ወይዘሮ መሰረት ታደሰ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት ቀጣና አንድ ነዋሪ ናቸው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በየቤቱ እየተዟዟሩ ልብስ በማጠብ እርሳቸውንና ሦስት ልጆቻቸውን ለማስተዳደር ያደርጉት የነበረውን እንግልት እንዲህ ያስታውሱታል፡፡ ‹‹ክፍያው በቂ አይደለም በዛ ላይ ሁሌ ስለማይገኝ መሳቀቁም አንድ ችግር ነበር፡፡ አሁን በከተማ ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ከታቀፍን በኋላ ቋሚ ገቢ ስላለን አንሳቀቀም፡፡ ገንዘቡም ቀላል አይደለም፡፡ ከቀኑ አራት ሰዓት በኋላ ነጻ ስለምንሆን ሌሎች ነገሮችም መሥራት እንችላለን›› ይላሉ፡፡
ወይዘሮ መሰረት ጨምረው እንደተናገሩት በሴፍቲኔት የአካባቢ ፅዳት ሠርተን 300 ብር ቁጠባ ተቀንሶ 1200 ብር በየወሩ ይሰጠናል፡፡ እኛ ደግሞ የሁለት መቶ ብር እቁብ እንጥላለን፡፡ ይሄም ከእለት ፍጆታ ውጪ አንዳንድ ቋሚ ንብረት እንድናፈራ ያስችላል፡፡ በተጨማሪም በወር አስር አስር ብር በባንክ እንቆጥባለን፡፡ይህንንም ለወለዱና ለታመሙ ሰዎች መጠየቂያ እናውላለን፡፡ በከተማ ጽዳትም በኩል ሕብረተሰቡ ለውጥ እያመጣ ይገኛል፡፡ እነዚህ ትላልቅ ሰዎች የሚያጸዱት ነው እያለ ቆሻሻ ሲያስወግድም በጥንቃቄ እየሆነ ነው፡፡ በመሆኑም ፕሮግራሙ እኛን ብቻ ሳይሆን ነዋሪውንም ተጠቃሚ እያደረገ ነው ይላሉ፡፡
ከገንዘቡ ጎን ለጎን በማህበራዊ ህይወታችንም ተጠቃሚ አድርጎናል የሚሉት በወረዳው የቀጣና ሁለት አስተባባሪ የሆኑት ወይዘሮ ሮማን ደበበ ናቸው፡፡ ወይዘሮ ሮማን እንደሚያብራሩት በወረዳው 90 ድጋፍ የሚደረግላቸው ሰዎች ሲኖሩ ለሦስት ቡድን ተከፍለን ሥራ ስንጨርስ የቡና ጠጡ ፕሮግራም እናደርጋለን፡፡ በዚህም ስለ ሥራችን ስለሀገር ስለሰላምና ሌሎችም ማህበራዊ ጉዳዮችም እናወራለን፡፡ ከግዴታው ቁጠባ ውጪ ሁለት መቶ ሁለት መቶ ብር እንቆጥባለን፡፡ ይህም ከሦስት ዓመት በኋላ መንግሥት የሚያደርገው ድጋፍ ሲቆም ራሳችንን ችለን ለመውጣት ጥሪት ለመያዝ ነው:: በየግላችንም የሚያዋጣንን ሥራ መርጠን ለመቀጠል እየተዘጋጀን እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ በወረዳው የቀጣና ስድስት ነዋሪና አንድ ለሰላሳ ቡድን መሪ የአሥር አለቃ እሸቱ ሽፈራው፣ እስከ ዛሬ ከእጅ ወደ አፍ እንኳ ለመኖር ይከብደን ነበር፡፡ ዛሬ ወር ከወር ቋሚ ገቢ አለን ይላሉ፡፡ አሁን እንደ ድሮው ጠዋት ተነስተን ሥራ ከመፈለግ ሥራ አለን ብለን እንወጣለን፡፡ ለልጆቻችን ሳንሳቀቀ ማብላት ችለናል፡፡ ሥራው ደግሞ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት እስከ አራት ሰዓት የሚጠናቀቅ በመሆኑ ከዛ በኋላ ሌላ ለመሥራት እድሉ አለን፡፡ እኛ ሁለተኛው ዙር ተጠቃሚ ብንሆንም ባለፉት ስምንት ወራት ለእለት ከምናውለው ባለፈ እንደየአቅማችን በመቆጠብ ጥሪት ማፍራትም ችለናል፡፡ እስካሁን ብዙ ሰው ተጠቃሚ ሆኗል፣ ነገር ግን አሁንም ብዙ መረዳት ያለባቸው ችግረኞች በየቤቱ አሉ ፡፡ ሥራውን በተመለከተ ግን የጽዳት ሥራ ለብዙ ነገር ስለሚያጋልጥ ነጻ ህክምና ሊሰጠን ይገባል፡፡ እንደ ቦቲ ጫማና የሥራ አልባሳት በበቂ ሁኔታ ይቀረብላችኋል የተባለ ቢሆንም እየቀረበ አይደለም፡፡ እነዚህ ቢስተካከሉ የበለጠ ደስተኛ ሆነን እንሠራለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በአራዳ ክፍለ ከተማ የምግብ ዋስትናና ልማታዊ ሴፍቲኔት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀብቶም ዘሚካኤል በበኩላቸው ክፍለ ከተማው ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቀጥሎ በድህነት ሁለተኛው ነው፡፡ በመሆኑም ቁጥሩ ብዙ ቢሆንም አሁንም ያልተካተቱ በርካቶች አሉ ይላሉ፡፡
አቶ ሀብቶም እንደሚያብራሩት እንደኛ ደረጃ የደሃ ደሃ፣ሁለተኛ ደሃ፣ ሶስተኛ መካከለኛ፣ አራተኛ ሀብታም ተብሎ ይለያሉ፡፡ በሁለቱ ዙሮች በዘጠኝ ወረዳዎች 20 ሺ 608 ዜጎች በደረቅ ቆሻሻ፣በተፋሰስ ልማትና በአረንጓዴ ልማት ተሳትፈዉ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡በድጋሜ ማጣራትም 372 ተተክተዋል፡፡ 2005 ዜጎች ደግሞ ምንም መስራት ስለማይችሉ የቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ በክፍለ ከተማው አስር ወረዳዎች ያሉ ሲሆን እስካሁን ዘጠኙን ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በሶስተኛ ዙር ተጠቃሚ የሚሆኑት ከቀረው ወረዳ ሰባት የተመረጡ ናቸው፡፡ ልየታ ተሠርቷል በዚህም 19 ሺ 828 የተለዩ ሲሆን 2800 ተጠቃሚ ይሆናሉ ፡፡ የዓለም ባንክ በራሱ መንገድ መረጃውን ሰብስቦ የማረጋጥ ሥራ ይሠራል፡፡ እነዚህም በአንድ ለአምስትና አንድ ለሰላሳ በመደራጀት ከላይ ከተዘረዘረው ውጪ በመጸዳጃ ቤትና አነስተኛ ድልድዮች ግንባታ መሳተፍ ይጀመራሉ፡፡ ለዚህም 154 አነስተኛ መለስተኛ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ተለይተዋል፡፡ በክፍለ ከተማው በሁለቱ ዙር 31 ሚሊዮን 466 ሺ 275 ብር ተከፈለ ሲሆን፤ 6 ሚሊዮን 293 ሺ 255 ብር መቆጠብ ተችሏል ሲሉ ተናግረዋል ፡፡
ፕሮግራሙ እንደ ሀገር ቢጀመርም ተጠቃሚ ከሚሆኑት ውስጥ ሰባ በመቶ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ናቸው የሚሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የልማታዊ ሴፍቲኔትና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ አሳምነው ጌራወርቅ ናቸው፡፡ ዳይሬክተሩ እንደሚብራሩት ፕሮግራሙ የተጀመረው በ2009 ዓ.ም በ35 ወረዳዎች ነበር፡፡ በወቅቱ 223 ሺ 918 በሁለተኛ ዙር ደግሞ በ55 ወረዳዎች 200 ሺ ዜጎች ተጠቃሚ ተደርጓል፡፡ ከነዚህ መካከል በተለያዩ ምክንያቶች መሥራት የማይችሉና ምንም የገቢ ምንጭ የሌላቸው 16 በመቶ የሚሆኑት የቀጥታ ድጋፍ የሚደረግላቸው ሲሆን፤ 84 በመቶው ደግሞ መሥራት የሚችሉ ነገር ግን ምንም አይነት የገቢ ምንጭ የሌላቸው በአካባቢ ልማት ሥራ በመሰማራት ድጋፍ የሚደረግላቸው ናቸው፡፡
የመረጣውንም ሒደት በተመለከተ በየቀጣናው ህዝቡ ራሱ ሁለት ኮሚቴ ያቋቁማል፡፡ አንደኛው ዘጠኝ አባላት ያሉት ሲሆን፣ ምልመላውን ይሠራል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ቅሬታ የሚሰማ ሰባት አባላት ያሉት ነው፡፡እነዚህ በከተማዋ ባሉት በ 782 ቱም ቀጣናዎች አሉ፡፡ በየቤቱ ምዝገባ ከተካሄደ በኋላ ነዋሪው በሀብት ደረጃው ተብሎ ይለያል፡፡ በሁለቱም ዙር 323 ሺ 918 ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፣ ለመጀመሪው ዙር 532 ሚሊዮን 52 ሺ 728 ብር፣ ለሁለተኛው ዙር 338 ሚሊዮን 124 ሺ790 ብር ክፍያ በመፈጸም 174 ሚሊዮን 35 ሺ 503 ብር ቆጥበዋል፡፡ ፕሮግራሙ የሚቆው ለሦስት ዓመት ብቻ በመሆኑ ተረጂዎቹ ከዛ በኋላ በዘላቂ ኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራም ታቅፈው እነሱ በቆጠቡትና በወቅቱ ምንዛሪ 500 ዶላር ከፕሮጀክቱ ለእያንዳንዱ ቤተሰብ መነሻ ካፒታል ይሰጠዋል፡፡ በዚህም የራሳቸውን ቢዝነስ ፕላን እንዲያቀርቡ በማድረግ ባቀረቡት መሰረት ሥልጠናና ድጋፍ ተደርጎላቸው ራሳቸውን ችለው ከተረጂነት በመውጣት እንዲኖሩ ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አቶ አሳምነው በተያዘው ወር የሚጀመረውን ሦስተኛ ዙር አስመልክተው እንደተናገሩትም፣ በአዲስ አበባ ካሉት 116 ወረዳዎች እስካሁን በሁለቱ ዙር 90 ወረዳዎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በሦስተኛው ዙር ደግሞ የቀሩት 26 ወረዳዎች ተጠቃሚ የሚደረጉ ሲሆን፤ ለዚህም ተቋም ማቋቋምና የልየታ ሥራ ተሠርቷል፡፡ በዚህም 92 ሺ አምስት ዜጎች የተለዩ ሲሆን፣ የሚሠሩትም ሥራ በህብረተሰቡ ድጋፍና ጥቆማ ተመርጦ ተጠናቋል፡፡ ባጠቃለይም በከተማዋ በቀጥታ ድጋፍና በአካባቢ ልማት በመሳተፍ በፕሮግራሙ 415 ሺ 923 ዜጎች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ለፕሮግራሙም ለአምስት ዓመት ከ 300 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት የሚደረግ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ ዓለም ባንክ 66 በመቶ እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግሥት 33 በመቶውን እንደሚሸፍኑ ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ