ቤተመንግሥት፣ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር፣የድል ሀውልት፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣የጤና እና ሌሎችም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሚገኙበት በአራዳ ክፍለከተማ ውስጥ ነው፡፡በመልሶ የቤት ልማት መርሐግብር መንደሮችና የተለያዩ ተቋማት ፈርሰው ነዋሪው ወደሌላ አካባቢ የሄደ ቢሆንም በአንድ አካባቢ ተጠጋግቶ የሚኖርበት መንደር እንደነበር ማስታወስ ይቻላል፡፡ በአካባቢው አሁን በሚታየው በአዲስ መልኩ የተለያየ የህንፃ ግንባታ ከመከናወኑ በፊት በሥፍራው ከጭቃ የተሰሩ ቤቶች ነበሩ፡፡አራዳ፣ፒያሳ፣ እሪ በከንቱ፣ ባሻ ወልደችሎት… የመሳሰሉት የአካባቢ መጠሪያ ስያሜዎች አካባቢው ጥንታዊ፣ታሪካዊና የሥልጣኔ ምንጭ እንደሆነ ማሳያ ናቸው፡፡
አራዳ በድምጻውያን ጭምር የተዘፈነለትና የተወደሰ ሲሆን፣በመኻል ከተማ የሚገኝ በመሆኑ ከተለያየ አቅጣጫ የሚመጣው ሁሉ ይገናኛል፡፡ሰዎች ቀጠሮ ለመያዝም የሚመርጡት አካባቢ ነው፡፡አራዳ ክፍለከተማ አስር ወረዳዎች ያሉት ሲሆን፣ጉለሌ፣የካና አዲስ ከተማ ክፍለከተማ በከፊል ያዋስኑታል፡፡
ስለአራዳ ክፍለከተማ እንዲህ ታሪክ ያወሳነው በምክንያት ነው፡፡ከጥንታዊነቱና ከታሪካዊነቱ አንፃር አካባቢውን ከብክለት ነፃ በማድረግና በማስዋብ እየተከናወኑ ሥላሉ ሥራዎችና ክፍተቶች ላይ ትኩረት አድርገናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአራዳ ክፍለ ከተማ ውስጥ ሰፋፊ ግንባታዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡በመሆኑም ክፍለ ከተማው ቀደም ሲል የነበሩት ገጽታዎች በመለወጥ ላይ ናቸው፡፡ ረጅም ዕድሜ ያስቆጠሩ መኖሪያቤቶችና የተለያዩ አገልግሎት መስጫዎች ዛሬ በአዲስ ግንባታ ተቀይረዋል፡፡
እንዲህ መልካም የሆኑ ነገሮችና ለውጦች በክፍለ ከተማው መታየት ቢጀምሩም ያልተቀረፉ ክፍተቶችም ይስተዋላሉ፡፡በተለይም ከአካባቢ ብክለት ጋር የተያያዙትን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ቀድሞ የተመሰረተ አካባቢ በመሆኑ ከመፀዳጃቤትና ከተለያዩ አገልግሎቶች የሚወገዱ ፍሳሽ ቆሻሻዎች ቀጥታ ከዋናው ፍሳሽ ማግለያ ጋር ባለመገናኘቱ ፍሳሹ የእግረኛ መንገድ ላይ የሚወጣበት አጋጣሚ ተደጋግሞ ይስተዋላል፡፡በተለይም በክረምት ወቅት ችግሩ የከፋ ነው፡፡የዝናብ አጋጣሚን በመጠቀም ከወራጅ ውሃ ጋር እንዲወርድ ከመፀዳጃቤት ፍሳሽ መልቀቅ የተለመደ ሲሆን፣እንዲህ ያለው ችግር ከሚታይባቸው የክፍለከተማው አካባቢ በብርሃንና ሰላም ጀርባ ያለው ይጠቀሳል፡፡
ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ ባለመኖሩም አራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ ኃይለኛ ዝናብ ከዘነበ አስፓልት ለመሻገር አስቸጋሪ ነው፡፡ሰዎች በሸክም አስፓልት ሲያሻግሩ ይስተዋላል፡፡እግረኛ ቀርቶ ተሽከርካሪዎችም እንደልባቸው እንዳይተላለፉ እንቅፋት ይሆንባቸዋል፡፡ የተደፈኑ ቱቦዎች በዝናብ ኃይል ሲፈነዱ በውስጥ የተጠራቀመ ደረቅ ቆሻሻ አስፓልት ላይ ወጥቶ ለመንገደኛ አስቸጋሪ የሚሆንበት አጋጣሚ የበዛ እንደሆነ መታዘብ ይቻላል፡፡
ክፍለከተማው በሚገኝበት ቅርብርቀት ላይ ከምግብ ቤቶች የሚወገዱ ፍሳሽ ቆሻሻ በመተላለፊያ ቱቦዎች ውስጥ ስለሚደፉ ለእይታም ለጤናም ጠንቅ ሆነዋል፡፡በራስመኮንን ድልድይና በከተማ ማዘጋጃ ቤቱ አካባቢዎችም ሰዎች እየተጸዳዱበት በተመሳሳይ ለአካባቢ ጠንቅ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ የድምጽ ብክለትም ሌላው የአካባቢው ችግር ሆኖ ይገለጻል፡፡ በክፍለከተማው በተለያየ አቅጣጫ ተንቀሳቃሽ መፀዳጃቤቶች ቢኖሩም ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ከመፀዳጃቤቶቹ አገልግሎት ጎልቶ የሚታየው ምግብና የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጡ ተቋማት መስተንግዶ ነው፡፡
በክፍለ ከተማው እንዲህ ያለውን ጉዳይ አንስተን ለመዳሰስ የወደድነው ከአንድ ወር በኋላ የምንጀምረው የክረምት ወቅት በመድረሱ እና ዝናቡም ከወዲሁ በመጀመሩ ጉዳዩ ትኩረት ማግኘት ስላለበት ብቻ ሳይሆን እነዚህ ጉዳዮች ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ ጭምር ለማሳሰብ ነው፡፡አራዳ ክፍለከተማ እነዚህን ጉዳዮች እንዴት አያቸው? ምንስ እየሰራ ነው? ቀጣይ አቅጣጫውስ?እነዚህን ጥያቄዎች በመያዝ የሚመለከታቸውን የአራዳ ክፍለከተማ ኃላፊዎች አነጋግረናል፡፡
በቅድሚያም በአራዳ ክፍለከተማ አካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሥርአቱ ኃይለገብርኤል እንዳስረዱት፤በአጠቃላይ አዲስ አበባ ከተማን አረንጓዴ፣ጽዱ፣ውብና ለነዋሪዎችዋ ምቹ ለማድረግ የከተማ አስተዳደሩ እየሰራ ይገኛል፡፡ አራዳ ክፍለ ከተማም በዚህ ረገድ በአካባቢው የሚያከናውነው ሥራ የዚሁ አካል ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ጽህፈት ቤታቸው ዋና ተልዕኮና ተግባር መከታተልና መቆጣጠር ቢሆንም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነትና ተግባራቸውን እንዲወጡ አስፈላጊውን ትብብር ያደርጋል፡፡
በክፍለከተማው በተፋሰስና አረንጓዴ ልማት ጽህፈትቤት አማካኝነት በመከናወን ላይ ያለው ተግባር አንዱ ሲሆን፣በልማቱ ሥራ ላይ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው እንዲሳተፉ በማድረግ በአንድ በኩል ልማቱ በሌላ በኩል ደግሞ የሥራ ዕድል በመፍጠር ተመጋጋቢ ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በክፍለከተማው ባሻወልዴ ተብሎ በሚጠራው የጋራ መኖሪያ ቤቶች በሚገኙበት አካባቢ ለፓርክ የሚሆን ቦታ ተፈቅዶ ተፋሰስና አረንጓዴ ልማት ለማከናወን ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል፡፡
ፓርኩ መያዝ ያለበትን ልማት አካቶ ከተጠናቀቀ በኋላ ለአካባቢው ነዋሪዎችና ለሌሎችም እንግዶች አገልግሎት እንዲሰጥ ታሳቢ ተደርጎ ነው የሚከናወነው፡፡ፓርኩ ሊሰራበት በታቀደው አቅራቢያ ከሚገኘው አንድነት ፓርክ ለየት የሚያደርገው ከክፍያ ነፃ የሆነ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑ ነው፡፡በሌላ በኩል ግን በዓለምአቀፍ መስፈርት መሠረት ለአንድ ሰው አምስት ካሬ ሜትር ነው የሚገመተው፡፡ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ መስፈርቱን ማሟላት ባይቻል እንኳን ከአንድ እስከ ሁለት ደረጃ ለማሟላት ነው ክፍለ ከተማው ጥረት እያደረገ የሚገኘው፡፡
ክረምትን ተከትሎ ከመፀዳጃ ቤቶች ከሚወገዱ ቆሻሻ ፍሳሾች ጋር በተያያዘ ለተነሳው ችግርም አቶ ሥርአቱ እንዳስረዱት የአካባቢ ብክለትን የሚያስከትለው ከመፀዳጃ ቤት ወይንም ከሌላ የሚወገድ ቆሻሻ ብቻ ሳይሆን፣ከፋብሪካና ከተለያዩ ድርጅቶች በሚወገዱ የሚከሰት የአየር የአፈር፣የድምጽ፣የእይታ ሌሎች ብክለት የሚያስከትሉ ስለሚኖሩ በመረጃ መደገፍ ይኖርበታል፡፡የተደራጀ መረጃ ሲኖር ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ቀላል ይሆናል፡፡
ስለጉዳዩ በዋናነት የአዲስ አበባ ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት የሚመለከተው ቢሆንም ክፍለከተማው የተበታተነ አሰራርን ለማስቀረት፣በዘመናዊ መልክ የተደራጀ መረጃ ለመያዝና አሰራሩንም ተደራሽ ለማድረግ በመረጃ አያያዝ ሥርአት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህ ረገድም በክፍለ ከተማው እያንዳንዳቸው ዘጠኝ አባላት ያላቸው አራት የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች መረጃ ሰብስበውና ተንትነው አቅርበዋል፡፡
መረጃዎችን የሰበሰቡት በአገልግሎት ሰጪና ማምረቻ ተቋማት ተዘዋውረው ሲሆን፣ኢንተርፕራይዞቹ ተንትነው ያቀረቧቸው መረጃዎች አምስት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው፡፡ለአብነትም ከማምረቻ ተቋማት መካከል የፕላስቲክና አረቄ ፋብሪካዎች ይጠቀሳሉ፡፡ፋብሪካዎቹ ተረፈምርታቸውን የሚያስወግዱት በወንዞች ውስጥ ነው፡፡
ፍሳሽ ቆሻሻ መወገዱን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ (ፕላንት) መትከላቸውን፣የሚወገደው ቆሻሻ በአካባቢው ላይ ስላደረሰው ተጽዕኖና በማህበረሰቡ ላይ ያስከተለው ጉዳት ጭምር ነው በመረጃ ማሰባሰቡ የተከናወነው፡፡ ማንኛውም ማምረቻ ተቋም የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ ማካሄድ ይጠበቅበታል፡፡ ይህን ያላደረገ ተቋም በህግ ይጠየቃል፡፡ ክፍለከተማው በጀማሪ ባለሙያዎች ተሰብስቦና ተተንትኖ በቀረበለት መረጃ መሥረት ክትትልና ቁጥጥሩን በማጠናከር እርምጃ እስከመውሰድ የደረሰ ሥራ ሰርቷል፡፡
እርምጃ ከተወሰደባቸው ተቋማትም የድምጽ ብክለትን በማስከተል ጥፋተኛ የሆኑ ይገኙበታል፡፡ህጉ የሚፈቅደው ቀን ላይ የድምጽ ልቀቱ ከ60 ዴሲቢል ወይም መጠን፣በላይ እስከምሽት ሶስት ደግሞ ከ55 ዴሲቢል፣ከምሽት ሶስት ሰዓት በኋላ ከ45 ዴሲቢል በላይ መልቀቅ አይፈቀድም፡፡ከተፈቀደው በላይ የድምጽ ብክለት ባስከተሉት ላይ ክፍለ ከተማው ቅድሚያ የማስተማርና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በማከናወን እንዲሁም ድምጽን ሊቀንሱ የሚችሉ መሳሪያዎችን እንዲጠቀሙ የባለሙያ እገዛ በማድረግ፣በክትትልና ቁጥጥርም የተሰራው የማስተካከያ እርምጃ መሟላቱን በማረጋገጥ ኃላፊነቱን የተወጣ ሲሆን፣በመቀጠል ከማስጠንቀቂያ እስከ መዝጋት ደረጃ የደረሰ እርምጃ ወስዷል፡፡
በአንድ የግል ትምህርት ቤት ውስጥ ለቤተሙከራ አገልግሎት ተብሎ የተከማቸ ጊዜ ያለፈበት ለአካባቢ ብክለት ሥጋት የሆነ ኬሚካል በአስቸኳይ እንዲወገድ፣የአወጋገድ ሂደቱ እስኪከናወንም ተከልሎ እንዲቀመጥ በክፍለ ከተማው በኩል ጥረት ተደርጓል፡፡የድምጽ ብክለትን በከፍተኛ ሁኔታ ከሚያስከትሉ ተቋማት መዝናኛዎችና የሃይማኖት ተቋማት ይጠቀሳሉ፡፡
ከመፀዳጃ ፍሳሽ ጋርም በተያያዘ የአዲስ አበባ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ባሻወልዴ ውስጥ ከተገነባው የጋራ መኖሪያ ቤት የሚወገደውን ፍሳሽ ቆሻሻ ቀጥታ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከሚገኘው ማግለያ ጋር እንዲገናኝ በማድረግ የነበረውን ችግር በማቃለል ያከናወነው ሥራ ሞዴል ሥራ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ ፒያሳ አካባቢ ወረዳ 10 ላይም በተመሳሳይ እያከናወነ ሲሆን፣በሌሎችም እንዲሁ በመሥራት ችግሩን ለመፍታት ጥረቱ ቀጥሏል፡፡ደንብ ጽህፈት ቤትም ችግር የሚያስከትሉትን ተከታተሎ ለህግ በማቅረብ ይሰራል፡፡በተጨማሪም ከምግብ ጤና ቁጥጥር ተቋም ጋርና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር በመናበብ፣ጎን ለጎን ክፍለ ከተማው ትምህርታዊ ግንዛቤዎችን በመሥራት ችግሮችን ለመቅረፍ ይንቀሳቀሳል፡፡
ራስ መኮንን፣ራስ እምሩ፣እስላም መቃብር ተብለው በሚጠሩት አካባቢዎች የሚወርዱት ወንዞች የአራዳ ክፍለከተማ ሀብቶች ናቸው፡፡ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻዎች በአግባቡ ካልተወገዱ ለነዚህ ወንዞች ስጋት መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡ለአብነትም እራስእምሩ አካባቢ የሚገኝ አንድ የማምረቻ ድርጅት የቆሻሻ ፍሳሹን ወደ ወንዙ መልቀቁ በመረጃ በመረጋገጡ ክፍለከተማው እርምጃ በመውሰድ እንዲስተካከል አድርጓል፡፡
ክፍለከተማው በሚያከናውነው ሥራ የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶችና በሰራቸው ሥራዎችም ጠንካራ ናቸው ያሏቸውን አቶሥርአቱ እንዲህ አስረድተዋል፡፡ በተለይ በድምጽ ብክለት ላይ የሚፈለገውን ያህል ለውጥ ለማምጣት አዳጋች የሆነው ከሥራ ሰዓት ውጭ ሌሊት ጭምር በመሆኑ እረፍት ላይ ያለውን ነዋሪ መታደግ አልተቻለም፡፡ክፍለ ከተማው በተቻለ መጠን ሌሊትም ጭምር የሰው ኃይሉን ከፀጥታ ኃይል ጋር በማሰማራት ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል፡፡
ተቆጣጣሪ አካል ሲኖር ድምጽ መቀነስ፣ዞር ሲል የመጨመር ሁኔታ በመኖሩ የድምጽ መጠን ደረጃን አስጠብቆ ለማስቀጠል ፈታኝ ነው፡፡ የሰው ኃይል በሌለበት ሊሰራ የሚችል ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ ለማዋል አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ አልተሞከረም፡፡አሁን ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ዴሲቢል የሚባል የድምጽ መለኪያ ነው፡፡አረንጓዴ ልማትን የራሴ ነው ብሎ በመንከባከብና በመጠበቅ በኩል ነዋሪው ላይ የሚታየው ክፍተትም ሌላው ተግዳሮት ሆኖበታል፡፡
የክፍለ ከተማው ጥንካሬ በመረጃ አሰባሰብ ላይ ያለው እንቅስቃሴ ይጠቀሳል፡፡በክፍለ ከተማው ያሉ መኖሪያ ቤቶች፣ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት የተደራጀ መረጃ በመኖሩ የአካባቢ ብክለት መንስኤዎችን በቀላሉ ለመከታተል ያስችላሉ፡፡አቶ ሥርአቱ የበጀት ዓመቱ ከመጠናቀቁ በፊት ክፍለ ከተማው ከዕቅድ በላይ ማከናወኑን ይገልጻሉ፡፡
እርሳቸው እንዳሉት በዓመት ውስጥ ለ220 ተቋማት ድጋፍና ክትትል ለማድረግ የተያዘው ዕቅድ የበጀት ዓመቱ ከመጠናቀቁ በፊት የተሻለ ሥራ ተከናውኗል፡፡የተከናወነው ሥራም ተቋማቱ ብክለት የሚያስከትሉ ነገሮች ላይ ትኩረት ሰጥተው መሥራታቸውን ማረጋገጥ፣የግንዛቤ ትምህርት መስጠት በሚሉት ይገለጻል፡፡ከክፍለ ከተማና ከባለድርሻ አካላት ጋር መድረክ በመፍጠር ሥራውን የጋራ በማድረግ፣በእውቀት የተመራ ሥራ በማከናወንና ከሁለት ዓመታት ወዲህ የተሻለ ውጤት በማስመዝገብም በግምገማ ለይቷል፡፡
ክፍለ ከተማው በቤተሙከራ የተደራጀ ቢሆን የተበከለ ውሃ፣ወይንም ሌሎች ብከለት ይሆናሉ ተብለው የተጠረጠሩ ነገሮችን ለመለየት ያስችለው እንደነበር የጠቀሱት አቶ እርስቱ ይህን እንደክፍተት በመጥቀስ ወደፊት የሚሟላበት ሁኔታ ቢመቻች የበለጠ መሥራትና የዘመነ ክፍለከተማ መፍጠር እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡አሁን ባለው ክፍለከተማው የብክለት ጥርጣሬ ሲያጋጥመው በከተማዋ በተቋቋመው የአካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት በመላክ እንደሚያረጋግጥ ገልጸዋል፡፡
የአራዳ ክፍለ ከተማ ምክትል ሥራ አስኪያጅና ደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ጽህፈት ቤትን የሚመሩት ወይዘሪት ቅድስት ተስፋዬም በተጨማሪ ሀሳብ አካፍለውናል፡፡እርሳቸው እንዳሉት በበጋው ወቅት 241ሺ842 የክፍለ ከተማውን ነዋሪ በማሳተፍ ውብና ጽዱ ለማድረግ በተለይም ደረቅ ቆሻሻን በማንሳት በተሰራው ሥራ ክፍለ ከተማውም ሚናውን ተወጥቷል፡፡ በበጋው መርሐግብር ያለውን ተሳትፎ በመገምገም ጥሩ የሰሩ እንዲበረታቱ እውቅና ይሰጣል፡፡ዕውቅና ማበላለጫ ሳይሆን ማነቃቂያ ተደርጎ መወሰድ አለበት፡፡ በተለይም ከተሰሩት ሥራዎች ቆሻሻ ሀብት መሆኑ ግንዛቤ ተይዞ በአግባቡ ተለይቶ እንዲወገድና ቆሻሻን የሚጠየፍ ማህበረሰብ ለመፍጠርና ዜጋ ተኮር ተግባር የማድረግ የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡
ክረምትን ተከትሎ የሚወገዱ ቆሻሻዎች የተለመዱ መሆን የለባቸውም ያሉት ምክትል ሥራ አስኪያጇ፤ህዝብንና ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ በክረምቱ መርሐግብር ይሰራል ብለዋል፡፡ማህበረሰቡን የማንቃት ሥራ በማጠናከር ከተሰራ ክፍለ ከተማውን ሞዴል የማድረጉ ተግባር ከባድ ይሆናል ብለው እንደማያምኑም ተናግረዋል፡፡ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር መስዋዕትነት መክፈል ግድ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡
ክፍለከተማው ያላስተዋላቸውን ደግሞ ማህበረሰቡ ችግሩ መልሶ እራሱን የሚጎዳው መሆኑን ተገንዝቦ በእኔነት ስሜት ማህበረሰቡ ከመኖሪያ ቤቱ እስከ 20 ሜትር፣ነጋዴው ደግሞ አምስት ሜትር ድረስ አካባቢውን በማጽዳት ሥራውን የጋራ እንዲያደርገው፣አንዱ የሰራውን ሌላው የሚያበላሽ ከሆነም አግባብ እንዳልሆነ ሁሉም ሊረዳው እንደሚገባ ጥሪም፣ማሳሰቢያም፣ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡
በአራዳ ክፍለከተማ ደረቅ ቆሻሻ የሚመነጩት በመኖሪያ ቤት በአባወራ ደረጃ 31 ሺ 808፣ሲሆኑ የተቀሩት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት መሆናቸውን ከክፍለ ከተማው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2013