ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባች የሚገኘውን ግዙፍ ግድብ ተከትሎ ግብጽ እና ሱዳን በየጊዜው የሀሰት መረጃዎችን እና ሙያዊ ማስረጃ የሌላቸው መረጃዎችን ሲለቁ ይስተዋላል። እነዚህም መረጃዎች በዓለም አቀፍ መድረኮች እና መገናኛ ብዙሃን ላይ ቀርበው በመሞገት እና እውነታውን በማሳወቅ ረገድ ደግሞ ከመንግስት ኃላፊዎች ባለፈ በእራሳቸው ተነሳሽነት ለሀገራቸው ጥቅም የቆሙ ምሁራን አሉ። ለሀገራቸው ጥቅም በተለይም በአባይ ጉዳይ ላይ አስረጂ ሆነው ለዓረቡ ዓለም መልዕክትን ከሚያስተላልፉ ኢትዮጵያውያን መካከል ደግሞ እጩ ዶክተር መካ አደም አሊ አንዷ ናቸው።
በይርጋለም ሜዲካል ኮሌጅ መምህር የሆኑት መካ አደም በተለይ በአልጀዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው በአረብኛ ስለህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያን አቋም በማንጸባረቅ ላይ ናቸው። በህዳሴ ግድብ ከታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት የሚደርሱ ተጽእኖዎች፣ ግድቡ የሚገኝበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጸጥታ እና ከኢትዮጵያውያን ስለሚጠበቁ ስራዎች እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች በተመለከተ ከእሳቸው ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያውያን በአባይ ወንዝ ላይ ያላቸውን ወቅታዊ ስሜት እና ግድቡን ለማጠናቀቅ በማሰብ የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንዴት ይገልጹታል?
መካ አደም፤- ኢትዮጵያውያን ከአባይ ወንዝ ተጠቅመን አናውቅም። ውሃችንንም አፈሩንም ይዞ እየተጓዘ ወደታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ነው የሚሄደው። በዚህ ጉዳይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘንድ ቁጭት ነበር። የፕሮጀክቱ መጀመር ሲነገር በወቅቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በደስታ ነበር የተቀበለው። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእራሳችን ወጪ ግድቡን ለመገንባት ያለውን ሲያዋጣ ቆይቷል። ደሃውም ሆነ ሀብታሙ በልጆቹም ስም ጭምር ቦንድ እየገዛ ነው እንዲገነባ ያደረገው። ከኢትዮጵያ ህዝባችን መካከል ከ21 በመቶው በላይ ከድህነት ወለል በታች ነው። ከአጠቃላይ ህዝባችን ውስጥ ደግሞ 65 ሚሊዮን የሚሆነው የኤሌክትሪክ መብራት አያገኝም።
ለገጠሩ ህዝብ መብራት እንዲያገኝ እና ለኢትዮጵያ እድገት ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑ ህዝብ ስላወቀ ከመነሻውም ህዝብ ደግፎታል። ለዚህም ነው ህዝቡ ያልተቋረጠ ድጋፍና ተሳትፎ የሚያደርገው። የኢትዮጵያውያን ተሳትፎ እና የግድቡን ወቅታዊ ስሜት ስንመለከተው እስከደም መስዋዕትነትም የደረሰ ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ እንደሆነ ይሰማኛል። ምንም አይነት ችግር ቢያጋጥም ለመጋፈጥ ዝግጁ የሆነው በርካታ ነው። በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት የሚኖር ኢትዮጵያዊ ግድቡን በመልካም ጎን ነው የሚያየው።
አረብ ሀገራት ጭምር ሰው ቤት ሰርተው በፍቃደኝነት ለግድቡ ቦንድ የሚገዙ በርካቶች ናቸው። እስካሁን ዘጠኝ ዓመት ሙሉውን ገንዘብ የሚያዋጡ ኢትዮጵያውያን አሉ። ጉሊት ላይ የሚሸጡ እናቶች ጭምር የተሳተፉበት እና የህዝብ ጉጉት ያለበት ፕሮጀክት ነው። እስከዚያው ድረስ የግድቡን ተሳትፎ ማጠናከር ያስፈልጋል። በተለያየ መንገድ ህዝብ እየሰጠ ያለው የሞራልና የገንዘብ ድጋፍ እስከመጨረሻው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነቴ ነው። እኔም ይህ ግድብ ተጠናቆ ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚ የሚሆኑበት ቀን ይመጣል የሚል ትልቅ ተስፋ አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ስለህዳሴው ግድብ በተመለከተ የአረቡ ዓለም የኢትዮጵያን እውነታ በእራሱ ቋንቋ እንዲያውቅ ከማድረግ አኳያ ብዙ አልተሰራም፤ እርስዎ ደግሞ በአልጀዚራ ጣቢያ ጭምር በመቅረብ መልዕክት ያስተላልፋሉ፤ ለዚህ መነሻ የሆነዎት ጉዳይ ምንድን ነው?
መካ አደም፡– እኔ ሱዳን ነው የተማርኩት፤ የመጀመሪያ ዲግሪዬንም እዛው ነው ያገኘሁት። ሱዳን ካርቱም ከተማ ላይ አባይ ወንዝን በተደጋጋሚ ጊዜ የማየት እድል ነበረኝ። ምን ያክል በወንዙ እየተጠቀሙበት እንዳሉ እና ከተማዋ ላይ በርካታ መዝናኛዎችን ገንብተው ገቢ እንደሚያገኙ አውቃለሁ። በተጨማሪም በወንዙ ዳር ሰፋፊ እርሻዎች ላይ እየሰሩ ብዙ ምርት ያገኛሉ። ይህን ሳይ እኛ ኢትዮጵያውያንም አንድ ቀን በአባይ ተጠቃሚ መሆን እንችላለን የሚል ስሜት ያሳድርብኝ ነበር። በኋላ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ እየሰራሁ ሳለ የህዳሴው ግድብ መሰረት ድንጋይ መቀመጡን መንግስት ይፋ አደረገ።
ያኔ በዩኒቨርሲቲው ጊቢ ተሰብስበን የግድቡ መጀመር እና ስለተሳትፏችን ሲነገረን በደስታ ነበር የተቀበልኩት። ሱዳን ጭምር ያሉ መምህራን ስሜትሽ ምንድነው ብለው ሲጠይቁኝ ደስተኛ እንደሆንኮ ነበር ስገልጽላቸው የነበረው። የግድቡ ግንባታ መከናወን ሲጀምር ደግሞ ሱዳኖቹም ሆነ ግብጾች የከፋ ቅሬታ አልነበራቸውም። በእራሳቸው አቅም እንዴት ይገነቡታል ብለው ስላሰቡ ይሆናል ብዙ ተግዳሮት አልፈጠሩም በወቅቱ።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግብጾች እውን ይሆናል ብለው ያልገመቱት እና ከፍተኛ ሃብት የሚጠይቀው የግድቡ ፕሮጀክት ህዝብ ከኪሱ እያዋጣ ማሰራት ሲቀጥል ጥያቄ ማንሳት ጀመሩ። ስለግድቡ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ያለውን ቁርጠኝነት ካዩ በኋላ ብዙ መሰናክሎችን ማቅረብ ጀመሩ። በመገናኛ ብዙሃን፣ በማህበራዊ ሚዲያ እና በአካል ጭምር ስለአባይ ግድብ መርዝ የታከለበትን የተዛባ መረጃ ማሰራጨት ጀመሩ። ግብጾች በህዝባቸው ላይ ድርቅ ሊመጣ ነው፣ ኢትዮጵያ ውሃ ልትከለክለን ነው፤ የሚል የሃሰት መረጃ ማሰራጨታቸውን ሲገፉበት ለምን እውነታውን ማሳወቅ አልጀምርም ብዬ ተነሳሁ።
እኛ ኢትዮጵያውያን በአማርኛ ቋንቋ ለውስጥ ፍጆታ ብቻ መረጃዎችን እናስተላልፋለን። በአንጻሩ ደግሞ እኛ የተከበብነው በአረቡ ዓለም ነውና የእኛ ድምጽ እንዴት ይሰማ የሚለውን አሰብኩ። እኔ በግሌ የአረቡን ዓለም ህዝብ መድረስ የምችልበት አቅም እያለኝ ለምን የበኩሌን አስተዋጽኦ አላበረክትም ብዬ ተነሳሁ። በእርግጥ ይህን ሳደርግ ተመችቶኝ አይደለም። አሁን ላይ በተለይ የሶስተኛ ዲግሪ እየተማርኩ ነውና ለትምህርቱም ብዙ ጊዜ እፈልጋለሁ።
ባለችኝ ጥቂት ጊዜ ግን ለሀገሬ ማበርከት ያለብኝን ነገር ላበርክት በሚል በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንም ሆነ በተለያየቱ መንገዶች ስለአባይ እና ኢትዮጵያ መረጃዎችን እያስተላለፍኩ ይገኛል። በአልጀዚራ አረብኛ ቋንቋ ጣቢያም ሆነ በተለያዩ መድረኮች የሀገሬን እውነታ ለዓለም በተለይ ለአረቡ ዓለም እያሳወቅኩ ነው። ለሀገሬ መብት ለመሟገት ያነሳሳኝ ጉዳይ እንግዲህ የግብጽ እና ሱዳን ባለስልጣናት የሚነዙት የሃሰት መረጃ ለማረም ከሚል የመነጨ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በህዳሴ ግድብ ጉዳይ ያለውን እውነታ ለማሳወቅ በግለሰብ ደረጃ ከሚደረጉ ጥረቶች ባለፈ በተደራጀ መልኩ የሚከወኑ ስራዎች እንደሚያስፈልጉ ምሁራን ይገልጻሉ፤ በዚህ ረገድ ምን አይነት አካሄድ ያስፈልጋል?
መካ አደም፡- እኔን መነሻ ብናደርግ በቅድሚያ በእራሴ ተነሳሽነት ስለግድቡ ለመጻፍ ሳስብ በፌስቡክ ነበር አንዳንድ መረጃዎችን በማስፈር ነበር የጀመርኩት። በአረብኛ ቋንቋ ስለአባይ እና የኢትዮጵያውያን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በተመለከተ እየጻፍኩ የተወሰኑ ሰዎች ጋር ለመድረስ ሞክሬያለሁ። የተለያየ ቦታ ያለን ሰዎች ለብቻችን በመንቀሳቀስ ብዙ ዓመታት ብናስቆጥርም የተደራጀ አካሄድ ግን አልነበረንም። በወቅት ከሱዳን እና ግብጽ እንዲሁም ከሌሎች ሀገራት ጓደኞቻችን ጋር ሃሳብ እንለዋወጣለን። በአቅማችን የእኛን ድምጽ ለማሰማት ሞክረናል።
በኋላ ላይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ከዲፕሎማቶቻችን አንዱ በሆኑት አቶ ሱልጣን አባጊሳ በኩል በአረብኛ ስለህዳሴ ግድብ የምንጽፍ እና የምንከራከር ሰዎችን የማሰባሰብ ሁኔታ ተጀመረ። እኔም እዛ ቡድን ውስጥ ተካትቼ በተደራጀ መልኩ መስራት ጀመርን። ከዚያም የሚታይ ውጤት ማምጣት ችለናል። የዓረቡ ዓለም ህዝቦች የኢትዮጵያን ችግር መረዳት ጀምረዋል። የመን፣ ሱዳን እና ሌሎችም ሀገራት የኢትዮጵያን ሃሳብ ደግፈው የሚጽፉ ሰዎችንም ማፍራት ችለናል። በቡድን ተቀናጅተን ስለኢትዮጵያ ጥቅም እና መብት በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ቀርበን በምናስረዳበት ወቅት ስራችንም ጎልቶ መውጣት ችሏል።
በቡድን መንቀሳቀሳችን ለሀገራችን መብት መከበር እና በአረቡ ዓለም ዘንድ ግብጾች የሚያሰራጩትን የተዛባ መረጃ ለማስተካከል እንድንችል እድል ፈጥሮልናል። እያንዳንዱ ሰው ጠጠር ሲወረውር ተሰባስቦ የእራሱ ውጤት ይኖረዋል በሚል በቡድን በተደራጀ መልኩ እየሰራን ነው። ስለዚህ በግለሰብ ደረጃ የሚደረጉ ጥረቶችን በቡድን መልክ ወስዶ ማሰራት ያስፈልጋል። በዚህ አካሄድ ሌሎችም ስለህዳሴው ግድብ ጉዳይ የተጠናከረ ስራ መስራት ቢችሉ ውጤቱ እንደሀገር የበለጠ ይሆናል።
ተጽእኖ በማህበራዊ ሚዲያውም ሆነ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ቀርበን ስለሀገራችን የምንሟገት ሰዎች በቡድን ብንንቀሳቀስ እንደሀገርም ተጽዕኖ ፈጣሪነታችንም የጎላ ይሆናል። ምንም ጥርጥር የለውም የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት የሃሰት መረጃዎችን በቡድን በተደራጀ መንገድ መከላከል ያስፈልጋል። ለዚህም የተጠና አካሄድን በመከተል የሀሰት መረጃዎች በሚሰራጩባቸው ቦታዎች መረጃን በመተንተን ህዝብ እውነታውን እንዲያውቅ ማድረግ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ሱዳን ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት የህዳሴውን ግድብ እንደሚጠቅማት ስትገልጽ ብትቆይም በአሁኑ ወቅት የግድቡን ግንባታ እንደሚጎዳቸው የመናገራቸው ምክንያት ምንድን ነው ብለው ያስባሉ?
መካ አደም፡– ይህ ሃሳብ የሁሉም ሱዳናዊ ሳይሆን የተወሰኑ የሱዳን ባለስልጣናት ነው ብዬ አስባለሁ። የህዝባቸውን ስሜት ሲታይ ግድቡ እንደሚጠቅማቸው ያውቃሉ። የተወሰኑ ባለስልጣኖቿ አቋም ደግሞ የግብጽ ተጽእኖ ያረፈበት ነው እንጂ ግድቡ የሚሰጣቸውን ከጎርፍ የመከላከል ጥቅም ሳያውቁት ቀርተው አይደለም። የግብጽ የስለላ ድርጅቶች በሱዳኖቹ ላይ የእራሳቸውን ፍላጎት ለመጫን ይሰራሉ።
በዚህም ተጽእኖ የሚደርስባቸው ባለስልጣናት አሉ። በተለይ የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያም አል ሳዲቅ አል መሐዲ ወደስልጣን ከመጡ በኋላ ስለኢትዮጵያ አንድም ጥሩ ነገር ተናግረው አያውቁም። ኢትዮጵያ ላይ የሚያሰሙት ንግግርም ጭምር የትዕቢት መልክ አለው። ሚኒስትሯ ወደግብጽ ለመሄድ ሲዘጋጁ ጠቅላይ ሚኒስትራቸው አብደላ ሃምዶክ እንደከለከሏቸው እና የሱዳን እና የግብጽ ጥያቄ የተለያየ መሆኑን እንደነገሯቸው ሰምቻለሁ።
ሱዳኖች ጭምር የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እያሉ ይጠሯታል። ይህ ግብጾች በሱዳን ባለስልጣናት ላይ የሚያደርሱት ተጽእኖ እንዳለ ማሳያ ነው። ስለዚህ የሱዳን አንዳንድ ባለስልጣናት በአባይ ግድብ ላይ የሚያሳዩት የተለዋወጠ አቋም የእራሳቸው ሳይሆን የሌሎች በተለይም የግብጾችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ነው። ባለፉት ዓመታት ግድቡ እንደሚጠቅማቸው ሲናገሩ ቆይተው አሁን ላይ እንደሚጎዳቸው የሚያስወሩት ወሬ የእራሳቸው ሃሳብ ሳይሆን የሌላ አካል አጀንዳ ይዘው በመቅረባቸው ምክንያት የመጣ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ሰሞኑን የህዳሴው ግድብ የሚገኝበትን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተመለከተ ሱዳኖች ውዥንብር ለመፍጠር ሞክረዋል፤ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የሚነካ ጉዳይ ከመሆኑ አንጻር እንደሀገር ምን አይነት ስራ ማከናወን ይገባል?
መካ አደም፡– ሱዳኖች በቤኒሻንጉል ጉዳይ ያነሱት ሃሳብ እንዲሁ በኢትዮጵያ ላይ ችግር ለመፍጠር አስበው ያመጡት ይመስለኛል። እነሱ የሚሉት ኢትዮጵያ እኤአ በ1959 የተፈረመው የቅኝ ግዛት የአባይ ወንዝ ክፍፍል ስምምነትን አልቀበልም ካለች እኛም በ1902 የተካሄደውን የድንበር ስምምነት አንቀበልም ነው። የውሃ ስምምነት እና የድንበር ስምምነት ፍጹም የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው። የአፍሪካ ህብረትም እንዳጸናው ደግሞ በየቅኝ ግዛት ጊዜ የተፈጸሙ ውሎች ተቀባይነት የላቸውምና የውሃ ክፍፍል ውሉ ዋጋ አይኖረውም። ስለዚህ የሚያነሱትን ሃሳብ የሚቀበላቸውም አይኖርም፤ እነሱ ያቀረቡት መከራከሪያ በመሰረቱ ምክንያታዊ አይደለም።
ከታሪክ አንፃር ኢትዮጵያን እና የቤኒሻንጉል ህዝብ ታሪክ ብናይ በአድዋ ጦርነት ወቅት እንኳን አምስት ሺህ ያክል የቤኒሻንጉል ተወላጆች ከአፄ ምኒልክ ጋር አድዋ ላይ መዝመታቸውን ተመዝግቦ ይገኛል። ስለዚህ ከ1902ቱ ስምምነቱ በፊትም ቢሆን ቤኒሻንጉል የኢትዮጵያ አካል በመሆኗ አሁን ውዥንብር ለመፍጠር የሚሞክሩት ነገር ውሃ የሚያነሳ አይደለም። ጉዳዩን ማንሳታቸው በቦታው የህዳሴ ግድብ ከመገንባቱ ጋር ተያይዞ ጫና ለማሳደር በማሰብ ነው። ግድቡ የሚገነባበት ቦታም የሱዳን ነው ለማለት ሞክረዋል። ነገሩን ሰፋ አድርጎ መመልከት ከተቻለ ግን ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ከመተከል እና አካባቢው ካለው የጸጥታ ሁኔታ ጋር አያይዞ መረዳት ያስፈልጋል።
አካባቢውን ለመበጥበጥ ስለሚሰሩ ነው ተቀባይነት ባይኖረውም ጉዳዩን የሚያነሱት። በአካባቢው ለዜጎች መፈናቀል እና ለህይወት መጥፋት ያደረሱ ችግሮች እንዳሉ ይታወቃል። በአካባቢው ያለውን ግጭት የሚያነሱት ደግሞ ሱዳን እና ግብጽ ናቸው። ሰሞኑን የግብጽ ሚዲያዎች ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ታጣቂዎች ብር እያዋጣን ክልሉ እንዲገነጠል እናድርግ እስከማለት ያደረሰ ንግግር አድርገዋል። ስለዚህ ጉዳዩን ቸል ማለት አያስፈልግም። ኢትዮጵያ ከቤኒሻንጉል ክልል ጋር በተገናኘ የሱዳንና የግብጽን እንቅስቃሴ በአጽንኦት መከታተል አለባት። ጉዳዩ በጣም አደገኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአካባቢው ያለውን እያንዳንዷን ጉዳይ መከታተል ያስፈልጋል።
በአካባቢው የሚፈጠሩ ግጭቶች በአፋጣኝ መፍትሄ በመስጠት ችግሩ ለውጭ ሃይሎች መግቢያ በር እንዳይሆን ማድረግ ይገባል። የህዳሴው ግድብ ትልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት ከመሆኑ አንጻር መንግስትም ግድቡ አካባቢ ጠንካራ ጥበቃ ያደርጋል ብዬ አስባለሁ። ኢትዮጵያ ከምታከናውነው ጠንካራ ጥበቃ ባለፈ የአካባቢው ጸጥታ እንዲረጋጋ በማድረግ ቤኒሻንጉል አካባቢ ያለውን ግጭት በዘላቂነት መፍታት አለባት። ያ ሲሆን የሱዳኖችም ሆነ የግብጾችን ችግር ፈጣሪነት መግታት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- 263 ድንበር ተሻጋሪ ሐይቆችና ወንዞች እንዲሁም ከ45 ሺህ በላይ ግድቦች ባሉበት ዓለም የታችኞቹ የተፋሰስ ሀገራት ያላቸው ተጽእኖ የተገደበ ቢሆንም በህዳሴው ግድብ ግን ግብጽና ሱዳን ይህን ያክል ተጽእኖ እንዲፈጥሩ ያደረጋቸው ምክንያት ምንድነው?
መካ አደም፡- በአባይ ወንዝ ውሃ እና በግድቡ ላይ ግብጽ እና ሱዳን ይህን ያክል ተጽእኖ መፍጠር የቻሉት በቅኝ ግዛት ውሎች ምክንያት ነው። በቅኝ ግዛት ውል መሰረት እ.ኤ.አ በ1959 ኢትዮጵያን ያገለለ ስምምነት በሱዳንና በግብፅ መካከል በዓባይ ውሃ ላይ ክፍፍል አድርገዋል። በስምምነታቸው መሰረት ለግብፅ 78 በመቶውን የወንዙን ውሃ እንዲሁም ለሱዳን 12 በመቶውን ድርሻ በመመደብ የአባይን ውሃ ለመከፋፈል ስምምነት ፈጽመዋል። ቅኝ ገዥዋ እንግሊዝ ስምምነቱን ስታስፈጽም የእራሷንም ጥቅም አይታ ነበር። ምክንያቱም በመስኖ የሚለማ የጥጥ እርሻ ሀገራቱ ላይ ነበራትና ኢትዮጵያን ያላካተተ ስምምነት እንዲፈጸም አድርጋለች።
ኢትዮጵያ ያኔም ከቅኝ ግዛት ነጻ የሆነች ሀገር ብትሆንም በስምምነቱ ሊያካፍሏት ግን አልፈለጉም። ለስምምነቱ ኢትዮጵያን አለመጥራታቸው የቅኝ ገዥዎች ንቀት ሊሆን ይችላል። በወቅቱ የነበሩት የኢትዮጵያ መሪ አፄ ኃይለስላሴ ስምምነቱን ተቃውመውታል። ተቃውሞውንም ለሚመለከታቸው አቅርበዋል። ስምምነት የፈጸሙት ሀገራት በአባይ ውሃ ላይ የበላይነት ይዘው ሲጠቀሙ ቆይተዋል። አሁን ላይ ግን ሱዳን እና ግብጽ ያንን ያለፈበት ስምምነት ይዘው እንሰራበታለን በማለታቸው ተጽእኖ እንዲፈጥሩ አስችሏቸዋል።
ቀድሞ በውሃው ሲጠቀሙ የነበራቸውን ልምድ በመያዝ ግድብ ሲገነባም ያ ጥቅማቸው እንዳይቀር አስበው ይሟገታሉ። ይህ ክርክራቸው እና ፍላጎታቸው ያመጣው እንቅስቃሴ ደግሞ ተጽእኖ እንዲፈጥሩ አድርጓቸዋል። በአባይ ውሃ ላይ እኩል እንድንጠቀም ያለመፈለግ ዝንባሌያቸው ብዙ ስለሚያናግራቸው ተጽእኗቸውን የጎላ ያደርገዋል። የቅኝ ግዛት ውል በአሁኑ ወቅት አይሰራምና ኢትዮጵያም የወንዙ ፍትሃዊ ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባት አምነው ሲቀበሉ እንዲሁም ግድቡም አልቆ ሙሉ በሙሉ ወደስራ ሲገባ ተጽእኖ የመፍጠር እድላቸውም በዚያው ልክ እየቀነሰ መምጣቱ አይቀርም።
አዲስ ዘመን፡- ግብጽ እና ሱዳን በሶስትዮሹ የግድቡ ድርድር ላይ አሜሪካ እና ሌሎች አካላት በቀጥታ ተሳታፊ እንዲሆኑ የመፈለጋቸው አዝማሚያ ምክንያት ምንድነው ብለው ያስባሉ?
መካ አደም፡– ምክንያታቸው አንድና አንድ ነው። የአሜሪካ መንግስትም ሆነ የአውሮፓ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በድርድሩ ቀጥታ እንዲገቡ የመፈለጋቸው ምክንያት በተዘዋዋሪ አካላት ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ነው። የአፍሪካ ህብረትን ባገለለ መልኩ ምዕራባውያኑን በመያዝ ግብጽ የእራሷን ጥቅም ለማስጠበቅ እንደምትችል ታስባለች። አምና ድርድሩን ስታስተባብር የነበረችው አሜሪካ በቀድሞ ፕሬዚዳንቷ ዶናልድ ትራምፕ በኩል ግብጽን ስትደግፍ እንደነበር አይተናል። ፕሬዚዳንቱ ግብጽ ግድቡን በመሳሪያ መምታት ትችላለች እስከማለት ያደረሰ እብሪት አስተጋብቷል። ግብጾችም ይህን የአሜሪካን እና የሌሎቹን ተጽእኖ ፈጣሪነት ለእራሷ እድል ልትጠቀምበት ትፈልጋለች።
ምዕራብያኑ ኢትዮጵያ ላይ ተጽእኖ ፈጥረው ማዕቀብ እስከመጣል ያደረሰ ችግር እንዲፈጥሩ እና የግድቡ ስራ እንዲቆም ከአፍሪካ ህብረት ውጪ ያለ አካል እንዲገባበት ይፈልጋሉ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን ከያዘው የጸጥታ ጉዳይ ነው በሚል ግድቡን አቁማችሁ ወደ ድርድር ግቡ ነው የሚለው። ይህንን ደግሞ ግብጾች ዓላማ አድርገው የሚደግፉት ጉዳይ ነው የሚሆነው። በዚህ መንገድ መዳኘት ደግሞ ለኢትዮጵያ ህዝብም ትልቅ ኪሳራ መሆኑ ይታወቃል።
መንግስት ደግሞ ይህንን አይነት ውሳኔ ለመቀበል የሚችልበት ጫንቃ የለውም። ምክንያቱም ድህነት ላይ ነው ያለነው፤ በየጊዜው የውጭ ምንዛሬ እየጨመረ ነውና ግድቡ ሲጓተት ወጪውም ያንኑ ያክል ይንራል። ስለዚህ በአፍሪካ ህብረት በኩል ውይይቱ እንዲቀጥል ነው ኢትዮጵያ ጫናዋን ማበርታት ያለባት። በትክክለኛው መንገድ ማሰብ ከተቻለ ደግሞ የአባይ ጉዳይ የሚያገባው የአፍሪካ ህብረት እንጂ ሌላው አይደለም። ምክንያቱም አባይ አፍሪካዊ ወንዝ በመሆኑ 11ዱም የናይል ተፋሰስ ሀገራት የሚገኙት አፍሪካ ውስጥ ነው።
ህብረቱ ደግሞ በትክክለኛ መንገድ በአባይ ጉዳይ ላይ ያሉትን ችግሮች ጠንቅቆ ያውቃል፤ አለመግባባቱንም ለመፍታትም አቅሙ አለው። ኢትዮጵያ በአቋሟ ጸንታ በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት ውይይቱን እንደምትቀጥል ስታሳውቅ ሱዳንና ግብጽም ተቀብለው መቀጠላቸው አይቀርም። ከቀናት በፊት ሱዳኖች በአፍሪካ ህብረት ስር ውይይቱ እንዲቀጥል እንፈልጋለን የሚል መግለጫም አውጥተዋል። ስለዚህ ተመልሰው ድርድር ላይ መቆየታቸው አይቀርም እና የግብጽና የሱዳንን ተጽእኖዎች ለመቀነስ የሶስትዮሹን ውይይት በአፍሪካ ህብረት ስር ማስቀጠል ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ከምታከናውነው ሁለተኛው ዙር ውሃ ሙሌት ጋር ተያይዞ ግብጽና ሱዳን ሊኖራቸው የሚችለውን ተገማች አካሄዶች በተመለከተ በኢትዮጵያ በኩል ምን አይነት ስራ ያስፈልጋል ብለው ያስባሉ?
መካ አደም፡- ግብጾች ከህዳሴው ግድብ ውሃ ሙሌት ጋር በተያያዘ ሰሞኑን ቀዝቀዝ ብለዋል። ከዚህ ቀደም የግብጽ ውሃና መስኖ ሚኒስቴር ለህዝባቸው ውሃ ሙሌቱ እንደማይጎዳቸው እና ችግር ቢፈጠር እንኳን መጠባበቂያ በቂ ውሃ እንዳለ ተናግረው ነበር። ይህም ሁለተኛውን የውሃ ሙሌት ኢትዮጵያ ከማከናወን የሚያግዳት ነገር እንደሌለ እያመኑ መምጣታቸውን ያሳያል። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ውሃ ሙሌት አከናውና ኤሌክትሪክ አላመነጨችም፤ አሁንም አታመነጭም እንዲሁ ነው ልሙላ የምትለው የሚል ነገር ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በበኩሏ ከሙሌቱ በኋላ ኤሌክትሪክ ማመንጨት እንደምትጀምር ገልጸዋል፤ ይህ የእኔም እምነት ነው።
ኢትዮጵያ ሙሌቱን አከናውና ኤሌክትሪክ ካመነጨች የጂኦፖለቲካዊ እይታ እንደሚቀየር ስለተገነዘቡ ባለፉት ወራት ሱዳንና ግብጽ ጩኸታቸው በርክቶ ነበር። ኢትዮጵያ በግድቡ አማካኝነት ኤሌክትሪክ ወደማመንጨት ከተሸጋገረች በአባይ ወንዝ ዙሪያ ባለው ፖለቲካ እና በቀጣናው ተጽእኖ ፈጣሪ መሆኗ አይቀርም። ስለዚህ ኢትዮጵያ በኩል ከዲፕሎማሲው ጎን ለጎን የግንባታ ስራዎችንም አጠናክራ መሄድ እና በተቻለ ፍጥነት የኤሌክትሪክ ማመንጨት ስራውንም መጀመር ይኖርባታል።
ለዚህ ስራ ደግሞ የሁለተኛው የግድብ ሙሌት በጊዜው መከናወኑ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። ግብጾች ይህ የኢትዮጵያ ዓላማ እንዳይሳካ እና ከሙሌቱ በኋላ ኤሌክትሪክ በማመንጨት ተጽእኖ ፈጣሪ እንዳትሆን የተለያየ ጥረት ማድረጋቸው አይቀርም። ለዚህ ምላሽ ደግሞ ከመንግስት ብቻ ሳይሆን ከተፎካካሪ ፓርቲዎች እና ከተለያዩ ተቋማትም የዲፕሎማሲ ጥረት ማድረግ ይጠበቃል። አባይ ግድብ የፖለቲካ አጀንዳ ሳይሆን የህዝብ ሀብት መሆኑን አምኖ መንቀሳቀስ ይገባል። በዚህ ጉዳይ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድነት መቆም መቻል አለባቸው።
እስካሁን ድረስ የፖለቲካ ፓርቲዎች በግድቡ ጉዳይ ከግብጽና ሱዳን የሚመጡ ጉዳዮችን ለመመከት ቢያንስ መግለጫ እንኳን ሲያወጡ አላስተዋልኩም። ግብጽ እና ሱዳን የጦርነት ነጋሪት እየጎሰሙ ባለበት ወቅት ከመንግስት ጋር አጋርነታቸውን ለማሳየት እና የጦርነት ነጋሪቱን ትክክል አይደለም ማለት መቻል ነበረባቸው። ከፓርቲዎች በተጨማሪም ህዝብም የውሃ ሙሌቱ ተከናውኖ ኤሌክትሪክ ማመንጨት እስክንጀምር እንኳን ቢያንስ በሀገሩ ጉዳይ በአንድነት መቆም አለበት። ይህ እና ሌሎች ጉዳዮች ተዳምረው ነው እነ ግብጽንም የልብ ልብ የሰጣቸው የሚል እምነት አለኝ። ሁለተኛውን የግድቡን ሙሌት ካከናወንን ግን በተጽእኖ ፈጣሪነቱም ቢሆን የሚችለን አይኖርም ብዬ አስባለሁ። ከዚያ በኋላ ነገሮችም እየቀዘቀዙ ኢትዮጵያ በእራሷ ሀብት የመጠቀም መብቷ ይበልጥ እየተከበረ ይሄዳል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ግብጽ እና ሱዳን በተለያዩ ጊዜያት የጦር ልምምድ ያደርጋሉ፤ ይህንን ያዩ ግብጽ በቀጥታ ጦርነት ልትጀምር ትችላለች ሲሉ ሌሎች ደግሞ የእጅ አዙሩን ጦርነት መጠንቀቅ ይገባል ይላሉ፤ በዚህ ጉዳይ ኢትዮጵያ ምን ይጠበቃል?
መካ አደም፡– ሀገራቱ የጦር ልምምድ ማድረጋቸው ኢትዮጵያን ለማስፈራራት ነው እንጂ በህዳሴው ግድብ ጉዳይ ፊት ለፊት ጦርነት ይገጥማሉ ብዬ አላስብም። አሊያም ግድቡን በመሳሪያ መምታት የሚችሉበት ሂደት አይኖርም። ይህን ካደረጉ በዓለም አቀፍ ህግም ከባድ ተጠያቂነት ስለሚያሳድር እስከማዕቀብ መጣል የሚያደርስ ቅጣት ሊያስከትልባቸው ይችላል። ስለዚህ ግብጽም ብትሆን ጦርነት ቀጥታ የምትከፍትበት ምክንያታዊነትም አይኖራትም። በሱዳን የድንበር ጥያቄን ሰበብ የኢትዮጵያን ድንበር ወራ መያዟን ካየነው ከህዳሴው ግድብ ውጥረት ጋር ተያይዞ በግብጽ ተጽእኖ የተፈጸመ መሆኑን መረዳት አያቅትም። የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጭምር ሱዳን ድንበሯን ለማስከበር በምታደርገው ጥረት እንደግፋለን ብለው በግልጽ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ጉዳዩን በትዕግስት በመያዟ ግጭቱ ከታሰበው በላይ እንዳይባባስ አድርጓል። ኢትዮጵያ የድንበሩ ጉዳይ በዲፕሎማሲ እንዲፈታ አቋም ባትይዝ ኖሮ ጥፋቱም የበዛ ይሆን ነበር። ይህ ደግሞ የግጭቱን አባባሾች አያስደስታቸውም። በታሪክ ካየነውም ግብጾች በ19ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሁለት ጊዜ ኢትዮጵያን ለመውረር ሞክረውም አልተሳካላቸውም። ስለዚህ በሱዳን የድንበር ጉዳይ አሳባ በተዘዋዋሪ ወረራ ለማካሄድ መሞከሯ ይገመታል።
በሌላ በኩል ግን በውስጥ ጉዳያችን ገብታ አማጽያኖችን እና በየቦታው ያኮረፉ ቡድኖችን ወደ መደገፍ መግባቷ አይቀርም፤ እያደረገችውም ነው። ነገሮችን ማጤን ከቻልን ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌት አከናውናለው ስትል ትልቅ ችግር ይፈጥራሉ። ዓምና የመጀመሪያው የውሃ ሙሌት ሊከናወን ሲል ነው የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ተፈጽሞ ግጭት ለመፍጠር የታሰበው። ይህ ተግባር ከግብጽ ጋር ግንኙነት አለው ብዬ አስባለሁ።
በጊዜው ግን የኢትዮጵያ ህዝብ አስተዋይ ነውና ችግሩን በቁጥጥሩ ስር አደረገው። ግብጾች ኢትዮጵያን ምስቅልቅል በማድረግ የግድቡ ስራ እንዲቆም የማያደርጉት ነገር አይኖርም። አስታውሳለሁ ህወሓት ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ከመፈጸሙ ሁለት ሳምንት አስቀድሞ አንድ የግብጽ ባለሀብት በትዊተር ገጹ 80 በመቶው የኢትዮጵያ ጦር መሳሪያ ያለው ትግራይ ነው፤ ትግራይ ክልል ደግሞ እያመጸ ነው ብሎ ነው የጻፈው።
ስለዚህ ግብጾች በኢትዮጵያ የማያባራ ግጭት ፈጥረው የአባይን ወንዝ ለብቻቸው ለመጠቀም የትኛውንም ቀዳዳ ለመጠቀም መፈለጋቸው አይቀርም። አሁንም ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት እንደሚከናወን ሲገለጽ ነው በተለያዩ ቦታዎች ግጭቶች መስፋፋታቸውን የቀጠሉት። ኢትዮጵያ ምስቅልቅሏ እንዲወጣ ለተለያዩ ቡድኖች ድጋፍ ያደርጋሉ። የውስጥ ችግራችንን ተጠቅመው ሰላማችንን ለማሳጣት ይሞክራሉ። አንዳንድ ተባባሪዎች ቢኖራቸውም የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ የሚጠቅመውን እና የሚጎዳውን ያውቃልና ደባቸው መጨረሻ ላይ ውጤት አያስገኝላቸውም።
አዲስ ዘመን፡- የግብጽና ሱዳን ሁለንተናዊ ተጽእኖ ለመቋቋም እና የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ኢትዮጵያ ውስጥ በተዘዋሪ መንገድ ዓላማቸውን እንዳያስፈጽሙ ለማድረግ ከህዝቡ ምን ይጠበቃል?
መካ አደም፡- የግብጽ እና የሱዳንን ጫና ለመቋቋም በቅድሚያ የውስጥ አንድነታችንን ማጠናከር ያስፈልጋል። ህዝብ ይህን መረዳት ደግሞ አለበት። በእርግጥ ችግር አለ፤ ነገር ግን አሁን ባለንበት ሁኔታ ቢያንስ የውጭ ጠላት ሲመጣብን መመከት የሚያስችል አንድነት ያስፈልገናል። ሱዳንም ብትሆን በድንበር አካባቢ ወረራ እንድታካሂድ የተነሳሳችው የውስጥ ችግሮቻቸንን አይታ ነው። አሁን ላይ ኢትዮጵያ ባጋጠሟት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ምክንያት ተዳከማለችና በዚህ ወቅት ማጥቃት እንችላለን የሚል ሃሳብ ይዘው ነው የሚንቀሳቀሱት።
በአባይ ጉዳይም ብናይ የቅኝ ግዛት ውሎችን ይዘው ለማጽናት እየተሯሯጡ ያሉት ኢትዮጵያ ተዳክማለች ብለው ስለገመቱ ነው። የውጭ ጠላቶች ኢትዮጵያ የሚቃጣባትን መመከት አትችልምና እኛም ማስፈራራትም እንችላለን ብለው በማሰባቸው የሚፈልጉትን ለማስፈጸም ጊዜው አሁን እንደሆነ ያስባሉ። ለዚህ ደግሞ መፍትሄው የውስጥ አንድነትን ማጠናከር ነው። የህዝብን ብሶት የሚያባብሱ ችግሮችን በመቀነስ ሀገር አንድ የምትሆንበትን መንገድ ማመቻቸት ይገባል። ይህ ሲሆን ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የልብ ልብ ያገኙ ሀገራት እንደማይሳካላቸው ይገነዘባሉ።
አዲስ ዘመን፤ ለሰጡን ሃሳብ እና ጊዜ ከልብ አመሰግናለሁ።
መካ አደም፡- እኔም ከልብ አመሰግናለሁ።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ግንቦት 3/2013