አዲስ አበባ በቅርቡ 11ኛ ክፍለ ከተማ መስርታለች፤ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ። ይህ የሆነው ደግሞ በከተማዋ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የተጀመሩ ሥራዎችን ስኬታማ ለማድረግ ፤ ከሰላምና ፀጥታ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ያሉ ክፍተቶችን ለመድፈንና ለነዋሪው የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት ይቻል ዘንድ ነው። በመሆኑም ይህንን ታሳቢ በማድረግ ክፍለ ከተማው ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ያለው አጠቃላይ ተክለ ቁመና ምን ይመስላል? አወቃቁሩስ? የተቋቋመበትን ግብስ አሳክቷል? ያለው ሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ምን ይመስላል የሚለውን የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈጻሚ ከሆኑት ከአቶ ኤልያስ መሐመድ ጋር ቃለምልልስ አድርገን እንደሚከተለው አቅርበናል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- መዲናዋን የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ከተማ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ይታወቃል። ክፍለ ከተማው ከተቋቋመ በኋላስ ምን ያህል ፕሮጀክቶች ተመረቁ? እርስዎስ የዚህ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ መሆንዎትን እንዴት ተመለከቱት?ዋና ስራ አስፈጻሚ፡- ይህ ክፍለ ከተማ ከተደራጀ ጊዜ አንስቶ የተሰሩ በርካታ ሥራዎች ናቸው። ቢሮውን በአመራር ከማደራጀት ጎን ለጎን ሲካሄዱ የነበሩ የልማት ስራዎችን ወደ አገልግሎት መስጠት ማብቃት ላይ በቅንጅት ከቦሌና ከየካ ክፍለ ከተማዎች ጋር ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል። የክፍለ ከተማው አወቃቀር ከቦሌና ከየካ ክፍለ ከተማዎች በተውጣጡ ወረዳዎች በመሆኑ ቀደም ሲል ሲሰሩ የነበሩ በርካታ ፕሮጀክቶች ተመርቀው አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው።
በወረዳና በክፍለ ከተማ ደረጃ በያዝነው ወር በርካታ ፕሮጀክቶች ተመርቀው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል። ከተመረቁት ውስጥ ሶስቱ ትምህርት ቤቶች ተጠቃሽ ናቸው። ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች ሀገር ናት። በተለይ አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ፣ የዓለም ዲፕሎማቶችና የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ከተማነቷን የምትገልጽ ናት። እንደ አዲስ አበባና እንደ ከፍለ ከተማችን የተያዘው እቅድ የአዲስ አበባ ህብረ ብሔራዊነትን የምትገልጽ ከተማ ናት ከተባለ ሁሉንም ሊገልጽ በሚችል መልኩ አደረጃጀት መኖር አለበት።
ሶስት ትምህርት ቤቶችን ስናስመርቅ ቀደም ሲል በየካ ክፍለ ከተማ በወረዳ 14 የነበረ አሁን ወደ ለሚ ኩራ የተጠቃለለ በሱማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሁለተኛ ከተማ በሆነች በጎዴ ስም የተሰየመ ነው። የጎዴ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚል ስያሜን ይዟል። እንዲሁም የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ዋና ከተማን አሶሳን በሚገልጽ መልኩ አሶሳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተብሎ ተሰይሟል። ሁለቱም ርዕሰ መስተዳድር እና ክብርት ከንቲባዋ በተገኙበት ተመርቀዋል። አዲስ አበባ የሚኖረው የሶማሌና ሌላው ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ በተገኙበት የተመረቀ ነው።
በአሶሳ ስም የተሰየመውን ትምህርት ቤትንም ብንወስድ በዛው ልክ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች በተገኙበት በክቡር አቶ አሻድሌ ሀሰን ተመርቋል። ሶስተኛው በሻሌ ትምህርት ቤት ሲሆን ቀደም ሲል በቦሌ የነበረ አሁን በአዲሱ ክፍለ ከተማ የተጠቃለለ ሲሆን ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል። እነዚህ ሥራዎች አዲስ አበባ የማንም በተለይ ደግሞ የአንድ የሁለት ብሔር ብቻ ሳትሆን የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች እንደሆነች ሁሉም በጋራ በእኩልነት የሚኖርባት መዲና መሆኗን ያስመሰከረችበት ነው።
ሁሉን በእኩል አቀናጅታ የምትይዝ ከተማ እንደሆነች ከተማ አስተዳደሩም እንደ አንድ ጠንካራ ስራ ወስዶ እየሰራበት ያለው ጉዳይ ነው። የእዛ ትሩፋት አንዱም እኔ ነኝ። ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላይ አይደለም በክፍለ ከተማ ደረጃ በወረዳ ደረጃም የሱማሌ ክልል ተወላጅ በአዲስ አበባ መስተዳድር ላይ የሚሰራ አልነበረም። ነገር ግን ከለውጡ በኋላ አዲስ አበባ ህብረ ብሔራዊ ነች የሚለውን በመያዝና የለውጡ አመራር በሰራው ሥራ በክፍለ ከተማ ደረጃ የሶማሌ ክልል ተወላጅ ክፍለ ከተማ ሲያስተዳድር እኔ የመጀመሪያው ሰው ነኝ። በተጠቃሚ ደረጃም ቢሆን የመጀመሪያው ሰው ነኝ።
ይህ ደግሞ ትልቅ ማሳያ ነው። በወረዳ በአመራር ደረጃ ብዙ ስራ የገቡ የሶማሌ ክልል ተወላጆችም አሉ። በክፍለ ከተማም የሚሰሩ አሉ። ይህ ደግሞ ብልጽግና ከተመሰረተ በኋላ የመጡ ለውጦች ናቸው። የለውጡ አመራር ኢትዮጵያን ለማስቀደም ሲያስብ አንዱ ልጅ አንዱ የእንጀራ ልጅ ሁኖ የሚኖርበት አግባብ መቆም አለበት። ሁሉም በእኩል ይችን ሀገር ማገልገልና መጠቀም አለበት። ከላይ የጠቀስኩልህ ትምህርት ቤቶች የልማትና የባህል ማዕከሎች ግንባታ ለክልሎች በአዲስ አበባ እየተሰጠ መሆኑ እውነትም አዲስ አበባ ህብረ ብሔራዊ ነች የሚለውን በተግባር የሚገልጽ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የክፍለ ከተማው አወቃቀር ምን ይመስላል? ምን ያህል ወረዳዎችስ በስሩ አሉት?
ዋና ስራ አስፈጻሚ፡- ክፍለ ከተማው አደረጃጀቱ ከዜሮ የሚጀምር ነው። የሰራናቸው ሥራዎች የቆየን ያስመስላሉ። ነገር ግን የተዋቀረው አመራር ጠንካራ ፣ የተቀናጀና ክፍለ የከተማው እገዛ አሁን ላለንበት ደረጃ አድርሶናል። አሁንም ቢሆን ሁሉም ነገር ምቹ አይደለም። ህብረተሰቡ አገልግሎቱ ተደራሽ እንዲሆን ይፈልጋል። መንግሥትም አገልግሎት ፈላጊ ወደ እኛ እንዲመጣ ሳይሆን መንግሥት እንደ መንግሥት ወደ አገልግሎት ፈላጊው በመድረስ ነው ህብረተሰቡን ማገልገል የሚቻለው የሚል ሀሳብ ስላለው በዛ ልክ እየሰራን ነው። ከተማ አስተዳደሩ የወሰደው እርምጃ የቆየና የዘመናት ጥያቄ በመሆኑ ህብረተሰቡን ያስደሰተ ነበር።
ከማቋቋም ጋር ተያይዞ ህጋዊ ሆኖ በምክር ቤትም ጸድቆ ወደ ስራ ሲገባ በበጀት አመት ሳይሆን መሃል ላይ ሶስተኛ ወር አካባቢ በመሆኑ ተመድቤ ስመጣ አንድ ብየ ነው ስራ የጀመርኩት። ክፍለ ከተማችንም ጠባብ ነበረች። በስድስት ነባር ወረዳዎች አራት ከቦሌና ሁለት ነባር ከየካ ክፍለ ከተማዎች በድምሩ ስድስቱ ወደ አስር አድገው ነው ክፍለ ከተማው የተዋቀረው። ለምሳሌ ከቦሌ ወደ ለሚ ኩራ ተካለው የነበሩት ወረዳ ስምንት፣ ዘጠኝ፣ አስርና አስራ አምስት የነበሩ ነባር ወረዳዎች ሲሆኑ ወረዳ አስራ አምስት ሰፊ የቆዳ ስፋት የነበረው ሕዝቡንም በአገልግሎት ተደራሽነት ያላማከለ ነበር። በዚህም የተነሳ ወደ ሶስት ወረዳ እንዲሆን በማድረግ ህብረተሰቡ በቀላሉ የሚፈልገውን አገልግሎት እንዲያገኝ ሁኗል። እንዲሁም ወረዳ አስራ አንድ ደግሞ ሰፊና የአርሶ አደር አካባቢ ስለነበር በሁለት ተከፍሎ ወረዳ አስራ አንድ ወደ ቦሌ ሲካለል ወረዳ ስድስት ወደ ለሚኩራ እንዲካተት በማድረግ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ተችሏል።
ከየካ የመጡት ወረዳ አስራ ሶስትና አስራ አራት ሲሆኑ ወረዳ አስራ አራት እንደነበረ ቀጠለ። ወረዳ አስራ ሶስት ግን በጣም ሰፊ ስለነበረ አገልግሎቱንም ወደ ህብረተሰቡ ለማድረስ ውስንነት የነበረ ሲሆን ሁለት ወረዳ እንዲሆን ተደርጎ ወረዳ አስራ ሶስት ባለበት ሲቀጥል የወጣው ወረዳ ሁለት ጋር ሁኖ በአጠቃላይ በአስር ወረዳ በማዋቀር ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት እየሰጠ ነው። ከአስሩ ውስጥ ቀደም ሲል ነባርና በሰውም በመሰረተ ልማትም በሁሉም የተሟሉ ስለነበሩ በነበሩበት ሲቀጥሉ አዲስ የተዋቀሩትና ክፍለ ከተማውን እንደ አዲስ በማደራጀት አገልግሎት መስጠት መጀመር ተችሏል። በተለይ ከወሳኝ ኩነት ጋር በተገናኘ ብዙ ሰዎችን ተደራሽ በማድረግ ረገድ ብዙ ሥራዎች ተሰርተዋል። ተገልጋዩ በቀላሉ የሚፈልገውን አገልግሎት እያገኘ ነው። በተለይ ከመሬት ጋር የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት ወደ መሬት በተግባር እየተሰራበት ነው።
ክፍለ ከተማው በአስር ወረዳዎች ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይኖርበታል። ያለው አቅጣጫም የዘመነ ክፍለ ከተማ በሥራውም ዘመናዊ የሆነ ክፍለ ከተማ እንዲሆን ስለተፈለገ የመጣው የሰው ኃይል የተመለመለው አመራር ቢያንስ ይህን ክፍለ ከተማ ለሌሎች ከፍለ ከተማዎች ምሳሌ እንዲሆን ያስችላል። እያንዳንዱ አመራር አንድ ወረዳ ላይ ያለ ችግርን ለይቶ ያውቃል። ምን አይነት የልማት ክፍተት አለ? ህብረተሰቡ ዘንድ ምን ችግር አለ? የሚለውን አጥንተን በካርታ ለይተን እየሰራን ነው። እንዲሁም ምን ያክል ነዋሪ አለ? አባወራ አለ? የሚለው ይታወቃል። ሰላም የጸጥታ ችግር የት አካባቢ አለ የሚለውን ለይተን እርምጃዎችን እየወሰድን ነው። ከፍለ ከተማውን ከማደራጀት አንጻር ብዙ ውስንነቶች ቢኖሩም በጣም ከሚገባው በላይ አመርቂ ስራዎች ተሰርተዋል።
አዲስ ዘመን፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ በርካታ የጸጥታ ችግሮች ይስተዋላሉ። በዚህ ክፍለ ከተማስ ያለው የጸጥታ ሁኔታ ምን ይመስላል?
ዋና ሥራ አስፈፃሚ፡- በዚህ ክፍለ ከተማ ምንም አይነት የጸጥታ ችግር አይስተዋልም። ጥቃቅን ስርቆቶች ካልሆኑ በስተቀር በርካታ ችግሮችን በቁጥጥር ስር ማዋል ችለናል። ይህ ደግሞ ሊሆን የቻለው ህብረተሰብን ያሳተፈ የሰላም ሥራ በመሰራቱ ነው። የክፍለ ከተማው ጸጥታ መዋቅር የስጋት ቦታዎች ተብለው የተለዩት ስለሚታወቁ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል። የማስፋፊያ አካባቢ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ብዙ ሪል ስቴቶችና ኮንዶሚኒየሞች ያሉበትና ብዙ ጸጉረ ልውጦች የሚንቀሳቀሱበት ስለሆነ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ሥራ በሰላምና በጸጥታ ጉዳይ ላይ ስለሚሰራ ብዙ ችግሮች አይስተዋሉም። ሰላሙን ከጠበቀ ነው ህብረተሰቡ በነጻ ሊንቀሳቀስና ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው። አገርንም እንደ ሀገር ሊያስቀጥል የሚችለው የሚል አስተሳሰብ በህብረተሰቡ ዘንድ እንዲሰርፅ የግንዛቤ ስራ ስለተሰራ እንቅስቃሴዎች በሙሉ በቁጥጥር ስር ናቸው።
በርግጥ ከባንክ ስርቆት ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ የስርቆት ችግሮች ነበሩ፣ ነገር ግን የቁጥጥር ስራዎች በመሰራታቸው ቆሟል። እያንዳንዷ የተፈጠረች ክስተት መረጃ አለን። በፍጥነትም በቁጥጥር ስር ይሆናል። የጸጥታ ኃይሎች፣ የደህንነት ባለሙያዎች፣ የደንብ አባላትና ፖሊሶች ተቀናጅተው የሚሰሩበት ሁኔታ ስላለ ከህብረተሰቡ ጥሩ ግብረ መልስ ነው ያለው።
አዲስ ዘመን፡- ክፍለ ከተማዎች በሙስናና በብልሹ አሰራር ይታማሉ። የለሚ ኩራ ከፍለ ከተማ ከዚህ የጸዳ እንዲሆን ያሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ምን ይመስላሉ?
ዋና ስራ አስፈጻሚ፡– በአዲስ አበባ ያሉ የሙስና ችግሮች አብዛኞቹ ከመሬት ጋር የተገናኙ ናቸው። መሬት ውስንና የሚያልቅ ሀብት ነው። በዛው ልክ ሀይለኛ የገቢ ምንጭ ያለው ነው። ከዚህ ጋር በተገናኘ በርካታ ችግሮች አሉ። እኛም እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ በዘመናዊ መልኩ እየሰራን ነው። ዘመናዊ አሰራር ከተዘረጋ ይህ ብልሹ አሰራር ሊቀንስ ይችላል። ይህ እንዳይሆን ደግሞ ሌት ተቀን እየተሰራ ነው። ልንሰራቸው ያቀድናቸው ሁሉ ማዘመንና ያሉ መሬቶችን በዘመናዊ መልክ መቆጣጠር ሲሆን የከተማ መስተዳደሩ ዓላማም ይህ ነው።
አሁን ያለው ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ከሙስና የጸዳ ነው ማለት አይቻልም። መቀነስ እንጂ ማጥፋትም አይቻልም ምክንያቱ ደግሞ የሰው አስተሳሰብ እየተበላሸ ነው። ሁሉም ሲሾምና ሥራ ሲመደብ ለማገልገል ሳይሆን ለመገልገል እና ለመብላት አይነት አስተሳሰብ ያለው ሰው ይበዛል። ይህ ደግሞ በሂደትና በትግል ለማጥፋት ይሰራል። እንደ አመራር በዚህ ጉዳይ ላይ ቁርጠኛ ሁነን እየሰራንበት ነው። ችግሮችን እየተቋቋምን መስተካከል ያለበትን በማስተካከልና መስመር በማስያዝ በሕግ አግባብ ሊፈጸምበት የሚችልበት አግባብ ላይ እየሰራን ነው። ከቦሌና ከየካ ክፍለ ከተማ ርክክቦችን እያደረግን ነው። ይህ ሥራ ሲጠናቀቅ ሁሉም ወደ ስራ ገብቶ ለውጥ ይመጣል። አሁንም ቢሆን በካርታ ላይ ካርታ ይዞ የሚመጣ አለ። ይህ እንዴት ተሰራ? የሚለው የሚታወቅ ነገር ነው። ይህን መሰል ችግር እንዳይገጥመንና በክፍለ ከተማው እንዳይስፋፋ ለማድረግ፣ ነዋሪዎች መብታቸው እንዲከበርላቸው ለማድረግና የሚሰጠው አገልግሎት ሁሉንም ደስተኛ እንዲያደርግ ከሙስና የጸዳ አሰራር እንዲኖር ከተማ አስተዳደሩ እገዛ እያደረገ ነው። ይህ ደግሞ እርግጠኛ ሁኜ መናገር የምችለው መቶ በመቶ እናሳካዋለን ብየ አስባለሁ። ሙስናውን ካለበት ደረጃ እናወርደዋለን። መጨረሻ ላይም ዜሮ ላይ መድረሱ አይቀርም።
አዲስ ዘመን፡- በሙስናና በብልሹ አሰራር ሲሳተፍ ተይዞ እርምጃ የተወሰደበት አመራር አለ?
ዋና ስራ አስፈጻሚ፡– ክፍለ ከተማው አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እስካሁን እርምጃ የተወሰደበት አመራር የለም። ነገር ግን የሚጣሩ ነገሮች ይኖራሉ። አሁን በእጄ ላይ ያለ አንድ ጉዳይ ብነግርህ ለአንዱ ሰው ሁለት ካርታ ተሰርቶለታል። አንድ ሴትዮ ደግሞ አንድ ካርታ አላት። ይች ሴትዮ ህጋዊነቷን የሚያረጋግጥ ሁሉ ነገር አላት። ቅድሚያ እንደተሰጣት የሚያሳይ ወረቀትና የግንባታ ፈቃድና የሊዝ ማረጋገጫ አላት። ሁለተኛው ደግሞ በአየር ላይ ካርታ ብቻ አለው። ያውም በሁለት ቦታ የተከፈለ። ከዚህም አልፎ ሴትዮዋ እየገነባች ያለችው እገዳ መጥቶበታል። እንዲህ አይነቱን ችግር ኮሚቴ በማቋቋም አጥንቶ በሚሰጠው አቅጣጫ መሰረትና የመንግሥት ጥቅም በማይጎዳ ሁኔታ የክፍለ ከተማው የሕግ አካሎች ጣልቃ በመግባት የመንግሥትን ጥቅም ያስከብራሉ።
ይህን በተመለከተ በርካታ ስራዎችም ተሰርተዋል። ከባድ የሆነ ሰንሰለት ቢኖረውም የመንግሥትን ጥቅም ሊጎዳ የሚችል ጉዳይ ላይ በስፋት እየሰራን ነው። ክፍለ ከተማው አዲስ በመሆኑ መካድ የማልችለው የሚመጣው ሰው ወይ ለሥራ ወይም ሊበላ እንደሚመጣ አመላካች ነገሮች አሉ። ይህ የሚስተካከለው በሥራ በመሆኑ ይህ ሊሰራ የሚችል ሕዝብ አገልጋይ ሰራተኛ ጉልበት ሊሰጥ የሚችል አመራር እያደራጀንና እያዋቀርን ቀጣይ ዓመት ሁሉም ነገር ከሁሉም ነገር የጸዳ ሕዝብ የሚረካበት አገልግሎት የሚያገኝበትን ይሆናል። ክፍለ ከተማው የአምስትና የስድስት ወር እድሜ ያለው ቢሆንም የተሰሩ ሥራዎች ግን ከዛ በላይ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ተጠያቂነትን ከማስፈን አንጻርስ ምን አይነት እርምጃዎች አሉ?
ዋና ስራ አስፈጻሚ፡- ተጠያቂነትን በተመለከተ አስቸኳይ መፍትሄ ነው የምንሰጠው። በሚቀርቡ ቅሬታዎች ላይ አስቸኳይ መፍትሔዎችን እየሰጠን ነው። ሲንከባለል የመጣ ከባድ የሆነ ከውሃ ጋር የተያይዘ ችግር አለ። ቀደም ሲል ሲስተናገዱ የነበሩት በቦሌና በየካ ክፍለ ከተማዎች ሲሆን ሁሉም አርሶ አደር መብራትና ውሃ እንዲገባለት ይፈልጋል። ነገር ግን መሬቱ ሕጋዊ አይደለም። በትክክል አርሶ አደር ያልሆኑ ሰዎች ስላሉ ያን ማጣራት ይፈልጋል። የመሬት ጉዳይ በጣም ውስብስብ በመሆኑ በጥንቃቄ ነው የሚታየው። አንድ ሰው የአርባ ግለሰቦችን ቅሬታ ይዞ ይመጣል። ይህ አግባብ አይደለም። እንዲህ አይነት ችግሮች አሉ። ሌላው ደግሞ የልማት ድርጀቶች ኢትዮ ቴሌኮምን ብንወስድ በሊዝ ቦታ ወስዶ እንዳይሰራ የተደረገበት ሁኔታ አለ። አቤቱታ ይመጣሉ። እኛም የማያዳግም እርምጃዎችን እንወሰዳለን። የእምነት ተቋማት ቦታው ተሰጥቷቸው ካርታ ይዘው ሳለ ግለሰብ ተነስቶ የኔ ነው ይላል። እኛ ሕግ ማስከበር ስላለብን ግለሰብ ካርታ ካለው አስተዳደራዊ መፍትሄ ይሠጠዋል። ካርታ ከሌለው ግን ፍርድ ቤት ሂዶ ነው መከራከር ያለበት። የእሱ ስለመሆኑ መረጃ ካለው ተከራክሮ ነው ማስመለስ ያለበት። ይህ አይነት ችግር የቆየ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እርካታ የሚሰጥ ሥራዎች እየተሰሩ አይደለም ባይ ነኝ።
ነገር ግን ደግሞ መስመር እንዲይዝ በማድረግ ረገድ ከአርሶ አደርና ከብሎክ ኮሚቴዎች ጋር በመሆን አርሶ አደሩ ግብር የከፈለበት ደረሰኝ መታወቂያውን ተጣርቶ ካለው ውሳኔ ይወሰንለታል። የአርባ ሰውን ውክልና ይዞ ሲመጣ ስንቱ ትክክለኛ ቅሬታ እንዳለውና ስንቱ ትክክል እንደሆነ አይታወቅም። የምናስተናግድው በግለሰብ ደረጃ ብቻ ነው። የመንግሥት ሀብትም እንዳይመዘበር በጥንቃቄ እየተሰራበት ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። እስከ ሰማንያ ድረስ ሁሉ ሁነው የሚመጣ ቅሬታ አለ። ነገር ግን ለጥንቃቄ ሲባል በዚህ መልክ የሚመጡ ቅሬታዎችን አናስተናግድም። ይህን በማድረጋችን ደግሞ አጭበርባሪዎች በሚፈልጉት ልክ አልሆነላቸውም።
አዲስ ዘመን፡- ክፍለ ከተማው ከኦሮሚያ ክልል ጋር አዋሳኝ ነው። የሕዝቡን የልማት ጥያቄ ለመፍታት በትብብር የመስራቱ ሁኔታ ምን ይመስላል?
ዋና ስራ አስፈፃሚ፡– ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ከብዙ አዲስ አበባ አጎራባች የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች ጋር ይዋሰናል። ከለገጣፎና ከዱከም ጋር በሰፊ እንዋሰናለን። እንደ ከተማ አስተዳደሩ እነዚህን አካባቢዎች ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ የትምህርት ቤት ምገባዎች፣ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታና የውሃ ዝርጋታዎች ተሰርተዋል። እንደ ክፍለ ከተማ ደግሞ የጸጥታና የሰላም ጉዳይ ላይ በጋራ እየሰራን ነው። ፖሊስና ደንቦችም ጋር በመሆን ለሰላም የሚሰሩበት ሁኔታ አለ። በተለይ ደግሞ ከኦነግ ሸኔ ጋር በተገናኘ እንቅስቃሴዎች አሉባቸው ተብለው በሚገመቱ ቦታዎች ሁሉ በጋራ ተቀናጅተን አዲስ አበባችንና ክፍለ ከተማችንን ሰላም እንዲሆን ሰዎች ሰላማዊ እንቅስቃሴዎችን እንዲያደርጉ የስጋት አካባቢዎች ላይ በተለየ መልኩ ተቀናጅተን እየሰራን ነው። በቀጣይም በጋራ በመስራት የሀገራችንን ሰላም ማስጠበቅና ሀገራችንን ወደፊት ለማስቀጠል አንዱ ለአንዱ አጋዥ እንጂ አፍራሽ ስላልሆነ በልማቱና በሰላሙ ተቀናጀተን ለመስራት መልካም የሆነ ግንኙነት አለን።
አሁን በትልቁ የትኩረት አቅጣጫችን አድርገን እየሰራን ያለነው በሰላም ጉዳይ ነው። ከጸረ ሰላም ኃይሎች ጋር በተያያዘ የሰዎችን እንቅስቃሴ በመከታተል በጋራ የሚሰሩ ስራዎች አሉ። ለምሳሌም ብዙዎች የኦነግ ሸኔ አባላት እራሳቸውን ቀይረው ወደ ስራ እየገቡ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ቀይረዋል ሲሉ ምናቸውን ነው የቀየሩት? በግልጽ ቢያስረዱን?
ዋና ስራ አስፈጻሚ፡– ድሮ የኦነግ ሸኔ አባላት ጸጉራቸውን አንጨብረው ነበር የሚንቀሳቀሱት። አሁን ከዛ በመውጣት ህብረተሰቡን በመምሰል የባጃጅ አሽከርካሪ ሁሉ የሆኑበት ሁኔታ ነው ያለው። የሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች የሚታወቁ ሲሆን ወረዳ ስድስት ጎሮ ላይ ከነጦር መሳሪያቸው የተገኙ አሉ። እንዲሁም በለገጣፎ አሉ። ግን ጠንካራ የሆነ ክትትል በማድረግ ወደ እርምጃ ሳይገቡ የመቆጣጠር ሥራ በስፋት ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን እየተሰራ ነው። ይህን ማድረግ የተቻለው ከልዩ ዞኖች ጋር በመሆን ነው። አመራሩ፣ ህብረተሰቡ፣ የፖሊስ አባላቱ በጋራ በመቀናጀት ጥሩ ሥራዎችን መስራት ተችሏል።
አዲስ ዘመን፡- እንደ አዲስ አበባ የመሬት ወረራ በከፍተኛ ደረጃ እንዳለ ይታወቃልና ይህ ክፍለ ከተማ ደግሞ የማስፋፊያና ከአርሶ አደሮች ጋር የሚዋሰን በመሆኑ ተጋላጭነቱ ምን ያህል ነው? የቅድመ መከላከል ስራውስ ምን ይመስላል?
ዋና ስራ አስፈጻሚ፡– ቀደም ሲል እንደነገርኩህ የመሬት ጉዳይ በጣም አስቸጋሪና ከባድ ነው። የሁሉም አይን፣ እግር፣ እጅና ልብ ሁሉ ያለው መሬት ላይ ነው። የአርሶ አደር አካባቢ በመሆኑ አርሶ አደርን ለመጥቀም ከተማ አስተዳደሩ ያወጣው መመሪያ አለ። አርሶ አደሩ ባለው መሬት ላይ ተጠቃሚ እንዲሆን በያዘው መሬት ላይ እያለማ መጀመሪያው ተጠቃሚ እንዲሆን ከሌለው ደግሞ ካለው ጋር ተቀናጅቶ በከተማ ግብርና እንዲጠቀም መመሪያ ወጥቶለታል። ችግር የሆነው ግን ሁሉም አርሶ አደር ነኝ የሚለው አካል መብዛቱ ነው፣ ነገር ግን አርሶ አደር ስለመሆኑ ማረጋገጥ የሚቻለው ከከተማ እስከ ወረዳ ኮሚቴ አቋቁሞ መስራት ሲቻል ነው። አርሶ አደሮች ነን ብለው የተመዘገቡ ከ5 ሺህ በላይ ነበሩ፤ በኮሚቴ ስናጣራ በመጀመሪያ ዙር 2500 ከዛ ውስጥ ደግሞ ወደ ልኬት ሲገባ ወደ 250 ደርሰዋል። ይህ ሲሰራ ግን ማንም ከምንም ነጻ ሆኖ አርሶ አደርም ሆነ መንግሥትን ሳይጎዳ ነው።
መሬት ዋጋ ስላለው ሁሉም ባለመሬት ነኝ ይላል። የማጥራት ስራው በጥንቃቄ ካልተሰራ ችግሮች ስለሚኖሩ አስፈላጊውን መንገድ ተከትሎ እየተሰራ ነው። ይህ ደግሞ የመንግስት አቅጣጫ ስለሆነ አርሶ አደሩ ከጠራ በኋላ የምስክር ወረቀት ይሠጠዋል። አሁን መሸጥም ሆነ መለወጥ አይቻልም። ነገር ግን መጠቀም ይችላል። ይዞታ እንዳለው መረጃ ተሰጥቶታል። በጋራ አልያም በራሱ አልምቶ መጠቀም ይችላል። አሁን ባለው ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ የመሬት ወረራ የለም ማለት አይቻልም። ከህገ ወጥ መሬት ወረራ ጋር በተገናኘ በየጊዜው የምናፈርሳቸው ቤቶች በቆርቆሮ የሚታጠሩ ቦታዎች ማሳያ ናቸው። ህገ ወጥ የመሬት ወረራው በግለሰብ ብቻ የሚቆም ሳይሆን የሃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ በርካታ ተቋማት ተሳታፊዎች ናቸው። ይህን ለመከላከል በጣም ሰፊ ስራ የሚጠይቅ ነው። እንደ ክፍለ ከተማ ወደፊት ሁሉም ነገር የተስተካከለ እንዲሆን በማሰብ ስራዎች እየተሰሩ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል ለአገልግሎት አሰጣጥ ምቹ ሁኔታዎች ባለመኖራቸው የተነሳ ነው በዋናነት የክፍለ ከተማው መቋቋም አስፈላጊ የሆነው፤ አሁን ይህ ችግር ተፈቷል ማለት ይቻላል?
ዋና ስራ አስፈጻሚ፡- ቀደም ሲል ከነበረው ችግር አንጻር መቶ በመቶ ማለት ይቻላል። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው አሁን ክፍለ ከተማው ያለበት ቦታ ለሁሉም ወረዳዎች ማዕከል መሆኑ ነው። ከሁሉም አቅጣጫ ለአገልግሎት ለሚመጣ ሰው የአንድ ታክሲ እርቀት ብቻ ነው ያለው። የህብረተሰቡም የዘመናት ጥያቄ ስለሆነ ወደ ሕዝቡ ቀርበናል። የሕዝቡ ግብረ መልስም በጣም አስደሳች ነው። ለምሳሌ ቀደም ሲል ከመታወቂያ እድሳትና ማውጣት ጋር ተያይዞ ብዙ ሰዎች ቅሬታ የሚያቀርቡበት ሁኔታ ነበር። ሌሊት 11 ሰዓት ወረፋ ይዘው ነበር የሚገለገሉት። በአዲስ መልክ ወደ ስራ ሲገባ የነበረው ብዙ ሰዓት መሰለፍና ቅሬታዎች ጠፍተዋል። የውሃ የመብራት አገልግሎቶችን ያለምንም እንግልት እያገኙ ነው። መቶ በመቶ ሕዝብ እንዲረካ ከተፈለገ አሁንም ቢሆን ጠንካራ ሥራን መስራት ያስፈልጋል። ይህን ለማሳካት የክፍለ ከተማው አመራር ሥራ ብቻ ሳይሆን እስከ ወረዳ ድረስ ተቀናጅቶ መስራትን ይጠይቃል። መንግስት ነው እንጂ ሕዝቡን ፈልጎ አገልግሎት መስጠት ያለበት ሕዝቡ አገልግሎት ፈልጎ ወደ መንግሥት መምጣት የለበትም የሚል አቅጣጫ ይዘን እየሰራን ነው።
ክፍለ ከተማው አዲስ በመሆኑ ከተማ አስተዳደሩም ከፍተኛ እገዛ በማድረግ ቀልጣፋ የሆነ አገልግሎት እንዲሰጥ እየተደረገ ነው። ሌሎችም ተቋማትም እገዛ ማድረግ አለባቸው። ከትራንስፖርት፣ ከበጀት ጋር በተገናኘ በርካታ ችግሮች አሉብን። ነገር ግን በችግሮች ሳይወሰኑ ባለን አቅም በመንቀሳቀስ ጥሩ ስራዎችን ሰርተናል። በቀጣይ የክፍለ ከተማው መስሪያ ቤት እንዲሰራ ጥያቄ አቅርበናል። ቢሮ የሌላቸው አሁን በኪራይ ያሉ ወረዳዎችም የራሳቸው ቢሮ እንዲኖራቸው ጥረት እየተደረገ ነው። ከኪራይ ወጥተን ለሌሎች ክፍለ ከተማዎች ተምሳሌት እንድንሆን የሁሉም እገዛ አስፈላጊ ነው። ችግር ቢኖርም ውጤት ሊመጣ እንደሚችል ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ምሳሌ መሆን ይችላል። ይህ የሆነው ደግሞ ሰራተኛውና የአካባቢው ነዋሪ ተባባሪ በመሆኑ ነው። ለምሳሌ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ፣ መከላከያ ሰራዊቱ በጁንታው ጥቃት ሲደርስበት የአካባቢ ህብረተሰብ ምላሽና እገዛ አስደሳች ነበር። እንዲሁም ለትግራይ ወገኖቹ ከፍተኛ እገዛ ያደረገ ክፍለ ከተማ ነው።
አዲስ ዘመን ፡- እናመሰግናለን
ዋና ስራ አስፈጻሚ፡- ክፍለ ከተማው ያለበትን ሁኔታ ለህብረተሰቡ ለማሳወቅ ቃለመጠይቅ ስላደረጋችሁልኝ አመሰግናለሁ።
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2013