የትምህርት ዓላማው ሰውን በዕውቀት መቅረጽና ስብዕናውን ማነፅ ነው እንጂ መቼም ማነዋወጽ አይሆንም። አይደለም እንዴ ጎበዝ ? ሰው በትምህርቱ በዕውቀቱ ከፍ ከፍ ሲል እኮ እኩይ ድርጊቶችን መራቅ ይጀምራል፤ ለእኩይ ድርጊቶቹ መፍትሄም ያመነጫል።
መቼም ሰው ሁሉ እኩይ ኩነቶችን አርቆ እጁን አጣጥፎ ይቀመጣል እንደማትሉ አምናለሁ፤ የተማረ መመራመር መራቀቅ ይጀምራልና። ከጥሬነት ወደ ብስልነት ይቀየራል ተብሎ ይታሰባል፤ ካልሆነ ግን ያልዘሩትን ማጨድ ይሆናል። የሚከተለው ‹‹ጠብታ ፍቅር›› ከሚል መጻፍ ያገኘሁት ግጥምም ይህንኑ ጽንሰ ሀሳብ ያስረዳል።
ሳይወጠውጥ
ነገ ብሎ ነገር
ያላቀኑት አገር
ያላቆሙት ማገር
ሳይፈጩ ጋገራ
ሳያጭዱ ጎተራ
ተቀምጦ ቁንጥጫ
ታውሮ ፍጥጫ
ሳይዘሩ አረማ
ሳይውሉ ከረማ
ሳይሸምቱ ሸማ
ያለዛሬ ሻማ
ነገማ ጨለማ
ሀገራችንም ለትምህርት ዋጋ ሰጥታ መስራት ከጀመረች ከአንድ ምአተ አመት በላይ ሆኗታል። በሀገሪቱ የመጡ መንግስታት ሁሉ በትምህርት ስርአቱ ላይ አሻራቸውን አሳርፈዋል።ዘመናዊ ትምህርት የመጣልን በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ከአድዋ ድል በኋላ ነው። የትምህርት አዋጅ በ1898 ዓ.ም ወጥቶ በ1900 ዓ.ም የዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት ተከፍቶ ዘመናዊ ትምህርት አሀዱ ተባለ። በወቅቱ መቶ ያህል ተማሪዎች ነበሩ። በ19 12 ኤርነስት ዎርክ የተባሉ አሜሪካዊ ፕሮፌሰር የትምህርት አሰጣጡን ገመግመው ሥርዓተ ትምህርቱ እንዲቀየር ሃሳብ ሰጥተው እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።
በጣልያን ወረራ ት/ቤቶች በመውደማቸው እስከ አብዮቱ ፍንዳታ ባሉት ዓመታት ብዙም መስፋፋት አልቻሉም። ዘመናዊው ትምህርት በኢትዮጵያ ሲተገበር ሙሉ ለሙሉ የምዕራባውያን ሥርአተ ትምህርት ተገልብጦ ነው። ይሄው አሁንም ድረስ ቀጥሎ ትምህርቱ ሀገራዊ ይዘት ይኑረው የሚሉ ጥያቄዎች እየተነሱ ይገኛሉ። በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ለተማሪዎች ግብረገብ ትምህርት ይሰጥ ነበር ፤ ይህም ተማሪዎችን በስነምግባር ለመቅረጽ ጉልህ ሚና ነበረው።
ወታደራዊ መንግሥት ሲመጣ ይህን አሸቀንጥሮ ጣለው። ሥርዓተ ትምህርቱም ከኮሚኒስት አገሮች የተገለበጠ ኅብረተሰባዊነትን ወይም ሶሻሊዝምን ማስፋፋትን ግብ ያደረገ ሆነ። የኢህአዴግ መንግስትም እንዲሁ አዲስ የትምህርት ፓሊሲ አውጥቶ ሰርቷል። በዚህም የትምህርት ሽፋንን ማሳደግ ተችሏል፤ በትምህርት ጥራት ላይ ግን አሁንም ችግሮች ይታያሉ።
የኢትዮጵያ ህዝብ ለተማረ ከፍተኛ ክብር ሲሰጥ ነው የኖረው። “ የተማረ ሰው ይግደለኝ” የሚለውን ይህን ያመለክታል። ለእዚህም ስድስት ኪሎ ሂደህ ተሰልፍ የሚል መልስ እየቀለዱ የሚሰጡ እንደነበሩም አስታውሳለሁ። አሁን ደግሞ ስድስት ኪሎ ድረስ ምን አስኬደህ በየሰፈረህ መጥውልሃል የሚል ቢመጣ አይገርመኝም። ያኔ አንድዬው ዩኒቨርሲቲ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስለነበር ይሆናል ስድስት ኪሎ መጠቀሱ፤ አሁን ዩኒቨርሲቲው በየደጁ ሆኗል። ትምህርት በሀገራችን የተዘራውን ያህል ባይሆንም ፍሬያማ ሆኖ ለሀገር አስተዋጽኦ አበርክቷል። በሀገሪቱ ለታዩ መሻሻሎችና በህዝቡም ላይ ለመጡ ለውጦች አንዱና ዋናው ምክንያት በትምህርት መስክ የተከናወነው ተግባር ነው።
በተማረው ህብረተሰብ ዘንድ የሚስተዋሉ አንዳንድ ችግሮች ግን ሊሃቃኑን ከቦታቸው እያሳጣ ይገኛል። ትምህርት በአንድ ሀገር ልጆች መካከል ፍቅርን እየጨመረ መደመርን እየፈጠረ መሄድ ይኖርበታል ፤ ከዚህ ይልቅ መቃቃርን እየጫረ መደነባበርን እየፈጠረ የሚሄድ ከሆነ፤ ትምህርቱ ከድህነት መንጭቆ የሚያወጣ ሳይሆን ወደ ድህነት አዘቅት አጥልቆ የሚከት የሚፋጅና የሚያፋጅ ይሆናል። በአንድ ወቅት በተማረው የህብረተሰብ ክፍል የተማረሩ አንድ እናት ‹‹መጥኔ ለጠመኔ ጠኔ›› ነው ሲሉ የሰማሁት። እኔም ይህን አባባላቸውን ወድድኩት፤ አዎን ለመፋጀት ለመተላለቅ መማር የለብንም ።
በእኔ አመለካከት የሚፋጁትና የሚያፋጁት ተምረው ያልተማሩት ወገኖቻችን ናቸው። ማነው ያልተመሩት ያቆዩዋትን አገርና ያጸኑትን አንድነት የተማሩት እያፈረሱ ነው ያለው። ይህም የተማረው የህብረተሰብ ክፍል ፍጹም በተሳሳተ አቅጣጫ እየሄደ መሆኑን ያመለክታል። በተማረው የህብረተሰብ ክፍል ይከናወናሉ ብዬ የማልገምታቸው ግን በዚሁ በተማረ ህብረተሰብ ክፍል የሚፈጸሙ ሀገርና ህዝብን የሚገድሉ ድርጊቶች እየበረከቱ ናቸው። ቁጥራቸው ምን ያህል ይሁን ምንም ድርጊቶቹ ግን ሀገርና ህዝብን እየናጡ ናቸው። ህብረተሰቡ የተማረውን ህብረተሰብ በመጠራጠር የሰጠውን ክብር ወደ ማንሳት ቢገባም አይደንቅም።
እውነቱን ነው፤ የተማረው ሊውል በማይገባው ቦታ ሲውል ሲመለከት፣ ችግር መፍታት ሲገባው ችግር ሲፈጥር ወይም ሲያባብስና ሲያቀጣጥል ሲያይ፣ በተማረው መሰረት ሰርቶ ራሱንም ሀገሩንም ዜጎችንም መጥቀም ትቶ፣ መልሶ ከህብረተሰቡ ሁሌም ደጋፍ ሲጠይቅ ሲመለከት ምን ያርግ። በአንድ ጨዋታ ላይ የሰማሁት ታወሰኝ። ጎልማሳው የሚኖረው ከእናት አባቱ ጋር ነው አሉ። ሰዎች ችግር በፈጠሩበት ጊዜ ሁሉ እዚያው መፋለም ሲገባው ዋ ለእማዬ እንዳልናገር ይላል ሲሉ የቀልዱት ታወሰኝ። ተምሮ ችግርን በራስ ለመፍታት አለመሞከርና አለመቻልም ከዚሁ ያስደምራል።
በሀገራችን የሚካሄዱ የእርስ በርስ ግጭቶችና የሚፈጸሙ ጥቃቶች ዘዋሪዎች ያልተማሩት አይደሉም፤ ዘዋሪዎቹ የተማሩት ናቸው። ይህን እኩይ ድርጊት ያርቃሉ ያደርቃሉ ተብለው የሚጠበቁት የተማሩት ናቸው። ድህነትን ያጠፋል ተብሎ ከሚታሰበው የተማረ ሀይል የወጣ አካል ድህነትን ከማጥፋት ይልቅ ሰውን ማጥፋትን ግብ አድርጎ እየሰራ ያለበት ሁኔታ፣ ሰርቶ ከማግኘት ይልቅ ኪራይ ሰብሳቢና በአቋራጭ ለመበልጸግ ከሚሰሩት ጋር የሚሰራ ከሆነ የተማረውን የህብረተሰብ ክፍል በጥርጣሬ መመልከት አልፎም ተርፎ መፈረጅ አካፋን አካፋ ማለት ነውና ችግር የለበትም።
የአመለካከት ልዩነትን ለመፍታት በሰከነ መንፈስ ከመወያየት ይልቅ በስሜታዊነት መተላለቅን መደበኛ ሥራቸው ያረጉ፣ በብዕር ሃሳብ ከመሰንዘር ይልቅ ጦር ለመወራወር የሚሹ፣ የሚወረውሩ፣ የሚያስወረውሩ የተማሩ የሚባሉ እየበረከቱ መምጣቸው ያሳስባል። የሚያሳስበው ደግሞ በየጎጡ በተመሰረቱት የፖለቲካ ድርጅቶች ስር ተሸጉጠው ይህን አቋም ማራመዳቸው ነው። ባለቤቷን የተማመነች በግ ላቷን ከውጪ ታሳድራለች እንደሚባለው ልሂቃኑም አጥፍተው ጎጣቸው ስር ይደበቃሉ። አደራ ማሳያ ጥቀስ ብላችሁ ከፓርቲዎች ጋር እንዳታጋጩኝ። እኔ በዘመናችን ለሚታየው ሁከትና ግጭት ምክንያቱ አንድም በትምህርታችን ላይ ያለው ጉድለት ነው እላለሁ። ለእዚህ መፍትሄው አሁንም ስርዓተ ትምህርታችንን መፈተሸ ነው። ስርዓተ ትምህርቱ ከስርዓት ጋር መያያዝ የለበትም። ነፃ መሆን ይኖርበታል። መንግስት በመጣ ቁጥር የማይለወጥ ሊሆን ይገባል።
እየተፈተሸ ባለው ሥርዓተ ትምህርታችን ላይ ምሁራን ችግር ፈቺ በሚሆኑበት ላይ መምከር ያስፈልጋል። ስነ ምግባር ትልቁ ጉድለታችን ነው። ሁሉም ነገር በስነ ምግባር ይመራል። የታሪክ ትምህርት የሚሰጥበት ሁኔታ ቢመቻች ብሔራዊ መግባባትን እናመጣለን ብዬ አምናለሁ፤ የእነዚህ ትምህርቶች ጉድለት አሁን በተማረው ህብረተሰብ ዘንድ ለሚታያው ወጣገባነት ምክንያት ነው። እነዚህ ላይ ለውጥ ለማምጣት ካልሰራንም ከርሞም ያው እንደተያያዝነው በብሔራዊ ግራ መጋባቱ እንቀጥላለን፤ ጉዞአችን ዘጭ እንቦጭ ይሆናል። ያኔም መጥኔ ለጠመኔ ጠኔ ልንል ማለት ነው።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2013