በድሬዳዋ ከተማ በርካታ አዛውንቶች ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው በተለያዩ ችግሮች ውስጥ እየኖሩ ይገኛሉ። አንዳንዶቹ እቤታቸው ውስጥ የሚኖሩ ቢሆንም የገቢ ምንጭ ስለሌላቸው የሚንከባከባቸው የቅርብ ሰው ባለመኖሩና ጥቂቶቹም የበሰለ ምግብ እንኳን ለማቅረብ የሚያስችል አቅም ስለሌላቸው በችግር ውስጥ ይገኛሉ። ቀሪዎቹ ደግሞ ይበሉት ብቻ ሳይሆን አረፍ የሚሉበት የራሳቸው ጎጆ የሌላቸው በመሆኑ ከረሀባቸው ጋር በየጎዳናው ሲሰቃዩ ይኖራሉ። አዲሱ የዳዊት የአዛውንቶች ቤት ደግሞ ከእነዚህ ጥቂቶቹን በዘላቂነት ለመታደግ የተጀመረና ወደሥራ በመግባት ላይ ያለ ሀገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው።
ዳዊት የአረጋውያን በጎ አድራጎት ማህበር ከአስራ ስድስት ዓመት በፊት በወጣት ዳዊት በቀለ መስራችነት የተቋቋመ ነው። ማህበሩ ለአረጋውያን የዕለት ጉርስ ከማድረስ ባለፈ ዛሬ በአምስት ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ሕንፃ አስፍሮ አረጋውያንን ለመንከባከብ እስከ መድረስ በቅቷል። ይህን ረጅም ዓመት የወሰደ አድካሚ ነገር ግን ውጤታማ ጉዞ ሕዝብን በማስተባበር የጀመረውና ለዛሬ እንዲበቃ ያደረገው ደግሞ የዛሬው የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ ወጣት ዳዊት በቀለ ነው። ዳዊት ውልደቱም እድገቱም በዚያው በድሬዳዋ ከተማ ሲሆን አባቱ የቀድሞ ሰራዊት አባልም ነው። ዳዊት አብዛኛውን ጊዜ ያሳለፈው ከእናቱ ጋር ሲሆን እዚህ ለመድረሱም ሆነ ለበጎ አደራጎት ሥራው መሠረት የእናቱና የታላቅ ወንድሙ አስተዋጽኦ እንዳረፈበት ይናገራል።
ገና በልጅነቱ ነበር ዳዊት በድሬዳዋ ሆህተ ብርሀን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን በሚያገለግልበት ወቅት ነበር የበጎ አድራጎት ሥራውን ሀ ብሎ የጀመረው። በወቅቱ በቤተክርስቲያኒቷ ስር ያገለግሉ በነበሩ ወጣቶች የተቋቋመ የነዳያን ጉባኤ ማህበር አባል ነበር። የማህበሩ አባላትም ወር በገባ በሃያ አንድ ገንዘብና ቁሳቁስ እየሰበሰቡ ነዳያንን ይመግቡ ነበር። ዳዊት ደግሞ በሌላ በኩል ከዚህ በተጨማሪ ከማዘር ትሬዛ የበጎ አድራጎት ድርጅትና ቀይ መስቀል ጋር በመሆን ዘጠነኛ ክፍል ከነበረበት ጊዜ አንስቶ በሌሎች የበጎ አድራጎት ሥራዎች ይሳተፍ ነበር። ዳዊት ዓለማያ ዩኒቨርሲቲ በመግባት ትምህርቱን የጀመረ ቢሆንም ሁኔታዎች ሳይመቻቹለት ቀርተው አቋርጦ በግል ኮሌጅ በአካውንቲንግና ፋይናንስ በዲፕሎማና በዲግሪ ለመመረቅም በቅቷል።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ እሱ ይኖርበት አካባቢ የነበሩ አንዲት እናት ነበሩ እኛ ባልቴት ሰባት ልጆች የነበሯቸው ቢሆንም ሁሉም አልቀውባቸው ነበር። እናም እሳቸውን ሊጠይቅ ወደ ማዘር ትሬዛ በሄደበት ወቅት ሽሮ አማረኝ ይሉታል እኒህ እናት እውነት የሚበሉት አጥተው ሳይሆን ቤተሰብ ቤተሰብ የሚል ነገር በመፈለጋቸው ነበር። ዳዊት የተጠየቀውን አዘጋጅቶ ይዞ ሲሄድ ውስጥ የነበሩት ይለምኑት ሁሉም ይጀምራሉ። ይህንን ገጠመኙን ይዞ ወደ መጀመሪያው ማህበሩ በመሄድ ለጓደኞቹ ያሳውቃል የማህበሩ አባላትም አንድ ሺ ብር አዋጥተው ይሰጡታል። እናም ያንን ይዞ ወደ ማዘር ትሬዛ በመሄድ የቀሩትን አረጋውያን ለመመገበ ጥያቄ ያቀርባል። እዛም ሲደርስ ይቀበሉትና ሃሳብህ ጥሩ ነው ነገር ግን አንተ ያለህ አንድ ሺ ብር ብቻ ነው ያሉት ተጧሪዎች ደግሞ አንድ ሺህ ሁለት መቶ አረጋውያንና ህመምተኞች ናቸው ይሉታል። እሱ ግን ተስፋ ባለመቁረጥ በድጋሜ የማህበሩን አባላት አሰባስቦ ከየቤቱ በመዞር አንድ ሺህ ሁለት መቶ እንጀራ ያሰባስብና ባሰበው መሠረት አረጋውያኑን ይመግባቸዋል።
በዚያው ደግሞ ከማህበሩ አባላት ጋር ነገሩ መቀጠል እንደሚኖርበት ይስማሙና በየወሩ ማድረግ ይጀምራሉ። በዚህ ሁኔታ ለጥቂት ጊዜያት ከቆዩ በኋላ ግን እያንዳንዱ የማህበሩ አባል ቀስ በቀስ እየተበታተነ በመምጣቱ ዳዊት ብቻውን በየቤቱ እየዞረ እንጀራውና ሌላውንም ነገር ማሰባሰቡን ይያያዘዋል። ነገር ግን አቅሙ የሚፈልገውን ሊያሟላለት ባለመቻሉ ዛሬ የትሬያንግ ሆቴል ባለቤት ወደ ሆኑት አቶ ብርሃኔ ገብረሕይወት ይሄድና ያለውን ነገር በሙሉ በማስረዳት እንዲተባበሩት ይጠይቃቸዋል። አቶ ብርሃኔም ነገሩን ለማየት ይጓጉና ወደ ግቢው ያቀናሉ። ባዩት ነገርም እጅግ በማዘናቸው ከዚያን ጊዜ አንስቶ በየቀኑ ለእንጀራ ዳቦና ንፍሮ ይወጣ ከነበረው መካከል እንጀራውን በሕይወት እስካለሁ እኔ እችላለሁ ብለው ቃል ይገባሉ። ይህ የሆነው ከዛሬ አስራ ሰባት ዓመት በፊት ነበር። በዚህ መልኩ ይጀምሩና በአሁኑ ወቅትም በቀን እስከ አስር ሺህ ብር እያወጡ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ።
ዳዊት በዚህ ሁኔታ የጀመረው የድጋፍ ሥራ እየተጠናከረ ይሄድና በአንድ ወቅት ታሞ ቱቦ ውስጥ ወድቆ የነበረ ሰው ነበር። ይህንን ሰው ከወደቀበት ለማንሳት ዳዊት ብዙ ሲሰራ ይቆያል እናም በማዘር ትሬዛ ድርጅት ከመሬት እንዲነሳ ይደረጋል። በዚሁ አጋጣሚ በድርጅቱ ውስጥ ይሰሩ የነበሩ አንድ ሰው «አንተ ጎበዝ ነህ ምን አልባትም ለዚህ በጎ ተግባር የተፈጠርክ ሰው ለምን አንተ ራስህ ድርጅት አቋቁመህ አትሰራም ብለው ጥያቄ ያቀርቡለታል»። እናም እሳቸውም ድጋፍ አድርገውለት ፈቃድ እንዲያገኝ መንገዱን ያስጀምሩታል። ድርጅቱንም ለመመስረት አባላት ያስፈልጉት ስለነበር ከዚያው ከማርያም ቤተክርስቲያን ሰባት ሰዎች ተሰባስበው ሰባት መቶ አርባ ብር በማዋጣት ዳዊት የበጎ አድራጎት ድርጅትን ይመሰርቱታል። የተዋጣውም ብር ማህበሩን ለማቋቋሚያ ያውሉታል።
ይህን ያየው የከተማ መስተዳድሩም «አደይ የሴቶች ማህበር» የሚባል የሴቶች ማህበር ይገለገልበት የነበረውን ምግብ ማብሰያ ሁለት በሁለት ቤትና አንድ ቢሮ ይሰጡታል። ከማዘር ትሬዛም ሳህን ብረድስትና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ ይደረግለት በከተማዋ ያሉትን አረጋውያን በመሰብሰብ ወደ ሥራ ይገባል። በዚህ መልኩ በ1998 ዘጠኝ መቶ ሰዎችን ይዞ በያሉበት በመርዳት ሥራውን ይጀምራል። በዚህ ዓይነት የተሰራውን ሥራ ያየው የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ደግሞ የነበረበትን ሦስት መቶ ካሬ ሜትር ቦታ ይሰጠውና አረጋውያኑን በስፋት መንከባከቡን ይቀጥላል።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ አያለም በአንድ ወቅት በተቋማቸው ይገለገሉ የነበሩ አቶ ከድር ሁሴን የሚባሉ አባት ነበሩ። እኚህ አባት የአርሲ ክፍለ ሀገር ተወላጅ ቢሆኑም በአስራ ዘጠኝ ስልሳ ዘጠኝ ሶማሊያ ኢትዮጵያን በመውረሯ ይህንን ለመታደግ ለጦርነት በመጡበት እዚያው ድሬዳዋ ቀርተው ትዳር መስርተው ልጆች አፈርተው ይኖሩ ነበረ። በዕድሜያቸው መጨረሻ ግን ልጆቻቸው ስለሞቱባቸውና በቂ መተዳደሪያ ስላልነበራቸው በዳዊት አረጋውያን መንከባከቢያ እንጨት በመፍለጥና የተለያዩ የጉልበት ሥራዎችን በመስራት ቀሪ ዕድሜያቸውን ይገፉ ነበር። በወቅቱ ዳዊት አረጋውያን መንከባከቢያ ማህበር ማሳደሪያ ስላልነበረው አብዛኛዎቹ ቤት አልባ አረጋውያን ያድሩ የነበረው በያገኙበት ጥጋጥግ ነበር። እናም በአንዲት ዕድለ ቢስ ቀን አቶ ከድር በተኙበት በአራት ጅብ ተበልተው ሕይወታቸው ያልፋል።
ዳዊት ይህ አጋጣሚ በሕይወቱ እጅግ አሳዛኝ ነበር። በአንድ ወገን እኒህን አባት በቅርብ ያውቃቸው ስለነበርና አባዲና የደረሰባቸውን ነገር ስላሳየው መቼም ከውስጡ የማይወጣ ኀዘን ፈጥሮበታል። በሌላ በኩል የሌሎቹ በመቶዎች የሚቆጠሩ በእሱ ስር ያሉ አረጋውያንም መጨረሻ ይኸው ይሆናል የሚል ሀሳብ ይመጣበታል። ዳዊት ለአረጋውያን የመጀመሪያ መቆያቸው ሊሆን የሚመረጠው ቤታቸው መሆኑን ያምናል ይህ ካልተሳካ ቀጥሎ ቢቆዩ የሚመረጠው በአካባቢያቸው ከማህበረሰቡ ጋር እንደሆነም ይረዳል። ለዚህም ነበር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም በመሆን በየቤቱ ሲንከባከብ የኖረው። በአቶ ከድር ላይ የተፈጠረው ነገር ግን የመጨረሻ አማራጭ ከታጣ የጅብ እራት ከሚሆኑ መውደቂያቸው ሊሆን የሚገባው የአረጋውያን ማቆያ ማዕከል መሆኑን በመገንዘብ አንድ ማቆያ ለማቋቋም እንቅስቃሴ ይጀምራል።
በሌላ በኩል በዘጠኝ መቶ አረጋውያን የተጀመረው ድጋፍ የዛሬ አስር ዓመት አካባቢ የማዘር ትሬዛ ድጋፍ ሲቋረጥ ቁጥሩ እየቀነሰ መምጣት ጀምሮ ነበር። ከዚያ በኋላም እራስን ለመቻል ይገባል በሚል እሳቤ አባላት ማሰባሰብ ይጀምራል። ለዚህ ሂደትም በተለይ በድሬዳዋ የአቢሲንያ ባንክ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ሱልጣን የሱፍ ራሳቸው አባል ሆነው አባልም አሰባስበው ሥራ ያስጀምሩታል። በአሁኑ ወቅት ዳዊት የአረጋውያን መንከባከቢያ በድሬዳዋ በየወሩ ድጋፍ የሚያደርጉ ሁለት ሺ አምስት መቶ አባላት አሉ አጠቃላይ ከሦስት መቶ ሃምሳ በላይ ደርሰዋል። የማህበሩ የገቢ ምንጭም ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ በጎ አድራጊዎች የሚሸፈን ነው።
ሰላሳ አረጋውያን በባልትና ተደራጅተው እስከ አስራ አምስት ሺ ብር ለመቆጠብ የበቁ አሉ ዳቦ ቤት በመክፈትም አረጋውያንን ጨምሮ በርካቶችን ተጠቃሚ አድርጓል። አረጋውያን እንደ ልጅ በአንድ ሰው ብቻ እንክብካቤ ማድረግ የማይቻልባቸው ሁኔታዎች አሉ። በየቤቱ ገላ ማጠብ ቤት ማደስና ሌሎች ሥራዎችንም ይሰሩ ነበር በየቤቱ የአልጋ ቁራኛ የሆኑ ከሰላሳ በላይ አረጋውያን ከሌሎች አገልግሎቶች ባለፈ የጤና ባለሙያም ተመድቦ እንክብካቤ ይደረግላቸዋል።
ይህንን ሥራ የተመለከተው የከተማ መስተዳድሩም አብዛኛው አረጋውያን በያሉበት የሚደገፉ በመሆኑ አረጋውያንን በያሉበት ከመደገፍ ይልቅ ተሰባስበው ቢቀመጡ ይሻላል በሚለው ሀሳብ በመስማማት ድሬዳዋ ሪፈራል ሆስፒታል አጠገብ አምስት ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ለዳዊት አረጋውያን ይሰጠዋል። ቦታው ግን ብቻውን ምንም ሊሆን ስለማይችል ዳዊት ለአረጋውያኑ መኖሪያና ለሌሎች ጉዳዮች የሚሆኑ ቤቶችን ለመገንባት የሚሆን ገቢ ለማሰባሰብ መንቀሳቀስ ይጀምራል። በዚህም በድሬዳዋ የጎዳና ላይ ሩጫ ለስድስት ተከታታይ ዓመታት በዚህም በመጀመሪያው በአንድ ሺ ሁለት መቶ ተሳታፊ የተጀመረው ቀስ በቀስ ሃያ ሺ ለመድረስ በቃ። በእነዚህ ውድድሮች በቲሸርት ሽያጭና ሌሎች እንቅስቃሴዎች ገቢ ያሰባስቡ ነበር።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ አቶ ጸደቀ ይገዙ የሚባሉ ባለሀብት ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት ግቢውን ዙሪያውን አጥረው ያስረክቡታል። ሌላ ከአዲስ አበባ የሚመጡና ሥራውን የሚያውቁ አቶ ቴዎድሮስ ወልደአምላክ የሚባበሉ በጎ አደራጊ ደግሞ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ መምህርት ከሆነች ጽዮን አዱኛ ከምትባል የሕንፃ ዲዛይን ባለሙያ ጋር በመሆን በግቢው የሚሰራውን ቤት ዲዛይኑን ሰርተው ያስረክቡታል። አቶ ቴዎድሮስ ይህንን ያደርጉ የነበረው ከአዲስ አበባ ድሬዳዋ በራሳቸው ወጪ በመመላለስ ሲሆን፣ በተጨማሪ የቤተሰብ በዓል የሚያከብሩበትን አርባ ሺ ብርም ልከውለታል።
ዲዛይኑ ከተጠናቀቀም በኋላ ወደ ግንባታ ለመግባት ከፍተኛ ወጪ ያስፈልግ ስለነበር ለዚህም አቶ ጸደቀ ይገዙ የሚባሉ የአካባቢው በጎ አድራጊ አምስት መቶ ሺ ብር ሰጥተው ግንባታውን እንዲጀመር ያደርጋሉ። ሥራው እያደገ ሲመጣም ተጨማሪ አምስት መቶ ሺ ብር ይጨምራሉ በሌላ ጊዜ ደግሞ ሦስት መቶ ሺ ብር ተጨማሪ ልገሳዎችንም አድርገዋል። እንዲህ እንዲህ እያለ የተጀመረውና ከአረጋውያን ማኖሪያና መንከባከቢያ ቀላል ህክምና መስጫን ጨምሮ ሌሎች ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን የሚሰጠው ሕንፃ ግንባታም በመገባደድ ላይ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት ሰባ አቅመ ደካማ አረጋውያን የተመዘገቡ ሲሆን በቅርቡ አዲሱን ቤታቸውን ይቀላቀላሉ።
ዳዊት ግን ዳቦ ቤት ለመክፈት፤ የከብት እርባታና የጓሮ አትክልት ለማልማት በዚህም ከአረጋውያኑ ፈቃደኛ የሆኑትን በአቅማቸው እንዲሰሩ ለማድረግና የገቢ ማስገኛ ለማድረግም ሀሳብ አለው። በተጨማሪ በግቢው ለአእምሮ ህሙማን ማረፊያ ለማስገንባትም እቅድ ይዟል። እኔንም ለዛሬ ቀን እንድደርስ ያደረጉኝ ማህበሩንም ለዚህ ያበቁት ከእኔ ጀርባ በርካታ ኢትዮጵያውያን አሉ የሚለው ዳዊት፤ አሁን የጀመረውንም ከግብ ለማድረስ ከገንዘብ ባለፈ አቅማቸው በፈቀደ የበርካቶች የሞያ የሞራልና የቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ይናገራል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2013