ኒኮሎ ማኪያቬሊን «መርዝ ስትሰጥ በጣፋጭ አድርገው» እንደሚለው ፈንጅ ቀባሪ ሃኪሞች የሚናገሯቸው ንግግሮች እውነት ያላቸው የሚመስሉ ፤ ተነበውም ተደምጠውም የማይጠገቡ በመሆናቸው ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ በዓለማች የሚገኙ ሰዎች የፈንጅ ቀባሪ ሃኪሞች አባባሎችን እንደእምነት ሊያመልኳቸው ምንም አልቀራቸውም፡፡ አባባሎቻቸውንም በመተንተን ለሃገራቸው ይጠቅማል ብለው የሚያስተምሩም ፖለቲከኞች ቁጥራቸው ቀላል አይደሉም፡፡
ወላጅ አባታችን አያ ጎዝጉዥው የእነዚህን ሃኪም አባበሎች «ሚስትህን ስደድ በሬህን እረድ ይላል ባለጌ ዘመድ» አይነት ነው ብሎ ስለሚያስብ የሃኪሞችን አባባል ማንበብም ሆነ ማዳመጥ ወባ የያዛቸው ያህል ያንቀጠቅጣቸዋል፡፡አያ ጎዝጉዥው የታወቀ ልብስ ሰፊ ነው፡፡ሰውየው የዋዛ አልነበርምና ምን አልባት እንደ ፈንጅ ቀባሪ ሃኪሞች አይነት ጠላት ቢመጣብን በሚል ስጋት በምስጥር እንነጋገርበታለን ብሎ በማሰብ ለራሱ እና ለሰፈሩ ብቻ መግባቢያ የሚሆን “ክላመኛ” የተባለ ቋንቋንም መፍጠር የቻለ ሊቅ ነው፡፡የአያ ጎዝጉዥው ቋንቋ የመፍጠር ብቃት ይኑረው እንጂ ኑሮው በችግር ገመድ የተተበተበ እና ከእጅ ወዳፍ የሆነ እና አሚካላ የበዛበት ነው፡፡የአያ ጎዝጉዥው ኑሮየ ከእጅ ወዳ አፍ የሆነው ፈንጅ ቀባሪ ሃኪሞቹ በሚፈፅሙብኝ ደባ ነው ብሎ ያምናል፡፡
አያ ጎዝጉዥው ከልጆቹ ብዛት እና ፈንጅ ቀባሪ ሃኪሞች በሚፈጠሩበት ደባ የተነሳ ለቤተሰቡ ሁሉን ነገር ማሟላት ስላልቻለ ‹‹ስቶይክ›› የሚባለውን ፍልስፍና የቤተሰቡ ዋና የመተዳደሪያ መርህ አድርጎ ከወሰደው ውሎ ማደሩን ሁሉም የሰፈሩ ሰው ያውቃል፡፡ ስቶይክ የሚባለው ፍልስፍና በእነአያ ጎዝጉዥው ቤተሰብ ውስጥ መቼ እንደተጀመረ ግን እርግጠኛ ሁኖ የሚያውቅ የለም፡፡ አንዳንዱ በአህመድ ግራኝ እና በአጼ ልብነድንግል በነበረው ጦርነት ነው የሚል አለ፡፡ግማሾቹ ደግሞ የጀርመኑ የታሪክ ተመራማሪ ጆብ ሉዶልፍ ኢትዮጵያ ከመጣ ጊዜ ጀምሮ ነው ይላሉ፡፡የተወሰኑት ደግሞ የቅኝ ገዥ አውሮፓውያን አፍሪካን መቀራመት ከጀመሩ ጊዜ አንስቶ ነው የሚሉም አሉ፡፡
በነገራችን ላይ ስቶይክ ሚባለው ፍልስፍና ደስታን መፍጠር ከፈለክ ባለህ ተደሰት የሚል የፍልስፍና አይነት ነው፡፡ የሰው ልጅ ፍላጎት እልቆቢስ በመሆኑ የአያ ጎዝጉዥው ልጆች በአባታቸው የቤት መተዳደሪያ መርህ ተቀርቅረው መኖር ባለመፈለጋቸው በተለያዩ ቦታዎች ተበታትነው ከአባታቸው እና ከሰፈራቸው ሰዎች በመራቅ መኖር ከጀመሩ ጊዜውን እርግጠኛ ሆኖ የሚያውቅ የለም፡፡ከመበታተናቸው የተነሳ አይደለም የሰፈሩ ሰው የት እንዳሉ ሊያውቅ ይቅር እና እርስ በርሳቸው እንኳን የት እንደሚኖሩ አያውቁም፡፡ይሁን እንጂ ከአባታቸው እርስት እንዳልወጡ ሁሉም ሰው ያውቃል፡፡
የአባቴን ብለቅ ሆኖባቸው ልጆቹም በሄዱበት ለራሳቸው እና ለሰፈራቸው ሰዎች ለብቻ የሚሆን ቋንቋንም በመፍጠር በፊት የነበራቸውን ማንነት እርግፍ አድርገው እረሱት፡፡ይህ በቋንቋ የመከፋፈሉ አካሄድ ሰፍቶ እና ተንሰራፍቶ ልጆች እና የልጅ ልጆች ዝምድናቸውን ረስተው መነታረክ ጀምረዋል፡፡የዚህ ንትርካቸው ምክንያት ደግሞ የፈንጅ ቀባሪ ሐኪሞች ምክር ነው የሚለው አያ ጎዝጉዥው የፈንጅ ቀባሪ ሐኪሞችን ልክ የኢቦላ ያህል ነው የሚፈራቸው እና የሚጠነቀቃቸው ፡፡
የአያ ጎዝጉዥው ልጆች ከአንድ አባት እንዳልተፈጠሩ ሁሉ ፈንጅ ቀባሪ ሃኪሞች የሚመክሯቸውን ምክር በመስማት የራሳቸውን የጎበዝ አለቃ በማበጀት በራሳችን የጎበዝ አለቃ ካልተመራን እንደዩጎዝላቪያ እንበታተናለን እየተባባሉ እርስ በርስ መነታረኩን ፋሽን አደርገው ይዘውታል፡፡ የሚገርመው ደግሞ ‹‹የሰው ሞኝ አንድ እንጨት ያስራል›› እንዲሉ ሁል ጊዜ የዩጎዝላቪያን መበታተን የሚነግሩን የጎበዝ አለቆች እንደዩጎዝላቪያ ከመበታተን የሚያሽር መድሃኒት መቀመም አለመቻላቸው ከሌሎች ሀገራት የማይማሩ የዓለም መሳቂያ መሳለቂያ ቂሎች አስባሉን፡፡
ይህ ንትርካቸው ለፈንጅ ቀባሪ ሃኪሞች በማጀታችን እንደፈለጉ እንዲሆኑ የተመቻቸ ነው፡፡አያ ጎዝጉዥው እና የአባቱን የአያ ጎዝጉዥው ሃሳብ የሚጋራው አስቻለው የተባለው ልጃቸው መቼ ይሆን አጨፋጭፍው ሊጨርሱን የሚችሉት በሚል ጭንቀት ወገባቸው ጎብጦ ለበሽታ ተጋልጠው ጤናቸው ከታወከ ዘመኑ አይታወቅም፡፡
«ለራበው ሰው ቆሎ ለቁልቁለት በቅሎ» እንዲሉ ምነው የእኛ ፖለቲካዊ ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር ፈንጂ ቀባሪ ሃኪሞች የፈጸሙብን ደባ መሆኑን እያወቃችሁ ፈንጅ ቀባሪዎችን በመፋለም ለራስ ጥላ ለአገሩ ከለላ በመሆን ከአባታችሁ ጎን መሰለፍ ሲገባችሁ ምነው ጠላቶቻችን ሊያጠፉን በፈጠሩልን ቦይ ለመፍሰስ ቋመጣችሁ?
«ለራሱ አያውቅ ነዳይ ቅቤ ለመነ ለነዋይ» እንዲሉ ለራሳቸው ማወቅ የተሳናቸው የጎበዝ አለቆች በመካከላቸው ምንም አይነት የሚዳሰስ ዓላማ ሳኖራቸው የምርጫ ጊዜ በደረሰ ቁጥር ምረጡን እያሉ ያላዝናሉ፡ ፡ምን እንድታደርጉን እንምረጣችሁ? እርስ በርስ እንድታደባድቡን?
ዓላማ ስል አንድ ውሻ የነበረው ሰው ተረት ትዝ አለኝ፡፡ አንድ ገበሬ በአካባቢዊው የሚያልፉትን መኪኖች በአይነ ቁራኛ ከሚጠብቅ ከውሻው ጋር መንገድ ዳር መቀመጥ ያዘወትር ነበር፡፡ውሻው አንድ መኪና ሲመጣ ካየ ወዲያውኑ ወደ መንገዱ እየሄደ በመጮህ ወደ መኪናው ሊደርስበት ይሞክራል፡፡አንድ ቀን ጎረቤቱ ውሻህ መኪና የሚይዝ ይመስልሃል ብሎ ቢጠይቀው «እኔን የሚያስጨንቀኝ እሱ ሳይሆን ውሻው መኪና መያዝ ቢችል ምን ሊያደርገው እንደሚችል ነው፡፡» በማለት ገበሬው ይመልስለታል፡፡ብዙ ሰዎች በህይወታቸው ትርጉም የለሽ ግቦችን እንደሚያሳደድ ውሻ ይሆናሉ፡፡ የእኛም የጎበዝ አለቆቻችን ብዙዎቹ እንዲህ ውሻ ዓላማ ያላቸው አይመስለኝም፡፡
ምርጫ የተባለው ፤ ፈንጅ ቀባሪ ሃኪሞች የፈጠሩት ነገር ሲመጣ የአያ ጎዝጉዥው ልጆች በጎበዝ አለቃቸው ተወክለው ምረጡኝ እያሉ ቁምስቅላችንን ያሳዩናል፡፡ ይሁን እሺ እንምረጣችሁ ፤ እንድንመርጣችሁ ግን የመነሻ ሃሳባችሁን እና ዓላማችሁን ንገሩን ስንላቸው አንድም ቀን የመነሻ ሃሳባቸውን እና ዓላማቸውን አስረግጠው ነግረውን አያውቁም፡፡የጎበዝ አለቃህ እኔ ብቻ ነኝ እያሉ አንድ ሁለት ቀን እርስ በርስ ይሰዳደቡና አየኸው አየሽው ለመባል እና ለሰዎች የቡና መጠጫ የምትሆን ስድድብ ብቻ ነው የሚያደርጉት፡፡
በዚህ ስድድባቸውም ከፈንጅ ቀባሪ ሃኪሞች በእጅ አዙር ወይም በቀጥታ የገዙትን በርበሬ ሳያነፍሱ እስከነጠጠሩ ዋጡ ይሉናል፡፡የምንውጠው በርበሬ ግን ይንቀዝ አይንቀዝ፣ በአፍላቶክሲን ይጠቃ አይቃ አናውቅም፡፡ብቻ በግድ እንድንውጠው እንደረጋለን፡፡ ምነው ፈጣሪ በግዳጅ የአልተጣራ ነገር ዋጡ ብሎ በጉልበት ከሚያንገላታ ፍርደ ገምድሎች የሚገላግለን መለኛ ቢጥልልን፡፡ ይህን ስል አንድ በአፋሮች የሚዘወተር ተንኮለኛው ቀበሮ የሚል ተረት ትዝ አለኝ፡፡
በአንድ ወቅት ላም ያላት ሰጎንና በሬ ያለው አንበሣ ነበሩ፡፡አንበሳውም ሰጎኗን እንዲህ አላት፡፡ “አንቺም ላምሽን እኔም በሬዬን ለምን አብረን ወደ ግጦሽ አንወስዳቸውም? እንዲህ ካደረግን ሁለታችንም እረኝነት ከምንውል አንድ ቀን አንቺ አንድ ቀን ደግሞ እኔ እየተፈራረቅን እንጠብቃቸዋለን፡፡” አላት፡፡በዚህ ሁኔታ በኑሮዋቸው ተደስተው ለሁለት ወራት ከኖሩ በኋላ የሰጎኗ ላም ታረግዛለች፡፡
ከእለታት አንድ ቀን ታዲያ ላሚቷ መውለጃዋ በደረሰ ጊዜ አንበሳው ሁኔታውን ስላየ እንዲህ አለ፡፡ “ሰጎን ሆይ! ግዴለም አንቺ አረፍ በይና ሰሞኑን እኔ እጠብቃቸዋለሁ” ይላታል፡፡
በዚህ ጊዜ ላሚቷ ስትወልድ አንበሳው ምን ቢል ጥሩ ነው “ያንቺ ላም ትልቅ የወፍጮ ድንጋይ የእኔ በሬ ደግሞ ጥጃ ወልደዋል” ይላታል ፡፡ ሰጎኗም “ይህ በጣም አስቂኝ ነገር ነው እንዴት ላም ድንጋይ በሬ ደግሞ ጥጃ ሊወልድ ይችላል” አለች፡፡ አንበሳውም “አይደለም የአንች ላም የወለደችው ድንጋይ ነው የኔ በሬ የወለደው ጥጃ ነው ” አለ፡፡በዚህም ሁኔታ ትልቅ ፀብ ውስጥ ስለገቡ ይዳኙ ዘንድ ሰጎን እና አንበሳ በጫካ ውስጥ ያሉትን ሁሉንም እንስሳ ይጠሯቸዋል፡፡ ትልቅ ስብሰባም ተካሄደ፡፡ነገር ግን የአንበሳው በሬ ጥጃ ሊወልድ አይችምል ብሎ ደፍሮ የሚናገር ጠፋ፡፡
ታዲያ አንድ ብልጣ ብልጥ ቀበሮ እንዲህ አለ፡፡“እኔ ወደ ስብሰባው አልመጣም፡፡ነገር ግን በፍጥነት እየሮጥኩ በስፍራው ስለማልፍ ፍርዱን እንድናገርልህ ልትጠይቀኝ ትችላለህ፡፡” በስፍራውም ቀበሮ እየሮጠ ሲያልፍ እንስሳቱ በሙሉ “አቶ ቀበሮ፣አቶ ቀበሮ፣ እባክህ ወደዚህ ና፡፡” እያሉ ተጣሩ ቀበሮውም “አልመጣም፣ እቸኩላለሁ፣ አባቴ በምጥ ላይ ስላለ ቢላዋ ይዤ እየሮጥኩ ነው፡፡በዚህ ላይ ጀንበሯም እየጠለቀች ነው፡፡ዝናቡም መጥቷል፣ ስለዚህ ምጥ ላይ ያለውን አባቴን ይረዱት ዘንድ ላግዛቸው ቢላዋ ይዤ እየሮጥኩ ነው፡፡” አላቸው፡፡አንበሳውም እንዲህ አለ፡፡“አንተ ቆሻሻ፣ አባትህ እንዴት ምጥ ሊይዘው ይችላል? ወንድ አይደለም እንዴ?”
ቀበሮውም “ስለዚህ ሌላ ቆሻሻ ነገር እንድነግርህ ትፈልጋለህ? በሬ ጥጃ ወለደ ብዬ!?” ብሎት ሮጦ ሔደ፡፡ አንበሳውም ቀበሮውን ተከትሎት ሲሮጥ ሰጎኗ ላሟንና ጥጃዋን ይዛ ሄደች፡፡ምናለበት እንደቀበሮው ሁሉ መለኞች ፖለቲከኞች ለእኛም ሃገር ቢጥልላት፡፡
በአጠቃላይ የአያ ጎዝጉዥው ልጆች ምርጫ ሲደርጉ የሚሉት ነገር አሳን እስከስንትሩ ዋጡ አይነት ነው፡፡እንቢ ብንል ደግሞ ምናልባት ምርጫውን ካሸነፉ ማዳበሪያ ፣ መታወቂያ እና ሌላ ነገር ቢከለክሉንስ ብለን እንፈራለን፡ ፡ስለሆነም የያዙት ሃሳብ ሳይብራራልን፣ ሳናውቀው መጥፊያችንን እስከስንጥሩ ለመዋጥ ተገደናል፡፡
የሚገርመው እኮ የጎበዝ አለቆቻችንን የተደራጁት በእኛ ፍላጎት ሳይሆን በእነ ወይዘሮ ምስር ሃሳብ አመንጭነት በፈንጂ ቀባሪ ሃኪሞቹ የተንኮል ሴራ ነው፡፡ «በሞኝ ክንድ ዘንዶ ይለኩበታል» እንዲሉ የአያ ጎዝጉዥውን ልጆች አንድነት ለማጥፋት ፈንጂ ቀባሪ ሃኪሞች እየተጠቀሙት ያለው የአያ ጎዝጉዥውን ልጆች እርስ በርስ ማፋጀት ነው፡፡
«በሞኝ ክምር ዝንጀሮ ልጇን ትድር» እንዲሉ በእኛ እልቂት እነሱ ሻምፓኝ እየተራጩ ለመጨፈር የተጓዙትን እርቀት ምን ያህል እንደሆነ እያዩ የጎበዝ አለቆቻችን ፈንጅ ቀባሪዎቹ በቃኙት ቅኝት አስክስታ ምን የሚሉት ነው፡፡
የሰው ሞኝ አንድ እንጨት ያስራል፡፡የእኛ ጎበዝ አለቆች ሃሳብ ስለሌላቸው ሁሌም ለምርጫቸው መወዳደሪያ የሚያደርጉት ፈንጂ ቀባሪዎቹ እርስ በእርስ እንድንባላ በፈለሰፉልን ጎሳን መሰረት አድርጎ ነው፡፡መቼ ነው ለመስማማት የምትስማሙት፡፡እስኪ ከስህተታችሁ ተምራችሁ የማይሞት ታሪክ ሰርታችሁ እለፉ፡፡
ከመቶ ዓመት በፊት አንድ ሰዉየ የጠዋቱን ጋዜጣ ሲመለከት የሙታን ስም ዝርዝር በሚወጣበ0ት አምድ ላይ የገዛ ስሙ ተለጥፎ በማንበቡ ከመገረሙም በላይ እጅጉን ደነገጠ፡፡ ጋዜጣው ላይ በስህተት የእሱን መሞት የተመለከተ ዘገባ ወጥቷል፡፡መጀመሪያ ላይ በጣም ተሸበረ አለሁ ወይስ ሞቻለሁ ሲል አሰበ፡፡ቀልቡን ከሰበሰበ በኋላ ደግሞ ስለሱ ሰዎች ምን እንዳሉ ለማወቅ ጉጉት አደረበት፡ ፡በአምዱ ላይ የተጻፈው ፅሑፍ «የደማሚቱ ንጉስ ሞተ» ይል እና በማስከተል ሟቹ በህይወት ዘመኑ «የሞት ነጋዴ ነበር» ይላል፡፡ ይህ ሰው ደማሚትን በመፈልሰፉ የተነሳ የሞት ነጋዴ መባሉን ሲያነብ ሰዎች የሚያስተውሉኝ በዚህ መልኩ ነውን? በማለት ራሱን ጠየቀ፡፡በዚህ መልኩ መታወስ እንደማይኖርበት ውሳኔ ላይ ደረሰ፡፡ከዚያን ቀን ጀምሮ ስለሰላም ለመስራት ተነሳ፡፡ይህ የደማሚት ንጉስ የተባለው ሰው አልፍሬድ ኖቬል ሲሆን ባለንበት ዓለም የታላቁ የኖቬል ሽልማት ይታወሳል፡፡
እንደ አልፍሬድ ኖቬል ሁሉ እናንተም የጎበዝ አለቆቻችን ወደ ኋላ በመመለስ የራሳችንን እሴቶች ፈተሽ ማድረግ ይገባችኋል፡፡ምን ቅርስ አላችሁ? እንዴት መታወስ ትችላላችሁ? ስማችሁ የሚታወሰው በከበሬታ እና በፍቅር ነውን? ሰዎች ይንፍቋችሁ ይሆን? ብላቹ ጠይቁ፡፡
«ሆድ የኔ ነው ሲሉት ቁርጠት ሆኖ ይገላል፡፡» እንዲሉ አያ ጎዝጉዥው ልጆች ፈንጂ ቀባሪ ሃኪሞች ከፈጠሩብኝ ችግሮች እና በደል አውጥተው ወደፊት ያራምዱኛል ብዬ ስመካ «ለመከራ ያለው መነኩሴ ዳዊቱን ሽጦ አህያ ይገዛል» ሆኖብኝ የአያ ጎዝጉዥው ልጆችም እንኳንስ ከችግር ሊጠብቋቸው ይቅር እና በዓለም የሚታወቁበትን አንድነታቸውን ሸጠው መበታተን ራሳቸውን ለባርነት በነጻ ለመሸጥ ሲነታረኩ ተመለከትኩ፡ ፡በዓለም ፖለቲካ ሩጫ ውስጥ ራሱን ለሚያወዳድር ሰው በየመን ፣ በሶሪያ ፣ በኢራቅ ፣ በቬትናም ወዘተ ፈንጂ ቀባሪ ሃኪሞች የፈጸሙትን ጥፋት መዘንጋት «ሰው ገበያ ሂዶ ማንቀላፋት ሁለተኛ ጥፋት» አይነት ነው፡፡
የአያ ጎዝጉዥው ልጆች በፈንጅ ቀባሪ ሃኪሞች የተመረዘ ሃሳብ በመነደፋቸው አንድነታቸውን እያጡ ነው፡፡እኛም ሱዳን እና ግብፅ ሊጣላ የመጣ ሰበብ አያጣ እንዲሉ ግብፅ እና ሱዳን በየቀኑ እኛን የሚጣሉበት ሃሳብ እየፈበረኩ ይነታረኩን ይዘዋል፡፡
መቼም አያ ጎዝጉዥው ነገሮችን በቀላሉ ለማስረዳት ምሳሌያዊ አነጋገር ይቀናዋል፡፡«ላይኛው ከንፈር ለክርክር ታችኛው ከንፈር ለምስክር፡፡» ይህን አካሄድ የምትሄዱ የጎበዝ አለቆች አንድ ጊዜ የጎበዝ አለቃ ለሆናችሁት ህዝብ አሳቢ ስትመስሉ አንድ ጊዜ ደግሞ የጠላት አገር ጉዳይ አስፈጻሚ ደላላ ስትሆኑ የሚያያችሁ ህዝብ እንደሚፍርባችሁ ምናለበት አንዴ እንኳን ቆም ብላችሁ ብታስቡ ብሎ በልጆቹ ቢያንቧርቅም በፈንጂ ቀባሪዎቹ ተንኮል ተንሻፈው አያ ጎዝጉዥውን ማን ይሰማቸው?
በመጨረሻም በማህተመ ጋንዲ ሰባቱ መጥፎ ሃጢያቶች የተባሉትን ትመለከቱት ዘንድ የጎበዝ አለቆቻችን እየጋበዝኩ ልሰናበት፡፡ ያለስራ የተገኘ ሃብት ፣ ህሊና የማይቀበለው ደስታ ፣ ምግባር ያልታከለበት እውቀት ፣ ግብረገብ የጎደለው ንግድ ፣ ሰብዓዊነት የሌለበት ሳይንስ፣ መስዋትነት የማይከፈልበት ሃይማኖት እና መርህ የሌለው ፖለቲካ የእሴቶቻችን መዛባት እና መጓደል ያንጸባርቃሉ፡፡ስለዚህ ጉድለቶቻችንን ለማረም በማህተማ ጋንዲ እንደሃጢያት ከሚታዩት እሳቤዎች ተቆጠቡ የዕለቱ መልዕክቴ ነው ፡፡
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2013