የከተማ ልማት ለሀገርም ሆነ ለክልል ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽፆ እንዳለው ይታመናል። ከተሞች በቴክኖሎጂ፣ በህንፃ ግንባታ፣ በመንገድና በሌሎች መሰረተ ልማቶች ሲለሙ ንግድ ይሳለጣል፤ የትምህርት ዕድልም ይሰፋል። ለሰዎች የሥራ ዕድልም ከመፈጠሩ በዘለለ የተሻለ ገቢም ይገኛል። የዛኑ ያህል ደግሞ የህዝብ አኗኗርም ይዘምናል፤ ኢኮኖሚም በየደረጃው ይጎለብታል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የሀገሪቱ ከተሞች ዕድገትም በዚህ መልኩ የተሳለጠ ነው ተብሎ ይታሰባል። በዚህ ሁለንተናዊ ዕድገታቸውን ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ ከተሞች ከአንዱ እድገታቸው ወደ ቀጣዩ የእድገት ደረጃቸው ይሸጋገራሉ። ከዚህም ጋር በተያያዘ የአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት በቅርቡ ደብረ ብርሃንን፣ ደብረ ማርቆስንና ኮምቦልቻን ወደትልቅ ከተማ (ሪጅኦ ፖሊታን) ከተማነት እንዲያድጉ ተወስኗል።
የአማራ ክልል የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ በሰላም ይመኑ እንደገለፁት፤ ሽግግሩ የከተሞቹን የሕዝብ ብዛት፣ወጪን የመሸፈን አቅም፣ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ፣ የሕዝብ አሠፋፈርና ጥግግትን መሰረት ያደረገ ነው። ምክር ቤቱ የአማራ ክልል ከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ ባቀረበለት ሀሳብ መሰረት ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም ሦስቱ ከተሞች ወደ ሪጅኦ ፖሊታን ከተማነት እንዲያድጉ ወስኗል።
ምክር ቤቱ ውሳኔውን ያሳለፈው በቢሮው በቀረበለት የከተሞች ፈርጅ መወሰኛ መሰረት ሲሆን ውሳኔው ከዚህ ቀደም የነበረውና ለአስራ ሁለት ዓመታት ያገለገለው የከተሞች አደረጃጀት ፈርጅ መወሰኛና ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 65/2001ን በአዲስ የማሻሻል ሥራ ከተሰራ በኋላ ነው። ምክር ቤቱም ደንቡ ጊዜ ያለፈበት በመሆኑና የከተሞችን ፈጣን ዕድገት እንዲሁም እየቀረበ የሚገኘውን የሕዝብ ጥግግትና የልማት እንቅስቃሴዎችን ታሳቢ አድርጎ አሻሽሎታል።
ምክር ቤቱ የከተሞች ማቋቋሚያ ማደራጃና ስልጣንና ተግባር መወሰኛ አዋጅ ቁጥር 245/2009 አንቀፅ 95 ድንጋጌዎች በተሰጠው ስልጣን መሰረት ደንቡን አሻሽሏል። ይህም በድሮው መመሪያ የነበረው ገቢን የመሰብሰብ አቅም አሁን ባለው ሁኔታ ወጪን በመሸፈን አቅም እንዲካተት ተደርጓል። በደንቡ መሰረትም የከተሞች ሽግግር ሲወሰን ወጪን የመሸፈን አቅማቸው መወሰዱ ብዙ ፋይዳ ይኖረዋል።
እንደ ኃላፊው ገለፃ የተሻሻለው ደምብ አንድ ከተማ አስተዳደር የሠራተኛ ደመወዝን ጨምሮ ለሚያወጣቸው የሥራ ማስኬጃ የካፒታል በጀት የሚጠይቁ ሥራዎች በራሱ ወጪ የሚሸፍን በመሆኑ ገቢ የመሰብሰብ አቅሙን ያጠናክርለታል። ከተሞች ያላቸውን የገቢ አማራጮች ሁሉ አሟጠው ተጠቅመው የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ የከተማ አስተዳደሩ ሕዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችሉ የልማት ሥራዎችን እንዲሰሩም ዕድል ይሰጣቸዋል። የከተማውንም ኢኮኖሚ ከማሳለጡ ባሻገር የንግድና ቱሪዝም እንቅስቃሴን፣የመንገድና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን በአጠቃላይ የልማት ሥራዎችን ያፋጥናል።
በአካባቢው የማኒፋክቸር ኢንዱስትሪዎችን መስፋፋት እንዲሁም ከዚሁ ጎን ለጎን የከተማው ነዋሪ ኑሮ የሚሻሻልበትን፣የሥራ ዕድል የማስፋበትን እንዲሁም የከተማዋና የክልሉ ኢኮኖሚ የሚያድግበትን ሁኔታ ይፈጥራል። እንደ አስፈላጊነቱ የክልል ከተማ አስተዳደሮች አደረጃጀቶችን መሰረት ያደረገ የሕዝብ ምክር ቤቶች እንዲፈጠሩ ዕድል ይሰጣል።
በተጨማሪም ከተሞች ወጪን የመሸፈን አቅም መስፈርት የሚያገኙት ገቢ ወደ ሪጅኦ ፓሊታን ሲሸጋገሩ ክፍለ ከተሞችን ለማዋቀር የሚያስፈልጋቸውን ዓመታዊ በጀት ለመሸፈን ያግዛቸዋል። በአሁኑ ጊዜ ወደ ሪጅኦ ፖሊታን የተሸጋገሩ ከተሞችም ይሄን መሸፈን ያስችላቸዋል። ለዚህም 40 በመቶ ተሰጥቷል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ከተሞቹ በሰበሰቡት የከተማ አገልግሎትና ከዚህ ውጪ በተገኘው መደበኛ ገቢ ላይ በተመሳሳይ ወቅት የነበረውን አማካኝ መደበኛ ወጪ ሸፍኖ የወጪ ፍላጎቱን 50 በመቶ መሸፈን የቻለም ያድጋል። 40 በመቶ ነጥብ የሚያገኝበትም መስፈርት ተቀምጧል። ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ 15 በመቶ ተሰጥቶታል።
ለአብነት በአመላካችነት የተቀመጡት በአምራች ኢንዱስትሪም ሆነ በቱሪዝምና በሌላ የልማት ማዕከል መሆን ሲሆን ከአስራ አምስቱ ስምንት በመቶውን ያሰጣል። ሁለተኛው አመላካች ምቹ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና የማስፋት አቅም ሲሆን ከአስራ አምስቱ ሦስት ተሰጥቷል። ሦስተኛው የትራንስፖርት አሳላጭነት ሚና ሲሆን ከተማው ለሕዝብ፣ ለባቡር፣ ለአየር፣ለውሀ ትራንስፖርት ምቹ መሆኑን ታሳቢ ያደረገና ከአስራ አምስቱ አራት ነጥብ የሚያሰጥ ነው። በአራተኛ ደረጃ መስፈርትነት የተወሰደው የሕዝብ አሰፋፈር ጥግግት ነው። ይሄ በቀድሞው መመሪያ ያልነበረና ከተሞች ወደ ጎን ብቻ ሳይሆን ወደላይም ማደግ እንዳለባቸው ከግምት ውስጥ በማስገባት ከአስራ አምስቱ አምስት ከመቶ ተሰጥቶታል።
ኃላፊው እንደሚሉት በከተሞች ሽግግር ሂደት ሪጂኦ ፖሊታን፣ መካከለኛ ከተማ፣አነስተኛ ከተማ፣ መሪ ማዘጋጃ ቤት፣ ንዑስ ማዘጋጃ ቤት፣ ታዳጊ ከተማና የገጠር ማዕከል አደረጃጀት ተፈጥሯል። ከተሞች ወደ ሪጅኦ ፖሊታን ከተማነት ሽግግር በሚያደርጉበት ጊዜም ከባለ ሁለት እርከን አስተዳደር ወደ ሶስት እርከን አስተዳደር ይሄዳሉ። በዚህ መሰረት አንድ የትልቅ ከተማ አስተዳደር ይዋቀራል። ቀጥሎ ክፍለ ከተማና ቀበሌ አስተዳደር ይኖራል።
ትልቅ ከተማ ለመሆን አንድ ክፍለ ከተማ 60 ሺህ ሕዝብ ሊኖረውም ይገባል። በዚህ መነሻነትም ከሁለት ክፍለ ከተማ በታች የያዘ ሪጅኦ ፓሊታን መሆን አይችልም። በመሆኑም ሁለትና በላይ ክፍለ ከተማ ያላቸው ከተሞች ወደ ሪጅኦ ፖሊታን ሽግግር ማድረግ ይችላሉ። ቀደም ሲል በነበረው ደምብ ሁለት ክፍለ ከተማ የያዘ ወደ ሪጅኦ ፖሊታን ከተማነት ለመሸጋገር 120 ሺህ ሕዝብ ሊኖረው ይገባል። መስፈርቶችን ታሳቢ በማድረግም በክልሉ ከተሞች ከአንደኛው ደረጃ ወደ ሌላኛው የተሻለ ደረጃ ተሸጋግረዋል።
በዘንድሮ ዓመትም በአማራ ክልል መንግሥትና በአማራ ክልል ከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ ውሳኔ የገጠር ማዕከል የነበሩና ወደ ታዳጊ ከተማ የተሸጋገሩ 10 ከተሞች እውቅና ተሰጥቷቸዋል። ከታዳጊ ከተማ ወደ ንዑስ ማዘጋጃ ቤት /ከፈርጅ አምስት ወደ ፈርጅ አራት/ የተሸጋገሩ 10 ከተሞችም አሉ። በተመሳሳይ አራት ከተሞች ከንዑስ ፈርጅ አራት ወደ መሪ ማዘጋጃ ፈርጅ ሦስት ተሸጋግረዋል።
ሰላሳ ከተሞችም ከፈርጅ ሦስት መሪ ማዘጋጃ ቤት ወደ ፈርጅ ሁለት አነስተኛ ከተማ አስተዳደር ተሸጋግረዋል። ከፈርጅ አንድ ከተማ አስተዳደር ወደ ሪጅኦ ፖሊታን ለማደግ ጥያቄ ካቀረቡት ውስጥም ሦስት ከተሞች ሽግግር አድርገዋል።ዘንድሮም በክልሉ ሦስት የሪጅኦ ፖሊታን ከተማ ደረጃ የነበራቸው ከተሞች ማለትም ደብረ ብርሃንን ፣ኮምቦልቻንና ደብረ ማርቆስን ጨምሮ ወደ ስድስት የሚሆኑ ከተሞች አድገዋል። በአጠቃላይ በክልሉ ሃምሳ ሰባት ከተሞች ወደሚቀጥለው ፈርጅ ተሸጋግረዋል።
ኃላፊው እንደሚያብራሩት ፈርጅ አንድ ከተማ 12 ፈርጅ፣ ሁለት ከተሞች 62 መሪ ማዘጋጃ እንዲሁም ፈርጅ ሦስት 120 የሚባሉት ናቸው። ንዑስ ማዘጋጃ ፈርጅ አራት 99፣ ፈርጅ አምስት ወይም ታዳጊ ከተሞች የሚባሉት 362 ናቸው።በአሁኑ ጊዜም በክልሉ ከደረጃ ደረጃ በመሸጋገር 660 ከተሞች በዕድገት ጎዳና እየገሠገሡ ይገኛሉ።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ይትባረክ አወቀ የምክር ቤቱ ውሳኔው ፍትሃዊና ጥያቄያቸውን መሰረት ያደረገ መሆኑን ይናገራሉ። ከተማዋ ወደ ጂኦ ፖሊታን ደረጃ የተሸጋገረባቸው ከተማ አስተዳደሩ ለክልሉ መንግስት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት መሆኑን ይገልፃሉ። ጥያቄውን ተከትሎ የአማራ ክልል ከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ የደረጃ ጥናት መላኩንና ጥናቱ ከተማዋ አሁን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ለማየት እድል መስጠቱንም ያስረዳሉ።
ጥናቱ የሕዝብ ቁጥር፣ ታሪካዊነት፣ የገቢ አቅም፣ እንዲሁም የቆዳ ስፋቷን ከግምት ያስገባ እንደነበርና በጥናቱም ከተማዋ የደረጃ ሽግግሩ የሚገባት መሆኑን መረጋገጡንም ይጠቅሳሉ። ለሽግግሩ ከጅምሩ እስከ ውሳኔው ድረስ የበኩላቸውን ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውና የሽግግር ውሳኔው በእሳቸው አስተዳደር ዘመን መወሰኑ ካላቸው አቅም የበለጠ እንዲሰሩና መነሳሳት እንደፈጠረባቸውም ይገልፃሉ። በክልሉ አመራሮች ላይ የበለጠ ዕምነት እንዲያሳድሩ ማድረጉንም ይጠቁማሉ።
ደብረ ማርቆስ ባለፉት ሃያሰባት ዓመታት የነበረው ስርዓት ጨቁኗቸዋል ከሚባሉ እንደ ደብረ ብርሃን ካሉ ከተሞች አንዷ መሆኗንም ጠቅሰው ከዚህ ወጥታ ወደ ሪጅኦ ፖሊታን ከተማ ማደጓ የመሰረተ ልማት ችግሯን እንደሚቀርፍም ያመለክታሉ። ሽግግሩም ከተማዋን ዳግም አምጦ የመውለድ ያህል መሆኑንም ይመሰክራሉ።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ደስታ አንዳርጌ በበኩላቸው እንደሚሉት ደብረ ብርሀን ኢትዮጵያዊት ከተማ ናት። ኢትዮጵያዊነትን ከማቀንቀን ሌላ ምንም የተለየ አጀንዳም የላትም። የእንዲች ዓይነቱ ከተማ ወደ ረጂኦ ፖሊተን መለወጥ የሚያስደስትና እራካታንም የሚሰጥ ነው። ከተማዋ ከአዋሽ በ130 ኪሎ ሜትር ርቀት ያለች በመሆኗ ለጅቡቲ ወደብም ቅርብ ናት ተብሎ ይታሰባል። ከ ስደስት መቶ ዓመት በላይ ዕድሜ ያላትና የከተሞች አያት ተብላ የምትጠራ ናት።
ለሶስት መቶ ዓመታት ያህልም የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና አገልግላለች። ታሪኳ ወደኋላ ሲፈተሽም ትልልቅ መሪዎች ወጥተውባታል። ማህል ሀገር ከመሆኗ አኳያ የፖለቲካው መዘወሪያና በስልጣኔ የተሻለ ሁኔታ ቢኖራትም ለረጅም ጊዜ ሳትለማ ቆይታለች።
በዚህም በኢኮኖሚው ደረጃ እስከዚህም አቅም አላት ተብላ የምትታሰብ አይደለችም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተለይ ለምስራቅ አፍሪካ ኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆን በሚያስችላት መልኩ እያደገች ትገኛለች። የውጪም ሆነ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ከፍተኛ ቀልብ እየሳበችም ነው። ይሄ ሁሉ ታሳቢ ሆኖና የኢንዱስትሪ ከተማ በመሆኗ ከሦስት ዓመት በፊት ያቀረበችው የመዋቅር ጥያቄ በምክር ቤቱ ውሳኔ አግኝቶ ወደ ጂኦ ፖሊተን ከተማነት ተሸጋግራለች።
የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ኢንጅነር ከማል መሐመድ እንደሚገልፁት ኮምቦልቻ በኢንዱስትሪ ማእከልነት የታወቀችና ለክልሉም ሆነ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፆኦ እያደረገች ትገኛለች። ለዚህም ኢንዱስትሪያል ፓርኳን ብቻ መጥቀሱ በቂ ነው። ይሄው የኢንዱስትሪ ማዕከልነቷም ከአዲስ አበባ በ375 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ከክልሉ መዲና ባህር ዳር በ505 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘውን የፍቅር ከተማ ለሪጅኦ ፓሊታን ከተማነት እንድትመረጥ አስችሏታል። ምክትል ከንቲባው የከተማውን ሕዝብ በማሳተፍ ኮምቦልቻ ለደረጃዋ የሚመጥን አገልግሎት ለነዋሪዋ እንድትሰጥ ለማስቻልና አዲሱን አደረጃጀቷን ለማሳለጥ የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉም ይናገራሉ።
ከአነስተኛ ከተማ አስተዳደር ወደ መካከለኛ ወይም ከፈርጅ ሁለት ከተማ አስተዳደር ወደ ፈርጅ ሁለት ከተማ አስተዳደር እንደግ ብለው ጥያቄ ያቀረቡ ከተሞች በቅርቡ መልስ ያገኛሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በተጨማሪም ከፈርጅ ሁለት ወደ ፈርጅ አንድ ከተማ አስተዳደር ሽግግር ለማድረግ ጥያቄ ያቀረቡ ከተሞች ጥያቄ ለመመለስ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጥናት እየተካሄደ እንደሚገኝ ከክልሉ የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ግንቦት 14/2013