መንገድ ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና ለማህበራዊ ግንኙነት የጎላ ድርሻ እንዳለው ይታወቃል። መንገድ በንግድ ሥራም ይሁን በሌላ ሰዎች ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው ለመስራት ከሚያስችላቸውና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስራቸውን ለማጠናከር ከሚጠቀሙበት መሰረተ ልማቶች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው። ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መንገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ሁሉ የሚጠይቀው መዋዕለ ነዋይም በዛው ልክ ከፍተኛ ነው። መንገድ ለከተሞች ዕድገትም የላቀ ድርሻ ያለውና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን ለማቀላጠፍ ያግዛል።
ለከተሞች እድገት መሰረታዊ ከሆኑት ጉዳዮች መካካል አንዱ የሆነው መንገድ ለከተሞች ዕድገት ጉልህ ድርሻ አለው። የመንገድ መሰረተ ልማት የተሟላላቸው የገጠር ከተሞች በተሻለ ሁኔታ ኢኮኖሚያቸውን ማንቀሳቀስ የሚችሉ ናቸው። በተመሳሳይ ደግሞ የመንገድ መሰረተ ልማት ያልተሟላላቸው የገጠር ከተሞች ኢኮኖሚያቸውን ማሳደግ አይችሉም። ከዚህም ባለፈ ከአጎራባች ወረዳዎችና ቀበሌያት ጋር ጠንካራ የሆነ ማህበራዊ ትስስር ለመፍጠር አያስችላቸውም። ከአጎራባች ቀበሌና ወረዳዎች ጋር ጠንካራ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችላቸው የመንገድ መሰረተ ልማት ከተሟላላቸው ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚ በመሆን ከተሞችን ማሳደግ ይችላሉ።
በሲዳማ ክልል የዳራ ኦቲልቾ ወረዳ እራሱን ችሎ ወረዳ ሆኖ ከተቋቋመ ወዲህ ህዝቡ ለረጅም ጊዜ ሲነሳ ለነበረው የመሰረተ ልማት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ችሏል። በመሆኑም ወረዳው የተሻለ የልማት እንቅስቃሴ በማድረግ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ ይገኛል።
በሲዳማ ክልል የዳራ ኦቲልቾ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሰለሞን ሁሞ፤ የወረዳው ነዋሪ ለረጅም ጊዜ ሲያነሳ የነበረው የፍትህ፣ የመልካም አስተዳደርና የመልማት ጥያቄ ለመመለስ ሰፊ ሥራ ተሰርቷል። ወረዳው በ2011 ዓ.ም ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ነዋሪዎች ርቀው ሳይሄዱ በአካባቢያቸው ፍትህ ማግኘት እንዲችሉ የፍትህ ተቋማት ተቋቁመዋል። የባለሙያ ድጋፍ የሚፈልጉ ለአብነትም የትምህርት፣ የጤናና የግብርና ሥራዎች በባለሙያ ድጋፍ ለህዝቡ ተደራሽ ሆነዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ህዝቡ የነበረውን የመልማት ፍላጎት እንዲሁም ሲያነሳ ለነበረው ሰፊ የመሰረተ ልማት ጥያቄ ምላሽ በመስጠት የወረዳውን እድገት ለማፋጠን በር ከፍቷል።
ከዚህ ቀደም የተጠናው የከተማው ፕላን ተግባራዊ ሳይሆን ከአስር አመት በላይ አስቆጥሯል። በመሆኑም መሰረታዊ ፕላን የነበረውን በመከለስ ስትራቴጂካዊ ፕላን ተዘጋጅቶ በአሁን ወቅት መሬት የወረደ ሥራ መስራት ተችሏል። ከዚህም ባሻገር በከተሞች የተለያዩ የልማት ሥራዎች በስፋት እየተሰሩ ይገኛሉ። ለአብነትም ወረዳው ከተቋቋመ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የኮብል ስቶን መንገዶችና ጠጠር የመድፋት ሰፋፊ ሥራዎች ተሰርተዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም በወረዳው በተለይም ከተማን ከሌሎች አጎራባች ወረዳዎችና ከተሞች ጋር የሚያገናኙ መንገዶች እየተሰሩ ይገኛሉ። ለአብነትም ከተፈሪ ኬላ ወደ ሳፋ ኢንተርናሽናል መንገድ እንዲሁም ከተፈሪ ኬላ ወደ ሀገረ ሰላም የሚወስደው መንገድ ጠጠር ተጥሎ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል። ከዚህም ባሻገር ተፈሪ ኬላ ከተማን በብዙ አቅጣጫዎች የሚያገናኙ መጋቢ መንገዶች እየተሰሩ ናቸው።
በክልሉ መንግስት ድጋፍም ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ሰፊ ድልድይ ተሰርቷል። ድልድዩም በጂጌሳ የሚባል ሲሆን ድልድዩ ከዚህ ቀደም ባለመሰራቱ ምክንያት በደራሽ ውሃ ሳቢያ ሁሉ ሰዎችና እንስሳትን ለአደጋ እየተጋለጡ ነበር። ይህም ዋነኛው የህብረተሰብ ጥያቄ የነበረና አሁን ላይ ምላሽ ያገኘ በመሆኑ ህብረተሰቡ እጅግ ደስተኛ ነው። ከመንገድ ባሻገርም በወረዳው የሚነሱ ሌሎች በርካታ የልማት ጥያቄዎች እየተመለሱ ሲሆን፤ የወረዳው አጠቃላይ ህንጻ ግንባታው ተጀምሮ 50 በመቶ አፈጻጸም ላይ ደርሷል።
የወረዳው መመስረት ለነዋሪዎች ሰፊ ጥቅም እያስገኘ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሰለሞን፤ በተለይም ንጹህ የመጠጥ ውሃን አስመልክቶ የአካባቢው ነዋሪ እጅግ ከሚቸገርበት መሰረተ ልማት አንዱ እንደነበር አስታውሰዋል። ይሁንና በአሁን ወቅት አይ ኤር ሲ ከተባለ መንግስታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር በርካታ የገጠር ቀበሌዎች ንጹህ የመጠጥ ውሃ ሽፋን እያገኙ ነው። ለአብነትም በተያዘው በጀት አመት ብቻ አራት ቀበሌዎች ላይ 58 ንጹህ የመጠጥ ውሃ ግንባታዎች ተከናውነው የአካባቢው ማህበረሰብ በአቅራቢያው ንጹህ የመጠጥ ውሃ ማግኘት መቻሉን አቶ ሰለሞን ያስረዳሉ ።
በቀጣይም በገጠሩ አካባቢ ንጹህ የመጠጥ ውሃን በስፋት ለማዳረስ የተያዙ እቅዶች መኖራቸውን እና በከተሞች አካባቢም ያሉትን ችግሮች ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ይሁንና በተለይም ተፈሪ ኬላ ከተማ ላይ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ከፍተኛ ችግር አለ። ችግሩንም የፈጠረው በኤሌክትሪክ ሀይል የሚሰራ የውሃ መስመር በመሆኑ ትራንስፎርመሮችን በመግዛት በቀጣይ አመት የመጠጥ ውሃ ተደራሽነትን በከተሞች ለማስፋት እየተሰራ ነው። ነገር ግን በአሁን ወቅት ከከተሞች በበለጠ የገጠሩ አካባቢ ንጹህ የመጠጥ ውሃ በተሻለ አቅርቦት እያገኘ ነው።
የወረዳዋ አየር ንብረት ቆላ፣ ወይናደጋ እና ደጋ ሲሆን በደጋው አካባቢ ድንችን ጨምሮ የተለያዩ ሰብሎች ይመረታሉ። በወይናደጋው አካባቢ ደግሞ ቡና እና ሌሎች ፍራፍሬዎች ይመረታሉ። በደጋም በቆላም አካባቢ ባህላዊና መሰረታዊ ምግብ የሆነው ቆጮ ወይም እንሰት ይመረታል። በተለይም በወይናደጋው አካባቢ አቡካዶን በስፋት በማምረት ለይርጋለም ማቀነባባሪያ ይቀርባል።
ተፈሪ ኬላ ከተማ ረጅም ዕድሜን ያስቆጠረች ከተማ ብትሆንም የሚመጥናትን መሰረተ ልማት አላገኘችም። ይሁንና በአሁን ወቅት ወረዳው ከተመሰረተ በኋላ በርካታ እንቅስቃሴዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። የተለያዩ ባለሃብቶች በአካባቢው የማልማት ፍላጎት እያሳዩ በመሆኑም ወረዳው ባለሃብቱን ለማስተናገድ ዝግጁ ሆኖ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል። አጠቃላይ የወረዳው ህዝብ እንግዳ ተቀባይ ከመሆኑም በላይ ለልማት ከፍተኛ ፍላጎት ያለው በመሆኑ በቀጣይ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ነው ተብሎ ይጠበቃል።
ለከተሞች ዕድገት ትልቅ ድርሻ ያለው መንገድ በወረዳው መሰራቱ ወረዳውን ጨምሮ የአጎራባች ቀበሌዎች ኢኮኖሚ እየተነቃቃ ይገኛል በማለት ሀሳባቸውን ያካፈሉን የዳራ ኦቲልቾ ወረዳ የመንገድና ትራንስፖርት ዋና ሀላፊ አቶ ዳግም ደርሰሞ በበኩላቸው፤ በወረዳው ከፍተኛ ፍሰት የነበረው ድልድይ አገልግሎት መስጠት ባለመቻሉ የበርካቶችን እንቅስቃሴ ገትቷል። በተለይም አዛውንቶችንና ተማሪዎችን ለችግር አጋልጦ ቆይቷል። አርሶ አደሮችም እንዲሁ ምርታቸውን ለገበያ ለማቅረብ ባለመቻላቸው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ይሁንና የክልሉ መንግስት የድልድዩን አስፈላጊነት በመረዳት ማህበረሰቡ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚ መሆን እንዲችል አስቸኳይ እርምጃ በመውሰድ ድልድዩን የመስራት ዕቅድ አውጥቶ በዕቅዱ መሰረት ድልድዩን በአጭር ጊዜ በጥራት መስራት ችሏል።
የሲዳማ ክልል ዞን እያለ ጀምሮ ማህበረሰቡ ሲያነሳ የነበረው የመልማት ጥያቄ ክልሉ ተቀብሎ መመለስ በመቻሉ ማህበረሰቡ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚ መሆን ችሏል። ክልሉ ከዞኑ የተቀበለውን ጥያቄ ለመመለስ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እየሰራ ይገኛል። ከእነዚህም መካካል የመንገድና የድልድይ ፕሮጀክት በዋናነት የሚጠቀስ ሲሆን በየጊዜው ክትትልና ድጋፍ በማድረግ በአሁን ወቅት የተሻለ አፈጻጸም ላይ ደርሷል።
በ2011 ዓ.ም የተጀመረው የድልድይ ሥራም ቁመቱ 18 ስፋቱ 16 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ነው። የሲዳማ ክልል 17 ሚሊዮን ብር በጀት መድቦ የሰራው ይህ ድልድይ ወረዳውን አጎራባች ከሆኑት የገጠር ቀበሌዎች ጋር እና ተፈሪ ኬላ ከምትባለው ከተማ ጋር የሚያገናኝ ከመሆኑ አንጻር ተማሪዎችን ጨምሮ በርካታ አርሶ አደሮችና አዛውንቶች ሲቸገሩ ቆይተዋል። ይሁንና በአሁን ወቅት ድልድዩ በመሰራቱ አርሶ አደሩም ምርቱን ወደ ከተማ አውጥቶ ለመሸጥ፤ ተማሪውም ለመማር፤ አዛውንቶችም ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት አስችሏቸዋል። በዚህም አጠቃላይ የአካባቢው ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚ መሆን እንደቻለ አቶ ዳግም ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም መንገድ ያልነበረ በመሆኑ ወረዳውን ከሌሎች ወረዳዎችና ከሶስት ቀበሌያት ጋር የሚያገኛኝ መንገድ ተሰርቷል። የመንገዱ ርዝመትም አራት ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር ሲሆን ይህ መንገድ አጠቃላይ ሥራው በመጠናቀቅ ላይ በመሆኑ በቅርቡ ለተጠቃሚዎች ክፍት ይሆናል። መንገዱ በዳራ ኦቲልቾ ከሚገኙ ቀበሌያት ባለፈ ከተለያዩ ወረዳዎች ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ አርሶአደሩ በቀላሉ ተንቀሳቅሶ ያመረተውን ምርት መሸጥ መለወጥ የሚያስችለው በመሆኑ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ ያስችለዋል። አርሶ አደሩ በሚያገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅምም የወረዳዊ ኢኮኖሚም የተነቃቃ ይሆናል።
የአካባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ የሆነ የመልማት ፍላጎት ያለውና ጥያቄ ሲያነሳ የቆየ ማህበረሰብ ነው። በተለይም ተፈሪ ኬላ የምትባለው ከተማ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠር በመሆኑ በርካታ ጥያቄዎች ከማህበረሰቡ ይመጣል። ዳራ ኦቲልቾ ወረዳ መሆን ሲችልም አስፈላጊና ለህዝቡ አገልግሎት የሚሰጡ በርካታ ፕሮጀክቶች ተጀምረዋል። ከእነዚህም መካካል በተለይም ከሳፋ ተፈሪ ኬላ፤ ከተፈሪ ኬላ እስከ ቶላ ባምቢሳ ከሀገረ ሰላም ጋር የሚያገናኝ አጠቃላይ 26 ኪሎ ሜትር የሚደርስ መንገድ ተሰርቷል። ይህ ሥራም በአጭር ጊዜ ውስጥ የተሰራ ከመሆኑም በላይ ለማህበረሰቡ በርካታ ጠቀሜታዎችን የሚሰጡ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።
ከመንገዱ አስፈላጊነት አንጻር የአካባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ ትብብር ሲያደርግ የነበረ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ዳግም፤ አሁንም ህዝቡ ካለው ፍላጎት አንጻር መንገዱን የራሴ ብሎ መጠበቅ እንዳለበትና መንግስትን ብቻ መጠበቅ የለበትም። ስለዚህ መንገድም ይሁን ሌሎች ፕሮጀክቶች ሕዙቡ መጠበቅ እንዳለበት። ጥበቃ ብቻም ሳይሆን መንግስት እገዛ እንዲያደርግ ህዝቡ በራሱ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መስራት አለበት።
መንግስት አሁን የጀመረው ሥራ በጣም ጥሩ ነው የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተጀምረው የማይቆዩና በፍጥነት ተጠናቅቀው ለህብረተሰቡ አገልግለት እየሰጡ መሆኑ የሚበረታታ ነው። ለዚህም በዳራ ወረዳ ኦቲልቾ የተሰራው ድልድይ አንድ ምስክር ነው።
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 7/2013 ዓ.ም