የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በህግ ከተሰጡት ተልዕኮዎች መካከል የትምህርት ተቋማትን በፍትሃዊነት ማዳረስና ተገቢ ድጋፍና ክትትል ማድረግ ዋነኛ ተግባሩ ነው። የትምህርት ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ፤ በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ አለማቀፍ ደረጃውን የጠበቀ፣ ብቃትና ጥራቱ የተረጋገጠ አጠቃላይ ትምህርት በተስማሚ ፕሮግራሞች ለከተማዋ ነዋሪ መስጠትም ከተልዕኮዎቹ መካከል ተጠቃሽ ናቸው። ከዚህ አንጻር ቢሮው ከኮቪድ 19 መከላከል፤ ከ12ኛ ክፍል ተፈታኞች፣ ከግል ትምህርት ቤቶች ክፍያ መናር እና ከመምህራን ልማት ጋር በተያያዘ ምን ስራዎችን አከናወነ በሚሉ ጉዳዮች ላይ ከቢሮው ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፦ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በዘንድሮ ዓመት እየተሰጠ የሚገኘውን ትምህርት መቼ ለማጠናቀቅ ታቅዷል?
አቶ ዘለላም፦ የዘንድሮው የትምህርት ጊዜ ከወትሮው በተለየ መልኩ በኮሮና ቫይረስ መከሰት ምክንያት ዘግይተን ነው የጀመርነው። በተለይ አዲስ አበባ ከፍተኛ የበሽታው ተጠቂዎች ቁጥር ያስመዘገበች በመሆኑ እና በሽታው ስጋት የፈጠረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ትምህርት በቶሎ እንዳንጀምር አድርጎናል። እንደሀገርም ቢሆን በኮቪድ 19 ምክንያት ትምህርት ዘግይቶ ቢጀመርም ጥንቃቄዎችን በማድረግ መጀመር ስላለበት ተወስኖ ነው ወደስራ የተገባው። ስንገባ በሽታው እያለ ህይወት ይቀጥላል በሚል እንደሌላው ሴክተር ሁሉ ትምህርትም መቀጠል ይችላል የሚል እምነት ነበረን። በወቅቱ የነበረው የዝግጅት ሥራ ከፍተኛ ጥረት የጠየቀ ነበር።
ወላጅ ልጆቼ ለበሽታው አይጋለጡብኝም ብሎ አምኖ እንዲልክ ለማድረግ እና ከላካቸውም በኋላ ለጥንቃቄው የሚረዱ ግብዓቶችን በትምህርት ቤት ውስጥ ለማሟላት ሰፊ ክንውን ተደርጓል። ትምህርት ቤቶች የኮቪድ 19 መከላከል ስታንዳርድን አሟልተው በደረጃ እንዲከፈቱ በማድረግ ከጥቅምት ወር ጀምሮ በተከታታይ ወራት ሁሉም ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ከፍተኛ ክትትል ተደርጓል፡፡ መማር ማስተማር ከጀመርን በኋላ ለኮሮና ቫይረስ ጥንቃቄ የታከለበት የአፍና አፍንጫ አጠቃቀም እንዲሁም የእጅ ንጽህና እና ርቀትን በማስጠበቅ ረገድ በየዕለቱ ቁጥጥር ይደረጋል። አሁንም ጥንቃቄው ሳይጓደል መማር ማስተማሩን ቀጥለን እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ የዘንድሮውን ትምህርት ዘመን እናጠናቅቃለን ብለን እየሰራን እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፦ በኮቪድ ምክንያት ትምህርት ሲጓተት የተፈጠረውን ክፍተት ለማካካስ የሚያስችል ምን አይነት ሥራ አከናውናችኋል?
አቶ ዘለላም፦ ማንኛውም ትምህርት የእራሱ የሆነ መስፈርት አለው፤ በይዘት፤ በክብደት ምጠና አንጻር መስፈርቱን ለማሟላት ተሞክሯል። የታችኛውን የትምህርት ዕርከን መሸፈን ሳይቻል ወደሚቀጥለው እርከን መሸጋገር አይቻልም። ስለዚህ ሳይሸፈኑ የቀሩ የትምህርት ክፍሎችን በማካካስ ነው ወደቀጣዩ ትምህርት ክፍል እንዲሸጋገሩ ጥረት እየተደረገ ያለው። በ2013 በጀት ዓመት የኮቪድ 19 ወረርሽን መከሰቱን ተከትሎ በትምህርት ዘርፍ ፈታኝ እና ጥንቃቄን መሰረት ያደረገ ትምህርት ለማስጀመርና የተቋረጠውን ትምህርት ለማካካስ ዘርፈ ብዙ የአማራጭ ትምህርት ዘይቤን ተግብረናል።
የትምህርት አመራሩና በየደረጃው ያሉ ባለሙያዎች አማራጭ የማስተማሪያ ስነ ዘዴን በመተግበር ለተማሪዎች ትምህርት እንዲያገኙ ከፍተኛ ሥራ ተከናውኗል፡፡ በኮቪድ ምክንያት የገጽ ለገጽ ትምህርት ሲቋረጥ ትምህርት በቤቴ በሚል መርህ በቴሌቪዥን አማራጮች፣ በማህበራዊ መገናኛዎች እና ቤት ለቤት የትምህርት አማራጮች ተጠቅመን ተማሪዎች ከትምህርት እንዳይርቁ ማድረግ ተችሏል። የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ተከትሎ የትምህርት በቤቴ በሚል መርሐ ግብር ከ1ኛ-12ኛ ክፍል በአራት ተተኳሪ የትምህርት አይነቶች በቴሌቪዥን፤ በሬዲዮ፤ በቴሌግራም፤ የመማር ማስተማር ሂደት ተከናውኗል። በኋላም ወደ ትምህርት ቤቶች ሲመለሱ እያንዳንዱ የትምህርት ክፍል ላይ ድጋሚ በማስተማር የማካካስ ሥራ ተከናውኗል።
በሌላ በኩል ጥግግትን ለመቀነስ በሚል በአንድ ክፍል የሚማሩ ተማሪዎች ቁጥር ወደ25 ዝቅ እንዲል መደረጉ በራሱ በተማሪዎች ላይ የሚፈጥረው መልካም ነገር አለ። መምህሩ እያንዳንዱ ተማሪ ዘንድ እየቀረበ ለማስረዳት እና የማካካስ ስራውን በውጤታማነት ለማከናወን በአንድ ክፍል ያሉ ተማሪዎቹ ቁጥር ማነሱ ወሳኝነት አለው። የተማሪ ክፍል ጥመርታም የትምህርት ጥራት ማረጋገጫ አንዱ መንገድ በመሆኑ ክፍተቶችን ለማሟላት ይረዳል። በእርግጥ ትምህርቱ በፈረቃ መሰጠቱ ከጊዜ አንጻር ጉዳት አለው እንጂ፤ በተቻለ መጠን ያልተሸፈኑ የትምህርት ክፍሎች እንዳይኖሩ ሰፊ ሥራ ተከናውኗል።
አዲስ ዘመን፦ ኮቪድ 19 በትምህርት ስርዓቱ ላይ የተለየ ችግር እንዳያስከትል ምን አይነት የጥንቃቄ ስራዎችን እያከናወናችሁ ነው?
አቶ ዘለላም፦ በኮቪድ 19 ምክንያት የዘገየው ትምህርት መልሶ እንዳይዘጋ ትልቅ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። በመጀመሪያ በኮቪድ 19 ታማሚዎች ማቆያ ፣በፖሊስ፣ በጤና ባለሙያዎች እንዲሁም በጎዳና ተዳዳሪዎች መንከባከቢያነት ተይዘው የነበሩ ትምህርት ቤቶች ለኮቪድ-19 ወረርሺኝ የተጋለጡ ስለነበር ተማሪዎች ከመግባታቸው በፊት የማፅዳትና የዲስ ኢንፊክሽን ሥራ ተከናውኗል። ከተለያዩ ተቋማት የተገኙ የኮቪድ-19 መከላከያ ግብዓት ድጋፎች ለትምህርት ቤቶች በማቅረብ የማስክ፣ የሳኒታይዘር እና ሌሎች የንጽህና መጠበቂያ ግብዓቶች ቀርበዋል። የትምህርት አመራርም ጭምር በየአካባቢው በመዘዋወር የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ አከናውኗል። በትምህርት ቤቶች ውስጥ በሚገኙ ክበባት ተማሪዎች እራሳቸውን እንዲጠብቁ እና ኮሮናን እንዲከላከሉ የሚያስችል ትምህርት እየተላለፈ ይገኛል።
ከሁሉም በላይ ትልቅ ኢንቨስትመንት የፈለገው የተማሪዎችን ጥግግት ለመቀነስ ታስቦ 2 ሺህ 230 አዳዲስ ክፍሎች ተገንብተዋል። በክፍሎቹም ውስጥ መቀመጫ ወንበር እና ሌሎች ግብዓቶች ለማሟላት በቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል። ይህም ተማሪዎች በአንድ ክፍል ሳይታጨቁ ዘና ብለው በተናፈሰ አየር እንዲማሩ እድል ፈጥሯል። ከውሃ አቅርቦት ጋር በተያያዘ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ላይ 1ሺህ500 የውሃ ማቆሪያ ታንከሮች ተገዝተው ቀርበዋል። ተማሪዎች ሲገቡም ሆነ ሲወጡ እጃቸውን መታጠብ ይችላሉ። በተጨማሪ ማስክ ሳያደርግ መምህሩም አያስተምርም ተማሪውም ካላደረገ ክፍሉ እንዳይቀመጥ ይደረጋል። ለዚህም ከርዕሰ መምህራን አንስቶ እስከ ተማሪ ተወካዮች ድረስ ቁጥጥር ይደረጋል።
በትምህርት ቤቶች ውስጥ ያለው ቁጥጥር መልካም በመሆኑ ተማሪዎችም ሆኑ መምህራን ጥንቃቄ እያደረጉ ነው። በእርግጥ ማስተካከል የሚገቡ ጉዳዮች መኖራቸው እሙን ነው። በተለይ ማስከ ያለማድረግ እና ተቃቅፎ የመሄድ ችግሮችን ርቀትን ያለመጠበቅ ችግር ሊስተካከል እንደሚገባው መልዕክት እያስተላለፍን ነው።ተማሪዎች ግን ከትምህርት ቤት ሲወጡም ጭምር ስጋት እንዳላቸው ይናገራሉ፤ እኛም የዳሰሳ ጥናት አድርገን እንደተረዳነው ተማሪዎቹንም ትምህርት ቤት ውስጥ ጥንቃቄ ቢያደርጉም ማህበረሰቡ ግን ስለበሽታው ዝንጋታ ላይ መሆኑ ያሳስባቸዋል። ተማሪዎች በትራንስፖርት ቦታ፣ በገበያ፣ በመዝናኛ ቦታዎች እና ሌሎች ቦታዎች ላይ በርካቶች ያለጥንቃቄ ስለሚንቀሳቀሱ የኮቪድ ስርጭቱም ተባብሶ ወደትምህርት ቤቶችም እንዳይስፋፋ ነው ስጋታቸው።
አዲስ ዘመን፦ ዘንድሮ ፈተና የወሰዱት የ2012 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች አብዛኛዎቹ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበዋል፤ ለዚህ ስኬት መነሻው ምንድን ነው? ቀጣይነት እንዲኖረውስ ምን እየተሠራ ይገኛል?
አቶ ዘለላም፦ ዋናው ነገር ተማሪዎች ስለእራሳቸው ውጤት እና የትምህርት ሁኔታ ልዩ ትኩረት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። ኮቪድ ሲመጣ እና ትምህርት ሲቋረጥ ተማሪው ትኩረቱ እንዳይቀንስ በሚል በተለያዩ አማራጮች ዕውቀት እንዲያገኝ እና ትምህርቱን እንዲከታተል ጥረት ተደርጓል። ወደትምህርት ቤት ሲመለሱም በተመሳሳይ የገጽ ለገጽ ትምህርት እና ዕውቀት የማስጨበጥ ስራዎች በተቻለ መጠን ተከናውነዋል። የ2012 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ከ24 ሺህ በላይ ናቸው። የተማሪዎቹን ውጤት ማየት ከተቻለ በታሪካችን ተመዝግቦ የማያውቅ ትልቅ ውጤት ነው የተገኘው። በዚህም ምክንያት ከ600 በላይ ውጤት ያስመዘገቡ 219 ተማሪዎችን አግኝተናል። በርካቶችም ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያሳልፋቸውን ነጥብ አግኝተዋል። በጥብቅ ዲሲፕሊን ውስጥ ፈተናውን አከናውነን ይህን ያክል ውጤት መመዝገቡ የሚያስደስት ነው።
ውጤቱን በዘንድሮው ዓመትም አሻሽሎ ለመቅረብ ነው አላማችን። ለዚህ ደግሞ ተማሪዎችን ማነሳሳት አለብን። የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ወደ ክፍል ከገቡ በኋላም ሳምንቱንም ሙሉ እንዲማሩ አድርገናል። ተጨማሪ የትምህርት ይዘቶችን እንዲያገኙ በሚል የትምህርት ቤት ቆይታ ጊዜያቸውን ጨምረነዋል። ተማሪውም በየሳምንቱ ቅዳሜ ቅዳሜ ሞዴል ፈተናዎችን ይወስዳል። በየሳምንቱ የሚወስዱት ፈተና የውጤታማነት አቅማቸውን ከማሳደግ ባለፈ ተማሪዎች በቀጣይም ወደፈተና ሲገቡ የስነልቦና ዝግጅታቸው እንዲዳብር ይረዳል። ይህንን ልምድ ማስቀጠል አለብን በሚል በሁሉም ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ ተደርጓል። በትምህርት ጉዳይ ላይ ስራዎች በዘላቂነት መከናወን አለባቸው ብለን እየሰራን ይገኛል።
በዘንድሮው ዓመት ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ፈተና ምዝገባ በማከናወን ላይ ነን። የተፈታኞቹ ቁጥርም ከ24 ሺህ በላይ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ባለፈው ለተገኘው ውጤት የቢሮው ፣የመምህራን፣ የወላጆችም ሆነ የተማሪዎች የተቀናጀ ሥራ ድምር ውጤት አድርጎ ማየት ይቻላል። ይህንን ልምድ በቀጣይም በተሻለ መልኩ ለማስመዝገብ ትምህርቱ በሁሉም የትምህርት ቀናት እየተሰጠ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፦ የተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብርን የሚከታተልና የሚያስፈጽም ተቋም ተቋቁሟል፤ በዚህ ረገድ ምን ያክል ተጨባጭ ሥራ ተከናውኗል?
አቶ ዘለላም፦ የተማሪዎች ምገባ ሰው ሆነህ ስታስበው ከስራም በላይ ጽድቅነት የታከለበት ጉዳይ ነው። መነሻውን እንግዲህ ማየት ከቻልን ቀድሞ አንድ ትምህርት ቤት ላይ ምገባ ሲከናወን የደሃ ደሃ ቤተሰብ ተብለው ለተለዩ ልጆች ነበር ምገባ የሚሰጠው። እናም በትምህርት ቤቱ የሚመገቡ የተወሰኑ ተማሪዎች ተሳቀውና ተደብቀው ነበር ወደመመገቢያ ክፍላቸው የሚሄዱት። የደሃ ደሃ ተብለው የተለዩበት የምገባ ፕሮግራም ትምህርት ቤቱ ውስጥ ከፋፋይ አስተሳሰብ በተማሪዎች ስነልቦና ውስጥ ቀርጿል። ጥቂት ተማሪዎች የበታችነት ስሜት ተሰምቷቸው ተጨቁነው እንዲማሩ የሚያደርግ ነበር። ይህን ስንረዳ ወይ ምገባውን ከነጭራሹ እናቁመው አሊያም ሁሉንም ተማሪ እንመግብ የሚል ጉዳይ መጣር።
ምገባው ይቅር ካልን ተማሪው በምግብ እጦት የሚወድቅበት እና የትምህርት መቀበል አቅማቸው የወደቀ ተማሪዎች ይባስ ብሎ ችግር ውስጥ ይውደቁ እንደማለት ነው። የከተማ አስተዳደሩ መቶ በመቶ ተማሪዎቹን መመገብ አለብን የሚለውን ውሳኔ በማስተላለፉ ሊመሰገን ይገባዋል። በተለይ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ሁሉም ተማሪ እንዲመገብ አድርገናል። ይህን ስናደርግ እና ምገባውን ስንመራ ደግሞ የትምህርት አመራሩንም ይበልጥ ጫና እየፈጠረበት በመምጣቱ ይህን ሥራ ሊከታተልና ሊመራ የሚችል ተቋም ያስፈልጋል በሚል የምገባ ኤጀንሲ ተቋቁሟል። ኤጀንሲው በዋናነት የተማሪዎች ምገባ ስርዓትን መምራት፤ የዩኒፎርም ጫማና ደብተር፤ እንዲሁም ሌሎች የግብዓት አቅርቦትን ይመራል። ከትምህርት ቢሮ ጋርም በቅንጅት እየሰራ ይገኛል።
ከምገባ ስርዓቱ ጋር ተያይዞ ላለፉት ሁለት ዓመታት ውጤት አይተናል። በተለይ የተማሪዎች ውጤት በስምንተኛ ክፍል እና በ12ኛ ክፍል የተሻለ ውጤት ተገኝቷል። ተማሪዎች የመቀበል አቅማቸው እየጨመረ፣ መጠነ ማቋረጥ እና መድገም እየቀነሰ እንዲመጣ ያደረገው የምገባ ፕሮግራም ነው። በምገባ ኤጀንሲ ስር ከ600 ሺህ በላይ የአዲስ አበባ ተማሪዎች በትምህርት ቤት አካባቢ ምግብና የትምህርት ቁሳቁሶችን እያገኙ ነው። ከከተማ አስተዳደሩ ባለፈ በርካታ በለሃብቶች እና ድጋፍ ሰጪ ተቋማትን ጭምር በማስተባበር እየሠራ ይገኛል። ይህን ልምድ ሌሎች ከተሞችን እንዲተገብሩት መልካም ተሞክሮ የሰጠ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ባለፈው ዓመት ኮቪድ 19 ከገባ በኋላ ምገባው ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ ቆይቷል፤ በወቅቱ ምገባውን ለተማሪዎች ቤት ለቤት ማድረግ ያልተቻለበት ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ ዘለላም፦ ትውልድ የሚገነባበት ትልቁ መሠረታዊ ነገር ትምህርት ቤት ነው። ይህ ትልቅ ተቋም ሲዘጋ እንደትምህርት ቢሮ ትልቁ ያስጨነቀን ነገር ተማሪዎችም ቤታቸው ለረጅም ጊዜ መዋላቸው የሚፈጥረው አሉታዊ ተጽእኖ ነው። ትምህርት ቤት ቢዘጋም ግን ትምህርት እንዳይቋረጥ አላደረግም። ሌላው አሳሳቢ ነገር ግን በምግብ እጦት ላይ ያሉ ልጆችና ምገባው ሲቋረጥባቸው እንዴት ይሆናሉ የሚለው ጉዳይ ነበር። ነገር ግን በየቤቱ ምገባውን ማድረስ በአንድ በኩል እየተስፋፋ ያለውን የኮቪድ 19 ስርጭት ይባስ ማዛመት ይሆናል በሚል ሃሳብ አደረብን።
በሽታው አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በእራሱ በምን መልኩ ስራውን ማስቀጠል እንችላለን የሚለውን አስቸጋሪ አድርጎት ነበር፤ መደናገጥ ውስጥም ነበርን። ነገር ግን እንደከተማ በየትምህርት ቤቱ የምግብ ባንኮች እንዲቋቋሙ ተወሰነ። ከብሎክ አደረጃጀት ከየመንደሩ የተለዩ አቅመ ደካሞች እና አነስተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ከዚያ በምግብ ባንኮች አማካኝነት የምግብ ግብአቶችን እንዲያገኙ ተደርጓል። ያንን ግብዓት እያበሰሉ በቤታቸው እንዲመገቡ ጥሬ እቃው ቀርቧል። ስለዚህ የምገባ መርሐ ግብር ቢቋረጥም በምገባ ባንክ አማካኝነት ተማሪዎቻችንን ማግኘት ችለናል። በዚህ ረገድ ኮቪድ 19ን ታሳቢ ያደረገ ትልቅ ስኬት አስመዝግበናል ብለን እናስባለን።
አዲስ ዘመን፦ በከተማዋ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች ከትምህርት ሚኒስቴርና ከቢሮው እውቅና ውጪ የእራሳቸውንም ካሪኩለም በማዘጋጀት ጭምር ያስተምራሉ፤ ይህን ለማስተካከል የተጓዛችሁበት ርቅት ግን ደካማ ነው፤ ለምን?
አቶ ዘለላም፦ ትምህርት ቤት ትውልድ የሚገነባበት ማሽን ነው ካልን፤ ትምህርቱን ተመሳሳይ የልቦና ውቅር ለመቅረጽ በሚያስችል መንገድ መዘጋጀት አለበት። ለዚህ ደግሞ መሰረቱ ስርዓተ ትምህርት ነው። ካሪኩለሙ እውቀት ከማስረጽ ባለፈ ሁለንተናዊ ሰብእና የተላበሰ እና ለሀገሩ ፍቅር ያደረበት ትውልድን መገንባት መቻል አለበት። የመጣንባቸው ያለፉት 27 እና 30 ዓመታት በትምህርት እና ትምህርት ካሪኩረም ረገድ የተዘበራረቀ አካሄድ ነበረው። ይህም እንደሀገር የተዥጎረጎረ አስተሳሰብ ይዘን እንድንወጣ አድርጎናል። አንዳንዱ የህንድን ስርዓተ ትምህርት ሲያስተምር፤ አንዳንዱ የእንግሊዝን አሊያም የእራሱን በየፊናው ያስተምራል። በመንግሥት እና በግል ትምህርት ቤቶች የካሪኩለም አጠቃቀም የተዥጎረጎረ ነው፤ ይህን ለማስተካከል ዝግጅት እያደረግን ነው። ችግሩን ለማስተካከልም ከትምህርት ፍኖተ ካርታ ጋር የተያያዙ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል።
ወደአዲስ ስርዓተ ትምህርት ልንገባ ስለሆነ አንድ ፊቱን ያን ጊዜ ከካሪኩለም ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን እንፈታለን ብለን እናስባለን። አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ትግበራ ላይ ነው። በሚቀጥለው ዓንድ ዓመት በኋላ ፍኖተ ካርታ ይዘን ወደሙሉ ትግበራ የምንገባበት አውድ ይፈጠራል። ትውልድ ከአንድ ምንጭ እንዲወጣ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ነው። ስለዚህ በቀጣይ የተዥጎረጎረውን ምዕራፍ ዘግተን ወደአዲስ ምዕራፍ እንሸጋገራለን። የትምህርት ካሪኩለሙን ተግባራዊ በማድረግ ትውልዱ በሁለንተናዊ መልኩ ለመገንባት ትልቅ ዝግጅት ተደርጓል። ያኔ የእራሴን ካሪኩለም አዘጋጅቼ እገባለሁ የሚል የግል ትምህርት ቤት ካለ አብሮ አይቀጥልም። እንደአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ጉዳይ ከማንም ጋር አንደራደርም።
ስርዓተ ትምህርቱ ማለት ለትምህርቱ እንደ ህገመንግሥት ሆኖ የሚቆጠርበት አሰራር ይኖራል፤ ይህን የጣሰ በስርዓቱ የማይቆይበት እና ይህን ያከበረ ብቻ በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ የሚቆይበትን አሰራር ለመፍጠር እየሰራን ነው። ከአሰሪ ማህበራትም ጋር በጉዳዩ ላይ ተወያይተናል። በቀጣይ ያልተመጠነ እና ያልተጠና ትምህርት መስጠት አይቻልም፤ የተዘበራረቀ ካሪኩለም አዘጋጅተው የሚያስተምሩ አካላትም ከወዲሁ ሊያስቡበት ይገባል። ለዚህም ትምህርት ቢሮ ቁርጠኛ መሆኑን ለማረጋግጥ እወዳለሁ።
አዲስ ዘመን፦ ከግል ትምህርት ቤቶች ክፍያ መናር ጋር በተያያዘ ሁል ጊዜም ቅሬታ ይሰማል፤ ይህን ለመቆጣጠር በቀጣይ ምን አይነት አሰራር ለመዘርጋት አስባችኋል?
አቶ ዘለላም፦ በእርግጥ የነፃ ገበያ መር ኢኮኖሚ እስከሆነ ድረስ ዋናው በሻጭና በገዥ መካከል በሚኖረው መስተጋብር የሚፈጠር ውሳኔ ነው። ነገር ግን የትምህርት ቤት ባለንብረቶች እና በተማሪ ወላጆች መካከል ያለው የድርድር አቅም በጣም ደካማ በመሆኑ ክፍያዎች ይንራሉ። የወላጅ ኮሚቴዎችን የመደራደር አቅም ከፍ ማድረግና መገንባት ያስፈልጋል። የወላጅ ኮሚቴዎች በትምህርት ቤቱና በወላጅና ተማሪ መካከል ድልድይ ሆነው መልካም ሥራ እንዲከናወን ይረዳሉ። አንዳንድ ቦታ ላይ ግን የማይሰራ የወላጅ ተማሪ ህብረትም እንዳለ ይታወቃል። በኮሮና ወቅትም ቢሆን በትምህርት ቤቶች እና ወላጅ ኮሚቴዎች መካከል የነበሩ አምባጓሮዎች አሰቃቂ ነበሩ። የሁለቱን መስተጋብር ቀና እንዲሆን በማድረግ የክፍያ ችግሮችን መፍታት ያስፈልጋል።
በሌላ በኩል ቀደም ባለው ጊዜ አዲስ አበባ ውስጥ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የደሃ ልጅ ወልዶ መጣያ ነው በሚል አስተሳሰብ ትምህርት የመደብ ልዩነት እንዲይዝ ተደርጓል። ስለዚህ ያለውም የሌለውም ተለቅቶም ሆነ ተበድሮ ልጆቹን የግል ትምህርት ቤት ይልካል። አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች ደግሞ ከመማር ማስተማር ይልቅ ስራውን ልክ እንደግል ሸቀጥና ቢዝነስ ይቆጥሩትና ክፍያ ያንራሉ። ከሙያም ሆነ ከስነምግባር ያፈነገጡ ስራዎችን ያከናውናሉ። ክፍያ የሚተመነው በግለሰቦች መልካም ፈቃድ ላይ ተመስርቶ ነው። ምንም እንኳን የመምህራን ደሞዝ ቢጨምርም፣ የተለያዩ ወጪዎች መኖራቸው ቢታወቅም አንዳንድ ጊዜ ግን ትልቅ የክፍያ ጭማሪ ይታያል።
በዚህ ረገድ ክፍያ ይህን ያክል አድርግ አታድርግ አይደለም የምንለው። በዋናነት የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ላይ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ስንችል ያኔ ሁኔታዎቹ ይስተካከላሉ። ባለፉት ሁለት ዓመታት በትምህርት ቤቶች አሰራሮችን ስናስተካክል፣ እድሳት ስናደርግ እና የተለያዩ ግብዓቶችን ስናቀርብ እና በግል ትምህርት ቤቶች እና በመንግሥት ትምህርት ቤቶች መካከል ልዩነት እንደማይኖር ሲገነዘቡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ናቸው ወደመንግሥት ትምህርት ቤት የተዛወሩት። አማራጭ ማሳየት እና የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን አቅም በማሳደግ ተገዳዳሪ አቅም ሲያሳዩ ችግሩን ይፈታል የሚል እምነት አለን።
ከዚህ ባለፈ ደግሞ በቀጣይ የትምህርት ካሪኩለሙን ለማስፈጸም ሲንቀሳቀስ እና የትምህርት ቢሮ የመቆጣጠር አቅም ሲፈጥርም ተመሳሳይ ካሪኩለም ስለሚተገበር ወላጆችም የግል ትምህርት ቤቶችን እንደአማራጭ የማያዩበት ሁኔታ ይፈጠራል። ሁሉም ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያለው ትምህርት ካለ ወላጅም በአቅራቢያው በሚገኝ ማንኛውም ትምህርት ቤት ያስተምራል።የግል ትምህርት ቤቶች ባለንብረቶችም ከትርፍ በላይ ትውልድ ይበልጣል፤ ከትርፍ በላይ ትውልድ እየገነቡ ያስተማሯቸው ተማሪዎች ሀገር ለመገንባት የሚችል ዜጎች ናቸው። ትልቅ የትምህርት መሰረተ ልማት ገንብተው ሀገር እየጠቀሙ የሚገኙ ባለንብረቶችም አሉ። እየሰጡ የሚገኘውን ትውልድ የመገንባት ተግባር ታሳቢ አድርገው ከሌላው የንግድ ዘርፍ ያነሰ የትርፍ ህዳግ በእራሳቸው ተግባራዊ ቢያደርጉ መልካም ነው።
አዲስ ዘመን፦ ከርዕሰ መምህራን እና ከሱፐርቫይዘሮች ምደባ ጋር በተያያዘ ምደባቸውን ከፖለቲካ እና ከብሔር አስተሳሰብ ነጻ ሆኖ እንዲሰራበት ከማድረግ አኳያ ምን ሰራችሁ?
አቶ ዘለላም፦ የርዕሰ መምህራን እና የሱፐርቫይዘሮች ምደባ ሹመት አይደለም። ከሹመት ወጥተን ግልጽ የሆነ የውድድርና የብቃት መመዘኛ እንዲመጣ ነው እያደረግን ያለነው። አንድርዕሰ መምህር ሲመደብ እድሜ ይፍታህ ይመስል ቦታው እንደቋሚ ንብረት የሚታሰብ መሆን የለበትም። በእያንዳንዱ ትምህርት ቤት የሚመደቡ ርዕሳነ መምህራን አራት ነበሩ፤ እነሱም በየተራ በፈረቃ የሚገቡበት የትምህርት ስርዓት ነበር፤ ይህንንም አስተካክለናል። አሥርም ተማሪ ያለበት ትምህርት ቤት ቢሆን አራት ርዕሳነ መምህራን ይመደቡ ነበር፤ አሁን ግን የተማሪዎችን ቁጥር ያገናዘበ ምደባ ነው ያለው። በተጨማሪ ሲመቻቸው የሚሰሩ ሳይመቻቸው ደግሞ ሌላ ቢዝነስ የሚያሯሩጡ ርዕሳነ መምህራን ነበሩ። ቀደም ባለው ጊዜ ልጆቻቸውን እንኳን እራሳቸው በተመደቡበት ትምህርት ቤት የማያስተምሩ በርካቶች ናቸው። ለእራሳቸው የማይሆን ትምህርት ካለ ደግሞ ለሌላውም አይሆንም የሚለውን አስተሳሰብ እንዲይዙ ለማድረግ በእርግጥ ጊዜ ይፈልጋል።
በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ምን አቅዶ ምን ውጤት አስመዝግቧል፤ ትምህርት ቤቱንስ ከምን ደረጃ አንስቶ የት ላይ አድርሷል የሚለው እየታየ ነው ምደባ የሚከናወነው። ከዚህ ቀደም እንደነበረው አሰራር ግን አንድ ትምህርት ቤት የተመደበ ርዕሰ መምህር እንደቋሚ አድራሻ እዛ ትምህርት ቤት ነው እየተባለ ብቻ እንደፈለገ የሚወጣበትና የሚገባበት አካሄድ አሁን የለም። ብቃት ያለው ሱፐርቫይዘርም ሆነ ርዕሳነ መምህር ይቆያል፤ ከሌለው እንዲወርድ ይደረጋል።
አንድ ርዕሰ መምህር በቦታው ሊቆይ የሚችለው በብቃቱ እና በሚያመጣው ውጤት ብቻ ነው የሚለውን አሰራር አስተካክለናል። በትምህርት አመራር ብቃቱ እና ክህሎቱ ብቻ ነው አንድ ሰው መመደብም መቆየትም ያለበት። ቀደም ካለው አሰራር ትልቁ የሽግግር ስራችንም ይህ ነው። አንድ ተቋም ማንን ይመስላል ቢሉ መሪውን ነው የሚመስለውና ትምህርት ቤቶችም ላይ ጠንካራ ርዕሰ መምህራን እንዲመደቡ የሚያግዝ የውጤታማነት መመዘኛ ተግባራዊ እያደረግን ይገኛል።
አዲስ ዘመን፦ከመምህራን ልማት፤ ቅጥር እና ድጋፍ ጋር በተያያዘ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ምን አይነት ስራዎችን አከናወናችሁ?
አቶ ዘላለም፦ በአጠቃላይ በአንደኛ ደረጃ ፤ በሁለተኛ ደረጃ እና በቅድመ መደበኛ ከ19 ሺህ400 በላይ አንደኛ ነባር መምህራን በስራ ላይ ናቸው። ሁለተኛውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝን መሰረት ባደረገ መልኩ የመማር ማስተማር ስራው ለመምራት ተጨማሪ የመምህራን ቅጥር አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። በዚህም መሰረት ማስታወቂያ አውጥተን በርካቶችን ከመዘገብን በኋላ በጥቅሉ የ1 ሺህ 600 ያህሉን ቅጥር በመፈፀም ላይ እንገኛለን።
እስካሁን ካሉን መምህራን ውስጥ በዘጠኝ ወሩ በተከናወኑ የቅጥር፣ የስልጠና እና የትምህርት እድል የማመቻቸት ስራዎች ተጠቅመን የመምህራንን የትምህርት ደረጃ በማሳደግ ላይ እንገኛለን። ባለፉት ጊዜያት የቅድመ አንደኛ ደረጃ በዲፕሎማ የሚያስተምሩ መምህራን ቁጥር 90 በመቶ ማድረስ ተችሏል። የአንደኛ ደረጃ በዲግሪ የሚያስተምሩ መምህራን ደግሞ 58 በመቶ አድርሰናል። በተመሳሳይ ከ9 እስክ 12ኛ ክፍል በማስተርስ የሚያስተምሩ መምህራን ቁጥር ወደ40 በመቶ ማሳደግ ተችሏል።
በሌላ በኩል ከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ለበርካታ ጊዜያት ችግር ሆኖ የቆየውን የመምህራን የክፍለ ጊዜ ጫና አለመመጣጠን እና የትምህርት አመራሮችን አዘዋውሮ የማሰራት ችግር ነበር። ይህን ለመፍታት መመሪያውን መከለስ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ በቢሮ ደረጃ ኮሚቴ በማዋቀር የመምህራን እና የትምህርት አመራር የዝውውር መመሪያ በማዘጋጀት ወደ ሥራ እንዲገባ ዝግጅቱን ማጠናቀቅ ተችሏል፡፡
በአጠቃላይ በከተማዋ የውስጥ እና የውጭ ዝውውር መመሪያን መሰረት በማድረግ የዝውውር መረጃ ሰብስበው እና አጠናቅረው ለዳሬክቶሬቱ ገቢ በማድረግ የዝግጅት ስራውን ማጠናቀቅ ተችሏል፡፡ በዚህም አንደኛ በቤተሰብ (የጋብቻ) ዝውውር በተመለከተ መስፈርቱን ያሟሉ ከሁሉም ክልሎች በጥቅሉ 290 መምህራን ዝውውር እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡
መምህራንን ከማበረታታት አኳያ የመምህራን ሽልማት የከተማ አስተዳደሩ ክብርት ከንቲባ እና የከተማዋ አመራሮች በተገኙበት የእውቅናና ሽልማት ለ130 አንጋፋ መምህራን፣ ለ10 ርዕሰ መምህራን፤ ለ10 ሱፐርቫይዘሮችና ሌሎች ባለሙያዎችን ጨምሮ በድምሩ 160 አካላት እውቅናና ሽልማት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ በዚህም ለ160 ተሸላሚዎች ሰርተፊኬት ሜዳሊያ እና ለእያንዳንዱ አሥር ሺህ ብር ሽልማት ተሰጥቷል፡፡ ይህም የትምህርት ቤት ውጤታማነትን በማሳደግ እና ሌሎችንም በማነሳሳት ረገድ መልካም ተጽእኖ እንደሚፈጥር ይታመናል።
አዲስ ዘመን፦ በቀጣይ ወራት በትምህርቱ ዘርፍ ምን አይነትስ ስራዎችን ለማከናወን አቅዳችኋል?
አቶ ዘለላም፦ የቀጣይ 4ኛ ሩብ ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች በግልጽ የተቀመጡ ናቸው። ከዚህም ውስጥ አንዱ የኮቪድ 19 ጥንቃቄን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ትምህርት ቤት ሳይዘጋ እንዲጠናቀቅ ማድረግ ነው። የንጽህና እና ጥንቃቄ ግብዓቶች በሚገባ ጥቅም ላይ እንዲውሉ አመራሮች ጭምር በእያንዳንዱ ትምህርት ቤት ወርደንም እንከታተላለን። በሌላ በኩል የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፓኬጅ በስድስት መርሐ ግብሮች በተሟላ ሁኔታ በሁሉም የትምህርት ተቋማት እንዲተገበር ማድረግ ሌላው የሚጠበቅብን ሥራ ነው። ባለፉት ዘጠኝ ወራት ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ ያልሆኑ ግቦችን በመለየት በቀሪ የስራ ጊዜያት እንዲከናወኑ ማድረግ ይኖርብናል። በተለይም 2013 በጀት ዓመት ያሉ ነባር አዲስ እንዲሁም በማስፋፊያ ያሉ ግንባታዎችን መከታተል ለትምህርት ዝግጁ ማድረግ ላይ ትኩረት ይደረጋል።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
አቶ ዘለላም፦ እኔም ከልብ አመሰግናለሁ
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2013