የዛሬ ወር አካባቢ የትግራይ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ በቅርቡ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የክልሉ ቀጣይ የእርሻ ስራ የሁሉንም አካላት ትልቅ ትኩረትና አስቸኳይ እገዛ እንደሚፈልግ መጥቀሳቸውን አስታውሳለሁ። አርሶ አደሩ በአሁኑ ወቅት ማረስና መዝራት ካልቻለ እስከ ሚቀጥሉት አራትና አምስት አመታት የሚዘልቅ ትልቅ ችግር ውስጥ እንወድቃለን ሲሉ አስገንዝበውም ነበር።
በተረጋጉ የክልሉ አካባቢዎች የእርሻ ስራ መጀመሩን ጠቅሰው ፣የማዳበሪያና ምርጥ ዘር እጥረት መከሰቱን በወቅቱ ተናግረዋል። የክልሉ የግብርና መዋቅር መፍረሱን በመግለጽም ፣ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር፣የእርሻ መሳሪያ የግብርናውን ስራ ለማስጀመር ወሳኝ መሆናቸውን መግለጻቸው የሚታወስ ነው። ከዚያ ቀደም ሲልም በትግራይ ክልል አጠቃላይ ሁኔታ ላይ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉ አንድ የክልሉ ተወላጅ ሰውም እንዲሁ መንግስት ለትግራይ ህዝብ የተለየ ስራ በመስራት ከትህነግ የተሻለ መሆኑን ማሳየት አለበት ያሉበትን ሁኔታም አስታውሳለሁ።
ሰሞኑን መንግስት ከትግራይ ክልል በቀረበው ጥያቄ ልክ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ማቅረብ መጀመሩ የክልሉ እርሻ ስራ ላይ ተደቅኖ የነበረው ስጋት በማስወገድ በኩል ትልቅ ትረጉም ይኖረዋል። ትልቅ እርምጃ ተብሎ ሊወሰድ የሚገባውም ነው። የግብርና ግብአት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለቆየው የትግራይ አርሶ አደር ብቻ ሳይሆን ለተቀረውም ወሳኝ እንደመሆኑ፣ መንግስት ከትግራይ ክልል ለቀረበው አስቸኳይ ጥሪ የወሰደው አስቸኳይ እርምጃ ክልሉን መልሶ ለማቋቋም ያለው ቁርጠኝነት በድጋሚ በተግባር ያረጋገጠበት ነው። ግብአቱ በወቅቱና በሚፈለገው ልክ ቀርቧል። በመሆኑም የእርሻ ስራው ሳይስተጓጎል እንዲያውም የበለጠ ምርታማ ሊሆን በሚችል መልኩ እንዲቀጥል ለማድረግ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው።
ከግብርና ሚኒስቴር የወጣ መረጃ እንደሚያ መለክተው፤ ክልሉ የግብርና ስራ ያስፈልጋል በሚል የቀረበውን የአፈር ማዳበሪያ መጠን መቶ በመቶ እንዲሁም ምርጥ ዘር መጠን ደግሞ ከሚፈለገው በላይ ማቅረብ ተጀምሯል። የክልሉ የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት 800 ሺ ኩንታል ሲሆን፣ መቶ በመቶ የቀረበው ጥያቄ እንዲመለስ ተደርጓል። በምርጥ ዘር በኩል ፍላጎቱ 23 ሺ221 ኩንታል ቢሆንም፣ ከቀረበው ጥያቄ በላይ 30 ሺ 800 ኩንታል እንደሚቀርብ ተገልጸል። ከዚህ ውስጥ 30 ሺ ኩንታሉን የተለያዩ ድርጅቶች ለማቅረብ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር እየተነጋገሩ ይገኛሉ።
አንድ ሰኔ የገደለውን አስር ሰኔ አያነሳውም በሚባልባት ሀገር የክልሉ ግብርና ዘንድሮ ጉዳት ቢደርስበት ለማገገም ግብርና ቢሮው እንዳለው በርካታ አመታትን ይጠይቅ ነበር። ይህ አቅርቦት በክልሉ ግብርና ስራ ላይ ተደቅኖ የነበረውን ስጋት በወሳኝ መልኩ ይፈታዋል። ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ አቅርቦት ነው። በተለያዩ ውስንነቶች ሳቢያ እስከ አሁን በዚህ ልክ ለክልሎች የማዳበሪያም ሆነ የምርጥ ዘር ቀርቦ ያውቃል ብዬ እኔ በበኩሌ አልገምትም። ይሄ ጎደለ ያ አነሰ ሲባል ከዜና ማሰራጫዎች ይሰማ የነበረው መረጃም አቅርቦቱ አይደለም ከተጠየቀው በላይ ሊሆን ከመቶ በመቶ ያነሰም ሊሆን እንደሚችል ያስጠረጥራል።
አሁን ለትግራይ ክልል የቀረበው የግብአት መጠን ክልሉ በአስቸኳይ እንዲቀርብ ከጠየቃቸው ለግብርናው ዘርፍ የሚያስፈልጉ ነገሮች ወሳኞቹ ናቸውና መንግስት በተጠየቀው መሰረት በአስቸኳይ ማቅረቡ ክልሉን መልሶ ለመገንባት የገባው ቃል አንድ ትልቅ ማሳያ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። በተለያዩ ወገኖች ለመንግስት ሲቀርብ ለነበረው ጥያቄም መልስ የሚሰጥ ነው ። ቀጣዩ እርምጃ ይህን ግብአት በፍጥነት አጓጉዞ አርሶ አደሩ እጅ እንዲደርስ ማድረግ መሆን ይኖርበታል። ማዳበሪያውን ከወደብ ወደ ክልሉ የማጓጓዙ ስራ እየተካሄደ ሲሆን ፣ ይህን ተቀብሎ በቀጥታ አርሶ አደሩ ቀዬ ማድረስ ቀጣዩ ትልቅ ርብርብ የሚጠይቅ ስራ ነው። በምርጥ ዘር ማጓጓዝ በኩልም ተመሳሳይ እርምጃ ሊወሰድ ግድ ይላል። በዚህ በኩል የሚመለካቸው አካላት ሁሉ በንቃት መሳተፍ ይኖርባቸዋል።
የግብአት አቅርቦቱ ግብርናውን መታደግ ብቻም ሳይሆን በሚገባ ከተሰራበት እስከ አሁን ታይቶ የማይታወቅ ለውጥ ያመጣበታል ብዩም አስባለሁ። ይህ እንዲሆን ግን አሁንም ትኩረት ተሰጥቷቸው መሰራት ያለባቸው ነገሮች አሉ። እንደሚታወቀው የጁንታውን መወገድ ተከትሎ በክልሉ የመንግስት መዋቅር ፈርሶ ነበር፤ የፌዴራል መንግስት ወዲያው በክልሉ አዲስ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም አድርጓል። መሀል ላይ ተፈጥሮ በነበረው ክፍተት ሳቢያ መንግስታዊ ስራዎች ተስተጓጉለው ነበር። በዚህ ክፍተት የተነሳ ከተሞች ብቻ ሳይሆኑ ገጠሩም አሉታዊ ተጽእኖ ሊደርስበት እንደሚችል ማንም ይረዳዋል። መንግስት አዲስ ጊዜያዊ አስተዳደር መመሰረቱን ተከትሎ ችግሩ እየተፈታ የመጣ ቢሆንም ግብርናውን ለመታደግ አሁንም ጠንከራ ስራ መስራትን ይጠይቃል።
ጁንታው ሲደመሰስ የተወሰኑት አውራዎችና ርዝራዦች የተሸሸጉት ወደ አርሶ አደሩ ቀዬ መሆኑ ይታወቃል። የተደመሰሱት ተደምሰሰው ፣ሌሎች ደግሞ በቁጥጥር ስር ቢውሉም አሁንም እንዳንዶቹ በዚያው በሽፍትነት ላይ ሆነው የጸጥታ ችግር እየሆኑ ይገኛሉ። እነዚህ ሀይሎች የጥፋት ሀይሎች እንደመሆናቸው አርሶ አደሩ ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራቱን ላይወዱት ይችላሉ። የብዙ ነገሮች የደም ስር የሆነውን ኤሌክትሪክ በተደጋጋሚ ያወደሙ እዚህ ላይ እጃቸው ይሰበሰባል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። ልማቱ በሚፈለገው ልክ እንዳይሄድም የሞት ሽረት ትግል ከማድረግ እንደማይቆጠቡ መገመት አይከብድም። ምክንያቱም ልማት ተሳለጠ ማለት ኮሽታ አይኖርም ማለት ነው። ጭር ሲል ለማይወዱት ለእነዚህ የጥፋት ሐይሎች የግብአት አቅርቦቱ ጥሩ ዜና ይሆናል ብዬ አልወስድም። ከሰላምና መረጋጋት፣ ወንጀለኞችን አድኖ ከመያዝ የአርሶ አደሩን አመለካከት ከመቀየር አኳያ አሁንም መጠነ ሰፊ ስራዎችን መስራት ያስፈልጋል ።
ሌላው ሊታብበት የሚገባው ጉዳይ ጁንታው የፈጠረው አለመረጋጋት አርሶ አደሩንም በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጎዳው መገመት ይቻላል። ከዚህ ጉዳት አገግሞ በቀረበለት ግብአት በመጠቀም የግብርና ስራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ ላይም ሌላ ትልቅ ስራ መስራትን ይጠይቃል። የግብርና ባለሙያዎች፣ የግብርና ቢሮና ሚኒስቴሩ፣ ህብረት ስራ ማህበራት፣ የግብርና ምርምር ተቋማት የዘንድሮው ስራቸው ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰፊ መሆኑን መረዳት ይኖርባቸዋል። መንግስት ይህን ያህል ግብአት ሲያቀርብ እናንተም ከድርሻችሁ በላይ በመስራት ግብርናውን መታደግ ብቻ ሳይሆን ከእስከ አሁኑም ለውጥ እንዲመጣበት አድርጋችሁ ልትሰሩ በሚገባችሁ ወቅት ላይ ናችሁ።
በአንድ ወቅት የግብርና ቢሮው ባቀረበው ጥሪ መሰረት የትግራይ ግብርና እና አርሶ አደር መንግስት ሊያቀርብ ከሚችለው በላይ ድጋፍ እንደሚፈልጉ ማስታወቃቸው ይታወሳል። ባለሀብቶች ለጋሾች እና ሌሎች በግብርና ላይ የምትሰሩ ሁሉ ድጋፉን የማድረጊያው ጊዜ ዛሬ መሆኑን ማወቅ አለባችሁ። ለግብርናው ዘርፍ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት ሙያዊና የፋይናንስ ድጋፋቸው በዚህ ላይ ማጠናከርም ይጠበቅባቸዋል። የተለያዩ ድርጅቶ 30 ሺ ኩንታል ምርጥ ዘር ለማቅረብ ቃል የገቡበት ሁኔታም አለ። ይህ አይነቱ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። እነዚህ ሁሉ ስራዎች በአግባቡ ከተከናወኑ የቀረበው ግብአት የክልሉን ግብርና ከተጋረጠበት ችግር የሚያወጣ ብቻም ሳይሆን በክልሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር የሚያስችል እንደሚሆን መገመት ይቻላል።
ዘካርያስ ዶቢ
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2013