ፍቼ ጨምበላላ በቁሙ የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል ነው። በእርግጥ የዘንድሮው ሲዳማ ፍቼ ጨምበላላ የዘመን መለወጫ በዓል በኮቪድ-19 ምክንያት በአደባባይ ለመከበር አልታደለም። ከወትሮው በተለየ መንገድ በየቤቱና በየተቋማቱ ነው ተከብሮ የዋለው። በተጨማሪም በዓሉ መገናኛ ብዙኃንን በስፋት በመጠቀምና ሕዝቡ ከበዓሉ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን፣ ሲወርድ ሲዋረድ አባቶች ጠብቀው ያስተላለፉለትን የፍቼ ጨምበላላ ዘመን አይሽሬ ፋይዳዎችንና ጠቃሚ እሴቶችን እንዲያገኝ በማድረግ ይበልጥ ዲጅታላዊ ሆኖ እንዲከበር መንግሥትና የሃገር ሽማግሌዎች በጋራ በተግባቡት መሠረት ከአደባባይ ይልቅ በይበልጥ ዲጅታላዊ በሆነ መንገድ እንዲከበር ተደርጓል። ከዚህ ባለፈ ግን ከሰሞኑ ለበዓሉ አከባበር የሚዲያ ሽፋን ለመስጠት ሐዋሳ ከተማ በተገኘንበት አጋጣሚ በፍቼ ጨምበላላ በዓል ውስጥ የሚገኙ ለታላቁ ፍጡር ለሰው ልጅና በጥቅሉ ለተፈጥሮ ደህንነት የላቀ ፋይዳ ያላቸውን እነዚህን መልካም ዕሴቶች የማወቅ ዕድል በማግኘቴ በዓሉን ከበዓልነት ባሻገር በፍልስፍናዊ መነጽር በመመልከት በውስጡ ያሉትን ሰናይ ዕሴቶች ላካፍላችሁ ወደድኩ።
መልካምነት፡- ከሁሉም የላቀው የሰው ልጆች ዕሴትበጊዜያዊው የምድራዊ ኑሮም ሆነ በዘላለማዊው ሰማያዊ ህይወት፣ በሚያልፈውም በማያልፈውም፣ በዓለማዊውም በመንፈሳዊውም ዓለም ከመልካምነት በላይ ለሰው ልጆች የሚጠቅም ነገር አለ የሚል ዕምነት የለኝም። ሃብት፣ ዝና፣ ስልጣን፣ ዕውቀትም ቢሆን ደግነት ከሌለ ብቻቸውን ለሰው ልጆች የሚጠቅሙ አይደሉም። መልካም አስተሳሰብ በሌለበት እነዚህ ሁሉ የማይጠቅሙ ናቸው፤ ይባስ ብሎ ሊጓጉም ይችላሉ። ለበጎ ዓላማ ካልዋሉና ለሰው ልጆች ህይወት መሻሻል አንዳች ፋይዳ ለማበርከት ታስቦ የሚደረጉና የሚፈጸሙ ካልሆኑ ለሰው ልጆች ያስፈልጋሉ የሚባሉ ማናቸውም ነገሮች ከጥቅማቸው በላይ ጉዳታቸው፣ ከልማታቸው ጥፋታቸው ሊያመዝን ይችላል። መልካምነት ካለ ሃብት ከራስ አልፎ ለሌሎች የድህነት መንገድ ይሆናል። ዕውቀትና ሥልጣንም እንደዚሁ ከፍ ያለ ፋይዳ ይኖራቸዋል። በጎነትን አልመው የማይደረጉ፣ በመልካም እሳቤ ለመልካም ዓላማ የማይውሉ ከሆነ ግን በተቃራኒው ለጥፋት ይውላሉ፡፡
የፍቼ ጨምበላላ ሲዳማ ዘመን መለወጫ በዓልንም ከበዓላዊ ክዋኔው ባሻገር በፍልስፍና መነጽር እንድመለከተው ያስገደደኝም ይህንን እውነት በውስጡ ማየት በመቻሌ ነው። ማለትም ከሁሉም በላይ ለሰው ለጆች ጠቃሚና አስፈላጊ በሆነው የመልካምነት ዕሴት ላይ የተመሠረተና ለሰው ልጆች ህይወትና ደህንነት ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸውን የሞራል ዋጋዎች (Moral Values) የሚያስተምር በመሆኑ ነው። ፍቼ ጨምበላላ ለሰው ልጆች ጠቃሚ የሆኑ እንዲህ ዓይነት በርካታ ዕሴቶችን በውስጡ አቅፎ የያዘ ቢሆንም ዋና ዋናዎቹ ግን ፍቅር፣ ይቅርታ፣ ሕብረትና መቻቻል በሚል ጠቅለል ብለው ሊቀርቡ ይችላሉ።
የበዓሉና የዕሴቶቹ ባለቤቶች ሲዳማዎች የሚያረጋግጡትም ይህንኑ ነው። አቶ ጃጎ አገኘሁ የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ናቸው። እርሳቸው ፍቼ ጨምበላላን፤ “የሲዳማ ብሔር ከጥንት ጀምሮ ዘመኑን የሚቆጥርበትና የዘመን መለወጫ በዓል ሲሆን በውስጡ ለሰው ልጆች ጠቃሚ የሆኑ ድንቅ ዕሴቶችን ያቀፈ፤ በዋናነት ፍቅርን፣ አብሮነትና መከባበርን፣ መቻቻልንና ይቅር ባይነትን የሚሰብክ፤ በአጠቃላይ ለሰው ልጆች መልካም ነገርን በማድረግ ላይ የተመሠረተ አባቶች ለዘመናት ጠብቀው ለትውልድ ያስተላለፉት ትልቅ ባህላዊ ቅርስ ነው” በማለት ይገልጹታል።
በመሆኑም በዓሉ ለሰው ልጆች ካለው ከፍተኛ ፋይዳ የተነሳ ከሲዳማ ሕዝብ አልፎ የሁሉም ሃገራችን ሕዝቦችና የመላው ዓለም ቅርስ ሆኖ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ተመዝግቧል። በዚህ ረገድ በተለይም አሁን በእኛ ሃገር ውስጥ ካለው ሁኔታ አኳያ ዕሴቶቹ ጥቅም ላይ ቢውሉ ሕዝባዊ ወንድማማችነትን በማጠናከርና ሰላምን በማስፈን እንደ ሃገር ያሉብንን ችግሮች ለመፍታት ጉልህ ፋይዳ ያለው መሆኑንም ያብራራሉ። እስኪ በትልቁ የመልካምነት ዕሴት ላይ ከተመሠረቱት የፍቼ ጨምበላላ ሰናይ ዕሴቶች መካከል ዋና ዋናዎቹን በምጥን ማሳያዎች አስደግፈን በአጭር በአጭሩ በወፍ በረር እንመልከታቸው።
ፍቅርና ርህራሔ
ፍቅር በዓለም ላይ ካሉ ኀልዮቶች ሁሉ የላቀው ነው። ፍቅር የመላ ዓለሙ ታላቅ ሚስጢራዊ ኑባሬ ነውና የሰው ልጆችን ጨምሮ ማናቸውም ፍጥረታት ከፍቅር ጋር አንዳች ሚስጢራዊ ውህደት ያላቸው ይመስላል። ብቻ ስለ ፍቅር ብዙ ተብሏል፤ ያም ሆኖ የፍቅርን ትርጉም በቃላት ለመግለጽ በራሱ ብዙም የማይሳካ ነው። ምናልባት በምድራዊው መለኪያ የፕላኔታችን ታላቁ ሰው እየተባለ የሚጠራው ታላቁ ሳይንቲስት አልበርት አንስታይን በአንድ ወቅት ለሚወዳት ሴት ልጁ በፃፈው ደብዳቤ ለፍቅር የሰጠው ትርጉም እስከ ዛሬ ከተባሉት ሁሉ ፍቅርን የበለጠ የሚገልፀው ስለሚመስለኝ ካነሳሁት ጋር ይበልጥ አብሮ ይሄዳል የምለውን ብቻ ትንሽ ቀንጭቤ ልጠቅሰው ወደድኩ።
አንስተይን በዚያ ደብዳቤው ውስጥ እንዲህ ይላል “…ፍቅር ብርሃን ነው፤ የሚሰጡትንና የሚቀበሉትን ዕዝነ ልቦና የሚያበራ። ፍቅር ስበት ነው፤ ሰዎች በሌሎች ሰዎች እንዲሳቡ የሚያደርግ ስሜት ይፈጥራልና። ፍቅር ኃይል ነው፤ መልካም ነገሮች እንዲበዙልን በማድረግ የሰው ዘር በጭፍን ራስ ወዳድነት ውስጥ ተውጦ ከምድረ ገጽ እንዳይጠፋ ይታደጋልና! …..ምናልባትም ዓለምን በጥፋት ጎዳና ላይ እየመሯት ያሉትን ጥላቻን፣ ራስ ወዳድነትንና ስግብግብነትን ሙሉ በሙሉ ከምድረ ገፅ ለማጥፋት የሚያስችል ከፍተኛ አቅም ያለው መሳሪያ፤ የፍቅር ቦምብን ለመስራት እስካሁን አልተዘጋጀን ይሆናል። ….ዝርያችን በምድር ላይ እንዲሰነብት ከፈለግን፣ ህይወት ትርጉም እንዲኖራት ከወደድን ዓለምንና በውስጧ ያሉ ፍጡራንን ሁሉ መታደግ ከፈለግን፣ ፍቅር አንድና ብቸኛው መፍትሄ ነው”።
ፍቼ ጨምበላላን እንድወደው ካደረጉኝና ከበዓልነቱ ባሻገር በፍልስፍናዊ መነጽር እንድመለከተው ካስገደዱኝ መግፍኤ ሃሳቦች መካከል አንደኛው ምክንያትም ይኸው ነው፤ ማለትም ታላቁ የሳይንስና የፍልስፍና ሊቅ አንስተይን እንዳለው መልካም ነገሮች እንዲበዙልን በማድረግ የሰው ዘር በጭፍን ራስ ወዳድነት ውስጥ ተውጦ ከምድረ ገጽ እንዳይጠፋ ሊታደገን የሚችለውን ፍቅርን የሚሰብክ መሆኑ። ፍቼ ጨምበላላ ሰዎች እርስ በእርሳቸው እንዲፈቃቀሩ ያዛል። ሲያከብሩትም በተግባር በፍቅር ውስጥ እንዲሆኑ ያደርጋል። ይህም ብቻ አይደለም በፍቼ ጨምበላላ ውስጥ ያለው የፍቅር ዕሴት ከሰው ልጆች አልፎ ለእንስሳትና ለተፈጥሮ ህልውናም ያስባል፤ ለሰው ልጆችም፣ ለሚኖሩባት ምድርም ይሳሳል፣ ይራራል።
እናም እንደ ብዙዎቹ በዓለም ላይ ያሉ ባህላዊና ሃይማኖታዊ በዓላት በዓሉ በእርድ አይከበርም። ለበዓል ተብሎ እንኳንስ ከብቶች ለምግብነት ሊታረዱ በዓሉ በሚከበርባቸው ዕለታት ሥጋ አይበላም፣ ቀደም ብሎ በቤት ውስጥ የነበረ ሥጋ ካለም ከቤት ወጥቶ እንዲሰነብት ይደረጋል። እንዲሁም ከብቶች በልዩ ሁኔታ ከአሞሌ ጋራ የተዘጋጀ ምግብና መጠጥ ይቀርብላቸዋል፤ በለምለም ቦታ እንዲውሉ በማድረግ ፍቅርና እንክብካቤ ይደረግላቸዋል። እንደዚሁ የተፈጥሮ አካላት የሆኑት ዕፅዋትም በበዓሉ አከባበር ሰሞን ፍቅር ይሰጣቸዋል፤ ሳሮችና ዛፎች አይቆረጡም። ለማገዶ የሚያስፈልጉ እንጨቶችም ከበዓሉ ቀደም ብሎ ከደረቅ እንጨት እንዲዘጁ ይደረጋል። ይህም ፍቼ ጨምበላላን ፍቅር የሰው ልጆችን በራስ ወዳድነትና በእርስ በእርስ ሽኩቻ ምክንያት ከሚመጣው ብቻ ሳይሆን ለተፈጥሮ ባለማሰብና ባለመጨነቅ የተነሳ ከሚከሰተው ጥፋትም የሚታደጋቸው መሆኑን የተገነዘበ ምጡዕ ትውፊት ያደርገዋል፡፡
ቆሞ ቀርነትን በይቅርታ የማሸነፍ ጥበብ
ከዋና ዋናዎቹ የፍቼ ጨምበላላ ጠቃሚ ዕሴቶች መካከል ከፍቅር ቀጥሎ ሌላው ብዙ ሊባልለት የሚገባው ባለብዙ ዋጋው ድንቅ የሞራል ዕሴት ይቅርታ ነው። ይህ የይቅርታ ዕሴት “ባለፉ ጊዜያት በህይወት ውስጥ የተከሰቱ ማናቸውም ዓይነት ስህተቶችን፣ ጥፋቶችንና ለሰው ልጆች የማይጠቅሙ እሳቤዎችንና ድርጊቶችን አሽቀንጥሮ በመጣል በአወንታዊ አስተሳሰብና በአዲስ የተስፋ ብርሃን ዛሬንና ነገን መልካም ማድረግ ይገባል” በሚል መርህ ላይ የተመሰረተ ነው። ይህም ለህልውናቸው ደህንነት ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጆች ሁለንተናዊ ዕድገትና መሻሻል እጅግ አስፈላጊ ነው። ለምን ቢሉ የሰው ልጅ ትናንትና በተከሰቱ ችግሮች ላይ ብቻ ተቸንክሮ ሁሌም እርሱን እያብሰለሰለ የሚቀጥል ከሆነ በእጁ ላይ ያለውን ዛሬንም ሳይጠቀምበት ይቀራል። ከፊት ለፊቱ ያሉትን ነገዎቹንም በዚሁ መንገድ ያባክናል። እናም በምግብ እጥረት የተነሳ በድሃ አገራት ልጆች ላይ እንደሚከሰተው አካላዊ መቀንጨር ሳይሆን በይቅርታ እጥረት ባለፈው ነገር ላይ ተቸክሎ በመቅረት በሰዎች ላይ የአስተሳሰብ መቀንጨር ይፈጥራል።
ይህም ካለፈው ተምሮ ዛሬን ለማሻሻል የሚደረገውን ተፈጥሯዊውን የሰው ልጆች የመሻሻልና የማደግ መብት ያስተጓጉላል፤ ከእድገት ኋላ ያስቀራል፤ ቆሞ ቀር ያደርጋል። በፍቼ ጨምበላላ ዘመን መለወጫ በዓል ግን “ፊጣራ” ተብሎ በሚጠራው በዋዜማው ዕለት ቂም፣ ጥላቻ፣ በቀልና ማናቸውም ለሰው ልጆች የማይጠቅሙ በአሮጌው ዓመት የተፈጸሙ ማናቸውም መልካም ያልሆኑ ነገሮችና አስተሳሰቦች ተጠራርገው ይባረራሉ። ሁሉም በየአካባቢው ካለፉ መጥፎ ነገሮችና በደሎች ነፅቶ ይቅር ተባብሎ በአዲስ ተስፋ ወደ አዲስ ዓመት ይሸጋገራል። ይህንንም “ሁሉቃ” ተብሎ በሚጠራው ከእንጨት በተሰራ በር ውስጥ ሁሉም በየአካባቢው ከሁሉም የቤተሰቡ አባላት ጋር በውስጡ በማለፍ በሚደረግ ስነ ስርዓት ይፈጽሙታል። ከዚያም የሲዳማ ብሄር የከበረ ማዕድ የሆነውና በቂቤ የረሰረሰ ቆጮና ወተት የሚዘጋጀውን “ቡርሳሜ” ወይም “ሻፌታ” የተባለውን ባህላዊ ምግብ ቤተሰቡ በአንድነት እየተመገቡ ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ በሚጀምሩት ሥነ ስርዓት በዓሉ መከበር ይጀምራል።
መከባበርና መቻቻል፣ አብሮነትና መተባበር
ሌላው በዚች አጭር ቅኝታችን ልናነሳው የወደድነው የፍቼ ጨምበላላ የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል የመከባበርና መቻቻል፣ የአብሮነትና መተባበር መልካም ዕሴቱ ነው። አብሮነት፣ ህብረትና አንድነት ቀላል ነገር አይደለም። “ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም” እንዲል ፈጣሪ አምላክ ራሱ ሰው ገና ሲፈጠር አብሮ እንዲኖር ነው የተፈጠረው። ታላቁ ግሪካዊ የፍልስፍና ሊቅ አሪስቶትልም “ሰው ማህበራዊ እንስሳ ነው” ብሎናል። ገለጻውን ቀየር አድርጎ “ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለም” የሚለውን እያስረገጠልን ነው። በአጭሩ አብሮ መኖር ለሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ነው። በቤተሰብ፣ በማህበረሰብ፣ በሃገር፣ በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰው የሚኖረው በማህበርና በህብረት ነው። ህብረት ደግሞ ኃይል ነው፤ የሰው ልጆች ይበልጥ ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ አስችሏቸዋልና። አንድነትና ሕብረት ትርጉሙና ፋይዳው ይኸው ነው፤ ብዙም ማብራሪያ አያስፈልገውም። ፍቼ ጨምበላላም መሠረቱ አንድነት፣ ህብረት መከባበርና መቻቻል ነው። ዕሴቱም ይህንኑ አጥብቆ ያስተምራል። ለአብነት በዋናው የበዓሉ ዕለት የሚከወኑ ሥርዓቶች ሁሉ ይህንን የሚገልጹ ናቸው።
በዋዜማው በቤተሰብ ደረጃ የብሔሩን የከበረ ማዕድ በጋራ በመቋደስ ከቤት በህብረት መከበር የሚጀመረው በዕለቱ ዕለት ሁሉም በባህል ልብሱ አጊጦ ወደ ትልቁ የጋራ አደባባይ ጉዱሌ በመውጣት እንደ ሕዝብ በጋራ ይከበራል። እንደየ ዕድሜ ክልሉ በሚከፋፈሉ በተለያዩ ዓይነት ባህላዊ ጭፈራዎች በህብር ይጫወታሉ። ልጆች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ጎልማሶች፣ አዛውንቶች፣ ሽማግሌዎች እርስ በእርስ “ኢሌ፣ ኢሌ” “እንኳን አደረሳችሁ” በመባባል፣ በአብሮነትና በመፈቃቀር በዓሉን ያደምቁታል። የሃገር ሽማግሌዎች ምርቃታቸውን ይሰጣሉ። እነዚህ ሁሉ በጋራ የሚከናወኑ ሥርዓቶች ደግሞ ከምንም በላይ መከባበርንና መቻቻልን ይጠይቃሉ። ይህም መልሶ ኃይል የሆነውን ህብረት ይፈጥራል። እናም በእርግጥም ድንቅ ነው፣ ይበል፣ ይቀጥል እያልን ድንቅ በሆኑ የፍቼ ጨምበላላ ሞራላዊ ዕሴቶች ላይ ያደረግነውን ፍልስፍናዊ ምልከታችንን በዚሁ ቋጨን።
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2013