የኢትዮጵያን የኋላ ታሪክ ስንመለከት ከገናና የአሸናፊነት ገድል ጀምሮ የድርቅ ተምሳሌት እስከመሆን፣ ከሰው ዘር መገኛነት እስከ ጥንታዊ ስልጣኔ፣ ከአልገዛም ባይነት እስከ የሌሎች አገራት አርአያነት ወዘተ የዘለቁ ጉራማይሌ ታሪኮችን እናገኛለን። እነዚህ ታሪኮቻችን አሁን አገራችን ላለችበት ደረጃ የየራሳቸውን አወንታዊና አሉታዊ አሻራ አኑረው ያለፉ ናቸው።
የአክሱም ሃውልቶች፣ የላሊበላ አብያተ ክርስቲናት፣ የጎንደር ቤተመንግስት፣ የጀጎል ግንብ፣ የአባጅፋር ቤተመንግስት፣ የንጉስ ጦና አስተዳደር፣ የገዳ ስርዓት፣ የፊቼ ጨምበላላ እና ሌሎች ቅርሶቻችን የኋላ ታሪኮቻችንና ባህላዊ እሴቶቻችን አገራችን በበጎ እንድትነሳ ጉልህ ድርሻ ያበረከቱ ናቸው።
በ19ኛው ክፍለ ዘመን አምባገነን የነበሩ የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን በተቀራመቱበት ወቅት ኢትዮጵያውን ወራሪዎችን በመመከት ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የአፍሪካ ወንድሞቻቸውም አርአያ መሆን የቻሉ ህዝቦች ናቸው። በ1887 በዓድዋው ጦርነት ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘር፣ ሃይማኖት፣ማንነትና የቦታ ርቀት ሳይገድባቸው በአንድ ልብ አገራቸውን ከወራሪ ሃይል ለመከላከል አጥንታቸውን ከስክሰዋል፣ ደማቸውን አፍስሰዋል። እነዚህ ታሪኮቻችን የኢትዮጵን አንድነት የሚመሰክሩ ህያው የጀግንነት ታሪኮቻችን ናቸው።
ይሁን እንጂ ካለፉት ሃምሳ አመታት ወዲህ የኢትዮጵያ ገጽታ ቀስ በቀስ እየተበላሸ የመጣበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ከዚህ ጋር ደግሞ በውስጥ በነበረው ፊውዳላዊና አምባገነናዊ ስርዓት የተነሳ ኢትዮጵያ ለህዝቦቿ ያልተመቸች አገር ወደ መሆን የሄደችበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በዚህ የተነሳም በአገራችን የርስ በርስ ግጭቶች መበራከት የጀመሩበትና ኢኮኖሚያችንም ቀስ በቀስ የተዳከመበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
ይሁን እንጂ ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ ተስፋን ባጫረው የለውጥ ሂደት የሃገራችን መፃኢ እድል ብሩህ እንደሚሆን ያመላከቱ በርካታ ተስፋዎች ታይተዋል። ከእነዚህም ውስጥ በተለይ ከልማት አንጻር በራሳችን አቅም የጀመርናቸው ትላልቅ ፕሮጀክቶቻችን እውን እየሆኑ የመጡበት ተጨባጭ ለውጥ እየታየ ነው። ለዚህ ደግሞ አንዱ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል።
ከዚህ በተጨማሪም ሃገራችን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የምታደርገውን ጉዞ አጠናክራ በመቀጠል ከፍተኛ እመርታን አሳይታለች። ይህ እውን ይሆን ዘንድም ዴሞክራሲያዊና ትክክለኛ ምርጫን በማካሄድ ስልጣን በምርጫ ብቻ የሚገኝበትን መንገድ ለማሳየት እየጣረች ትገኛለች። ከዚህም ባሻገር እያንዳንዱ ዜጋ ያለምንም የፖለቲካ ተፅዕኖ የመሰለውን ሃሳብ እንዲያራምድ እድል የተሰጠበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
እነዚህ ሁሉ ለውጦች ያላስደሰታቸው በርካታ የውስጥና የውጭ ሃይሎች አሉ። በተለይ ከልማት አንፃር የኢትዮጵያን ብልጽግና የማይፈልጉት ግብፆች ሱዳንን ጭምር በማስተባበር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ። በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች በተለይ በቤኒሻጉል ጉሙዝና ምዕራብ ወለጋ አካባቢ በተደጋጋሚ ሰላም እንዲጠፋ እጃቸውን በማስገባት ሃገር እንዳትረጋጋ በማድረግ የተጀመሩ ውጥኖች እውን እንዳይሆኑ እየሰሩ ነው።
በሃገር ውስጥም ለ27 አመታት ያህል በስልጣን ላይ የቆየውና በህዝብ ትግልና በውስጡ በነበሩ ለውጥ ፈላጊዎች ከስልጣን ላይ የተነሳው ህወሓት የተጀመረው የብልፅግና ጎዳና እውን እንዳይሆን በርካታ ሴራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። በዚህም መሰረት ቡድኑ ባለፉት ሶስት አመታት የሰሜን እዝን እስከወረረበት ጊዜ ድረስ ብቻ ደም ካፈሰሱ፣ ንብረት ካወደሙና ዜጎችን ካፈናቀሉ 113 ግጭቶች ጀርባ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እጁን በማስገባት ሃገር እንዳትረጋጋ ሲያደርግ ቆይቷል።
ከዚህ በተጨማሪም ላለፉት አምስት አስርት አመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የጎላ አወንታዊ አስተዋፅኦ ማበርከት ያልቻለው የኦነግ ወታደራዊ ክንፍ ሸኔ በርካታ ንፁሃን ዜጎችን በመግደልና ሃገርን በማሸበር ለውጡ እውን እንዳይሆን ሲሰራ ቆይቷል። በዚህም እነዚህ ሁለት ቡድኖች ሰሞኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብለው መፈረጃቸው ቡድኖቹ ምን ያህል ሃገርን የማተራመስ እንቅስቀሴ ውስጥ እንደነበሩ የሚያሳይ ነው። የእነዚህ ቡድኖች ዋነኛ አላማ ሃገርን ማፍረስ ነው። እና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ማንኛውም ሃገርን የማሸበር ተልዕኮ የተሸከሙ ሰዎችና ቡድኖችን ሃይ ሊል ይገባል።
እያንዳንዱ ሰው በሰላማዊ መንገድ በነፃነት መኖር የሚችለውና መብቶቹ ሊከበሩለት የሚችሉት ሉኣላዊ አገር ሲኖረው ብቻ ነው። የአገር ሉኣላዊነት የሚከበረው ደግሞ አገራዊ አንድነት ሲኖር ብቻ ነው። በአንድ አገር ውስጥ የህዝቦች የእርስ በርስ ግጭት ካለ አገር እንደ አገር ሊቀጥል አይችልም። በዚህ አጋጣሚም በውጭ ሃይል የመጠቃት እድሉ ሰፊ ይሆናል። ለዚህም ሰሞኑን ሱዳን እያሳየች ያለችውን የጠብ አጫሪነት ምልክት ብቻ ማየቱ በቂ ነው። በአንፃሩ የህዝቦች አንድነት ከተፈጠረ አገርን ለመጠበቅም ሆነ ለማልማት ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
ልማትና ዴሞክራሲን ማረጋገጥ ደግሞ እንደአገር በሰላም ለመቀጠል ከሚያስችሉ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ነው። ድህነትን ማሸነፍ የሚቻለው ልማት ሲረጋገጥ ነው። ከዚህ ጎን ለጎንም እያንዳንዱ ሰው በአገሩ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲሰፍን ይፈልጋል። እነዚህ ጉዳዮች ለእንዳንችን አስፈላጊ መሆናቸውን እንረዳለን፤ እንፈልጋለንም። ነገር ግን የሚተገበሩበት መንገድ ላይ የተለያየ አቋም ልንይዝ እንችላለን።
ይህ እውን እንዲሆን ታዲያ የስራ ባህላችንን መለወጥ የግድ ነው። በተለይ ተባብሮ የመስራት ባህላችን ሊዳብር ይገባል። አበው እንደሚናገሩት ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ፣ ለሃምሳ ሰው ግን ጌጡ ነው። ይህም የሚያመላክተው አንድን ጉዳይ በጋራ መስራት ጉልበትን በማጠናከር ስራን ለማፋጠን ጠቃሚ መሆኑን ነው። ለዚህ ማሳያ የሚሆኑ በርካታ ጉዳዮችን ማንሳት ይቻላል። ለምሳሌ አንድ አርሶ አደር የዘራው ሰብል በሚደርቅበት ወቅት ዝናብ ከመምጣቱ በፊት ቶሎ ሊታጨድና ሊሰበሰብ ይገባል። ይህንን በአጭር ጊዜ ለማከናወን ደግሞ የሌሎችን ትብብር መጠየቅ የተለመደና አዋጭ መንገድ ነው። በዚህ የተነሳ “ደቦ” የሚል የቆየ የትብብር ባህላዊ አሰራርን በመፍጠር እንዲህ አይነት ወቅቶችን በስኬት ያሳልፋሉ።
ደቦ የአካባቢው ሰዎች በመሰባሰብ የአንድን አርሶ አደር ስራ በፍጥነት የሚፈጽሙበት አሰራር ሲሆን እጅግ ውጤታማና የተለመደም አሰራር ነው። ይህ የትብብር መንፈስ ደግሞ ከስራውም ባሻገር የአርሶአደሮችን አንድነትና የወዳጅነት መንፈስ የሚያጠናክር ተግባር ነው።
በሌላ በኩል በከተማም ሆነ በገጠር ያለውን እድር ማየት ይቻላል። እድር በአብዛኛው በችግር ወቅት ለመረዳዳት የሚፈጠር እና አልፎ አልፎም በደስታ ወቅት የሚገለግል የመረዳዳትና የአንድነት መንፈስ የሚጠናከርበት የኢትዮጵውያን ባህል ነው። ይህ ባህል አንድ ድንገተኛ ችግር የደረሰበት ዜጋ ችግሩን ብዙ ሳይጎዳ እንዲያሳልፍ የሚገለገሉበት ጠንካራ ባህል ነው።
አሁን አሁን ግን በአገራችን ከአንድነት ይልቅ ልዩነት፣ ከአገራዊ ማንነት ይልቅ ጠባብ ብሄርተኝት እየጎላ የመጣበትን ሁኔታ በስፋት ተመልክተናል። እንዲህ አይነት ባህል እየጎለበተ ሲመጣ ደግሞ አገራዊ አንድነት ላይ አሉታዊ ጫና ያሳድራል። በዚህ ሂደት ውስጥ የሚሳተፉት ደግሞ በመከፋፈል ውስጥ ጥቅም አገኛለሁ የሚል ተስፋ ያላቸው አካላት ብቻ ናቸው።
ስለዚህ በአገራችን አንድነትን እውን ለማድረግ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እኔ በአገሬ ሁሉም አካባቢ በሰላም የመንቀሳቀስ፣ ሰርቶ የመኖርና ሃብት የማፍራት፣ እንዲሁም በሰላም የመኖር ዋስትና እንዲኖረኝ የሌላውን መብትም ማስከበር አለብኝ የሚል እምነትና ቆራጥነት ሊኖረን ይገባል። እኔ ባለሁበት አካባቢ ለሌላው ኢትዮጵያዊ በሰላም እንዲኖር እድል ስሰጥ እኔም በየትኛውም የአገሬ ክፍል በሰላም እንድኖር እድል አገኛለሁ ብሎ ማሰብና ይህንንም በተግባር ማሳየት ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል።
ውቤ ከልደታ
አዲስ ዘመን ግንቦት 5 ቀን 2013 ዓ.ም