የሞጣ ከተማ በምሥራቅ የመርጦ ለማርያም መካነ ሰላም መንገድ፤ በደቡብ መሥራቅ አዲስ አበባ ደጀን፤ በደቡብ ደብረማርቆስ ቢቡኝ፤ በምዕራብ የአዴት፣ ባህርዳር፣ ጎንደር እና በሰሜን ደግሞ እስቴ ደብረ ታቦርን የሚያገናኙ መንገዶች የሚያልፉባት ከተማ ናት።ከከተማዋ የንግድ ማዕከልነት ጋር ተያይዞ የሰዎች የማልማት ፍላጎት ከፍተኛ ነው።የዛሬው የፍረዱኝ አምዳችን በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ወደ ምትገኘው የሞጣ ከተማ አስተዳደር ይወስደናል።
በሞጣ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ ዜጎችን የቤት ጥያቄ ለመፍታት ከተማ አስተዳደሩ በዙሪያው ከሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች ለአርሶ አደሮች የመሬት ካሳ በመክፈል የቤት ጥያቄ ላላቸው በማህበር ለተደራጁ አካላት ማስተላለፍ ይጀምራል።ይሁን እንጂ መሬታቸው ለቤት መስሪያ ሲወሰድባቸው ካሳ የተከፈላቸው አርሶ አደሮች እንዳሉ ሁሉ ካሳ ያልተከፈላቸውም አርሶ አደሮች በርካታ ናቸው።ከዚህ ጋር ተያይዞ መሬታችን በከተማ አስተዳደሩ ለቤት መስሪያ ከተካለለ በኋላ ምንም ካሳ ሳይከፈለን መሬታችንም ከጥቅም ውጭ ሆኖብን ለችግር ስለተጋለጥን ችግራችንን አይቶ ህዝብ ይፍረደን ሲሉ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አቤት ብለዋል።
ዝግጅት ክፍሉም ካሳ ባለመከፈላቸው ለችግር ተጋልጠናል ያሉትን አርሶ ደሮች በቦታው ሂዶ ማየት ችሏል።በቦታው ለማየት እንደተሞከረው ችግሩ ደርሶብናል ያሉት አርሶ አደሮች በርካታ ስለሆኑ እና ተፈፀመብን ያሉት አስተዳደራዊ በደል ተመሳሳይ በመሆኑ ለማሳያ ያህል የሁለቱን አርሶ አደሮች ቅሬታ ይዘን ቀርበናል። አርሶ አደር እንየው ጌትነት በምሥራቅ ጎጃም ዞን በሁለት እጁ እነሴ ወረዳ የአየን ቀበሌ ነዋሪ ናቸው።አርሶ አደሩ ባለትዳር እና ሦስት ልጆች አባት ናቸው።
እንደ አቶ እንየው ገለፃ፤ እስከ 2009 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ቤተሰባቸውን የሚያስተዳደሩት ግማሽ ሄክታር ከሆነችው መሬታቸው በሚያገኙዋት ምርት ነበር።ይሁን እና “ድሀን ሲበድለው …. ያደርገዋል” ሆነ እና ከነበረቻቸው ግማሽ ሄክታር መሬት ውስጥ ከፊሉ መሬት በ2009 ዓ.ም የከተማ ክልል ተብሎ ከሁለት እጁ እነሴ ወረዳ ለሞጣ ከተማ አስተዳደር ተሰጠ ይላሉ።የሞጣ ከተማ አስተዳደርም መሬቱን ለተደራጁ ማህበራት ሊመራቸው እንደሆነ በመግለጽ እና ለመሬቱ ባለይዞታ ለነበሩ አርሶ አደሮች ካሳ እንደሚከፍል በማሳሰብ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በይዞታ ሲያስተዳድሩት የነበረው መሬታቸው የእርሳቸው አለመሆኑን ይነገራቸዋል።
ይሁን እንጂ የከተማ አስተዳደሩ በማህበር ለተደራጁ ቡድኖች መሬቱን ሲመራ መደዳውን ያልሆነ እና አልፎ አልፎ በመሆኑ የእኔ እና እኔን መሰል የአርሶ አደሮች መሬት ለአዲስ ቤት ሰሪዎች ሳይተላለፍ ማህል ላይ ከቤቶች ማህል መቅረቱን አቤቱታ አቅራቢው ይናገራሉ። በመሆኑም ይላሉ አርሶ አደር እንየው፤ እኔን ጨምሮ ማሀል ላይ መሬታቸው ሳይመራ የቀሩት አርሶ አደሮች ካሳ ሳይከፈለን ቀረ።መሬታቸው ከሁለት እጁ እነሴ ወረዳ ወደ ሞጣ ከተማ አስተዳደር እንደተወሰደ እና ከሳ ስለሚከፈላቸው እናዳያርሱት ከተነገራቸው በኋላ ለምንድን ነው ካሳ የማይከፈለን ? ብለው ቢጠይቁም «የእናንተ መሬት የተረከበው የከተማ አስተዳደሩ በመሬት በፕላኑ መሰረት የእናንተን መሬት የከለለው ለአረጓዴ ስፍራ( ለግሪን ኤሪያ) ነው።አሁን ላይ ደግሞ ግሪን ኤሪያውን ከተማ አስተዳደሩ ስለማይፈልገው ለመሬቱ ካሳ የማይሰጥ በመሆኑ ማረስ ትችላላችሁ፡፡» የሚል መልስ እንደተሰጣቸው አቤቱታ አቅራቢው አርሶአደር ይናገራሉ።
እንደ አቶ እንየው ገለፃ፤ እኔ እና መሰል ችግሩ የደረሰባቸው አርሶ አደሮችም «እንዴት ነው ይህ ሁሉ መሬት ለግሪን ኤርያ የሚሆነው ?» ብለን ጠይቀን ምላሽ የሚሰጠን በማጣታችን በመንደር ማህል ያለውን ማሳችንን ለማረስ ተገደናል።ይሁን እንጂ ማሳችንን ስንት እና ስንት የጉልበት እና የገንዘብ ወጭ አደርገን እህል ከዘራነው በኋላ አዲስ መሬት ተመርተው ቤት የሰሩት ሰዎች መውጫ መግቢያ ስለሌላቸው በእኛ ማሳ ላይ ይመላለሱበታል።ቆሻሻም ይደፋሉ።የሚያረቧቸው እንስሳቶቻቸውም በወጡ በገቡ ቁጥር የሚበሉት የእኛን ማሳ ሆነ ሲሉ ምሬታቸውን ይናገራሉ።
አንድን ማሳ በተፈለገው ደረጃ ምርት እንዲሰጥ ለማስቻል ተገቢው የእርሻ ሥራ ከመሥራት እና ተገቢውን የምርጥ ዘር ከመጠቀም ባለፈ ማሳው አላስፈላጊ ከሆነ የእንስሳት እና የሰዎች ንክኪ ነፃ መሆን እንዳለበት የጠቆሙት አቶ እንየው፤ ነገር ግን እኔን ጨምሮ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ አርሶ አደሮች ከሁለት እጁ እነሴ ወረዳ ተወስዶ ለሞጣ ከተማ አስተዳደር ቤት ሰሪዎች ከተላለፈ ወዲህ ማሳቸው ላልተፈለገ የእንስሳት እና የሰዎች ንክኪ በመጋለጡ ከማሳቸው ማግኘት የነበረባቸውን ምርት እንዳያገኙ እንቅፋት መፈጠሩን አመላክተዋል።
“መሬታችንን ተጠቅመን ልጆቻችንን ማሳደግ ሲገባን እና የሞጣ ከተማ አስተዳደርም በመሬታችን መጠቀም ያለብንን ያህል እየተጠቀምን እንዳልሆነ ተገንዝቦ ለመሬታችን ካሳ መስጠት ይገባው ነበር ” የሚሉት አቶ አንየው ፤ ምንም እንኳን የአርሶአደሮችን መሬት የከተማ አስተዳደሩ ቢከልለውም አልፎ አልፎ የተተወ መሬት ለወደፊት ለአረጓዴ ስፍራ ታስቦ ስለሆነ እና አሁን ላይ የከተማ አስተዳደሩ መሬቱን እስካልፈለገው ድረስ ካሳ የመስጠት ግዴታ የለበትም የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው አቶ እንየው ይናገራሉ።
በመሆኑም ይላሉ አቶ እንየው፤ እኔ እና እኔን መሰል አርሶ አደሮችም የምናደርገው መላ ስለጠፋን ዝም ብለን ከተማ ውስጥ ያለን ማሳን ለመዝራት ተገደናል። መንደር መካከል እህል ተዘርቶ ለታሰበለት አላማ ሊውል እንደማይችል ህፃንም የሚገነዘበው ነገር እንደሆነ ይናገራሉ ። እንደ አቶ እንየው ገለፃ የእንስሳት እና የሰዎች ቁጥር ከፍተኛ በሆነበት ከተማ ነው አርሳችሁ ብሉ እየተባለን ያለነው።የአዲስ ቤት ሰሪዎች ከብቶች ይመጡና በእኛ ማሳ ላይ የሚረማመዱት።ቆሻሻ የሚጣለው እንዲሁ እኛ ማሳ ላይ ነው።መንገዱም በእኛ ማሳ ላይ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ማሳው እንዳይሆን የሆነበት አርሶአደር ከጋራ የገዘፈውን ችግር እንዲጋፈጥ እየተደረገ ይገኛል።በዚህም አዲስ ቤት ከሰሩ ሰዎች ጋር ወደ አላስፋላጊ ግጭት እየገቡ መሆናቸውን እና ግጭቱም ሰዎችን እስከሞትም ማድረሱን አቶ እንየው ይናገራሉ።
“እኔ አርሶ አደር ነኝ፤ ብዙ ወጭ ያወጣሁበት እና ያለ የሌለ ማሳየ በሰው ሲረገጥ በእንስሳት ሲበላ እና የሰዎች ቆሻሻ መጣያ ሲሆን ማየቱ ያማል፡፡ ” የሚሉት አቶ እንየው፤ ስለሆነም ከሁለት እጁ እነሴ መሬታቸውን የተረከበው የከተማ አስተዳደር መሬታቸውን በባለቤትነት ከሁለት እጁ እንደተረከበ ሁሉ ተጨማሪ የሰው ህይወት እና ግጭት ሳይፈጠር ለመሬታቸው ካሳ ወይም ምትክ ሊሰጥ ይገባዋል ሲሉ አመላክተዋል።
የሞጣ ከተማ ህዝብ፣ ከብት እና በግ በማሳው ላይ በሚያሳድረውን ጫና ምንም አይነት ምርት ማምረት እንደማይቻል የከተማ አስተዳሩ እየተመለከተ ምንም ምላሽ ሊሰጠን አልቻለም ሲሉ አርሶ አደሩ ገልፀዋል።“በዚህም ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ የምናደርገው ጠፍቶብን እና ለማን አቤት እደምንል ግራ ተጋብተን በርሃብ አለጋ እየተገረፍን ለከፋ ችግር ተጋልጠን እንዲሁ ተቀምጠናል ፡፡” ሲሉ አቶ እንየው ተናግረዋል።
በዚህም በደል የደረሰባቸው አርሶአደሮች እንደሌሎች አርሶ አደሮች ካሳ ይክፈለን ወይም ትክ ይሰጠን ቢሉም አንድም ሰው መልስ ሊሰጥ የፈለገ አካል አለመኖሩን አቶ እንየው ይገልፃሉ።ስለሆነም በፊት መሬቱን ያስተዳድር ወደነበረው ሁለት እጁ እኔሴ ወረዳ በመሄድ መፍትሄ ቢጠይቁም ካሁን በኋላ መሬቱ በከተማ አስተዳደሩ ይዞታ ውስጥ ስለተካተተ ሁለት እጁ እነሴ ወረዳ የማይመለከተው መሆኑን እንደተነገራቸው ያስረዳሉ።
እንደ አቶ እንየው ገለፃ፤ እኛ አብዛኛዎቹ በደል የደረሰብን አርሶ አደሮች ያልተማርን በመሆናችን ማን እንኳን እንደሚጠየቅ በደንብ አናውቅም።አንዳንድ ፊደል የቆጠሩ አርሶ አደሮች ጋር አብረው ተሰብስበው ጥያቄውን ይዘው ወደ ሚመለከተው አካል ቢሄዱም ምላሽ ሊሰጣቸው ፈቃደኛ የሆነ አካል አለመኖሩን ይናገራሉ። ከዛሬ ነገ አንድ መፍትሄ ይመጣል የሚል ተስፋ ይዘው ቢጠብቁም እስከዛሬ ድረስ ማንም ይሄነው የሚል ምላሽ ሊሰጣቸው የቻለ አካል አለመኖሩን አመላክተዋል።
በሌላ በኩል ካሳ የማይሰጥ ከሆነ ደግሞ መሬቱን አከራይተን እንጠቀማለን ሲሉ ደግሞ አይቻልም ተብለው እንደተከለከሉ አቶ እንየው ጠቁመው፤ አርሶ አደሩ ለከፋ ችግር ተጋልጦ ስለሚገኝ የከተማ አስተዳሩ ወይም የሚመለከተው ማንኛውም አካል ያለንበት ሁኔታ አይቶ ይፍረደን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። እንደ አቶ እንየው ገለፃ ከካሳ ጋር ተያይዞ ቅሬታ ያለባቸው ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ አርሶአደሮች በተገናኙበት ቅጽበት ሁሉ የሚወያዩት በዚህ ጉዳይ ላይ ነው።አንዳንድ ጊዜ ለተበደለው አርሶ አደር ምላሽ የሚሰጥ አካል ሲጠፋ ሳይ በመንግሥት ላይ አርሶ አደሩ እንዲያምጽ እየተገፋ እንዳለ ይሰማኛል።
እንደ አቶ እንየው ገለፃ፤ በሩቅ አገር እንደምንሰማው አርሶ አደሮች ተፈናቀሉ፣ ሞቱ፣ ንብረታቸው ወደመ ወዘተ ይባላል። እነዚህ አርሶ አደሮች በአንድ ቁርጡ ተፈናቃይ ተብለው በረድኤት ድጅቶች ይረዳሉ።“እኛ ግን የሚፈፀምብን ግፍ ማንም ሳያይልን እንዲሁ ተደብቆ ለከፋ ርሀብ ተጋልጠን ሞትን እየተጠባበቅን እንገኛለን፡፡” ሌላኛዋ ቅሬታ አቅራቢ ወይዘሮ ያሳብ ብዙነህ ይባላሉ። በሁለት እጁ እነሴ ወረዳ አየን ብርሃን ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ አምስት ልጆቻቸውን ያስተዳድራሉ። ወይዘሮ ያሳብ እንደ አቶ እንየው ጌትነት ሁሉ የከተማ አስተዳደሩ በማህበር ለተደራጁ ቤት ፈላጊዎች መሬት መስጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ መሬታቸው ከሁለት እጁ እነሴ ወረዳ ተወስዶ በሞጣ ከተማ አስተዳደር ውስጥ መካተቱን ይናገራሉ።ይሁን እንጂ ለመሬታቸው ከተማ አስተዳደሩ ምንም አይነት ካሳ ሳይሰጣቸው ባልታወቀ ምክንያት ማሳቸው ተለይቶ ማህል ተለይቶ ጦም ማደሩን ይናገራሉ።በዚህም ክፍኛ እንደተጎዱ ይናገራሉ።
እንደ ወይዘሮ ያሳብ ገለፃ፤ ከ2009 ዓ.ም በፊት ያለችኝ መሬት ሁለት ገመድ ወይም ግማሽ ሄክታር ብቻ ነው።በዚች ሁለት ገመድ መሬት አምስት ልጆችንም ያስተዳድሩ ነበር።ይሁን እንጂ ከ2009 ዓ.ም በፊት ከነበራቸው መሬት ግማሽ ያህሉ የከተማ ክልል ውስጥ በመካተቱ ከዚህ በፊት ያመርቱ የነበረውን ያህል ምርት ማምርት አልቻሉም።አዲስ ሰፈራ መንደር መሃል የቀረው መሬታቸው ወደ ከተማ አስተዳደሩ ከመከለሉ በፊት በበጋ ብቻ እስከ ሰላሳ ኩንታል ጓያ ያመርቱበት ነበር።አሁን ግን ቦታው ወደ ከተማ አስተዳደሩ መካለሉ ጋር ተያይዞ በዙሪያው ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ሰዎች በቦታው አዲስ ሰፈር ከመፍጠራቸው ጋር ተያይዞ አዲስ የሰፈሩት ሰዎች ከብቶች ደግሞ ማሳቸውን ስለሚበሉባቸው እና ስለሚረገጡባው ፣ ነዋሪዎችም ማሳቸው ላይ ቆሻሻ ስለሚደፉበት፣ ነዋሪዎችም መንገድም ስሌላቸው በማሳቸው ላይ እንደመንገድ ስለሚጠቀሙበት ማግኜት የነበረባቸውን ምርት ማግኘት አልቻሉም።
በመሆኑም ከ2009 ዓ.ም እና ከዚያ በፊት ከሰላሰ ማደባሪ በላይ ያገኙ የነበረው የጓያ ምርት አምና ወደ ስድስት ማደበሪያ ዝቅ አለ የሚሉት ወይዘሮ ያሳብ፤ ዘንድሮ ደግሞ ቤት እየሰራ የገባው ሰው እየበዛ በመምጣቱ ጭራሽ የዘሩት እህል በሜዳ ለከብቶች እና ለበጎች ሲሳይ ሆኖ መቅረቱን ይገልፃሉ።ለዘር እናጉልበት ስንት ያወጡበት መሬት እንዳይሆን ሆኖ እንደተበላሸባቸው በቁጨት ይናገራሉ። እንደ ወይዘሮ ያሳብ ገለፃ፤ በነዋሪዎች ተከቦ ከጥቅም ውጭ በሆነው መሬታቸው ዙሪያ ወራጅ ወንዝ በመኖሩ በበጋ ወራት በመስኖ ተጠቅመው ሽንኩትርት፣ ድንች፣ ወዘተ በማምረት ራሳቸውን ከመደጎም ባለፈን ለገበያም ያቅርቡ ነበር። በዓመት ሁለት ጊዜ ያመርቱበት ስለነበር ልጆቻቸውንም በጥሩ ደረጃ ያስተምሩ እንደነበር ይናጋራሉ።
አሁን ላይ ግን ከተፈጠረው አዲስ ሰፋራ ጋር ተያይዞ ብዙ የገንዘብ እና የጉልበት አፍሰው ቢያርሱም በተደጋጋሚ ለኪሳራ በመጋለጣቸው ምክንያት አሁን ተስፋ በመቁረጥ ስንት ጥቅም ያገኙበት የነበረው እና ልጆቻቸውን ከሌሎች ሰዎች ልጆች ጋር እኩል እንዲሆኑ ያስችላቸው የነበረው መሬት ፆም እንዲያደር መገደዳቸውን አመልክተዋል። መንግሥት ከሚሰጣቸው ካሳ በበለጠ መሬታቸው ደህንቱ የተጠበቀ ቢሆን የሚሰጣቸው ጥቅም እንደሚበልጥ የሚናገሩት ወይዘሮ ያሳብ፤ በዓመት ሁለት ጊዜ ይመረትበት ለበረ ማሳ በመቶ ሃምሳ ካሬ ሜትር 16 ሺህ ብር ካሳ ቢያገኙ ምንም እንደማፈይድላቸው ይናገራሉ።ይሁን እንጂ ይላሉ ወይዘሮ ያሳብ “እኔ ከመንግሥት ውጭ የምሆንበት ምንም መብት ስለሌለኝ እና እንዲሁ ማሳው ያለምንም ነገር ከሚቀር ትንሽም ቢሆን የካሳ ክፍያው እንዲሰጠኝ እፈልጋለሁ፡፡”
እንደ ወይዘሮ ያሳብ ገለፃ፤ አሁን ላይ ይህ የልጆቻቸውን ጉሮሮ በሰዓቱ ምላሽ የሚሰጠው መሬት ፍሬ አልባ እንደመሆኑ ሴት ልጃቸው ዱባይ አገር ሂዳ አፋቸው ላይ ባትጥልላቸው ኖሮ ምን እንደሚሆኑ ሲያስቡት እጅጉን ይጨነቃሉ።አሁን ላይ ከመሬታቸው የሚያገኙት ጥቅም ሲቆምባቸው ለቤታቸው መሟላት ያለበትን ሁሉን ነገር እያደረገች ያለችው ልጃቸው ናት።ነገር ግን እስከመቼ እርሳቸውን እና ህፃናት ልጆቻቸውን እየረዳች ትቆያለች ሚለውን ሲያስቡ ጭንቀታቸው ከመቼውም ጊዜ በላይ አይሏል።ስለሆነም መንግሥት እኔ እና መስል አርሶ አደሮች የገባንበትን ችግር ተመልከቶ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጠን ሲሉ ጠይቀዋል።
የሞጣ ከተማ አስተዳደር የከተማ ልማት ቤቶች ኮንስትራክሽን አገልግሎት ጽህፈት ቤት ምላሽ የሞጣ ከተማ አስተዳደር የከተማ ልማት ቤቶች ኮንስትራክሽን አገልግሎት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፀሐዬ ወንድም እንደሚሉት፤ ከ2007 ዓ.ም በፊት በሞጣ ከተማ አስተዳደር ዙሪያ የሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች በሞጣ ከተማ አስተዳደር ሥር ይተዳደሩ ነበር።ነገር ግን ውሉ በውል በማይታወቅ ምክንያት ከ 2007 ዓ.ም በኋላ በሞጣ ከተማ ዙሪያ የነበሩ አራቱ የገጠር ቀበሌዎች ለሁለት እጁ እነሴ ወረዳ በመሰጠታቸው ምክንያት የከተማ አስተዳደሩ ሥር ግብርና ጽህፈት ቤቱ የከተማ ግብርና እንዲሰራ የሥራ ሂደት የተቋቋመ ቢሆንም በሁለት እጁ እነሴ ወረዳ እና በሞጣ ከተማ አስተዳደር መካከል ርክክብ ባለመደረጉ እና እስካሁን ወደ ሥራ ባለመግባቱ በአካባቢው የሚነሱ የተለያዩ ጥያቄዎችን መመለስ አልተቻለም።በዚህም አርሶ አደሩ በካሳ ግምት ምክንያት ከሁለት እጁ ወደ ሞጣ ከተማ አስተዳደር፤ ከሞጣ ከተማ አስተዳደር በመመላለስ ለከፍተኛ ችግር ዳርጓቸዋል።ይህ ከፍተኛ የሆነ የመልካም አስተዳደር ችግር ነው።ስለሆነም ለችግሩ መንግሥት በአፋጣኝ መፍትሄ መስጠት አለበት ብዬ አምናለሁ።
ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ በሞጣ ከተማ አስተዳደር የሚኖሩ በርካታ ዜጎች የቤት ባለቤት መሆን ችለዋል የሚሉት ሃላፊው፤ ለአራት ጊዜ በተከታታይ ቤት ለሚያስፈልጋቸው በማህበር ለተደራጁ ዜጎች ቦታን በመምራት የሞጣ ከተማ አስተዳደርን ያህል የሰራ ወረዳ የለም የሚል ሙሉ እምነት እንዳላቸው ይገልፃሉ። ቦታን ከአርሶ አደሩ በካሳ ተረክቦ ለማህበራት ማስተላለፍ እንዲህ በቀላሉ የሚሰራ ሥራ አይደለም የሚሉት ሃላፊው፤ በአርሶ አደሮች እየተነሱ ያሉት የመልካም አስተዳደር ችግሮችም ከዚህ የመነጩ መሆናቸውን ገልፀዋል።
እንደ ኃላፊው ገለፃ፤ በአንድ ወገን በማህበር ተደራጅቶ ቦታ የሚፈልግ አካል አለ።በሌላ ወገን ደግሞ የአርሶ አደሩ የካሳ ጥያቄ አለ።ስለዚህ የሁለቱን ፍላጎት አጣጥሞ መሄድን ይጠይቃል።በ2006 ዓ.ም በማህበር ለተራጁ የከተማዋ ነዋሪዎች ከተማ አስተዳደሩ ቦታ መርቷል።በ2008 ዓ.ም 2009 ዓ.ም እና በ2012 ዓ.ም ላይ እንዲሁ ከተማ አስተዳደሩ ቦታ መርቷል።በመሆኑም በሞጣ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ ቤት ፈላጊዎችን የቤት ባለቤት ማደርግ ተችሏል።
ሆኖም ለአርሶ አደሩ ካሳ የሚከፈለው ከቦታ ተመሪው ገንዘብ ተሰብስቦ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፤ ተመሪዎች ለአርሶ አደሩ ካሳ ከመክፈል ባለፈ ለቤት መስሪያ ቦታ ከተመሩበት አካባቢ ለሚሰሩ መንገዶች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችም ጭምር ነው።ነገር ግን በፕላን ምደባው ኮሜርሻል ለሆነ እና ማህል ቦታ ላይ ለሚገኝ ክፍት ቦታ ተመሪው ገንዘብ እንደማይከፍል ገልፀው ለዚህም በዋናነት የሚነሳው ምክንያት ተመሪው ደግሞ የካሳ ዋጋ በዛብን ስለሚል ጥያቄ ስለሚያነሳ መሆኑን አመላክተዋል። እንደ ኃላፊው ገለፃ፤ አንድ ቦታ የተመራ ሰው ለአንድ መቶ ሃምሳ ካሬ ሜትር 50 ሺህ ሰባት መቶ ብር ለአርሶ አደር ካሳ ይከፍላል።ከተመሪው ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያለ ከመሆኑ አንፃር ይህ በጣም ትልቅ ገንዘብ ነው።
ተመሪው የመክፈል አቅሙ ዝቅተኛ መሆኑ የሚታወቅ በመሆኑ በሊዝ መጫረት የማይችል መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ ባለፉት ምራታዎች ተደራሽ ያደረገው ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለውን የማህበረሰብ ክፍል ነው ።ይህ በመሆኑ ሁለቱ ፍላጎቶች ማለትም የተመሪው እና የካሳ ፈላጊው አርሶ አደር ፍላጎቶች ሊጣጣሙ አለማቻላቸውን አመላክተዋል።ስለሆነም በፕላን ምደባው መሰረት ቁርጥራጭ ቦታዎችን ተመሪዎች ከፍለው ለመውሰድ ፈቀደኛ አይሆኑም።መንግሥት ደግሞ የዚያን ሁሉ አርሶ አደር ካሳ የመክፈል አቅም አይኖረውም ሲሉ ኃላፊው ጠቁመዋል። በመሆኑም ይላሉ ኃላፊው፤ የአረሶ አደሮችን ጥያቄ ለመመለስ ችግር መፈጠሩን ገልፀዋል።
እንደ ኃላፊ ገለፃ፤ የአርሶ አደሮች ጥያቄ በጣም ትክክል ነው።ቁርጥራጭ መሬቶች ተመሪው ካሳ ከፍሎ ስለማይወስዳቸው ለተመራበት እና በፕላን ምደባው ውስጥ ላለው ብቻ ስለሚወስድ የአርሶ አደሩ ቁርጥራጭ መሬቶች ጥቅም ላይ እየዋሉ አይደለም። ስለሆነም የአርሶ አደሮች ቅሬታ ተገቢነት ያለው እና ትክክለኛ ነው። ስለዚህ አሁን መደረግ ያለበት ከተማ አስተዳደሩ በቀጣይ በጀት እየያዘ እነዚህን በሰፈራ መንደሮች መሀል መሀል ላይ የሚገኙ ቁርጥራጭ መሬቶች ካሳ እየከፈለ በፕላን ምደባው መሰረት ለአገልግሎት እንዲውሉ ማድረግ ነው። ዘንድሮ ለመንገድ ከፈታና ተዛመጅ ችግሮች ለመፍታ አምስት ሚሊዮን ብር ካሳ ይዘናል።የካሳ ግምትም አሰርተናል።የከንቲባ አመራሩ እስከዚህ ድረስ እየሰራ ነው።
እንደ ኃላፊው ገለፃ፤ በተለያየ ምክንያት በፕላን ምደባው መሰረት የከተማ አስተዳደሩ እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ በዓመት እስከ 10 ሚሊዮን ብር የካሳ በጀት ይያዛል፣ ይህንንም የካሳ ክፍያ እየከፈለ ይገኛል።ይህ ግን በጣም ትንሽ ነው። ሌላው የአርሶ አደሮች ችግር ሳፈይታ ለብዙ ጊዜ እየተንከባለለ እንዲቆይ ያደረገው ዋናው ምክንያት በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ የአመራሮች በተደጋጋሚ መቀያየር ጋር ተያይዞ በሚፈጠር መሰናክል መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ እርሳቸው በነበሩበት መስሪያ ቤት በአንድ ዓመት ብቻ ከአራት በላይ ሥራ አስኪያጆች መቀያየራቸውን ጠቁመዋል።ኃላፊው አሁን ባሉበት መስሪያ ቤት በአለፈው ዓመት ብቻ ከእርሳቸው ውጭ ሁለት ኃላፊዎች መቀየራቸውን እና እርሳቸው ደግሞ ለሦስተኛ ጊዜ መመደባቸውን ገልፀዋል።
እንደ ኃላፊው ገለፃ፤ አመራሩ አንድ የሥራ ቦታ ላይ ተረጋግቶ መሥራት ባለመቻሉ አንዱ አመራር በደንብ ሥራውን መገንዘብ ሲጀምር እና በደንብ ኃላፊነቱን መወጣት ሲጀምር በሆነ ምክንያት ትቶት ይሄዳል። ስለዚህ ባለፈው ዓመት ቦታ ሲታደል ወይም ሲመራ እስከየት ነበር ለአርሶደሩ ካሳ የተከፈለው? የትኛው አርሶ አደር ነው ያልተከፈለው ? የሚለው በትክክል እየታወቀ አይደለም።ስለዚህ የአርሶ አደሩን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ ስለእያንዳንዱ ነገር ማወቅ እና ውሳኔ መስጠትን ይጠይቃል።በመሆኑም ኃላፊው ወደ ቦታው ከመጡ ጊዜ ጀምሮ እያደረጉት ያለው ምንድን ነው በሞጣ ከተማ አስተዳደር የከተማ ልማት ቤቶች ኮንስትራክሽን አገልግሎት ጽህፈት ቤት በምክትል ኃላፊ የሚመራ ከእያንዳንዱ የሥራ ቡድን ብዙ ጊዜ የሰሩ እና መሬትን ለተመሪው ያከፋፈሉ የነበሩ ባለሞያዎችን ያጣመረ ኮሚቴ ተቋቁሞ የትኛው አርሶ አደር ነው ካሳ የተከፈለው ? የትኛው ነው ያልተከፈለው ? እሱን የመለየት ሥራ እና እዚያው አካባቢው ከተመሪው ጋር የቦታ እርክክብ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።
አንዳንድ ጊዜም አርሶአደሩ ካሳ በተከፈለው ቦታ ላይ የሚያርስ እና የተለያዩ ዛፎችን የሚተክሉም አሉ የሚሉት ኃላፊው፤ እነዚህን እና መሰል ችግሮች ለመቅረፍ ያልተቻለው ከዚህ በፊት የተሄዱባቸው የመፍትሄ አቅጣጫዎች ህብረተሰቡን የአሳተፈ አለመሆናቸውን ነው። በቀጣይም ችግሮችን በአጭር ጊዜ ለመፍታት ህብረተሰቡን በባለቤትነት በማሳተፍ እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል።
እንደ ኃላፊው ገለፃ፤ ከግንቦት አንድ 2013 ዓ.ም ጀምሮ ሁሉን ያጣመረው ኮሚቴ እየተዘበራረቀ ያለውን ችግር በማጥራት የመሬት ርክክብ የሚያደርጉ ይሆናል።ለዚህም ዝግጅታችን ጨርሰናል።በዚህም የአርሶአደሮችን ጥያቄ ሙሉ በሙሉ በዚህ ዓመት እንፈታዋለን ባንልም አርሶ አደሩ ተገቢውን ካሳ እንዲያገኝ ተመሪውም በከፈለበት ልክ አገልግሎት እንዲያገኝ በማድረግ ተገቢውን ምላሽ ለመመለስ ያስችላል።
የሞጣ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ምላሽ
የሞጣ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ የሺዋስ አንዱአለም በበኩላቸው በከተማዋ ከንቲቫ ሆነው የተሸሙት ከአንድ ዓመት እንደማይበልጣቸው ገልፀው፤ የቦታን ምራታን በተመለከተ በተለይ የህብረተሰባችን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ከመመለስ አኳያ እርሳቸው ወዲያውኑ አመራር ሆነው እንደመጡ በከተማ አስተዳደሩ ካሉት አመራሮች ጋር በመሆን የህብረተሰባችን ችግር ምንድን ነው? የሚለውን ቅድሚያ አጀንዳ ወስደው ሲመለከቱ የመኖሪያ ቤት ጥያቄ የመጀመሪያው እና አንገብጋቢው ጥያቄ በመሆኑ ለባለፉት ሁለት ዓመታት ማለትም ከ2010/11 ዓ.ም ጀምሮ እርሳቸው ወደስልጣን ከመምጣቸው በፊት ለአሉት ለሦስት እና ለአራት ዓመታት ያህል ተደራጅተው የቆጠቡ 51 ሺህ ብር ከፍለው ይጠባበቁ የነበሩ በርካታ ዜጎች ነበሩ።
የእነዚህን ዜጎች የቤት ጥያቄ ለመፍታት የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ተወያይተው ወደ ሥራ መግባታቸውን የተቆሙት ከንቲባው፤ አዲሱ የወረዳው አመራር በመጣ አንድ ዓመት በኋላ ለአንድ መቶ 49 ማህበራት ከአራት ሺህ በላይ ተመሪዎችን የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ማድረግ መቻላቸውን ይናገራሉ። ይህንን ሲያደርጉ በከተማ አስተዳደሩ የራሱ ፕላን እና ክልል ወሰን መሰረት መሆኑን ይናገራሉ።
በዚህ ፕላን እና ወሰን መሰረት ያሉትን የከተማ በቦታዎች ምን ይመስላሉ ? የሚለው ከከተማ አገልግሎት ጋር በመነጋገር አንድ መቶ 35 ቦታዎች ማግኘታቸውን ሚናገሩት ከንቲባው፤ ሌሎች ቦታዎችን ደግሞ ከሁለት እጁ እነሴ ወረዳ ካቢኔ ጋር በመነጋገር ለከተማ አስተዳደሩ ቦታ እንዲሰጡን በማድረግ እንደ ከተማ አስተዳደር የክልል ሕግ እና መመሪያ ተከትለን ለአርሶ አደሮች ካሳ እንዲከፈል በማድረግ የቦታ ምራታውን ማከናወናቸውን ገልፀዋል።
እንደ ከንቲባው ገለፃ የቦታ ምራታውን ሲሰጡ አንደኛ ለአርሶ አደሩ በአዲሱ የካሳ መመሪያ መሰረት የካሳ ክፍያ እንዲከፈል በማድረግ፤ ሁለተኛ አርሶ አደሩ ራሱ በከተማው ክልል እስካለ ድረስ በፕላኑ መሰረት ቅድሚያ ለራሱ 5 መቶ ካሬ ሜትር እንዲሰጠው እና እድሜው 18 እና ከዚያ በላይ የሆነ ልጆች ደግሞ ካሉት በመመሪያው መሰረት የልጆችም መብት እንዲከበር የማድረግ ሥራ በሰፊው ተሰርቷል።ስለሆነም በከተማ አስተዳደሩ የሚኖሩ ዜጎችንም የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ለመፍታት በተደረጉ እንቅስቃሴዎች የአርሶ አደሩን መብት እና ጥቅም በማይፃረር እና በማይጎዳ መልኩ በመነጋገር እና መመሪያው በፈቀደ መልኩ ተከናውኗል። የካሳ ጋር በተያያዘ የነበረው መመሪያ ከ10 ዓመት ወደ 15 ዓመት ሆኖ አድጎ መጥቷል።ስለሆነም የክልሉ መንግሥት በዘንደሮው ዓመት እንደአዲስ በላከው መመሪያ መሰረት የአምስት ዓመት ካሳን ጨምሮ ለመክፈል ታቅዶ እየተሰራ ነው።
ስለዚህ አሁን ላይ እንደ ሞጣ ለተማ አስተዳደር ቦታ ሲመራ ወጥ እንዲሆን ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን የሚገልጹት ከንቲባው፤ ወጥ ለማድረግም በየጊዜው የሄዱበትን አቅጣጫ በመገምገም ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል ደካማ ጎኖችን ደግሞ በመለየት ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ያለውን ጥረት የሚበረታታ መሆኑን አመላክተዋል።
“እኔ ከንቲባ ከመሆኔ በፊት ባልነበርኩበት ዘመን ያለውን አላውቅም።ነገር ግን እኔ ከመጣሁ በኋላ በ2012 ዓ.ም የመራናቸውን ቦታዎች ብቻ የማውቀው ” የሚሉት ከንቲባው ፤ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ አርሶ አደሮች እንዳሉት አልፎ አልፎ ቤቶችን በመምራት በአርሶደሮች ላይ ችግር መፈጠሩን እንደማያውቁ ጠቁመዋል። “በባለፈው ዓመት እኛ ቦታውን ስንመራ ያደረግነው ሁሉንም ቦታዎች መደዳውን እኩል እንዲሆን፤ የሚዘለል ቦታ እናዳይኖር ትንንሽ ቁርጥራጭ የአርሶ አደር መሬቶች እንኳን ካሉ እንዳይባክኑበት ካሳ ጭምር እንዲሰጣቸው እና በከተማ መስተዳደሩ ተከብረው እንዲቆዩ ነው አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ ያለው፡፡” የሚሉት ከንቲባው በዚህ አቅጣጫ መሰረት አንደኛ ካሳቸውን እንዲንሰጣቸው ነገር ግን ካሳቸውን ስንሰጣቸው ለምንም ጥቅም የማይውል ቁርጥራጭ መሬቶች ካሉ አርሶ አደሩን እንዳይጎዳ እነዚህን ቁርጥራጭ መሬቶች ወደ ከተማ አስተዳደሩ ተካልለው ካሳ ተከፍሎባቸው እና ተከብረው እንዲቆዩ እና መንግሥት ለልማት ሲፈልጋቸው ጥቅም ላይ እንዲውሉ እንደከተማ አስተዳደር አጽኖት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ከንቲባው ገለፃ፤ ከ2007 ዓ.ም በፊት በሞጣ ከተማ አስተዳደር ዙሪያ የነበሩ አራት ቀበሌዎች በከተማ አስተዳደሩ ሥር የነበሩ ሲሆን አሁን ላይ ግን እነዚህ አራት የገጠር ቀበሌዎች በሙሉ ወደ ሁለት እጁ እነሴ ተካተዋል። በመሆኑም የከተማ አስተዳደሩ የምራታ ቦታ ሲፈልግ ከገጠሩ ቦታ ለማግኘት የሁለት እጁ እነሴ ወረዳ መሬት አጠቃቀም እና አስተዳደር ጋር በመነጋገር ለዜጎች የመኖሪያ ቤት እየሰጠ ይገኛል።በእነዚህ የማህበር ቤቶች አካባቢ ደግሞ ስታንዳርዱን ጠብቀው መንገዶች ይወጡለታል። በዚሁ አካባቢ ከመንገዶች በተጨማሪ ግሪን ኤሪያዎች ተከብረው እንዲያዙ እና በፕላኑ መሰረት ሥራዎች እንዲሰሩ ለከተማው ገቢዎች ሃላፊነት በመስጠት ቴክንካል የሆነውን ሙያውን ደግሞ የከተማ አገልግሎት እየመራ ይገኛል።
ከቦታ ምሪት ሂደቱ ጋር ተያይዞ በዚህ ልክ ነው እኔ የማውቀው የሚሉት ከንቲባው፤ ምናልባት ቁርጥራጭ መሬት እያለን ካሳ አልተከፈለንም ብለው ከንቲባው ላይ የመጡ አርሶ አደሮች አለመኖራቸውን ጠቁመው፤ ከንቲባ ጽህፈት የሚመጡ ካሉ ግን እንደ ከተማ አስተዳደር ወዲያውኑ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን አመላክተዋል። ይሁን እንጂ ከተማ አስተዳደሩ ካሳ ያልተከፈላቸውን በመለየት እና ካሳ እንዳልተከፈላቸው በማረጋገጥ ካሳ እየከፈሉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።አሁን ላይ ቅሬታ ያቀረቡት አርሶ አደሮች መሬታችን ከቤቶች መካከል ላይ በመገኘቱ ለእርሻ ጥቅም እየዋልነው አይደለም የሚሉ ካሉ ማስረጃቸውን በመያዝ ለከንቲባ ቢሮው ያመለክቱ።የከተማ አስተዳደሩም አስፈላጊውን ካሳ ሊከፍላቸው ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2013