የኢትዮጵያ ዋና ከተማ የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባን ጨምሮ በአገሪቱ በርካታ ከተሞች አሉ። አዲስ አበባን ጨምሮ በአገሪቱ የሚገኙት በርካታ ከተሞች በጽዳት ጉድለት ይታማሉ። በተለይም ቀደም ባለው ጊዜ ከባህርዳር፣ ከመቐለ፣ ከሀዋሳ፣ ከአዳማ፣ ከድሬዳዋና ከደብረ ብርሃን ውጪ ያሉት ከተሞች ከጽዳት አንፃር እምብዛም ስማቸው ለአርአያነት አይጠቀስም ነበር።
ብዙዎቹ የአገሪቷ ከተሞች ከአራቱም ማዕዘናት እየጎረፈ ከሚከማችባቸው ሕዝብ ብዛት የተነሳ ከመጨናነቅ አልፎ ጽዳታቸው ሲጓደል ማስተዋል የተለመደ ነበር። የዋና መዲናችን አዲስ አበባ ጽዳት ጉድለትማ ለብቻው ሆኖ የኖረ ነው። የቆሻሻ ቅርጫት እስክትመስል ውበቷ ከመጠልሸቱ የተነሳ ውበቷን ለማድነቅ ብቅ እያሉ በሚጎበኟት የታናናሽ ከተሞቿ ነዋሪዎች ሳይቀሩ ‹‹ድንቄም የአፍሪካ መዲና›› በሚል ሽሙጥ በመተቸት እንደ ሽንኩርት ስትላጥ ኖራለች። ለአፍታ እንኳን ፀአዳ ሆና ‹‹በእናንተው ነው ለዚህ የበቃሁት›› የሚል ምላሽ መስጠት የሚያስችል አፍ እንኳን ሳታገኝ የኖረችው አዲስ አበባ ብቻ ሳትሆን ብዙዎቹ የአገራችን ከተሞች ከቱቦዎቻቸውና ከየጉያቸው በሚወጣ በደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ጠረን አፍንጫ የሚተነፍጉ የጤና ጠንቆች ነበሩ ቢባል ማጋነን አይሆንም።
‹‹ቆሻሻ ሀብት ነው›› የሚለው ነጠላ ዜማ በየከተሞቹ ተለቆ መቀንቀን ከጀመረና ውሎ ካደረም በኋላ የከተሞቻችን ጽዳት እንዲህ በቀላሉ ከቆሻሻ ነፃ መሆን የቻለና የተሻሻለ እንዳልነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ይመሰክራል። ይሄ ደግሞ አብዛኛው የከተሞች ነዋሪ የሆነ ሕብረተሰብ ካለው ቆሻሻን በአግባቡ የማስወገድ ልምድ ማነስ ጋር በጽኑ የተቆራኘ ነው። ከሕብረተሰቡ አንዳንዱ ግለሰብ በተለይ ክፉ ልማድ ያለበት መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ይሄን ለማረጋገጥ ጊቢውን አጽድቶ ጥራጊውን በአጥር በኩል በመንገድ ተላላፊ አናት ላይ የሚወረውረውን የከተማ ነዋሪ ማየቱ ብቻ በቂ ማሳያ ነው። በየከተሞቻችን በዚሁ ምክንያትም ብዙዎቹ የከተማ ነዋሪዎች በእንደዚህ ዓይነቱ ክፉ አመላቸው በመጠለፍ ነው ጤናቸው ሲታወክ የሚስተዋለው።
በአጠቃላይ በከተሞች አካባቢ የሚኖረው ሕብረተሰብ ቆሻሻን በአግባቡ የማስወገድ በቂ ግንዛቤ የለውም። ቢኖረውም አንድም አይጠቀምበትም ሁለትም ሲጠቀምበት አይታይም። ሦስትም ምን አልባት የሚኖርበት ከተማን ማቆሸሽን እንደ ባህል ይዞት ሊሆን ይችላል።
ከዚሁ ከከተሞች ጽዳት መጓደል ጋር አያይዘን ያነጋገርናቸው በአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የአካባቢ ብክለት ሁኔታ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ የአየር ብክለት ቁጥጥርና ክትትል ባለሙያ አቶ መሰረት አብዲሳ እንዳካፈሉን ሀሳብ ከተሞች ላይ አስፈላጊው ጥንቃቄ ካልተደረገ ጉዳታቸውም ከሚያስገኙት ጥቅም በላይ የሚሆንበት አጋጣሚ ብዙ ነው። ባለሙያው እንደሚመክሩት ከዕድገት ጋር ተያይዞ የሚያደርጓቸው የተለያዩ እንቅስቃሴዎች በጥንቃቄ መከናወን ይኖርባቸዋል። በተለይም ከተሞች ከፍተኛ ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ የሚያመነጩ በመሆናቸው አካባቢን በመጥፎ ጠረን ይበክላሉ። ለውስጣዊና ውጫዊ የጤና ጉዳትም ይዳርጋሉ። በአጠቃላይ ከተሞች ለመኖሪያ ተስማሚና ምቹ የማይሆኑባቸው በርካታ መጥፎ አጋጣሚዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ።
ለምሳሌ፦ በከተሞች ቆሻሻዎች በየቦታው ይጣላሉ። የከተማ ነዋሪው ቆሻሻን በአግባቡ የማስወገድ ልምድም አናሳ ነው። አንዳንዱ ነዋሪ ልቤ ውልቅ እስኪል ግቢዬን አፀዳሁ የሚለው የጠረገውን ቆሻሻ ከግቢው ውጪ አጥሩ ሥር በመጣል ነው። እንዲህ ያለው ቆሻሻ የማስወገድ ልምድና ስርዓት የአካባቢ ብክለትን በማስከተል ጉልህ ሚና ይጫወታል። ከፍተኛና መጥፎ ጠረን ያስከትልና ይረብሻል። በመጥፎ ጠረን አማካኝነት ጉንፋን ከማስያዝ ጀምሮ ከጊቢ ውጪ የተጣለው ቆሻሻ በጫማ አማካኝነት ተመልሶ ወደ ቤት የሚገባበት ጊዜ ብዙ ነው። እንዲሁም በንፋስ ኃይል በረቀቀ ሁኔታ አየር ውስጥ ገብተው ተመልሰው የሰውን ልጅ ጤና ይጎዳሉ። ተላላፊ ለሆኑ የጤና ችግሮች በማጋለጥ ክቡር የሆነውን የሰው ሕይወት የሚቀጥፉበት ሁኔታም ይስተዋላል።በአሁኑ ጊዜ እንዲህ ዓይነት የጤና እክሎችን ከሚያስከትሉት አንዱ በአግባቡ ባልተወገደ ቆሻሻ ምክንያት የሚመጣ የአካባቢ ብክለት እንደሆነም አቶ መሠረት ያስረዳሉ።
‹‹የአብዛኛው የከተማ ነዋሪ ሕብረተሰብ ቆሻሻ አወጋገድ ባህል ደካማ ነው›› ይላሉም። ባለሙያው እንዳከሉልንም ከዚህ ከከተማ ነዋሪ ሕብረተሰቡ ባህርይና ልማድ ወጣ ተብሎ ሲታሰብ ከተሞች በራሳቸው ለችግር ተጋላጭ ባህርይ እንዳላቸው ማየት ይቻላል። አሁን ላይ እንደሚታወቀው ከተሞች ከአየር ንብረት ለውጥና የሕዝብ ብዛት መጨመር ጋር ተያይዞ ለተለያዩ ችግሮች እየተጋለጡ ይገኛሉ። በተጨማሪም በቆሻሻ ክምችትና አወጋገድ ላይ ክፍተት ያላቸው መሆኑም ጎልቶ ይስተዋልባቸዋል። ከባለፈው እየተሻሻለ መምጣቱ እንደተጠበቀ ሆኖ አረንጓዴ ቦታዎች በአግባቡ ያልተጠበቁበት ሁኔታም በከተሞች ውበትና ጽዳት አጠባበቅ ላይ የሚያሳርፈው የራሱ የሆነ ተፅዕኖ አለ። በዚህ ምክንያት ብቻ ሳይሆን በከተሞች ውስጥና አካባቢያቸው በሚደርሰው ሕገወጥ ሰፈራና ደን ጭፍጨፋም ከተሞች የሚቆሽሹበት፣ ውበታቸው የሚጠፋበት ሁኔታ ይታያል። ቆሻሾች በፍሳሽ ማስተላለፊያ መስመሮች ወይም ቱቦዎች ተጥሎ መስመሮች የሚዘጉበት ለሙቀት መጨመር፣ለጎርፍ አደጋ ሲጋለጡ የሚታይበት አጋጣሚ ብዙ ነው። በከተሞች ውስጥና አካባቢያቸው ከሕዝብ ብዛት አንፃር ቆሻሻ ሊከማችባቸው መቻሉ አያጠያይቅም ብለዋል።
እኛም እንደታዘብነው በእርግጥም ከዚህ አኳያ ከተሞች ብዙ ሕዝብ በአንድ ላይ ተጠጋግቶ የሚኖርባቸው ቦታዎች መሆናቸውን መካድ አይቻልም። አራት ኪሎ አካባቢ በጎዳና ጽዳት ሥራ የተሠማሩት አቶ ቦንሳ ሞሲሳ እንደሰጡን አስተያየት ከጥግግቱ አንፃር ብዙዎቹ ከተሞቻችን አካባቢያቸውን አረንጓዴና ውብ ማድረግ ሲሳናቸው አስተውለዋል። የሥራቸው ባህርይ ሆኖ ከፍተኛ መጠን ባለው ቆሻሻ ንጽህናቸው ሲጓደል አስተውለዋል።
በተመሳሳይ ቦታና ሥራ የተሰማራችው ወጣት ዓለም ገብሩ እንደሰጠችን አስተያየትም ከተሞች ከንጽህና ጉድለት የተነሳ የነዋሪዎቻቸው ጤና ሊታወክና ለተለያዩ ከቆሻሻ ጋር ግንኙነት ላላቸው በሽታዎች ሊጋለጥ ይችላል። ሲጋለጥ የምታይበት አጋጣሚም ቀላል አይደለም። በመሆኑም አሁን ባለው ትውልድ ሊታሰብበት ይገባል። በእርግጥ ከዚህ አንፃር ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በዚሁ ትውልድ በተወሰኑ የአገራችን ከተሞች ቆሻሻን በብቃት በማስወገድና መልሶ በመጠቀም ዙሪያ እየተጀማመሩና እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች መኖራቸውን ታውቃለች። ጅምሩ ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባውና የሚበረታታ ነውም ባይ ነች።
ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተውም ቆሻሻን በብቃት የማስወገዱና መልሶ የመጠቀሙ ተግባር በጥቂት ከተሞች መጀመሩ ዕውነት ነው። የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ላቀው አበጀ ተግባሩ የተጀመረው የዛሬ አራት ዓመት እንደሆነም ነግረውናል። እንዳብራሩልን ቆሻሻ በከተሞች ገጽታና በነዋሪዎቻቸው ህልውና ላይ የሚያደርሰው ጥፋት የሚያሳስበው ትውልድ መፈጠሩ በራሱ ለአገራችን ከተሞች ትልቅ ብስራት ነው። እንደሳቸው ዕምነት ይሄ ለጉዳዩ ትኩረት የሰጠው ትውልድ በእርግጥም ዓይኖቹ ንዑዳን ናቸው። አእምሮውም ቢሆን በግንዛቤ የላቀና የረቀቀ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም።
ምክንያቱም የከተማ ቆሻሻን በብቃት ማስወገድና መልሶ መጠቀም በፍፁም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በእጅጉ የሚደነቅና የሚበረታታ ሀሳብ ፈጠራ ነው። የአእምሮ ልህቀት ልኬቱ ጥግ መድረሱንም ያመለክታል። ከተሞች በቆሻሻ ተውጠው ነዋሪዎቻቸው ለከፋ አደጋ ከመዳረጋቸው በፊት የሚታደግ መሆኑም አስፈላጊ ነው። ከተሞችን አረንጓዴና ውብ በማድረግ የሕብረተሰቡን ጤንነት ጠብቆ ምርታማ እንዲሆንም ያስችላል ነበር ያሉን ስለ ከተሞች ቆሻሻ በብቃት ማስወገድና መልሶ መጠቀም ስርዓት ሲያብራሩልን።
ስርዓቱ ከተሞች ጥሩ የሥራ አካባቢ እንዲሆኑ በማድረግ የላቀ ድርሻ ያበረክታል። በተለይ አሁን ላይ በየከተሞቹ የተጀመሩና እየተካሄዱ ያሉ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በማፋጠን በኩል ዓይነተኛ መፍትሄም መሣሪያም ነው። የከተሞችን ውበት ለማሻሻልም ጉልህ ሚና ይጫወታል።
ዳይሬክተሩ እንዳብራሩልን መንግስት ከተሞች ከቆሻሻና አካባቢ ብክለት ጋር ተያይዞ የተጋረጠባቸውን አደጋ በፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ዕቅድ ቅድሚያ ሰጥቶ ለማስወገድ ጥረት እያደረገ ይገኛል። በናማ ኮምፖስት ፕሮጀክት በስድስት የአገሪቱ ከተሞች እየተከናወነ ያለው ተግባር አንዱ ማሳያ ነው። ሆኖም ጥረቱ እንዲህ እንደ ናማ ኮምፖስት ፕሮጀክት የማህበረሰቡንና የአጋር ድርጅቶች ንቁ ተሳትፎና ድጋፍን በእጅጉ ይሻል። የእነዚህ አካላት ድጋፍ ካልታከለበት የሚፈለገውን ውጤት ያስመዘግባል ብሎ መጠበቁ አደጋች ነው ባይ ናቸው አቶ ላቀው።
ናማ ኮምፖስት ከመንግስት ጥረት ጎን ለጎን በአጋር ድርጅቶች እየተሰሩ ካሉ ሥራዎች መካከል አንዱ ተጠቃሽ ነው። ፕሮጀክቱ ፈርጀ ብዙ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ጠቀሜታ ያለው ነው። እየተሰራ ያለው በተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅትና ግሎባል ኢንቫይሮመንታል ፋሲሊቲ የሚደገፍ ነው። ፕሮጀክቱ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችሉ ከተሞችን መፍጠር ዓላማ አድርጎ የተቋቋመ ነው። ፋይዳውም እጅግ ብዙ ነው። ከተሞችን ንፁህ፣ ፅዱና አረንጓዴ ፣ ለኑሮ ተስማሚ እንዲሆኑ ያስችላል። የሥራ ዕድል በመፍጠርም ከፍተኛ ድርሻ አለው። በዋናነት ሊሰበስባቸው የሚችለውን የደረቅ ቆሻሻ ክፍል ወደ ኮምፖስትነት የሚቀይር ነው። የተቀየረው ኮምፖስት ደግሞ የተራቆቱ የከተማ ቦታዎችን ያለማል። በዚሁ አማካኝነትም የአካባቢ አየር በካይ ሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀትን መቀነስንም ዓላማው አድርጎ ይንቀሳቀሳል።
በአጠቃላይ ፕሮጀክቱ በድሬደዋ፣ በአዳማ፣ በባህር ዳር፣ በሀዋሳ፣ በቢሾፍቱ፣ በመቐለ ስድስት ከተሞች እንደ አገር እየተተገበረ ያለ ነው። በ6ሚሊዮን 917 ሺህ 123 ዶላር በጀት የሚከናወን ነው። ትግበራው እ.ኤ.አ. ከ2017 እስከ 2021 ድረስ ለአምስት ዓመት ይዘልቃል።
ዳይሬክተሩ እንደነገሩን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በበኩሉ ቆሻሻ ከምንጩ እንዲቀንስ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል። ከናማ ጋር በመሆን በአግባቡ እንዲሰበሰብ፣ ከተሰበሰበም በኋላ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል እያደረገ ያለውም ተግባር ማሳያ ነው።
‹‹ይሄ ፕሮጀክት ተግባራዊ ከሆነ አራት ዓመታትን ያስቆጠረ ነው›› ይላሉ አቶ ላቀው። እንዳከሉልን አሁን ላይ በፕሮጀክቱ የተገኙ ስኬቶች፣ ያጋጠሙ ችግሮች፣ ፕሮጀክቱ በቀጣይ ወደ ሌሎች የአገሪቱ ከተሞች የሚስፋፋበትና ህልውናቸውን በሚታደግበት ሁኔታ ሥራ እየተሰራ ይገኛል።
‹‹በከተሞች ከሚመነጨው ቆሻሻ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ብስባሽና ወደ ኮምፖስት ሊቀየር የሚችል ነው›› ብለውናል። በመሆኑም ቆሻሻን በአግባቡ በማስተዳደር ወደ ሀብትነት ለመቀየር ተቀናጅቶ መሥራት ግድ እንደሚልም አጫውተውናል። ቆሻሻን በአግባቡ ማስተዳደር ከቻልን ገንዘብ ነው። ካልቻልን ደግሞ በተቃራኒው አደጋው የከፋ መሆንም ጠቅሰውልናል።
ዳይሬክተሩ በተጨማሪ እንዳብራሩልን አደጋውን ለመቀነስና ስድስቱ ከተሞች ኮምፖስት በዘመናዊ መልኩ በማምረት ቆሻሻን ወደ ሀብትነት መቀየር እንዲችሉ ሚኒስቴር መሥሪያቤታቸው ትራክተር፣ ተርነርና ሌሎች ኮምፖስት ማምረት የሚያስችሉ ግብዓቶች ገዝቶ ማበርከት ችሏል። በዚህም 91 ሺህ ቶን ኮምፖስት ተመርቷል። እንዲሁም ከ21 ሺህ ሄክታር በላይ በከተሞችና በከተሞች ዙሪያ የሚገኙ የተራቆቱ ቦታዎችን መልሶ ማልማትም ተችሏል። እነዚህኑ ቦታዎች ደን በማልበስ ነዋሪዎቻቸው በጎርፍ እንዳይጠቁ የመከላከል ሥራ ተሰርቷል። ከ55 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎችም ቋሚና ጊዚያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 30/2013