ልጆች የተስተካከለ ህይወት እንዲኖራቸውና ስኬታማ እንዲሆኑ በቂ የህይወት ክህሎት መያዝ እንዳለባቸው ይነገራል። የህይወት ክህሎትን ከሚማሩበትና ከሚያዳብሩበት ቦታዎች መካከል ደግሞ ቤተሰብ ቀዳሚው ነው። ለመሆኑ ልጆች ከቤተሰባቸው በቂ የህይወት ክህሎት እንዴት ሊያገኙ ይችላሉ ስንል በኢምፓክት ኢትዮጵያ የስነልቦና አገልግሎቶችና የማህበረሰብ ጤና ማማከር ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ከሆኑት ከአቶ አለማየሁ ጥበበ ሙላቱ ጋር ቆይታ አድርገናል።
ባለሙያው እንደሚያብራሩት የህይወት ክህሎት ማለት ሰዎች በእለት ከእለት ኑሯቸው የሚያጋጥሟቸውን ኃላፊነቶችና ፈተናዎች በብቃት ለመወጣት የሚያስፈልጓቸው አቅሞችና ብቃቶች ማለት ናቸው። ከነዚህም መካከል ችግርን የመፍታት ክህሎት፤ ነገሮችን በጥልቀት የመመርመር ከህሎት፤ ራስን የመገንዘብና የማወቅ ክህሎት፤ የተግባቦት ክህሎት፤ ጭንቀትን የመቋቋምና በዛም ወስጥ ሆኖ ውሳኔ የመስጠት ክህሎት እንዲሁም ስሜትን በተገቢው መንገድ የመግለጽና ራስን በሌሎች ቦታ አስቀምጦ የማሰብና ነገሮችን የመመልከት ይጠቀሳሉ።
የህይወት ክህሎት ከሁሉም ወቅት በላይ የሚያስፈልገው በወጣትነት እድሜ ሲሆን የህይወት ክህሎት ልጆች የተስተካከለና ጠንካራ ስነልቦና እንዲኖራቸው፤ በማህበረሰቡ ተቀባይነት ያለው መልካም ከሰዎች ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩ ነገሮችን በማመዛዘን እንዲመለከቱ ብሎም በየትኛውም ሁኔታ ወስጥ ሆነው ችግሮችን ለመፍታትና ውሳኔ ለመወሰን የሚያስችል አቅም እንዲፈጥሩ የሚያበቃቸውም ነው። እነዚህን ነገሮች ማድረጋቸው ህይወታቸው ቀና እንዲሆን ባጠቃላይ ደስተኛና ለራሳቸው ትልቅ ግምት የሚሰጡ በቤተሰብና በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው እንዲሆኑ ያስችላቸዋል።
በተጨማሪ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ወስጥ ሲሆኑም የግል ጥረትን በመጠቀም አካባቢያቸውን ጤናማና ምቹ ለማደረግ እንዲችሉ ብቁ የሚያደርጋቸው ይሆናል። ባጠቃላይም ወደ ችግር እንዳይገቡ ብቻ ለመጠበቅ ብቻ ሳይሆን ምናልባትም ከገቡ በራሳቸው ጥረት በቀላሉ ለችግሩ ለመገላገል የሚያስችላቸው ይሆናል።
በአንጻሩ በቂ የህይወት ክህሎት ያላዳበሩ ያልጨበጡ ወጣቶች ከቤተሰብ ድጋፍ ውጪ የሚገጥሟቸውን ችግሮች በሙሉ የመሻገርም ሆነ የመቋቋም አቅማቸው ደካማ ይሆናል። ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰባቸውንና ማህበረሰቡን ለችግር የሚያጋልጡ ግብታዊ ውሳኔዎችን የሚወስኑ ይሆናሉ። ሥራ ፈጣሪ ያለመሆን። ለሚገጥሟቸው ችግሮች በቀላሉ የመንበርከክና ለአቻ ተጽእኖ ተጋላጭ መሆንም ይታይባቸዋል። ይህም በመሆኑ ለበርካታ ችግሮች የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ ሲሆን አንዳንድ ግዜ እስከ ህይወታቸው መጨረሻ አብረዋቸው ለሚዘልቁ ለጭንቀት፣ ለደባል ሱስና ሌሎች ችግሮችም ተጋላጭ ይሆናሉ። በመሆኑም ልጆች በቤተሰብ ወስጥ እያሉ ውሳኔ እየሰጡ ውሳኔ መስጠትን፤ ኃላፊነት እየወሰዱ ኃላፊነት መውሰድን፤ በችግር ወስጥ እያለፉ ችግር መቋቋምን ሊማሩ ይገባል።
የህይወት ክህሎትን በተለያየ መንገድ መማር የሚቻል ቢሆንም እንደ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ግን እነዚህ ክህሎቶች ልጆች በዋናነት ሊይዟቸውና ሊያዳብሯቸው የሚችሉት በቤተሰብ ውስጥ ባሉበት ወቅት ነው። የትምህርት አላማ በእውቀት በክህሎትና በአመለካከት ትውልድን ለመቅረጽ ነው።
ከእነዚህ መካከል የልጆች አመለካከት የሚቀረጸው ደግሞ በሚኖራቸው የህይወት ክህሎት ብቃት የሚወሰን ይሆናል። ነገር ግን ከመደበኛው የትምህርት ስርዓት ጋር ተቀናጅቶ የማይሰጥ በመሆኑ ልጆች እነዚህን ነገሮች ሊያገኙ የሚችሉት በጣም በተወሰነ ደረጃ እንደ ሚኒ ሚድያና በሌሎች የተለያዩ ክበባት ባሉ ኢ-መደበኛ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ነው።
ልጆች እነዚሀን የህይወት ክህሎቶች ሊጨብጣቸውና ሊያዳብሯቸው የሚገባው ደግሞ ገና በልጅነት እድሚያቸው ጀምሮ ነው። ለምሳሌ ቤተሰብ ወስጥ እያሉ በየደረጃው በሚደረግ ውይይት ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ የማይስማሙበትን የመቃውም ልምዳቸውን ያዳብራሉ፤ በልጅነታቸው ከእኩዮቻቸው ጋር ሲጣሉ እንዴት መስማማት እንዳለባቸው እንዴት ግጭቶችን መፍታትእንደሚኖርባቸው ያስባሉ።
በዚህ ሁኔታ ቆይተው ከጊዜ በኋላ ጉርምስና ሲመጣ ጓደኛ መያዝ ሲጀምሩ የሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች ይኖራሉ። እነዚህን ተግዳሮቶች ለመቋቋም የሚያስችላቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ ሲያካብቱት የኖሩት አእምሯዊም አካላዊም የህይወት ክህሎቶች ናቸው። ይሄ ሳይሆን ቀርቶ ልጆች ችግር ሲገጥማቸው እንደ ትምህርት በአንድ ወቅት አቅም አንዲኖራቸው ለማስቻል መሞከር ውጤታማ አያደርግም።
በመሆኑም ቤተሰብ ለልጆች ፍቅርን በመስጠት ስለፍቅርና ስለርህራሄ እንዲያውቁ ማስቻል፤ ሥራን እየሰሩ አሰርተው የሥራ ባህላቸው እንዲዳብር በማድረግ፤ እያንዳንዱ ቤተሰብ ልጆቼን እንዴት ላሳድግ ብሎ በሚይዘው ፍልስፍና ውስጥ ሊካተት ይገባል። ይህ ማለት ግን ቤተሰብ ልጆችን ካለ አቅማቸው ሁሉንም ነገር ራሳቸው ይወጡት ብሎ መልቀቅ ሳይሆን ሀሳባቸውን በመቀበል ችግሮች ሲያጋጥሟቸው አብሮ በመሆን የጋራ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በማድረግ በአብሮነት መምራት ማለት ነው።
ይህንንም ለማለፍ መጀመሪያው ለልጆች ግዜ መስጠት፤ እድሚያቸው በሚፈቅደው መሰረት ኃላፊነት እንዲወስዱ ማድረግ፤ ለወሰዱት ኃላፊነት ተጠያቂነት እንዳለባቸው ማስገንዘብ፤ በዚህም ከተጠያቂነት ራሳቸውን እንዲያሸሹ ሳይሆን ለሚፈጠሩ ችግሮች፣ ለሚከሰቱ ስህተቶች ራሳቸው ኃላፊነት ለመውሰድ እንዲዘጋጁ ማብቃት ይጠበቃል።
ልጆች የጉርምስና እድሜ ላይ ሲደርሱ በርካታ የህይወት ምርጫዎች ስለሚገጥሟቸው የበቃ ውሳኔ ሰጪነት ክህሎት ያስፈልጋቸዋል። ለዚህ ዝግጁ ሆነው ያደጉ ካልሆኑ የሚጎዳቸውን ውሳኔ ሊወሰኑ አልያም መወሰን ተስኗቸው በእነሱ ህይወት የሌሎች ጣልቃ ገብነት እንዲከሰት በር የሚከፍቱና ተገቢ ያልሆነ ቦታ እንዲገኙ ይዳርጋቸዋል። ስለዚህ ገና በልጅነት በለጋ እድሚያቸው እነሱን በሚመለከቱ ለምሳሌ የትምህርት ፍላጎታቸውን በተመለከተ፣ መሆን የሚፈልጉትን ለመምረጥና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ እየተሳተፉ ምክንያታዊ የሆነ ውሳኔ እየወሰኑ እንዲመጡ ማለማመድና ማብቃት ይጠበቃል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሚገጥሟቸው ችግሮችም ስለሚኖሩ ራሳቸውን አዘጋጅተው በተረጋጋ መንፈስ የሚገጥሟቸውን መሰናክሎች የሚያልፉበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹ ማብቃት ይጠበቃል።ከላይ የተዘረዘሩት ነገሮች እንደተጠበቁ ሆነው ልጆችን ጥሩ የህይወት ክህሎት እንዲኖራቸው ለማብቃት ቤተሰብ በሚያሳድግበት ወቅት ማድረግ የሚችሉትንና የማይችሉትን እንዲሁም ማድረግ ያለባቸውንና የሌለባቸውን በመለየት ገደብ ሊያስቀምጡላቸው ይገባል።
ማንኛውም የሰው ልጅ በየትኛውም ሁኔታና ቦታ ቢሆን ማድረግ ያለበትንና የሌለበትን ለዛ ጉዳይ ያለውን አቅም ጠንቅቆ ማወቅ አለበት። በተመሳሳይ ልጆችም ምን ማድረግ አለብኝ ይህንንስ ለማድረግ ምን ያህል አቅም አለኝ የሚለውን እንዲለዩ ማስቻል ይጠበቃል። ካልሆነ ሌሎች ስላደረጉት አልያም እነሱ ስለፈለጉት ብቻ ከአቅማቸው በላይ የሆነና የማይገባቸውን ነገር ለማድረግ ሞክረው ለሞራልና ሌሎች ውድቀቶች ሊዳረጉ ይችላሉ።
በሌላ በኩል ቤተሰብ በየወቅቱ የሚለዋወጥ ደረጃና ሀሳብ ለልጆች ማስቀመጥ የለበትም። አንድ ቤተሰብ ዛሬ እንዲህ አታድርግ ያለውን ልጅ ነገ እንዲያደርግ ከፈቀደለት፤ አልያም ዛሬ እንዲህ ብትሆን ይጠቅምሀል ያለውን የመከረውን ነገ ይሄ ነገር ችግር አለው ብሎ የሚያፈርሰው ከሆነ ልጆች በወጥነት የሚይዙት ሀሳብ አላማና አካሄድ እንዳይኖራቸው ያደርጋል። በመሆኑም በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ እየተከተሉ ይህን አታርጉ እንዲህ አትሁኑ ሳይሆን ማለት ያለብን የማያደርጉበትን፤ የማይሄዱበትን፤ የማይሆኑበትን ምክንያት በመንገር ጥርት ያለ ራእይና የህይወት ግብ እንዲኖራቸው ማብቃት ነው። ይህም ለችግር የሚያጋልጣቸው ከጓደኞቻቸው የሚያገላቸው ነገር ግን የማይጠቅማቸው ሁኔታዎች በሚገጥሟቸው ወቅት ውሳኔያቸው የሚሆነው አለመቀበል መቃወም ይሆናል።
አንድ ልጅ በቤተሰብ ወስጥ እያለ በሚያሳልፋቸው ግዜያት እንዴት ውስኔ መስጠት እንደሚችል ካወቀ፤ እንዴት ችግሮችን መፍታት እንደሚኖርበት ከተረዳ፤ እንዲሁም በተለያዩ ጉዳዮች ከሚገጥሙት የተለያየ ማንነት ካላቸው ሰዎች ጋር ግንኙነቱን በምን አይነት መልኩ ማድረግ እንዳለበት ከተገነዘበ በወጣትነት እድሜው ለችግር የመጋለጥ እድሉ ጠባብ ይሆናል። ስለዚህ ቤተሰቦች ልጆች ራሳቸውን እንዲያውቁ ራሳቸውን እንዲገነዘቡ የማድረግ ሥራ መስራት ያለባቸው ገና በልጅነታቸው ጀምሮ መሆኑን መገንዘብ ይጠበቃል። በአንጻሩ ለከት ባለው መልኩ ከሰው ጋር እንዲግባቡ የአካባቢውን ማህበረሰብ ኑሮ እንዲጋሩ ማድረግም ይጠበቃል።
ለዚህም አንደኛ የልጆችን ሃሳብ ለመስማት ፈቃደኛ መሆን፤ ድክመትም ሆነ ችግር ሲገጥማቸው ሞራላቸውን በጠበቀ መልኩ እንዲሻገሩት ለማብቃት መስራት፤ በቤተሰብ ውስጥ በእናትና አባት አላስፈላጊ መሳሳብ እንዳይኖር ማድረግ ይገባል። በሁለቱ ወላጆች መካከል አንድነት ከሌለና መሳሳብ ካለ ልጆች ሌሎች አማራጮችን እንዲያማትሩ በር የሚከፍት ይሆናል። ይህ ካልሆነ ግን ከቤተሰብ ያጡትን ድጋፍ ከቤተሰብ ያጡትን ሞራልና እንክብካቤ ለማግኘት ለጎረቤት ለጓደኛና ለሌሎችም ሚድያን ጨምሮ ጆሯቸውንም ልባቸውንም መስጠት ይጀምራሉ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ወላጆች ለልጆች የአፍ ብቻ ሳይሆን የተግባርም መምህር አርአያ ሊሆኑ ይገባል። ልጅን ጠንካራ ሰራተኛ አንዲሆን የሚመክር ቤተሰብ ስለ ሥራ የሚኖረው አመለካከትና ተግባር ጠንካራ መሆን አለበት፤ በስነ ምግባር ረገድም ሲጋራ የሚያጨሱ፣ መጠጥ የሚጠጡ፣ ጫት የሚቅሙ ወላጆች ልጆቻቸውን ይህን አታድርጉ ብቻ ሳይሆን ከእነዚህ ነገሮችም ተቆጥበው ራሳቸውን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።
ልጆችን እርስ በእርስ ተዋደዱ፣ ለሰው ክብር ስጡ የሚል ቤተሰብ መሪ የሆኑ እናትና አባትም እነሱ ተዋደው እነሱ ተከባብረው እየተደጋገፉና እየተመካከሩ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። ልጆች ሊኖራቸው ከሚገባ የህይወት ከህሎት መካከል የሚኖሩበትን አካባቢ የኑሮ ደረጃ ያሉበትን ሁኔታ ሌሎችም በአካባቢያቸው ስላሉ ሁኔታዎች ግንዛቤ እንዲኖራቸውና እንዲቀበሉትም ማድረግ ይጠበቃል። ይህን ማድረጉ የሚጠቅመው ባሉበት ሁኔታ እንዲቀጥሉ ለማድረግ ሳይሆን ያሉበትን ሁኔታ አምነው ተቀብለው ለመሻሻል ለመለወጥ እንዲንቀሳቀሱ በር ስለሚከፍትላቸው ነው።
በሌላ በኩል ወላጆች ልጆችን ትምህርት ቤት መላካቸው ብቻውን የህይወት ከህሎት ሊያስጨብጣቸው እንደማይችል ሊገነዘቡ ይገባል። ከትምህርት ቤት የሚገኝ እውቀት በአብዛኛው መረጃንና የአንድን ዘርፍ ሞያ መሰረት ያደረገ ነው። ይህ ደግሞ ለዛ ውሱን ጉዳይ በተለይ በሥራ ዓለም ብቻ የሚጠቅማቸው መሆኑን መገንዘብ፤ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለሥራ የሚሰጡት ክብር እንዲበላሽ የሚደረግበት አካሄድ ማስወገድ ልጆች በዩኒቨርሲቲ እያሉ ራሳቸው ልብሳቸውን አንዲያጥቡ፣ ቁጠባ እንዲማሩ ማድረግ ይጠበቃል።
አንዳንድ ቤተሰብ ልጆቹን ዩኒቨርሲቲ ሲልክ ተመርቀው ወጥተው ሥራ ሲያገኙ ሊከፈላቸው ከሚችለው በላይ ገንዘብ እየሰጣቸው ይቆይና ተመርቀው ከወጡ በኋላ ስለ ስራም ሆነ ስለሚያገኙት ገቢ የሚኖራቸው እይታ የተንሸዋረረ እንዲሆን ያደርገዋል። ቤተሰብ ሥራ ሊፈጥርላቸው ሲፈልግ የቤተሰብ አቅምንና ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ከማስገባት ይልቅ ለራሳቸው ፍላጎትና ለሌሎች ተጽእኖ በር በመክፈት ሥራ ማማረጥ በአጭር መንገድ ለመበልጸግ ይሞክራሉ።
በተመሳሳይ ወጣቶች ከቤተሰብ አልፎ መንግሥት እያደራጀ ሥራ ለመፍጠር የሚያደርገው ጉዞ በአንዳንድ ቦታዎች ውጤታማ የማይሆነው ወጣቶች በቂ የህይወት ክህሎት ባለመጨበጣቸው ነው። ስራውንም ለመስራት ትንሽ እንቅፋት ሲገጥማቸው በራሳቸው አቅም ትግል ለማለፍ ከመሞከር ይልቅ አማራጭ የሚያደርጉት ማቆም፤ የሌሎችን እርዳታ መፈለግ እየሆነ ይመጣል። ልጆች በቂ የህይወት ክህሎት ሲጨብጡ ከማማረር ይልቅ ለመማር ዝግጁ ይሆናሉ። በእያንዳንዷ ስራቸው ደግሞ ማበረታታትና ገንቢ ሀሳብ መስጠትም ይጠበቃል።
በአብዛኛው ወጣቶች ትዳር ሲመሰርቱ ይዘው የሚገቡት በቤተሰባቸው ውስጥ የነበረውን ባህሪና የኑሮ ዘይቤ ነው። ሁለቱም ጥንዶች የሚመጡት ደግሞ ከተለያየ ቤተሰብ በመሆኑ በአንድ ግዜ ተስማምቶ ሁሉንም ነገሮች የማድረጉ ነገር ሊፈጠር አይችልም። በመሆኑም ትእግስትና መቻቻል የሚሉትን ነገሮች በትልቁ ይዘው እንዲገቡ ማድረግ ይጠበቃል።
ሰዎችን ውጤታማ፤ ጤናማና ስኬታማ የሚያደርጋቸው ምስጢር ምንድን ነው የሚለውን ለመለየት የተሰራ ግራንድ ስተዲዮ የሚባልና ለሰባ ስደስት ዓመታት ያህል የተሠራ ጥናት አለ። ጥናቱ በሰባ ሰድስተኛ ዓመቱ ያስገኘው ወጤት የሚያሳየው ሰዎች ትዳራቸው ውጤታማና ህይወታቸው ስኬታማ እንዲሆን የሚያደርገው ዋናው ነገር ሰዎቹ በልጅነታቸው ከቤተሰባቸው ጋር የነበራቸው መልካም ግንኙነት ነው።
በርካታ ሰዎች በትምህርት፣ በስራ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ የቻሉ ቢሆንም የቅርብ የቤተሰብ ክትትልና ድጋፍ ስላልነበራቸው በህይወታቸው ደስተኛና ስኬታማ አልነበሩም። እነዚህ ሰዎች በአካላዊ ጤንነታቸውም ውጤታማ መሆናቸው በጥናቱ ተመላክቷል። በመሆኑም ለልጆች የተቃና ህይወት ወላጆች ትልቅ ሚና እንዳላቸው በመገንዘብ ልጆቻቸውን አቅርበውና ትኩረት ሰጥተው ሊንከባከቡና ሊጠብቁ ይገባል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2013