በቅድሚያ “ዳርዊኒዝም” የሕያውን ዓለም ታሪካዊ እድገት የሥነ-ሕይወትን ዝግመተ ለውጥ ንድፈ-ሀሳብ ባመነጨውና የሰው ልጅ ከሰው መሰል እንስሳት የተገኘ ለመሆኑ ሳይንሳዊ ማረጋገጫ ማቅረቡ በሚነገርለት እንግሊዛዊው የተፈጥሮ ሳይንቲስት ቻርለስ ዳርዊን ስም የተሰየመ አስተምህሮ መሆኑን፤ ንድፈ-ሀሳቡ ባጠቃላይ “ተፈጥሯዊ ማጣሪያ” (Natural selection) እና “ለህልውና መታገል” (Survival of the fittest) በሚሉ ጽንሰ ሀሳቦች ላይ መመስረቱን፤ እንዲሁም በቀዳሚነት “The Origin of Species by means of natural selection or the preservation of favored races in the Struggle for life” (1859)፤ “Origin of the species” (1860) የሚሉት ሥራዎቹ ከተፅእኖ ፈጣሪዎቹ ቀዳሚዎቹ መሆናቸውን በመያዝ ወደ ውስጥ እንዘልቃለን። (ከዝርያዎች የአፈጣጠር፣ ሂደትና ለውጥ ጋር በተያያዘ ያሉትን ሦስት መላ ምቶች (ሀይፖተሲስ) ማለትም:- የተለያየ አፈጣጠር ያላቸው፣ በሂደት የማይለወጡና በመጨረሻም እርስ በርሳቸው የተለያዩ ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያመለክተው Creationism፤ የተለያየ አፈጣጠር ያላቸው፣ በሂደት ሊለወጡ የሚችሉና በኋላም አንዳቸው ካንዳቸው ሊለያዩ የሚችሉ – Transformism፤ እንዲሁም ሁሉም ዝርያዎች የጋራ አፈጣጠር ያላቸው፤ በሂደትም ሊለወጡ የሚችሉ (ዳርዊን “Descendant with modification” የሚላቸው) – Evolution፤ ከዝግመተ ለውጥ ጥናት ጋር በተያያዘ የማይዘለሉ መሆናቸውን መገንዘብ ይገባል።)
ዓለምን ለሁለት በመሰንጠቅና አመለካከትን በተቃራኒ አስተሳሰብና ተግባር በመክፈል ይህችን የዛሬዋን ውስብስብና ግራ አጋቢ ዓለም ከፈጠሩት “ዲያቢሎስ” ፈላስፎች አንዱ ነው የሚሉት ብዙዎች ናቸው፤ ይህ ወቀሳም ገና ሥራዎቹን አደባባይ ማውጣት ከጀመረበት ወቅት ጀምሮ መሆኑ ስለ እሱ የተሰጡትና የሚሰጡት አስተያየቶች ያስረዳሉ። በእርሱ ላይ የተጠኑትም በርካታ ጥናቶች (Biographies)) እንዲሁ።
ይህም “ካፒታሊዝም” እና “ሶሻሊዝም” በማለት ዓለምን በሁለት የማይታረቁ ርእዮቶች በመክፈልና በማጠዛጠዝ፤ ሁለት ተቃራኒ (እርስ በእርስ የሚጫረሱ) ዓለማትን በመፍጠር ወደ እማያባራ ቀውስ ውስጥ “ከተተ” የሚባለውን ካርል ሔንሪክ ማርክስ (1818 – 1883)ን ጨምሮ ማለት ነው፤ ዳርዊንንም የሰው ልጅ አጥብቆ ከያዘው ሃይማኖታዊ እምነቱና ሳያወላውል ከተቀበለው የእግዚአብሔር ፈጣሪነት በመነጠልና ዓለም በሳይንስ እና በሃይማኖት መካከል እንድትዋዥቅ በማድረግ ዛሬ ላለንበት ዥንጉርጉርነት (ሳይንሳዊና ሃይማኖታዊ አተያዮች/ግጭቶች) ያበቃ፤ ከፈጠረው ፈጣሪ ጋር አምርሮ የተጣላ “እርኩስ” ሰው ሲሆን፤ ለዚህ ሁሉ ውርጅብኝ ያበቃው ደግሞ (ደበበ ሰይፉ “በስሙ ሰየማት” እንዳለው) በስሙ የተሰየመው “ዳርዊኒዝም”፤ በተለይም “የተፈጥሮ ምርጫ” (አንዳንዶች “የአውሬ ፍልስፍና” የሚሉት) እና “ለህልውና መታገል” (Survival of the fittest)ን የተመለከተ አስተሳሰቡን ከፍ ያደረገባቸው ከላይ የጠቀስንለት ሥራዎቹ ነው።
በዚህ ከፋፋይ (ሲበዛም አተራማሽ) ፍልስፍና አፍላቂና አራማጅነታቸው የሚታወቁ ፈላስፎች በርካታ ቢሆኑም በዚህ ጽሑፍ ግን በዳርዊንና ፍልስፍናው (ዳርዊኒዝም) ላይ ሀሳብ እንለዋጣለን። በተለይም ከ”የተፈጥሮ ምርጫ” ጋር በተያያዘ ያለውን የአሁኑን ዘመን አተያይ እናንፀባርቃለን።በአንድ ሰንበት ባለ ጽሑፍ ላይ እንደጠቀስኩትና አሜሪካን አገር ከሚታተመውና ከፍ ያለ ተቀባይነት ካለው (መሰረቱ ኃይማኖታዊ ሆኖ)፣ “The Good News” (ቅ∙18፣ ቁ∙6) መጽሔት “The Rotten Apples That Are Corrupting Society” በሚል መራር ርእስ ስር አምደኛና የፍልስፍና ተንታኙ ማሪዮ ሴይግሌይ ካብጠለጠሏቸው ፈላስፎች፣ ሳይንቲስቶችና እንቅስቃሴዎቻቸው፣ የአሁኑ ዘመን ትውልድ እንዲህ እንዲጠፋ ያደረጉ በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም በቀዳሚነት መንገዱን የጠረጉት ከ18ኛው ጀምሮ ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩት የ19ኛው ክ/ዘ ፈላስፎች ሲሆኑ፤ አንዱም ይሄው እየተነጋገርንበትና እያነጋገረን ያለው ዳርዊን (Charles Robert Darwin (1809 – 1882)) ነው።
እንደ ብዙዎች እምነት ፈላስፎቹ፣ በተለይም ሞገደኞቹ የማህበረሰቡን ልብና አእምሮ በመውሰድ ለተለያዩ ውድቀቶች የዳረጉት ሲሆን ለሞራል መላሸቅ፣ ለሰብአዊነት ድርቀት፣ ለነባር እሴት ጠልነት፣ ከፈሪሀ እግዚአብሔር ማራቅና የመሳሰሉት በቀዳሚነት ተጠቃሽ ናቸው። በተለይ ከፍተኛ የመጨቃጨቂያ አጀንዳ የሆነውን “እግዚአብሔር አለን?” (Does God exist?) የማይረባ ጥያቄ እንዲነሳና ሰዎች ፈጣሪያቸውን እንዲጠራጠሩ በማድረግ በሰውና በአምላክ መካከል ያለውን መንፈሳዊ ግንኙነት በመስበር አሉታዊ ሚና የተጫወቱት እነዚሁ ፈላስፋ ተብዬ ፈላስፎች ናቸው ባዮች ቁጥራቸው በየጊዜው እየጨመረ በመምጣት ላይ ነው።
ምንም እንኳን በደቀመዝሙራኑ (Neo-Darwinists) በኩል ተሰሚነት ባይኖረውም፤ ማይክል ዴንተን (1985) የተባለው ሰው የእነዚህን ሰዎች ፍልስፍና አምርሮ የሚቃወም ሲሆን በተለይ የ”ዳርዊኒያን ንድፈ-ሀሳብ”ን ከማብጠልጠል ባለፈ ከተረት ተረት ያልተሻለና ፍፁም የማይጨበጥ ሲል ከማጣጣልም አልፎ የሰውየውን ልፋት ሁሉ ከንቱ ያደርገውና ያርፋል። ከዘመናዊው ሳይንስ አኳያ ሲታይ “Everything about Darwin’s theory is false, illogical, impossible and a disgrace to science.” ከሚሉት አስተያየት ሰጪዎች (ለምሳሌ Tyke Morris) ጋር መሳ ለመሳ በሆነ አስተያየት ማለት ነው።
የኤማን ዳረዊን (1839 – 1882) የትዳር አጋር፤ የእንግሊዛዊው ማልተስ (Thomas Robert Malthus)ን ሥነ-ሕዝብ ላይ ያተኮረ ንድፈ-ሀሳብ (Malthusian Theory of Population) አድናቂና አዘውትሮም ሥራዎቹን በማንበብ የሚታወቀው ዳርዊን “ሕያው ዝርያዎች ሁሉ ከጋራ ወላጅ በዝግመተ ለውጥ እንደ ወረዱ …” የሚያሳየውን ሀልዮት ወይም ንድፈ-ሀሳብ (theory of evolution) ቀመረ። ንድፈ-ሀሳቡ ሰዎች ብቻ ሳይሆን “እንስሳትና ተክሎች ሁሉ ከአንድ ዝርያ ወደ ሌላ ዝርያ በመለወጥ አንድ ወላጅ እንደነበራቸው” ጭምር የሚያረጋግጥ ነው። (መለስ ብለው መግቢያ አንቀፃችንን ይመለክቱ።)
በግዙፍ ሥራውና ንድፈ ሀሳቡና አስተምህሮው (“Darwinism”) የተነሳ በ19ኛው ክፍለ ዘመኗ እንግሊዝ (ትውልድ አገሩ) የዳርዊንን ስምና ሥራዎቹን ከዓለማችን “አደገኛ” ፈላስፎችና ሥራዎቻቸው ምድብ ስር ያሰፈሩ ያሉ ሲሆን ምክንያታቸው ደግሞ “በአንጀሊካን ቤተክርስትያን ለዘመናት ሲታመንበት የኖረውን እምነት መፈታተኑና አጠቃላይ ሕዝቡንም ማምታታቱና ለጥርጣሬ መዳረጉ” መሆኑም በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል።
ይህ ንድፈ ሀሳብ ያስገኛቸው በርካታ ፅንሰ ሀሳቦች ያሉ ሲሆን ከሁሉም በላይ ግን ሁለቱ (“Branching descent” እና “natural selection”) ግን ለዳርዊን እጅጉን የገነኑለትና በአካደሚውና ምሁራን ደብር ዓለም አቀፍ ተፅእኖን የፈጠሩለት ናቸው። ሦስቱ ዋና ዋና የዝግመተ ለውጥ ዓይነቶችም (divergent, convergent, and parallel evolution)፤ አራቱ መርሆች (variation, inheritance, selection እና time)፤ በአምስት ዘርፎች ሊከፈል የሚችለው ፍልስፍናው (“evolution as such”, common descent, gradualism, population speciation, እና natural selection) ሊመደቡና
ሊተነተኑ መቻላቸው፤ ወይም በእነዚህ ዘርፎች ላይ አተኩረው የተከናወኑ መሆናቸው፤ በንድፈ ሀሳቡ መሰረት “ተፈጥሯዊው ምርጫ” (natural selection) በአራት (Stabilizing selection, directional selection, diversifying selection, frequency-dependent selection, እንዲሁም sexual selection) ሰፋፊ ዘርፎች/ዓይነቶች መከፈላቸውና ሁሉም ይህ ተፈጥሯዊ (የተፈጥሮ) ምርጫ በሰዎች (population) መካከል ልዩነት (variation) ይፈጠር ዘንድ የራሳቸውን አስተዋፅኦ ማድረጋቸው ነው።
ጉዳዩ እንዲህ ነው፤ በመግቢያችን ሰፋ አድርገን እንደተነጋገርንበት ዳርዊን ብዙ ተፅእኖ ፈጣሪ ሥራዎች አሉት። ይሁን እንጂ ዛሬም ድረስ፣ ምናልባትም እስከ ነገና ከነገ ወዲያ ድረስ፣ እንደ “የዝግመተ-ለውጥ ንድፈ-ሀሳብ” እና “የተፈጥሮ ምርጫ” የጦፈ ክርክር፣ ያልተቋረጠ ውዝግብና ያላባሩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች እንዲፈልቁ ምክንያት የሆኑ ሥራዎች የሉም። ይሁን እንጂ፣ ይህ በአጭሩ “የሰው ልጅ ምንጩ ዝንጀሮ ሲሆን ቀስ በቀስ በአዝጋሚ ለውጥ ወደ ሰውነት ተቀየረ” የሚል መልእክትን በቀዳሚነት የሚያስተናግደው የዳርዊን ፍልስፍና በሂደት ተቃውሞ እየገጠመው ይገኛል። “ከማስተማሪያ መጽሐፍት ውስጥ ካላወጣነው …” እስከማለት የዘለቀ እሰጣ’ገባ ድረስ ማለት ነው። (በአንዳንድ የጀርመን ተቋማት እየተስተዋለ ያለው ይህ አስተሳሰብ ወደ ተግባር ለመቀየር በአመራር አካሉ ተቀባይነት ማግኘትን ብቻ እየተጠባበቀ ይገኛል።) ምክንያቱስ?
ጥናቶቹ እንደሚናገሩት ዳርዊን ለነጮች ያደላ፣ የነጭ የበላይነት (ኋይት ሱፕሪማሲ)ን ለማስጠበቅ የሚጥርና ከእውነታ ውጪ የሆነ የፈጠራ ሥራውን ለህትመት በማብቃት ሰዎችን ለዘመናት ያሞኘ፤ እራሱን በፈጣሪ ቦታ ያስቀመጠ (እራሱን “Creationist” ብሎ የሰየመ) ሰው ነው። በመሆኑም የሱ ፍልስፍና ተብዬ ፍልስፍና ዕድሜው ከዚህ በላይ ሊቀጥል አይገባምና ውሳኔ ያስፈልገዋል የሚል ነው ቀዳሚ ምክንያቱ።
ዳርዊን “ሰው የመጣው ከሰው መሰል እንስሳ [ዝንጀሮ] ነው” የሚለው ፍልስፍናው ተቃውሞ ሲገጥመው የመጀመሪያ አለመሆኑ ቢታወቅም (የብዙዎችን ልብ እንዳልማረከም ጭምር) በተከበረበት የአካዳሚና ምሁራን ደብር የ”መነቀል” እድል (በጥናትና ሀሳብ ደረጃም ቢሆን) ሲገጥመው ግን ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
በመሸና በነጋ ቁጥር (በተለይም በአካዳሚያዊያን) ከሚጎነጡና እሚጎነተሉት ፈላስፎችና ንድፈ-ሀሳብ ቀማሪያን አንዱ የሆነው ዳርዊን ከእነ ኤንግልስ በፊት ይምጣ እንጂ ጥናቱ ሙሉ ይሆን ዘንድ ያላከናወናቸው በርካታ ጉዳዮች መኖራቸው ነው ሥራዎቹ በተጠኑ ቁጥር ፊት መሪ ሆነው የሚቀርቡት ሀሳቦች።
ከማህበረሰብ ጥናት አኳያ የዳርዊንና የማርክሲዝም፣ ሌኒኒዝምና ኤንግልስን ሥራዎች የመረመሩ አጥኚዎች እንደሚሉት ዳርዊን የሰው ልጅ ከእንስሳ መሰል ዝርያዎች መምጣቱን ያመላከተው በእርግጥ እነዚህ ፈላስፎች በፊት ቢሆንም ሥራውን ምሉእ ያደረገው ግን የማርክሲዝም ሌኒኒዝም ፍልስፍና ነው። በእርግጥ ይህ የዳርዊን ሥራ የሰውን ልጅ አመጣጥ በተመለከተ ነባሩን አስተያየትና እምነት የፈተነው ሲሆን በአዲስ መንገድ እንዲመረመርና እንዲፈተሽ ዕድል ፈጥሯል። ይሁን እንጂ ሥራዎቹ ሙሉ አልነበሩም። የዳርዊንን ሥራዎች ሙሉ እንዳይሆኑ ያደረጋቸው ደግሞ የሰውን ልጅም ሆነ ማህበረሰብን ከለውጥ፣ ተግባርና እንቅስቃሴ አኳያ አለመመርመሩ ( ስቴቨን ኪስተቭ “It doesn’t explain how evolution works out, rather why it’s happening.” እንደሚሉት ማለት) ነው።
የፍልስፍናው ተከታዮች (ለምሳሌ ሮዝ፣ Darwin, race and gender) በበከላቸው ዳርዊን በፍፁም በአሁኑ ዘመን መመዘኛ ሊሰፈር አይገባውም፤ ከተወለደ ከ200፣ “ዘ ኦሪጅን ኦፍ ስፒሽስ” ከተፃፈ እንኳን ከ150 ዓመት በኋላ ተነስተን ዳርዊን እንዲህ ነው/አይደለም ልንል አይገባንም። ምርጥ ሥራ ሰርቶ ማለፉን ልናደንቅ ነው የሚገባን ሲሉ ነው የሚሟገቱት። ዳርዊን ዘረኛ ሳይሆን የፍልስፍናው “መነሻ ለባርነት ያለው ስር የሰደደ ጥላቻ መሆኑ”ን በማስረጃነት በማቅረብ ጭምር።
ዳርዊንን የሚቃወሙ ወገኖች የሚተቹት አቋሙን ብቻ አይደለም አስተምህሮውም የሱ ሳይሆን አያት ቅድመ አያቶቹ ሲነግሩት የነበረውን ነው ቅርፅ ሰጥቶ ለሕዝብ እጅ ያደረሰው። “survival of the fittest”ም ቢሆን ዋና የሀሳቡ አመንጭ እሱ ሳይሆን ሀርበርት ስፔንሰር (1820 –1903) ነው እና የመሳሰሉትን በማሳያነት በመጥቀስ ነው።
በማርክሲስቶች ሂስ መሰረት ዳርዊኒዝም “የሰው ልጅ ከእንስሳት የመጣ መሆኑን ቢገልፅም የሰውን ልጅ ከእንስሳው ዓለም ሊለየው ያስቻለውን ማህበራዊ መንስኤ አላመለከተም። በዚህ ሽግግር ውስጥ በተለይ ሥራ የነበረውን ሚናና በኋላም ሥራ ተፈጥሮንም ሆነ ሰውን ራሱን ለመለወጥ የሚኖረውን ቦታ አልገለፀም። […] የሰው ልጅ ከእንስሳ የሚለይበትን ማህበራዊ ምክንይት ሥራው፣ ቋንቋውና አኗኗሩ መሆኑን በመግለፅ የተሟላ ሳይንሳዊ መደምደሚያ የሰጠው ኤንግልስ ነው።” በማለት ሥራው ያልተሟላ መሆኑን ከመግለፅም ባለፈ “ዳርዊን ቁስ አካላዊ አመለካከት የነበረው፣ ግብታዊ ዲያሌክቲክስን የሚያራምድና ኢአማኒ ነበር።
ይህ አቋሙ ከአንዳንድ የቡርዧ አስተሳሰቦች የፀዳ ባይሆንም ሥራው በሥነ-ሕይወት መስክ ለሳይንሳዊ ምርምር በር ከፍቷል። በተጨማሪም በሀሳባዊነት፣ በሥነመለኮትና በዲበ አካል ላይ ለሚደረገው ትግል አስተዋፅኦ ከማበርከቱም በላይ የተፈጥሮ ሳይንስ በዲያሌክቲካዊ ቁስ አካልነት ላይ እንዲመሰረት ረድቷል።” የሚለው የማርክሲዝም ሌኒኒዝም መዝገበ-ቃላት “ከቡርዧ አስተሳሰቦች የፀዳ ባይሆንም …” በማለት የገለፀው ከላይ በመግቢያ አንቀፃችን ላይ በጠቀስነው ሥራው ርእስ ውስጥ ያለውን “favored races” ያስታውሰናል። “Was Charles Darwin racist?” እና የመሳሰሉ ጥያቄ አንሺና መላሽ ጥናቶች እየተበራከቱ እንዲመጡም ገፊ ምክንያት እየሆነ መሆኑንም መናገር ይቻላል። ይህም ዳርዊን በሰዎች እኩልነት ላይ ያለውን አተያይ ጥያቄ ምልክት ውስጥ በመክተት ጉዳዩን ለአሁኑ ዘመን ክርክርን ይዳረግ ዘንድ ወደ መሬት አውርዶታል።
በ”ፈላስፎቹን በሁለት መልኩ” ላይ እንደገለፅነው የሰው ልጅ በፈጣሪ አምላኩ መፈጠሩን አምኖና በሃይማኖቱ ፀንቶ እየኖረ ሳለ “ይህ ስህተት ነው፤ የሰው ልጅ አመጣጥ ከዝንጀሮ ነው” በማለት የዓለምን “የሰው ልጅ አመጣጥ”ን የተመለከተ አስተሳሰብ በሁለት ተቃራኒ ጎራ የሰነጠቀውና የ”ተፈጥሯዊነት” አቀንቃኙ (Naturalist ነው) ቻርልስ ዳርዊንና ሌሎች 1800 እና 19ኛው ክ/ዘ ያፈራቸው በርካታ ፈላስፎች ሲሆኑ፤ እንደ “The Good News” ከሆነ እነዚህ ፈላስፎች የተወደዱትን ያህል እየተጠሉ፤ ፍልስፍናቸው የሚያለማውን ያህል እያወደመ፣ ምንልባትም የበለጠ እያወዳደመ፤ ከሚያስማማው የበለጠ እያጋጨ ወዘተ የሚኖር እንጂ ለዓለም ሕዝብ ምንም የፈየደውም ሆነ የሚፈይደው ነገር የለም።
ይህን መሰሉ ክርክር እየጦፈ፣ በተለይም የጥናትና ምርምር ርእሶች እየጠበቡና ወደ ጠጉር ስንጠቃ ደረጃ ድረስ እየዘለቁ (ይገባልም) በሄዱ ቁጥር የሚጠበቅ ነው። በመሆኑም የ19ኛው ክፍለ ዘመኑን ቻርለስ ዳርዊንን እዚህ እናንሳው እንጂ ይህን መሰሉ ዕጣ ፈንታ እየደረሳቸው ያሉም ሆነ የደረሳቸው በርካቶች ናቸው። ለምሳሌ “ልቅ ወሲብ እንዲስፋፋ አድርጓል” ተብሎ በሥነምግባር ምሁራን ዘንድ ሲዘለዘል የሚውለውንና የሥነ-ልቡና እውቀት አባት የሆነውን ሲግመን ፍሮይድን እዚህ መጥቀስ ይቻላል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2013