አሁን ላለንበት አገራዊ ሁኔታ መውጫ ይሆነን ዘንድ ጥበብን ከሰለሞን (ሱሊማን) ትዕግስትን ከእዮብ (አዩብ) መማር ግድ ይለናል፡፡ እውነትን ለማሳየት ጥበብ መጠቀምና እውነታው እንዲታወቅ መታገስ በብርቱ ስለሚያስፈልገን፡፡ ጠቢቡ ሰለሞን ሁለት እናቶች አንድን ህፃን ልጅ “የእኔ ነው! የእኔ” በሚል ክርክር ገጥመው የህፃኑ ልጅ እናት ማንነት የለየበት ልዩ ጥበብ ያስደንቀኛል፡፡
ውዶቼ! አስቡትማ ፤ያቺ የምር ልጅዋ በሌላ የእኔ ነው በተባለባት እናትና የራስዋ ያልሆነን ልጅ የእኔ ነው ባለችው እናት መሐል ያለው ልዩነት፡፡ በእርግጥ ሁለቱም እናቶች ልጅ ወልደው ነበር፡፡ አንደኛዋ ወዲያው በሞት ተነጠቀች፡፡ ሌላኛዋ እናት ደግሞ የወለደችውን ልጅ ታቅፋ በተኛችበት በዚያች ወልዳ ልጇ በሞተባት እናት ተሰረቀባት፡፡ እናት የእስዋ ልጅ ፈፅሞ እንዳልሞተና እንደተሰረቀባት ባወቀች ጊዜ ልጄን መልሽልኝ
አለቻት፡፡ ነገር ግን ልጅዋን በሞት ያጣችው እናት የእኔ ልጅ ነው፤ የአንቺ ሞቷል ስትል መለሰችላት፡፡
ይሄኔ ክርክር ተነሳና አለመግባባቱ ጠነከረ፡፡ ሁለቱን እናቶች ልጁ የእኔ ነው በሚል ሙግት ውስጥ የሚያስታርቃቸው ጠፋ፡፡ በመጨረሻም ንጉሱ ዘንድ ቀረቡ፡፡ ይህ ንጉስ ጥበበኛ ነበርና ሁለቱንም ጎን ለጎን አቁሞ ሀሳባቸውን ጠየቀ ፡፡ ሁለቱም ልጄ ነው ያሉበትን ምክንያትና እውነት አስረዱ ፡፡ ያቀረቡት ማስረጃ ሁሉ ግን ተመጣጣኝ ነበር ፡፡ እውነትና ውሸት ልክ የሚያስመስል ማስረጃ ታውቃላችሁ ፡፡ ልክ እንደዚያ ማለት ነው፡፡
ይሄኔ ጥበበኛው ንጉስ አንድ ነገር አሰበና ለወታደሮቹ እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፡፡
ጎራዴ አምጡና ልጁን ለሁለት ቦታ ክፈሉት፤ እናም የልጁን አካል ግማሽ ግማሽ ይካፈሉት
አላቸው፡፡ ሴቶቹም በዚህ ይስማሙ እንደሆን ጠየቀ፡፡ ይሄን አንደኛዋ እንደተስማማች
ተናገረች፡፡ አንደኛዋ ደግሞ በዚህ ሀሳብ ደንግጣ ተብረከረከች፤ ልጇ ሊጎዳ ሊቆረጥ ነውና ፍርሀት ያዛት፤ በሀሳቡም አልተስማማችም፡፡ እያለቀሰች ፤ ልጁ ለሁለት ተከፍሎ ከሚጎዳብኝ እና ከሚሞት እርስዋ ትውሰደው ብላ ተናገረች፡፡
በዚህ ንግግር የህፃኑ እውነተኛ እናትነት ተለየ፡፡ እውነተኛ የእናትነት ፍቅርና እውነት ያለው የትኛዋ እናት ጋር እንደሆነ በቀላሉ ተለየ፡፡ ልጄ እንዳይጎዳ እስዋ ትውሰደው በቃ ያለችው እናት እውነተኛ እናት መሆንዋ ታወቀ፡፡ የራስዋ ያልሆነው የእኔ ያለችው ደግሞ የራስዋ እንዳልሆነ ተረጋገጠ፡፡
አዎን የእኛን እውነት ለሌሎች ለመግለጥ የሚያስፈልገን ጥበብ ነው፡፡ እዚያው እውነት ላይ ፀንቶ በመቆም የሚገኝ ዘላቂ የሆነን ድል ማጣጣም ነው ያለብን ፡፡ የዚህች ታላቅ አገር እውነት ላይ መፅናት፤ የዚህ ሕዝብ በሀቅ ላይ መቆም ፈፅሞ ሳይለዝብ መቀጠል የሚኖርበት ወቅት ላይ ነን ፡፡ እውነታችንን ተቀምተን የቆምንበት ሃቅ ተወስዶብን ዛሬ ተሸናፊ መስለን ልንታይ እንችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን እያደር እውነት ፀሀይ መሞቅዋ አይቀርም፡፡ ያኔ ከፍ ብልን የምንታየው እኛ ነን፡፡
እርግጥ ነው ፤እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል፡፡ በትዕግስት ውስጥ የሚገኝ ድል ይጥማል፡፡ በጥረት የሚገኝ ስኬት ወደር የሌለው ነው፡፡ እውነት ላይ ፀንቶ የቆመ የቆመለትን ዓላማ ሳያሳካ ቢያልፍ እንኳን በእውነት መዛግብት ውስጥ ጎልቶ ይወሳል፡፡ የያዘው እውነት የቆመበት ሀቅ ውሎ አድሮ ሁሉም ይረዳውና ስለእውነት ብሎ በፈፀመው ታላቅ ተግባር ሲዘከር ይኖራል፡፡ በተፈጥሮው ተሰባሪ የሆነው ሰው የማይሰበረውንና ዘላለማዊ የሆነውን እውነት ከራሱ በላይ ከፍ አድርጎ ማንገስ የሚገባው ለዚሁ ነው ፡፡
ማን ነበር “ጩኸቴን ቀሙኝ” ያለው? ይህ ግለሰብ ወይም አካል የተቀማው እውነቱን የተነጠቀው ፍትህን መሆኑ ለምን እንዲህ አለ ብለን ብንመረምር የሚሰጠን ምላሽ ነው ፡፡ ራሳችሁ ተጎድታችሁ ስታበቁ የጎዳችሁ አካል ከእናንተ ጉዳት አግዝፎ “እኔ ነኝ የተጎዳሁት” ብሎ መጎዳቱን ቢያውጅ ይሄን እወጃ ተከትሎ የሰማ ሁሉ እናንተ ላይ ቢፈርድ ምን ይባላል ጎበዝ አያድርስ ነው ፡፡
ምንም ያህል ለእውነት የቀረበ የሚመስል ማስረጃ ቀርቦ እውነት ቢሸፋፈንም፣ እውነትን ይፋ ማድረግ ልዩ ጥበብ መላበስ ይጠይቃል ፡፡ እርግጥ እኛ ጋር ያለው እውነት በብዙዎች ቢታበይም እውነታችን ግን ከእውነትነቱ ፈፅሞ ሊወርድ አይችልም ፡፡ የከፍታ ጥግ ላይ የሚያደርሰው እውነት እንጂ አስመስለው በቀጠፉት እብለት አልያም እውነት እንዲመስል በተዶለተ ሀሰት አይደለም፡፡
ይህቺ ታላቅ አገር እውነት ላይ መቆምዋን ዓለም ቢያውቅም እውነቷን ሊቀሟት ፍትሐዊ ተጠቃሚነትዋን ሊያዳፍኑባት ያኮበኮቡም ተገኝተዋል፡፡ ወገን ዛሬ ዓለም ጆሮ የምትሰጥህ በያዝከው እውነት ልክ አይደለም፡፡ እስዋ ከአንተ መስማት የምትፈልገውን ርዕሰ ጉዳይ ብቻ
ነው፡፡ አንተ እውነትነት ያለው አቋም ይዘህ ቅረብ፤ አልያም መነሻህ ፍትሐዊነት ያዘለ መርህ ይሁን ፤በዚያኛው መነፅር ስትታይ የአንተ እውነታ ምንም ነው፡፡
ሩቅ ተሻግረህ ተመልከት ፤ የእነሱ አሳፋሪ የሰብዓዊ መብት ረገጣ በዓለም ላይ ተወዳዳሪ የሌለው መሆኑን በብዙ መልኩ ማስረዳት ይቻላል፡፡ማስረጃዎች ሲቀርቡ የሚያስተጋቡት ግን ጥቂቶች ናቸው፡፡ምክንያቱም ለዓለም የሚያስተጋቡት ልሳኖቻቸው የተገነቡት በራሳቸው የተቀጠቀጠ ሀሰት፤እውነት መስሎ በሚታይ እብለት ላይ ስለሆነ፡፡
አንዳንድ ምዕራባውያን መንግሥታት ለጥቅማቸው የሚቀጥፉ ለራሳቸው ጥቅም ብዙዎችን ለመስዋዕትነት የሚያቀርቡ ራስ ወዳዶች መሆናቸው ዓለም አውቆት ያልተነፈሰው ሀቅ ነው፡፡ ነገር ግን እውነት ነገ ላይ አቅም ማግኘቱ ፀሀይ አንድ ቀን መውጣትዋ አይቀርምና ተስፋችን አይነጥፍም፡፡ በዓለም ታሪክ እውነትን ይዘው ያለፉት አገራትና ሕዝቦች በተለየ መልክ ይወሳሉ፤ስለ እውነት ፀንተው የቆሙት በአያሌው ይዘከራሉ፡፡
እኛም እንደ ሕዝብ እውነት ላይ መቆም ያለብን ለዚህ ነው፡፡ ምድር በሙሉ በሀሰት ትርክት ተገፍቶ እኛ ላይ ቢፈርድ ለእውነት እስከቆምንና እዚያ ላይ እስከፀናን ድረስ አሸናፊዎቹ እኛ ነን፡፡ ኢትዮጵያ በታሪክዋ እውነት ፊት ቆማ ተሸንፋ አታውቅም፤ ምክንያቱም የእውነተኞች መኖሪያ አገር ስለሆነች፤ ለእውነት ብለው በተዋደቁ ጀግኖች ደምና አጥንት የተዋቀረች ስለሆነች፡፡ ዛሬም ነገም ሁሌም ኢትዮጵያና እውነት ያሸንፋሉ፤ቸር ይግጠመን፡፡
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2013