ከዓመታት በፊት፣ በዚህ ሳምንት (ከየካቲት 4 እስከ 10) በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከተከናወኑ ድርጊቶች መካከል ጥቂቶቹን ለማስታወስ ያህል፡- የካቲት 4 ቀን 1909 ዓ.ም – የንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ልጅ፣ ዘውዲቱ ምኒልክ ‹‹ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ወለተ ለዳግማዊ ምኒልክ ስይምተ እግዚአብሔር›› ተብለው ነገሱ፡፡
ዘውዲቱ ምኒልክ የተወለዱት ከንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ አና ከወ/ሮ አብችው በያን ነው፡፡ ገና የስድስት ዓመት ተኩል ልጅ ሳሉ ለንጉሰ ነገሥት አጤ ዮሐንስ ፬ኛ ልጅ ለራስ አርዓያሥላሴ ዮሐንስ ተዳሩ፡፡ ከአምስት ዓመታት በኋላም ራስ አርዓያሥላሴ ዮሐንስ ስለሞቱ ዘውዲቱ ወደ ሸዋ ተመለሱ። በ1884 ዓ.ም ደግሞ ደጃዝማች ውቤ አጥናፍሰገድን አግብተው መኖር ጀመሩ፡፡ ይህ ጋብቻም ፈረሰና፣ በ1893 ዓ.ም የእቴጌ ጣይቱ የወንድም ልጅና የጎንደር ገዢ የሆኑትን ራስ ጉግሳ ወሌን አገቡ፡፡ መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም፣ ልጅ ኢያሱ ሚካኤል ከስልጣን ሲሻሩ ዘውዲቱ ምኒልክ ንግሥት፤ ተፈሪ መኮንን ደግሞ ‹‹ራስ›› ተባሉና አልጋ ወራሽ ሆነው ተሾሙ፡ ፡
ራስ ጉግሳ ወሌም ከቤተ-መንግሥቱ ገለል እንዲገለሉ ተደረገ፡፡ በልጅ ኢያሱ መተካታቸው ከተነገረ ከአምስት ወራት በኋላ፣ የካቲት 4 ቀን 1909 ዓ.ም ዘውዲቱ ምኒልክ ‹‹ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ወለተ ለዳግማዊ ምኒልክ ስይምተ እግዚአብሔር›› ተብለው በመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በሊቀ ጳጳሱ በአቡነ ማቴዎስ እጅ ቅብዐ መንግሥት ተቀብተው የንግሥትነት ዘውድ ጫኑ፡ ፡ በዚሁ ዕለትም የራስ መኮንን ወልደሚካኤል ልጅ የሆኑት ተፈሪ መኮንን፣ ‹‹ራስ ተፈሪ›› ተብለው ታላቁን “የሰለሞን ኒሻን” ተሸልመውና ለአልጋ ወራሽ የሚገባው ክብርና ስርዓተ-ፀሎት ተደርጎላቸው፣ ‹‹ልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን›› ተብለው ተሰየሙ፡፡
የካቲት 4 ቀን 1910 ዓ.ም – በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ጉልህ ስፍራ ካላቸው ግለሰቦች መካከል አንዷ የሆኑት እቴጌ ጣይቱ ብጡል ኃይለማርያም አረፉ፡፡ እቴጌ ጣይቱ ምኒልክን አግብተው ወደ ሸዋ ከመጡ ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ የነበራቸው ተፅዕኖ ብዙና የገዘፈ ነው፡፡ ባለቤታቸው ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ከታመሙ በኋላ ስልጣኑን በእጃቸው አስገብተው ፖለቲካውን ለመዘወር ያላመነቱት ብርቱዋ ሴት ጣይቱ፣ ይህ ተግባራቸው ከሸዋ መኳንንት ጋር አጣላቸውና ወደ እንጦጦ ማርያም ሄደው እንዲቀመጡ አስወሰነባቸው፡፡ በመጨረሻም ከአብዛኛዎቹ የባለቤታቸው የዳግማዊ ምኒልክ ውሳኔዎች ጀርባ የነበሩትና አዲስ አበባን የመሰረቱት ብርቱዋ እመቤት እቴጌ ጣይቱ የካቲት 4 ቀን 1910 ዓ.ም አረፉ። የካቲት 5/1847 ዓ.ም – ደጃዝማች ካሣ ኃይሉ የግዛት ባላባቶችን በጦርነት አሸንፈው ድል ካደረጉ በኋላ ‹‹ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሰ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው ነገሱ፡፡
ደጃዝማች ካሣ በኅዳር ወር 1845 ዓ.ም ደጃዝማች ጎሹ ዘውዴን ጉርአምባ ላይ፣ በሰኔ ወር 1845 ዓ.ም ደገሞ ራስ አሊ አሉላን (ዳግማዊ ራስ አሊን) አይሻል ላይ ካሸነፉ በኋላ ከወቅቱ የግዛት ኃያላን መሳፍንት መካከል ለደጃዝማች ካሣ ያልገበሩት የስሜንና የትግራይ ገዢ የነበሩት ደጃዝማች ውቤ ኃይለማርያም ብቻ ነበሩ፡፡
በተለይ ደግሞ ደጃዝማች ካሣ ጎንደር ላይ ሆነው ንጉሥ የመሾምና የመሻር ስልጣን የነበራቸውንና የወቅቱ ባላባቶች ሁሉ አለቃ የነበሩትን ራስ አሊን ካሸነፉ በኋላ ንጉሥ መሆናቸው እንደማይቀር እየታወቀ መጣ፡፡ ደጃዝማች ካሣ እና የደጃዝማች ውቤ ጦር የካቲት 3 ቀን 1847 ዓ.ም ‹‹ቧሂት›› በተባለ ቦታ ላይ ገጥሞ ድሉ የደጃዝማች ካሣ ኃይሉ ሆነ፡፡ የደጃዝማች ውቤም ንብረት ተወረሰ፡፡
ከሁለት ቀናት በኋላ (የካቲት 5 ቀን 1847 ዓ.ም)፣ ደጃዝማች ውቤ ኃይለማርያም ሊነግሱባት አስጊጠው ባሰሯት ደረስጌ ማርያም ቤተ-ክርስቲያን ዕጨጌው በግራ፤ ጳጳሱ በቀኝ በኩል ተቀምጠው፣ መጽሐፈ ተክሊል እየተነበበ፣ በጳጳሱ በአቡነ ሰላማ እጅ ተቀብተው፣ ‹‹ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሰ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው የኢትዮጵያ ንጉሥ ሆኑ፡ ባለቤታቸው ወይዘሮ ተዋበች አሊ (የራስ ዓሊ ልጅ) ደግሞ አብረው ቆርበው አክሊል ተደርጎላቸው የእቴጌነት ማዕረግ ተሰጣቸው፡፡
ሕዝቡም ከራስ አሊ መሸነፍ በኋላ ‹‹ደጃች ካሣ መቼ ይነግሱ ይሆን? ስመ መንግሥታቸውስ ማን ይባል ይሆን?›› እያለ ይጠይቅ ስለነበር ‹‹እኔ በመራሁህ ተጓዝ፤ ስሜን በስሜን እነግርሃለሁ›› ብለው የተናገሩት ቃላቸው መፈጸሚያው ደረሰ፡፡ ከዚህ በኋላም አዋጅ ወጥቶ ነጋሪት እየተጎሰመ፣ ‹‹ከዛሬ ጀምሮ ደጃዝማች ካሣ ስማቸው ‹ቴዎድሮስ› ተብሎ ንጉሰ ነገሥት ሆነዋልና ‹ደጃዝማች ካሣ› ብለከህ የጠራህ ሁሉ ትቀጣለህ›› ተብሎ ተነገረ
አዲስ ዘመን የካቲት 8/2011
አንተነህ ቸሬ