የተወለዱት በቀድሞው አጠራር ወሎ ክፍለሃገር ኮረም ከተማ ውስጥ ነው። የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሌተናል ጀነራል ሃይሉ ከበደ እና እቴጌ ጣይቱ ብጡል በሚባሉ ትምህርት ቤቶች ነው የተማሩት። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ወልዲያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቋንቋና ስነ ፅሁፍ አግኝተዋል። የማስተርስ ዲግሪያቸውንም በዚያው ዩኒቨርስቲ ‹‹እንግሊዝኛን እንደውጭ ቋንቋ ማስተማር›› በሚባለው የትምህርት ዘርፍ ሰርተዋል። በመደበኛ መምህርነት ወልዲያ ፣ ኮምቦልቻና አዲስ አበባ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለ27 ዓመታት አገልግለዋል። በመቀጠልም ወደ ህዝብ ግንኙነት በመሸጋገር በኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ውስጥ ለአንድ አመት ከሶስት ወር ያህል ሰርተዋል።
በኢትዮጵያ የጥራትና ደረጃዎች ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነትና የትምህርት አገልግሎት ሃላፊነት እንዲሁም ተቋሙ በአዲስ መልክ ሲዋቀር ደግሞ የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ሆነው በድምሩ ለዘጠኝ አመታት አገልግለዋል። ጎን ለጎንም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በትርፍ ሰዓት መምህርነት 23 ዓመታት የበኩላቸውን ሚና ሲወጡ ቆይተዋል። በዚህም ሳይወሰኑ ካገኙት ልምድና ካነበቧቸው መፅሃፍት በመነሳሳት ‹‹ውጤታማ የንግግር ዝግጅትና አቀራረብ፣ሕይወትን በጥራት ፣ ኮሙዩኒኬሽን›› የተሰኙ መፅሃፍቶችን ለአንባቢዎች አበርክተዋል። በቅርቡም ‹‹በክርክር እና በውይይት የማሸነፊያ ስልቶች›› በሚል አራተኛውን መፅኃፋቸውን ለህትመት አብቅተዋል። የዛሬው የዘመን እንግዳችን አንጋፋው የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያና መምህር አቶ ሲሳይ አሰፌ ናቸው። ከእንግዳችን ጋር በፃፏቻው መፅሓፎች ዙሪያና ዘንድሮ እየተካሄደ ባለው ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የፓርቲዎች የክርክር ሂደት እንዲሁም በወቅታዊ አጀንዳዎች ላይ ውይይት አድርገናል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- የፃፏቸው መፅሓፎች ይዘት ምን ላይ እንደሚያተኩሩ ያብራሩልንና ውይይታችንን እንጀምር?
አቶ ሲሳይ፡- የፃፍኳቸው መፅሓፍት አሁን በቅርቡ ካሳተምኳቸው ጋር አራት ናቸው። የመጀመሪያው መፅሓፍ በ2003 ዓ.ም የፃፍኩት ሲሆን ‹‹ውጤታማ የንግግር ዝግጅትና አቀራረብ›› የሚል ነው። ይህንን የፃፍኩበት ምክንያት ብዙ ጊዜ በነበረኝ የህዝብ ግንኙነት ሙያ የተለያዩ ቦታዎች ስሄድ ብዙ የስራ ሃላፊዎች ንግግር ሲያደርጉ ንግግሩን የሚከታተለው ተሰብሳቢ በአብዛኛው ለይስሙላ ሲያጨበጭብ አያለሁ። ይሁን እንጂ እነዚህ አመራሮች የብዙዎቹን ሰዎች ልብ የሚገዛ ንግግር ሲያቀርቡ አይስተዋልም። ይህንን ደግሞ በተለያየ ምክንያት ግምት ወስጃለሁኝ። በሁለተኛ ደረጃ የህዝብ ግንኙነት ስሜቴና የመምህርነት ተሞክሮዬ በዚህ ዙሪያ ላይ እንድፅፍ ውስጤ ይነግረኝ ስለነበር በእነዚህ ምክንያቶች ይህንን መፅሃፍ ለመፃፍ ችያለሁ።
ከዚያ በኋላ በ2007 ዓ.ም ደግሞ ‹‹ሕይወትን በጥራት›› በሚል በጥራትና ደረጃ አስፈላጊነት ላይ ያተኮረ መፅሓፍ ፅፊያለሁኝ። ይህንንም የፃፍኩት በጥራትና ደረጃዎች ኤጀንሲ በምሰራበት ወቅት አብዛኛው ህብረተሰባችን የመንግስት ሃላፊዎች በዘርፉ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ ይህንን ግንዛቤ ለማሳደግ የበኩሌን አስተዋፅኦ ማበርከት አለብኝ በሚል ነው። ‹‹ኮሙዩኒኬሽን ለቢዝነስና ለአጠቃላይ ሕይወት›› የተሰኘው ሶስተኛው መፅሃፌን ለመፃፍ ደግሞ ወደ ስምንት ዓመት ነው የወሰደብኝ። በዚህ መፅሓፍ ላይ የኮምዩኒኬሽን አይነቶች፣ ጥበቡና አተገባበሩ የሚሉትን ነገሮች ለመዳሰስ ነው የሞከርኩት። ይህንን የፃፍኩበትም ምክንያት እኔ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሆኜ አገልግያለሁ፤ የኮሙዩኒኬሽን ሰው ነኝ እላለሁ፤ መንግስት ራሱ የኮሙዩኒኬሽን ተቋም አቋቁሞ ሰርቷል፤ ነገር ግን ይህ ዘርፍ የሚገባውን ያህል ታውቋል ብዬ ስለማላምን እኔ አውቄ ሌሎችን ማሳወቅ አለብኝ ብዬ ነው የፃፍኩት። ለዚህም የሚረዱኝን መፅሓፍት ሳገላብጥ የሰለጠነው ዓለም የሚያስተምረውን መሰረታዊውን የኮሙዩኒኬሽን ክህሎቶችን በስፋት ነው ለማየት የሞከርኩት።
በእኛ ጋር ኮሙዩኒኬሽንን ተግባቦት ብለን ለመተርጎም እንሞክርና በአጭሩ መግባባት ብቻ አድርገን እናየዋለን። ያ ብቻ ግን አለመሆኑን ተረዳሁኝና በጣም ሰፊ ዘርፍ መሆኑና በሁሉም መስክ ልንጠቀምበት የምንችልበት መሆኑን እንዲሁም በአገራችን ያሉትን የኮሙዩኒኬሽን ችግሮችና መፍትሄውን ጭምር ነው በመፅሃፌ ላይ ያካተትኩት። ይህ መፅሓፍ በግለሰቦችም ሆነ በቡድንና በተቋም ደረጃ ያሉ ግጭቶችን በምን መልክ መፍታት እንደሚቻል የሚያሳዩ ጥበቦችንም ጭምር አመላክቷል። በአካልም በገንዘብም ወገብ የሚያጎብጥ ቢሆንም ሰፋ ያለ ዝግጅት አድርጌ ነው ለህትመት ያበቃሁት።
አራተኛው መፅሓፌ ደግሞ ወቅቱ የምርጫ ጊዜ እንደመሆኑ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በዚህ ምርጫ ምን አስተዋፅኦ ማድረግ አለብኝ በሚል ግብዓቶች ሳሰባስብ ነው የቆየሁት። በተለይም የሚመለከታቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ሊያገለግል የሚችል ስራ መስራት አለብኝ በሚል ነው የፃፍኩት። ይህም በዋናነት አንጃና ግራንጃ እንዲሁም ከስድብና ዘለፋ የውይይት ስልት ወጥተው ሳይንሳዊ መንገዱን የሚያሳይ መፅሃፍ ነው። በነገራችን ላይ ይሄ ሁለት ክፍል ያለው መፅሃፍ ነው። መሰረታዊ ግንዛቤና ፖለቲካዊ ክርክሮችን ምንነትም ይዳስሳል። ክርክር በቤተሰብም፣ በጓደኛ፤ በስራ ቦታም ሊከሰት ስለሚችል በምን መንገድ ልናደርገው ይገባል የሚለውን ነገር ለማሳየት ያስችላል።
አዲስ ዘመን፡- የክርክር አስፈላጊነት ምንድን ነው? በውይይትስ ማሸነፊያ ስልቶች ምንስ ናቸው?
አቶ ሲሳይ፡– በመሰረቱ የዚህ ውይይት ዋነኛ ጭብጥ ሆኖ ቢወጣ ደስ የሚለኝ ክርክር ጠብ ወይም ግጭት አለመሆኑን በማስገንዘብ ነው። ክርክር የአንድ ሰው ወይም የአንድ ቡድን አቋም ትክክለኛነት ማረጋገጥ የሚችልበት መንገድ ማለት ነው። ክርክር እውነትን በመፈለግ ማሳመን ማለት ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚከራከሩ ሰዎች አንደኛ ከዋነኛ የመከራከሪያ ነጥባቸው እንዳይወጡ፣ አቋማቸውን እንዳይስቱ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። ሁለተኛ የሌላውን ሰው እይታ ወይም አመለካከት ለማየት ምቹና ዝግጁ መሆን አለባቸው። የሌላውን ሃሳብ ለመቀበል ደግሞ አዕምሮን ክፍት ማድረግ ያስፈልጋል። ብዙ ጊዜ የራስን አቅጣጫ ብቻ በመናገርና በማቅረብ ተቀበሉኝ በማለታቸው ነው ሰዎች ችግር ውስጥ የሚገቡት።
አሳማኝ እስከሆነ ድረስ የሌላውን ሃሳብ ለመቀበል ሊያስፈራን የሚችልበት ምክንያት የለም። ያ ሲሆን ራሱ ተከራካሪው ወገንም አመኔታና ተቀባይነት እንዲሁም ክብርንም ያገኛል። አንድ ተከራካሪ ‹‹የእኔን ተቀበሉኝ›› እንደሚለው ሁሉ የሌላውን የመቀበል ብልሃትና ትዕግስት ሊኖረው ይገባል። የፈጠጠውን እውነት አንቀበልም ብንል ህዝቡም ግምት ይወስድብናል፣ ይታዘበናል። አድማጭና ተመልካች ሁኔታውን እያየ ‹‹አልቀበልም›› የሚለውን ሰው አዕምሮው ዝግነት ነው ሊረዳ የሚችለው። ሌላው ስሜታዊነትን መቆጣጠር ያስፈልጋል። አንድ ተከራካሪ ስሜታዊነቱን ከተቆጣጠረ ነጥቦቹን አይስትም። ለማሸነፍም ይረዳዋል። በተረጋጋ ስሜት ሊናገር ወይም ሊፅፍ የፈለገውን ነገር ማድረግ ይችላል።
ክርክር ሂደት ነው። ስለዚህ ከመጀመሪያውም መከራከር ያለብን ይሄ ክርክር መቋጫ ሊያገኝ ይችላል ብሎ ተስፋ በማድረግ ነው። ይሁንና እኔን ካልተቀበሉኝ አይቋጭም ብሎ የተነሳ ሰው ወደ ገደል ነው የሚሄደው። በመፅሃፌ ላይ እንዳሰፈርኩትም ሰው ሃሳብ የማይቀበልና ግትር ከሆነ መጨረሻ ላይ ከሁሉም ጋር መናከሱና መጣላቱ አይቀሬ ነው። አንድ ግለሰብ የማያዳምጥ ከሆነ የሃሳብ ግትርነት ካለበት ተከራካሪዎቹን ብቻ ሳይሆን ህዝቡንም ነው ገደል ይዞት የሚገባው። ማህበረሰቡ ችግር ውስጥ ይወድቃል።
ይህንን ዓላማ አርቆ አስቦ ነው አንድ ሰው ወደ ክርክርና ውይይት መግባት ያለበት። ሌላው የማሸነፊያ አንዱ ስልት ተቃራኒን ማክበር ነው። ተቃራኒ የፈለገውን ያህል ቢናገር መብቱ ነው፤ ትክክል መሆኑንና አለመሆኑን መዝኖ የራሱን አተያይ ማቅረብ ነው እንጂ የግድ ተቃራኒ ሊሆን ሲባል ብቻ ሃላፊነት ሳይኖር የሚወሰድ አቋም ትክክል አይደለም። በመሰረቱ ሰዎቹን አይደለም መቃወም ያለበት፤ ሃሳባቸውን ነው። ሃሳባቸውን ስንቃወም ደግሞ በአክብሮት ነው መሆን ያለበት። ይህ ከሆነ ደግሞ መደማመጥ ይኖራል። እኔም በተራዬ እከበራለሁኝ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አንፃር ላይ እንደሀገር ቁጭ ብሎ ለመነጋገርም ሆነ ለመደማመጥ ያልተቻለበትና ለልዩነቶቻችን መስፋት ምክንያት ምንድናቸው ብለው ያምናሉ?
አቶ ሲሳይ፡- አስቀድሜ የጠቀስኩልሽ ኮሙዩኒኬሽን መፅሃፌ ላይ መደማመጥ የሚለው ፍሬ ሃሳብ ራሱን የቻለ ሰፊ ርዕስ አለው። ከዚያ ውስጥ ትልቁን ቦታ የያዘው የመደማመጥን ጥቅም የሚያነሳው ክፍል ነው። በመሰረቱ አንድ አፍ ሁለት ጆሮ የተሰጠን ከማውራት ይልቅ ለማዳመጥ ቦታ እንድንሰጥ ነው። ይሁንና ብዙዎቻችን የሌላውን ለማዳመጥ ልባችንም ሆነ ጆሯችን ክፍት አይደለም። ለዚህ ደግሞ አንዱ ችግራችን ‹‹እኔ ብቻ ላውራ›› ማለታችን ነው። አስቀድሜ እንደገለፅኩልሽ እኔ ብቻ ላውራ የምንል ከሆነ ሌላውም ሊያዳምጠን ፍቃደኛ አይሆንም፤ አይገደድም። ያለመደማመጥ የፈጠረውን ችግር ካየን እንዳው የእኛን ለጊዜው እናቆየውና ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ነው። በደቡብ ሱዳን አለመደማመጥ በመኖሩ በርካታ ህዝብ አልቋል።
ሁሉም እኔ ብቻ ነኝ ትክክል በማለቱ በርካታ ህዝብ ተፈናቅሏል፤ ተሰዷል። የሶሪያ መሪዎች ህዝቡን ለማዳመጥ ባለመቻላቸው ዛሬ የሶሪያ ህዝብ በመላው አለም ባሉ ሀገራት ተሰዷል። ይህ የሆነው በፖለቲከኞች አለመደማመጥ ምክንያት ነው። ሊቢያን ብንወስድ በአፍሪካ ጠንካራ የነበረች ሀገር እንደነበረች ይታወቃል፤ ምንም እንኳን ሌሎች የፖለቲካ ተፅዕኖ እንዳለ ሆኖ አንዱ ሌላውን ለማዳመጥ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት በሁለት ቡድኖች ተከፍላ ወደ ነውጥ የገባችበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
ይህ ደግሞ በሱማሊያም ተመሳሳይ ሁኔታ ነው የተከሰተው፤ በትንንሽ የጎሳ መሪዎች ምክንያት ህዝቡ ተለያይቶ ለዓመታት ጠንካራ መንግስት አልነበራትም፤ ይህም ጦሱ ለእኛም ሀገር ጭምር የተረፈበት ሁኔታ ነው ያለው። በእኛም ሀገር ተመሳሳይ ሁኔታ ነው ያለው። እርግጥ ነው አባቶቻችን ቁጭ ብለው በትዕግስት የመደማመጥ የቆየ ባህል አላቸው። ባለፉት ዓመታት ግን በተለያዩ ምክንያቶች ሰዎች የቡድን፣ የብሔር፣ የአካባቢ፣ የጥቅም ስሜት እያሳዩ በመምጣታቸው ምክንያት መደማመጥ ጠፍቷል።
ሁላችንም የየግላችን ጥቅም እንዲጠበቅልን ብቻ በመሮጣችን ሀገሪቱን በመፍረስ ስጋት ውስጥ ጥለናታል። በመሰረቱ ሌላውን ማዳመጥ ያልፈለገ ሰው እሱ እንዴት ነው ሊደመጥ የሚፈልገው? ቅዱስ መፅሃፍት እንደሚለው በራሳችን ላይ እንዲፈፀም የማንፈልገውን በሌላው ላይ እንዲሆን መዳዳታችን ለውድቀት ነው የዳረገን። በአጠቃላይ በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ራስወዳድነት፣ ፅንፈኝነት ስሜት እያደገ መምጣቱ ለዘመናት ተቻችለው የኖሩትን የህብረተሰብ ክፍሎች ወይም ቡድኖች እንዳይደማመጡ አድርጓል ባይ ነኝ።
በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ‹‹አልተማረም›› ከምንለው ህብረተሰብ ይልቅ በትምህርት ደረጃ ትልልቅ ማዕረግ የያዙ ፖለቲከኞች ጭምር ራስ ወዳድ ሆነው፣ አይናቸውን በጨው አጥበው ‹‹ እኛ በምንለው መንገድ ብቻ ካልሄዳችሁ ይሄ ህዝብ አይኖርም፤ ይህች ሀገር አትቀጥልም›› ብለው ሲናገሩ መስማታችን ነው። ይህንን ፀያፍ አነጋገር በተለይም ከተማሩት የህብረተሰብ ክፍሎች አንደበት መደመጡ በጣም አሳፋሪና አስነዋሪ ተግባር ነው። ይሄንን ደግሞ የወለደው እነዚህ ሰዎች ለራሳቸው ካላቸው የተሳሳተ ግምትና ራስወዳድነት ነው።
ሁሉም በኪሱ ትንንሽ ዘውድ ይዞ እኔ ያልኩት ብቻ ይሰማ ብሎ የሚደረገው ሩጫ ፈፅሞ ተሰሚነት ሊኖረው አይችልም። በነገራችን ላይ ራስንም ማዳመጥ አንድ ችሎታ ነው። ይህም ማለት ራስን በትክክለኛ መንገድ ካዳመጥነው እየሄድንበት ያለው የስህተት መንገድ ያሳየናል፣ ወደቀናውም መስመር ይመልሰናል ብዬ አምናለሁ። ነገር ግን ለእኔ ጥቅም ብቻ ብዬ ከሆነ ራሴን የማዳምጠው ይዞኝ ገደል ይገባል። በአጠቃላይ ያለመደማመጥ ጦሱ ብዙ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ህወሓት ባለፉት 27 ዓመታት በሀገሪቱ ህዝብ ላይ የፈጠረው መከፋፋልና አሁን ላጋጠመው አገራዊ ስሜት መጥፋት ዋነኛ ምክንያት አይሆንም?
አቶ ሲሳይ፡– ጥሩ ጥያቄ ነው ያነሳሽው!፤ በሌሎች ሀገሮች የታየው አለመደማጥ በእኛ ሀገር ደግሞ ባለፉት 27 ዓመታት በተዘራው የልዩነት አስተሳሰብ ምክንያት ምን ላይ እንዳደረሰን ሁላችንም በተጨባጭ የሚታይ ነው። ባልና ሚስት እርስበርስ መደማመጥ ካልቻሉ ትዳሩ መፍረሱ እንደማይቀረው ሁሉ አንድ መንግስትም ሆነ ቡድን እርስ በርስ መደማመጥ ሌላውንም ማድመጥ ከተወና ወደአላስፈላጊ እልህ ከገባ አገርን ማፍረሱና ህዝቡንም መበተኑ አይቀሬ ነው። በሚፈጠሩ ክርክሮች የሌላውን ላለማዳመጥ ረግጦ የሚወጣ ከሆነ ለመለያየት በሩን ከፈተ ማለት ነው።
በመሰረቱ ሌላውን የማያዳማጥ ሰው በመጀመሪያ ደረጃ በራስ መተማመን እንዲሁም በቂ እውቀትና ችሎታ የሌለው ሰው ነው። እንዲህ አይነቱ ሰው አለማወቁን ለመሸፈን ሲል ብቻ ነው የሌላውን ማዳማጥ የማይፈልገው። አንቺ ያነሳሽው የህወሓት ጉዳይም ተመሳሳይ ነው። ከመጀመሪያውም ጀምሮ የህወሓት መሪዎች ለመደማመጥ ፈቃደኛ አልነበሩም። ህወሓቶች እስቲ በራሳቸው ጊዜ ይስተካከሉ፤ ወደ አዕምሯቸው ሲመለሱ ይሄንን ነገር ይተውታል ተብሎ ጊዜ ቢሰጣቸውም ለማዳመጥ ፈቃደኛ አልነበሩም። ሌላውን ማዳመጥ ያለመፈለግና ከውስጥ የሚነጭ እብሪትም እያደገ ሄደና ከነጭራሹ ወደ ሃይል እርምጃ ተገባ።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው የጀርመኑ ናዚ ነው። እንደሚታወቀው በሁለተኛው የአለም ጦርነት ናዚ መራሹ የጀርመን መንግስት የራሳቸውን ንፁህ ዘር አለምን መግዛት አለበት ብለው ሲነሱ ሊመክሯቸው የፈለጉትን ባለመስማማታቸው ሀገሪቱም ፈረሰች፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብም አለቀ። አለመደማመጥ የሚፈጥረው ችግር ይሄ ነው። ወደሀገራችንም ስንመለስ አንዱ ቡድን ነባራዊውን ሁኔታ መቀበል ካልፈለገ እውነታው እያፈጠጠ ሲመጣ ወደ ገደል መግባቱም ሆነ መሸነፉ አይቀሬ ነው።
አሁን በሀገራችን ያየነው ህግ ወደማስከበር የተገባበትን ሂደት ስንመለከት ካለመደማመጥ እና እኔ ብቻ ያልኩት ይሁን ከማለት አልፎ ተርፎም እኔ የያዝኩትን መልቀቅ የለብኝም ከማለት የመነጨ ነው። ህወሓት እኔ በምፈልገው መንገድ ካልተኬደ ሌላውን ማዳመጥ አልችልም በማለቱ ነው ሁላችንም ወደዚህ አይነት ችግር ውስጥ የገባነው። እንዲህ አይነቱ ቀውስና ውርደት ውስጥ የገባነው በእነዚህ አካላት ግትር ማንነት ነው። እንዳውም የህዝቡ ተቻችሎ የመኖር ባህልና እሴት ባይኖር ኖሮ የተፈጠረው ችግር ሀገሪቱ አሁን ካለው በላይ ትልቅ ችግር ውስጥ ትገባ ነበር የሚል እምነት አለኝ።
እንዳውም እንደሀገር የመቀጠሏ ነገር ጥያቄ ውስጥ ይገባ ነበር። ትላንት ኢትዮጵያን ለመፍትሄ ስትማፀን የነበረችና ስንት ውለታ የዋልንላት ሱዳን እንኳን ይህችን አጋጣሚ ተጠቅማ መሬት የመውረር ሙከራ አድርጋብናለች። ይሄ አንግዲህ ለእኛ የመፍረስ ምክንያት ሊሆነን ይችል ነበር፤ ነገር ግን እኛ ኢትዮጵያውያን ጠንካራ እሴት ያለን በመሆኑ ነው እንዳሰቡት ያልፈረስነው፤ ያልተበተንነው።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ሰላማዊና ምክንያታዊነት የተላበሰ የክርክር ባህል ነበር ማለት ይቻላል?
አቶ ሲሳይ፡- ምንአልባት ለዚህ እንዲረዳን አንድ ነገር ላንሳ፤ በምርጫ ወቅት በሚደረጉ ክርክሮች መራጮች የተሟላ መረጃ አግኝተው ወደ ምርጫ ሳጥን እንዲሄዱ የሚረዳ መሆኑ እሙን ነው። እጩዎችም ከግል ስብዕናቸው፣ ከሃይማኖት ወይም ከጎሳ ታማኝነት ይልቅ ህዝብ ሊጠቅም በሚችል ፖሊሲ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉም ያበረታታል ተብሎ ይታሰባል። በህዝብ መካከል ውይይት ማድረግ ለግጭት መንስኤ የሆኑ ነገሮችን ለማቃለል ይረዳል። የተመረጡ ባለስልጣኖች በምርጫ ዘመቻ ወቅት ለገቡት ቃል ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግና ለዲሞክራሲ ማበብም የላቀ ሚና አለው።
በዚህ ረገድ አሁን ያልሽውን ነገር ስናነሳ በንጉሱ ዘመን ምክር ቤት ውስጥ ክርክር ይደረግ ነበር። በዚያ ጊዜ በነበረው ተጨባጭ ሁኔታ ሰዎች አንፃራዊ የሆነ ውይይት ያደርጉ ነበር። በደርግ ጊዜም የተለያዩ የምርጫ ውይይቶችና ክርክሮች ነበሩ። ይህም ሲባል ግን ሳይንሳዊ መስመርን ተከትለው ፣ እውነተኛ በሆነ መልኩ ነው ብሎ መናገር አይቻልም። ምንአልባት በወቅቱ የነበሩ ሰዎች ወይም ጥናት አድራጊዎች የራሳቸው አተያይ ሊኖራቸው ይችላል። ግን ብዙዎቻችን ልንስማማ የምንችለው ነገር ውይይቱና ክርክሩ በዳበረ ፖለቲካ ውስጥ ያልመጣ በመሆኑ ሊጎለብትና ሊያድግ አለመቻሉን ነው።
በደርግ ጊዜም በተወሰነ መልኩ በርዕዮተ ዓለም ጉዳይ ክርክሮችና ውይይቶች ቢኖሩም በፖለቲካ ድርጅቶች መካከል በነበረው ሽኩቻ በቀይና በነጭ ሽብር እንዲደመደም ነው ያደረገው። ይህም እንግዲህ በሃሳብ አለመለዋወጥ መቻልን ነው የሚያሳየን። ይህ በሚሆንበት ወቅት ህብረተሰቡ ነው የሚጎዳው። የታሪክ ጠባሳ ይኖራል። በቀይሽብርና ነጭ ሽብር ስንል ስንት ወጣት ነው ያለቀው?። በቀይ ሽብር ትውልድ ያለቀው በፖለቲካው ዘርፍ የክርክር እና የውይይት ባህላችን ያልዳበረ በመሆኑ ነው። በእኔ አመለካከት ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ተከራክሮ ለማሸነፍ፤ ተገናኝቶ ለመወያየት የፖለቲካ ልምዱ አልነበረንም።
በወቅቱ በነበረው አለምአቀፍ ደረጃ ከነበረው የፖለቲካ ስርዓት ጋር ተያይዞ የነበረው የፖለቲካ ሽኩቻ የራሱን ጠባሳ ነው ያስከተለው። በኢህዴግ ጊዜም ስንመለከት ለምልክት ያየነው አንፃራዊ የክርክር መድረክ በ1997 ዓ.ም ምርጫ ነው። ይህም ማለት የምርጫው ውጤት ሌላ ሆኖ የተሻለ የሰውን ስሜት ሊገዛ የሚችል የክርክር ሂደት ያየነው በዚያ ወቅት ነው። አሁን ላይ ሰው ሁለት ስሜት ያለው ይመስለኛል። አንዳንዱ ‹‹እንደ 1997ቱ ምርጫ ክርክርና ውይይት ቢደረግ የተሻለ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ ይችላል›› የሚል አመለካከት አለው።
ሌሎች ደግሞ ክርክር ቢደረግም፤ ባይደረግም የሚያሸንፈው አንዱ ስለሆነ ምንም ዋጋ የለውም›› ብሎ ተስፋ የሚቆርጥም አለ። ትልቁ ነገር አሁን እያንዳንዱ ህብረተሰብ ለራሱ ያለው እውነት ምክንያታዊ ሆኖ ሌላውን አሳምኖ የሌላውን ሃሳብ ለመረዳት መፈለጉ ላይ ነው። ያ ከሆነ የጋራ ነገር ይኖረናል። ስለዚህ እስካሁን የመጣንበት ሂደት በትክክል ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ወይም አለም በሄደበት መንገድ አልተከተልነውም። በነገራችን ላይ ክርክር በባህላችን አዲስ አይደለም።
ጥንታዊ ባህልን ስንመለከት ‹‹በላ፤ ልበልሃ›› የሚለው የዳኝነት ሂደት አባቶቻችን ተከራክረው ለማሳመን የሚጠቀሙበት ባህል መኖሩን ነው። በየፍርድ አደባባዩ የምናያቸው ክርክሮች እኮ የዚያ ነፀብራቆች ናቸው። ይህንን ባህል ማስቀጠል ባለመቻላችን አሁን ያለው ትውልድ እርስበርስ ከመደማመጥ ይልቅ ወደአላስፈላጊ ንትርክና ጠብ ውስጥ ሲገባ ይታያል። አንዱ የጠብና ችግር መንስኤ የሚሆነው በያዝነው መረጃ ላይ በቂ እውቀት አለመኖሩ ነው።
ይህ ሲሆን በአግባቡ ተከራክሮ ከማሳመን ይልቅ ወደ ስድብ ነው የምናመራው፤ ሌላውንም ማዳመጥ አንፈልግም። ምክንያቱም ሲጀመርም እውቀቱ ስለሌለን ክርክሩ ከቀጠለ የእኛ የተበላሸ መረጃ ሊጋለጥብን ይችላል የሚል ስጋት ስለሚኖረን ነው። ሌላውን በአጠቃላይ በሀገራችን የፖለቲካ ክርክር ያልዳበረ በመሆኑ ዲሞክራሲን ማሳደግ አልቻልንም። እየተሻሸለ መምጣት ሲገባው የፖለቲካ ልምድ ባለመኖሩ ወደ ጭቅጭቅና ወደ ጠብ የምንደርስበት ሁኔታ በተጨባጭ አይተነዋል።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን ብልሹ አስተሳሰብ ለመቀየር ትውልዱ ምን ያህል ዝግጁ ነው ብለው ያምናሉ?
አቶ ሲሳይ፡- አሁን ላይ ያለው የህብረተሰብ ክፍል በተለያየ የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ ያለፈ ነው። በጥንታዊው ክርክር ባህላዊውን ነገር አይቶ የመጣና ከቀደመው ትውልድ የወረሰ፣ የደርግ ዘመኑን ቀይ ሽብሩንም ሆነ ነጭ ሽብሩን አይቶ ያለፈ ትውልድ አለ። በሌላ በኩልም ከ27 ዓመቱ የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ የ1997ቱ ምርጫ አይነት ጭላንጭል ተስፋ ያየ ብሎም ለውጥ እየጠበቀ ያለ አዲስ ትውልድ አለ። በዚህ አይነቱ የተደበላላቀ ዘመንን ያለፈ ትውልድ ባለበት ይሄ ነው ብሎ ለመናገር ያስቸግራል። ያም ሆኖ አሁንም ድረስ ትልልቅ የፖለቲካ ሰዎችና ሊሂቃን ጭምር ያለፈውንና አሮጌውን ብልሹ ባህል ለማምጣት ጥረት የሚያደርጉ አካላት መኖራቸውን በተጨባጭ አይተናል። ራስን ከጊዜ ጋር መለወጥ ስልጣኔ መሆኑ ቢታመንም ዛሬም አሮጌውንና የተጎዳንበትን ስርዓት ለማምጣት የሚጥረው ቁጥሩ ቀላል አይደለም። የዛሬ 20 ዓመት የተከራከርኩበትን ነጥብ አሁን ይዤ ልቀርብ አልችልም። አለም የደረሰበትን ደረጃ ለመድረስ ከተፈለገ ወጣቱ የሚፈልገውን ነገር ለማወቅ መጣርና አዲስ ነገር ይዞ መቅረብ ይጠበቅብናል።
ከሁሉም በላይ ግን እነዚህን አላስፈላጊ ጠቦችና ክርክሮች በዘመናዊ የክርክር ባህል መቀየር ያስፈልጋል ባይ ነኝ። በእውነቱ ይህንን ለመቀበል ፈቃደኝነት ያስፈልጋል። በዚህ የምርጫ ጊዜ የሚፎካከሩ ሃይሎች ይጠቀሙበታል ብዬ መፅሃፍ ባሳትምም የንባብ ባህላችን ደካማ በመሆኑ እና ሁሉም ለማሸነፍ ብቻ ስለሚሮጥ ብዙም እየተጠቀሙበት አይደለም። ምክንያቱም አብዛኛው ተፎካካሪ የሚጠቅመውን ነገር አስቦ ከመዘጋጀት ይልቅ እንዴት አድርጎ ተቀናቃኙን ከትፎ እንደሚያወርደውና እንደሚጥለው ነው የሚጨነቀው። ልክ በንግድ አሰራር አንዳንዱ ስርዓቱን ጠብቆ ቢሰራም ሌላው በአቋራጭ ለመክበር ሲል ብቻ ጓደኛን ጠልፎ ለመጣል እንደሚጥረው ሁሉ በፖለቲካውም ዓለም በቅንነትና በህጉ መሰረት ከመሄድ ይልቅ የምቀኝነት አካሄድን ነው የሚከተለው።
ወቅቱ እውቀት የሚጠይቅ ቢሆንም ያለፈው ጠባሳ አብዛኛውን ፖለቲከኛ ስላልለቀቀው አንዱ ሌላውን ጠልፎ ለመጣል ሲሯሯጥ ነው የሚስተዋለው። ዘመናዊው የክርክር አቀራረብ በውይይትና በጥበብ ማሸነፍ፣ የሌላውን ሃሳብ የመቀበል ልምድ በማዳበር ነው። ይህ ሲሆን የምናስበውን አላማ እናሳካለን ማለት ነው። አገራችን እንድታድግና ማህበረሰባችን የተሻለ ህይወት እንዲኖረው የምንፈልግ ከሆነ በውይይት የሚያምን ፖለቲከኛ ሊኖረን ይገባል። ሀገሪቱ ያላትን ሃብት ተጠቅማ ለማደግ የምትችለው የዚህ አይነት የፖለቲካ ባህል ማዳበር ስንችል ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አንፃር በዘንድሮ ምርጫ እየተሳተፉ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የክርክር ሂደት ምን ያህል ሳይንሱን የተከተለ ነው ብለው ያምናሉ?
አቶ ሲሳይ፡– የተወሰኑትን ክርክሮች ተከታትያለሁ፤ አንዳንዶቹ ያላቸውን ፖሊሲና ዓላማ በጨዋ መንገድ ለማቅረብ ጥረት ያደርጋሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ ገና ሲጀምሩ በስድብ የሚጀምሩም አሉ። ተቀናቃኛቸውን በመዘርጠጥ ለማንቋሸሽ ጥረት ያደርጋሉ። በመሰረቱ ጥሩ ነገር ያለው ፖለቲከኛ ሰውን በመዝለፍ አይጀምርም። ያልጣመሽ ነገር ቢኖር እንኳን በጨዋ መንገድ ስታቀርቢ የአድማጭና ተመልካቹን ስሜት መያዝና ተቀባይነት ማግኘት ትቺያለሽ። ከዚህ አንፃር ስመለከት መድረኮቹ መፈጠራቸው መልካም ነው፤ ለሁሉም በተቻለ አቅም ተመጣጣኝ እድል ለመስጠት እንደተሞከረ እረዳለሁ።
ግን ከጥቂቶቹ በስተቀር ብዙዎቹ ተፎካካሪዎቻችን የክርክር መርህን ይዘው ከመሄድ ይልቅ ወደዘለፋ፣ ወደ ማንቋሸሽ ይሄዳሉ። እኔ ይሄ የሚያሳየኝ መጀመሪያ በእጃቸው በቂ መረጃና ፖሊሲ እንደሌላቸው ነው። ፖሊሲያቸውን ለህዝብ በማስተዋወቅ ቢጀምሩ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያገኛሉ። ብዙ ጊዜ የሚያሸንፉት የነቃፊዎቻቸውን ውርጅብኝ በእርጋታ ተቀብለው የራሳቸውን እውነት ለማሳየት ጥረት የሚያደርጉ አካላት ናቸው። የፖለቲካ ክርክርን በተለያየ ዓውድ ማሸነፍ የሚቻለው በሃሳብ ልዕልና እና በጥበባዊ አቀራረብ ብቻ ነው። ከዚህ አንፃር አሁን ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ይበልጥ በእውቀት፣ በስልት፣ በመረጃ፣ በዲሲፒሊን ላይ የተመሰረተ ክርክርና ውይይት ሊያርጉ ይገባል የሚል እምነት አለኝ። በዘለፋ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ክርክርና ውይይት የትም አያደርስም።
አዲስ ዘመን፡- በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ አንድ ፓርቲ ለረጅም አመታት አገርን ሲያስተዳድር ይስተዋላል። ይህም በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ የሚኖረው አሉታዊ ሚና ምንድን ነው ብለው ያምናሉ?
አቶ ሲሳይ፡- ምንአልባት ይሄ ጥያቄ ከእኔ ይበልጥ ለፖለቲከኞች ቢጠየቅ የተሻለ ነው ብዬ አምናለሁ። ነገር ግን እንደአንድ ዜጋ ከውስጥም ከውጭም ስታዘብ በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ አገርን ለረዥም ዓመታት የሚገዙ ፓርቲዎች ‹‹እኔ ብቻ አውቅልሃለው›› በሚል ለሌላው እድል የማይሰጡ ናቸው። አብዛኞቹ የአፍሪካ መሪዎች የእድሜ ልክ ፕሬዚዳንት ሆነው 40 እና 50 ዓመት አገር የሚያስተዳድሩ አሉ። ይህ መሆኑ በራሱ አዲሱን ትውልድ የማያሳትፍ ከመሆኑም ባሻገር የሃሳብ ብዝሃነትን ይገድባል።
ይህም ሄዶ ሄዶ የዲሞክራሲ ሂደቱን ማቀጨጩ አይቀሬ ነው። ህዝቡም የፈለገውን መምረጥና ማውረድ የሚችልበትንም እድል ያጠባል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ቀውስ ይፈጠራል። ደግሞም ለብዙ ጊዜ በአንድ መሪ ወይም ፓርቲ የሚተዳደሩ አገራት ሲታዩ ከፕሮፖጋንዳ ስራቸው ባለፈ ህዝብን በፍትሃዊነት ተጠቃሚ ያደረጉ አይደሉም። በአንፃሩ አሳታፊ የምርጫ ሂደት የሚከተሉ አገራት በዲሞክራሲም ሆነ በልማቱ ከፍ ያለ ደረጃ የደረሱበት ሁኔታ ነው ያለው። ምክንያቱም ህብረተሰቡ የፈለገውን የመምረጥ መብቱን በጠበቅሽለት ቁጥር የመስራት፣ የማደግ ፍላጎቱን ታሟይለታለሽ።
አዲስ ዘመን፡- በዘንድሮ ምርጫ ቅስቀሳ ሂደት ህብረተሰቡ ስለፓርቲዎቹ ፖሊሲ በቂ እውቀት እያገኘ ነው ማለት ይቻላል? ፓርቲዎቹ ለህብረተሰቡ ተደራሽ የሚሆኑበት እድልስ አግኝተዋል?
አቶ ሲሳይ፡– እኔ ሁለት ነገሮች ነው የሚታዩኝ። የመጀመሪያው ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ስሜታዊ ሆኖ ሳይሆን መሰረታዊ የሆኑትን የሃገሪቱን ችግሮች ከልብ መረዳት መቻል አለበት። ይህንን ሲጨብጥ በእውነት ላይ የተመሰረተ ማስረጃ ፣ እውቀት ይዞ የመፍትሄ ሃሳብ ማቅረብ የሚችል መሆን አለበት። ከዚህ አንፃር አንዳንዶቹን ስመለከት ሃገሪቱን በተጨባጭ ያውቋታል ብዬ ለመናገር ይከብደኛል። ምክንያቱም የሚያቀርቡት መረጃ በጣም ውስን በሆነና ስሜታዊነት የተሸፈነ ነው።
በእርግጥ አንዳንዶቹ የተሻለ የፖሊሲ አማራጭ ይዘው የቀረቡ አሉ። እነዚህ ፓርቲዎች ሊበረታቱ ይገባል። ነገር ግን አብዛኞቹ አስቀድሜ እንዳልኩሽ ሌላን በመኮነን እና በመዝለፍ ላይ የተመሰረተ ሃሳብ ነው ይዘው የሚቀርቡት። ይህ የሆነው ደግሞ በእውቀት ላይ የተመሰረተ የውይይት ባህል እየዳበረ ባለመምጣቱ ነው። በቀሪ ጊዜ ውስጥ አሁንም የሃገራችንን ችግሮችና ተጨባጭ ሁኔታ ከፖለቲካ ስልጣንና ከስሜታዊነት እንዲሁም ከራስ ወዳድነት ፣ ከፅንፈኝነት፣ ከዘውድ ደፊነት ስሜትም ወጥተው አቋማቸውን ለህብረተሰቡ ማድረስ መቻል አለባቸው። የህዝቡን የልብ ትርታ ያደመጠና የሚመልስ ሃሳብ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። ይህንንም በእውነተኛ የሀገር ፍቅር ስሜትና ለህዝብ ተቆርቋሪነት ተነስተው ሊሆን ይገባል።
ከዚህ አንፃር ፓርቲዎቹ እስካሁን እያረጉት ባለው የቅስቀሳ ሂደት ህዝቡ በሚገባ አውቋቸዋል ለማለት ይከብደኛል። ነገር ግን አሁንም ህዝቡ ጋር መድረስ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይገባቸዋል። በቀራቸው ጊዜ በመላው ሀገሪቱ ያለው ህዝብ በትክክል ያሉትን አማራጮች ተገንዝቦ እንዲመርጥና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ምርጫ እንዲያካሂድ ከፍተኛ ስራ መሰራት መቻል አለበት። በተለይም ፓርቲዎቹ ህዝቡን ያማከለ የምርጫ አካሄድ መከተል አለባቸው። እርግጥ ነው ዘንድሮ በየቦታው የሚለጠፉ ፖስተሮች በአንፃራዊነት የተሻለ ነው ብዬ አምናለሁ።
ይህም ህብረተሰቡ ከሌላው ጊዜ በተለየ የሚመርጣቸውን ሰዎች ማንነት ከወዲሁ እንዲገነዘብ አድርጎታል። ነገር ግን በመገናኛ ብዙሃን የሚካሄዱት ቅስቀሳዎች ለህዝቡ በሚመች ሰዓትና ሁኔታ እየተካሄዱ ነው ለማለት አልችልም። ህዝቡም የትኛው ፓርቲ መቼና በየትኛው ሚዲያ ያቀርባል የሚለው መረጃ በአግባቡ አለው ብዬ አላምንም። ህብረተሰቡ ፓርቲዎችን የሚያውቅበት እድል ካልተፈጠረለት ወደተሳሳተ ድምዳሜ ሊደርስ ይችላል። ይሄ ትልቅ ሃላፊነት በመሆኑ የሚመለከተው አካል አፋጣኝ ስራ መስራት አለበት።
አዲስ ዘመን፡- በፖለቲካ ክርክር ሂደት በሁሉም ጉዳይ ከተፎካካሪው ጋር ተቃራኒ ሆኖ መገኘት ምን ያህል አዋጭ ነው ብለው ያምናሉ? በተለይም በኢትዮጵያ ፓርቲዎች በጋራ ተቀናጅተው ለአገር እድገት ከመስራት ይልቅ የጠላትነትና የባላጋራ ስሜት ያላቸው መሆኑ በምህዳሩ ላይ ያሳደረው ጫና ምንድን ነው?
አቶ ሲሳይ፡– እንዳልሽው በእኛ አገር ያለው የፓርቲዎች የግንኙነት ልምድ የሚያሳየው ባለጋራ ወይም በጠላትነት ላይ የተመሰረተ ነው። ይህንን አስተሳሰብ ከስሩ ለመንቀል አርቆ አሳቢ መሆንን ይጠይቃል። አንድ አገርን ለመምራት የተዘጋጀ የፖለቲካ ድርጅት ቶሎ ስልጣን ለመቆናጠጥ ሲል የተፎካካሪውን አማራጭ ሃሳብ ሁሉ በማጣጣል ላይ የተመሰረተ አካሄድ ሊከተል አይገባም። ስልጣን ላይ የሚቀመጠውን የሚወዱትን ወይም የመረጡትን ሰዎች ብቻ ለማገልገል አይደለም። ይልቁኑ ሁሉንም ህብረተሰብ በቀናነትና በፍትሃዊነት የመምራት እድል መስጠት ይገባዋል።
ከዚህ አንፃር እሱ ያላየው ግን ደግሞ ለሀገርና ለህዝብ የሚጠቅመውን ሃሳብ ከማጠልሸትና ከማጥላላት ይልቅ ተቀራርቦ ለመስራት ልቡንም በሩንም ክፍት ሊያደርግ ይገባል። እስከዛሬ የተኬደበት የመጠላለፍ አካሄድ እንዳልጠቀመን እሙን ነው። ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ሃላፊነት ሊሰማው ይገባል። ስሜታዊ ከሆነ ድርጅቱንም ሀገሪቱንም ነው ይዞ የሚወድቀው። የፖለቲከኞች በሽታ ለማዳመጥም ሆነ እውነታውን ለመረዳት ፍቃደኛ ያለመሆናቸው ነው።
ይህ ደግሞ እነሱንም ሆነ ሀገርን አይጠቅምም። ይህ የፅንፈኝነት መስመር ከራሳቸው አልፎ ህዝብ ጋር የሚጋባበት ሁኔታ በተጨባጭ አይተናል። በመሆኑም እነዚህ ፓርቲዎች ከምንም በላይ ህዝብና ሀገርን ሊያስቀድሙ ይገባል። በጥላቻ ላይ ተመስርተን የምናካሂደው የፖለቲካ አካሄድ ሁላችንንም ገደል ነው ይዞን የሚገባው። በዚያ መልክ በሃሰት የተነዳ ህብረተሰብ የእነዚያ ሰዎች መጠቀሚያ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ላለፉት 27 ዓመታት ሲሰራበት የቆየው የጥላቻ ፖለቲካ በምን መልኩ ሊቀረፍ ይችላል ብለው ያምናሉ?
አቶ ሲሳይ፡– እንዳልሽው ይህ የጥላቻ ፖለቲካ ለዓመታት የተሰራበት እንደመሆኑ በቀላሉ ከማህበረሰቡ ይወጣል ማለት ከባድ ነው። ትውልዱ በዘረኝነት፣ በፅንፈኝነት፣ የተንሻፈፈ የፖለቲካ አስተሳሰብ እንዲታወር ተደርጓል። ከዚያ አስተሳሰብ ይህን ትውልድ ለማውጣት ብርቱ ትግል ይጠይቃል። ይህንን ችግር ለመቅረፍና ምህዳሩን ለማስፋት ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ እየተደረገ ያለው ጥረት በመልካምነት የሚወሰድ ነው። ሰሞኑን ምርጫ ቦርድ ዱባይ የሚታተመውን የምርጫ ካርድ ለተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማሳየቱ ይህ በጥርጣሬና በጥላቻ ላይ የተመሰረተውን ግንኙነት ለማሻሻል በጎ ጅምር ነው ባይ ነኝ። ነገር ግን ተከታታይነት ያለው የማስተማርና ትውልዱን የማነፅ ስራ መስራት ይጠይቃል። መንግስት ሚዲያውን በመጠቀም ሚዛናዊ አስተሳሰቦች አንዲንሸራሸሩ በማድረግና በማቅረብ አስተሳሰቡን መቅረፅና አመኔታን መፍጠር ይገባዋል። በዚህ መልኩ ህብረተሰቡን ካላገዝነው በአቅራቢያው ለሚያገኛቸው ፅንፈኛ ፖለቲከኞች መሳሪያ ነው የምናደርገው።
አዲስ ዘመን፡- እንደሀገር የህዝቡን አብሮነት ሊያጠናክሩ የሚችሉ ነገሮችን በምን መልኩ ማሳደግ ይገባል?
አቶ ሲሳይ፡- የመጀመሪያው ነገር አንድ የጋራ አገር አለን ብለን ማሰብ ስንችል ነው አብሮነታችን ሊጠናከር የሚችለው። ዝንጀሮዋ ‹‹መጀመሪያ መቀመጪያዬን›› እንዳለችው ሀገራችንን ማስቀደም ይገባናል ። አንድ የጋራ ሀገር አለን ብለን ካሰብን የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በቀላሉ እንፈታቸዋለን። ምከንያቱም የጋራ የሆነችውን ሀገራችንን እንድትፈርስ ማንኛችንም የማንፈልግ በመሆኑ ነው። እስከዛሬ በነበረው ታሪካችንም መንግስታት እርስበርስ ቢጣሉም የአገር ህልውናን የሚጋፋ ነገር ሲመጣ ሁላችንም አንድ ሆነን ነው የምንመክተው።
ይህ ትልቁና ልናስቀጥለው የሚገባን እሴታችን ነው። አባቶቻችን ሀገርን እንደጋራ ቤታቸው ባይቆጥሩና ባይዋደቁላት ኖሮ ዛሬ ይህችን ሀገር ባላገኘናት ነበር። ለዚህ ደግሞ አድዋ ትልቅ ምሳሌ ነው። ምኒሊክ ብቻቸውን አይደለም እኮ ጣሊያንን ያሸነፉት፤ ከደቡብ እስከ ሰሜን ፤ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ የተከተሏቸው የአካባቢ ገዢዎች ሳይቀሩ ልዩነታቸውን ወደጎን ትተው በአንድ ኢትዮጵያዊነት ስሜት ተሰልፈው የውጭውን ጠላት ድል ነስተዋል። በመሆኑም ባህላችን ተሳስቦ የመኖር ነው፣ የተሳሰረው ባህላችንና ኑራችን እንኳን ለሌላው የሚተርፍ ነው። ይህንን ወርቃማ እሴት ጊዜ አመጣሽ በሆነ ዘረኝነትና ፅንፈኝነት ልንቀይረውና ልናጣው አይገባም። አንዴ ካጣነው የማንወጣው አዘቅት ውስጥ ነው የምንገባው።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ሲሳይ፡- እኔም የዘመን እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ ከልብ አመስግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ግንቦት 14/2013