በእስልምና ውስጥ በከፍተኛ ድምቀት የሚከበሩ ሁለት ኢዶች (በዓሎች) አሉ። የመጀመሪያው የረመዳን ፆምን ማብቃት የሚያበስረው ኢድ – አልፈጥር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከሁለት ወራት በኋላ የሐጂ ስነ – ስርዓትን ተከትሎ የሚመጣው ኢድ – አልአድሓ(አረፋ) በዓል ነው። ዛሬም 1442ኛውን የኢድ አልፈጥር በዓል መሰረት በማድረግ የኢድ በዓል ከትርጓሜውና አስተምሮው ጋር በተያያዘ እንዲሁም የአገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ ጨምረን በዓሉ እንዴት መከበር እንዳለበት እና አጠቃላይ ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎቹ ዙሪያ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች የኡለማ ምክር ቤት አባልና በምክር ቤቱ የሰላምና እርቅ ዘርፍ ኃላፊ ሼህ መሀመድ ሲራጅ ጋር ያደረግነውን ቆይታ አቀረብንላችሁ። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- የኢድ አልፈጥር በዓል ምን አይነት ትርጉም አለው፤ እንዴትስ ይከበራል?
ሼህ መሐመድ፡- ኢድ ማለት ተደጋጋሚ ሆኖ የሚከበር የደስታ በዓል ማለት ነው። ኢድ አልፈጥር ሲሆን ደግሞ የፆም ማጠናቀቂያ ክብረ በዓል እንደማለት ነው። በዓሉ በብዙ አገሮች በተለያዩ መንገዶች የሚከበር ሲሆን፤ የጋራ የሆነ ነገርን በብዛት ያስተናግዳል። በበዓሉ ቀን ሁሉም አማኞች በጧት ተነስተው ልዩ የሶላት ስግደት ወደሚደረግበት ቦታ ይተማሉ። ስግደቱንም በመስጂድ ውስጥ ወይም ሁሉንም አማኝ ሊያሰባስብ በሚችል አንድ ገላጣ ቦታ ላይ የሚያደርጉ ሲሆን፤ በአዲስ አበባም ሕዝበ ሙስሊሙ በደማቅ ሁኔታ ወጥቶ ያከብረዋል።
የእምነቱ ተከታዮች በቡድን እየሆኑ የበዓሉን የውዳሴ ዜማዎች/ነሺዳ/ በማድረግም ወደ ስግደቱ ቦታ ይተማሉ። ከስግደት መልስ ደግሞ የበዓል ድግስ አድርገው ከቤተሰብ፣ ከዘመድ አዝማድ እንዲሁም ከጐረቤት ጋር በዓሉን በደስታ ያሳልፋሉ። ቤተ ዘመዶችን እየዞሩ መጠየቅና እንኳን አደረሳችሁ መባባልም የኢድ አልፈጥር ልዩ መለያው ነው። የምግቡ አይነት እንደ የባህሉ ከአገር አገር ቢለያይም ልዩ ምግቦችን ማዘጋጀት ግን የማይቀር ጉዳይም ነው። እንደውም አንድ ሙስሊም በረመዳን ማፍጠሪያ ወቅት ምጽዋት ያልሰጠ ከሆነ የኢድ አልፈጥር በዓልን ተጠቅሞ ለምስኪኖች ዘካ መስጠት አለበት። የምግብ አልያም የገንዘብ ስጦታ ሊሆን ይችላል። ብዙ ሙስሊሞች የበዓል ድግስ ደግሰው ድሆችን የሚመግቡበት፤ የሚያለብሱበት ምስጢርም ይኸው ነው። ስለዚህም ካለው ላይ ማካፈልና አብሮ በዓሉን ማሳለፍ የኢድ አልፈጥር በዓል በጐ ተግባር ተደርጎ የሚወሰድ ሃይማኖታዊ ሕግ ነው። ስለዚህም ይህ በዓል በሁሉም ሕዝበ ሙስሊም ዘንድ ትልቅ በረከትና ደስታ የሚታፈስበት፤ በጎ ነገር የሚሰራበት ተደርጎ ይወሰዳል። የሚከበረውም በዚህ መልኩ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ሕዝበ ሙስሊሙ ኢድን ሲያከብር በመረዳዳትና በመከባበር ነው። አሁንም ይህንን ባህሉን አስቀጥሎ እንዲጓዝ ምን ማድረግ አለበት ይላሉ?
ሼህ መሐመድ፡- ይህ በዓል የደስታ ቀን ነው። በደስታ በዓሉንም ማሳለፍ ይኖርበታል። ደስታ ደግሞ የሚመነጨው ከአብሮነት፣ ያለው ለሌለው ከመስጠት፣ ከመተሳሰብና ደስታ የሚያመጡ ነገሮችን ከመስራት ነው። መስገጃ ቦታ ሳይቀር መካፈልን መሰረት ያደርጋል። በምንም መልኩ ኃዘን ወይም አንድን ሰው ማስከፋትና አሳንሶ ማየት አይፈቀድም። መከባበርም ግድ ነው። በመልካም ነገር መመካከርንም ይጠይቃል። ስለዚህም እነዚህን ማድረግ የውዴታ ግዴታ ይሆናል።
በኢድ ቀን የሰጠ፣ መልካም ነገርን ያሰበ አብልጦ ይከፈለዋል። ከፈጣሪ ማግኘት የሚፈልገውን ያህልም እርሱም ማድረግ ይኖርበታል። ምክንያቱም ተንኮል ብቻ ሲቀር ሲሳይ ሁሉ ፤ መልካም ነገሮች ሁሉ ከፈጣሪ ውጪ አይገኝም። ስለዚህም በኢድ ሜዳ ላይ የሚደረግ ሁሉ እስላማዊ ሕግን የጠበቀ መሆን አለበት። ከዚያ ውጪ የተንኮልና ተንኮለኝነት የተሞላበት ተግባር ጎን ከወገንን የዲያቢሎስ እንጂ የፈጣሪ መሆናችን ይቀራል። ስለሆነም ማንንም ባለመግፋት፣ ባለመጨካከን፣ በመተዛዘንና በመከባበር ኢዳችንን ማሳለፍ ይኖርብናል።
ሙስሊም እጁም እግሩም፣ ምላሱም ጭምር ሰላማዊ መሆን አለበት። ምላስ የሰውን ልጆች ደም እያፋሰሰ ነው፤ ምላስ፣ የሰውን ልጅ እያጋጨ ነው። ምላስ ዓለምን እያፈረሰ ያለም ነው። እናም ከምላሳችን፣ ከእጃችንና ከእግራችን ተቆጥበን መልካም ነገሮችን በማድረግ በዓላችንን በደስታ ማክበር ያስፈልገናል። ሰላም ለሁሉም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ሙስሊሙ ሰላም ሆነ ማለት ክርስቲያኑም ሰላም ይሆናል። ጎረቤት ጭምር በልቶ፣ ተኝቶ ያድራል። እናም በኢትዮጵያ ያለን ሙስሊምና ክርስቲያኖች ደስታችንም ፣ ኃዘናችንም በአንድነት የሚሆን ፤ መከፋታችንም ፣መደሰታችንም በአብሮነት የሚተገበር ስለሆነ ይህንን አስበን መንቀሳቀስ አለብን። እኛ ስንከፋ የሚከፉልንን፣ ስንደሰትም አብረው የሚደሰቱልንን ደስታቸውን ልንነፍጋቸው አይገባም። ምክንያቱም የእኛም ደስታ ይደፈርሳልና። ሁከት፣ መደማማት የሙስሊም ባህሪ አይደለም። እንደውም በእስልምና በቃላት አንድን ሰው ያስከፋ በአላህ ዘንድ ተጠያቂ ይሆናል። ስለዚህም ደስታችን ግላዊ ሳይሆን አገራዊ ጭምር መሆን አለበት።
በኢድ ቦታ ላይ ሆኖ የሚሰራ መጥፎ ተግባርም ሆነ መልካም ነገር አለም የሚያየው ሰለሚሆን በዚያ ልክ ለክቶ ማሳየት ያስፈልጋል። እኛ ለአለም ማካፈል ያለብን ደስታችንን ብቻ መሆንም አለበት። ችግር ካለብንም በራሳችን ልንፈታው ይገባናል። በየአደባባዩ ችግርን ማጉላት ሙስሊማዊ ባህሪም አይደለም። በዓሉን ስናሳልፍም በዚህ መልኩ መሆን ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ አንዳንድ ጸረ ሰላም ኃይሎች እምነትን ተገን አድርገው ሊያጋጩ ሲሞክሩ ይስተዋላሉ። ይህንን ወደጎን በመተው ሕዝበ ሙስሊሙ የቀደመ የመተጋገዝ ባህሉንና መቻቻሉን እንዴት ያስቀጥል ይላሉ ? ምንስ መደረግ ይኖርበታል?
ሼህ መሐመድ፡- በመጀመሪያ ጥሪው የማን ነው የሚለውን መለየት ለዚህ ሁሉ መፍትሔ ነው የሚል እምነት አለኝ። ምክንያቱም አሁን ላለንበት ችግር ያበቃን የተንኮል ጥሪውን ከትክክለኛው ጥሪ መለየት አለመቻል ነው። የተንኮል ጥሪን ጥሩ አዕምሮ ያለው ሰው አይቀበልም። ኢትዮጵያውያንን ራስ በራስ የሚያጋጭ፤ ሙስሊሙን ከሙስሊሙ ጋር የሚያጋጭ፤ ሙስሊሙን ከክርስቲያኑ ጋር የሚያላትም ጥሪ መቼም ቢሆን መልካም አይሆንም። ይህንን ጥሪ የሚሰሙ ሰዎች ደግሞ የሰይጣን መልዕክተኞች ናቸው። ምክንያቱም ጥሪው ሰይጣናዊ ነው። ጥሩ የሚያስብ ሰው ጥሪም አይደለም።
ምንነቱንና ማንነቱን የማላውቀው ሰው በፌስቡክ ሲጠራኝ መመርመር የማልችለው ለምንድነው? ምክንያቱም እኔ ሙስሊም ነኝ። ሙስሊም ደግሞ ሰላም ነው እንጂ ጸብ ጫሪ፣ አቀጣጣይ፣ የተንኮል አዋጅ አዋጅ አይደለም። እናም እኔ አማኝ እስከሆንኩ ድረስ ሰውን ባስከፋሁት ልክ እንደሚከፈለኝ አውቃለሁ። አላህ በቁርኣን እንዳስቀመጠው ‹‹ዛሬ ከፈጣሪ ፊት ሰው ሁሉ ይቀርባል። ፊቱ ሲቀርብም ራቁቱን ሆኖ ነው። በዚያን ጊዜ ዛሬ የምትዋሽ ምላስ ትታሸጋለች። ምስክር ሆኖ የሚቀርበውም የምንጠቁምበት ሰው ሳይሆን ስጋት የሚሆነው የራስ አካል ነው።›› ስለዚህም ይህንን ፈጣሪ ስለምፈራ የተንኮል ጥሪ ሲመጣ በፍጹም እላለሁ። እንዳይፈረድብኝም አልፈርድም። ይህ ጥሪ የሚያደርገው ሰው ዲያቢሎስ ሆኖ ሳለ አላህን ትቼ ለምንስ ለእርሱ እታዘዛለሁ? ስለዚህም ሕዝበ ሙስሊሙም አማኝነቱን እያሰበ የአላህን ጥሪ እንጂ የዲያቢሎስን ጥሪ መስማት የለባቸውም። ጥሪው ተለይቶ መከተል ከመጣ አገርም ፣ሰውም ሰላም ይሆናል።
ዲያቢሎስ ግልጽ የሆነ ጠላታችሁ ነው። ሰውን ከሰው የሚያጋጭ፣ ሰውን ደም የሚያፋስስ፣ የሰውን ህይወት የሚያስቀጥፍም ሰው ከዲያቢሎስ አይለይም። የጠላትን ጥሪ ማንም እሺ ሊለውም አይገባም። ዛሬ አገር ውስጥ ያለው ብቻ ሳይሆን መጠቀሚያ የሚያደርገን የውጪ ጠላትም ነው። ስለሆነም የእርሱን ጥሪ እንቢ ብለን በአገራችን የሚመጣውን ከወንድማችን ጋር አብረን ሁሉንም ከክፉ ነገር መጠበቅ ያስፈልገናል። በመካከላችን መቃቃርም ካለ ጠላትን ከመለስን በኋላ በመመካከር መፍታት ይቻላልና ይህንን ሰከን ብሎ መመልከትም ይገባል።
አቅሙ ያለው ሰው፣ አዕምሮው ጥሩ የሚያስብ ሰው በአገሩ አይደራደርም። መጥፎ ጥሪንም አይቀበልም። ዛሬ አገር የሚያስፈልጋትም ይህ አይነት ሰው ነውና ይህንን እንሁንላት። የኢትዮጵያ ሙስሊምና ክርስቲያን በታሪክ መተሳሰብና መከባበር እንጂ መቃረን አያውቁም። አብሮነትን እንጂ መለያየትም ባህሪያቸው አይደለም። አልፎ አልፎ ያቆሳሰሉን ሰዎች ስልጣን ፈላጊ ይሆናሉ እንጂ መሰረታዊ የሕዝቡ አኗኗር ግን ከዚህ የተለየና ነባር ታሪኩን የያዘ ነው። ስለሆነም በባህሉና በአብሮነቱ የጸናበትን ሊያጸናው ይገባል። ይህንን ማንነት የሚፈታተኑ የክፉ ጥሪ አድራጊዎችንም አደብ ግዙ፣ ቁጭ በሉ ማለት ያስፈልጋልም።
አዲስ ዘመን፡- እንደ ኢትዮጵያ የእስልምናና ክርስትና አንድነት እንዴት ይገለጻል?
ሼህ መሐመድ፡- እንደ ኢትዮጵያ ከታየ ብዙ ነገሮችን ማንሳት ይቻላል። ለአብነት የእስልምናና ክርስትና ውህደት ከቤተሰብ ይጀምራል። በቤት አቀማመጡም ቢሆን በጣም አስገራሚ ነው። በትምህርት ቤትና በተቋም ደረጃ የተቋቋሙት እንዲሁም በጋብቻም ቢሆን በይፋ ይህንን አልቀበልም፣ አላስተናግድም የሚባልበት ሁኔታ የለም። ይህ ደግሞ አንድነታችን ከዚህ እንደሚጀምር ጥሩ ማሳያ ነው። ሁሉን ተቋም ለሁሉም ማድረግ መቻሉም ቢሆን አብሮነት ለአገር ዋና ጉዳይ መሆኑን የሚያሳይም ነው።
እኔ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ነኝ፤ እኔ ኢትዮጵያዊ ክርስቲያን ነኝ የሚል ሰው የፋሲካና የኢድን በዓል አከባበር ከሕዝቡ አኗኗር ጋር ያለውን ዝምድና ብቻ አይቶ መቃቃሩን ያጠፋል። ምክንያቱም ፋሲካ ለክርስቲያኑ ቢሆንም ሙስሊም ጎረቤት ያለው ሁሉ አብሮ የሚያከብረው በዓል ነው። ኢድም ቢሆን እንዲሁ ክርስቲያን ጎረቤት፣ ቤተሰብ ያለው በአንድነት እንኳን አደረሰህ እየተባባለ የሚያከብረው በዓል ነው። የዘንድሮው በተለይ በጾምና በጸሎት ጭምር ተባብሮ አንድ ሆኖ ዛሬ ላይ የደረሰ ነው። ደስታን መመኘት በራሱ አንድነትን ከመፈለግ የተለየ አይደለም። ስለዚህም በእምነት ተኮራርፎም ተለያይቶም አይታወቅም። በአብሮነት ባህልን ከፍ እያደረጉ ይኬድበታል እንጂ።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ሁሉ ባህልና መተሳሰብ ካለን ለምን እንድንጋጭ ሆንን? ማነውስ ይህንን የሚያደርገው?
ሼህ መሐመድ፡- ከሌሎች የምንወስደውን ባለማወቃችን፣ መተጋገዝ ባለመቻላችን፣ በምክክር ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ ተቃራኒውን ለማየት ዝግጁ መሆናችን ነው። ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ሙስሊም መጥቶ የአንተ ወገን ነኝና ተከተለኝ ሲለን ከመከተላችን በፊት እኔ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ነኝ ማለት አለመልመዳችንም አንዱ ችግር ነው። ማንነታችንን በአገራችን መግለጽ ከምንም በላይ ከችግሮች ያድነናል። ይሁንና ይህንን ስናደርግ አይታይም። በአገሬ ጥቅም ዙሪያ እምነትን ተታኮ የመጣ አማኝ ማስተናገድ ተገቢነት የለውም። እነርሱ በብዙ ነገር ሊሸረሽሩን ይፈፈልጋሉ። ግን መረታት የለብንም።
አንድነታችንን የሚሸረሽረው በዋናነት በመልካም ጎኑ ከመረዳት አሉታዊውን ማየት መፈለጋችን ይመስለኛል። መጥፎ ጎኖችን ነጸብራቅ እያደረጉ መልካሙን እየቀበሩ ያሉት ደግሞ አቅማቸውን ለማጎልበት ሃይማኖትን ወይም ብሔርን ተገን አድርገው የሚሰሩ አካላት ናቸው።
ስብከታችንም አሉታዊ መሆኑ አንዱ ተጽዕኖ ፈጣሪ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ወጣት ችኩል ነው ሁሉንም መንካትና ማየት ይፈልጋል። ጥሩ አድርገን ካልሳልነው ደግሞ ልማት፣ ጉልበት፣ የአገር ሀብት የሆነውን ወጣት እናጣዋለን። ይህ ሆነ ማለት ደግሞ ሰዎች ጧሪ ቀባሪ ያጣሉ፤ አገር ሰላሟ ይደፈርሳል፤ ተተኪ ትውልድንም በቀና አዕምሮ ማውጣት ይከብዳል። ስለዚህም ዛሬ እየተከሰተ ያለው የዚህ ፍሬ ሊሆን ይችላል። አባቶች እና እናቶች ሳያስቡት ልጆቻቸውን ቀርጸው ራሳቸውም አብረው እየሞቱ የሚሆኑበት አጋጣሚም ይኖራል። ይህ ደግሞ ለችግሩ መፍትሄ ሰጪነትን አሳንሶታል።
እንደእኔ እምነት የሆነ ቦታ ላይ ያመለጠን አለ ብዬ አስባለሁ። ይህንን ደግሞ በማስተማር፤ በጥናት መመለስ ያስፈልጋል። ሰው እየሞተ ያመለጠንን ለመፈለግ እናጥና የሚባለው ትክክል አይደለም ከተባለ ይህ ወረርሽኝ እንጂ የነበረ ማንነት ያመጣው አይደለም። ስለዚህም ወላጆች ከልጆቻቸው የጀመረ ሥራ መስራት አለባቸው። የሃይማኖት አባቶችም የሃይማኖት አስተምሯቸውን በሚገባ በአርአያነት ማስተማር አለባቸው። በትምህርት ቤት የሚሰጠውን ትምህርትም አስመልክቶ መንግስት በሚገባ ሊፈትሸው ያስፈልጋል። ሥራው የዘመቻ ተግባርን ይጠይቃል። ስለዚህም ችግሩን ለይቶ መፍትሄ እየሰጡት መሄድን ዋና ተግባራችን ማድረግ ይኖርብናል።
አዲስ ዘመን፡- በአገር ደረጃ 98 በመቶ የሚሆነው አማኝ ነው ይባላል። ነገር ግን ችግር ፈጣሪውም አማኝ ነኝ ባዩ ላይ ይሰፋል። ከዚህ አንጻር አማኝነትን እንዴት ይገልጹታል?
ሼህ መሐመድ፡- እንደ አገር ወደ አንድ አካባቢ ብንሄድ አሳድሩኝ የምንለው በአካባቢው ታዋቂ የሆኑ የእምነት አባቶች ጋር ነው። ምክንያቱም እኔን ይጎዱኛል ሳይሆን አብልተው አጠጥተው ተንከባክበው ያሳድሩኛል ብዬ አምንባቸዋለሁ። ይህ የሚያሳየው ደግሞ ለእነርሱ ያለንን ትልቅ ቦታ ነው። የእምነት መግለጫውም ይኸው ነው። እምነት በአለባበስ ሊለይ ይችላል እንጂ በተግባር አንድ ነው። ምክንያቱም ዋና መሰረቱ መልካም ማድረግ፤ መልካሙን ሁሉ ማሰብና በዚያ መኖር ነው። አንድ ሰው አማኝ ነው አይደለም የሚያስብለውም ሥራው እንጂ ንግግሩ ወይም አለባበሱ አይደለም።
በቁጥር ደረጃ ትክክል ነው። ነገር ግን በሥራና አሁን በአለው ነባራዊ ሁኔታ አማኝነት ከተግባር ውጪ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። የሚሰራው ሥራ የማንም እምነት መግለጫ ናቸው ብዬም አላምንም። ምክንያቱም የትኛውም እምነት ክፉነትን፣ መቃቃርን አያስተምርም። እንደውም ቢቻላችሁ ከሁሉም ጋር በሰላም ኑሩ ነው የሚለው። ከማይመስል ጋር እንኳን በሰላም መኖር የውዴታ ግዴታ ነው።
ሰዎች በእምነት ከኖሩ መደጋገፋቸውን ማንም ሊሸረሽረውና ሊነካው አይችልም። በብዙዎቹ የአገራችን ክፍሎች የሚታየውም ይኸው ነው። ሙስሊሙ ክርስቲያኑን ይጠብቃል፤ ክርስቲያኑም እንዲሁ ሙስሊሙ እንዳይነካበት ይከላከላል። ነገር ግን የሚታየው አሉታዊው ስለሆነ ይህንን ለማንሳት አልተቻለም። ኢትዮጵያውያኖች ያለን መተሳሰብና አብሮነት በሁሉም አለም የሚታወቅ ነው። ነገር ግን አሁን ያለን አድራጎት እምነታችንን የሚገልጥልን አልሆነም። እናም አማኝነታችንን ለሌሎች ጭምር ማጋባት ያስፈልገናል። እኛ ካመንን ብዙ አማኞችን ማፍራት እንችላለን። ሳናምን ግን እመነኝ በፍጹም የማይታሰብና የማይሆን ነገር ነው።
አዲስ ዘመን፡- በአገራችን ከመጣው ለውጥ ጋር ተያይዞ ብዙ ችግሮች ከብሔርና ከሃይማኖት ጋር ሲያያዙ ይስተዋላል። ይህ ሁኔታ ምንጩ ምን ሊሆን ይችላል? እንዴትስ መፈታት አለበት?
ሼህ መሐመድ፡- ደካማ ሰዎች ድክመታቸውን የሚጠግኑት ብሔርን ወይም ሃይማኖትን ተገን በማድረግ ነው። አሁን እየታየ ያለውም ችግር የደካሞች ሰለባ መሆናችን ያመጣው ነው።ጥሩ ሰዎች የሚያስቀይማቸው ነገር ካለ በግልጽ ይናገራሉ። ለአቅም ማጎልበቻ ብሔራቸውንም ሆነ ሃይማኖታቸውን አይጠቀሙም። በእኔ ምክንያት ለምን ሰው ይጎዳል የሚሉ ናቸው። ሰውነታቸውን ተረድተው ለሰዎች መልካም ከማድረግ አይቦዝኑም። ችግሩ በእነርሱ ላይም እንደሚመጣም ያውቃሉ። እኔ ሰው ነኝ፤ እዚህ ምድር ላይ ያለኝ ቆይታም ጊዜያዊ ነው። ስለዚህም ጊዜዬን በመልካም ነገር ማሳለፍ አለብኝ የሚሉም ናቸው።
ጥሩ ሰዎች መጥፎ ታሪክ አላስመዘግብም የሚሉ ብቻ አይደሉም፤ የሚያስተሳስር የእምነት ሥርዓቱን የሚጠብቅ ተግባር የሚከውኑም ናቸው። ወገኖቼን በማቁሰል፣ በማድማት፣ ህይወታቸውን በመቅጠፍ ፤ ሀብታቸውን በመዝረፍ ታሪኬን አልቀብርም የሚሉም በመሆናቸው መጥፎ ተግባር ላይ አይሳተፉም። በፈጣሪ እንጂ በማንም መከለልም አይፈልጉም። አቅምና ጉልበታቸው እርሱና ሥራቸው ስለሚሆን። ስለዚህም የመጥፎ ተግባር ከዋኞቹ አማኞች ሳይሆኑ ከዚያ ውጪ የሆኑ ናቸው።
እንደ አማኝ ሆኜ ሳስብ ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔርተኛ ዜጋ አለ ብዬ አላስብም። ምክንያቱም ሙስሊም ክርስቲያኑ ብቻ ሳይሆን ኦሮሞ ፣አማራው፣ አፋርና ጉራጌው፣ ሱማሌና ቤኒሻንጉሉ ወዘተ በጋብቻ የተሳሰረ ነው። ይህ ደግሞ ጥርት ያልኩ ነኝ የሚያስብለው ብሔር እንዳይኖረው አድርጓል። በተመሳሳይ በሃይማኖትም ጥርት ያልኩ ነኝ ለማለት የሚቻልበት ሁኔታ የለም። ታሪክም ቢሆን ይህንን አይነግረንም። ስለዚህም የኢትዮጵያን ሕዝብ ብሔርተኛ የሚያስመስሉት ደካሞች የአቅም መጠቀሚያ ለማድረግ በሚሰሩት ስራ ነው። ለአቅማቸው ማጎልበቻም ሃይማኖቱንና ብሔርን ተጠቅመውበታል።
አንዳንዴ በደንብ አይናችን ከተገለጠ የኢትዮጵያን ሕዝብ የትም ላይ አልተለያየም። ከዚያ ይልቅ ሁሉ ነገሩ ድርና ማግ እንደሆነ በግልጽ ማየት ይቻላል። ይሁን እንጂ ይህ እንዳይታይ የደፈኑ አካላት አሉ። እነዚህን ለመለየት ደግሞ የእድሜ ክልልን ብቻ መመልከት በቂ ነው። ስለብሔር አርገብጋቢው ፤ ስለ ሃይማኖት አጯጯሂውም ማን ነው የሚለውን መመርመር ያስፈልጋል። ምክንያቱም ይህንን የሚያደርጉት የማገናዘብ ችግር ያለባቸው፣ አቅማቸውን ለማጎልበት የሚሯሯጡ ጥቅመኞች ስለሚሆኑ እነርሱን ማስቆም ይገባል።
አማኝ፣ ሕዝብ በምንም መልኩ አንድነቱ ላይ አይደራደርም። ለመጥፎ ነገርም አይተባበርም። ተሳታፊውም እርሱ ነው ብዬ አላስብም። ስለሆነም አሁን ያለውን መፈናቀል፣ ህይወት መጥፋት በብሔርና በሃይማኖት ተገን እንጂ በትክክል በሕዝቡ ዘንድ ያለ እንዳልሆነ በማመን በአንድነት ለችግሩ መፍትሄ መስጠትም ከእያንዳንዱ ዜጋ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- በጾሙ ወር ተቆጥሯል። ከዚያ ጎን ለጎንም መረዳዳቱና መቻቻሉ በስፋት ታይቶበታል። ከዚህ አኳያ በቀጣይም ይህ ድርጊት ሳይቋረጥ እንዲከናወን ሕዝበ ሙስሊሙ ምን ሊያደርግ ይገባል ይላሉ?
ሼህ መሐመድ፡- ጾም ማለት ሰዎች ከፈጣሪያቸው ጋር የመገናኛ ድልድይ ነው። ከፈጣሪው የሚፈልገውን ማግኛም ነው። በተለይ ከመአትና ችግር ፈጣሪው እንዲታደገው መለመኛም ነው። ስለዚህም በቁርአን እንደተቀመጠው አዛኞች አዛኙ ጌታ ያዝንላቸዋል ነውና ይህ ጾም የምናዝንበትና እርሱም እንዲያዝንልን የምናደርግበት ነው። ማዘን ደግሞ ያለን በማካፈል ይጀምራል። መከባበርንም ይጠይቃል። የጾም ልፋት ዋጋ የሚከፈለው ደግሞ ፈጣሪን የሚያስደስት ሥራ ሲሰራ የሚገኝ ነው።
የጾም ማሳረጊያው ለሁሉም ደስታን መፍጠር ነው። ይህ የሚሆነው ደግሞ በመተባበርና በመተጋገዝ ያለን ችግር መፍታት ሲቻል፤ ስለአገር ፣ ስለሕዝብ መጨነቅና በተግባር ሰላምን ማስፈን ሲቻል ነው። የተፈናቀሉ ወገኖቻችን የእኛ ጉዳይ ናቸው። ቤተሰቦቻቸውን በእኛው ያጡ ሰዎች መጽናናትን ይፈልጋሉና ለእነርሱም መድረስ ያለብን እኛው ነን። ስለዚህም አብረን ከእነርሱ ጋር በዓልን ማሳለፍም ይገባናል። የምናግዛቸውንም በቻልነው ሁሉ ማድረግ የውዴታ ግዴታችን መሆን አለበት። ይህንን ስናደርግ መጥፎ ምልከታቸውን ጭምር እናጠፋላቸዋለንና በዓላችን በዚህ መልኩ ማለፍ ይኖርበታል።
መልካም ሥራ የጊዜ ገደብ የለበትም። ተጨማሪ በረከትን ለማግኘት ደግሞ በቋሚነት መልካምነትን ማሳየት ግድ ነው። ረመዳን ጾምም ሲያልቅ አብሮ መልካም ነገርም አያልቅም። ከዚያ ይልቅ እጥፍ ሂሳብ ይከፈለናል ብለን የምናምንበትን ስራ እናስቀጥላለን። መልካም ነገር እዚህ ምድር ላይ እስትንፋሳችን እስካለበት ድረስ የሚቀጥል ነው። ምክንያቱም የጀነት መግቢያ ቁልፍ አሰጪው ሥራችን ስለሆነ። እስትንፋሳችንን የሚጠብቀው ተንኮል በህይወታችን ሳለን ዛሬውኑ መታረም አለበት። የቆምንበት ቦታ ላይ ተንኮልን ማረም ያስፈልጋል። መቼ ሞት እንደሚወስደን ስለማናውቅ። እናም በጾም ብቻ የተወሰኑ መልካሞች ስለሌሉ በተግባር እስከመጨረሻው በመረዳዳት ልንጠቀምባቸው ይገባል።
በረመዳን ወቅት አንድ ሱና የሰራ ማለትም ሰራም አልሰራም የማያስጠይቀውን ተግባር የተገበረ ሰው በእጥፍ የሚታሰብለት እንጂ የሚቀነስበት አይሆንም። ስለዚህ መልካም ተግባራት እስትንፋስ እስከሚቋረጥ ድረስ መቀጠል አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- በአጠቃላይ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካልዎት ?
ሼህ መሐመድ፡- አላህ በቁርአን እንዳለው በመልካም ነገር ላይ ተባበሩ፤ በመልካም ነገር ላይ ተረዳዱ፤ በወንጀልና መጥፎ ነገር ላይ ግን እንዳትሳተፉ። ወንጀል ትብብር አያስፈልገውም። የስናፍጭ ቅንጣት ታክል መልካም ስራን የሰራ ሰው የመልካም ሥራውን ውጤት ያያል ነውና ይህንን ለማድረግም እንትጋ። ለዚህች ቅንጣት ቢሆን እንኳን ሂሳቡን ለመክፈል እኔ ዝግጁ ነኝ ስለሚልም ከፈጣሪ ይህንን ክፍያ ለማግኘትም በመልካም ሁሉ ላይ መረባረብ የሁልጊዜ ተግባራችን ልናደርገው ይገባል።
በእምነታችን ጀነትና ሲኦል እንዳለ እናውቃለን። እናምናለንም። ስለዚህም በሥራችን የቅንጣቷን ያህል ተንኮል ከሰራን ክፍያችን ሲኦል እንደሆነ ማሰብ በዚያው ልክ ቅንጣቷ መልካም ተግባራችን ጀነትን እንደምታቀዳጀን አምነን ምርጫችንን ማስተካከል ያስፈልገናል። የሸሩን ውጤት ሳይሆን የመልካም ተግባራችንን ክፍያ በማብዛትም ከአሁኑ ሥራችንን መልካም ማድረግ ላይ ማተኮር ያስፈልጋል። መልካሙን ማብዛት ክፉን መቀነስ ግዴታ መሆኑን መጓዝም የዛሬው ሥራችን መሆን አለበት።
አገራችን የሁላችንም ነች። ከሁላችንም ድጋፍን ትፈልጋለች። ሰላም ለማምጣት ደግሞ የሁላችንንም ሥራ ይጠይቃል። ከአንድ አቅጣጫ ብቻ ሰላም እንዲወርድ መጠበቅ የለብንም። ሰው ሁሉ ሲተባበርና ከአምላኩ ጋር ሲታረቅ፣ በእምነት ሲጓዝ ነው ሰላም የሚወርደው። ለዚህ ደግሞ የሃይማኖት አባቶች በጸሎትና ልጆችን በማስተማር ሊተጉ ይገባል፤ ፖለቲከኛውም እንዲሁ ለአገሩ እንጂ ለራሱ ብቻ ማሰብ የለበትም። ምክንያቱም አገር ስትኖር ስለሆነ እርሱም የሚቆመው። ወጣቱም ዝም ብሎ ከመነዳት መመርመር ይጠበቅበታል። መንግስትም እንዲሁ የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል። ሁሉም የራሱን ኃላፊነት ችላ ሳይል መስራት ለአገር አንድነትና ሰላም አስፈላጊ መሆን አምኖ ነገን የተሻለ ማድረግ ላይ መስራት ይገባዋል።
ዛሬ ተንኮል እንኳን በመተባበርና በመረዳዳት ካልሆነ በቀር በምንም መልኩ መቆም አይችልም። ምክንያቱም ተንኮል ሁሉንም ይበላል፤ የተከበሩ ሰዎችን ያዋርዳል፤ የተከበረችን አገርም ያጠፋል። ስለዚህ ተንኮሉን ለማቆምና መልካሙን ለማስቀጠል መረዳዳት ግዴታ እንደሆነ ማሰብ ያስፈልጋል። ጥሩ አገር ትኑረን ብለን ካሰብን በብሔርና በሃይማኖት እየተነቋቆርን የምናመጣው ለውጥ አይኖርምና ይህንን ቆም ብሎ ማሰብና የተዛቡ ነገሮችን አርሞ መጓዝ ላይ ሁሉም በየበኩሉ መስራት አለበት። በዓላችንን የደስታና የፍቅር ያድርግልን።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ሀሳብ እናመሰግናለን።
ሼህ መሐመድ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ግንቦት 5 ቀን 2013 ዓ.ም