መንገዶች ኢኮኖሚ የሚሽከረከርባቸው የደም ቧንቧዎች ናቸው፡፡ አምራቾችን ከገበያዎች፣ ሰራተኞችን ከስራ፣ ተማሪዎችን ከትምህርት ቤት፣ ህሙማንን ከሆስፒታሎች በማገናኘት መንገድ ለማንኛውም የልማት ተግባር ወሳኝ ነው፡፡ ለዚህም ነው የኢትዮጵያ መንግስት ትልቅ ትኩረት ከሰጣባቸው ዘርፎች አንዱ የመንገድ ዘርፍ የሆነው፡፡ ለዚህም ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ለዘርፉ የሚመድበው በጀት መጠን ነው፡፡ ከኢትዮጵያ አመታዊ በጀት ከፍተኛውን በመውሰድ ከሚጠቀሱ ዘርፎች አንዱ የመንገድ ዘርፍ ነው፡፡ ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት ባለፉት አስርት ዓመታት የሀገሪቱ የመንገድ ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ አድጓል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ለመንገድ ግንባታ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመትም በክልል መንግስታት የሚገነቡ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ሳይጨምር በፌዴራል መንግስት ለሚገነቡ መንገዶች ብቻ 56 ቢሊየን ብር በጀት ተበጅቷል፡፡ ሆኖም የመንገድ ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜ እየተጠናቀቁ አይደለም፡፡ የተለያዩ ችግሮች የመንገድ ፕሮጀክቶቹ በታቀደላቸው ጊዜ ተገንብተው እንዳይጠናቀቁ እንቅፋት እየሆኑ ነው፡፡
ሰሞኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሰራጨው ዘገባ እንዳመላከተው፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ መሪነት የፌዴራልና የክልል የስራ ሃላፊዎችና የመሰረተ ልማት ተቋማት ተወካዮች በተቀናጀ የመሰረተ ልማት አተገባበር ላይ ውይይት አድርገዋል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማት ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴም ከመንገድ ግንባታ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን አንስተዋል፡፡
የመንገድ ፕሮጀክቶች በተለያዩ ምክንያቶች እየተጓተቱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ለፕሮጀክቶቹ መጓተት ምክንያት እየሆኑ ካሉ ችግሮች አንዱ የመንገድ አልሚዎች ተቀናጅቶ ያለመስራት ችግር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት መንግስትን አላስፈላጊ ወጪ እያስወጣ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው ገምግሟል፡፡
በመሰረተ ልማት ላይ የተሰማሩ ተቋማት ስራቸውን ተናበውና ተቀናጅተው አለመስራታቸው ለመንገድ ፕሮጀክቶች መጓተት አንዱ ምክንያት መሆኑን ያነሳው ቋሚ ኮሚቴው ይህም የመንግስትና የህዝብ ሃብት እንዲባክን ከማድረግ ባለፈ ፕሮጀክቶቹ ጥራት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠሩ በውይይቱ ላይ ተገልጿል።
አገራዊ የካሳ ክፍያ አዋጅ በአግባቡ ተግባራዊ እየተደረገ አለመሆኑና ለመንገድ ግንባታ ብቻ የሚወጣው የካሳ ክፍያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄድ 10 ቢሊዮን ብር መድረሱም የተገለጸ ሲሆን፤ በአንዳንድ አካባቢዎች የመንገድ ግንባታ ሊጀመር መሆኑን ሲሰሙ የመንገድ ግንባታ በሚካሄድባቸው ቦታዎች ህገ ወጥ ቤቶችን በመገንባት ያልተገባ ካሳ የሚጠይቁ ግለሰቦች መበራከት የዘርፉ ተግዳሮት ሆኗል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ተገኝ እንዳሉት፤ መንግስት ለመንገድ ግንባታ ዘርፍ ከፍተኛ በጀት በመመደብ የመንገድ ግንባታን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ 184 ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ ናቸው፡፡ ከነዚህ መካከል 61 ፕሮጀክቶች በካሳ ክፍያና በጸጥታ ችግሮች ምክንያት ተጓተዋል፡፡ ይህም ለተጨማሪ ወጪና ጊዜ ከመዳረጉ ባለፈ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ለመስራት ማነቆ ሆኗል።
አንዳንድ የልማት ተነሺዎች የተጋነነ የካሳ ክፍያ መጠየቅ፣ ካሳ ከተከፈለ በኋላ ንብረታቸውን አለማንሳት፣ የተቋራጮች አቅም ማነስም ለፕሮጀክቶቹ መዘግየት በምክንያትነት የተነሱ ሲሆን፤ ከመንገድ መሰረተ ልማት ውጭ በኤሌክትሪክ፣ በውሃ፣ በቴሌኮምና በባቡር ፕሮጀክቶች ላይ ያለው የቅንጅት ክፍተትም ኪሳራ እያስከተለ መሆኑ ተነስቷል።
የፌዴራል የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ማስተባበሪያ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰዓዳ ከድር በበኩላቸው፤ “የመሰረተ ልማት ተቋማት ተናበው ባለመስራታቸው የመልካም አስተዳደር ችግር እየፈጠሩ ነው። ይህም የአገሪቷን ውስን ሃብት ለብክነት እየዳረገው ይገኛል።›› ብለዋል።
በ2006 ዓ.ም ተቋቁሞ በ2009 ዓ.ም ወደ ስራ የገባው ኤጀንሲው የአደረጃጀት፣ የማስፈፀምና የመፈፀም አቅም ውስንነት የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ እንዳይወጣ እንዳደረገው የተናገሩት ወይዘሮ ሰዓዳ፤ ኤጀንሲው ከአስፈጻሚ ተቋማትና ከክልሎች ጋር ተቀናጅቶ ለመስራት የሰው ሃይልና ሎጂስቲክስን ጨምሮ ችግሮች እንዳሉበት ገልጸዋል። ፕሮጀክቶች ሲዘገዩ በየደረጃው ያሉ አካላትን ተጠያቂ የማድረግ ስርዓት መዘርጋት እስካልተቻለ ድረስ ችግሩ ተባብሶ መቀጠሉ አይቀሬ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ የህዝብ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ የተሰማሩ ተቋማት ስራቸውን በጋራ ማቀድ፣ መገምገምና መፈፀም እንዳለባቸው አሳስበዋል። “በተለይም በካሳ ክፍያና በፀጥታ ችግር ግንባታቸው የተጓተቱትን 61 የመንገድ ፕሮጀክቶችን ችግር ለመፍታት በየደረጃው የሚገኙ የክልልና የፌዴራል ባለድርሻ አካላት መፍትሄ ማፈላለግ አለባቸው” ብለዋል።
የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አባላትም ፕሮጀክቶቹን በአካል ተገኝተው ክትትልና ድጋፍ እንዲያደርጉ አሳስበዋል። “በካሳ ክፍያ ላይ ሁሉም ክልሎች ወጥ የሆነ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት ይኖርባቸዋል” ብለዋል አፈ ጉባኤው። ምክር ቤቱ በካሳ ክፍያም ሆነ በፕሮጀክቶች መዘግየት ተጠያቂነት ላይ ያሉ የህግ ክፍተቶችን ፈትሾ ማስተካከያ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 30/2013