ ናችሁ ? ምንም አይነት ኮፒ ሳታስቀሩ ኦርጅናል ሰነድ ለምርመራም ቢሆን መስጠት ተገቢ ነው ወይ ? ለምርመራ ከተፈለገስ ለምን ኮፒ አይሰጥም ? እና የመሳሰሉትን ሌሎች ጥታቄዎችን ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ያልናቸውን ጋር ቃለ ምልልስ አደረግን፡፡
በዚህም መሰረት መጀመሪያ ያናገርናቸው የቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት ማኔጅመንት ኃላፊ የሆኑትን አቶ ኡመር ደሴን ነው ፡፡ እንደ አቶ ኡመር ገለጻ ፤ ማንኛውም በሕግ ዙሪያ የሚሰራ የመንግሥት አካል ለምርመራ ዋና ሰነድ ( ኦርጅናል ዶክመንት) ቢፈለግ እና ኦርጅናል ዶክመንት ይላክን ተብሎ በደብዳቤ ቢጠይቅ በጥያቄው መሰረት ኦርጂናል ዶክመንት ወይም ዋናው ሰነድ ይላክላቸዋል፡፡ ምርመራቸውን ከጨረሱ በኋላ ዋናው ሰነድ (ኦርጅናል ዶክመንቱን) ይመልሳሉ፡፡ “የተመለሰው ሰነድ ዋና ሰነድ (ኦርጅናል ዶክሜንት ) መሆኑን ለማረጋገጥ ከምርመራ በኋላ የሚመጣውን ዶክሜንት ኦርጅናል መሆኑን እንዴት ማወቅ ትችላላችሁ?” ሲል የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል አቶ ኡመርን ጠይቆ ነበር ፡፡ አቶ ኡመርም እንዲህ ይላሉ “እኛ ጋር ያለው ሰነድ ወረዳም ላይ ይገኛል፡፡ በግለሰቦችም እጅ የሚይዙት ሰነድ ይኖራቸዋል፡፡ ነገር ግን ለምርመራ የሚፈልገው የመንግሥት ተቋም እስከሆነ ድረስ ዋናው ሰነድ በተመሳሳይ ይተካል የሚል ግምት የለንም ፡፡”
“የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ከመመሪያ አንጻር ዋናውን ሰነድ (ኦርጅናል ዶክሜንት) መስጠት ይቻላል?” ሲል አቶ ኡመርን ይጠይቃል፡፡ ይህንን ጥያቄ ተከትሎ አቶ ኡመር እንደገለጹት ፤ ለደህንነት ሲባል ኮፒ እያደረጉ በማስቀረት ዋናውን ሰነድ ለምርመራ መስጠት
ይቻላል ፡፡ ነገር ግን እጅግ ብዙ ጥርጣሬ ያለባቸው ሰነዶች ለምርመራ ስለሚጠየቅ ያን ሁሉ ኮፒ ማድረግ አስቸጋሪ ነው ፡፡ ይሁን እንጂ አሁን የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ያነሳቸው ጥያቄዎች አግባብነት ስላላቸው እንደግብዓት መውሰድ ወደፊት የምንሰራባቸው ይሆናሉ፡፡
ሌላው ከሰነድ ጋር ተያይዞ የጠየቅናቸው የቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት ይዞታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑትን አቶ ይስሃቅ ሻፊ ነበር ፡፡ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል አቶ ይስሃቅን እንዲህ ሲል ይጠይቃል “ዋናውን ሰነድ (ኦርጅናል ዶክሜንት) ለሶስተኛ አካል አሳልፎ መስጠት ከመመሪያ አንጻር እንዴት ይታያል?” የሚል ነበር፡፡ አቶ ይስሐቅ ለተጠየቁት ሲመልሱ ፤ ስለመመሪያው ምንም ግንዛቤው የላቸውም ፡፡ የመንግሥት ተቋማት ከምንም ጋር በተያያዘ ዋናውን ሰነድ ሲጠይቁ እንሰጣቸዋለን፡፡ ምክንያቱም የመንግሥት ተቋማት ዋናውን ሰነድ ይቀይራሉ ብለን ስለማናምን፡፡
ይህን ተከትሎ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም “ለዛሬ ቃለምልልስ የጋበዘን ባለቤቱ የማያውቀው የቤት ካርታ የመንግስት ተቋማት ስለሰጠ አይደለም እንዴ ? መንግሥታዊ ተቋም ስለሆነ ብቻ ምንም ስህተት አይሰራም ለማለትስ ይቻላል?” ሲል ይጠይቃል፡፡ በዚህ ጊዜ አቶ ይስሐቅ ንዴት በተሞላበት አኳኋን “ቃለምልልሳችንን እናቁም !” በማለት ለዝግጅት ክፍሉ ምላሽ ሰጥተውናል ፡፡
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም መረጃ ፈልገን እንደሄድን ለአቶ ይስሐቅ በመግለፅ አቶ ይስሐቅን እንደገና ለቃለመጠይቁ አግባብተን ለመንግሥታዊ አካላት ክፍለ ከተማው እንዴት ሰነድ እንደሚሰጥ እንዲያብራሩ አደረግን ፡፡ አቶ ይስሐቅም መንግሥታዊ መዋቅር ላይ ያሉ ተቋማት እንደወንጀል ምርመራ፣ ፀረ ሙስና ያሉ አካላት በቀጥታ የግለሰብ ስም ጠቅሰው ዋናውን ሰነድ (ኦርጅናል ዶክመንት) ላኩ ሲሉን ኮፒ አስቀርተን ዋናውን ሰነድ (ኦርጅናል ዶክመንት) እንልካለን ፡፡ ኮፒ ሲቀር የተቆጠረበት ገፅ የፋይል ቁጥር እና ሌሎች ነገሮችን ከግንዛቤ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ምርመራውን ሲጨርሱ ዋናውን ሰነድ መልሰው ያመጡታል ፡፡ አሁን ላይ ያለው እና እየተሰራበት አካሄድ ይህ ነው ፡፡ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ከወይዘሮ ትግስት ጋር በተያያዘ ኮፒ አላስቀራችሁም ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ “ከምርመራ በኋላ የሚመለሰውን ሰነድ ዋናው ሰነድ መሆኑን እንዴት ታውቃላችሁ? ለምንስ ኮፒ አላስቀራችሁም ? ” ስንል ጠየቅን ፡፡ ከዚህ ጋር ዋናው ሰነድ ወረዳም ላይ ስለሚገኝ ከዚያም ጋር እንደሚያመሳክሩ የሚናገሩት አቶ ይስሐቅ፤ ነገር ግን የዋናው ሰነድ ኮፒ ግን ክፍለ ከተማ ላይ መገኘት ነበረበት ይላሉ ፡፡ ይህን ያለአደረጉ አካላትን በአሰራሩ መሰረት እንደሚጠየቁ አመላክተዋል፡፡
ሌላው ከሰነድ አያያዝ ጋር ጥያቄ ያነሳንላቸው በቦሌ ክፍለ ከተማ የማህደር አስተዳደር ቡድን መሪ የሆኑትን አቶ ደምሴ ጌታቸውን ነበር ፡፡ እንደ አቶ ደምሴ ገለጻ ፤ በመመሪያው መሰረት አንድ ማህደር ከሕግ ትዕዛዝ ውጭ ለሶስተኛ ወገን ኮፒ እንኳን ተደርጎ አይሰጥም ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሕግ አካላት የሚባሉት እነማናቸው የሚለውን በዝርዝር ያስቀምጣል ፡፡ ፖሊስ ፣ፍርድ ቤት ወዘተ ብሎ ያስቀምጣል ፡፡ ከፍርድ ቤት ዋናውን ሰነድ (ኦርጂናል ዶክመንት) ላኩልን ብሎ ደብዳቤ ከተላከ እና ደብዳቤ ለመውሰድ የሚመጣው አካል ከተገለጸለን ኮፒ በማስቀረት ዋናው ሰነድ ደብዳቤ ለፃፈው የሕግ አካል ይላካል፡፡
አቶ ደምሴ አክለውም አንድ ሕጋዊ የመንግሥት አካል ሰነድ እንዲሰጠው ደብዳቤ ሲልክ የሚመለስበትንም ቀነ ገደብም እንዲያስቀምጥ መመሪያው ይጠቅሳል ፡፡ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም “አንድ ዋና ሰነድ ለምን ያህል የጊዜ ገደብ በሕግ አካላት እጅ ሊቆይ ይችላል?” ሲል አቶ ደምሴን ጠይቆ ነበር ፡፡ ለምርመራ ምን ያህል ጊዜ እንደሚፈጅባቸው የሚያውቁት መርማሪዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ መርማሪዎች ምርመራቸውን እንደጨረሱ ይመልሳሉ፡፡ ዋናው ሰነድ እስከሚመለስ ኮፒው ኮድ ተሰጥቶት ከተጠየቀበት ደብዳቤ ጋር እና ከወሰደው ሰው ፊርማ ጋር ተያይዞ በጊዜያዊ ማህደር ይቀመጣል፡፡ ዋናው ሰነድ ሲመጣ ከኮፒው ጋር በማመሳከር ወደ ፋይሉ እንዲገባ ይደረጋል፡፡
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም “ከወይዘሮ ትዕግስት ጋር በተያያዘ የእናንተ ቢሮ ኮፒ አልተቀመጠም ፡፡ ስለዚህ የሚመጣውን ሰነድ ዋናው ሰነድ መሆኑን እንዴት ታረጋግጣላችሁ? ” ሲል አቶ ደምሴን ይጠይቃል፡፡ አቶ ደምሴም ዋናው ሰነድ ስንልክ ከጀርባ ቁጥር ሰጥተን ማህተም ጨምረን ነው የምንልከው ፡፡ በዚህ ማረጋገጥ የሚቻል ቢሆንም ኮፒ ሳይቀመጥ ለሕግ አካላትም መሰጠት የለበትም ፡፡ ይህ ተደርጎ ከሆነ የሰጠው አካል ተጠያቂ ይሆናል ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል፡፡
በፖሊስ እጅ የቆየው ሰነድ እንደሚያመለክተው ካርታው አገልግሎት እንዳይሰጥ መክኗል ይባል እንጂ ፍርድ ቤት የወሰነው ውሳኔ በወረዳው ሆነ በክፍለ ከተማው አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ሊገኘ አልቻለም፡፡
የፍርድ ቤት ውሳኔ ምን እንደሆነ፣ ማንስ በሕግ እንደተጠየቀ፣አሁን ላይ በሕገወጥ መንገድ ካርታ የተሰራበት ቦታ በምን ደረጃ እንደሚገኝ እና በደል የተፈጸመባቸው አርሶ አደር እንደሌሎች አርሶ አደሮች መሬት ይሰጣቸው ይሆን ስንል ለወረዳ 12 የመሬት ማኔጅመንት ባለሙያ ለሆኑት ለአቶ ዮናስ ተስፋዬ ጠይቀን ነበር ፡፡ አቶ ዮናስ ከፍርድ ቤት ስለጉዳዩ የመጣ ነገር ባለመኖሩ ስለጉዳዩ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸው፤ ወይዘሮ ትዕግስት አርሶ አደር ከሆኑ እና ማህደራቸው አርሶ አደር እንደሆኑ መረጃ ካለ እንደማንኛውም አርሶ አደር የመኖሪያ ቤት ሊሰጣቸው እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2013