ተወልደው ያደጉት ምዕራብ ሸዋ ዞን ጨሊያ ወረዳ ነው። እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ በአካባቢያቸው ከሚገኝ ቄስ ትምህርት ቤት ለጥቂት ወራት ተምረዋል። የአስር ዓመት ታዳጊ ሲሆኑም ሚዳቀኝ በተባለ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወላጅ አባታቸው ያስገቧቸዋል። እንግዳችን ምንም እንኳን ትምህርታቸውን ዘግይተው ቢጀምሩም በነበራቸው ፈጣን አቀባበልና ጉብዝና ምክንያት በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ አራተኛ ክፍል መግባት ቻሉ። የስድስተኛ እና የስምንተኛ ክፍልን ብሔራዊ ፈተና መቶ በማምጣት ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ገቡ። ጌዶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ 12ኛ ክፍል ተምረው በጥሩ ውጤት ጅማ መምህራን ኮሌጅ ቢመደቡም በወቅቱ በሀገሪቱ በነበረው የፖለቲካ ሁኔታ ምክንያት ኮሌጅ ላለመግባት ይወስናሉ። በአንድ ግለሰብ ምክረ ሀሳብም የነበራቸውን ውጤት ይዘው ለውጭ ትምህርት እድል ትምህርት ሚኒስቴር አመለከቱና ጥያቄያቸው ተቀባይነት አገኘ።
በዚህም መሰረት በቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ስር በነበረችው ዩክሬን መዲና ቺፍ ለመማር እድሉን አገኙ። ለስድሰት ዓመታት በአለም አቀፍ ህግ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሰሩ። በጥሩ ውጤት በማጠናቀቃቸውና የሰሩት የመመረቂያ ፅሁፍም በፈታኞች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት በማግኘቱ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በዚያው የጥናት ርዕስ የሚሰሩበት እድል አገኙ። በተመሳሳይ የዶክትሬት መመረቂያ ፅሁፋቸውም ከፍተኛ ተቀባይነት በማግኘቱም ከዩክሬን ታላላቅ ፕሮፌሰሮችና ምሁራን ስራዎች ጋር እንዲታተምና ለተማሪዎች ማጣቀሻ ይሆን ዘንድ በዩክሬንኛ ተተርጉሞ በዩኒቨርስቲው ቤተመፅሃፍት እንዲቀመጥ ተደረገ። በመምህርነት ተቀጥረው መስራት ከጀመሩ በኋላ ‹‹ THE SYSTEM OF CONFLICT OF RUELS BRIVET INTHERNATIONAL LAW›› የተባለ መፅሃፍ ፅፈው ለህትመት አብቅተዋል።
ዩክሬን በቆዩባቸው ጊዜያት ከመማርና ማስተማሩ ጎን ለጎን ትዳር መስርተው ልጆች ያፈሩት እኚሁ ሰው ከዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ሀገራቸው ለጎብኝት ሲመለሱ ወላጅ አባታቸው አርፈውና የቤተሰባቸውም ሁኔታ ጥሩ አለመሆኑን ሲገነዘቡ እዚሁ ለመቆየትና ቤተሰባቸውን ለመርዳት ብሎም አገራቸውን በምርምር ለማገዝ ይወስናሉ። ሀገራቸውን በምርምር ለማገዝ ከፍተኛ ህልም የሰነቁት እንግዳችን እንዳሰቡት መንገዱ ቀላል አልሆነላቸውም። በተለየዩ የመንግስት ተቋማት ውስጥ ተቀጥረው በጥናትና ምርምር ለመስራት ያቀረቡት ጥያቄ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ስላልሆኑ ብቻ ተቀባይነት በማጣቱ በዩኒቲ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት ተቀጠሩ። በዩኒቨርስቲው በቆዩባቸው ዓመታትም ተቋሙን በመደገፍ፤ የተለያዩ የህትመት ውጤቶችን በማበርከት፤ በዲፓርትመንት ሃላፊነት፤ በሴኔት አባልነት ከፍተኛ ከበሬታን አግኝተዋል። በተደጋጋሚ እውቅና ተሰጥቷቿዋል። በትርፍ ጊዜያቸውም ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ያስተምሩ ነበር።
በርካታ ጥናታዊና የመማሪያ መፅሃፎችን ለማሳተም የቻሉት እንግዳችን የህዝቡን የህግ ግንዛቤ ለማሳደግ ሲሉም በግላቸው የህግ ጋዜጣም ማሳተም ጀምረው ነበር። በተጨማሪም የሥልጠና ማዕከል ከፍተው ሰዎችን ማሰልጠን ጀመሩ። ይህም የስልጠና ማዕከል ‹‹ፕሪቶር ሎው›› ወደተባለ ኢንስቲትዩትነት ብሎም ወደ ኮሌጅነት አደገና በህግ ትምህርት ተማሪዎችን እያስተማረ ዲፕሎማ መስጠት ጀመረ። ኮሌጁ ለአምስት ዙር ተማሪዎችን ካስመረቀ በኋላ ግን የህግ ትምህርት የግል ኮሌጆች እንዳይሰጡ በመንግሥት በመከልከሉ ኮሌጁን ለመዝጋት ተገደዱ። ወድቆ መነሳትን የለመዱት እኚሁ ሰው ተስፋ ሳይቆርጡ የስልጠና እና የህግ ማማከር አገልግሎት መስጠታቸውን ቀጠሉ።
በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ተዘዋውረው በማስተማርም አቅማቸውን ገነቡ። አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ እያሰተማሩ በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ትምህርት ተምረው ተጨማሪ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ያዙ። ይህም ካሪኩለም(ስርዓተ ትምህርት) አዘጋጅተው የራሳቸውን ኮሌጅ ዳግም ለመክፈት አገዛቸው። ከትምህርቱ ዘርፍ ጎን ለጎን በጥናትና በምርምር ዘርፍ የሚታወቁት ዶክተር ግርማ ግዛው የዛሬው የዘመን እንግዳችን ናቸው። በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴና በተለየዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከእንግዳችን ጋር ያደረግነው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- ከሰሯቸው በርካታ የጥናትና ምርምር ስራዎች ውስጥ በአባይ ወንዝ ላይ ያከናወኗቸው የምርምር ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው። ለመሆኑ በአባይ ላይ በተለየ መንገድ ለማጥናትና የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎችን ለማሳተም ያነሳሳዎት ምክንያት ምንድን እንደነበር ያስታውሱንና ውይይታችንን እንጀምር?
ዶክተር ግርማ፡– እንዳልሽው በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በርካታ የጥናት ስራዎችን ለህትመት አብቅቻለሁ። በተለይም አለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ ተቀጥሬ በምሰራበት ወቅት በምስራቅ አፍሪካ ሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ ጥናት አድርጌያለሁ። በዚህም ወቅት በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት በተጎዱ ንፁሃን ዜጎች ጉዳይ ላይ ማጥናትና መመርመር ስጀምር የግብፅ የጦር አውሮፕላን የኤርትራን ጦር ለማገዝ ገብቶ መከስከሱን አነበብኩኝ። በዚህ ምክንያት የግብፅ መንግስት ለምን ማገዝ ፈለገ? ምንስ ነው የሚፈልገው? የሚለውን ነገር መጠየቅና ማጥናት ጀመርኩ። በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ መንግስት በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ ለመስራት ገንዘብ ለማግኘት አለም ባንክን እየጠየቀ ነበር። ግብፅ ደግሞ ገንዘቡ እንዳይሰጥ አለም ባንክ ውስጥ በነበሯት ሰዎች አማካኝነት እንዳይሰጥ የምታደርገውን ጥረት ተገነዘብኩኝ።
በመሆኑም እንደ አንድ የተማረ ኢትዮጵያዊ ወጣት ይህንን የግብፅን አሻጥር ለማጋለጥና ይህንን የሚያሳይ ጥናት አደረኩኝ። በነበረው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሁኔታ በተለይ ደግሞ ጦርነቱ ካደረሰው ጉዳት ሳታገግም በምንም ዓይነት ጦርነት ውስጥ መግባት እንደሌለባት የሚያትት ፅሁፍ ፃፍኩኝ። ያንን እንድፅፍ ያነሳሳኝ ድንበር ተሻጋሪ በሆኑ ወንዞች ምክንያት የሚነሱ ግጭቶችን የአለም ሀገራት እንዴት መከላከልና ማስቀረት እንደቻሉ በማንበቤ ነበር። ስለሆነም ኢትዮጵያ ጦርነትን ከሚቀሰቅሱ አማራጮች ይልቅ በሰላምና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ችግሮችን መፍታት የምትችልበትን ሁኔታ መፍጠር እንደለባት በፅሁፌ ላይ አካተትኩኝ። በነገራችን ላይ ይህንን ፅሁፍ የፃፍኩት ከ21 ዓመት በፊት ነው። በወቅቱ ለአምባሳደር ሥዩም መስፍን ይህንኑ ፅሁፍ ላኩላቸው። በአጋጣሚ በቀጥታ ስለደረሳቸው ምስጋናቸውን በኢ-ሜል አደረሱኝ። የሚገርምሽ እዚህ እንደመጣሁ በቀጥታ እሳቸውን ለማግኘት ነው የሞከርኩት። በወቅቱ ታዲያ ባደረጉልኝ አቀባበልና መስተንግዶ ተማርኬ ስለነበር እዚያው ለመስራትና በጥናት ለመደገፍ ጥያቄ አቀረብኩኝ። እሳቸውም በአጭር ጊዜ ውስጥ ቦታ እንዲሰጠኝ መሩኝ።
ይሁንና የተመደብኩበት ስፍራ የፖለቲካ አባል መሆንን ይጠይቅ ስለነበር እኔ በፈለኩት ዘርፍ መስራት የምችለው በኢንቨስትመንት ኮሚሽን ውስጥ በመሆኑ አቶ ታደሰ ሃይሌ ጋር ይልኩኛል። ይሁንና በዚህ ሰው የተደረገልኝ አቀባበል ጥሩ ሆኖ አላገኘሁትም። በገዛ አገሬ ልጅ ያልጠበኩት መስተንግዶ ስላጋጠመኝ በቀጠሩኝ እለት ቀረሁ። ተመልሼም አልሄድኩም። እንዲያውም በዚያ ምክንያት መንግስት መስሪያ ቤትን ጠላሁኝ። በመሰረቱ በወቅቱ ፍትህ ሚኒስቴር፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ አመልክቼ ተቀባይነት አግኝቼ ሁሉም ጠርተውኝ ነበር። ግን በዚያ ጊዜ ዩኒቲ በጣም እየታወቀ የመጣ ተቋም በመሆኑና ከፍተኛ ከፋይም በመሆኑ እዚያ ተቀጠርኩኝ።
ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ በነበረኝ ቆይታ ከነበሩኝ ሃላፊነቶች በተጨማሪ በርካታ መፅሐፍቶችን አሳትሜያለሁ። ከመፃፍና ከማሳተሙ ባሻገር የሀገሬን ህዝብ የማስተማር ፅኑ ፍላጎት ነበረኝ። በተለይም አብዛኛው ህዝብ የህግ ግንዛቤ የሌለው በመሆኑ እንባውን ወደ ፈጣሪ ከመርጨት ባለፈ መብቱና ግዴታውን ማወቅ ይችል ዘንድ ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ እያለሁ የህግ ጋዜጣ ከጓደኞቼና ከማውቃቸው ታላላቅ ሰዎች ጋር በመሆን ማሳተም ጀመርኩኝ። እግረ መንገዴን እንደህዳሴ ግድብ የሀገሬን ጥቅም በሚያስጠብቁ ፕሮጀክቶች ለአለም ህብረተሰብ በማስተዋወቅ ረገድ የተለያዩ ፅሁፎችን እፅፍ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ውጭ ሀገር እያሉ በፃፉት ፅሁፍ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ምክንያት ጦርነት መግባት የለባትም ሲሉ ግድብ መገንባት የለባትም ማለትዎ ነበር?
ዶክተር ግርማ፡- ፈፅሞ አልነበረም!። አባይ እኮ ከልጅነታችን ጀምሮ ስንዘምርለትና ስንቆጭበት የነበረ ወንዛችን ነው። በወቅቱ የነበረኝ አቋም አስቀድመን ኢኮኖሚያችንን ማሳደግና አቅማችንን ማጎልበት ይገባናል የሚል ነው። በዚያን ጊዜ ግብፆች በተሻለ ሁኔታ ውስጥ ነበሩ፤ እኛ ደግሞ በአንፃሩ በጦርነትና በድህነት ብዙ ፈተና ውስጥ ነበርን። በዚያ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ወደ ጦርነት ብንገባ የበለጠ ተጎጂ የምንሆነው እኛ ነበርን። በመሰረቱ የኢትዮጵያ መንግስትም ፕሮጀክቱን ዘግይቶ ከ11 ዓመት በኋላ ነው ይፋ ያደረገው። አቅሙን ካጎለበተና ጦሩን ካደራጀ በኋላ ነው የአለም ህዝብ እንዲያውቀው ያደረገው። በዚያን ጊዜ ግን ይፋ አድርጎት ቢሆን ኖሮ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ይገጥመን ነበር። እናም ያ ስጋት ስለነበረኝ ነው ያንን ፅሁፍ የፃፍኩት።
አዲስ ዘመን፡- ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በሚመለከት የአገራት ተሞክሮ ምን ይመስላል? የአለም አቀፍ ህጎችስ በምን አግባብ እንዲፈቱ ነው የሚደነግጉት?
ዶክተር ግርማ፡- በመሰረቱ አለም አቀፍ ህግ ማለት የተለያዩ ራሳቸውን የቻሉ ወይም ነፃ ሀገራት የሚመሩበትን ስርዓት የሚዘግቡበት ሁኔታ ማለት ነው። በዚህ መሰረት ከ17ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ የአንድ የውሃ አካል ባለቤትነትን የሚያረጋግጠው በየትኛውም ሉዓላዊ ሀገር ውስጥ ያለ ውሃ የድንበር ወሰን ውስጥ እስከካለ ድረስ የዚያ ውሃ ባለቤት መሆኑና እንደፈለገ መጠቀም እንደሚችል በአለም አለም አቀፍ ደረጃ ተደነገገ። ይሁንና የታችኞቹ አገራት የሚጎዱበት ሁኔታ በመፈጠሩ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚል ነገር መጣ። ለዚህ ደግሞ ወንዝም ሆነ መሬትን የፈጠረው ፈጣሪ በመሆኑ የሰው ልጅ ሁሉ ሊጠቀምበት የሚል ሃሳብ በአንድ አንድ የአለም ሀገራት በመምጣቱ ነው።
አሁን ደግሞ የህዝብ ቁጥርና የወንዞች ተፈላጊነት እየጨመረ በመምጣቱ እኔ ብቻ ልጠቀም የሚለው ነገር አያስኬድም። አንዱ ብቻ የሚጠቀም ከሆነ ደግሞ የውሃ ጦርነት እዚህም እዚያም ሊነሳ ይችላል የሚል ስጋት ተፈጠረ። በመሆኑም እንደዚህ አይነት ችግር በሚፈጠርበት ጊዜ በርካታ የአለም ሀገራት በግልግል ዳኝነት ነው የፈቱት። ለምሳሌ ብንጠቀስልሽ አማዞንና የዱናቤን ወንዞችን መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የሚያልፉባቸው አገራት ችግራቸውን የፈቱት ፍትሃዊ ተጠቃሚ የሚያደርግ ስርዓት በመፍጠር ነው። አሁን ላይ ይህ ስርዓት ልማድ በመሆኑ የተነሳ በአለም ላይ በወንዝ ምክንያት የሚጣላ የለም። ይህ ባህል ሊገነባ ያልቻለው አፍሪካ ውስጥ ነው። በተለይም በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል ብቻ ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድን በአለም ታዋቂ የሆነ ኦፕን ጋየን የተባለ ምሁር እንደፃፈው መንግስትና ድንበር አይለያይም፤ መንግስት ያለወሰን ሊኖር እንደማይችል ይገልፃል። ሌላው የላቲን አሜሪካ አገራት አባል የሆኑበት በእ.ኤ.አ 1933 ዓ.ም ሞንቴንሊዶ ኮንቬንሽን የሚባል ስምምነት ላይ እንደሰፈረውም አንዲት አገር የምትባለው ቋሚ የሆነና የማይዋዥቅ ህዝብ ሰፍሮ ሲኖርባት ነው ይላል። ሁለተኛ የተገለፀው ነገር ድንበር ወይም ወሰን የሚባለው መሬትን ብቻ ሳይሆን ወንዞችና ጅረቶችንም ጭምር እንደሆነ ይገልፃል። በተጨማሪም ራሱን ችሎ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማድረግ የሚችል መንግስት ካለ እንደሆነ ይጠቅሳል። በዚህ መሰረት የአባይ ወንዝ በኢትዮጵያ ሉዓላዊ ክልል ውስጥ እስካለ ድረስ የኢትዮጵያ ነው። ከኢትዮጵያ ሲወጣ ብቻ ነው ሌሎቹ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉት።
ስለዚህ አለም አቀፍ ህግ ይህ ወንዝ ኢትዮጵያ ተፈጥሮ የሰጣት ሃብት ነው። በዚህ ውስጥ ለድርድር የምናቀርበው ነገር የለም። የራሳችንን ጥማት ከተወጣን በኋላ ነው ለሌላው የምንሰጠው። ከእኛ የሚመነጭ እንደመሆኑ እኛ ተጠቅመን የሚተርፈንን ነው ለእነሱ ልንሰጣቸው የምንችለው። አለም አቀፍ ህጉ የሚደነግገው ፍትሃዊ ተጠቃሚነትም ተግባራዊ ቢደረግም ከእኛ ሲተርፍ መጠቀማቸውን አይከለክልም። በቅድሚያ ተጠቃሚ ሊሆን የሚችለው የወንዙ ባለቤት ነው። 86 በመቶ የሚሆነውን ውሃ እኛ እያመነጨን ሌላውን የምንለምንበትና የምንለማመጥበት ሁኔታ ሊኖር አይገባም ነበር። የምንለምንበት ምክንያት በኢኮኖሚ ደካማ በመሆናችን ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የውሃ ድርሻን በሚመለከት ኢትዮጵያ ባልፈረመችው የቅኝ ግዛት ውል ተፈፃሚ እንድታደርግ የሚያስገድድ ህጋዊ አግባብ አለ?
ዶክተር ግርማ፡– ጥሩ ጥያቄ ነው ያነሳሽው፤ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ግን በጥቂቱ ታሪካዊ ዳራውን መፈተሸ ይገባናል። በ1880ዎቹ እንደምታውቂው የአውሮፓ ሀገራት አፍሪካን ለመቀራመት በተስማሙት መሰረት ጣሊያን ኢትዮጵያን በውጫሌ ውል መሰረት ወረረች። እንደምታውቂው ደግሞ ጣሊያን ካልፈቀደች ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት ጋር ግንኙነት ማድረግ እንደማትችል አድርገው ነው አሳስተው ያስፈረሙን። ይህ ውል አገርን አሳልፎ የሚሰጥና ለጣሊያን ያጋደለ መሆኑን አፄ ምኒሊክና እቴጌ ጣይቱ ሲረዱ ለመኑ፤ አስለመኑ። ግን ስልተሳካላቸው ወደ ጦርነት ገቡ። እናም በአድዋ ጦርነት ድል አደረግን። የሚገርመው ነገር እ.ኤ.አ በ1890 ዓ.ም የእንግሊዝ መንግስት እንግሊዝ በአባይ ወንዝ ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን አለባት የሚል አዋጅ አወጣ። ከአድዋ ጦርነት ሳናገግም በስድስተኛው ዓመት ሌላ አጀንዳ እንግሊዝ ይዛ መጣች።
እ.ኤ.አ በ1902 ዓ.ም አምስት አንቀፆች ያሉት ውል በተሳሳተ መልኩ በተወካያቸው አማካኝነት እንድትፈርም አድርገዋታል። በተለይም አንቀፅ ሶስት ላይ እንደተደነገገው አባይን ከእንግሊዝ መንግስት ጋር አስቀድሞ ሳይስማሙ ወንዙ ላይ ምንም ዓይነት ስራ መስራትም ሆነ ለሌላ አካል አሳልፋ መስጠት እንደማትችል ነው የተቀመጠው። ይህንን ውል ያስፈረሙት እጅ ጠምዝዘው ነው። በዚህ ዙሪያ ያገኘኋቸው ፅሁፎች እንደሚያስረዱት ይህንን የፈረሙት አፄ ምኒሊክ ሳያውቁ ወይም አሳስቶ ቃል አቀባያቸው እንደፈረሙት ነው። የአባይን ውሃ ከእንግሊዝ ውጭ ማንም ሰው መቆጣጠር እንደማይችል፤ ኢትዮጵያ ምንም መብት እንደሌላት አድርጋ ነው የደነገገችው።
ከዚህ በተጨማሪም እ.ኤ.አ 1929 ዓ.ም ኢትዮጵያን ያገለለ፤ ግን ደግሞ በቅኝ ግዛት ከያዘቻቸው ታንጋኒካን፤ ኡጋንዳንና ኬንያን ወክላ ከግብፅ ጋር ተዋውላለች። በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበት ስምምነት ነው የምንለው ይህንን ውል ነው። ግብፅ 48 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የውሃ ድርሻ እንዲኖራት፣ ሱዳን አራት ቢሊዮን ብቻ እንዲደርሳት የተስማሙበት ነው። ሌላው እጅግ በጣም የሚገርመው ነገር ይኸው ስምምነት ሌላ የሰጣት መብት አባይን ብቻ ሳይሆን የአባይን ወንዝ ገባሮችንም ጭምር መቆጣጠር እንድትችል ነው። ለራሷ ጥቅም ማዋል እንድትችል የሚያደርግ ውል ነው የተፈራረሙት።
ይህ ውል 86 በመቶ የሚሆነውን ውሃ የምታመነጨውን ኢትዮጵያን ያገለለ ነው። ኢትዮጵያ የማታውቀው ፍትሃዊ ያልሆነ ስምምነት ነው። በእ.ኤ.አ 1959 ዓ.ም ደግሞ ሶስተኛው ውል የተደረገው በግብፅና በሱዳን አማካኝነት ነው። ይህ ውል ለግብፅ ተሰጥቶ የነበረው የውሃ ድርሻ ወደ 55 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ከፍ ያደረገና ሱዳን ደግሞ ወደ 18 ነጥብ 5 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ከፍ በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተስማሙበት ነው። የውሃው መጠን ከጨመረ እኩል ለመጠቀም አጨብጭበው ተፈራርመው የተለያዩበት ነው። ይህ ሲሆንም ኢትዮጵያ የለችም። የዚህ ሁሉ ዋና መሰረቱ እንግሊዝ ናት።
አዲስ ዘመን፡- ከተጠቀሱት ውሎች አንፃር ነባራዊ ሁኔታና አለም አቀፍ ህግ ግብፅ እየተከተለች ያለችው መንገድ ምን ያህል አዋጭ ነው ተብሎ ይታመናል?
ዶክተር ግርማ፡– በምንም መልኩ ይህንን ጊዜ ያለፈበት ውል ለማስቀጠልም ሆነ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አለም አቀፍ ህግም ሆነ ነባራዊ ሁኔታ የላትም። ግብፅ ራሷ የቅኝ ግዛት ውሉ ተፈፃሚ ሊሆን እንደማይችል አሳምራ ታውቃለች። እርግጥ ነው በጦር መሳሪያ በአፍሪካ ቀዳሚ ሀገር ናት። በአለምም ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ካላቸው አገራት ተርታ ነው የምትሰለፈው። ይህች አገር አባይን የህልውናዋ መሰረት በመሆኑ ያንን ውሃ የግሏ አድርጋ ለዘለዓለም ለመቆጣጠር ያስችላት ዘንድ ለዘመናት ራሷን በጦር መሳሪያ ስታስታጥቅ ነው የኖረችው። በተለይም የውሃው ምንጭና ባለቤት የሆነችውን ኢትዮጵያ በሃይል አሽመድምዳ ለማስቀረት ወደኋላ አትልም።
እስካሁን ያላደረገችበት ምክንያት ብዙዎቹ እንደሚሉት ኢትዮጵያ በጦርነት ጀግኖችና ሁልጊዜም እንደሚያሸንፉ ስለሚታወቅና በአንፃሩ ደግሞ ግብፅ ምንም እንኳን በጦር መሳሪያ የላቀች ብትሆንም ጄነራሎቿ በተግባር ያልተፈተኑ እንዲሁም አቅም የሌላቸው በመሆኑ ልሸነፍ እችላለሁ የሚል ስጋት ስላላት ነው። ይህ ብቻ ግን አይደለም ያለው፤ አለም አቀፍ ህጉ እንደማይፈቅድላት ስለምታውቅም ጭምር ነው ደፍራ ወደ ጦርነት ያልገባችው። ይህንን ብታደርግ በአለም ህዝብ ዘንድ መዋረዷ እንደማይቀር በሚገባ ትገነዘባለች። ያሏት ምሁራኖችም ቢሆኑ ሊደርስባት የሚችለውን አለም አቀፍ ውርደት ሳያስገነዝቧት የሚቀር አይመስለኝም።
ስለዚህ ምርጫ አድርጋ ያየዘችው ኢትዮጵያን በእጅ አዙር ማዳከም ነው። እርስ በርስ እንድንባላ የተገኘውን ሁሉ ቀዳዳ ትጠቀማለች። በአሁኑ ወቅት ግብፅ በቀጥታ ከመምጣት ይልቅ የውክልና ጦርነት ማካሄዱ ላይ ተጠምዳለች። ይህም ማለት እዚህ ያኮረፈውን ሁሉ በገንዘብና በመሳሪያ በመደገፍ በሀገር ውስጥ ሰላም እንዳይኖር ማድረግና ለመንግስት የቤት ስራ ትሰጣለች። በኢኮኖሚ ወደፊት እንዳይሄድ እያባሉን፣ እየከፋፈሉን በፕሮጀክቱ ዘልቀን እንዳንሄድ፣ ወደፊት እንዳናስብ፣ የጀመርነውን እንዳንጨርስ ነው የተለያዩ ሴራዎችና አሻጥሮችን እያደረገች ያለችው። በአፍሪካ በጦር መሳሪያ ግዙፍነቷና በኢኮኖሚም የተሻለች እንደመሆንዋ ዓላማዋን ማሳካት በቻለች ነበር። ነገር ግን ከዚያ በላይ አለም አቀፍ ህግም ሆነ ሀገራት የማይደግፏት መሆኑን ስለምታውቅ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከግብፅ ወገን የተሰለፉ አገራት ግብፅ የጀመረችው መንገድ እንደማያዋጣትና በህግም የማይደገፍ መሆኑን ሳያውቁ ቀርተው ነው ወይስ የተለየ ምክንያት ስላላቸው ነው?
ዶክተር ግርማ፡- እነዚህ ሀገራት የሚደግፏት ለፖለቲካቸው ጥቅም ሲሉ ነው። እንደሚታወቀው የአለም ሀገራት የፖለቲካ ጎራ አላቸው። ለምሳሌ አሜሪካና እንግሊዝ በአንድ ጎራ ወይም የፖለቲካ አሰላለፍ ላይ ነው ያሉት። በታሪክም እንደታወቀው አንዳቸው የአንዳቸው ደጋፊ ሆነው ነው የኖሩት። ምክንያቱ ደግሞ አሜሪካ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የነበረች አገር በመሆንዋ ሁለመናዋ የእንግሊዝ ቅጅ ነው፤ ደግሞም ታሪካዊ የሆነ ትስስር አላቸው። ወደ መካከለኛው ምስራቅ ስትመለከችም የምታገኚው ተመሳሳይ ሁኔታ ነው። ግብፅ አፍሪካ ውስጥ ሆና ራስዋን እንደአፍሪካዊ አድርጋ የማትቆጥር ሀገር ነች። እንዲያውም ‹‹አረብ ነኝ›› ብላ የአረብ ሊግ አባልና በአባል ሀገራቱ መካከል ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሀገር ናት። እነዚህ ሀገራት በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካ የተሳሰሩ ከመሆናቸው የተነሳ በዚህ ዓይነት አጣብቂኝ ጊዜ ከእሷ ጋር መቆም አለብን በሚል እንጂ መቶ በመቶ በህግ ብትሄድ ያዋጣታል በሚል አይደለም የሚደግፏት።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የአለም አቀፍ ህጉ እንደሚደግፋት ከታወቀ ጉዳዩ ለምን ወደ አለም አቀፍ ፍርድቤት እንዲሄድ አልፈለገችም ታዲያ?
ዶክተር ግርማ፡– ለመሆኑ የአባይ ወንዝ የእኛ ሀብት መሆኑ እየታወቀ ለምንድን ነው አለም አቀፍ ፍርድ ቤት መሄድ የሚያስፈልገን? ለምንስ ነው በዚህ መልኩ ወደ ድርድር የምንሄደው? መቶ በመቶ የእኔ መሆኑን እያወኩኝ አለምም እያወቀ ሌላ ጊዜ ለምንድነው የምናባክነው?። ግብፅ እኮ ይህንን የምታደርገው ለማደናገሪያ ነው። እንደማይወሰንላት ታውቃለች። ፕሮጀክቱን ለማዘግየትና በመሃል ላይ ለማተራመስና ኢትዮጵያ በኢኮኖሚና በፖለቲካ አለመግባባት ተፈጥሮ ወደቀውስ እንድንገባ ከማለም ነው።
ይህንን ጉዳይ በአግባቡ ማየት ያስፈልጋል። ራሺያና ቻይና የተቃወሙት እኮ ኢትዮጵያን ስለወደዷት ብቻ አይደለም፤ ፍትሃዊ አለመሆኑንና በህግም የማይደገፍ መሆኑን በማወቃቸው እንጂ!። ሌሎቹም ቢሆኑ ይህንን ሳያውቁ ቀርተው አይደለም። የፖለቲካ ጥቅም ስለሚያገኙበት ነው። አሜሪካ ህግ ያደገበት የበለፀገበት አገር ሆና ሳለ በከፍተኛ የህግ ጥሰት መሪም ናት። ይህም የሚሆነው ከፖለቲካና ኢኮኖሚ ጥቅም አንፃር ነው። ጥቅማቸውን የሚነካ ሆኖ ከተገኘ እንደዚያ የሚመፃደቁበት ህግም ቢሆን ያለምንም መወላወል የሚጥሱት እነሱ ናቸው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ወደዚያ የምትሄድበት ምክንያት የለም።
እርግጥ ነው በህጉ መሰረት ኢትዮጵያ 86 በመቶ ውሃ የምታመነጭ አገር እንደመሆንዋ ከየትኛው የተፋሰሱ ሀገራት ቅድሚያ ሊሰጣት ይገባል። ኢትዮጵያ አባይን ለመጠቀም በተፈጥሮም ሆነ በአለም አቀፍ ህግም ትደገፋለች። ግብፅ ይህንን እውነት አሳምራ ብታውቅም ጉዳዩ በፍርድ ቤት ተይዞ ፕሮጀክቱ እንዲስተጓጎል ነው። ግብፅ ያላትን ሁሉ አማራጭ ከመጠቀም ወደኋላ እንደማትል በመገንዘብ ሁልጊዜ የምታነሳውን አጀንዳና ወሬ ወደ ጎን ትተን ዝም ብለን ስራችንን ማስቀጠል ነው የሚገባን።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ምንአለባት ሰሞኑን የአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያ በምታደርገው ምርጫ ያቀረበችውን ቅድመ ሁኔታ መንግስት በእጅ አዙር ቅኝ ለመግዛት ያለመ መሆኑን ተገንዝቦ መቃወሙ የሚደነቅ ነው። እነዚህ ሰዎች በሁሉም አቅጣጫ የኢትዮጵያን ሞራል የሚነካ ስራ ነው እየሰሩ ያሉት። እኛ በአቋማችን ስንፀና ይኸው በራሳቸው ጊዜ ለመምጣትና ለመታዘብ ጥያቄ አቀረቡ። አንድ ጊዜ ምን ሆነ መሰለሽ! በ1928 ዓ.ም ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ ሀገራችን የሊግ ኦፍ ኔሽን አባል እንደመሆኗ በድርጅቱ ህግ መሰረት ጉዳዩ እንዲታይላት ቅሬታዋን ስታቀርብ የአውሮፓ ሀገራት ተፅዕኖ መፍጠር እየቻሉ የእንግሊዝ ንግስት ‹‹ እንግሊዝ ሴት ንግስት ናት፤ ሴት ደግሞ ጀግና ነው የምትወደው›› የሚል ምላሽ ነው የሰጠችው።
ይህም ማለት ኢትዮጵያ ከቻለች ታሸንፍ ካልቻለች ለጣሊያን እጇን ትስጥ ማለት ነው። ስለዚህ ምንም እንኳን ህግ የበላይ ቢሆንም ከህግ በላይ ሃይል የበላይ ሆኖ ነው የሚታየው። ይህም ማለት ሃይል ካለሽ በሃይል ሁሉንም ከወሰድሽ በኋላ ህጋዊ ታደርጊያለሽ፤ ህጉን ይዘሽ ህጉን ሃይል አደርጋለሁ ብለሽ ከተነሳሽ ትችያለሽ። የአለም ሁኔታ ይህንን ነው የሚያሳየው። ሃይል ጦር ብቻ አይደለም፤ በኢኮኖሚና በቴክኖሎጂ ሃያል መሆን ይጠይቃል። እኛም አሁን ያለን አማራጭ በሁሉም አቅጣጫ ሃይላችንን ማጠናከር ነው። ጠንካራ የሆነ ጦር ሰራዊት፣ ኢኮኖሚ፣ ቴክኖሎጂ መገንባት መቻል አለብን። ራሺያ አውሮፓን ማሸነፍ የቻለችውና አሜሪካንን የምትገዳደረው በሁሉም ነገር ሃይሏን ማጠናከር በመቻሏ ነው። ይህ ባይሆን ኖሮ ቀድመው የሚያጠፏት ራሺያን ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አንፃር ከግብፅና ከሱዳን ውጭ ያሉ የተፋሰሱ ሃገራት መብታቸውን በምን መልኩ ነው ሊያስጠብቁ የሚገባው ይላሉ?
ዶክተር ግርማ፡– ትክክል ነሽ፤ እስካሁን ባለው ሁኔታ የተፋሰሱ ሃገራት በርካታ ቢሆኑም ለዘመናት ያለማንም ተቀናቃኝ ግብፅና ሱዳን ነበር በውሃው ሲጠቀሙበት የኖሩት። በተለይም ግብፅ በብቸኛ ባለቤትነት በአባይ ወንዝ ኢኮኖሚዋን ማሳደግ ችላለች። ይህ ሁኔታ ግን ለዘላለም ሊቀጥል አይችልም። በቅርቡ ህንድ ሀገር ባሳተምኩት ፅሁፌ ላይ እንዳሰፈርኩትም በአሁኑ ጊዜ የአፍሪካም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ነው ያለው።
ይህ እየጨመረ ያለ ህዝብ ፍላጎቱን ለማርካት ሲል ያለውን የተፈጥሮ ሃብት መጠቀሙ አይቀሬ ነው። በመሆኑም ግብፅ ከዚህ ቀደም ትከተል በነበረው አካሄድ መቀጠል አትችልም። ሁሉም የተፋሰሱ አገራት የህዝባቸውን ፍላጎት ለማሟላትም ሆነ ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ ይህንን ውሃ መጠቀማቸው አይቀሬ ነው። ስለዚህ ግብፅ ማሰብ የሚገባት ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ሌሎችም አገራት ተመሳሳይ ፕሮጀክት የመገንባትና የመጠቀም መብት እንዳላቸው ነው። በመሆኑም ይህንን እውነት ብዙ ሳይረፍድባት ተገንዝባ ለሠላማዊ ውይይት በሯን መክፈት መቻል አለባት።
ከዚህም በላይ የውሃው መጠን እንዳይቀንስባት በተፋሰሱ ሀገራት ስነምህዳሩን ለማስጠበቅ መደገፍ ነው የሚገባት። የናይል ኢንሼቲቭ ስምምነት አንደሚለውም የተፋሰሱ ሀገራት መሰረታዊ ጉዳት ሳያደርሱ መጠቀም እንደሚችሉ ይደነግጋል። ግብፅ አሁን ላይ በሰላማዊ መንገድ መቀጠል ካልፈለገች መሰረታዊ ጉዳት በሚያደርስ መልኩ ሊጠቀሙ ይችላሉ። ግብፅ የእኛ ግድብ መስራት ሳይሆን ሊያሳስባት የሚገባው ሌሎች አገራትም ተመሳሳይ ግድብ ሰርተው ተጨማሪ ራስ ምታት እንዳይፈጠርባት ነው።
ምክንያቱ ደግሞ አስቀድሜ እንደጠቀስኩልሽ እነሱም መብታቸው በመሆኑ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ግብፅ ከአፍሪካ ሀገራት ሁሉ በኢኮኖሚም፣ በዲፕሎማሲም፤ በተማረ ሰው ሃይል ነኝ የሚል ከፍተኛ የሆነ እብሪት አላት። ይሁንና ኢትዮጵያም ሆነ ሌሎች ሀገራት ከግብፅ ያልተናነሰ አቅም እያጎለበቱ ነው። በተለይም በዲፕሎማሲ ኢትዮጵያን ማታለል አትችልም። በርካታ ኢትዮጵያም ሆነ ሌሎች ሀገራት ከፍተኛ የተማረ ሃይል እያፈሩ ነው። በመሆኑም ግብፅ ካለችበት እብሪት መውጣት አለባት።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ደግሞ ከድህነት ለመውጣት ብቸኛው አማራጭ ስራ መሆኑን ማወቅና መንቀሳቀስ ይገባታል። አሁን ላይ ብዙዎቻችን በወሬ ነው ጊዜያችንን እያጠፋን ያለነው። በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ኢኮኖሚያችንን ከማበልፀግ ይልቅ የተሰራውን ማጥፋት ላይ ነው ትኩረት እያደረግን ያለነው። በየቦታው ክቡር የሰው ህይወት እየተቀጠፈ፣ ለዘመናት የተለፋበት ሃብት እየወደመ ነው ያለው። ትውልዱ የማደግ ራዕይ ሰንቆ ከመስራት ይልቅ እዚሁ ዳዴ እያ ፣ እርስ በርስ እየተባላ መኖርን ነው የሚመርጠው። ከሁሉ በላይ የሚያሳዝነው ከውጭ ጠላት ጋር በማበር የገዛ አገሩን ለማጥፋት የሚጥር ኢትዮጵያዊ መኖሩ ነው። ህዝቡ የውጭ ጠላቶቻችን አላማ ሊገነዘብና ሊነቃ ይገባል።
ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ናት፤ ስርዓተ ህግም ከአፍሪካ ቀድማ ነው ያደገችው። በነፃነትም በዲፕሎማሲም ትቀድማለች። ግን አሁን ባለንበት ሁኔታ ስርዓተ ህግ የሌለ እስከሚመስል ድረስ በከፍተኛ ማዕበል ውስጥ እየተናወጥን ነው ያለነው። የሃይማኖት አባቶች የማይከበሩባት፣ ስርዓተ ህግ የማይከበርበት፤ መሪ የማይከበርበት፤ ዜጋ እንደዜጋ የማይቆጠርበት ሁኔታ ውስጥ ገብተናል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ እዚህ ያለውን ዜጋ ለመግደልም ለማስገደልም ከውጭ ዜጋ ጋር የሚሻረክ፣ ሀገር ለማፍረስ ከጠላት ጋር የሚሰራ ኢትዮጵያዊ መበራከቱ ነው። ይህ ለእኔ እርግማን ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግስት ለሀገር ሰላም ጠንቅ የሆኑ አካላት ምህረት የለሽ ቅጣት መቅጣት ይገባዋል። በአለም ላይ የሌለ ቅጣት እስከሚባል ድረስ ሀገርን አሳልፎ የሚሰጥ፤ ሀገር ላይ የሚዶልት የሚያስዶልተውን መቅጣት ይጠበቅበታል። አሁን ላይ መንግስት ስርዓተ ህጉን እያስከበረ አይደለም። ወንጀለኞችን ከሃዲዎችን እሽሩሩ ማለት አያስፈልግም።
በእኔ እምነት በመዋቅሩ ውስጥ ያለው አካል ራሱ በችግሩ ውስጥ የተዘፈቀ በመሆኑ ነው ችግሩ እየተባባሰ የሄደው። እስካሁን ድረስ ህግ በዚህች ሀገር ላይ ተፈፃሚ ያልሆነው እስካሁን ድረስ ራሳቸው ውስኪ እየጠጡ ህግን ይፈጥራሉ፤ ለምክር ቤት ቀርቦም ይፀድቃል። ህጉ ሲጀመርም መሰረት የለሽና የእነሱን ጥቅም የሚያስከብር ነው። በአንፃሩ ደግሞ የሌላው መብት ሲጣስ ዝም ይላሉ። ምክንያቱም ሲጀመርም ለማወናበጃ የወጣ ህግ ነው እንጂ ህዝቡ ተወያይቶበትና አምኖበት አይደለም የፀደቀው። ይህም በአጠቃላይ ከዘመነ መሳፍንት የባሰ ሁኔታ ውስጥ ከቶናል። በጭራሽ የሰው ልጅ አዕምሮ ሊቀበለው በማይችልበት ሁኔታ ነው ያለነው።
ስለዚህ ግልፀኝነት የጎደለው አካሄድን ነው እየተመረጠ ያለው። ህዝብ የሚያምንበት ተዓማኒ የሆነ ስርዓትም ሆነ መሪ መፍጠር አልተቻለም። ፍትሃዊ የሆነ ስርዓት የሚያሰፍን መሪ ከሆነ እኮ ህዝቡ ወርቅ ይሸልማል። ከሁሉም በላይ ህዝብ ከረካ መሪውን ሊሸከመው ይችላል። የሚያወጣው ህግ ህዝባዊ መሆን አለበት። ህዝቡ የተወያየበትና የሚያውቀው ህግ መሆን አለበት። ይህም ከሆነ በኋላ ህጉ መከበር መቻል አለበት። ይህ ሊሆን የሚችለው ግን ህጉን በሚጥሱ አካላት ላይ መንግስት ምህረት የለሽ ርምጃ መውሰድና እሹሩሩ ማለት ማቆም ሲቻል ነው። ከወንጀለኞች ጋር በአገር ሽማግሌ፣ በአባ ገዳና በሃይማኖት አባቶች መሸማገል አያስፈልግም። አሁን ባለንበት ሁኔታ ይህ አካሄድ ውጤት ከማምጣት ይልቅ ጉዳት ነው እያስከተለ ያለው። ደግሞም እንደእኔ እምነት ትውልዱ ሽምግልና ይቀበላል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው። በአጠቃላይ ያለንበትን ችግር መፍታት የሚችለው ህግና ስርዓት ብቻ ነው። መሪ ጠንካራ ውሳኔ ሊኖረው ይገባል። የህግ መላላት ነው በየቦታው ግጭት እንዲበራከት ያደረጉት።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የውሓ ሙሌት ለማካሄድ ዝግጅት ላይ ናት። ግብፅም ይህ አንዳይሆን የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገች ነው። ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ መንግስት ሊጠነቀቅ ወይም ሊሰራ ይገባል የሚሉት ነገር አለ?
ዶክተር ግርማ፡- ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር ውሃ እንደምትሞላ በበኩሌ ምንም ጥርጥር የለኝም። ግብፅ ምንም ዓይነት ጥረት ብታደርግ ታሸንፋለች የሚል እምነት የለኝም። ምክንያቱም እውነትን የያዘ ተሸንፎ አያውቅም። ነገር ግን አስቀድሜ እንዳልኩልሽ ጠላቶቻችን ለክተው በሚሰጡን አጀንዳ እርስ በርስ እየተባለን ለግድቡ ያለንን ትኩረት ልንቀንስ እንችላለን የሚል ስጋት አለኝ። ስለዚህ ለገንዘብ ብለውና ከግብፅ ጉርሻ ተቀብለው ሀገርን ወደነውጥ የሚከቱ አካላትን ስርዓት ማስያዝ ይገባል። እርግጥ ነው ህዝብን ለማጣላት የተለያዩ አጀንዳዎችን የሚፈጥሩ አካላት ውሎ ሲያድር በህዝቡ መተፋታቸው አይቀርም። አሁን እነሱ የሚናገሩት ነገር በታሪክ መዝገብ ላይ እየተመዘገበ ነው፤ አንድ ቀን መጥፋታቸውና እንደዜጋ መኖር እንኳን የማይችሉበት ሁኔታ መፈጠሩ አይቀርም። የዘሩትን ማጨዳቸውም አይቀሬ ነው። በመሆኑም ካሉበት ሁኔታ ፈጥነው ሊወጡ ይገባል የሚል እምነት ነው ያለኝ።
በሌላ በኩልም አሁን ወቅቱ የወሬ አይደለም፤ የሳይንስና ምርምር ነው። ኢትጵያውያን በሱዳን፣ በግብፅ፣ በአባይ ወንዝ ላይ ምርምር ማድረግ መቻል አለባቸው። እኔ በበኩሌ በሰራኋቸው ምርምሮችና ፅሁፎች ደስተኛ ነኝ። በዚህ ረገድ ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ የተመራመሩና በአለም ታዋቂ በርካታ ምሁራን አሏት። ሌሎች ኢትዮጵያውያን ምሁራኖችም ከማውራት ይልቅ የተማሩትን እውቀት በተጨባጭ ስራ ላይ ማዋል፣ ለሀገራቸው የሚጠቅም የምርምር ውጤት ማበርከት፣ የመፍትሄ ሃሳብ ማምጣት መቻል አለባቸው። የግብፅ ምሁራን በአባይ ወንዝ ላይ ተክነዋል።
በአለም ዘንድ የአባይ ፖለቲካን ቀይረዋል። እኛም እውነቱን የሚያሳይልን ምርምር መስራትና መፃፍ መቻል አለብን። እነሱ እረፍት የላቸውም። አሁን ላይ ሁለተኛው ዙር ቢሳካማ እንኳን ሶስተኛው ዙር እንዳይሞላ ሊሰሩ ይችላሉ። በመሆኑም አሁን ኢትዮጵያን ከጦርነት አማራጭ ይልቅ የምሁራን የምርምር ውጤት አለምን ሊያሳምን እና ተቀባይነት ሊያስገኝልን እንደሚችል አምነን በህብረት መስራትና መንቃት ይገባናል። ምክንያቱም ጊዜው የሚጠይቀው ይህ ነው።
በዚህ ረገድ እኔ ሌላ እየፃፍኩት ባላው መፅሃፍ እኛ በአባይ ላይ እንኳንስ ግድብ መገደብ አይደለም ገና ግብፅን መክሰስ የሚያስችል ምክንያት እንዳለን ነው ለማሳየት እየሞከርኩኝ ያለሁት። ይህም ማለት ግብፅ ውሃችንን ብቻ ሳይሆን በየአመቱ በገፍ እየወሰደች ላለችው ለም አፈራችን ካሳ ልትከፍለን ይገባል። ወደኋላ ተመልሰን የሁለት ሺህ ዓመታት ካሳ መጠየቅና ካልከፈለች ውሃችንን ልንይዝባት እንደምንችል ልንነግራት ይገባል። ይኼ በተጨባጭ ባይተገበር እንኳን መነጋገሪያ አጀንዳ ልናደርገው ይገባል። በዚህ መልኩ ለአለም ህዝብ ግንዛቤ ማስጨበጥ ከቻልን ግብፅ ወደ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት አቋም ሳትወድ በግዷ ትመጣለች።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ አንድ አሜሪካዊ የፃፈውን ምሳሌ ልጥቀስልሽ፤ ለአሜሪካ ገበሬዎች ያለማዳበሪያ እርሻ አይታሰብም። ያለው አማራጭ ማፈራረቅ አሊያም መሬቱን ፆሙን ማሳደር ነው። ነገር ግን የግብፅ ገበሬዎች በየአመቱ አዲስና ንፁህ አፈር ያገኛሉ። የታደሉ ገበሬዎች እንደሆኑ ይህ አሜሪካዊ ፃሃፊ ያነሳል። ይህንን ለም አፈር የሚያገኙት ከኢትዮጵያ መሆኑ የበለጠ የሚያስቆጭ ነው። ስለዚህ እኛ መጠየቅ ያለብን በውሃችን ብቻ ሳይሆን በአፈራችንም ጭምር ነው። የጠየቅነውን ያህል ባይሆንም እንኳን የተወሰነ ካሳ ክፍያ መጠየቅ የምንችልበት እድል አለ። ይህ ባይሆን እንኳን ግብፆች አፋቸውን እንዲዘጉ ማድረግ ይቻላል። ይህንን ማድረግ ከቻልን ያጣነውን ማስመለስና መብታችንን ማስከበር እንዲሁም ተከባብረን መኖር እንችላለን። ለዚህ ደግሞ ምሁራኖች ቀን ከሌሊት መስራት አለብን።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሠግናለሁ።
ዶክተር ግርማ፡- እኔም አመሠግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ግንቦት 7/2013