– -አቶ አለማየሁ ጢሞቴዎስ የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ
ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ውስጥ አምስት ምርጫዎችን ማካሄዷ ይታወሳል።በእነዚህ በአምስት የምርጫ ሂደቶች የተከሰቱ በጎም ከፉም ተግባር እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን፣ እንደየአመጣጣቸውም ምላሽ ተሰጥቶባቸው የጊዜ ጅረቱ እየፈሰሰ ስድስተኛው አገር አቀፍ እና ክልላዊ ምርጫ ላይ አድርሷታል።ይህም ምርጫ ሊካሄድ የቀረው ጊዜ ቢኖር የሳምንታት ያህል እድሜ ብቻ ነው።በዚህ ምርጫ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ብቻ ሳይሆኑ መላ ህዝቡም በሚያስብል ደረጃ ስለጉዳዩ ማሰላሰል ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል።በርካቶችም የመራጭነት ካርዱን በእጃቸው አስገብተዋል።
በዚህ አገር አቀፍ ምርጫ በጸጥታው ችግር ምክንያት የማይካሄድበት ክልል የመኖሩን ያህል፣ በሌሎች ክልሎች ያሉ አንዳንድ ዞኖችም ውስጥ ካለው የሰላም መደፍረስ የተነሳ ስጋቶች እንዳሉ እሙን ነው።ከዚሁ ከስድስተኛው ምርጫ ጋር ተያይዞ አዲስ ዘመን ከጥቂት ወራት በፊት የክልል ምስረታ ያካሄደውን የሲዳማ ክልል ለዚህ አገር አቀፍ ምርጫ በተለይ በሰላም እና በጸጥታው ዙሪያ እያካሄደ ስላለው እንቅስቃሴ አስመልክቶ ከክልሉ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቴዎስ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጎ እንደሚከተለው አጠናቅሮ አቅርቧል።መልካም ንባብ ይሁንልዎ።
አዲስ ዘመን፡- ስድስተኛው አገር አቀፍ እና ክልላዊ ምርጫ ላይ የሚሳተፉ መራጮች ካርድ መውሰዳቸው ይታወቃል፤ በሲዳማ ክልል በእስካሁኑ ሂደት ያለው የሰላሙ ሁኔታ እንዴት ይገለጻል?
አቶ አለማየሁ፡- ስድስተኛው አገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫን በተመለከተ አጠቃላይ ሁኔታው በክልላችን ሲስተዋል ያለው ሁኔታ ሰላማዊ ነው።እኛ ደግሞ ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን እንደክልል መንግስት የራሳችንን እቅድ አዘጋጅተናል።ይህም እቅድ ከምርጫ አስቀድሞ የሚተገበር ስራ እና በምርጫው ወቅት የሚሰራ ሲሆን፣ እንዲሁም ከምርጫው በኋላ የሚተገበር በሚል ነው በሶስት ፈርጅ በመከፋፈል አቅደን ለማከናወን በመንቀሳቀስ ላይ የምንገኘው።ይህም እቅድ አጠቃላይ የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ የዳሰሰ ሲሆን፣ ያቀድናቸው እቅዶች ስለመሳካታቸው ደግሞ በየደረጃው ያለ ራሱን የቻለ ኮሚቴ አደራጅተናል።የእቅድ ዝግጅቱ ከተገመገመ በኋላም ነው ወደ ትግበራም የገባነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በሲዳማ ክልል ያሉት የምርጫ ጣቢያዎች 2 ሺህ 242 ሲሆኑ፣ በሌላ በኩል ደግሞ 19 የምርጫ ክልሎች ናቸው ያሉት።በእነዚህ ቦታዎች የሚደረጉ በርካታ እንቅስቃሴዎች ስለመሆናቸው እርግጥ ነው።በተለይም የምርጫ ቁሳቁስ፣ ለምርጫ የሚቀርቡ እጩዎች እንዲሁም የምርጫ አስፈጻሚዎችን ጨምሮ ሁሉም ከምርጫው በፊት የሚከናወኑ ሂደቶች ናቸው።
እነዚህም ጉዳዮች የምርጫ ሂደቶች ሰላማዊ ይሆኑ ዘንድ በቅድመ ምርጫ የያዝናቸው እቅዶች ናቸው።በእስካሁኑም በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ምንም አይነት እክል እንዳያጋጥም በተለይ የምርጫ ቁሳቁስ ከማዘዋወር እንዲሁም ጥበቃ ከማሰማራት እና መራጮች መምረጥ የሚያስችላቸውን ካርድ እስኪወስዱ ድረስ ያለው ሂደት ፍጹም ሰላማዊ እና በተቀመጠውና በታቀደው ልክ እየተሰራ ያለ ተግባር ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ያጋጠመን ምንም አይነት ችግር የለም።ነገር ግን አንድ በክልላችን ለአንድ ተፎካካሪ ፓርቲ እጩ አባል ሆኖ የቀረበ ተወካይ በማጭበርበር ወንጀል በመጠርጠር ተይዞ መታሰሩን ልገልጽ እወዳለሁ።የወንጀሉ መነሻ የሆነው እና ለእስር የዳረገው ነገር የራሱ ያልሆነውን ቤት የራሴ ቤት ነው በማለት የተጭበረበረ (ፎርጂድ) ፕላን በማዘጋጀት ከሚገዛው ሰው ጋር ዋጋ የተስማማ ሲሆን፣ ይህም ወደ ሁለት ሚሊዮን ብር ያህል መሆኑ ታውቋል፤ ግለሰቡ ስምምነት በማድረግ እና ከተጠቀሰው ብር ላይ ደግሞ ቀብድ 20 ሺህ ብር በመቀበል ቤቱ አካባቢ ሄዶ ሊሸጥ ያሰበውን ቤት ይህ ነው የእኔ ቤት እያለ ሲናገር የነበረ ሲሆን፣ የቤቱ ባለቤትም በወቅቱ ወጥቶ ሊይዘው ችሏል።ይህንንም ጉዳይ ለሚመለከተው ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሪፖርት አድርገናል።ከዚህ ክፍተት ውጭ በተፎካካሪ ፓርቲ በኩልም ሆነ በገዥው የብልጽግና ፓርቲ በኩል ያጋጠመን ችግር የለም ማለት ይቻላል።
ይርጋለም ከተማ ላይ ግን አንድ የምርጫ ማስፈጸሚያ መረጃ የያዘ ፍላሽ ጠፍቶ የነበረ ሲሆን፣ እሱም ቢሆን በዛ አካባቢ የተመደበ ተረኛ ፖሊስ ሊያገኘው ችሏል።ከዚህ በተጨማሪ ያጋጠመን ነገር ቢኖር በሐዋሳ ከተማ በአንደኛው ምርጫ ጣቢያ ላይ ለጥበቃ የተመደቡ አባላት የጥበቃውን ስፍራ ትተው ወደ ቤታቸው ሄደው በማደራቸው ከስራ እንዲሰናበቱ ተደርጓል።ከስራ ማሰናበት ብቻም ሳይሆን ህጋዊ እርምጃም ተወስዶባቸዋል።ከእነዚህ ከጠቀስኳቸው ክፍተቶች ውጭ በክልሉ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ውስጥ የታየ ችግር የለም።
አዲስ ዘመን፡- ምርጫው ሊካሄድ የቀረው የሳምንታት ያህል እድሜ ነው፤ በጸጥታው ረገድ ምን አይነት ዝግጅት እየተደረገ ነው? ምንስ ያህል የጸጥታ ኃይሎች ናቸው የሰላሙን ሁኔታ ለማስጠበቅ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ወደ ስምሪት የገቡት?
አቶ አለማየሁ፡- ከምርጫው ጋር ተያይዞ ባሉት በአራቱም መዋቅሮች የሐዋሳ ከተማንም ጨምሮ በሁሉም አደረጃጀት ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በተቀመጠው የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ መሰረት ሁሉም መዋቅር የራሱን እቅድ እያዘጋጀ ነው ያለው።የዝግጅታቸውን ሁኔታ በክልሉ ፕሬዚዳንት በሁለት ቀን አንዴ ይገመገማል።በሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ደግሞ በየቀኑ ግምግማ ይካሄድበታል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ወደ ስድስት ሺህ ገደማ የሚጠጉ መደበኛ ፖሊሶች ለዚህ ስራ የሚሰማሩ ይሆናሉ።ከልዩ ኃይሎች ደግሞ ወደ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ገደማ የሚደርሱ የሚሳተፉ ሲሆን፣ ከሚሊሻው ደግሞ ወደ አምስት ሺህ የሚደርስ በምርጫው ሂደት ተሳትፎ ያደርጋሉ ተብሎ ነው አቅጣጫ የተቀመጠው። ከእነዚህ ውጭ ሌሎች የጸጥታ አካላት በምርጫ 2013 ስጋት ናቸው ተብለው የሚታሰቡበት ቦታ ላይ ዝግጁ ሆነው ይጠብቃሉ።
አዲስ ዘመን፡- እነዚህ የጠቀሳችኋቸው መደበኛ ፖሊስ ፣ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ ምን አይነት የስነ ልቦና ዝግጅት አድርገው ነው ወደስራ የሚሰማሩት ? የተሰጣቸው የመመሪያ አቅጣጫስ ይኖር ይሆን ?
አቶ አለማየሁ፡- አጠቃላይ ለሁሉም መደበኛ ፖሊስ አካላት በገለልተኛነት በክልላችን በምርጫው እንሳተፋለን ያሉ ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ 13 ፓርቲዎች አሉ ።እነዚህ ፓርቲዎች መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እና ዴሞክራሲያዊ ምህዳርን ከማስፋት አኳያ እንደ አገር የተወሰደው አቋም ተግባራዊ እንዲሆን በገለልተኛነት እንዲያገለግሉ ማንም ይመረጥ ማን የጸጥታ፣ የሰላም እና የደህንነት ሁኔታን የማስጠበቁን ስራ ብቻ እንዲሰሩ ነው የሚደረገው።እየተደረገ ያለውም ይኸው ነው።
በክላስተር አቀራረብ በየወረዳው ይሁን በአንድ ማዕከልም የጋራ ግንዛቤ እንዲያገኙ ተደርጓል ።በዚህ አግባብ በአሁኑ ሰዓት ሚሊሻን የማደረጀት ስራ በስፋት በሁሉም አካባቢዎች በመሰራት ላይ ነው የሚገኘው።በዚህ የስራ ድርሻ ውስጥ ተመልምሎ የሚገባው የሚሊሻ ሁኔታ ደግሞ አጠቃላይ አገራዊ እና ክልላዊ ሁኔታ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ የተካሄደ ሲሆን፣ ከስድስተኛው ምርጫ የሚጠበቀውን ግብ ጨምሮ በማስረገጥ የግንዛቤ አድማሱ እንዲሰፋ ነው የተደረገው።በጥቅሉ የግንዛቤ መድረክ ላይ የተገኘ እንጂ ግንዛቤውን ያላገኘ የጸጥታ ኃይል በምርጫ ሂደቱ ላይ የሚሳተፍ አይሆንም ።
አዲስ ዘመን፡- በሲዳማ ክልል በእስካሁኑ የመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይም ሆነ በተፎካካሪ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል፤ እንዲያው ከዚህ በኋላ በምርጫው ሂደት በክልሉ ያጋጥማሉ ተብለው በዋናነት በስጋትነት የተለዩ ችግሮች ይኖሩ ይሆን?
አቶ አለማየሁ፡- እንደ እኛ ክልል የምርጫን ሁኔታን በተመለከተ ሁኔታውን የለየነው በሶስት አይነት ፈርጅ ነው።አንደኛውና ሰፊው ጉዳይ ነው ብለን የለየነው ነገር በአረንጓዴው ምድብ ውስጥ የሚካተተውን ሁነት ነው።እንዲህም ሲባል ምንም ችግር የማይታይባቸው ምድብ ናቸው ማለት ነው።
የተወሰነ ደግሞ በወሰን ይገባኛል የተወሰኑ ነገሮች ሊመጡ ይችላሉ ብለን የለየናቸው ጉዳዮች ያሉ ሲሆን፣ እነዚህም በዝርዝር ሲታዩ ሁለት በመቶ እንኳ በቅጡ የማይሞሉ ጉዳዮች ናቸው።በቀይ ምድብ ውስጥ ያየነው ነገር ደግሞ እስካሁን አለ ብለን ያስቀመጥነው ጉዳይ ባይኖርም በተለይ በኦሮሚያ ክልል በሚያዋስነው አካባቢ ከሟቹ ልጅ ከሸኔ አንጻር አንዳንድ ቦታ የምርጫ ጣቢያዎችንም ለማደናቀፍ የሚሞክሩ አካላት ይኖራሉ የሚል ስጋት ግን መኖሩ አልቀረም።…
አዲስ ዘመን፡- የትኛውን የሟች ልጅ ነው… ?
አቶ አለማየሁ፡- ሟቹ የምልሽ ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሓት)ን ሲሆን፣ የሟቹ ልጅ ያልኩሽ ደግሞ ሸኔን ነው፤ ሸኔ የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ(ህወሓት) ልጅ ሲሆን፣ ይኸው አባቱ የሞተ ነው።በመሆኑም ከእሱ ጋር ተያይዘው ሊከሰቱ የሚችሉ ጉዳዮች አሉ በሚል የለየናቸው ውስን አካባቢዎች አሉ።ለእነዚህም ደግሞ የራሱ የሆነ የመፍትሄ አቅጣጫ ያቀመጥን ሲሆን፣ ከዚህም አልፎ የሚከሰት ከሆነ ደግሞ መንግስት
የመቆጣጠር አቅሙን በተጠናከረ አካሄድ ያደራጀ መሆኑን ልገጽልሽ እችላለሁ።
እስካሁን ባለው ሁኔታ የለየናቸው ጉዳዮች ያሉት አረንጓዴ እና ቢጫ ውስጥ ናቸው እንጂ ቀይ ውስጥ የገባ ነገር የለም።ቀደም ሲል ሁለት በመቶ ብዬ የጠቀስኩልሽ በቢጫ ውስጥ የተያዘውን ጉዳይ ሲሆን፣ ይህም በቢጫ ውስጥ አካተን ያስቀመጥነው ጉዳይ ምናልባት ተላልፎ ወደ ቀዩ ሳጥን ውስጥ እንዳይገባ ነው ጠንክረን እየሰራን ያለነው ማለት ይቻላል።ችግሩ ተላልፎ ወደቀይነት የሚቀየር ከሆነ ለመግታት የሚያስችል የራሱ የሆነ ተመጣጣኝ ዝግጅት ተደርጓል።
አዲስ ዘመን፡- የሲዳማ ክልል በተለይም ስድስተኛውን አገር አቀፍ እና ክልላዊ ምርጫን አስመልክቶ ከጸጥታው ሁኔታ ጋር በተያያዘ ከአጎራባች ክልሎች ጋር የፈጠረው መስተጋብር ካለ ቢገልጹልን?
አቶ አለማየሁ፡- አጠቃላይ የሲዳማ ክልል ስድስተኛውን አገራዊ እና ክልላዊ ምርጫ ሰላማዊ ከማድረግ አኳያ ከምንዋሰንባቸው ከሁለቱ ክልሎች ማለትም ከኦሮሚያ ክልል እና ከደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ፍጹም በሚያስብል ደረጃ ቅንጅታዊ አሰራራችንን በጣም እያጠናከርን ነው ያለው።ሚያዚያ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ከኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጋር የምክክር መድረክ በሐዋሳ ከተማ አዘጋጅተን ተወያይተናል።በተለይ ከምዕራብ አርሲ፣ ከምስራቅ ጉጂ፣ ከምዕራብ ጉጂ እና ከቢሻን ጉራቻ ከተማ አስተዳደር ጋር የኦሮሚያ ክልል ሰላምና ጸጥታ አመራሮች ባሉበት እንዲሁም የሶስቱ ዞን አስተዳዳሪዎች ባሉበት ሲዳማ ክልል ከኦሮሚያ ክልል ጋር አዋሳኝ የሆኑበት 21 ወረዳዎች ጋር ይህን የ2013ን ምርጫ ሰላማዊ ለማድረግ ከፍተኛ ምክክር በማድረግ ላይ እንገኛለን።
ከሚያዚያ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ምርጫው እስኪጠናቀቅ ድረስ ያለውን እንቅስቃሴ እና ምርጫውን የሚያስፈጽሙ አካላት ተለይተው ታውቀዋል።ይህም የሆነው በአራት ክላስተር ነው።አንደኛው ክላስተር የበንሳ ክላስተር በመባል የሚታወቅ ነው።ሁለተኛው ደግሞ የቦሬ ክላስተር ነው።ሌላው ሶስተኛው ደግሞ የአርሲ ክላስተር ሲሆን ፣ የመጨረሻውና አራተኛው ክላስተር የሐዋሳ ማዕከል ክላስተር በመባል የሚታወቀው ነው።
ለዚህ ነገር በጥብቅ ዲሲፒሊን ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልል የጸጥታ ተቋማት ሲሆኑ፣ በዚህ ሂደት ውስጥ በየክላስተሩ ያሉ ናቸው።የሀገር መከላከያ ሰራዊት ፣ ብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት ፣ ብሄራዊ የኢንፎርሜሽንና መረብ ደህንነት ፣ የፌዴራል ፖሊስ ፣ የሁለቱ መንግስታት ማለትም የሲዳማ ክልል እና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይሎች ፣ የብርጌድ አዛዦች አባል የሆኑበት እንዲሁም የሁለቱ ክልሎች የፖሊስ ኮሚሽነሮች ባሉበት በክላስተር ደረጃ አስፈላጊው ሰው ሁሉ ተመድቦ በመስራት ላይ ይገኛል።
በተመሳሳይ ኩታ ገጠም የሆኑ የወረዳ አመራሮች ደግሞ ህዝቡ ለሰላሙ በጋራ እንዲቆም እና አፍራሽ ተልዕኮ ያነገቡ ኃይሎችን ለጸጥታ ኃይሉ በማጋለጥ እንዲሰጥ ከማድረግ አኳያ የህዝብ ለህዝብ ውይይት ሳይቋረጥ እስከ ድምጽ መስጫ እለት ድረስ በተከታታይ የሚደረግ ነው የሚሆነው።ይህ ህዝብ ለህዝብ ውይይት አሁንም እየተደረገ ሲሆን፣ ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም ለምሳሌ ቦረና ላይ ተካሂዷል።በተመሳሳይ በንሳ እና ሻሸመኔ ላይም እንዲሁ የህዝብ ለህዝብ ውይይቱ ተካሂዷል፡፤ በተመሳሳይ ሲራሮንም ጨምሮ ሐዋሳ ማዕከልም እንዲሁ ሐሙስ እለት የተደረገ ሲሆን፣ በየክላስተሩ ይህንን ስራ ካላቸው መደበኛ ስራ ተነጥለው ይህንኑ ስራ ብቻ የሚሰሩ አካላት አሉ።እነዚህም ከሁለቱ ክልሎች ፖሊስ መዋቅር እንዲሁም ከጸጥታ መዋቅር በተጨማሪም ከፌዴራል ተቋማትም የተመደቡ ከፍተኛ አመራሮች አሉ።
በዚህ ጉዳይ እስከምርጫ ማጠናቀቂያ ድረስ መጽዳት ያለበት ጉዳይ ካለ እያጸዳን እና የአካባቢውን ሰላም እያረጋገጥን ነው የምሄደው ብለን በማቀድ እየተንቀሳቀስን ነው።ህዝቡ ደግሞ የሰላም ትርጉሙ ቀላል እንዳልሆነ በደንብ ተረድቶት መከፈል ያለበት ዋጋም ካለ ለሰላም ሲል ከፍሎ አንድነቱን እና የቀደመውን መተሳሰብ እንዲሁም መከባበር ይዞ እንዲሄድ ነው የእኛ ፍላጎት።ይህን መልካም የሆነውን የአብሮነት እና የመከባበር እሴቱን እንደዋዛ እንዳይጥል የሚመለከተው አካል በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ የተቀመጠ አቅጣጫ አለ።በመሆኑም ስራችንን ዋና ትኩረታችን በሆነው በሰላምና በጸጥታ ጉዳይ ላይ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ በመስራት ላይ እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡- በምርጫ ወቅት ጊዜውን ጠብቀው የሚነሱ ረብሻዎች እና አንዳንድ ወጣ ያሉ ድርጊቶች እንደሚኖሩ ይገመታልና በዚያን ጊዜ ኢ – ሰብዓዊ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ ምን ያህል እየተሰራበት ነው?
አቶ አለማየሁ፡- በአጠቃላይ በምርጫ ወቅት ላይ እንደዚህ አይነት በተለይ ኢ – ሰብዓዊ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ በየምርጫ ጣቢያዎች የየክላስተር መዋቅሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ጊዜያዊ ችሎቶች ደግሞ ይደራጃሉ።ለዚህም እንቅስቃሴ ጉዳዩ ከሚመለከተው ከጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ጋር እንዲሁም ከክልሉ ፍርድ ቤት ጋር እንዲሁም ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ ዘርፍ ጋር የተደራጀ ኮሚቴ በማዋቀር የት ቦታ የትኛውን አካባቢ ማዕከል ያደረገ ጊዜያዊ ችሎት ያስፈልጋል የሚለውን ጉዳይ በዝርዝር ለይተን ጨርሰናል።ለምርጫ ሁለት ሶስት ቀን ሲቀረው ደግሞ በዝርዝር ለይተን ያሰናዳነው እቅድ ወደ መሬት ወርዶ ተግባራዊ ይሆናል ማለት ነው።ስለዚህም ወንጀል ፈጽሞ የተገኘ አካል ካለ ወደርቀት ቦታ ሳይኬድ እዛው በተደራጀው ጊዜያዊ ችሎት በህግ አግባብ ተጠያቂ ሆኖ ጉዳዩ ይጣራል።በዚህም አይነት አካሄድ ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን እና ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚሰራ ይሆናል። በዚህ አግባብ የዜጎች መብት በማይረገጥ መልኩ ህግንና ስርዓትን ብቻ ተከትለን ለመስራት የራሳችንን ዝግጅት አስቀድሜ እንደነገርኩሽ እያጠናቀቅን ነው።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት እንደ አገር በተለይ ምርጫው ሲቃረብ የተለያየ አይነት ብጥብጥና ሁከት ለመፍጠር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እየተስተዋሉ ነው፤ ከዚህ አንጻር የሲዳማ ክልል ምርጫው ሰላማዊ ይሆን ዘንድ ህዝብን ከማስተባበር አኳያ ምን እየተሰራ ነው? የጸጥታው ዘርፉስ ህብረተሰቡን ከማንቃት አንጻር ምን ይጠበቅበታል?
አቶ አለማየሁ፡- የጸጥታ ዘርፉ በህግ የተሰጠውን ስልጣን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርበታል።ለዚህ ስራው ደግሞ በስነ ልቦናውም ሆነ በብቃት ደረጃ ዝግጁ እንዲሆን የክልሉ መንግስት ከመቼውም ጊዜ በላይ አጥብቆ እየሰራበት ይገኛል።
ህብረተሰባችን ደግሞ የጸጥታ መዋቅሩ የሚከፍለው መስዋዕትነት ለዜጎቹ ደህነት ሲል እንደሆነ በማስተዋል እና በመረዳት ለሰላሙ ዘብ መቆም እና ለጸጥታ አካሉ የጀርባ አጥንት ሆኖ ማገልግል እና የበኩሉን መወጣት ይኖርበታል።በሚያፈልገው ሁሉ ድጋፉን ሊሰጠው ይገባል።
ከዚህ ውጭ በሁከት አሊያ በብጥብጥ አገርን ለማተራመስ የሚንቀሳቀስ ኃይል ካለ አስፈላጊው እርምጃ የሚወሰድበት ይሆናል።ለዚህ ደግሞ በበቂ ሁኔታ ዝግጅት የተደረገ ሲሆን ፣ ለጸጥታ ኃይሉ ቅድመ ግንዛቤ የተሰጠው ስለመሆኑ መግለጽ እወዳለሁ።ለዚህ እንቅስቃሴ ተፈጻሚነት ደግሞ የ24 ሰዓት የመረጃ መረብ እና ስርዓቱ በዚህ አግባብ የተዘረጋ ነው።
ህዝባችን ይህንን አውቆ ከጸጥታው አካል ጎን በመቆም አጠቃላይ ሂደቱ እና እንቅስቃሴው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩሉን ትልቅ ኃላፊነት እንዲወጣ እሻለሁ።በዚህም የምንመኛት የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ለምናደርገው ግስጋሴ ህዝባችን ሰላሙን በማስጠበቅ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ መብቱንም በመጠቀም ይበጀኛል፤ ይጠቅመኛል የሚለውን የፈለገውን አካል መምረጥ መቻሉን ማረጋገጥ አለበት።ከፍላጎቱ ውጭ በኃይል ሊጫንበት የሚመጣውን የትኛውንም የብጥብጥና የሁከት ተግባርም በማውገዝ በጥባጩንና ሁከት ፈጣሪውን ኃይል በማጋለጥ እና አሳልፎም በመስጠት የየራሱን አካባቢ ሰላማዊ ማድረግ ይኖርበታል።ማንኛውም ከህዝቡ አቅም በላይ የሆነውን በጥባጭ ኃይል ደግሞ አሳልፎ ለጸጥታ ኃይሉ እንዲሰጥም ጥሪዬን ለማስተላለፍ እወዳለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ሲዳማ ክልል አገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫን ከዚህ ቀደም ክልል ሆኖ አስተናግዶ እንደማያውቅ ይታወቃል፤ ከዚህ አንጻር አሁን እየተካሄደ ያለው የምርጫ እንቅስቃሴ አዲስ ይሆንብኛል ብሎ የሚያሳስበው ነገር ይኖር ይሆን? ወይስ ያካበተው ልምድ ይኖራል?
አቶ አለማየሁ፡- ያነሳሽው ጥያቄ ጥሩ ነው፤ የዚህ የአገር አቀፍ እና የክልል ምርጫን በታሪክ አጋጣሚ ክልል ሆነን ስናስፈጽም የመጀመሪያችን ነው።ይሁን እንጂ ከልምድ አንጻር እና ካለን የቅርብ ጊዜ እውቀት የተነሳ ከሌሎች ክልሎች የተሻለ ተሞክሮው አለን ብዬ መናገር እችላለሁ።
ምክንያቱም ሲዳማ የክልልነት ጥያቄው ሰሚ አግኝቶና ተገቢው ምላሽ ተሰጥቶት ጉዳዩን ለማስፈጸም ባካሄደው የህዝበ ውሳኔ ድምጽ ያካበተው የራሱ የሆነ ልምድ አለው።ራሳችንን በራሳችን ለማስዳደር ባደረግነው የሪፈረንደም ምርጫ በምርጫ ክልሎች እና በምርጫ ጣቢያዎች ያደረግን መሆናችን የሚታወቅ ነው፤ የህዝበ ውሳኔውን ምርጫ ካስፈጸምን ገና ሁለት ዓመት እንኳ በቅጡ አልሞላም።ወደ ሌሎች ክልሎች ስትሄጂ ግን እንዲህ አይነቱን ምርጫ አካሂደው የነበረው ከአምስት ዓመት በፊት ነው።ከዚህ አንጻር የሲዳማ ክልል ከሌሎች ክልሎች በተሻለ ሙሉ ልምድ እና ተሞክሮ አለን ብዬ መናገር እችላለሁ።በመሆኑም የተሻለ ነገር ለመፈጸም የሚያስችል ቁመና ላይ ነን የሚል አቋም አለኝ።የህዝበ ውሳኔውን ስናስፈጽም በነበረበት ጊዜ አጥቃላይ የጸጥታ ሁኔታንም እሱን ተከትሎም የሚፈጠሩ ጉዳዮችን ፈጠን ብሎ ከማየት አኳያ እየሰራን ካለንበት ተግባር አላረፍንምና የሚቸግረን ነገር የለም ማለት እችላለሁ።ስለዚህ ይህን ምርጫ በተሻለ አካሄድ እናስፈጽማለን የሚል ሙሉ እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ስድስተኛውን አገር አቀፍ እና ክልላዊ ምርጫን አስመልክተው ለክልሉ ነዋሪ እና ለጸጥታው ዘርፍ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?
አቶ አለማየሁ፡- የክልላችን ነዋሪዎች ሁሉ ከዚህ ቀደም በተደረገው ህዝበ ውሳኔ ላይ ያሳዩት የጨዋነት አካሄድ መሆኑ የሚታወስ ነው።በዚህም መሰረት ይህንንም ስድስተኛውን አገር አቀፍ እና ክልላዊ ምርጫ የአገር ገጽታንም ሊቀይር የሚችል ምርጫ እንደመሆኑ መጠን እንዲሁም የሁሉንም የዓለም አቀፉን ህብረተሰብ ቀልብ እና ትኩረት የሳበ ምርጫ በመሆኑ ሁሉም በክላልችን የሚኖር ህዝብ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል።
የጸጥታ አካሉ ደግሞ ከወትሮው በበለጠ ሁኔታ የሰላም ኃይሉን እንቅስቃሴ ተግቶ በመከታተል ችግርም ሲኖር ደግሞ አስፈላጊውን እርምጃ እየወሰደ ህዝባችንን ከጸጥታ ስጋት ነጻ እያደረገ የተለመደውን የሰላም ማስከበሩን ተልዕኮ በአግባቡ መወጣት ይኖርበታል።ይህንንም በታማኝነት እንዲወያይ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ አለማየሁ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 6 ቀን 2013 ዓ.ም