በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች የሚኒስትሩ አማካሪና የኢትዮጵያ የድርድር ቡድን የህግ አማካሪ ናቸው ። የኢትዮጵያና የሱዳን ወሰን ኮሚሽን አባል እንዲሁም የግብጽ አምባሳደርም በመሆን አገልግለዋል ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በነበሩባቸው ጊዜያትም የሰላም ማዕከልን በመመስረትና ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተጀመረውን አፈርማቲቭ አክሽን በማስጀመር ይታወቃሉ ። በፓርላማ የሚቀመጥ የህግ መጸሐፍ አዘጋጅተው አበርክተዋል ። አሁን የምንጠቀምበትን የጦርነት ህግ ማለትም አራቱ የጄኒቫ የጦርነት ህጎች የሚባሉትንና ሁለት ፕሮቶኮሎችን ወደ አማሪኛ በመተርጎም በመከላከያምአገልግሎት ላይ እንዲውልም አድረ4ገዋል ። በአማካሪነትም በአለም አቀፍና አገራዊ ተቋማት ስተዋል ። ዛሬ በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ አነጋግረናቸው ምላሻቸውን እንደሚከተለው አቅርበነዋል ።
አዲስ ዘመን፡- አምባሳደርነትን እንዴት ይገልጹታል?
አምባሳደር ኢብራሂም፡– አምባሳደር ማለት ዲፕሎማት የሚለውን ሀሳብ ይወስዳል። በዚህም አምባሳደርነት እንደ አገር በ አለም አቀፍ መድረክ የሚደረጉ ግንኙነቶችን በውጪ ፖሊሲ ማሳለጥ ነው። አላማውም መንግስት በአገር ውስጥ ያለውን ጥረትና እድገት እንዲሁም እንቅስቃሴ የሰመረ እንዲሆንለት አለም አቀፍ ድጋፍን ማሰባሰብ ነው ። ከዚያ ባሻገር የኢትዮጵያንና የሌሎች አገሮችን ግንኙነት ለኢትዮጵያ በሚጠቅም መልኩ መግራትን ያመላክታል ። አምባሳደር ሲመረጥ ከአገር ውስጥ ነው ፤ ዋና ሥራውም የኢትዮጵያን አቅምን ለውጪው ማሳየት ነው። ስለዚህም ይህንን ማድረግ የሚችለው አካል በውጪ ጉዳይ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ይመረጣል ። ሥራውን ውጪ አገር ወይም አገር ውስጥ ሊያከናውነው ይችላል ። ከፍ ያለ ተጠያቂነት አለበት።
የሀገራችን አምባሳደሮች እንደእኔ እምነትም የተሰጣቸውን ስራ በሀላፊነት እየተወጡ ነው። ምክንያቱም በዲፕሎማሲያዊው ሥራ በልጠን ካልተገኘን ብዙ ነገሮች ሊያመልጡን ይችላሉ። የአንድ አገር ምሰሶ ዲፕሎማሲ ነው። ስለሆነም ይህንን በማድረግ ዙሪያ አምባሳደሮች እየተጉ እንደሚገኙ አምናለሁ ። ሰርተዋል አልሰሩም የሚለውን ብንተወው ተጨማሪ ሥራዎች ግን ያስፈልጋሉ። አገሪቱ ያለችበት ችግር በቀላሉ የሚፈታ አይደለምና ይህንን መፍታት የእነርሱ አንዱ ሥራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የግብጽ አምባሳደር ነበሩ ። በግብጽ በነበሮት የአምባሳደርነት ቆይታ ሰራሁት የሚሉት ትልቁ ነገር ምንድን ነው ?
አምባሳደር ኢብራሂም፡– ይህንን ሰርቻለሁ ማለትና ራስን ማመስገን ጥሩ ባይሆንም አምባሳደር ከመሆኔም በፊት ሆነ ከሆንኩ በኋላ ለአገሬ ብዙ የሚጠቅም ነገር አበርክቻለሁ ። ከእነዚህ መካከል በዋናነት የሰራኋቸውን ብቻ ላንሳ።
እኔ የህግ ባለሙያ በመሆኔ ብዙ የማማከር ሥራዎችን ሰርቻለሁ ። ከእነዚህ ውስጥ 20 ዓመታትን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሳሳልፍ ያከናወንኳቸው ተግባራት ይጠቀሳሉ ። የጦርነት ህግ፣ ሰብዓዊ መብት ላይና በስነዜጋና ስነምግባር ላይ የሚያተኩሩ ሥራዎችን ማከናወኔ አንዱ ነው ። አሁን የምንጠቀምበትን የጦርነት ህግ ማለትም አራቱ የጄኒቫ የጦርነት ህጎች የሚባሉትንና ሁለት ፕሮቶኮሎችን ወደ አማሪኛ በመተርጎም አገልግሎት እንዲሰጡ አድርጌያለሁ። ባህላዊ የጦርነት ህጎች ካዘጋጁት ፤ግማሽ ፍታብሔር ህጉን ካሻሻሉት መካከልም ነኝ።
ወደ ውጭ ጉዳይ ስገባ ደግሞ አገሪቱ አራት ከበባድ ችግሮች ላይ ነበረች። በዚህም የማማከሩንና መሰል ተግባራትን ስከውን ቆይቻለሁ። እነዚህም የኢትዮ ኤርትራ የድንበር ችግር ፤ከኤርትራ ጋር የፍትሀብሔር ክርክሮች ፤ በግብጽ፣ በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል የናይል የውሃ ጉዳይ፤ የድንበርና የአፍሪካ ህብረት ከኢትዮጵያ ይውጣ ክርክሮች ናቸው። በእነዚህ ውስጥ ደግሞ ብዙ ለውጦችን ከጓደኞቼ ጋር በመሆን ለማምጣት ችያለሁ ።
አምባሳደር ሆኜ ስሾምም እንዲሁ የሰራኋቸው ሥራዎች አሉ። ትክክለኛ ቪዛ አግኝተው የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ እንግልት ይደርስባቸው ነበርና ይህንን ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት ባልችልም ሌሊት ሳይቀር እየተገኘሁ መፍትሄ እንዲሰጣቸው አድርጌያለሁ። በተመሳሳይ የኢትዮጵያና የግብጽ የንግድ ግንኙነት እንዲጠናከር አድርጌያለሁ ።
በዚህ ወቅት ከባድ የሚባል ችግርም ገጥሞኝ ነበር። ይህም የኢትዮጵያ የቀንድ ከብትም ሆነ ሥጋ እንዳይገባ ተብሎ ከስምምነት ውጪ በተወሰነበት ወቅት በሜድሮክ አማካኝነት የገባ ወደ 32 ሺ ኪሎግራም የሚደርስ ሥጋ የተበላሸበትን ሁኔታ በማየት እኔም ሥጋው ተፈላጊ ስለሆነ ነጋዴዎቻቸውን በጎን እየላኩ ይሰሩ ነበርና ያንን ማስቆምና ለሁለት ዓመት ቪዛ የመከልከል ሥራ ሰርቻለሁ። ስምምነቱ በእርቅ ሲጠናቀቅና ይቅርታ ሲጠይቁም ወደነበረበት የንግድ ትስስር እንዲመለስም ማድረግ ችያለሁ ።
ከናይል ጋር በተያያዘም ቀደም ሲል ተደራዳሪ ስለነበርኩ ብዙ ፈተና ቢደርስብኝም የተሻለ አቅጣጫ እንዲይዝ ካደረጉት መካከል ነኝ ። አሁንም በውጪ ጉዳይ የድንበርና ድንበር ተሸጋሪ ሀብቶች ጉዳይ የሚኒስትሩ አማካሪ በመሆን የአምባሳደርነት ተግባሬን እያከናወንኩ እገኛለሁ ። በተለይም የህዳሴ ግድቡ የህግ አማካሪምና የኢትዮጵያና የሱዳን ወሰን ኮሚሽን አባል በመሆኔ በዚህ ዙሪያ ያላሰለሰ ጥረት እያደረኩ ነው ።
አዲስ ዘመን፡- ግብጻዊያን በዲፕሎማሲው ለኢትዮጵያ ቀንአዊ እንዳይደሉ ይጠቀሳል። ምክንያታቸው ምን ይሆን ?
አምባሳደር ኢብራሂም፡- በዋናነት በውሃው ጉዳይ እኛን እንደተቀናቃኝ ማየታቸው ነው። ኢትዮጵያ የግብጽ እንቅፋት ነች ብለው ያምናሉ። በእርግጥ ህዝብ እንደ ህዝብ በጣም ጥሩ ናቸው። ችግሩ የህዝቡ ሳይሆን የባለስልጣኑ እና የአጋሮቹ ነው። የህዝቡን አዕምሮ ፖለቲከኞቹ፣ የታሪክ ምሁራን፤ ባለስልጣናቱና ጋዜጠኞች በርዘውታል ። ሁሉም በግብጽ ጉዳይ ላይ አንድ አይነት አመለካከት ይዘውም ነው የሚንቀሳቀሱት። በአምስት ዓመት ቆይታዬም ጸረ ኢትዮጵያ እንደሆኑ አረጋግጫለሁ።
የግብጾች ጥላቻ ሁለት ነገሮችን መሰረት ያደረገ ነው። የመጀመሪያው የውሃው ጉዳይ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ እያለች የግብጽ ውሃ ጉዳይ አደጋ ውስጥ ይወድቃል ብለው ያስባሉ። ከዚህ የተነሳም በጋራ እንስራ የሚለው ሀሳብ አይዋጥላቸውም ። ሁለተኛው ደግሞ የታሪክ ጉዳይ ነው፤ ግብጾች በ18ኛው ክፍለዘመን መጨረሻ ላይ ኢትዮጵያን የመቆጣጠር ሀሳብ ነበራቸው። በተለይም ጣናን አካባቢ በእንግሊዞች አማካኝነት ለመያዝ አልመው ነበር። የተቻላቸውን ሁሉ ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም። ይህ ሁኔታም ኢኮኖሚያቸው ላይ ከፍተኛ ድቀት አድርሷል። እንደውም ያሉበትን ሁኔታ ለመሸፈን ሲሉ ገንዘብ ከአውሮፓ ባንኮች እስከ መበደር ደርሰዋል። ብድሮንም መመለስ አልቻሉም። በዚህም በእንግሊዞች ቅኝ እንዲገዙ ሆነዋል። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ላይ ቂም እንዲይዙ አድርጓቸዋል።
ይህ ታሪክ ህዝባቸው ላይ እንዲሰርጽ ሆኗል። ስለዚህም ኢትዮጵያ ካለች ውሃ አንጠጣም ይላሉ። ህዝባቸው ካልጠላን የውስጥ ሀይላቸውን ማጠናከር አይችሉም። በዚህም የውጪ ጠላት በአገሪቱ ላይ እንዲበዛ ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋሉ። እንደውም አንዱ ግብጽን ለየት የሚያደርገው በውሃ ፖሊሲ ዙሪያ አንድ አይነት አቋም ኖሯት መስራት መቻሏ ነው ። የውጪ ፖሊሲያቸውም ቢሆን የውሃ መብት ላይ ጠንከር ያለ አቋም ይይዛል።
መንግስትም ወደ ስልጣን ለመሄድ በሚያደርገው ግብግብ ላይ የውሀ መብት ጉዳይ ትልቅ አጀንዳ ነው። ለምሳሌ አል ሲሲ ወደ ስልጣን ሲመጡ በህገመንግስቱ አንቀጽ 44 ላይ ታሪካዊ ውሃህን አስከብርልሀለሁ የሚል ነው። ዲፕሎማሲያቸው ቀና ያልሆነው ተቀናቃኝ አድርገው ስለሚወስዱንና ተቀናቃኛችን እየበዛ ነው ። በዚህም በውሀው ላይ ያለን የበላይነታችን ይወሰዳል የሚል ፍራቻ ስላለባቸው የተከሰተ ነው። ከፖለቲካው አኳያ ሁልጊዜ እኛ ነን ትልቅ ብለው ያምናሉ። ሆኖም የሚገዳደራቸው በየአቅጣጫው መብዛቱ ፍራቻ ውስጥ ከቷቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- ግብጽ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የነበራትና ያላት ጣልቃ ገብነት እንዴት ይገልጹታል? ከምን የመነጨ ነውስ ይላሉ?
አምባሳደር ኢብራሂም፡– ምንጩ በብዙ መንገድ ጥረው ያለማሸነፋቸው ነገር ሁልጊዜ ከአዕምሯቸው አለመጥፋቱ ነው። ሁልጊዜ ኢትዮጵያ አሸናፊ እንደምትሆንም ያምናሉ። ምክንያቱም አይተውታል። ስለዚህም ጣልቃ ገብነታቸው በተለያየ መልኩ ሌሎችን በማገዝ ነው ። በተለይም ኢትዮጵያ ጠል ቡድኖችን ካገኙ መጠቀምን ወደኋላ አይሉም ። ከዚህ በተጓዳኝ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ሰርታ መጠቀምና ማትረፍን በተከዜ ያሳየች መሆኗን ስለሚረዱ ልማቱን ለማደናቀፍ የማይቆፍሩት ድንጋይ አይኖርም። ተከዜ ሲሰራ ለምን ተነካ በሚል ከፍተኛ ጩኸት ከሱዳንም ከግብጽም ተሰምቶ ነበር ። ሲጠናቀቅ ግን ዝምታው ሰፍኖ ሱዳን ክረምትም በጋም ሰፊ የእርሻ መሬቷን ማልማት ችላለች ። ግብጽም ብትሆን በውጪ ሚኒስትሯ በኩል ውሀዬ ጨምሯል ስትል ምስክርነቷን አውጃለች። አሁንም ይህ እንደሚሆን ስለሚገነዘቡ ጣልቃ ገብነታቸውን ሳይተው ሀሳባቸውን በመለዋወጥ ይሰራሉ። ሰላም እንዳይኖርና ልማት ላይ ትኩረት እንዳይደረግም ይለፋሉ። ግን መቼም እንደማይሳካላቸው ማወቅ አለባቸው ።
ግብጾች ኢትዮጵያን ማዳከም የሚችሉት ውሃውን ከእርሷ ቁጥጥር ውጪ ሲያደርጉ ብቻ እንደሆነ አምነው የሚሰሩ ናቸው። ለዚህም ተግባራቸውን እውን ለማድረግ ባለፉት 150 ዓመታት ብዙ መጣራቸው ነው ። ከእነዚህ መካከልም በሀይል ለመጠቀም መሞከር አንዱ ነው ። እነ ጉንደትና ጉራንም ማንሳት በቂ ይመስለኛል ። ነገር ግን ሀያሉ የኢትዮጵያ ህዝብ አይበገሬነቱን አሳይቷል። እንደውም በታሪክ አንድ የግብጽ መሪ ባሻ የሚባለው ሱልጣን ብዙ ወገኖቹንና ወታደሮቹን ከሰዋ በኋላ መሬቱን ባለመያዙ ግብጽ ውስጥ አባይ ዳርቻ ተቀምጦ አፈሩን ዘግኖ ‹‹ አንተ አፈር ስንት እኮ ለፍቻለሁ አንተን ለማግኘት። ለምንስ ነው የምለፋው እዚሁ እየመጣልኝ መጠቀም ስችል›› አለ ይባልለታል ። ስለዚህም አሁንም ግብጾች ይህ ነገራቸው ከእነርሱ እንዲርቅ አይፈልጉምና ሰበብ በማይሆነው ነገር አሳበው ልማቱን ለማደናቀፍ ይሞክራሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ በገንዘብ ለማማለል መሞከርም ሌላው ዘዴያቸው ነው። መጀመሪያ ከእንግሊዞች ጋር ከዚያ ደግሞ ከጣሊያኖች ጋር በመሆን ሞክረውት ነበር። አልተሳካላቸውም። ውሃው የእኛ ነው የሚልም ሀሳብ አላቸው። እየሰሩበትም ይገኛሉ ። ሌላው ልማቱ በፍጥነት ተጠናቆ አገሪቱ ተጠቃሚ እንዳትሆን ብድርን ዝግ ማድረግ ሲሆን፤ በተወሰነ ደረጃ ተሳክቶላቸዋል ያስብላል። ምክንያቱም እነዚህ ፕሮጀክቶች ትልቅ አቅምን ይጠይቃሉ። ይህንንም ስለሚረዱ የተለያየ እንቅስቃሴ አድርገው መንገድ ይደፍናሉ። ለዚህም ነው ኢትዮጵያ ከአንዴም ሁለት ጊዜ በራሷ አቅም ወደመስራቱ የገባችው።
ተከዜ ማለት ከተራራ ላይ የሚወርድ ውሃ ነው። ክረምት ላይ ጢም ብሎ ሞልቶ አደጋ የሚፈጥር በጋ ላይ ደግሞ ድርቅ የሚመታው ነው። ሆኖም ለምን ተነካ በሚል ከፍተኛ ጩኸት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ ውሃው መጨመሩንና የሚሰጠውን ጥቅም ሲያዩ ጸጥ አሉ። በተለይም ሱዳን ክረምትም በጋም ሰፊ የእርሻ መሬቷን ማልማት የቻለችው በዚህ የኢትዮጵያ ትግልና ውጤታማ ሥራ ነው። እንደውም የግብጽ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ሳይቀር በተከዜ ምክንያት ተጨማሪ ውሃ አግኝተናል ብሎ እንዲመሰክር ያደረገውም ይኸው ውጤታማ ሥራችን እንደሆነ ያውቁታል። ስለዚህም ብዙ ነገሮቿ ሲከሽፉ የግብጽ ዋነኛ ስራ ኢትዮጵያን የሚቃወሙትን መደገፍ፣ የሰላም እጦት በአገሪቱ እንዲንሰራፋ ማድረግ ነው። ይህ ከሆነ ህዝቡ ለልማት አያስብም። የማያለማ ከሆነ ደግሞ ውሃውን የመጠቀም አቅምም አይኖረውም። ይህንን ማሰባቸው ግን ሞኝነት ነው።
ግብጾች ለዘለቄታው የውሃ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉት በሚሰሩት ሴር ሳይሆን በህዳሴ ግድቡ መጠናቅ ነው። ኢትዮጵያን በማደናቀፍ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ጋር ተባብሮ በመስራት ነው። ምክንያቱም እኛ ውሃው ላይ ነንና ምንም ማድረግ እንችላለን። 86 በመቶ የሚሆነውን መልቀቅም ማፈንም የምንችለው እኛ ብቻ ነን ። ውሃው ከሚመነጭበት ህዝብ ጋራ መጋጨት የትም አያደርስም። ስለሆነም ወቅታዊ ጥቅማቸውን ትተው ዘለቄታዊ ደህንነታቸውን ተባብሮ በመስራት ማስተማመኛ መስጠት ያስፈልጋቸዋል። ሁልጊዜ ወተት ማለትም አይገባም ። ላሚቱን መንከባከብ አስፈላጊ ነው ።
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፓርላማ ላይ ቀርበው ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት እደማይጎዳቸው ተናግረዋል፤ ይህን ለምን አሉት ፤ ያለውስ አንድምታ ምንድነው?
አምባሳደር ኢብሪሂም፡– ቀደም ሲል በሰሩት ሥራ ኢትዮጵያን የሚያንበረክኩ መስሏቸው ነበር ። ግን ውድቀት እንጂ ውጤት አላመጡም። እውነታውም በሚሰራው ሥራ እየተገለጠ መጥቷል። ይህ ደግሞ ተጨማሪ ስጋት ውስጥ ይከታቸዋል። ምክንያቱም ህዝባቸው እውነቱን ሲረዳ ፊት ይነሳቸዋል። እናም ይህንን ለመሸፈንና ያሴሩት ሴራ እንዳይታወቅባቸው ለማድረግ ብዙ ነገሮችን መልስ መስጠት ይኖርባቸዋል። የዛሬ ተግባራቸውም ከዚህ የመጣ ነው። ብዙ ነገሮች ግልጽ እየወጡ መጥተዋል። ማን ከጎናቸው እንደሚቆምና እንደማይቆምም እየተረዱ ነው። ሥራቸው ትክክል እንዳልሆነም በራሳቸው ምሁራን ጭምር ይፋ እየወጣባቸው ይገኛል። ስለዚህም ነገሩን ማለሳለስ ለነገ የሚሰጡት ጉዳይ አልሆነላቸውም። በዚህም በተሳሳተ መንገድ ህዝቡን ሲመሩት የቆዩት እነርሱ በመሆናቸው ለህዝባቸው ለመንገር ሲሉም ምልከታቸውን ቀይረዋል።
አዲስ ዘመን፡- ከአባይ ወንዝ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ የሚነሱት የ1902 እና የ1903 የሱዳንና የግብፅ ሳምምነቶች ናቸው፤ እነዚህ ስምምነቶች ኢትዮጵያን ይመለከታሉ?
አምባሳደር ኢብሪሂም፡- በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የ1903 ሳይሆን የ1902 ላይ በአንቀስ ሦስት የተቀመጠውን ማንሳት የዘወትር ተግባራቸው ነው። ይህ አንቀጽ ከአጼ ምኒልክ ጋር ሲደራደሩ ያስገቡት ሲሆን፤ ከሰነዱ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለውም። የሚለውም ‹‹ከእንግሊዝ መንግስት ወይም ከሱዳን ፈቃድ ሳያገኝ ጣናን፣ አባይን፣ ባሮ አኮቦ የመሰሉትን ወንዞች መገደብ ማድረግ አይችልም›› ነው ። ኢትዮጵያ ይህንን ስምምነት እየተቃረነች ነው የሚሉትም በዚህ የተነሳ ነው ።
ነገር ግን ይህ ሀሳብ በፊትም ሆነ አሁን ገዢያችን እንዳልሆነ ጠንቅቀው ይረዱታል። ምክንያቱም አለማቀፋዊ ህጉ ጨምሮ ኢትዮጵያን የውሃ መብት የመጠቀም ሁኔታን አይከለክላትም። በሚሰራው ሥራና ድርድርም መንገድ እንደሌላቸው በግልጽ እያዩት መጥተዋል። የመመለስም አዝማሚያ እያሳዩ ይመስላሉ።
አዲስ ዘመን፡- አለም አቀፉ ህግ የውሃ የመጠቀም መብትን እንዴት ያስቀምጠዋል፤ ኢትዮጵያስ ከዚህ አንጻር ምን ዋስትና አላት?
አምባሳደር ኢብራሂም፡- ፍትሀዊ ውሃን የመጠቀመብት የአገራት ግዴታም የአለም ህግም ነው። በዚህም መብቷን መቼም ማንም ሊነፍጋት አይችልም። በ1997 የአለማቀፉ ስምምነት ላይም የተቀመጠው ይኸው ነው። በእርግጥ ኢትዮጵያም ሆነች ግብጽ አባል አይደሉም። ሆኖም አለም የማይገዛው አካል ስለሌለ ይጠቀሙበታል፤ ይዳኙበታልም። እናም በዚህ ህግ መሰረት መብት መብት እንደሆነ ተደንግጓል ። ድርድሩ ሳይቀር እየተካሄደ ያለው ይህንን መርህ በመከተል ነው ። ስምምነቱም ቢሆን አሁን በሚደረገው ውስጥ ተካቷል።
አዲስ ዘመን፡- በአለም ላይ ከ250 በላይ ድንበር ተሸጋሪ ወንዞች አሉ፤ ለመሆኑ በእነዚህ ላይ የተካሄዱ የልማት ስራዎችም ሆኑ በተጋሪ ሃገራቱ መካከል ሲደረጉ የነበሩ የድርድር ሂደቶች ምን ይመስላሉ? ከእነዚህስ ምን እንውሰድ?
አምባሳደር ኢብራሂም፡– አለሙን የአለሙ ህግ ገዝቶት ብዙ አትርፏል ። ልማት በጋራ ሲሰራ ምን አይነት ተጠቃሚነት እንዳለም አሳይቷል። በተለይ በልማቱ መረጋጋት እንደሚመጣ በግልጽ ያሳዩ ብዙ አገራት አሉ። ልዩ የሆነው እኛ ጋር ብቻ ነው። እነርሱ ቁጭ ብለው ተደራድረው አንተ ይህንን ያህል ውሰድ ይባባላሉ ። እኛ ጋራ ግን ያለው በግብጽ አካሄድ ጎዶሎነት ብዙ ነገሮች የተወሳሰቡ መስለዋል። የበታች ተፋሰስ አገር ሆና ፈተና የደረሰባት አገር የለችም። ውሃ የሚሰጠውን አካል አንተ ከውሃው መጠቀም አትችልም ያለችም ግብጽ ብቻ ነች። ፍትሀዊነት አለማቀፋዊ ነው ። መልማትም እንዲሁ። ሆኖም ህጉን ቢያውቁትና ቢያምኑበትም ከታሪክ የመጠቀም መብቱ የእኛ ነውና አትችሉም ይላሉ።
ህጉ ወንዙ የሚነካው አገር በሙሉ ተወያይቶ የመጠቀም መብቱን ያስከብራል ይላል። ሆኖም እአአ በ1959 ግብጽና ሱዳን ብቻቸውን በኢትዮጵያ ውሃ ዙሪያ ተስማምተው ነበር። አሁንም ያንን ተቀበሉ ነው ጫና እያሳረፉ የሚገኙት። ነገር ግን ይህ ደግሞ አይደለም በባለቤቷ በተጋሪው እንኳን ቢሆን አይቻልም። አንድ አገር በማያምንበት ባልተሳተፈበት ፤ ፍላጎቱን ባልገለጸበትና ስምምነቱን ባላደረገበት ሁኔታ የእኛን ተቀበል ሊባልም አይችልም። ይህ ተግባር ሲከናወንም የኢትዮጵያ መንግስት ተቃውሞ ነበር ። እንደውም ጊዜ ሲኖረን እንደምንሰራው ሁሉ ተነግሯቸዋል ።
አዲስ ዘመን፡- በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከውጪው የሚደረገውን ጫና እንዴት ያዩታል?
አምባሳደር ኢብራሂም፡- ጫናው ከፍተኛ በሚባል ደረጃ አለ። ይህ ደግሞ ግብጾች አለም በተሳሳተ መልኩ እንዲረዳው ማድረግ በመቻላቸው የተፈጠረ ነው። ይሁን እንጂ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተረባርቦ ነገሩን ማሳወቅ ሲጀምር ስህተት መሆናቸውን ወደ መረዳቱ ገብተዋል። አንዳንዶች ከዚህ በተለየ መልኩ ቢያዩትም። ከህግ ውጪ እየተጓዙ እንደሆነ ሲረዱ ተስማሙ ወደማለቱም የገቡት ለዚህ ነው ። እኛ የምንለው ውሃው የጋራ ነው። እነርሱ ደግሞ የእኛ ብቻ ነው ነው ። ከዚህ አንጻር ለመስማማት አዳጋች ሆኗል ።
የዓለም አቀፉ ህግ የግብጽን ፍላጎት አሟሉ እያለ አይደለም። ከግብጽ ጋር ተነጋገሩ እንጂ። ይህንን ይዘን እንነጋገር ስንልም በድፍኑ ውሃው የእኛ ነው የሚል ሀሳብ ብቻ ያቀርባሉ። ሲቀጥል እኛ የምንነጋገረው በሙሌቱ ዙሪያ እንጂ በኦፕሬሽኑ ወይም በአለቃቀቁ አይደለም። አለቃቀቁ ከፍትሀዊ ክፍፍሉ ጋር ይያያዛልና ሁኔታውን በስራው ሂደት እየወሰነው የምንጓዘው ነው። ይህንን ሲሰሙም ሄደው ያለቅሳሉ። ከአረቡም ሆነ ከአውሮፓው ጋር የሚያቆራኛቸው አለና ያንን ተጠቅመው ይጮሀሉ። ከዚህ በተጓዳኝ ህግ ማለት በተለይም አለም አቀፍ ህግ ከሀይል ሚዛን ጋር ይያያዛል። በዚህም ጠንካራ ሆነን እስካልተገኘን ድረስም እንበለጣለን።
አዲስ ዘመን፡- ሱዳን ከህዳሴው ግድብ ጋር ተያይዞ የምታሳየው አቋም ተለዋዋጭ ነው ምክንያቱ ምንድነው ይላሉ?
አምባሳደር ኢብራሂም፡- የህዳሴ ግድቡ ለሱዳን 20 ወይም 30 ኪሎሜትር ነው የሚርቀው። በዚህም ግድቡ የሱዳን ውሀ ማጠራቀሚያ ተደርጎም መወሰድ አለበት። ተጠቃሚነትም ከእርሷ ውጪ ማንም ሊያገኝ አይችልም። ምክንያቱም እርሷ በሚሊዬኖች የሚቆጠሩ የእርሻ መሬት ያላቸው ናቸው። ይህንን በተሸለ ሁኔታ ለማረስ ደግሞ ውሃ ግድ ነው። እናም ውሃውን መጠቀም ከቻሉ አካባቢያቸውን ብቻ ሳይሆን ሌሎችን ጭምር መመገብ ይችላሉ።
ሱዳን በነዳጅ የታወቀች ነበረች ። አሁን ግን ይህ ነገሯ በብዙ መልኩ ቀንሷል። ስለዚህም ያላት ማስተማመኛና አማራጭ እርሻዋን የተሸለ ማድረግ ብቻ ነው ። ከዚህ በተጓዳኝ ክረምት ላይ እንደሚያጥለቀልቃት ታውቃለች። እናም በዚህ ብቻ በሁለት መልኩ ትጠቀማለች። የመጀመሪያው ከመሰደድ ፤ ከሚጠፋው ሀብት ትድናለች፤ የአሸዋ ደለልን ለመጥረግ በዓመት የምታወጣውን 50 እና 60 ሚሊዮን ዶላር ታድናለች ።
የአስዋን ግድብንም ቢሆን ዕድሜ 100 ዓመት ይጨምራል። በበርሃ የሚተነውን ውሃ መጠን ይቀንሰዋል። የአስዋን የትነት መጠን በዓመት ከ15 እስከ 16 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ነው። የህዳሴ ግድብ ግን ሸለቆ ውስጥ በመሆኑ ለትነት ስለማይጋለጥ ከሁለት ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር አይበልጥም። እናም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ለሱዳን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ለተፋሰሱ አገራት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ጠንቅቃ ታውቃለች።
መጀመሪያ አካባቢ እንደሚጠቅማቸው ተረድተው ዶዘር ጭምር ሲያግዙ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ይሁን እንጂ ይህንን እንዳትቀበለው የሚያደርጋት ከግብጽ በኩል ጫና ያርፍባታል ። ከእነዚህ መካከልም የባለስልጣኑ ከግብጽ ጋር ያላቸው ቀረቤታ አንዱ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ሁለተኛው የውሃው ሙሌት አሁን ኢትዮጵያ በምታደርገው ድርድር ላይ የሚያሳርፈው ጫና አለ ?
አምባሳደር ኢብሪሂም፡– የለም። አሁን ብቻ ሳይሆን ወደፊትም አይኖርም። ምክንያቱም ግድቡ ጊዜውን ጠብቆ ይሞላል። ይህ ደግሞ በእኛ እምነት ጉዳዩ መሰረት እንዲይዝና የኢትዮጵያን የመደራደር አቅም ከፍ እያደረገው ይሄዳል። ተሰሚነታችንም ይጨምራል ። ከዚህም በላይ በተግባር እንደማንጎዳቸው የምናሳይበት ነው። ወደፊትም ባለስልጣኑም ሆነ ህዝቡ በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን ምልከታ ይቀይራሉ ። እንዳማይጎዳቸውም የሚያረጋግጡበት ይሆናል። ምክንያቱም ውሃው አይቋረጥም ፣ በተሸለ ምጥጥን ይሄዳል እንጂ ።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በሃገር ውስጥ እዚህም እዚያም የሚነሱ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራሉ?
አምባሳደር ኢብራሂም፡- ከባድ ተጽዕኖ ይፈጥራል የሚል እምነት የለኝም። ምክንያቱም ህዳሴ የግለሰቦች ፣ የአንድ ብሔር ወይም ሀይማኖት ሳይሆን የሁሉም ዜጋ ነው። በዚህም ሁሌ አንድነት ይጠናከርበታል እንጂ ልዩነት አይሰበክበትም። ከዚህ አንጻርም ችግሮቻችንን በውይይት እንድንፈታ ያቀራርበናል። የአንድ አገር የዲፕሎማቲክ አቅም የሚታየው የውስጥ ጉዳይ እንደሆነ ግልጽ ነው። ስለዚህም ውስጣችንን ጠንካራ ካላደረግን ከባድ የሚሆንበት ሁኔታ ይፈጠራል። የጋራ ጉዳዮቻችንንም እንዳናይ እንሆናለን። ውስጥን ለማጠናከር ገንዘብ አያስፈልግም፤ የውጪ ጫናንም ለመቀነስ እንዲሁ። የሚጠይቀን በጋራ መኖር ብቻ ነውና ይህንን ማድረግ ይገባናል። አሁን ባለው ሁኔታ የውስጣችን አለመረጋጋት ከባድ ፈተና ላይጥልብን ይችላል። ሆኖም ችግር አለውና ይህንን አውቆ ማስተካከል ለነገ የሚባል መሆን የለበትም።
ህዳሴ ስድስት ክልሎችን የሚያካትት ነው። ስለዚህም ይህ አይመለከተኝም የምንለው ጉዳይ እንዳይሆን ያስተሳሰረንም ነው። ግጭቱም ቢሆን መሰረት የሚያደርገው እነዚህ ክልሎች እንዳይለሙ በመፈለጉ የሚተገበር ነው። የውጪው ሀይል ፍላጎቱ እነርሱን እንድናስፈቅድ ነው። ይህን የሚፈልግ አንድም ኢትዮጵያዊ ይኖራል ብዬ አላምንም። ኢትዮጵያ የቅኝ ግዛት ስምምነቶችንም መቼም ቢሆን አትቀበልም። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር የወንድማማቾች ችግር ስለሆነም በ መነጋገር ይፈታል ። እናም ይህ በየአቅጣጫው የሚደረገው ግጭትም ከዚህ አንጻር ያከትምለታል ።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ምሁራን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ ፕሮጀክት ነው፤ በዚህ ላይ ድርድር ማድረግ ተገቢ አይደለም፤ ስለዚህ ከመነሻም ለድርድር እድል መሰጠት አልነበረበትም ይላሉ፤ይህ ሀሳብ እንዴት ይታያል?
አምባሳደር ኢብራሂም፡- ይህ ሀሳብ መጀመሪያዎቹ አካባቢ የነበረ ነው። ብዙ ድርድርም ተደርጎበታል። ነገር ግን መንግስትን ጨምሮ የተወሰደው አቋም እኛ አካባቢው ላይ ሰላም መፍጠር አለብን፣ ተሳስበን እንስራው በሚል ለመደራደር ተወስኗል። በእርግጥ ሱዳንና ግብጽ ግድባቸውን ሲሰሩ እኛን አላማከሩም። እኛም ማማከር ላይኖርብን ይችላል። ነገር ግን በህዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት የጠነከረ ነውና ያንን ማሻከር ተገቢነት እንደሌለው ታምኗል ። በዚያ ላይ ላለመደራደር ጠንካራ መንግስት መሆንን ይጠይቃል። ምንም ስለማይጠይቀን። ሆኖም ይህ ስላልሆነም መልካሙን በማሰብ ውይይቱ ይሻላል ወደማለቱ ተገብቷል።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ እጅግ አድርገን እናመሰግናለን።
አምባሳደር ኢብራሂም፡- እኔም አመሰግናለሁ ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2013