-አቶ ቶማስ ቱት ፑክ የጋምቤላ ክልል የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ
ስድስተኛው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ሊካሄድ የቀረው ጥቂት ጊዜ ነው። ምንም እንኳ ለመምረጥ የሚያስችለውን ካርድ ለመውሰድ የተቀመጠው ጊዜ ባለፈው አርብ የተጠናቀቀ ቢሆንም መራጩ ህዝብ ግን የመመረጥ መብቱን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችለውን የመራጭነት ካርድ በእጁ ካስገባ ሳምንታት ተቆጥረዋል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድም የተለያዩ መረጃዎችን ወደህዝቡ እያደረሰ ይገኛል። አዲስ ዘመንም ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በየክልሉ ያለው የሰላምና የጸጥታው ጉዳይ ምን እንደሚመስልና ያለው ዝግጅት እንዴት እየሄደ እንደሆነ የየክልሎችን የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊዎችን እያነጋገረ መረጃውን ለህዝቡ በማድረስ ላይ ይገኛል። ዛሬም የጋምቤላ ክልል የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ከሆኑት ከአቶ ቶማስ ቱት ፑክ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጎ እንደሚከተለው አጠናቅሮ አቅርቧል፤ መልካም ንባብ ይሁንልዎ።
አዲስ ዘመን፡- ስድስተኛው አገራዊና ክልላዊ ምርጫን ለማካሄድ መራጮች ካርዳቸውን ወስድዋል፤ የመራጮችን እንቅስቃሴ በተመለከተ በክልሉ በእስካሁኑ ከሰላምና ከጸጥታው አኳያ የነበረው ሂደት ምን ይመስል ነበር?
አቶ ቶማስ፡- ክልላችን ወደ 431 ምርጫ ጣቢያዎች አሉት። በእነዚህ ምርጫ ጣቢያዎች ምዝገባ ከመጀመሩ በፊት የምርጫ ቁሳቁስ የማጓጓዝ ሂደቱ ነበርና ቁሳቁሱ በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች እንዲጓጓዝ በአግባቡ ተሰርቷል። የመራጩ ምዝገባም በሰላም ተከናውኗል። ከዚህም የተነሳ በእስካሁኑ ሂደት በመራጮች ምዝገባ ያጋጠመን ችግር የለም። እንዲያውም እንደክልል ይመዘገባል ተብሎ ከታቀደው በላይ መራጮች በሰላማዊ መንገድ ተመዝግበው ካርዳቸውን ወስደዋል።
እንደክልላችን ለመምረጥ የሚያስችላቸውን ካርድ ለመውሰድ ይመዘገባሉ ተብለው ይጠበቁ የነበሩት 312 ሺህ ነዋሪዎች ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት ግን የተመዘገቡት የመራጮች ቁጥር ከ400 ሺህ በላይ ሄዷል። ይህም በመቶኛ ሲሰላ ወደ 134 ነጥብ 6 የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ከእቅድ በላይ መሆኑን አመላካች ነው። ስለዚህም በክልላችን ምርጫ አይካሄድም የሚል ምንም አይነት ስጋት የለም።
አዲስ ዘመን፡- ምርጫው የሚካሄደው በዚህ ወር መጨረሻ አካባቢ እንደደሆነ ነው የተነገረው፤ ከዚህ አንጻር ምርጫው ሰላማዊ ይሆን ዘንድ እንደክልል ያላችሁ ዝግጅት እንዴት ይገለጻል?
አቶ ቶማስ፡- በእስካሁኑ እያደረግን ያለው እንቅስቃሴ ምንም የጎላ ችግር አለመኖሩን አመላካች ነው። ችግር እንኳ ያጋጥማል ቢባል በቂ ዝግጅት አድርገናል። በክልላችን ወሰንና ድንበር አካባቢ እስካሁን በነበረው ሂደት ብዙ ስጋቶች ነበሩ። ይሁንና እኛ እንደክልላችን በቂ ዝግጅት አድርገናል። በተለይ በድንበሮቻችን አካባቢ በደቡብ ሱዳን ብዙ ጊዜ በሙርሌ ጥቃት ያጋጥመን ነበር። ሙርሌ የሚፈጽመው ያልተገባ ድርጊት ለምርጫው ስጋት እንዳይሆን በቂ የሚሊሻ ስልጠና አድርገናል። ተጨማሪ የሚሊሻ ኃይል አሰልጥነን ወደድንበር በመላክ እያንዳንዱ ቀበሌ እንዲጠበቅ ተደርጓል። ከእነሱ አቅም በላይ የሆኑና የከፋ ችግር ይኖርባቸዋል ብለን ያሰብናቸው ስፍራ ደግሞ ልዩ ኃይል መድበናል። ስለዚህ በድንበሮች አካባቢ እስካሁን ያጋጠመን ችግር የለም።
በከተሞች አካባቢ ችግር ሊፈጥሩ የሚችሉ ወጣቶች ሊኖሩ ይችላሉና የማጭበርበርና የስርቆት ተግባር እንዳይከሰት በበቂ ሁኔታ የኮሚዩኒቲ ፖሊሲንግ ራሱን እንዲጠብቅ በተጨማሪም በከተማ ፖሊስም ጥበቃ በመደረግ ላይ ነው። ከዚህ ውጭ ግን በአዋሳኝ ክልሎች ለምሳሌ ከኦሮሚያ ክልል ጋር ቄለም ወለጋና ኢሉ አባቦራ ጥሩ መስተጋብር ፈጥረናል። በተለይ ቄለም ወለጋ ሸኔ የሚንቀሳቀስበት ቦታ እንደመሆኑ ችግር ሲፈጠር ሮጠው ወደ ጋምቤላ ይመጣሉ። ይህ ሁኔታ ለምርጫ ስጋት እንዳይሆን ከኦሮሚያ ክልል ጋር በመሆን በቂ ቅንጅት ፈጥረን ችግር እንዳይፈጠር በቂ የሚባል ስራ ሰርተናል። እንዲሁም የጋራ ውይይቶችን አድርገናል። በቀጣይም የተለያዩ የጋራ ውይይቶች ከተለያዩ አዋሳኝ ክልሎች ጋር ማድረጉ ይቀጥላል። ይህ ሁሉ የሚደረገው በምርጫ ዙሪያ ምንም አይነት የሰላም መደፍረስ እንዳይከሰትና እንቅስቃሴው ሁሉ ሰላማዊ እንዲሆን በማሰብ ነው።
ሌላው ከእኛ ጋር የሚዋሰነው የደቡብ ክልል ሲሆን፣ በተለይ እኛ በምንዋሰንበት ጉራ ፈርዳ አካባቢ ችግር ተፈጥሮ እንደነበር የሚታወስ ነው። በዚያም ቦታ ችግር የፈጠሩ አንዳንድ አካላት ሮጠው ወደ ጋምቤላ የሚመጡበት ሁኔታ ስላለ ይህም ለምርጫ ስጋት እንዳይሆን ከደቡብ ክልል ጋር ባለፈው ሚያዚያ ወር ላይ በሚዛን ተፈሪ ከተማ የጋራ ውይይት አድርገናል። በያዘነው የግንቦት ወር አጋማሽ ላይም በድጋሚ ለመወያየት እቅድ ይዘናል። ይህን ያደረግንበት ምክንያት በጉራ ፈርዳ ዲማ፣ ማጂ አካባቢ አንዳንድ ችግሮች እንዳይፈጠሩ በሚል ነው። ስለዚህ በክልላችን በአጠቃላይ ሁሉም ቦታ በሚያስብል ደረጃ ለምርጫ እንደማያሰጋ መናገር ይቻላል። ምርጫው ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሚካሄድ ይሆናል።
በክልላችን ወደስድስት ፖለቲካዊ ፓርቲዎች እንደሚወዳደሩ ታውቋል፤ እነዚህ ፓርቲዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲወዳደሩ የጋራ ውይይት እየተደረገ ነው። አንዳንድ ጥቃቅን ችግሮች የሚከሰቱ እንኳ ቢሆን መረጃውን በመቀባበል በጋራ በመሆን መፍትሄ በመፈልግ ላይ ነው ያለነው። ስለዚህ እስካሁን በፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ በምናደርገው ቅንጅት በኩል የተፈጠረ ምንም ችግር የለም።
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ ለመወዳደር ከተዘጋጁ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ችግር አጋጥሞናል በሚል ቅሬታ ያሰማ አካል ይኖር ይሆን?
አቶ ቶማስ፡- ቀደም ሲል ሳልጠቅሰው ያለፉኩት ነገር ቢኖር የህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በክልላችን በርከት ብሎ የሚስተዋል ድርጊት ነው። በተለይ ህገ ወጥ መሳሪያው ከደቡብ ሱዳንም ጭምር የሚመጣ ነው። ደቡብ ሱዳናውያን አምጪዎቹ ሲሆኑ፣ ደላላዎቹ ደግሞ የእኛ ኢትዮጵያውያኑ ናቸው። ገዢዎች ደግሞ ከመሃል አገር ናቸው። ገዢው አካል ጁንታ አሊያ ሸኔ የሚባለው ሊሆን ይችላል። በርካታ ሻጭና ገዢዎች አሉ። መሳሪያው ቀጥታ ከደቡብ ሱዳን በደላላዎች አማካይነት ወደመሃል አገር ይገባል።
በተለይ በዚህ በያዝነው ሩብ ዓመት ወደ 300 በላይ ህገ ወጥ መሳሪያ መያዝ ችለናል። በተመሳሳይ ባሳለፍነው ሳምንትም ወደ 12 ያህል መሳሪያ ተሽከርካሪውን ቦርቡረው በውስጠኛው ክፍል ያስቀመጡ ቢሆንም በኬላ አካባቢ በፌዴራል ፖሊስ ሊያዝ ችሏል። ስለዚህ እንደእነዚህ አይነት ህገ ወጥ መሳሪያ ዝውውሮች ለምርጫ ስጋት ሊሆን ስለሚችል ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመሆን በቂ ዝግጅት አድርገን ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎች ይገባሉ ብለን ያስብነውን ቦታ ዘግተናል።
ወደጥያቄው ስመጣ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ያጋጠማቸው ብዙ ችግር የለም። ነገር ግን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚያደርጓቸው ስህተቶች አሉ። በተለይ በቅርቡ አንዳንዶቹ ፖስተሮቻቸውን የሚሰቅሉት ክልክል የሆኑና መለጠፍ የሌለባቸው ቦታዎች ላይ ነበር። በተለይ ትምህርት ቤቶች አካካቢ የመለጠፍ ሁኔታ ነበር የታየው። አግባብ እንዳልሆነ ሲነገራቸው ደግሞ ይህ የትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ አይደለም ሲሉ ነው ማስተባበያ የሚሰጡት። እኛ ግን ይህን ነገር ከርሮ ግጭት እንዳይፈጠር ጉዳዩን በኮሚቴ አማካይነት አካባቢው ትምህርት ቤት ስለመሆኑ በማረጋገጣችን ሊስተካከል ችሏል።
ከዚህ ሌላ እነዚሁ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳቸውን በቤተ እምነት ቅጥር ግቢ በመገኘት ሲያከናውኑም ተስተውለዋል። ይህ ድርጊት በተለይ ጎደሬ አካባቢ ታይቷል። አንድ ተፎካካሪ ፓርቲ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብቶ ከአባላቱ ጋር ውይይት አድርጓል። በዚህ ወቅት ያደረግነው ነገር ቢኖር ፓርቲው አባላቱን እያወያየ ባለበት ጊዜ አስቁመን ብናስወጣው ሌላ አተካራ ውስጥ ሊያስገባ ይችላልና ውይይቱን ሲጨርስ ብናነጋግራቸው ይሻላል በሚል ውይይታቸውን በሰላም ጨርሰው ሲወጡ ጠብቀን ጉዳዩን አስረድተናቸው ዳግም በቤተ እምነት ውስጥ ውይይት እንዳያደርጉ አሳስበናቸዋል። በእርግጥ ይህ አካሄድ አግባብ እንዳልሆነ ሳያውቁ ቀርተው ሳይሆን ሆነ ብለው ያደረጉት ጉዳይ ነው። እስካሁን እነዚህን መሰል ችግሮች እንጂ የጎላ የተፈጠረ ችግር የለም። ይሁንና አዳራሽ ተከልክለናል እና መሰል ችግር አጋጥሞናል በሚል የተለያዩ አቤቱታዎችን ቢያሰሙም ጉዳዩን ይዘን በምናጣራበት ጊዜ ግን ችግር አለመፈጠሩን ነው የምናረጋግጠው።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ውጭ በቀጣይ በምርጫው ወቅት ሊያጋጥሙ ይችላሉ ብላችሁ የለያችኋቸው ስጋቶች ይኖሩ ይሆን? ካሉስ ለመፍትሄው ምን አይነት እንቅስቃሴ ነው የምታደርጉት?
አቶ ቶማስ፡- እንደ ክልል ስጋት ናቸው ብለን የለየናቸው በተለይ ጎደሬ አካባቢ በደቡብ ክልል ካለው ጉራ ፈርዳ አካባቢ እንደስጋት በማየት ለይተናል። ምክንያቱም አዋሳኝ ቦታዎች ሰላም የማይኖር ከሆነ በክልላችንም ሰላም አይኖርም በሚል ነው በመንቀሳቀስ ላይ የምንገኘው። ምክንያት ቢባል ጎረቤት በሰላም ካልተኛ እኛም መተኛት አንችልምና ነው በዚህ መልኩ በመንቀሳቀስ ላይ የምገኘው። ስለዚህም ቦታውን ለየተን ከደቡብ ክልል ጋር ቅንጅት ፈጥረን በመስራት ላይ እንገኛለን።
ሌላው በክልላችን ውስጥ በስጋት ሊታዩ የሚችሉ አካባቢዎች አኝዋክ ዞን ጆር ወረዳ አካባቢ ምርጫ በሚካሄድበት ወቅት ችግር ቢፈጠር እንኳ መረጃ መለዋወጥ የሚያስችል ኔትዎርክ የለም።፡ በተመሳሳይ በኑዌር ዞን አኮቦ አካባቢ ምንም አይነት ኔትዎርክ የለም። በዚህ ምክንያት እንዲህ ኔትዎርክ የሌለባቸው አካባቢዎች እንደስጋት የለየናቸው ናቸው። ከዚህ ውጭ በሌላው የክልሉ ቦታ ሰላም ነው።
አዲስ ዘመን፡- ስጋት ናቸው ብላችሁ ለለያችኋቸው ቦታዎችና የኔትዎርክ አለመኖር እንደመፍትሔ የተቀመጠ ነገር ምንድን ነው?
አቶ ቶማስ፡- በተለይ አኮቦ አካባቢ የአንድ አቅጣጫ (oneway) ብቻ ኔትዎርክ አለ፤ ይህ ደግሞ አንዳንዴ ይበላሻልና እንዳይበላሽ ዝግጅት ማድረግ ነው። ምክንያቱም አሁን ባለው የተጣበበ ጊዜ ለፌዴራል ብናቀርብም አስቸኳይ መፍትሄ ሊያገኝ አይችልም። ምክንያቱም አሁን የኔትዎርክ ችግር አለባቸው ብዬ የጠቀስኳቸው ወረዳዎች ቀደም ባለው ጊዜም የመሰረተልማት ዝርጋታ የሌለባቸው አካባቢዎች ናቸው። ከዚህ በፊት የነበረው
መንግስት በእነዚህ ወረዳዎች ላይ ምንም የመሰረተልማት አልሰራም ማለት ይቻላል። ይሁንና ከዚህ ምርጫ በኋላ ተስፋ ያላቸው ወረዳዎች ናቸው። በቀጣይ መንግስት በሚያደርገው በአሁኑ አያያዙ መፍትሄ ያገኛሉ ተብለው ተስፋ የተያዘባቸው ወረዳዎች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- የጋምቤላ ክልል የሰላምና የጸጥታውን ሁኔታ በተመለከተ ከጎረቤት ክልሎች ጋር የጀመራችኋቸው የቅንጅት ስራዎች እንዳሉ ጠቅሰዋል፤ ቅንጅታቸው በምን መልኩ ነው እየተካሄደ ያለው? ዋና ትኩረታችሁስ ምንድን ነው?
አቶ ቶማስ፡- ከደቡብ ክልል ጋር ተቀናጅተን እየሰራን ነው። በተጨማሪ ደግሞ ከኦሮሚያ ክልልም በተመሳሳይ ተቀናጅተን በመስራት ላይ እንገኛለን። የጋራ እቅድ አዘጋጅተን ነው ወደስራ የገባነው።፡ በሌላ በኩል ደግሞ እንዲሁም የእኛን ክልል ጨምሮ ኦሮሚያ ክልል እና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ስራችንን በመወያየት ጀምረናል።
ከዚህ ቀደምም የጋራ የሆነ በልማትና በመሰል ጉዳዮች ላይ እንደምናደርግ የሚታወቅ ሲሆን፣ አሁንም እንዲሁ በተለይ ሰላምና ጸጥታን በተመለከተ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተን የጸጥታ አካላት ነን በመወያየት ላይ የምንገኘው። የዚህ የጸጥታ ኃይሉ ውይይትም ዋና ትኩረቱ ምርጫው በሰላም ይጠናቀቅ ዘንድ ነው። ከዚህ በተጨማሪ እኛ ኢትዮጵያውያን አንድ ስለመሆናችን የምናሳይበትም ምቹ ሁኔታን ስለሚፈጥርልን ነው። ምክንያቱም ኦሮሚያ ችግር ካለ ጋምቤላ ተኝቶ ማደር የለበትም። የኦሮሚያ ችግር መጋራት አለብን። ጋምቤላ ከተቸገረ ደግሞ ኦሮሚያ እኔ ሰላም ነኝ ብሎ ተኝቶ ማደር የለበትም፤ ስለጋምቤላ ይመለከተዋልና መተጋገዝ የግድ ነው። በደቡብም ሆነ በቤኒሻንጉል ጉምዝም እንዲሁ ነው። ህዝባችን አንድ ሲሆን ቅንጅት ይኖራል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- በምርጫው ወቅት ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ በክልሉ ምን አይነት ዝግጅት ነው እያደረጋችሁ ያላችሁት?
አቶ ቶማስ፡- ዋናው ነገር ኢ-ሰብዓዊ የሆነ ነገር እንዳይፈጸም ውይይቱ የሚያተኩረው ለዚህም ጭምር ነው፤ እኛ ሁሌ ረቡዕ ዕለት በየሳምንቱ የቴክኒክ ኮሚቴ የጋራ ስብሰባ አለን። በየ15 ቀኑ ደግሞ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ የጋራ ስብሰባም አለን። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አስቸኳይ ነገር የሚያጋጥመን ከሆነ በየመሃሉም ስብሰባውን እናካሂዳለን።
ችግር እንዳይፈጠር ደግሞ እያንዳንዱ ዞን የየራሱ የጸጥታ ምክር ቤት አለው። በእነዚህ ዞኖች ውስጥ በሚካሄደው ውይይት እንደየአስፈላጊነቱ እኛ ደግሞ እየተገኘን በጉዳዩ ላይ እንመክራን። የደረሱበትን ተረድተን ያጋጠማቸው ችግር ደግሞ ካለ ድጋፍ ለማድረግ እንሞክራለን። በዚህ መልኩ በቂ ዝግጅት አድርገን በመንቀሳቀስ ላይ እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡- ምርጫው ሰላማዊ ይሆን ዘንድ የተለያየ ስራዎችን እየሰራችሁ እንደሆነ ገልጸዋልና እንደክልል ምን ያህል መደበኛ ፖሊስ፣ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ነው ለማሰማራት ያስባችሁት?
አቶ ቶማስ፡- ቁጥሩን መግለጽ ብዙ ባያስፈልግም እኛ ያን ያህል በቂ ኃይል አለን ለማለት ብዙም አያስደፍረንም። ምክንያቱም በቂ የሆነ ኃይል አሰልጥኖ ለማሰማራት በቂ ፋይናንስ ሊኖር የግድ ይላል። በክልሉ ለሚገኙ ለእያንዳንዱ ቀበሌ ከ15 እስከ 20 የሚጠጉ ሚሊሻዎች አሏቸው። ለእነዚህ ሚሊሻዎች ስልጠና እየተሰጣቸው ነው።
በየወረዳዎቹ ግን የመደብነው ልዩ ኃይሎችን ነው። በተለይ ከሌሎቹ በተለየ ስጋት አለባቸው የምንላቸው ወረዳዎች ላይ ነው ልዩ ኃይሎችን የመደብነው። ይኸውም አዋሳኝ የሆኑ አካባቢዎች በተለይ አኮቦ አካባቢ ኑዌር ዞን፣ መኮይ፣ በአኝዋክ ዞን ደግሞ ጆር፣ ጎፕ እና ዲማ፤ በመዠንገር ዞን ደግሞ ጎደሬ በበቂ ሁኔታ ምደባ የተደተረገባቸው አካባቢዎች ናቸው። ጎደሬ አካባቢ የሽፍቶች ምልልስ በመኖሩ በአካባቢው የሚፈጠሩ ግጭቶች ነበሩ። ይህ አይነቱ ስጋት በድጋሚ እንዳይኖር ታሳቢ ያደረገ ምደባ ነው ያካሄድነው። መደበኛ ፖሊስ ዘንድ ስንመጣ ደግሞ እነርሱ በየከተማው ነው የተመደቡት። በእያንዳንዱ ወረዳ ንዑስ ጣቢያዎች አሉ። እነዚህ ንዑስ ጣቢያዎች በራሳቸው እንደገና ደግሞ ምደባ ያካሂዳሉ። በዚህም መሰረት እያንዳንዱ ወረዳ ከ70 በላይ መደበኛ ፖሊሶች አሏቸው ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- በምርጫ ወቅት እንዲጠበቅ የሚፈለገው የሰላምና ጸጥታው ሁኔታ እንደወትሮው ላይሆን ይችላልና ምን ያህል የስነ ልቦና ዝግጅት እንዲያደርጉ ነው ግንዛቤ የተሰጣቸው?
አቶ ቶማስ፡- ልዩ ኃይል ከዚህ በፊት በቂ ስልጠና ተሰጥቷቸው ነው ስራቸውን በመስራት ላይ የሚገኙት። ከዚህ የተነሳ የጋምቤላ ልዩ ኃይል ያለው ቁመና ጥሩ የሚባል ነው። ከዚህ ቀደም የነበረው ታሪክ ግልጽ ነበር፤ በ2008 ዓ.ም የአኝዋክና የኑዌር ግጭት ለልዩ ኃይሉ መከፋፈል ምክንያት ሆኗል። መከፋፈል ብቻ ሳይሆን እርስበእርስ እስከመዋጋት ድረስ ደርስው እንደነበር ይታወቃል።
ከዚያ በኋላ ግን በፌዴራል ድጋፍ ወደጦላይ ማሰልጠኛ አምጥተን በወቅቱ በቂ ስልጠና ተሰጥቷቸው ነው የወጡት። በህገ ወጡ ተግባር ቀጥተኛ ተሳትፎ የነበራቸው አካላት ህጋዊ እርምጃ ተወስዶባቸው በእስር ቤት ውስጥ ለብዙ ዓመታ ቆይተዋል። ግማሹ ደግሞ ከልዩ ኃይሉ እንዲባረር ተደርጓል። ስለዚህ የቀደመውን ተሞክሮ ሁሉም ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ድጋሚ ስህተትን መስራት አይፈልጉም። በአሁኑ ወቅት በክልላችን የትኛውም አይነት ችግር ቢያጋጥም ልዩ ኃይሎቻችን አንድ ላይ ነው የሚተሙት። አንድነታቸውን ሊፈትሽና ጥንካሬያቸውን ሊለካ የሚችል ችግር ባለፉት ሁለት ዓመት ውስጥ አጋጥሞን የነበረ ቢሆንም ልዩ ኃይሉ ለተሰለፈበት ዓላማ ያለውን ጽናት በተግባር ማሳየት ችሏል።
አዲስ ዘመን፡- ምን ነበር ባለፈው ሁለት ዓመት ውስጥ ያጋጠማችሁ ችግር?
አቶ ቶማስ፡- በተለይ በ2011 ዓ.ም በክልላችን ትንሽ ግጭት ተፈጥሮ ነበር። በኑዌር ዞን አንድ ልዩ ኃይል ተገደለ። በተመሳሳይ ደግሞ ቆየት ብሎ በአኙዋክ ዞን እንዲሁ አንድ ልዩ ኃይል ተገደለ። ይሁንና ከራሳቸው ወገን ይሁን ከሌላው ወገን ይሙት ልዩ ኃይሉን የከፋፈለው ነገር አልነበረም። እኛ እንዲያውም በመካከላቸው ልዩነት እንዳይኖር ግንዛቤ ልንሰጣቸው ብንሞክርም ይልቁኑ በሚያስደምም ሁኔታ የየትኛው ሰው ይሁን ማንም መገደል የለበትም። ሁሉም እኩል ነው፤ እኛ ደግሞ የተጣለብን ኃላፊነት በእኩል ህዝብን እንድናገለግል ነው ሲሉ ነው የገለጹልን። ከዚህ የተነሳ ልዩ ኃይላችን ሊመሰገን የሚገባው ነው የሚል አመለካከት ነው ያለኝ። በአሁኑ ወቅት ለዚህ ምርጫ በማሰልጠኛ ወደ 350 የሚጠጉ ልዩ ኃይሎች ያሉ ሲሆን፣ ከ20 ቀን በኋላ ስልጠናቸውን ጨርሰው ይወጣሉ የሚል እምነት አለን።
አዲስ ዘመን፡- እንደሚታወቀው በቅርቡ ሸኔ እና ህወሓት በአሸባሪነት ተፈርጀዋል፤ በተለይ ሸኔ እናንተ በምትዋሰኑበት በቄለም ወለጋ አካባቢ እንደሚንቀሳቀስና ወደ ጋምቤላ አካባቢም እንደሚመጣ ተናግረዋል፤ ችግር እንዳይከሰት ከቄለም ወለጋ ዞን ጋር ምን ያህል ነው በቅንጅት እየሰራችሁ ያለው?
አቶ ቶማስ፡- ሸኔ ስጋት የሚሆንበት ምክንያት በአንደኛ ደረጃ ህገ ወጥ መሳሪያን የሚያገኙት ከጋምቤላ ነው። የተያያዘ መረብ አላቸው። ጥይትም ያገኛሉ። ከዚህ ውጭ እነሱ ይጠቀማሉ የሚባለው ከቀለብ ጀምሮ ሌሎችንም ያገኛሉ። ቡና ከቄለም ወለጋ ዘርፈው ወደእኛ ዘንድ አምጥተው ይሸጣሉ። እኛ ሳንቦዝን በርካቶችን ለመያዝ ችለናል። ቡና ሲያመጡ በኮንትሮባንድ ነው። እኛ በመከታተል ጸጉረ ልውጥ የሆኑትን በመያዝ ለመመርመር ችለናል።
ባለፈው የሚያዚያ ወር ብቻ ወደ 10 የሚጠጉትን ይዘን ባደረግነው ምርመራ አንድ ግለሰብ ብቻ ብዙ ተንቀሳቃሽ ስልክ የያዘ፣ ሌላው ደግሞ ብዙ የተለያየ መታወቂያ የያዘ፣ ትከሻቸው ሲፈተሸ ለብዙ ጊዜ መሳሪያ ማንገታቸውን የሚናገር ሆኖ አግኝተናቸው ይዘን ለኦሮሚያ መንግስት አስረክበናል። በአሁኑ ወቅት ወደ አራት የሚጠጉ በማረሚያ ቤት ውስጥ ይገኛሉ። አንደኛው ደግሞ በስመ ኢንቨስተር ይስራ እንጂ የሸኔ መረጃ ሰብሳቢ እንደሆነ ነው የተደረሰበት። የሸኔ ፍላጎት ኦሮሚያ ላይ የሚፈጥረውን አይነት ችግር ጋምቤላ ላይም መፍጠር ነው፤ ስለዚህ እኛ መተኛት የለብንም።
ስለዚህ እንዲህ አይነቱ ችግር እንዳይፈጠርብን ከቄለም ወለጋ ዞን ጋር በመሆን በቅንጅት ለመስራት እቅድ አለን። እንደ ክልል ብቻ ሳይሆን እንደዞንም ቄለም ወለጋ ከአኝዋክ ዞንና ከኢታንግ ልዩ ወረዳ ጋር በመሆን ለመስራት የጋራ እቅድ ተነድፏል። ዞን ከዞን ብቻ ሳይሆን ወረዳ ከወረዳ ጋር እንዲሁም ቀበሌ ከቀበሌ ጋር ነው ለመስራት የታቀደው፤ በእነሱ በኩልም እንዲሁ ነው። ለዚህም ነው በጋምቤላ ክልል ሰላም የሰፈነው ማለት ይቻላል።
አንድ መግለጽ የምፈልገው ነገር ቢኖር ሸኔ በአሸባሪነት መፈረጁ አግባብ ነው፤ ነገር ግን ዘግይቷል። መፈረጅ የነበረበት ቀድሞ ነበር። በአሸባሪነት ሊያስፈርጀው የቻለው ድርጊቱ ነው። ስለሆነም በአሸባሪነት መፈረጁ ትክክለኛ ውሳኔ ነው። በዚህ ላይ የሚያከራክር ምንም አይነት ነገር የለም።
አዲስ ዘመን፡- በደቡብ ሱዳን ድንበር አካባቢ ያለው ሁኔታ ምርጫውን ሊረብሸው ይችላል የሚል ስጋት ይኖር ይሆን?
አቶ ቶማስ፡- ጋምቤላ የሚዋሰነው ከሁለት ክልሎችና አንደኛው ደግሞ የአስተዳደር ወሰን አካባቢዎች የሚል አለ፤ ጆንግላይ ስቴት፣ አፐርናይል ስቴት፣ ግሪክ ቦር ማለትም ከተማ አስተዳደር ጋር እንዋሰናለን። ጆንግላይ ስቴትና አፐርናይል ስቴት በሚያዋስነው አካባቢ ብዙም ችግር የለም። ችግር ቢኖር እንኳ በውይይት መፍታት እንችላለን። ምክንያት በፒቦር ማዶ ለማዶ የሚኖረው ህዝብ የሚናገረው ቋንቋ አንድ አይነት ነው። በተለይ ጆርዲ ስቴት ያለው ከዚህኛው ወገን ጋር አንድ አይነት ኑዌር ናቸው። ስለዚህ ኑዌር ኑዌር በመሆኑ በአንድ ቋንቋ ነው የሚናገረው። አተርናይል ደግሞ ከዚህ ከእኛ ጋር የለያቸው ድንበር ነው እንጂ አንድ ናቸው።
ነገር ግን እኛን ያጋጠመን ችግር የጎሳ ግጭት በተለይ በአፐርናይል ስቴት ጋር ሲሆን፣ ማዶ ያለ ግጭት ወደእኛ ዘንድ ይመጣል። እንዲያውም አንደኛው ወረዳ ላይ የነበረው ችግር በቅርቡ ነው ኮንፈረንስ በማድረግ የተጠናቀቀው። ደቡብ ሱዳን ውስጥ ግጭት ተፈጽሞ እና የሰው ሕይወት ጠፍቶ ነበርና ደቡብ ሱዳን ውስጥ የገዳዩን ጎሳ ማግኘት ስላልቻሉ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በኢትዮጵያ ካለው ጎሳ ሶስት ሰው በድብቅ ገድለው የተሰወሩበት ሁኔታ አለ፤ ይህን ተከትሎ ግጭት እንዳይነሳ የማረጋጋት ስራ ሰርተን ነው ሰላም የወረደው። የክልሉ ልዩ ኃይል፣ የክልሉ ፖሊስ እንዲሁም የፌዴራል ፖሊስ በጋራ ሄደን ለአንድ ወር ያህል ጉዳዮችን ለማረጋጋት ሞክረናል። ምክንያቱም ሁለት ጎሳ ተከፋፍሏል። በመጨረሻ ግን እንደጠቀስኩት ጠቅላላ ኮንፈረንስ አካሂደናል። በዚህም ሰላም ወርዶ ህዝቡም ወደአንድነቱ የተመለሰ ሲሆን፣ ተፈናቅለው የነበሩትም ወደየቀዬያቸው የማስመለሱ ስራ እየተሰራ ነው።
በቀጣይም ስጋት እንዳይኖር የአፐርናይልስቴት ምክትል ገዢ ወደ ጋምቤላ ክልል መጥተው ውይይት አድርገናል። ከደቡብ ሱዳን መጥተው ግድያ ፈጽመው ተመልሰው ወደእነርሱ የተሸሸጉ ሰዎችን ይዘው ለእኛ አሳልፈው እንዲጡንም ነው ለማድረግ የተስማማነው። በዚህም ጉዳይ ቃል ገብተውልናል። ለእናንተ የምርጫ ጉዳያችሁ ስጋት እንዳይሆን እኛ ዘንድ የተደበቁትን አካላት አሳልፈን እንሰጣለን ብለውናል።
የግሪክ ቦር የሙርሌ ጉዳይ ላይ ውይይት አላካሄድንም። ምክንያቱም ውይይት ለማድረግ የፌዴራል መንግስት ጣልቃ ገብነት ያስፈልገዋል። እዛ ያለው ጎሳ እኛ ዘንድ ካለው ጎሳ ጋር የተለያየ ነው። ምክንያቱም የሙርሌ ጎሳ ጋምቤላ ውስጥ የለም። ሙርሌዎች ብዙ ጊዜ የሚፈጽሙት ከባድ ወንጀል ነው። ምክንያቱም እነሱ ሰው የመግደል፣ ህጻናትን የመውሰድና ከብቶችን የመዝረፍ ባህሪ ስላላቸው ወንጀላቸው ከፍ ያለ ነውና ከእነርሱ ጋር ለመወያየት የፌዴራል ጣልቃ ገብነትን ይጠይቃል። በዚህም የተነሳ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያለው ሁኔታ አስቸጋሪ በመሆኑ እኛም ድንበሮቻችንን አጥብቀን የመጠበቁ ስራን በመስራት ላይ ነን፤ ከዚህ ውጭ ሌላ ችግር እስካሁን የለም።
አዲስ ዘመን፡- ስድስተኛው አገራዊና ክልላዊ ምርጫን በተመለከተ ከክልሉ የጸጥታ ኃይልና ከህዝቡ ምንድን ነው የሚጠበቀው? አያይዘውም ለጸጥታ ዘርፍና ለህዝቡ የሚያስተላፉት መልዕክት ካለዎት?
አቶ ቶማስ፡- ከጸጥታ ኃይሉ የሚጠበቀው ነገር ወሳኝ የሆኑ ቦታዎች የቅድሚያ ስራ መስራት ነው። በዚህም የተነሳ ስራዎችን በመስራት ላይ ነን። ከህብረተሰቡ የሚጠበቀው ደግሞ በአካባቢያቸው የሚስተዋል ችግር ካለ ለጸጥታ ኃይሉ በመጠቆም ትብብር ቢያደርጉ መልካም ነው።
ዋናውን ችግር መፍታት የሚችለው የጸጥታ ኃይሉ ብቻውን መንቀሳቀስ በመቻሉ አይደለም። ዋናውና በአንደኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጠው የህብረተሰቡ ትብብር ነው። ይህም ነው በቅንጅት የክልሉን ሰላም ማምጣት የሚችለው። ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ወንጀለኞች የሚመገቡት፣ የሚያድሩትና የሚነሱት ከህብረተሰቡ መሃል ነውና ነው። ስለዚህ ህብረተሰቡ የመጀመሪያ የራሱ ጠባቂ ራሱን ካደረገ ችግሮች ሁሉ ሊፈቱ ይችላሉ። ከዚህም አንጻር ነው የህብረተሰቡን ያላሰለሰ ድግፍ እንፈልጋለን ማለታችን።
በመጨረሻም ማለት የምፈልገው ምርጫ ወሳኝ መሆኑን ነው። ያለምርጫ የሚቋቋም መንግስት ምንም አይነት መሰረት እንደማይኖረው ሁላችንም ማወቅ ይገባናል። በኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ ካልተካሄደ በፊትለፊታችን ሊፈጠር የሚችል ችግር እንደሚኖር ሁላችንም ልንገነዘብ ይገባል ባይ ነኝ። ምርጫው ከተካሄደ የአይናችን ብሌን የሆነው የህዳሴ ግድባችንም አስተማማኝ ጠባቂ ይኖረዋል የሚል እምነት አለኝ። ምርጫው ካልተካሄደ ደግሞ የህዳሴ ግድባችን ስጋት ላይ ይሆናል። ምክንያቱም ህጋዊ መንግስት ስለማይኖር ጠባቂ አይኖረውም የሚል አተያይ አለኝ። ስለዚህ ኢትዮጵያ የወደፊቷን በጥሩ ሁኔታ መቀጠል የምትችለው ሰላማዊ ምርጫ ማካሄድ ሲቻል ብቻ ነው። ስለዚህ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ለምርጫው ሰላማዊነት ዝግጁ መሆን አለበት፤ ለሚፈጠረው ችግርም በመፍትሄነት ተባባሪ መሆን ይጠበቅበታል።
አዲስ ዘመን፡- ለቃለ መጠይቁ ፍቃደኛ በመሆንዎ ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ቶማስ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
በአስቴር ኤልያስ