– መላከ ህይወት ቆሞስ አባ አክሊለ ማርያም በምስራቅ ሀረርጌ ሀገረ ስብከት በሀረር ዙሪያ ቤተ ክህነት የላንጌ ቅዱስ ራጉኤል ቤተክርስቲያንና የላንጌ ቢላል መስጊድ አስገንቢ
ኢትዮጵያ እንደ አገር የቆመችው በህዝቦቿ አንድነትና ትብብር መሆኑ የማይታበይ ሃቅ ነው። በጦርነት በረሀብ በችግር ብሎም በአገር ላይ አንዳች ነገር በሚመጣ ጊዜ ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው መቆማቸው የተለመደ ተግባር ነው። ኢትዮጵያውያን ከዚህም ባሻገር የብዙ ሀይማኖቶች አንድነት ተከባብሮና ተፋቅሮ መኖር የሚታይባቸውም ናቸው። በተለይም እስልምናና ክርስትና ምንም እንኳን አስተምህሯቸው ቢለያይም ህዝቡ አንድ ሆኖ ተባብሮ የአንዱን እምነት አንዱ አክብሮ በዓልን በጋራ ተጫውቶ ተደስቶ አሳልፎ በአንዱ ሀይማኖት ላይ ችግር ሲመጣም እንደ ጋራ ችግር ወስዶ አብሮ መክቶ በጠቅላላው የእኔ የአንተ የሚባል ነገር ሳይፈጠር ሁሉን እኩል አድርጎ እዚህ ደርሷል።
ምንም እንኳን ዛሬ ላይ ተማርን አወቅን መጠቅን ያሉ ጥቂት አክራሪያን መካከል ገብተው ለማለያየት ቢጥሩም እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ የተቻላቸው አይመስልም። እንደውም ሁለቱም ሀይማኖቶች የተጋመዱበትን ጠንካራ ገመድ እያጠበቁት ህዝቡም በአንድነቱ እየጸና ይገኛል። ለዚህ ትልቅ ማሳያ እንዲሁም ኢትዮጵያዊነትና አንድነት በተግባር እንዲገለጥ ካደረጉ አባቶች መካከልም መልዓከ ህይወት ቆሞስ አባ አክሊለ ማርያም ተጠቃሽ ናቸው። እኚህ አባት በምስራቅ ሀረርጌ ሀገረ ስብከት በሀረር ዙሪያ ቤተ ክህነት የላንጌ ቅዱስ ራጉኤል ቤተክርስቲያን አባት ሲሆኑ እርሳቸው የሚያገለግሉበትን የላንጌ ቅዱስ ራጉኤል ህንጻ ቤተክርስቲያን ለምነው እያሰሩ ነው። ይህ ምናልባት ለእሳቸው ግዴታ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን እኚህ የኢትዮጵያዊነት ልክ የሆኑ አባት ከሚያሰሩት ቤተክርስቲያን እኩል በአካባቢው ላይ የነበረውን የቢላል መስጊድ በማሰራት በታሪክም በህዝብም ልብ ውስጥ ሰርጸው ገብተዋል። እኛም ስለ ስራቸው አናጋግረናቸው ይህንን ብለውናል።
አዲስ ዘመን ፦ እርስዎ ቤተክርስቲያንም መስጊድም እያሰሩ እንደሆነ ይታወቃልና እንደው ምን እንዳነሳሳዎት ቢነግሩኝ ?
አባ አክሊለማርያም ፦ እዚህ ላይ ከሁሉም የሚበልጠው ነገር ኢትዮጵያዊ መሆን ነው። ኢትዮጵያዊ ሆኖ መፈጠር በራሱ አንደኛና ዋነኛ መልካም እድል ነው ለእኔ። ምክንያቱም በዓለም ሁሉ ብንዞር እንደ ኢትዮጵያውያን ያለ ከፍ ያለ አስተሳሰብ ያለው የትም አይገኝም። ይህንን ሳብራራልሽ ማንኛውም ሰው ቀለሙን፣ ብሔሩን፣ ሀይማኖቱን ሊጠጋ ይችላል፤ ነገር ግን ሰው ሀይማኖት አለኝ ብሎ እግዚአብሄርን ካላቀፈና ከእርሱ እውነት ካልተቀዳ ይህ ሰው እራሱን እያታለለ ነው ማለት ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን በቀደምት አባቶቻችን አማካኝነት የእውቀት የፍቅር ጥግ የሆነውን እግዚአብሔርን እውቀት ተደግፈነው ስለምንኖር አስተሳሰባችንም አለም አቀፋዊ ሆኗል ማለት ነው።
በኢትዮጵያ ቀለማዊ አስተሳሰብ አሁን የመጣ ወረርሽኝ ነው። ዘራዊ አስተሳሰብን መከተልም የሰይጣን መገልገያ እቃ መሆን ነው። ከከፍታም ወደታች እንደመውደቅ ነው። ከባለጸግነት ወደ ድህነት መምዘግዘግም ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያ ያላት እሴት ምንድን ነው? ነጭነት፣ ጥቁርነት፣ ሙስሊምነት፣ ክርስቲያን መሆን፣ ፕሮቴስታንትነት አልያም ካቶሊክነት፤ ልዩነት አልነበረውም፡፡ ይህ አሁን የመጣ አለመረዳት የፈጠረው ችግር ነው። በነገራችን ላይ ሰዎች በየራሳቸው ማንነት ባህል ቢኖራቸው ምንም ክፋት የለውም፡፡ ነገር ግን በአግባቡ ካልተያዘ ሰይጣን መለያያ ያደርገዋል። ከጥጉ ተነስተን ካከበርን ግን መለያያ ሳይሆን ውበት ይሆናል ማለት ነው ።
አሁን ግን ያለው ነገረ የእውነቱን ጥግ የለቀቀ ትውልድ በመፈጠሩ እንዲሁም የእውነት ጥግ ይህ ነው ያዙ ሲባሉም ፍቃደኞች ስላልሆኑ አሁን ያለንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ይህንን ማስተካከል ደግሞ እጅግ በጣም ትግል የሚጠይቅ ነው።
እኔ በሀይማኖቴ ስኖር የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ ነኝ፡፡ ነገር ግን ይህች እምነት ለእኔ አውነትን ካልሰጠችኝ አንድ ቀን እርሷን ተከትዬ አልሄድም። እኛ ኢትዮጵያውያን አዳም የተገኘባት ምድር ላይ የታየን እንደመሆናችን እዳ አለብን ፤ እኛ ስለ ሰው ልጆች ካላሰብን ሌላው የዓለም ህዝብ ስለ ሰው ልጆች ሊያስብ አይችለም፤ ለሰው ልጅ ስናስብ ደግሞ ቀለሙን፣ብሔሩን ሀይማኖቱን አክብረን ሊሆን ይገባል።
አሁን በእኛ ዘንድ የሚታየው ግን እንኳን ለቀረው አለም ልናስብ እርስ በእርሳችን እንኳን መተሳሰብ አቅቶን እንደ አውሬ ሆነናል። በመሆኑም ሁላችንም በእርግጥ ሁለት አይን ስላለን ብቻ ነው ሰው የምንባለው ወይም ሌሎች የአካል ከፍሎቻችን ተሟልተው ስለተሰጡን ብቻ አይደለም ሰው ሰው የሚሆነው፡፡ አስተሳሰባችን ልክ እንደ እግዚአብሔር ሲሆንና ሌላውን መውደድና መርዳት ሲቻል ነው። ይህ ባለመሆኑ ግን ዛሬ ላይ ሰው ፈልጎ ማግኘት በጣም ከባድ ሆኗል። በመሆኑም ፈጣሪ ታግሶ ታግሶ ፊቱን እንዳያዞርብን አልፎም እንዳያጠፋን የምንናገረውን ከአባቶቻችን ከመምህራን አንደበት የሚወጣውን መስማት ያስፈልጋል። አንዳንድ መምህራንም በሚያስተላልፉት መልዕክት ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አቃፊ ናት፤ በዚህች ቤተክርስቲያን መሆኔ ደግሞ ከእኔ አልፎ የሌላውንም እምነት እንዳስብ ምን ብሰራስ ነው ፈጣሪዬን የማስደስተው አማኙንም የማገለግለው የሚለውን እንዳስብ ስላደረገኝ ወደዚህ ስራ ገብቻለሁ ። ምንም እንኳን እምነቴ የግሌ ቢሆንም አገሪቱ ግን የጋራችን በመሆኗ ለዚህች የጋራ ቤታችን ደግሞ የሚጠቅም ስራ ሰርቶ ማለፍ እንደ ሰውም እንደ ሀይማኖት አባትም አለፍ ሲልም እንደ ኢትዮጵያዊ ወሳኝና አስፈላጊ በመሆኑ አድርጌዋለሁ።
ኢትዮጵያዊ ክርስቲያን ደግሞ እንደ ክርስቶስ ሁሉን ወዳጅ አቃፊ ለሌላው እምነት ተጨናቂ በመሆኑና እኔም በዛ ውስጥ በማለፌ ለእህት ወንድሞቼ ሙስሊሞች ይህንን ብሰራ ብዬ ተነስቼያለሁ፤ በጠቅላለው ግን ለዚህ ስራ ያነሳሳኝ ሰው መሆኔና ኢትዮጵያዊ ኦርቶዶክስነቴ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ግንባታው መቼ ተጀመረ አሁን ያለበት ሁኔታስ ምን ይመስላል ?
አባ አክሊለማርያም፦ አሁን እኔ ከራሴ አስቀድሜ ለጓደኛዬ ነው ቅድሚያ መስጠት የምፈልገው፤ ምክንያቱም ፍቅር ማለት ለምሳሌ “ወደሮሜ ሰዎች ምዕራፍ 13 ከቁጥር 8 ጀምሮ ስናየው እርስ በእርሳችሁ ከመዋደድ በስተቀር የማንም እዳ እንዳይኖርባችሁ” ይላል። ይህ ማለት ደግሞ ሌላውን የሚወድ ህግን አክብሯል ፈጽሟል ማለት ነው። በሌላ አገላለጽ ደግሞ አንድ ሰው ሃብት ሲኖረው ለሌለው ያካፍላል። ፍቅር የበዛለት ሰው ደግሞ ለሌላው በተለየም ከእርሱ ሀይማኖት፣ብሔርና አስተሳሰብ ውጪ ለሆኑ ያካፍላል።
ይህ መሆኑ ደግሞ ፍቅር ያለው ሰው ለጓደኛው ክፉ አያደርግም፤ ወደ አእምሮውም የሚመጣው መልካም ሃሳብ ብቻ ነው። በእውነት ነው የምልሽ እኔ በዚህ ስራ ላይ ለቤተክርስቲያኑ ስራ ቅድሚያ ሰጥቼ አላውቅም። ሁሌም ለመስጊዱ ስራ ቅድሚያ እሰጣለሁ። ይህ ግን ማንንም ለማስደሰት የማደርገው ሳይሆን ኢትዮጵያዊነቴ ክርስቲያን መሆኔ ነው።
ኢትዮጵያውያን ሙስሊም ወንድሞቻችንን እወዳቸዋለሁ፤ ከእነሱም አልፌ ነብዩ መሀመድን ነብያችን ነው የምላቸው፤ ምክንያቴ ደግሞ እርሳቸው የኢትዮጵያ የግላችን በመሆናቸው ነው። ምናልባት ነብዩ መሀመድ ተወልደው ያደጉት መካ ነው፤ ግን ስለ አረቡ አለም ወይም ስለ መካ ሳይሆን ስለ ኢትዮጵያ “እውነተኛይቱ ምድር” በማለት ጽፈዋል፤ ለዚህ ደግሞ መነሻቸው ኢትዮጵያውያን እውነተኛ አስተሳሰብ ያላቸው ልዩነት የማያደርጉ መሆኑን ስላዩ ብቻ ነው። ሌላው ደግሞ ኢትዮጵያ እስልምናና ክርስትናን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም እምነት በፍቅር የምታስተናግድ አገር ስለሆነች በአገሪቱ ላይ ምንም አይነት የሀይማኖት ሽኩቻ በተለይም ደግሞ” ጀሀድ” እንዳይፈጸም አዘዋል።
በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች ኢትዮጵያና መካ የጠበቀ ግንኙነት አላቸው። ይህንን የጠበቀ ግንኙነት ደግሞ አባቶቻችን ጠብቀውና ተንከባክበውት ስለኖሩ እስከ ዛሬ ድረስ በፍቅርና በሰላም በመተሳሰብና በመቻቻል ኖረናል፡፡ እስከ አሁንም ጥሩ የሆኑት ሙስሊሞች በዚህ
መንገድ ነው እየኖሩ ያሉት።
የቤተክርስቲያን ግንባታ ስራው ሀምሌ 15 ቀን 2009 ዓም የተጀመረ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ደረጃውን የጠበቀ ቤተክርስቲያን ሆኖ እንዲያልቅ በምዕመናን ድጋፍ ግንባታው እየተሰራ ነው። እኔ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ አባት ብሆንም ጎን ለጎን ደግሞ ለሙስሊም አባቶቼ እህት ወንድሞቼ አምልኮ ስርዓታቸውን መፈጸሚያ መስጊድ ያስፈልጋቸው ስለነበር የላንጌ ቢላል መስጊድም እኩል ስራው እንዲሰራ እየተደረገ ነው ። በጠቅላለው ግን ሰው ሰው ነው፤ እኔም ሰው ነኝ፤ ሰው በመሆናችን ደግሞ እምነት የግል ቢሆንም በጋራ አገራችን ላይ ተጋግዘን ተደጋግፈን መኖራችን መገለጫችንም በመሆኑ እኔም የእኔን እምነት ቤተክርስቲያን እየለመንኩ ሳስገነባ ጎን ለጎንም ለሙስሊም ወገኖቼ ስራውን እየሰራሁ እገኛለሁ።
አዲስ ዘመን፦ እርስዎ የትውልድ አካባቢዎ ነው ወይስ እንዴት ወደዛ ሊሄዱ ቻሉ? በተጓዳኝም የአንድ ሀይማኖት ተከታይ ደግሞም አባት ሆኖ የሌላን ሀይማኖት ቤተ እምነት ማስገንባት ትንሽ አይከብድም እንዴት አሰቡት ?
አባ አክሊለማርያም ፦ አካባቢውን ቀደም ብዬ ባውቀውም ወደ ቦታው የመጣሁት በ2007 ዓ.ም ነው። ከዛ ጀምሮም እስከ 2009 ዓ.ም ድረስ ለቤተክርስቲያኑ የሚያስፈልጉ ንዋየ ቅድሳትን በማሟላት በኋላም የመስጊዱ ጉዳይ ይመለከተኛል በማለትና ወደ አዲስ አበባ በመሄድ ለኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ማመልከቻ በማስገባትና ህጋዊነትን በመያዝ አዲስ አበባ ያሉ ሙስሊም ወንድም እህቶች በመስጊድ ግንባታው ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ ችያለሁ። በዚህ ሂደትም አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ3 መቶ 30 ሺህ ብር በላይ ተሰብስቦ በእኔ በኩል የመስጊዱ ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል።
መስጊዱን ለማሰራት እንግዲህ መነሻ የሆነኝ ነገር አንደኛ ሰው መሆኔ ነው። አካባቢው ላይ ያለው ማህበረሰብ አርሶ አደር ነው፡፡ የዝናብ ወቅትን ጠብቀው በሚዘሩትና ለገበያ በሚያቀርቡት ምርት ነው ገቢን የሚያገኙት ፤ እኛ ቤተክርስቲያናችንን አዲስ አበባ ባሉ የክርስትና እምነት ተከታዮች ተሳትፎ ስናስገነባ እዚህ ያሉት ወንድም እህት ሙስሊሞች ደግሞ መስጊድ ያስፈልጋቸው ስለነበር እኔ ይህንን ሀላፊነት ብወስድና አዲስ አበባ ያሉ ሙስሊሞችን አስተባብሬ ለእዚህ አርሶ አደር ማህበረሰብ የሆነ ነገር ባበረክት በማለት ጀምሬዋለሁ፤ እግዚአብሔር ይመስገን በጥሩ ሁኔታ እየሄደልኝ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያዊ ክርስቲያን ለሁሉም አሳቢ ነው፤ ሌላው ደግሞ ሁለቱም እምነቶች በአምልኮ ቢለያዩም ፍቅራቸው ግን አንድ ነው፤ እነዚህን መሰል ሁኔታዎች ደግሞ እኔንም ለሁለቱም ሀይማኖቶች እንድሰራ አድርጎኛል።
አዲስ ዘመን ፦ ከኢትዮጵያዊ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሀይማኖት አስተምሮ ባሻገር ግን ስለ እስልምና እምነት ለማወቅ ያደረጉት ጥረት ይኖር ይሆን ?
አባ አክሊለማርያም፦ አዎ ቅዱስ ቁራንን እንደ መጽሀፍ ቅዱስ አነባለሁ፤ በዚህም ስለ ሀይማኖቱ አውቃለሁ፤ ለምሳሌ ቅዱስ ቁራአን ላይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለእስልምና ሀይማኖት ውለታ እንደዋለች ተጽፏል። በተለይም አረቦች ነጃሺ በሚሉት ንጉስ ዘመነ መንግስት የኢትዮጵያ ንጉስ ለሙስሊሞች ውለታ መዋሉ ተቀምጧል። ይህንንም ማወቄ ደግሞ የእስልምና ሀይማኖት ለእኔ አደራዬም ጭምር እንደሆነ እንዳስብ አድርጎኛል ።
በእኔ አመለካከት አንድ ሰው ኢትዮጵያዊነት ሊገባው የሚችለው መንፈሳዊ ሲሆን ብቻ ነው። ምክንያቱም ቅዱስ ዳዊት” ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” ይላል ፤ እኔም ለትምህርት ከፍተኛ የሆነ ፍቅር ቢኖረኝም ግብረገብን ደግሞ በእጅጉ እፈልግ ነበርና ወደ ቤተክርስቲያን መጣሁ፡፡ የፈለኩትንም አገኘሁ፤ ቢቻል ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሚከተለው እምነት መንፈሳዊ ሆኖ ማለፍ ቢችል አገሩን በስነ ምግባር የሚያገለግል ይሆናል ብዬም አስባለሁ።
አዲስ ዘመን ፦አካባቢው ላይ ያሉ የእስልምና እምነት ተከታዮች ለእርስዎ ምእመናን ያላቸውን አመለካከት እንዴት ይገልጹታል?
አባ አክሊለማርያም ፦ ቤተክርስቲያኑም መስጊዱም የሚሰራበት አወዳይ የተባለው አካባቢ ላይ ሲሆን ቦታው ከምስራቅ ሀረርጌ ከተሞች ሁሉ አስቸጋሪ ነበር ፤ ምክንያቱ ደግሞ ህብረተሰቡ ካለመረዳት የመነጨ የግለኝነት ባህርይ ወይም የእኔ ሀይማኖት ብቻ የሚል አስተሳሰብ ውስጥ የገባ ነበር ። በመሆኑም እኔ ወደ አካባቢው መጥቼ በዚህ መልኩ ስራ ከጀመርኩ በኋላ ያደረኩት ነገር ወይም የወሰድኩት ድምዳሜ የኢትዮጵያን ሰላም ፍቅር አንድነት አብሮ የኖረውን መቻቻል በመናገር ብቻ ማምጣት እንደማይቻል በመረዳት ወደ ዋና እሴታችን ወደቀደመ ማንነታችን መመለስ እንደሚያስፈልግ በመረዳት ያንን ለማምጣት ነው የጣርኩት።
ምክንያቱ ደግሞ አሁን አገራችን ያለችበት አደጋ አስፈሪ ነው በዚህ ከቀጠልን ደግሞ ሶሪያ ሊቢያና የመን ጋር ነው የምንመጣው ምናልባትም የእኛ የከፋም ሊሆን ይችላል። በመሆኑም በዚህ አካባቢ ያለውንም የአንድነት መጥፋት ቅዱስ ቁርአንና መጽሀፍ ቅዱስን ይዤ በመነሳት ህዝቡ እንዲረዳ የማድረግ አንድነቱን የመመለስ ስራ ሰራሁ፤ በዚህም የተለወጠ ብዙ ነገር አለ።
በነገራችን ላይ ሌላውም አካባቢ ይህ ሁኔታ እንዲመጣ በተለይም የታሪክ ምሁራን ትልቅ ሀላፊነት እንዳለባቸው በመረዳት የየራሳቸውን ብቻ መተረክ ትተው የቀደመውን አገራዊውን ጉዳይ ለትውልዱ ማስገንዘብ አለባቸው። ይህንን ሳያደርጉ ግን ዝም ባሉ ቁጥር ስይጣን ጣልቃ ይገባና ታሪክንም ህዝብንም ሊቀብር ይፈልጋል።
በዚህ የተነሳ አሁን የማስገነባው ቤተክርስቲያኑ ብቻ ሳይሆን መስጊዱም የእኔ ነው፤ ነገር ግን እዛ መስጊድ ውስጥ ገብቼ የማላደርገው ነገር ስለ እስልምና ማውራት ብቻ ነው፤ ይህንንም የማላደርገው የምከተለው ሃይማኖት ሌላ ስለሆነ ነው፤ ከዛ ውጪ ግን ባለው ነገር ሁሉ እኩል እሳተፋለሁ።
በሌላ በኩልም በዚህ በላንዲ አካባቢ ያሉ ክርስቲያኖች አድገዋል፤ በዚህም ሙስሊሞች ወንድሞቻቸው እንደሆኑ ጠንቅቀው ያውቃሉ ፤ እርስ በእርስ መረዳዳቱ አንዱ የአንዱን እምነት ማክበሩና መተሳሰቡ ያስደስታል፤ እኔ እንደውም ሁሉም አካባቢ ይህ መሰሉ ሁኔታ እንዲኖር እመኛለሁ።
አዲስ ዘመን ፦ ለመስጊድ ግንባታ ገንዘብ የሚሰበስቡት እንዴትና ከየት ነው? ክርስቲያን አማኞች ለመስጊድ ማስገንቢያ ብለው ገንዘብ ሲጠይቋቸውስ ያላቸው ምላሽ ምን ይመስላል?
አባ አክሊለማርያም ፦ እኔ ይህንን የምሰራው በደምና በስጋ ብቻ አይደለም ፤ ከዛ ይልቅ በትክክለኛ ሀይማኖታዊ ፍቅርና መንገድ እንጂ ፤ ይህንን ደግሞ አምላክም ይወደዋል። በመሆኑም እኔ መስጊድ ገብቼ ለግንባታው የሚያስፈልገውን ገንዘብ ስጠይቅ ከኢማሞቹ ጀምሮ በእንባ ነው የሚቀበሉኝ፤ ምክንያቱ ደግሞ ምን መሰለሽ ህዝቡ ውስጡ አንድነትና ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው በመሆኑ ነው። እንዲህ ባለው ፍጹም አንድነትና ፍቅር ተቀብለውኝ ለሚሰጡትም አይሳሱም ። በእኔ ምእመናን በኩልም አንድ መስጊድ ላይ ዝግጅት ኖሮ አዲስ አበባ ሳይሆን እዛው አገር ላይ በመንገድ ስንሄድ ሙስሊሙም ክርስቲያኑም እኛ እኮ ይህንን ነው ያጣነው በማለት እጅግ በመደሰት ግማሹ ፎቶ ይነሳል፤ ገሚሱ ምን ላግዝ ይላል፤ በመሆኑም ይህ ስሜት ቤተክርስቲያኑም ሆነ መስጊዱ በጥቂት ሰዎች የሚሰራ ነው።
የሚገርመው ነገር ሙስሊሞች ሀብት ያላቸው በተለያየ ስራ ላይ የሚገኙ ሰዎች ለሁለቱም ግንባታ የሚሆን መኪና እና ሌሎች ነገሮችንም ለመጠቀሚያነት ይሰጣሉ፤ በመሆኑም ኢትዮጵያ የምትባለው አገር በእንደዚህ አይነት ሰዎች ነው ልትገነባ የምትችለው፤ በነገራችን ላይ የቤተክርስቲያኑን ግንባታ ሰራተኛ በመቅጠር በማሰራት በመቆጣጠር ሁሉንም ነገር ሃላፊነት ወስዶ የሚያሰራው ሙስሊም ወጣት ነው። እንግዲህ ይህ ነው የእኛ ኢትዮጵያውያን ማንነት አሁን በሰፈራችን ቤታችን በአገራችን እያየነው ያለነው ነገር ግን ፍጹም የእኛ ያልሆነ ወረርሽኝ ነው። በመሆኑም በጥቂት አተራማሾች ንጹህ ልብ ያላቸው ለእስልምናውም ለክርስትናውም ብዙ ማድረግ መስራት የሚችሉ ሰዎች ሲወሰዱ በሌሎች የክፋት አዙሪት ውስጥ ሲጠመዱና ሲወድቁ ሳይ በጣም አዝናለሁ። ሊሆን አይገባውም ማንነትን ኢትዮጵያዊነትን መመርመር የግድ ይላል፤ ይህንን በመረመርንና በተመራመርን ቁጥር የሌሎች መጫዎቻም አንሆንም ።
አዲስ ዘመን ፦እርስዎ እያደረጉ ያለው አይነት ቀደምት የአገራችን የመቻቻል ባህል በሁሉም ዘንድ እንዲስፋፋ ምን መደረግ አለበት? ከማን ምን ይጠበቃል? ምዕመኑስ ራሱን (እምነቱን) ከሁለት ወገን አክራሪዎች እንዴት ሊጠብቅ ይችላል?
አባ አክሊለማርያም፦ ለምሳሌ የኦሮሚያ ክልልዊ መንግስት በክልል ያሉ የሁሉም ሀይማኖቶች አባቶችን እያገናኘ እያወያየ ነው። ከአንድ ወር በፊትም በአዳማ ከተማ በመላው ኦሮሚያ ያሉ የሀይማኖት አባቶችን ያሳተፈ ትልቅ ጉባኤ ተካሂዶ ነበር፤ በወቅቱም “መልካም ነገር ፣መልካም ስራ ፣የዜግነት ግዴታ ለምን ጠፋ “ በሚል ውይይት ተደርጓል። በመሆኑም ይህ ተሞክሮ ለሌሎችም ጠቃሚ ነውና እንደው ሁሉም ክልሎች ይህንን አካሄድ ቢከተሉ የጠፋውን እኛነታችንን በቀላሉ ለማምጣት ለችግሮቻችን ሁሉ መፍትሔ ለማግኘት ያስችላል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከአድዋ ጦርነት በባሰ ፈታኝ ጊዜ ላይ ነው የምትገኘው፤ ምክንያቱም አድዋ ላይ ጣሊያን ብቻ ነው ቅኝ ልግዛችሁ እያለ ይደበድበን የነበረው። አሁን ግን አለም የራሱን ጥቅም ፈላጊ ስለሆነ ከዚህ ቀደም ያሉ መሪዎቻችን ራሳቸውን ቄራ እንደ ገባ ከብት አርደው ለአውሮፓና ሀያላን ነን ለሚሉት ህዝቡን ለማቅረብ ያስቡ ስለነበር በእነዛም ወገን ብዙም ችግር አልታየም ። አሁን ያለው የለውጡ መንግስት ግን ለዚህ ምቹ ስላልሆነላቸው ኢትዮጵያ ላይ ሁሉም እያጉረመረመ ይገኛል። በመሆኑም ህዝቡ ወደ እውነቱ ወደ እምነቱ በመምጣትና ጥቅምና ጉዳቱን በመለየት እነዚህን ሊያባሉት የተዘጋጁ በሀይማኖት ጭምብል ውስጥ የተሸሸጉትን ለይቶ ማውጣት አለበት ።
አሁን አገራችን ላይ ዘረኞች ብሔርተኞች የማይረዱ ጠባቦች አሉ፡፡ እንዲሁም በገንዘብ ተደልለው የሚመጡም አሉ። እነዚህንም ቢሆን መንግስት ቁጭ አድርጎ በማወያየት ታሪክን እንዲረዱ ኢትዮጵያ ማናት የሚለውን እንዲያውቁ ማድረግ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
አባ አክሊለማርያም፦ እግዚአብሔር ይስጥልኝ
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2013 ዓ.ም