ፖለቲካ አንድ ሲሆን በርእዮት ሲደገፍ ግን ዘርፈ ብዙ ነው። በ”-ኢዝም” ሲታገዝ ደግሞ አጥንትና ጉልጥምት አበጅቶ፣ ጎራ አስለይቶ ወይ በተመሳሳይ አሊያም በተቃራኒው፤ ካልሆነም በደጋፊነት፤ ወይም ገለልተኛነት ተርታ ያቆማል። ምንም ይሁን ምን ግን ዓለምን እያሽከረከረና እያሾረ ያለው ፖለቲካ መልከ ብዙ ነውና ከእነዛም መካከል “ግራ ዘመም” (leftism) አንዱ ሲሆን፤ በዚህ ጽሑፍም እሱኑ እንመለከታለን።
“ግራ ክንፍ” እና “ቀኝ ክንፍ” በፈረንሳይ አብዮት ወቅት የተፈጠሩ ስያሜዎች ሲሆኑ አመጣጣቸውም በወቅቱ የነበረው (“Estates General” ይባሉ የነበሩት)ን የጉባኤ አቀማመጥ ተከትሎ ሲሆን በስተግራ የነበሩት ነባሩን እሴትና ሥርዓት አጥብቀው ይጠሉና ይቃወሙ፤ ከነጭራሹም ምንም አይጠቅምምና መወገድ አለበት፤ ከእሱ ጋርም ለውይይትም ሆነ ድርድር አንቀመጥም፤ ሁሉም ነገር መለወጥ ከዜሮ መጀመር አለበት ወዘተ በማለት ይወተውቱ የማይታረቅ አቋምን ያራምዱ የነበሩ ናቸው።
ግራ ዘመም ፖለቲካዊ አቋም በማንኛውም ዘንድ ሊኖር ይችላል። በሊብራሉም ሆነ ዲሞክራቱ ውስጥ ግራ ዘመም ፖለቲከኞች አሉ። በራሱ በግራ ዘመም ፖለቲካ ውስጥም በርካታ የተለያዩ ልዩነቶች ያሉ ሲሆን አንዱም “ስር ነቀላዊ ግራ ዘመምነት” (radical leftism) ነው። ለሥርዓተ ፆታ እኩልነት በመታገያነትና ማታገያነት እያገለገለ ያለው “እንስታዊነት” (Feminism) ውስጥም ነባሩ ዓለም ሙሉ ለሙሉ የወንዶች ብቻ ስለነበረ ከነስሩ መነቀልና በሴቶች መተካት አለበት ባዮች እንዳሉ ሁሉ፤ በሃይማኖት፣ በሰብአዊ መብት፣ (በ”Enviromentalism”) ተፈጥሮን ለማዳን በሚደረጉ እንቅስቃሴ(ዎች) ውስጥ ተፈጥሮን በቁጥጥር ስር ካላዋልን ሞተን እንገኛለን ባዮች (በሌላው ጽንፍ ደግሞ ተፈጥሮን ወደ ነበረችበት የክብር ቦታዋ አሁኑኑ መመለስ አለብን እና የመሳሰሉ አቋሞች – በሁለቱም የግራ ዘመም አተያዮች (እኔ ያልኩት/የምለው ብቻ ነው ትክክል) አሉበት) እና በመሳሰሉት ሳይቀር ግራ ዘመም አስተሳስብ እንደ መመሪያ ሆኖ የሚያገለግልባቸው አጋጣሚዎች ቀላል አይደሉም። ጉዳዩን በቅጡ እንገነዘብ ዘንድ እንዲያግዘን ከአስተሳሰቡ ክንፎች አንዱ የሆነውን፤ ከብያኔ አንፃር ምሳሌ ይሆነን ዘንድ “ግራ ክንፍ ኮሚኒዝም”ን መመልከት እንችላለን። (በምዕራቡም ሆነ አሜሪካን በመሳሰሉት ዘንድ ግራ ዘመም ርዕዮትን ሙሉ ለሙሉ የሶሻሊዝም ተቀፅላ፤ አቀንቃኞቹንም ሶሻሊስቶች አድርጎ የመውሰድ ነገር እንዳለ ልብ ይሏል።)
ግራ ክንፍ ኮሚኒዝም (Left-wing Communism) በጥሩ ሁኔታ በአማርኛ በተዘጋጀው “ማርክሲዝም ሌኒኒዝም መዝገበ ቃላት” ላይ እንደተበየነው “ብስለት ከማጣት የተነሳ ስህተቶችን የሚፈፅም፤ በኮሚኒስት እንቅስቃሴ ውስጥ የሚከሰት አዝማሚያ ነው። ግራ ክንፍ ኮሚኒዝም የአብዮት ሕጎችን የማይረዳ፣ ተጨባጭ ሁኔታዎችን የማይመለከት፣ ችኩልና በስሜት ኃይል ብቻ የሚንቀሳቀስ ነው። የአመፅ ጥሪ ማስተላለፍ፣ በፓርቲ ውስጥ መኖር ያለበትን ጠንካራ ዲሲፕሊን አለመቀበል፣ የቡርዧ ፖለቲካዊ ሥርዓት በሚፈቅዳቸው ዲሞክራሲያዊ መድረኮች ለመጠቀም አለመፈለግ፣ ሁኔታዎች የሚጠይቁትን አንዳንድ ድርድሮች ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆን ወዘተ … የግራ ክንፍ ኮሚኒዝም ገፅታዎች ናቸው።
“ግራ ክንፍ ኮሚኒዝም” የትግልን ስልት የማይረዳና ከተጨባጩ ውጭ የሚቆም በመሆኑ ለአብዮታዊ እንቅስቃሴ አደገኛ ሁኔታን የሚፈጥር፤ በአንፃሩም አብዮቱን በማስጠቃት ተሸናፊ የሚያደርግ አዝማሚያ ነው።” (አድርባይነት (opportunism)፣ ጽንፋዊነት (extremism)፣ አውዳሚነት (nihilism)፣ ስር-ነቀላዊነት (radicalism)፣ ዘረኝነት (racism)፣ ነጣይነት (separatism) ከዚሁ ክንፍ ጋር የሚወራረሱት ባህርይና የግብር አንድነት እንዳላቸውም ይታወቃል።)ይህንን መሠረት አድርገን “ግራ ዘመም”ን ከተጨባጩ ዓለም ጋር ስናገናዝበው ምንም የተለየ ሆኖ አናገኘውም። የምናገኘው በመጽሐፉ የተሰጠውን ብያኔ ሲያፀድቅና ለተሰጠው ብያኔ ሲያድር ነው።
ከዚሁ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ ሳይጠቀስ የማይታለፈው የአንቀሳቃሸ ሞተሮቹ የፖለቲካ ፓርቲ(ዎች) ጉዳይ ሲሆን ልክ እንደ ፖለቲካው ሁሉ እነሱም መልካቸውም ሆነ ቁመና አቋማቸው የተለያየ ነው (ልክ እንደ “ዲሞክራሲ” – የሶሻል ዲሞክራሲ፣ አብዮታዊ ዲሞክራሲ፣ የኢንዱስትሪ ዲሞክራሲ (Industrial democracy)፣ ሊብራል ዲሞክራሲ ወዘተ)። በመሆኑም ምድባቸው ከሚከተሉት ርዕዮትና ከሚያራምዱት “…ኢዝም/…ism” አኳያ ይሆናል ማለት ነው።
“ግራ ዘመም” ቀጥተኛ ተቃራኒ ያለው ሲሆን በአቋምም ሆነ አላማና ግብ ከ”ቀኝ ዘመም” (Right-wing) ጋር ስምሙ አይደሉም። በአገራችን በ1960 እና 70ዎቹ እንደተከሰተው ዓይነት፣ ማለትም “ግራ ዘመም”፣ “ቀኝ ዘመም” (አለ/የለም?)፣ “መሀከል” ላይ ያለ (Centeris(m)t)፣ ስርነቀል ወዘተ መፈራረጅ፤ በዋናው በግንዱ (umbrella) እምነታቸው በሆነው ማርክሲዝም-ሌኒኒዝም (በደርግ ዘመን “ማርክሲዝም-ሌኒኒዝም” የፓርቲው – ኢሠፓ(አኮ) “መመሪያ” ነበር።) አስተሳሰባቸው አንድ ሆነው፤ ነገር ግን እንደ ነጠላ ቁጨት ዘርፍ ዘርፍ አውጥተው ለየብቻ በመቆም መጨረሻቸውን መጠፋፋት ያደረጉትን (ወይም ያደረገውን “ያ ትውልድ”) እዚህ ላይ እንደ ማሳያ አድርገን መውሰድና ማስተንተኛ ማድረግ የምንችል ሲሆን ለጊዜው ጉዳያችን እሱ ባለመሆኑ ወደ ተነሳንበት እንመለሳለን።
ከላይ በብያኔው እንደተመለከትነውና እንደተገነዘ ብነው ግራ ዘመም አንድ እራሱን የቻለ የፖለቲካ ፍልስፍና (ለአንዳንዶች ሳይንስ፣ ላንዳንዶች ደግሞ ርዕዮት፣ ለሌሎች ቀኖና) ነው። በመሆኑም ነው የራሱ የሆኑ ተከታዮች፣ አቀንቃኞችና አራማጆች ያሉት። ስለ “ግራ ዘመም” ፖለቲካዊ ፍልስፍና እዚህ ማውራት ለምን አስፈለገ? የሚል ጥያቄ በብዙዎች አእምሮ ሊመጣ እንደሚችል ይገመታል፤ ትክክል ነው። መልሱም ቀላል ነው። (ሌላው ገፅታው ግን እንደ መልሱ ቀላል አይደለም።)
መልሱ “ዓለም እየተተረማመሰች ነው። በአሁኑ ሰዓት እዚህም እዚያም ትርምስ አለ። ጥናቶችም ሆኑ ዜና-ዘገባዎች ዕለት በዕለት እንደሚያሳዩት፤ እኛም የአሁኗ ዓለም ነዋሪዎች እየኖርነው እንዳለነው ከእነዚህ ሁሉ፣ ከቀላል እስከ ዘግናኝ ቀውሶች ጀርባ የግራ ዘመም ፖለቲካና ፖለቲከኞች እጅ አለበት። በመሆኑም “ይህ የግራ ዘመሞች ሥራ ነው” ከሚል ጠቅላይ አገላለፅ ባለፈ “ግራ ዘመም” ምን እንደሆነ እራሱን አስችለው የሚያብራሩ አይደሉም። ይህ በመሆኑም ጽንሰ ሀሳቡም ሆነ ትርጉምና ፋይዳው ምን እንደሆን አያሳዩም። ያ ደግሞ ለብዙዎች አጠቃላይ መልዕክቱንም ሆነ ዝርዝር ጉዳዩን ለመረዳት እንቅፋት ሲፈጥር ይታያል። ይህን ችግር በመገንዘብ የተዘጋጀ ጽሑፍ ሲሆን፤ በላይኛው አንቀፅ ላይ ለቀረበው ጥያቄም መልሱ ይኸው ነው።
እራሳቸውን በተዋበ ስም በመጥራትና እራሳቸውን በራሳቸው ዲሞክራት መሆናቸውን ባለፈ “ግራ ዘመም ነን” ከማለት የሚቆጠቡት ግራ ዘመሞች (ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ ኤኤንሲን በከፍተኛ ደረጃ የተፈታተኑት ተቀናቃኝ ፓርቲዎች – EFF, Numsa, AMCU)፤ አንድ የሚያደርጋቸው ወይም የሚያመሳስላቸው ገፅታ ቢኖር ምንጩ የማይታወቅ የደለበ ሀብት (ድጋፍ) ያላቸው መሆኑ፣ የሕዝብን ስስ ብልት (ብሶት) ማራገብና ስሜት መቆስቆስ መቻላቸው፣ በማናቸውም በሚወድም ንብረትም ይሁን በሚጠፋ የንፁሀን ሕይወት ደንታቢስና ምንም የማይፀፀቱ መሆናቸው ወዘተ ሲሆን፤ ለአላማቸው መሳካት የማይፈነቅሉት ድንጋይ አለመኖሩም የልዩ ልዩ ያደርጋቸዋል።
(በአሜሪካ የ”ግራ ዘመም” (“woke left”, “woke racism”ም ይሏቸዋል)ን አስቸጋሪ ባህሪና ፀረ-መንግሥትና ፖሊሲዎች ተግባራት ርዕዮቱ ወይም አስተሳሰቡ ምን ያህል በአገሪቱ እንደተነሰራፋና በእያንዳንዷ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ተሰግስጎ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ወደ እራሱ ፖለቲካዊ ጥቅም በመቀየር እየተጠቀመበት እንደሆነና ሕዝብን በመንግሥት ላይ በማነሳሳት ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ ተግባር እንደሚመራ ለመታዘብ “Woke racism is a systemic problem in America” በሚል ርዕስ የቀረበውን ጽሑፍ ይመለከቷል። በፈረንሳይም “left-wing association” በሃይማኖት በኩል መንግሥቱ ላይ እየፈጠረ ያለውን ተገቢ ያልሆነ ተፅእኖም እንደዚሁ።)ግራ ዘመም አቋም ለፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ የተሰጠ ወይም የተተወ ርዕዮት አይደለም፤ ከግለሰብ ጀምሮ ግራ ዘመም ርዕዮት አራማጆች ሞልተዋል።
ግራ ዘመምነት የማይታይባቸው ዘርፎች አሉ ለማለት ይቸግራል። በሃይማኖት ሳይቀር አለ። በኪነጥበብ ዘርፉም የጉድ ነው። በድምፃዊያን ሥራዎች፣ በፀሐፍት ድርሰቶች፣ በሠአሊያን ቀለማት፣ በአዝማሪዎች ክራርና ማሲንቆ ወዘተ ሁሉ አለ። (እዚህ ላይ ከተለመዱት ማለትም ከዜማና ቅንብሩ፣ ገፀባህሪያት እና አሳሳላቸው እና ከ”ፐፐፐፐፐ …” ዓይነት አሰልቺና በማስተማር አቅማቸው ደካማ (ከዘመኑ አንፃር) ሂሶች በመውጣትና የተለያዩ አተያዮች (perspectives)ን በመመርመሪያ መነፅርነት በመጠቀም ሥራዎችን የመፈተሽ ልምድ ቢኖር ኖሮ ስንትና ስንት ግራ፣ ቀኝ ዘመሞችን ወይም/እና መሀል ላይ በመሆን ለውውይትና ድርድር ዕድል የሚሰጡ ሥራዎች እንዳሉ ባየን ነበር፤ ወይም ስንትና ስንት ባህልና ወግን የመበረዝ ሥራዎች ላይ የተጠመዱ እንዳሉ ባወቅን ነበር። ኪነጥበብም ሆነ ባለሙያዎቹ ምን ያህል ከዕለት ዕለት በተሻሻሉ ነበር። ለማንኛውም (“ነበር ባይሰበር” ነውና) ይህ የዛሬው ጉዳያችን ባለመሆኑ በቅንፍ አልፈነው ወደ ተነሳንበት እንመለስ።)
በራሱ ሲገለፅ እንደሚሰማው ከሆነ ግራ ዘመም ፖለቲካ አጥብቆ የሚያምነው በማህበራዊ እኩልነት (egalitarianism) ነው። ይሁን እንጂ ወደ ተግባር ሲወረድ ጉዳዩ ሌላ ሆኖ ነው የሚገኘው። ለዚህ ማሳያዎቹ ደግሞ አስተሳሰቡና አቀንቃኝ/አራማጆቹ ለነባር እሴቶች ቁብ ባለመስጠታቸውና በኃይልና ጉልበት፤ ሁከትና ብጥብጥ ማመናቸው፤ ስር ነቀላዊነትን የተላበሰ አቋማቸውና ሌሎች ተግባሮቻቸው በተጨባጭ ማስረጃነት እየቀረቡባቸውና ለተለያዩ ትችቶች ያጋለጧቸው መሆኑ ነው። በመሆኑም ሁሌም ግጭት፤ ሁሌም ሁከት፤ ሁሌም ውድመት ነው።
(“ግራ ዘመም አስተሳሰብ በኢትዮጵያ አለን?” ብሎ የሚጠይቅ ካለ መልሳችን “ከፈረሱ አፍ” እንዲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “ኢትዮጵያ አትፈርስም፤ የምትፈርሰው እኛ ከፈረስን በኋላ ብቻ ነው።” ያሉትን ጠቅሰን ማለፍ ብቻ ነውሊሆን የሚችለው። ስላለፈው ከሆነ ደግሞ የዚህን ጽሑፍ መውጪያ ልብ ይበሉ።)“ለመሆኑ ለግራ ዘመም ፖለቲካ መንሰራፋት ሰበቡ፣ መነሻው ምንድን ነው?” የሚለው ለብዙዎች የጋራ ጥያቄ ሲሆን ምላሹም፤ በተጠቃለለ መልኩ ሲታይ የሚከተለውን ይመስላል።
በአንድ አገር የፖለቲካ ሕይወት ውስጥ ግራ ዘመም ርዕዮት ሊፈጠር የሚችልባቸው ዕድሎች ብዙ ሲሆኑ፤ ከሁሉም አይሎ የሚታየው ግን የዛች አገር መንግሥት (በተለይም የገዥ ፓርቲው) ንቅዘት ነው። ይህ ዝቅጠት፣ ለምሳሌ የተንዘላዘለ የሥልጣን ዕድሜ፣ ቅጥ ያጣ ሙስና፣ የወጣት ሥራ አጥነት ችግር በመቀረፍ ፈንታ እየጨመረ መሄድ፣ ኢ-ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል፣ አድልኦና መድሎ፣ የዲሞክራሲ እጦት፣ አምባገነንነት፣ የዜጎች ሰብአዊ መብቶች መጣስ ወዘተ ወዘተ ለግራ ዘመም፣ ስርነቀልነት፣ ጽንፈኛ አስተሳሰቦችና ርዕዮት መፈጠር፤ በተለያዩ ምክንያቶች የተገፉ ወገኖችን በተለይም ወጣቱን በማሰባሰብ ወደ ነውጥ ለመውሰድ ምቹ መደላድሎች (ፖለቲካል ኦፖርቹኒቲ) ናቸው።
በአንድ አገር የፖለቲካም ሆነ አስተዳደር ሕይወት ውስጥ እነዚህ አሉ ማለት የሚመራው (ገዥው) መንግሥት የመምራት አቅምም ሆነ ፍላጎት የለውም ማለት ስለሆነ ከነጭራሹ እንዲገረሰስ የግራ ዘመም ፖለቲከኞች ፅኑ ፍላጎት ነው። ለዚሁ ሲባልም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ አላማን ለማስፈፀም ከአገር ጠላት ጋር ከመተባበር ጀምሮ ከፍተኛ ዋጋ እስከ መክፈል ድረስ ይሄዳሉ (የጠላቴ ጠላት … እንዲሉ)።
ይህ ከላይ ያመለከትነው እንደየአገራቱ የፖለቲካ አየር ፀባይ የሚወሰን ሲሆን እንደ አጠቃላይ ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ግራ ክንፍ ፖለቲከኞች በቋሚነት የሚቃወሟቸውና ሙሉ ለሙሉ ከምድር ጠራርገን ካላጠፋናቸው የሚሏቸው ሦስት አንኳር ጉዳዮች ያሏቸው ሲሆን እነሱም ብሔር (nationality)፣ የኢምፔሪያሊዝም ተፅእኖ እና ብሄርተኝነት (nationalism) ናቸው። ወደ እኛው ስንመጣስ? በአንድ ወቅት ጽሑፋችን ለማሳየት እንደሞከርነው የኢትዮጵያ አብዮትን አስመልክቶ አብዝተው የታተሩት እንደሚሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ግራ ዘመምና መሰሎቹ አስተሳሰቦች ከፍተኛ ውድመትን አስከትለዋል። በዚህ ዓይነቱ አስተያየት የማይስማሙ ስለመኖራቸው ባይታወቅም ካሉም እውነቱ ይሄው መሆኑን ከሚቀጥሉት አናቅጽ መረዳት ይቻላልና እዚህም እንደግማቸው ዘንድ ርእሰ ጉዳያችን የግድ ይለናል።
በፕሮፌሰር መሳይ ሥራዎች ላይ ዳሰሳ ያደረጉት ዶክተር ቴዎድሮስ የተባሉ አስተያየተኛ በ”ውይይት” (ይመስለኛል) መጽሄት ላይ እንዳሰፈሩት ስርነቀላዊነትን ሲያራምዱ የነበሩ አብዮታዊያን ቡድን በተፈበረከ እመርታዊና ግብታዊ የርዕዮተ ዓለም ጥምቀት ምክንያት አሁን ያለው ታሪክና አገር በቀል እውቀትን የመንቀል/መገርሰስ ተግባር እውን ሊሆን ችሏል። ወደዚህ አደገኛና ጦሰኛ ምርጫ በመገፋፋት ረገድ የኃይለሥላሴን አውሮፓ ቀድ የትምህርት መርህ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።
ከዛም ይህ ስርነቀላዊነት እየቀጠለ ሄደና እዚህ ደረጃ ደረሰ። የአንድ አገር ጤናማ የእድገት ሥርዓት የሚገነባው በሁለገብ ነባራዊ ሀብቱ ላይ መሆኑን የረሳው የአብዮታዊያኑ ቡድን ውጤት ዛሬ ድረስ ሰንኮፉው እንዳልተነቀለ፤ ይህም ‘የትውልድ ክፍተት’ ፈጥሯል። “አገሪቱ ዛሬም ድረስ ትእቢትና ዘረኝነት በማሰው የጥፋት አፋፍ ላይ ትገኛለች።” በተለይ “የ’ያ ትውልድ’ ችግር ቅጥ ያጣ ስርነቀላዊነቱ ሲሆን፤ የዚህ ባህርይው ጠንቅ ደግሞ አውሮፓ ቀድ ዘመናዊ ትምህርት ያሰረፀበት የባህል ብዥታ፤ ማርክሲዝም-ሌኒኒዝምን በጭፍን መቀበሉና የሙጥኝ ማለቱ ነው። […] የትምህርት ሥርዓቱ ሌላው ጎጂ ውጤት ልሂቃዊነት በፈጠረው የቀላዋጭነት ቁራኛ” ይሆን ዘንድ መዳረጉ ነው።
በእነዚህ ሁሉ ላይ ዘረኝነት፣ ጭፍን ብሔርተኝነት፣ ግራ ዘመምነት፣ ጽንፈኝነት፣ የተሳሳተ የታሪክ አረዳድ፣ የመሪዎችና አብዮታዊያኑ ብሔራዊ ርዕይና አጀንዳ አልባነት፣ የሰብአዊነት መንጠፍ፣ የትምህርትም ሆኑ ሌሎች ተቋማት እየወረዱ መምጣት፣ የባህል ወረራ፣ አገር በቀል ምሁራንን ማፍራት አለመቻል፣ አድርባይነት፣ አገር በቀል ርዕዮት አለመኖር፣ የአሳታፊነት ችግር፣ ነባር ፍልስፍናንና እሴትን የመንቀል (“… ቀብረነዋል …” ያሉትን ባለስልጣን ያስታውሷል) ሁኔታ ስር መስደድ መኖርና መደራረብ እዚህ እዛሬው ችግር ላይ ሊጥለን እንደቻለም በመጻሕፍቱ መጠቀሱን ዳሰሳው አሳይቷል።
ለተሻለ ማጠቃለያ፣ አሁንም “ከፈረሱ አፍ …” እንዲሉ፣ የ”ያ ትውልድ” ደራሲ ክፍሉ ታደሰ “የግራ ርዕዮት ዓለምን ብዙዎቻችን ስንቀበል፣ ርዕዮቱ ሙሉ ለሙሉ ለችግሮቻችን መፍትሄ ያመጣል ብለን እናስብ ነበር፡፡ ግን ይሄን ርዕዮት ምን ያህል ተረድቸዋለሁ፣ ምን ያህል አብላልቼዋለሁ? የሚለውን ማየት ነበረብን፡፡ እኔ ብቻ ነኝ ትክክለኛ የሚለው ግትርነታችን ይቆጨኛል፡፡ ይሄ የአስተዳደጋችን ውጤት ነው፡፡ […] አሁን በኢትዮጵያ ያለው ሁለት ኃይል ነው፤ ብሔርተኛና ኢትዮጵያ የሚለው፡፡ የአሁን ፖለቲከኞች እኔ ብቻ ነኝ ትክክል ከሚለው የግትርነት ባህል ወጥተው፣ ሃሳብ መቀባበል አለባቸው፡፡” በማለት በገለፁት ፀፀትና ቁጭት እናብቃ።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 3/2013