በመላው ዓለም በዓመት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን እንደሚያጡ የዓለም የጤና ድርጅት ሪፖርት ያመለክታል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ አገራችን የራሷን ድርሻ በመውሰድ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ያጣሉ። ይህ በጣም ከፍተኛ የሆነ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለና የአገራትን ኢኮኖሚ እየጎዳ ከዕለት ዕለትም እየጨመረ የሚገኝን የትራፊክ አደጋ እ.ኤ.አ በ2030 ቢያንስ በአደጋው ሕይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር በግማሽ ለመቀነስ ከአንድ መቶ የሚልቁ አገራት የተለያየ ተግባራትን በቅንጅትና በተናጠል እያከናወኑ ይገኛሉ።
አደጋው እጅግ አሳዛኝ ችግሮችን እየፈጠረ ልጆችን አላሳዳጊ አዛውንቶችን ያለ ጧሪ ቀባሪ። አገርንም ተተኪ ትውልድ እስከማጣት እያደረሰ ከመሆኑም አንጻር አገራት በሚኒስትሮቻቸው አማካይነት ለችግሩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ስለመሆኑም ይኸው የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ያመላክታል።ይህም ቢሆን ግን በዘርፉ እየታየ ያለው ለውጥ እጅግ አዝጋሚ ስለመሆኑም ይነሳል።
በቅርቡ የወጡ ዓለም አቀፍ የመንገድ ደህንነት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ከሆነ ከ5 እስከ 29 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሕፃናትን እና ወጣቶችን ሕይወት ከሚቀጥፉ መንስዔዎች መካከል የትራፊክ አደጋ ቀዳሚውን ስፍራ ይዟል። አደጋው በዋናነት እግረኞችን፣ ብስክሌተኞችንና ሞተረኞችን ሰለባ ያደርጋል። በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገራት ዜጎች ናቸው በአደጋው እጅግ ተጎጂ መሆናቸውም ነው የሚነገረው። በዚህም ከፍተኛ ገቢ ካላቸው አገራት በ3 እጥፍ የሚበልጥ አስከፊ አደጋንም እነዚሁ አገራት እንዲያስተናግዱ ተገደዋል። ይህ ደግሞ ሊያመጣ የሚችለው ምጣኔ ሀብታዊ ድቀት ቀላል የሚባል አይደለም።
ብዙዎቹን አደጋዎች ልንከላከላቸው የምንችላቸው ከመሆናቸው አንጻር ሁሉም ማለትም መንግሥት፣ አሽከርካሪው፣ እግረኛው፣ የመንገድ ባለሙያው፣ የሕግ አስከባሪው እና በዘርፉ የተሰማሩ አካላት በሙሉ እጅና ጓንት ሆነው ከሰሩ አደጋው የማይቀንስበት ምክንያትም የለም። በኢትዮጵያም ከሐምሌ 1 ቀን 2012 እስከ ታኅሣሥ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በደረሰ የትራፊክ አደጋ 1 ሺ 849 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። ከሞቱት ሰዎች ባሻገር 2 ሺ 646 ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት፣ 2 ሺ 565 ዜጎች ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ 495 ሚሊዮን 240 ሺ 473 የሚገመት የአገርና የሕዝብ ንብረት ላይ ውድመት አስከትሏል።
ኢትዮጵያም ይህንን ችግር ለመቀልበስ የተለያዩ ተግራትን እያከናወነች ሲሆን በተለይም የመንገዶችን ደረጃ ከፍ ማድረግ የመንገድ ላይ ምልክቶች በአግባቡና በቦታቸው ላይ እንዲኖሩ በማድረግ እንዲሁም የተለያዩ የመንገድ ደህንነት ሕጎችን በማውጣትና ለተፈጻሚነታቸውም ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች።ሥራው ግን በመንግሥት ወይም በሚመለከተው ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አልያም ቢሮ ብቻ ተሰርቶ የሚጠናቀቅ ካለመሆኑም በላይ ውጤቱም ያን ያህል አመርቂ ስላልሆነ እግረኛው፣ አሽከርካሪው፣ የመንገድ ደህንነት ባለሙያውና የሕግ አስከባሪው ሁሉም እጅና ጓንት ሆኖ ሊሰራበት የሚገባ ዘርፍም ነው።
ይህንን የመንገድ ደህንነት ጉዳይ ያሳልጣሉ ተብለው ከተቋቋሙ ቢሮዎች መካከል የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ አንዱ ነው።ኤጀንሲው የመንገድ ደህንነትን የማስጠበቅና የተሳለጠ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር በማድረግ በኩል ትልቅ ኃላፊነትን ወስዶ የሚሰራ ነው።እኛም ከኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂሬኛ ሂርጳ ጋር ተቋሙ እያከናወናቸው ባሉ ተግባራትና በተገኙ ውጤቶች ዙሪያ ቃለ ምልልስ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፦ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የተቋቋመበት ዋና ዓላማና ግብ ምንድን ነው?
አቶ ጂሬኛ ፦ ኤጀንሲው በ2008 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን በ2009 ዓ.ም አደረጃጀቱንና የሰው ኃይሉን አሟልቶ ወደ ሥራ ገብቷል።የተቋቋመበት ዋና አላማም ከስሙ እንደምንረዳው ትራፊኩን ማስተዳደር ነው።ይህ ማለት ደግሞ የመንገድ መሠረተ ልማት፣ የመንገድ ተጠቃሚ እግረኛ፣ ተሽከርካሪዎች ሁሉ በምን ዓይነት አግባብ ነው መንገዱን ሊጠቀሙ የሚገባው የሚለውንና ምን ዓይነትስ ተገቢ ሕጎች ሊኖሩ ያስፈልጋል የሚለውን ማውጣት፣ ማስተግበር እንዲሁም ማስተማርና ሌሎች የማኔጅመንት ሥራዎችን ማከናወን ነው ።
በሌላ በኩልም የመንገድ አጠቃቀምን የማሳደግ ሥራንም ይሰራል፤ በዚህም አንድ መንገድ ምንና አጠቃቀሙ እንዴት ቢሆን ነው የተሻለ አገልግሎትን መስጠት የሚችለው፤ የሚለውን በማየት በተለይም ከመንገድ ደህንነት ከትራፊክ ፍሰት አንጻር በማየት አጠቃቀሙን እንዴት እናስተካክለው የሚለውን ይሰራል።በነገራችን ላይ ኤጀንሲው እንደ ራእይ አስቀምጦ የሚንቀሳቀሰው ሰላማዊና ተቀባይነት ያለው የትራፊክ እንቅስቃሴን ማረጋገጥ የሚል ሲሆን ይህ እንዲሳካ ደግሞ ተልዕኳችንን ማየት ይኖርብናል።በዚህም ተገቢ የመንገድ አጠቃቀም ሕግ ማኖር ሕጎቹም እንዲከበሩ ማድረግ እንዲሁም ተጠቃሚው እንዲያውቅ ማድረግ የሚሉ ናቸው።
ይህንን ለማሳካትም እያንዳንዱ የምንሰራው ሥራ በልኬት እየተመዘነ እንዲሁም ተጠቃሚውን ያገናዘበ እንዲሆንና ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ እንዲሆን ስለሚያስፈልግ በዚያ መሠረት የተለያዩ አደረጃጀቶችን ከመፍጠር ባሻገር አምስት ያህል የሥራ ክፍሎችን በማዋቀር ሥራዎች እየተሰሩ ነው።ከዚህ በተጨማሪም ኤጀንሲው አምስት ያህል ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን በእነዚህም የሚሰሩ ሥራዎች ተደራሽ ለማድረግ የሚያግዙ ናቸው። በእያንዳንዳቸው ስርም የሚመለከታቸው የመኪና መቆሚያ (ፓርኪንግ) የሚመለከታቸው የትራፊክ ተቆጣጣሪዎችም በእነዚህ አምስት ቅርንጫፎች ተበትነው ሥራቸውን በማከናወን ላይ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን፦ ኤጀንሲው ከአላማና ከግቡ አንጻር ያከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት በተለይም ውጤት ያመጡትን እንዴት ይገልጿቸዋል?
አቶ ጂሬኛ፦ ኤጀንሲው አዲስ ተቋም ቢሆንም ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት የሰራቸው ሥራዎች ሲታዩ ትልቅ ውጤት ያመጣ ተቋም ነው ።በዚህም ቶሎ ወደ ሥራ ገብቶ የኅብረተሰቡን ችግር እየፈታ ከመሄዱም በላይ ጎን ለጎንም ራሱን ለማብቃት በርካታ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑ ትልቅ ነገር ነው። በዋናነት ካከናወናቸው ተግባራት መካከልም ተገቢ የሆነ የመንገድ አጠቃቀም ሥርዓትን መዘርጋት ነው፤ ይህም ሲባል መንገድ እየተወሳሰበ ሲሄድ በተለይም ደግሞ አዲስ አበባ ከተማ የአገሪቱ የፖለቲካ የኢኮኖሚ ማዕከል እንደመሆኗ በርካታ ሰዎችም ስለሚመጡ በዚህም ልክ ተሽከርካሪው እየጨመረ ከመሆኑ አንጻር ይህንን ሊያስተዳደር የሚችለው ማኔጅመንት ካልተጠናከረ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ሊፈጥር ስለሚችል ይህንን የመንገድ አጠቃቀም ሕግ ከማስፈን አንጻር በተለይም የመንገድ ዳር ምልክቶች የአስፋልት ላይ ቀለሞችን እንዲሁም የትራፊክ መብራትን ከመዘርጋት አንጻር ሰፊ ርቀት ተሂዷል።
ለምሳሌ ኤጀንሲው በ2008 እና 2009 ዓ.ም ላይ በከተማዋ የነበረው የትራፊክ መብራት ቁጥራቸው አነስተኛ ነበር፤ ኤጀንሲው በሰራው ሥራ ግን በርካታ የትራፊክ መብራቶች በመላው ከተማ ተተክለዋል።ይህ ደግሞ የከተማዋን የትራፊክ ሥርዓት አንድ ደረጃ ከማሳደግ አንጻር ሰፊ ሚና ያለው ነው። በነገራችን ላይ በየትኛው ዓለም ቢሆን የትራፊክ መብራት የትራፊክ ማኔጅመንቱን በማሳለጥ በኩል ሰፊ ሚና ያለው ከመሆኑ አንጻር አብዛኞቹ አገሮች በአግባቡ ይጠቀሙበታል፤ እኛም ይህንን እያስፋፋን ለመሄድ ሰፋፊ እቅዶች ይዘን ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንገኛለን።
በሌላ በኩልም በተለይም ተገቢ የሆነ የመንገድ አጠቃቀም ከመዘርጋት አንጻር ቀለም ተራ ነገር ይመስላል። ነገር ግን ወሳኝ የሆነና የትራፊክ ፍሰቱ ሳይቋረጥ ወይም ሳይስተጓጎል ሁሉም ረድፉን ይዞ እንዲሄድ በዚህ መካከልም የሚፈጠሩ አደጋዎች በተቻለ መጠን የቀነሱ እንዲሆኑ በማገዝ በኩል ከፍተኛ ሚና ያለው ነው።ይህ ወሳኝ የሆነ የመንገድ ላይ የቀለም ቅብ ከዚህ ቀደም የአፍሪካ ህብረት ስብሰባና አንዳንድ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ሲኖሩ ብቻ መሀል ከተማዋን የመቀባት ሥራ ይከናወን ነበር፤ አሁን ግን ይህንን አሠራር በመቀየር ሙሉ ከተማውና አብዛኛው የከተማው መንገድ በተከታታይ እየተቀባ ይገኛል።ምልክትም ለትራፊክ ፍሰቱ ትልቅ ሚና ያለው በመሆኑ ዘንድሮ ብቻ ከ1 ሺህ የሚበልጡ ምልክቶች በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ተተክለዋል።ከዚህ ውጪ ከትራፊክ ፍሰቱና የመንገድ አጠቃቀምን ከማሳደግ አንጻር በጣም ወሳኝ ከሆኑ ነገሮች መካከል አንዳንድ
አላስፈላጊ የትራፊክ ፍሰቱንም ከማቀላጠፍ ይልቅ ያውኩ የነበሩ አደባባዮችን በማንሳት በመብራት የመተካት ሥራ እየተሰራ ሲሆን ለማሳያም በቀለበት መንገድ ላይ ያሉ አደባባዮች በትራፊክ መብራት እንዲተኩ ሆኗል፤ የመንገድ አጠቃቀምንም በተቻለ መጠን ቀልጣፋ ከመዘጋጋትም ነፃ ለማድረግ በመንገድ ዳር የሚቆሙ መኪኖችን የሰዓት ገደብ እንዲደረግባቸው ሆኗል።በተለይም በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ላይ መንገዶች እንዳይዘጉ በማሰብ ጠዋት ወደ መሀል ከተማ በሚያስገባ መንገድ ላይ መኪና ለአጭርም ይሁን ለረጅም ሰዓት አቁሞ መሄድን በመከልከል ማታ ደግሞ በተቃራኒው ያለው መንገድ እንዲሁ ነፃ እንዲሆን የማድረግ ሥራ 21 በሚሆኑ መስመሮች ላይ ተግባራዊ ሆኗል።ይህ ሁኔታም የትራፊክ ፍሰቱ ቀልጣፋና ከመጨናነቅ የጸዳ እንዲሆን አስችሏል።
አዲስ ዘመን፦ እንዳሉኝ የትራፊክ ፍሰቱን ጤናማ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል፤ ግን አሁንም በመንገዶቻችን ላይ የሚታየው መጨናነቅ እንደቀጠለ ነውና የዚህስ ምክንያቱ ምንድን ነው?
አቶ ጂሬኛ፦ አዎ፤ አሁንም የሚያስተናግደው መኪና ብዙ ሊሆንና መንገዱ ላይችል ይችላል። ይህ ሲሆን ደግሞ መንገዱ ካልቻለ የተወሰነ የመንገድ ተጠቃሚን መከላከል ሊያስፈልግ ይችላል።ከዚህ አንጻር ለአውቶቡስ ብቻ የተፈቀዱ መንገዶች እንዲኖሩ አድርገናል።በተጨማሪም መኪኖች በተቃራኒው መንገድ ገብተው እንዲሄዱም ፈቅደናል፤ በሌላ በኩልም የከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎች የሚንቀሳቀሱበትን ሰዓት የመወሰን በዚህም የትራፊክ ፍሰቱ ለውጥ እንዲያመጣ ሙከራዎች ተደርገዋል።
አዲስ ዘመን፦ ከመንገድ ደህንነት አንጻርስ የተከናወኑ ተግባራት ምን ይመስላሉ?
አቶ ጂሬኛ፦ ብዙ አመርቂ ውጤቶች የመጡበት ኤጀንሲው በ 2008 ዓ.ም ወደ ሥራ ሲገባ በየዓመቱ በትራፊክ አደጋ የሚሞተው ሰው በ7 በመቶ እየጨመረ ነበር፤ ይህ ማለት በጣም ትልቅ ቁጥር ነው። ይህንን ታሪክ ለመቀየርና ለመቀልበስ ስትራቴጂ ነድፈን ወደ ሥራ የገባን ሲሆን በዚህም መጀመሪያ ያደረግነው ሥራ ሁኔታን መረዳት ነው፤ በከተማዋ ለአደጋ አጋላጭ የሆኑ ነገሮች ምንድን ናቸው? የትኛው የመንገድ ተጠቃሚስ ነው በዋናነት እየተጎዳ ያለው? የችግሩስ መንስኤ ምንድን ነው? የሚለውን ስናይ በዋናነት የተረዳነው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ ለአደጋ እየተጋለጠ ሕይወቱን እያጣ ያለው እግረኛ ነው፤ አደጋዎቹ ደግሞ የሚደርሱት በዋና ዋና መንገዶች ላይ ነው።ብዙ አደጋ የሚያደርሱት ደግሞ የሥራ የንግድ ተሽከርካሪዎች ናቸው።
ለዚህ መውሰድ ያለብን መፍትሔ ምንድነው? ብለን ስናስብ አንዱ የእግረኛ ደህንነትን ለመጠበቅ የእግረኛ መንገድ መሠረተ ልማቶች መሻሻል አለባቸው የሚለውን ወስደናል።በዚህ መሠረትም በእያንዳንዱ 40 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ ይሰራል።ይህም ትልቅ ለውጥ አምጥቷል።አንዳንድ አሽከርካሪዎች ከተማ ውስጥ በፍጥነት ያሽከረክራሉ። በመሆኑም ፍጥነትን መቆጣጠር እግረኛን መታደግ ነው በሚል በተለይም በተደጋጋሚ አደጋ በሚደርስባቸው አካባቢዎች ላይ የፍጥነት መገደቢያዎችን በመስራት አደጋን የመቀነስ ሥራ ተሰርቷል።ከዚህ በተጨማሪም ዘመናዊ የፍጥነት መቆጣጠሪያ (ራዳሮችን) በመግዛትና የትራፊክ ፖሊሶችን በማሰልጠን የቁጥጥር ሥራዎችን በመስራት ላይ ስንሆን፤ ሌሎች ቁልፍ የደህንነት ሕጎች የሚባሉት እንደ ደህንነት ቀበቶን አሽከርካሪውም በጋቢና የሚቀመጠውም ተሳፋሪ ተግባራዊ እንዲያደርገው አድርገናል።
በሌላ በኩልም ምቹ የእግረኞችና የተሽከርካሪ መጋጠሚያዎች(ሴፍ ኢንተርሴክሽን) ፕሮግራም በሚል ደግሞ መጋጠሚያዎቻችን ለእግረኛ ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ የማሻሻልና የትራፊክ ፍሰቱንም በማያውኩ ሁኔታ እንዲካሄድ የማድረግ ሥራ ተሰርቷል።በተለይም በከተማዋ ላይ ላለው የትራፊክ ፍሰት መሳለጥ ዓይነተኛ ድርሻን እየተወጡ ያሉት በቅርቡ የተቀጠሩትና ሥራ የጀመሩት አንድ ሺ አንድ መቶ አካባቢ የትራፊክ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች ናቸው፤ እነዚህ ደግሞ ከተማ ውስጥ በየትኛውም የሕግ ማስከበር ሥራ ላይ የበኩላቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን፦ ምናልባት እነዚህ የትራፊክ ተቆጣጣሪ ተብለው በእናንተ በኩል የተሰማሩት እንዲሁም የትራፊክ ፖሊሶች መንገድ ትራንስፖርት የሚያሰማራቸው የቁጥጥር ባለሙያዎች መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ሥራውንስ ተናበን እየሰራን ነው ብለው ያምናሉ?
አቶ ጂሬኛ፦ ኤጀንሲው ትራንስፖርት ቢሮ ስር ነው፤ ለምሳሌ ሌላው በቢሮው ስር ያለው ትራንስፖርት ባለሥልጣን ተግባርና ኃላፊነቱ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችን መቆጣጠር አቅርቦቱንና ፍላጎትን በተቻለ መጠን የማመጣጠንና የመቆጣጠር ሥራ ነው፤ ኤጀንሲው ደግሞ ሙሉ ትኩረቱ የትራፊክ ማኔጅመንቱ (አስተዳደሩ) ላይ ነው።በመሆኑም በተለይም ትራፊክ ፖሊሶች ኤጀንሲው ሥራውን አስተላልፎላቸው ነው እየሰሩ ያሉት።ለምሳሌ የትራፊክ ቅጣት ኤጀንሲውን ነው የሚመለከተው፤ በመሆኑም ትራፊክ ፖሊሶች ኤጀንሲው በሚያወጣው መመሪያና አሠራር መሠረት ሕጉን ያስከብራሉ ማለት ነው።በመሆኑም ሥራችንን በዚህ መልኩ ተከፋፈለን ነው እየሰራን ያለነው።
አዲስ ዘመን፦ የሥራ ክፍፍላችሁ ይህንን ይምሰል እንጂ የእናንተ ተቆጣጣሪዎች ትራፊክ ፖሊሱ በአንድ መንገድ ላይ ሲሰሩ ምንድን ነው ልዩነታቸው?
አቶ ጂሬኛ ፦ ትራፊክ ፖሊስና እኛ መካከል ትንሽ ልዩነት ሊኖር ይችላል፤ ምክንያቱም ኤጀንሲው መንገድ ደህንነት የትራፊክ ፍሰት ላይ ነው ፤ ፖሊስ ደግሞ የቁጥጥር ሥራውንና ሕግ ማስከበሩን የሚሰራ በመሆኑ ኃላፊነቱ ትንሽ ሰፋ ይላል። ይህንን በምሳሌ ባስረዳሽ ትራፊክ ፖሊስ ትርፍ የጫነን አገልግሎት ሰጪ ለምን ብሎ ይጠይቃል፤ በሕጉ መሠረትም እርምጃ ይወስዳል፤ ለእኛ ግን ይህ ኃላፊነት አልተሰጠንም፤ ቦሎ መቆጣጠር ላይ አሽከርካሪ ተሽከርካሪ ቁጥጥር ባለሥልጣን አለ፤ ምናልባት ልንተጋገዝ እንችል ይሆናል፤ ትራፊክ ፖሊስ ግን ይህንንም ይሰራል።በጠቅላላው ግን ኤጀንሲው በሚሰጠው መመሪያና በሚያስቀምጣቸው ምልክቶች እየተጋገዝንና እየተናበብን የምንሰራ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ፦ ሥራው ከብዙ አካላት ጋር የሚያገናኝ እንደመሆኑ ትልቁ ፈተናው ደግሞ ሙስናም ነውና በዚህስ ላይ እየተሰራ ያለው ሥራ ምን ይመስላል?
አቶ ጂሬኛ፦ ይህንን በተለያየ መንገድ ማየት ያስፈልጋል፤ በመንገድ ላይ ቆመው ሕግን በማስከበር ሥራ ላይ ያሉት ልጆች ሥራቸውንና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ተወጥተዋል ወይ የሚለውን ብቻ እንኳን ብናይ በጣም ብዙ ውጤት መጥቷል።ይህ ማለት ደግሞ ልጆቹ ከመቀጠራቸው በፊት የመንገድ ላይ መጨናነቅን የሚፈጥሩ ነገሮችን በማስወገድ መንገዱን ለትራፊክ ፍሰቱ ምቹ እንዲሁም ተላላፊዎችንም መቅጣት አልቻልንም ነበር። ልጆቹ በዚህን ያህል ሥራውን እያገዙ የሚፈለገውንም ውጤት በተወሰነ ደረጃ እያመጡ ከመሆኑም በላይ ሥራ የሚሰጣቸው ተቆጥሮ ነው።ለምሳሌ አንዳንድ መንገዶች ጠዋት ወደ ሥራ በመግቢያና ማታ መውጪያ ላይ መኪና አቁሞ መሄድ ክልክል ነው። እነዚህ ቦታዎች ላይ መኪና እንዲያቆም ብር ተቀብሎ የፈቀደ እንደሆነ የሚታይ በመሆኑ ተጠያቂነትም ይኖረዋል።
የባለፉትን ስምንት ወራት አፈጻጸም እንኳን ብናይ 7መቶ 7 ሺ ሰው ደንብ በመተላለፍ ተቀጥቷል።በመሆኑም ሙስና ቢኖር ኖሮ ደግሞ ይህ ሁሉ ሕግ ተላላፊ ባልተቀጣ ነበር።በነገራችን ላይ ኅብረተሰቡ ራሱ ሕግን ማክበር ትቶ ለሥራ የወጡትን ልጆች ለማሳሳት ይሞክራል፤ በዚህ ምክንያት ደግሞ እነዚህም ልጆች ህሊናቸውን እንዲሸጡ ማበረታታት ነውርም በመሆኑ ኅብረተሰቡም ሁለት መቶ 50 ብር ላለመቀጣት በዚህ መልኩ እነሱን ወዳልተገባ ባህርይ ውስጥ ከማስገባት መቆጠብ አለበት ።
በሌላ በኩል ደግም ፖሊሶች ህግ አስከባሪ ትራፊኮች በሙሉ ሌባ ብሎም የሚያስብ ብዙ ነው፤ በመሆኑም ኅብረተሰቡም ይህንን አስተሳሰብ ከአእምሮው ማውጣት በሥራው ላይ ያሉ ሰዎችንም ለማሳሳት አለመሞከር፤ በተጨባጭ የተገኘ ካለ ደግሞ ማቅረብና በማስረጃ አስደግፎ ለሕግ አካል መስጠት ይገባል።
አዲስ ዘመን፦ ለመንገድ ማኔጅመንት እንቅፋት ከሆኑ ነገሮች መካከል በተደጋጋሚ በመንገዶች ላይ የሚያጋጥሙ የትራፊክ አደጋዎች ናቸው፤ የእነሱ መንስኤ ከሆኑ ነገሮች መካከል ደግሞ የአሽከርካሪዎች የብቃት ጉዳይ ነውና እንዲያው በዚህ ላይ ያልዎት ሀሳብ ምንድን ነው?
አቶ ጂሬኛ፦ ብቃትን የምንረዳበት መንገድ ትንሽ ክፍተት ያለበት ይመስለኛል።አብዛኛው አሽከርካሪ የማሽከርከር ብቃቱ አለው፤ ችግሩም የብቃት አይደለም፤ ለምን መሰለሽ አሁን ላይ በብዛት ሕግ የሚጥሱ߹ ሰዎች ላይ ጉዳት የሚያደርሱና ንብረት የሚያወድሙ ߹ መንጃ ፍቃዳቸው የሚታገዱት ሰዎች 30 ዓመትና ከዚያ በላይ ያሽከረከሩ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ናቸው።በመሆኑም ለእኔ የሚመስለኝ እንዲያውም በጣም ልምድ መያዝ ይመስለኛል።
በመሆኑም በመንገድ ደህንነታችን ለትራፊክ አደጋ መጨመር ትልቁ መንስኤ የሥነ ምግባር ችግር ነው።የእግረኛ ማቋረጫ ላይ መኪና አቁሞ መሄድ እና ሰው በሚበዛበት የገበያ ቦታ ላይ ፍጥነትን በ80 አድርጎ ማሽከርከር የሙያ ብቃት ማነስ ሳይሆን የሥነ ምግባር ችግር መገለጫ ነው።በነገራችን ላይ ሥልጠናውም ትኩረቱ ቴክኒክ ላይ በመሆኑ የመጣ ችግር ስለሆነ በቀጣይ ይህንን ለማሻሻልና ወደ ሥነ ምግባር ሥልጠናው ለማተኮር ትራንስፖርት ባለሥልጣንም እየሰራ ይገኛል።
በመሆኑም እንደ ኤጀንሲ ሕጎች እንዲወጡ ማድረግ የወጡትንም ተከታትሎ ማስተግባር ላይ በትኩረት ለመስራትም በበኩላችን አቅደናል።ከዚህ አንጻርም አሽከርካሪው ሕጎቹን እንዲያውቅ አውቆም እንዲተገብር ሳይተገብራቸው ሲቀር ግን ተጠያቂ ማድረግም ያስፈልጋል።በጠቅላላው ሕግ አክባሪ አሽከርካሪም ሆነ እግረኛ ለማፍራት መጀመሪያ ጠበቅ ያሉ ሕጎችን ማውጣት፣ ማሳወቅና ማስተማር ተጥሰው ሲገኙም ጠበቅ ያለና አስተማሪ የሆኑ ቅጣቶችን ማስቀመጥ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ጂሬኛ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2013