በዕለተ ትንሳኤ ዋዜማ ከአንድ የሚዲያ ተቋም ጋር ቆይታ አድርጌ ነበር። በውይይታችን ጣልቃ ጋባዤ ጋዜጠኛ “የኢትዮጵያ ወቅታዊ መልክ ምን ይመስላል?” በማለት ያልተዘጋጀሁበትን ጥያቄ በመወርወር ፈተና ውስጥ ዘፈቀኝ። የአገሬ ቀደምትና ወቅታዊ መልክ ምን ይመስል እንደነበርና የአሁኑ ላህይዋም (ደም ግባቷ) ምን ገጽታ እንዳለው ማሰብና ማሰላሰል የጀመርኩት ከዚያ እረፍት ከሚነሳው የጋዜጠኛው ጥያቄ ወዲህ ነው።እርግጥ ነው የአንድ ሀገር ውበት የሚለካው በተፈጥሮ ሃብቷ ብልፅግናና ድህነት፣ በመልክዓ ምድሯ ልምላሜና መቀንጨር ወይንም በዜጎቿ ቋንቋ፣ ባህል፣ ፖለቲካ፣ ማሕበራዊ መስተጋብርና የሕዝቦቿ የቆዳ ቀለማት ኅብር መገለጫነት ብቻም አይደለም።
አንዱን ሰበዝ ብቻ መዘን ለጊዜው በአጽንኦት እንቃኘው። የዓለማችን ዜጎች የቆዳ ቀለም ከአህጉር አህጉር፣ ከሀገር ሀገር፣ አልፎም ተርፎ በአንድ የድንበር አጥር ውስጥ በተከለሉ ሀገራትም ውስጥ ቢሆን ከክፍለ አገር ክፍለ አገር ሳይቀር የሰዎች መልክ ዥንጉርጉር ነው። ለዚህም ነው ምድራችንን ያቆነጃትን የሕዝቦች መልክ ልክ እንደ ሰንደቅ ዓለማ ቀለማት ነጭ፣ ቢጫ፣ ጥቁር፣ ጠይም እያልን የምንመድባቸው። እነዚህ የውበት ፈርጦች ለምንኖርባት እናት ምድር እንደ ፀዳል ያደመቋት ፀጋዎቿ ናቸው እንጂ የየሀገራቱን መልክ በምልዓት የሚወክሉ መገለጫዎች ብቻ ተደርገው ሊታሰቡ አይገባም።
ከእያንዳንዱ ሕዝብ የቆዳ ቀለም ባሻገር ማንኛውም ሀገር የራሱ የሆኑ ሃይማኖቶች፣ ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ የፖለቲካና የማኅበራዊ ተራክቦ ሥርዓቶች አሉት። የሩቅ ባዕድን እንደ ፍዘት የሚያዩአቸው እነዚህን መሰል እሴቶች ለባለጉዳዩና ለባለቤቱ ፍካትና በረከቶች እንጂ የሚነቀፉ አይደሉም። እንዲያም ቢሆን ግን እነዚህ ሁሉ መገለጫዎች የአንድን ሀገር የውስጥና የውጭ መልክ ሙሉ በሙሉ ፍንትው አድርገው ያሳያሉ ማለት አይቻልም።
በራስ የንጽረተ ዓለም (ፍልስፍና) መነጽር በዓለማችን ሰሜን ንፍቀ ክበብ ላይ ተቀምጦ ደቡባዊውን የዓለማችን ክፍል መተቸት ወይንም በምሥራቃዊው የፀሐይ መውጫ ክፍል የሚኖረው ሕዝብ “ኑሮዬና ገመናዬ” ብሎ “በአንቱታ” በሚያከብረው የሕይወት መርህ ላይ የምዕራቡም ሆነ የሰሜኑ የሰው ዝርያ ጣቱን እየጠቆመ “እኔን አልመሰልክም” እያለ በነቀፋ ቢተችና ድፍረት በተሞላበት ስሜት ቢያንቋሽሽ ችግሩ የተነቃፊው ሳይሆን የነቃፊውን “የአምልኮተ ራስ በሽተኛነት” ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። እርግጥ ነው ከላይ የተዘረዘሩት ጉዳዮች በሙሉ የየሀገራቱ መልኮች ቢሆኑም በመልዓት ፍረጃ ግን ምልዑ መገለጫዎች ናቸው ብሎ ከድምዳሜ ላይ ለመድረስ ያስቸግራል።
“ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዝንጉርጉርነቱን” መለወጥ እንደማይችል የታመነ መሆኑን የምንቀበለውን ያህል የሰሜናዊ ንፍቀ ክበቦቹ ቤትኞች ቤልጅዬም፣ ካናዳና ቻይናን የመሳሰሉት ሀገራትም እንዲሁ በዐውዳቸው አንጻር “የራሳችን” በሚሏቸው “የነብር ዝንጉርጉርነት” ማንነታቸውን ቢያስተዋውቁ ሊያጣላ አይገባም። ኦርዬንታሎቹም (ምሥራቃውያን) ሆኑ ፕራይም ሜሪዲያን የተባለው የሐሳብ መስመር ወደ ምዕራብ የከፈላቸው አለያም የምድር ወገብ ድንበር ሆኖ ወደ ደቡብ የከለላቸው አብዛኞቹ የደቡብ አሜሪካና የአፍሪካ አገራትም እንዲሁ መልካቸውን እናሻሽል፣ ባህል ቋንቋቸውን በራሳችን የአመለካከት ዐይን ውሃ እናቅልምና እኛን እናስመስላቸው ማለትም ያዳግታል። እንዲህም ቢሆን እንኳን የየሀገራቱ መልክ ተሰርቶ አልቆለታል ለማለቱ ድፍረት አይኖርም።
እነዚህ ተፈጥሯዊና የዘመናት ታሪኮች ድምር ውጤቶችና አንኳር እውነታዎች እንደተጠበቁ ሆነው ከየሀገራቱ የማንነት መገለጫዎች ጎን ለጎን የአንድ ሀገር እውነተኛ መልክ የሚባለው የራሳቸው የየዘመናቱ ትውልዶች መልክ ነው። በራሳቸው ዜጎች በጎም ሆነ መልካም የተግባር ውጤት፣ በጉልበተኛ ሀገራት “ጠብ ያለሽ” በዳቦ ሴራ፣ ድርጊቶችና ወረራዎች፣ ወይንም በተፈጥሮ ንፍገትና ቸርነት የየሀገራቱ መልኮች በየጊዜው ሊለዋወጡና ሊቀያየሩ ይችላሉ።
በሰላማዊ ሕይወት ለሺህ ዘመናት በአንቱታ ተከባብሮ የኖረ አንድ አገር በአጭር ጊዜ ውስጥ ሥልጣኔው ተንኮታኩቶ፣ ክብሩ ተዋርዶ፣ አቅሙ ተልፈስፍሶ መዘባበቻ በመሆን መልኩና ገጽታው ሊጠፋ ይችላል። ነበር ታሪኩም በነባር እውነታዎች ወይቦና ገርጥቶ በጥቋቁር ዜና መዋዕል መዛግብት ውስጥ ሊመዘገብ ይችል ይሆናል። የሶርያ ሥልጣኔ ምን ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር? ዛሬስ? ኢራቅ፣ ሊቢያና የመን ወዘተን. እየጠቀስን ለምን ወደ ፍርስራሽ ክምርነት እንደተለወጡ ብንፈትሽ የምናገኘው መልስ ሁላችንንም የሚያግባባ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።
ከሦስትና ሁለት ዐሠርት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ መልክና ገጽታ በምን ዓይነት አሳፋሪ ክስተቶች የተሞላ እንደነበር የቅርብ ጊዜ “መሸማቀቂያ ትዝታችን” ነው። በተለያዩ ተጽእኖ ፈጣሪ የዓለም የሚዲያ አውታሮች ሲሰራጭ የነበረው “ውብ” የሚሰኝ የሀገራችን መልክና ገጽታ ሳይሆን ጉስቁልናዋ፣ ድህነቷና ርሃብተኝነቷ እንደ ነበር ቢያሸማቅቀንም ደግመን ማስታወሱ ክፋት አይኖረውም። “የፊተኛውን ወዳጅህን በምን ቀበርክ በሻሽ፤ የኋለኛው እንዳይሸሽ” እንዲሉ የተከደነ የሚመስለውንና “ነቀዝና አረማሞ” ወርሮት የነበረውን የታሪካችን ጎታ ደግሞ መፈተሹ ለጸሎትም ይባል ለእውቀት ብቻ ዛሬ ለደረስንበት አሳዛኝ ሁኔታ በትምህርት ሰጭነቱ ሊረዳን ስለሚችል ባይዘነጋ ይመረጣል።
ያለፈውን መተረኩ ባይከፋም የዛሬውስ የሀገራችን መልክ ምን ይመስላል? ብሎ መጠየቁ እጅጉን ብልህነት ነው። የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ አስኳልም ይሄው ነው። ጥያቄው የመቅለሉን ያህል መልሱም እንዲሁ ቀላል ይመስላል። የኢትዮጵያ ሀገራችንን የዛሬ መልክ ለማመላከት ወዲያና ወዲህ ታሪክና ነበርን እያጣቀስን ብዙ ማለቱ ፋይዳ ስለማይኖረው በአጭሩ የዛሬው የሀገራችን መልክ የሚወከለው በሕዝባችን የመልክ ዥንጉርጉርነት፣ በባህሎቻችን ውበት፣ በቱሪዝም ፀጋችን ወይንም “እንግዳ ተቀባዮች እያልን” ራሳችንን በምንደልልባቸው የትናንትናና ከትናንት ወዲያ እውነቶቻችን ሳይሆን በእኛ በዛሬዎቹ ትውልዶች መልክ ነው። እንዴታውን ጥቂት ላብራራ።
በአድዋና በፋሽስት ኢጣሊያ ጦርነቶች ላይ ከተጎናጸፍናቸው ዘርፈ ብዙ ድሎች ማግሥት የነበሩት ትውልዶች ስሜት በድል አድራጊነት የወዛ፣ በጀግንነት ወኔ የተሞላ፣ በአሸናፊነትና በአትንኩኝ ባይነት እምነት የደደረ ነበር። “አንድነት ኃይል ነው!” የዘመኑ መሪ መፈክር ነበር። አስፈላጊ ከሆነ የዚህን መሰሉን የአገራችን በድል የደመቀ መልክና ውበት ፈትሾ ለማረጋገጥ በጽሑፍ የሰፈሩ ታሪኮቻችንንና በኅብረ ቀለማት የተከሸኑትን የወቅቱን የሥዕል ጥበባት ትዕምርቶች መፈተሽ ይቻላል።
አገሬ አሏት ከምንላቸው ተፈጥሯዊና ባህላዊ ገጽታዎቿ ይልቅ ባለፉት ዘመናት በስፋት ሲተዋወቁ የከረሙት በአድዋ፣ በፋሽስት ኢጣሊያ ወይንም በዚያድ ባሬ የሱማሊያ ወረራዎች ላይ የተጎናጽፍናቸው ወታደራዊ ድሎች ወይንም እንደ ሀገራዊ ስኬት ስንቆጥራቸውና ስናስቆጥራቸው የኖርነው እዚህም እዚያም የምንጠቃቅሳቸው የልማትም ይሁኑ ማኅበራዊ እሴቶች አይደሉም።
በአጭሩ በቀዳሚዎቹ ትውልዶችም ሆነ ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያ የተወከለችበት የየዘመኑና የዛሬው መልኳ በአብዛኛው “አፍ ሞልተን፣ እውነትን ተማምነን” እዩልን ስሙልን ስንል የኖርነውና ዛሬም ለዓለም ማኅበረሰብ እያስተዋወቅን ያለነው “ጎሽ!” አሰኝቶ ለአድናቆት ጭብጨባ የሚበቃ ገድል አይደልም። በዚሁ በምድራችን የተፈጸሙ ግፎች፣ ጭቆናዎች፣ አሰቃቂ ድርጊቶች ወዘተ. በቁጥር ብዛት ብቻም ሳይሆን በዓይነትና በአደራረግ ጭምር ያሳፍራሉ፤ መልካም የምንላቸውንም ጥቂቶች ይጋርዳሉ።
ታሪካችን የደመቀው በእነዚህ ሳንካዎች ነው። የሀገሬን ፊት ማድያት እንዲለብስ ምክንያት የሆኑት በሽታዎቿም እነዚሁ ናቸው። ከዚህን መሰል አሳር ሳንላቀቅና በነባርና በትኩስ ታሪካዊ ህፀፆች እርስ በእርስ ሰንጎሸማመጥና እርስ በእርስ ስንፋለም ተፈጥሮም እየተቀየመችን ቀጥታናለች። የድርቅና የርሃብ ተደጋጋሚ ቅጣቶቹ እንደምን ክብራችንን ዝቅ አድርገው አርዝመን ለእርዳታ የዘረጋነውን እጆች እስከ ዛሬ መሰብሰብ እንዳላስቻለን ከራሳችን ከባለጉዳዮቹ የተሻለ ምስክር መጥራት ያዳግታል።
የኢትዮጵያን መልክ “የሚስሉት እጆቻችን”፤
ዛሬስ የኢትዮጵያ መልክ ምን ይመስላል? መልኳን እየሳሉ ያሉት እጆችስ የማን ናቸው? የጥያቄው መልስ አጭርና ግልጽ ነው። የዛሬዋ የሀገራችን መልክ በእኛው የተግባር ውክልና የሚገለጽ የእኛው የራስ ምስል (Portrait) ነው። ሀገሪቱን የምንስልባቸው ፈዛዛና ጠቋቁር ቀለማት የተቀመሙት ደግሞ ከማንነታችን ትምክህት፣ ከአፍራሽና አውዳሚ ጭካኔያችን፣ ከመግደልና ከማፈናቀል ድርጊቶቻችን፣ ካለመደማመጥ ግትርነታችን እያዋሃድን ነው። የመሣሪያውን ብሩሽ የጨበጡት እጆቻችንም ደፋሮች ናቸው።
በዚህ ጸሐፊ እምነት ኢትዮጵያ ባለፈችባቸው ዘመናት ሁሉ እንዲህ እንደ ዛሬው የገጽታዋ መልክ ወይቦ፣ የፊቷ ማዲያት አጥቁሯት፣ የውስጥና የውጭ ስብዕናዋ በግፈኞች እጆች ቆሽሾ መልኳ የገረጣበት ዘመን ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም፤ ንባቤም አላገዘኝም። ሰቅዘው የያዟት “የሠዓሊያኑ ልጆቿ እጆች” የበረቱና በቀላሉ ልትላቀቃቸው የተቸገረችባቸውም ይመስላል።
የልማት ጅምሮቻችንም ቢሆኑ “ግማሽ ልጩ ግማሽ ጎፈሬ” ይሉት ብጤ ሆነውብን እዚያ ማዶ የስኬት ሪበን ሲቆረጥ እዚህ ማዶ የጥፋትና አውዳሚ እጆች ይበረታሉ። የፖለቲካው አካሄድም “ከድጡ ወደ ማጡ” እንዲሉ ብስልና ጥሬውን መለየት ተስኖን “ታጥቦ ጭቃ” አባዜ ተጠናውቶናል። ለመንፈስ ሰላምና የነፍስ እረፍት ይሰጡናል ብለን በፈጣሪ ፈቃድና በራሳችን ምርጫ የተጠለልንባቸው የሃይማኖት ተቋማትም ቢሆኑ ነውጥና ውጥረት ቀስፎ ስለያዛቸው እንኳን ለምእመኖቻቸው መድኃኒት ሊፈልጉ ቀርቶ እነርሱ ራሳቸው “ባለመድኃኒት ሆይ ወዴት ነህ!?” እያሉ ተራዳዒ ፍለጋ ላይ ናቸው። ከደጀ ሰላማቸው የሚደመጠው ድምፅ የዕልልታ ዝማሬና አፅናኝ መንዙማ ሳይሆን በኤሎሄ የሰለለ የጣር ጩኸት ነው። ይሄንንም እየሣሉ ያሉት የምናብ እጆች የእኛው የራሳችን መዳፎች ናቸው።
የተገኘንበት ብሔረሰብ፣ አፍ የፈታንበት ቋንቋ፣ የታነጽንበት ባህልና ወግ እንዲያው በጥቅሉ ማንነታችን የተሸመነባቸው ጌጦቻችን ከመሆን ይልቅ የእሳት ማቀጣጠያ ክብሪቶች ወይንም የወላፈን ማጋጋያ ነዳጆች እየሆኑ እያነባንም ቢሆን የሀዘን ፍራሾቻችን ላይ ተሟሙቀን እንድንቀመጥ አስገድደውናል።
እኛው ምክንያትና ሰበብ የሆንባቸው አሳሮቻችንና የውስጥ ፍልሚያዎቻችን ለታሪካዊ ጠላቶቻችንና “ለጆሮ ጠገብ” የሩቅ ተመልካቾች ከሰማይ እንደወረደ “የመና ፀጋ” እየሆነላቸው ችግሮቻችንን ሲያባብሱ፣ በሀገራችን መልክ ላይ አሲድ ለመድፋት ሲሞክሩ፣ የወገቧ ጅማት እንዲፈታ፣ ጉልበቶቿም ዝለው እንዲብረከረኩ በተቻላቸው ዘዴና ብልሃት እየተረባረቡ መሆናቸውን እያስተዋልንም እየሰማንም ነው። የውስጥ ጥዝጣዜያችንን ማን አመረቀዘው? እኛው ራሳችን። የኢትዮጵያችን መልክ በማድያት እንዲዥጎረጎር ማን ምክንያት ሆነ? የእኛው የራሳችን እጆች። ሀገራችን በጠላቶቻችን ዒላማ ውስጥ እንድትገባ ማነው የአብሪ ጥይቱን እየተኮሰ ያለው? እኛው ራሳችን።
ይሄም ቢሆን ግን!
የእናት ዓለም ጊዜያዊ መልክ በተለያዩ የውስጥና የውጭ በሽታዎች ቢጎሳቆልና መፍትሔ አልባ ቢመስልም ኢትዮጵያ ወድቃ የምትሰበር ሸክላ አይደለችም፤ ሆናም አታውቅ። በተኩላዎች ጩኸት በርግጋ የምትባዝን የ“የዋህ በግ ምሳሌም” አይደለችም። ያሰፈሰፉ ባእዳን አውሬ ጠላቶቿና የቤት ውላጅ ተናካሽ ልጆቿም አስደንብረው ገደል የሚሰዷት አቅመ ቢስ ምስኪን አይደለችም። ይዋል ይደር እንጂ ዘመናት ባስተማሯት ማስተዋልና ጥበብ፣ ክፉዎች ራሳቸው ባጀገኗት ብርታት ዕንቆቅልሾቿን ሁሉ የምትፈታበት ቀን ሩቅ አይሆንም። ሕልሟንም በተግባር ትተረጉማለች። ቋጠሮዎቿን በጣጥሳም ራሷን ነፃ ታወጣለች። የፈጣሪም እገዛ አይለያትም።
ተፈጥሮ፣ ታሪክና ዕድሜ ላላስተማራቸው የእንግዴ ልጆቿ ይብላኝላቸው። ይብላኝ አንጸባራቂ የሆኑት ቀደምት ታሪካዊ አሻራዋ የማይደገምና የደበዘዘ ለመሰላቸው የውጭ ጠላቶቿ። አልገባቸውም እንጂ ኢትዮጵያ ምሥጢር ነች። ኢትዮጵያ ረቂቅ ጥበብ ነች። ሊገፈትሯት ቢሞክሩም አትወድቅም። ጠላቶቿ መርዝ ቀብተው የሚያስፈነጥሩት ቀስት ወደ ራሳቸው ታጥፎ ያቆስላቸው ካልሆነ በስተቀር በኢትዮጵያ ገላ ላይ አርፎ አይመርዛትም። የጥቂት እኩይ ማቲዎቿ የውስጥና የውጭ ሴራ በብዙኃን ልጆቿ ይመከታል፤ ይመክናልም። የኢትዮጵያ መልክ በአጭር ጊዜና በእኛው እድሜ ተውቦ እንደገና ይፈካል። የእርስ በእርስ መጎሻሸማችን ተረት ሆኖ መወራቱ አይቀርም። ከመከራችን ተምረንና በድርጊታችን ተጸጽተን በመመለስ በጥብጠን የያዝናቸውን የግፍ ቀለማት የምንደፋ ከሆነና ያበላሸነውን የሀገራችንን መልክ ለማደስ ንስሐ የምንገባ ከሆነ የፈውሳችን ጊዜ ሩቅ አይሆንም። ፈጣሪ ይርዳን! ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2013